Tuesday, May 9, 2017

ድስትና ሰሐን


 click here for pdf
እሳቱን ግር አድርገው አንድደው ይለበልቡታል፡፡ ዕዳው የጀመረው ‹ትንሽ እሳት ይስማው› ብለው የጣዱት ጊዜ ነው፡፡ እሳቱ ሞቅ ሲያደርገው ሽንኩርቱን አቀመሱት፡፡ ሽንኩርቱ ብቻውን አልመጣም፡፡ ወደል ማማሰያ ይዞ እንጂ፡፡ ባልተወለደ አንጀቱ ሆዱን ያተራምስለት ገባ፡፡ አንዴ እያማሰለ፤ አንዴም ሆዱን እየፋቀ የክብደት አንሽ እግር የሚያህለው ማማሰያ  ድስቱን ይፈቀፍቀዋል፡፡ ሽንኩርቱ አጋም ሲመስል ደግሞ ውኃውን ቸለስ አደረጉበት፡፡ እፎይ አለ ድስቱ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው እፎይታው የዘለቀው እስኪንፈቀፈቅ ድረስ ብቻ ነው፡፡
የድስቱ ዙሪያ መጀመሪያ ጠቆረ፣ ቀጥሎም ጥላሸት ተቀባ፡፡ በመጨረሻም ራሱ ከሰለ፡፡ ሁለቱ ጆሮዎቹ ከሥሩ የሚነደውን ገሞራ እያዩ ‹ማርያም ማርያም› ይላሉ፡፡ ሥጋው ከገባበት በኋላማ ከሥሩ ማገዶውን፣ ከሆዱ ማማሰሉን እያከታተሉ ስቃዩን አበዙት፡፡ ደግሞ የጉልቻው መከራ፡፡ ይቆረቁራል፡፡ ‹‹የእናት ሞትና የድንጋይ መቀመጫ እየቆዩ ይቆረቁራል›› እንዲሉ በአንድ በኩል የድንጋዩ ጉብጠት፣ በሌላ በኩል የድንጋዩ ትኩሳት፣ እንኳን ለመቀመጫነት ለሲኦልነት እንኳን ሲበዛበት ነው፡፡
ለአራት ሰዓታት ያህል በውስጥ በአፍኣ አሳሩን ሲበላ ቆይቶ እዚያው ምድጃው ላይ ተዉት፡፡ እርሱም ተንፈቅፍቆ - ተንፈቅፍቆ፣ በመጨረሻ በክዳኑ በኩል ትንፋሹ እያወጣ ያንኮራፋ ጀመር፡፡ እሳቱም እየደከመውና ዓይኑ እየተስለመለመ ሄዶ አሸለበ፡፡ አልፎ አልፎ ብቻ ቆይተን የዚህን ድስት መጨረሻ እናያለን ያሉ ጉማጆች የዐመድ ሻሽ ለብሰው፣ ዓይናቸውን ከፈት ከደን እያደረጉ ሙቀቱ ጨርሶ እንዳይጠፋ አድርገውታል፡፡ ጉልቻውም ዋናው እሳት የተወውን እኔ ‹ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ› አልሆንም ብሎ መቀዝቀዝ ጀምሯል፡፡ 

