ግንበኛው ድንጋዩን ይጠርብና በድርድሩ
ላይ ሰክቶ አንዴ ፈገግ፣ አንዴ ተከዝ፣ አንዴ ቆም አንዴም ጎንበስ ይላል፡፡ ላት አይቶ በግ እንደሚገዛ ሰው በግራ በቀኝ ያገላብጠዋል፡፡
እንደ ገዳም ጸሎት ሲመሰጥ፣ እንደ ጉብታ ዛፍ ሲናወጥ ይታያል፡፡ እንደ ኮከብ ቆጣሪ ሲያፈጥ፣ እንደ ጥሩ ወጥ ቀማሽ ምራቁን ሲወጥ
ይታያል፡፡ ድንጋዩን በግራ ቀኝ ሲፈልጠው ልጇን እንደምታጥብ እናት ሲሳሳ፣ ቅባት እንደምትቀባ ፀጉር ሠሪ ሲዳስስ ይታያል፡፡
ይህንን ሁሉ ያየ መንገደኛ ‹ጌታው፣
ሲያዩህ እንደ ግንበኛ ድንጋይ ትጠርባለህ፣ ግንብ ትሰድራለህ፤ ሁኔታህን ላስተዋለው ግን እንደ ሙዚቀኛም፣ እንደ ቲያትረኛም፣ እንደ
ቀማሚም እንደ ዘማሚም ትመስላለህ፡፡ ለመሆኑ ምን እያደረግኩ ነው ትላለህ?› ሲል ጠየቀው፡፡ ግንበኛው መዶሻውን ድንጋዩ ላይ አንተራሰና
እኔ! እኔማ እየፈለጥኩም ግንብ
እየሠራሁም አይደለም፡፡
እኔ! እኔማ እንደ ያሬድ አዜማለሁ
እንደ ተዋነይ እቀኛለሁ
እንደ ላሊበላ ድንጋዩን አናግረዋለሁ
እንደ ጊዮርጊስ አመሠጥራለሁ
እንደ አፈወርቅ እስላለሁ
እንደ ሐዲስ እደርሳለሁ
እንደ ጸጋዬ እገጥማለሁ
እንደ ወጋየሁ እተርካለሁ
እንደ ሺመልስ እተውናለሁ
እንደ ኤልያስ አቀናብራለሁ
እስኪ ተመልከታቸውማ፤ የበቃ ባለቅኔ የሰባ ቃል እንዲሻ፣ እነዚህ ጥርብ
ድንጋዮች ለእኔ ቃላት ናቸው፡፡ እመርጣለሁ፣ እቀርጻለሁ፡፡ የሰላ ባለ ቅኔ ያማረ ቃል እንዲሻ፣ እኔም እኒህን የድንጋይ ቃላት አሣምራቸዋለሁ፡፡
እኔ ድንጋይ አልፈልጥም፡፡ ሕይወትም በድንጋይ አትኖርም፤ ሕይወትም በድንጋይ አትረካም፡፡ ድንጋይማ የጉልበት ሥራ ነው፡፡ እኔ ቃላትን
በፈለገው ቅርጽ ከመዝገቡ እንደሚያወጣ እንደ ርቱዕ ደራሲ ነኝ፡፡ አንዳንዱ ድንጋይ ፈሊጥ ነው፤ አንዳንዱ ድንጋይ ምሳሌ፤ አንዳንዱ
ድንጋይ ተረት ነው አንዳንዱ ድንጋይ ዘይቤ፡፡