ድስቱ ግን ዕንቅልፍ ሊወስደው አልቻለም፡፡ ኳ - ኳኳ - ቂው - ቂው ቂው - ቻ - ቻቻ - የሚል ድምጽ ማዕድ ቤቱን ሞላው፡፡ እዚህና እዚያ የሚጣደፉ ሰዎች ይታያሉ፡፡ ይወጣሉ፤ ይገባሉ፡፡ ይከራከራሉ፤ ይነታረካሉ፡፡ ድስቱን ረበሸው፡፡ እንዲያም ሆኖ ድካሙ ስለበረታበት ክዳኑን አናቱ ላይ ጣል አድርጎ ሸለብ ማድረግ ሲጀምር - ኳ - የሚል የቅርብ ድምጽ ሰማ፡፡ ይበልጥ ያነቃው ደግሞ - ኳ - የሚለው ድምጽ እዚያው ድስቱ አካባቢ የተሰማ መሆኑ ነው፡፡
የድስቱ ክዳን ተነሣ፡፡ ‹እባብ ያየ በልጥ ይደነግጣል› እንዲሉ ለአራት ሰዓታት ያህል ያሰቃየው እሳት ደግሞ ሊመለስ ነው ብሎ ሰቀጠጠው፡፡ ግድንግዱ ማማሰያ መጥቶ ሊወቅጠኝ ነው ብሎ ሲጠብቅ አንዲት አንገቷ የሰለለ፣ አናቷ የሞለለ ጭልፋ ቀጫ ቀንቧ እያለች ስትመጣ ታየች፡፡ ‹ይቺ ደግሞ ምንድን ናት?› አለ ድስቱ፡፡ የሚገርመው ነገር ብቻዋን አልነበረችም፡፡ ሁለት ድንቡሽ ያሉ ወጣት ሴቶች አንዲት እንደነርሱ ድንቡሽ ያለች ሰሐን ይዘዋል፡፡ ዙሪያዋን በአበባ ምስል ተጊጣለች፡፡ ሁለመናዋ ነጭ ነው፡፡ አንድም የቆሸሸ ነገር አይታይባትም፡፡ እንዲያውም ከሁለቱ ወጣት ሴቶች ጀርባ ፎጣ ይዛ አንዲት ልጅ ትከተል ነበር፡፡  ያቺ ሰሐን አንዳች ነገር ጠብ ሲልባት ፈጠን ብላ ጠረግ ታደርግላታለች፡፡ 

ጭልፋዋ ወደ ወጡ ጎንበስ ስትል ድንገት አንዲት ፍንጣቂ ዘልላ ሰሐኗ ላይ ዐረፈች፡፡ ያቺ እንደ ደንገጡር ከኋላ የምትከተል ወጣት እንደ ጀት ፈጥና በያዘችው ፎጣ ጥርግ አደረገችላት፡፡ ድስቱ ተገረመ፡፡ አራት ሰዓት ሙሉ ሲንፈቀፈቅ፣ ከታች የሚመጣ እሳት፣ ከውስጥ የሚፈነጥቅ ወጥ እንዲያ ጥቁርና ቀይ ሲያደርገው ዘወር ብሎ ያየው የለም፡፡ ጠቁሮ - ጠልሽቶ -ከስሎ -  እንኳን ሌላ ራሱ ድስቱ ራሱን እስኪረሳው ድረስ - ካሉት በታች ከሞቱት በላይ ሆነ፡፡ ያን ጊዜ ቀርቶ ወጡ በስሎ ሲያልቅ እንኳን ልጥረግህ፣ ልወልውልህ ያለው የለም - አየ ድስት መሆን፡፡
‹ደግሞ አንቺ ማነሽ?› አላት ድስት በሁለት ቆነጃጅት እጆች የተያዘችውን ሰሐን፡፡
‹የወጥ ማቅረቢያ ሰሐን ነኝ› አለችው ፈገግ እያለች፡፡
‹ምን ልታደርጊ መጣሽ?› አለ ከዚህ በፊት እዚያ አካባቢ አይቷት አያውቅም፡፡
‹ለእንግዶቹ ወጥ ልወስድ ነው› አለች የወጡ ፍንጣቂ እንዳይነካት ፈንጠር እያለች፡፡
‹ማን የሠራውን ማን ያቀርበዋል?› አለ ድስት እንደመፎከር ብሎ፡፡
‹ድስቶች ለፍተው የሠሩትን ሰሐኖች ተዉበው ያቀርቡታል› አለችውና ፍልቅ ብላ ሳቀች፡፡
‹የት ነበርሽ አንቺ ለመሆኑ? እሳት ከሥር፣ ማማሰያ ከላይ ሲኦል እንደገባ ኃጥእ ሲያሰቃዩኝ? ለመሆኑ ሽኩርቱ ሲቁላላ፣ ቅመሙ ሲዋሐድ፣ ሥጋው ሲወጠወጥ፣ ጨው ጣል ሲደረግ፣ ማማሰያው ሆዴን ሲያተራምሰው - ለመሆኑ አንቺ የት ነበርሽ? የመሥዋዕቱ ጊዜ የት ነበርሽ፣ የመከራው ጊዜ የት ነበርሽ፣ የችግሩ ጊዜ የት ነበርሽ፣ ሽንኩርቱ፣ ቅመሙ፣ ቅቤው፣ ሥጋው መልክና ስማቸውን ቀይረው ‹ወጥ› እስኪባሉ ድረስ የት ነበርሽ? አሁን ወጥ ሆኑ ሲባል ነው የምትመጭው› አላት ድስቱ ከጉልቻው ላይ እየተወዛወዘ፡፡
‹ስማ ድስቱ› አለችው ሰሐኗ፡፡ ‹ዋናው መሥዋዕትነቱ አይደለም፡፡ አቀራረቡ ነው፡፡ ሰውኮ ድስቱን ሳይሆን ወጡን ነው የሚፈልገው፡፡ ወጡ ደግሞ በእኛ በኩል ነው የሚቀርበው፡፡ በድስት ይሠራ፣ በበርሜል ይሠራ፣ በገንዳ ይሠራ፣ በጉድጓድ ይሠራ ማን ያይልሃል፡፡ ተጋባዦቹምኮ አዳራሹን እንጂ ማዕድ ቤቱን አያዩትም፡፡ ለመሆኑ ምግብ ቤት ገብቶ ‹አስተናጋጇ በደንብ አላስተናገደችኝም› የሚል እንጂ ‹ወጥ ሠሪዋ በሚገባ ለብሳ፣ ጤናዋን ጠብቃ፣ ከአደጋ የሚከላከል ልብስ አጥልቃ፣ አካባቢዋን አጽድታ አልሠራችውም› ብሎ የሚያማርር ተስተናጋጅ ሰምተህ ታውቃለህ? ወዳጄ ዘመኑ ለድስቶች ሳይሆን ለሰሐኖች ነው ዋጋ የሚሰጠው›› አለችው፡፡
ድስቱ አልተዋጠለትም፡፡ በተለይ ደግሞ አራት ሰዓት ሙሉ ከሥር ከላይ የከፈለውን መሥዋዕትነት ሲያስበው - እንኳን ሊዋጥለት፣ ሊጎረስለት አልቻለም፡፡
የለፋነው እኛ፣ የነደድነው እኛ፣ የተማሰልነው እኛ፤ መከራውን የቀመስነው እኛ - ለመሆኑ ከየት የመጣ ወጥ ነው ብሎ ነው ተጋባዡ የሚያስበው? ለመሆኑ ያለ አኛ እናንተ መኖር ትችሉ ነበር? ያንቺ ውበት የኔ መቃጠል ውጤት አይደለም? አንቺ በሁለት እልፍኝ አስከልካዮችና በአንዲት ደንገጡር እንድትከበቢ ያደረግንሽ እኛ አይደለንም? እኔና የወጥ ማማሰያ የከፈልነው መሥዋዕትነት እንዴት ቢረሳ ነው አንቺና ጭልፋ በመጨረሻ መጥታችሁ የምትሽረቀሩት››
ሁለቱ ሴቶች ወጡን እያወጡ ወደ ሰሐኗ ሲጨምሩ - ‹ስማ› አለቺው ሰሐኗ ‹አንተ የተናገርከው እውነቱን ነው፡፡ እኔ የምነግርህ የሚያዋጣውን ነው፡፡በዚህ ዘመን በሚፈለገውና በሚያስፈልገው መካከል ልዩነት መፈጠሩን አልሰማህም መሰል፡፡ በዚህ ዘመን ማራቶኑን የምትፈልገው ለጤና ከሆነ ዐርባ ሁለቱን ኪሎ ሜትር ሩጥ፤ ማራቶኑን የምትፈልገው ለሽልማቱ ከሆነ ግን ዐርባውን ሌሎች ይሩጡልህ፣ አንተ ግን ሁለት ኪሎ ሜትር ሲቀር ገብተህ ቅደም፡፡ ያን ጊዜ ልፋቱን ሌላው ይለፋል -ሽልማቱን አንተ ትወስዳለህ፡፡ እስኪ ለሀገራቸው ዋጋ የከፈሉትን፣ የተሠዉትን፣ የሞቱትን፣ የደከሙትንና ሀገሪቱን ሀገር ያደረጉትን አስባቸው፡፡ ምን አገኙ? እነርሱ እንዳንተ ማዕድ ቤት ውስጥ ተረስተው  ቀርተዋል፡፡ ስለ እነርሱ የሚደሰኩረውና የሚተርከው ግን ዛሬ የት ነው ያለው? ዘመኑ የዐርበኞች ሳይሆን የድል አጥቢያ ዐርበኞች ነው፡፡››
ይህንን ስትነግረው ወጡ ተጠቃልሎ ወጥቶ ደንገጡሯ የተፈናጠቀውን እየጠረገች ነበር፡፡ በድስቱ ክዳን አናት ላይ ባለችው ቀዳዳ አበባ ተደረገባት፡፡ ሰሐንዋን የያዘችው ወጣት ለሌላዋ ወጣት ስትሰጣት እንደ አራስ ልጅ በባለ አበባ ጨርቅ አደግድጋ ተቀበለቻት፡፡ ጭልፋ የያዘችው ወጣት ከፊት እንደ እልፍኝ አስከልካይ እየመራች፣ ፎጣ የያዘችው ወጣት እንደ ደንገጡር እየተከተለች አጅባት ሄደች፡፡ ድስቱም ‹እዚህ ሀገር እንደ ጠረጲዛ አበባ ፊት  ሆኖ የሚታየውን እንጂ፣ እንደ ጄነሬተር ከኋላ ሆኖ የሚሠራውን የሚያየውና የሚያከብረው የለም ማለት ነው?›› አለ፡፡ ይህን ሲናገር ሁለት ወጠምሻ ጎረምሶች መጥተው ከጉልቻው አውጥተው ድስቱን ዐመድ ላይ ጣሉት፡፡
  

23 comments:

 1. min malet endalbgne alwkem becha hilena lalew betam kebad melket new

  ReplyDelete
 2. ሰሞኑን እየሆነ ያለውም ይኸው ነው ታሪክ የሠራው ሳይሆን ያወራው ገዝፎ እየታየ ጭራሽ ለሀገር የሞተውን ከአዝማሪ ጋር ማወዳደር ምን የሚሉት አስተሳሰብ ነው? አድናቂ ነን ባዮች አምላኪ እየሆኑ እንዳሉ ቆም ብለው ራሳቸውን ቢመለከቱ ባይ ነኝ፡፡ ማንም ሰው በተሰማራበት ሥራ ጥሩ ከሠራ ይሞገሳል፣ ይወደሳል ይገባዋልም ነገር ግን አዝማሪ ከአዝማሪ እንጂ ከጀግና ጋር አይወዳደርም፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. Bexam yemitigerm sewu neh tedin lemenqef yihen yahile mehedih ebakih wed hellinah temelese endante meleyayetin meseleh yesebekewu andineten enji endante ayinet sewoch gin andinete yemilewun mesmate cinqilatachihun silmiamachihu ayitayibachihum

   Delete
 3. ሰሚ የለም እንጂ ተናጋሪ ነበር
  ታዲያ ምን ያደርጋል ያልታደለች አገር፡፡
  የሚሠራው ሌላ የሚሸለም ሌላ፣የሚጥር የሚግር ሌላ የሚበላ ሌላ፣አገር ያቀና ሌላ ኒሻን ያለው ሌላ፡፡
  ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ
  የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ
  አይደል ያለው ያ አርበኛ፡፡ለማንኛው ፈጣሪ የተሻ ለውን ነገር ያምጣልን፡፡ፈጣሪ ያንተንም እድሜ እንደማቱሳላ ያርዝምልህ ፡፡ሰናይ ዘመን ይሁንልህ፡፡

  ReplyDelete
 4. ሰሚ የለም እንጂ ተናጋሪ ነበር
  ታዲያ ምን ያደርጋል ያልታደለች አገር፡፡
  የሚሠራው ሌላ የሚሸለም ሌላ፣የሚጥር የሚግር ሌላ የሚበላ ሌላ፣አገር ያቀና ሌላ ኒሻን ያለው ሌላ፡፡
  ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ
  የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ
  አይደል ያለው ያ አርበኛ፡፡ለማንኛው ፈጣሪ የተሻ ለውን ነገር ያምጣልን፡፡ፈጣሪ ያንተንም እድሜ እንደማቱሳላ ያርዝምልህ ፡፡ሰናይ ዘመን ይሁንልህ፡፡

  ReplyDelete
 5. ሰሚ የለም እንጂ ተናጋሪ ነበር
  ታዲያ ምን ያደርጋል ያልታደለች አገር፡፡
  የሚሠራው ሌላ የሚሸለም ሌላ፣የሚጥር የሚግር ሌላ የሚበላ ሌላ፣አገር ያቀና ሌላ ኒሻን ያለው ሌላ፡፡
  ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ
  የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ
  አይደል ያለው ያ አርበኛ፡፡ለማንኛው ፈጣሪ የተሻ ለውን ነገር ያምጣልን፡፡ፈጣሪ ያንተንም እድሜ እንደማቱሳላ ያርዝምልህ ፡፡ሰናይ ዘመን ይሁንልህ፡፡

  ReplyDelete
 6. ሰሚ የለም እንጂ ተናጋሪ ነበር
  ታዲያ ምን ያደርጋል ያልታደለች አገር፡፡
  የሚሠራው ሌላ የሚሸለም ሌላ፣የሚጥር የሚግር ሌላ የሚበላ ሌላ፣አገር ያቀና ሌላ ኒሻን ያለው ሌላ፡፡
  ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ
  የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ
  አይደል ያለው ያ አርበኛ፡፡ለማንኛው ፈጣሪ የተሻ ለውን ነገር ያምጣልን፡፡ፈጣሪ ያንተንም እድሜ እንደማቱሳላ ያርዝምልህ ፡፡ሰናይ ዘመን ይሁንልህ፡፡

  ReplyDelete
 7. ሰሚ የለም እንጂ ተናጋሪ ነበር
  ታዲያ ምን ያደርጋል
  ያልታደለች አገር፡፡
  የሚሠራው ሌላ የሚሸለም ሌላ፣የሚጥር የሚግር ሌላ የሚበላ ሌላ፣አገር ያቀና ሌላ ኒሻን ያለው ሌላ፡፡
  ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ
  የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ
  አይደል ያለው ያ አርበኛ፡፡ለማንኛው ፈጣሪ የተሻ ለውን ነገር ያምጣልን፡፡ፈጣሪ ያንተንም እድሜ እንደማቱሳላ ያርዝምልህ ፡፡ሰናይ ዘመን ይሁንልህ፡፡

  ReplyDelete
 8. እዚህ ሀገር እንደ... no, no, .. that is the world...

  ReplyDelete
 9. Love you DAni!Berberaw ayn aynun siyakatelewes ? I mean for real not cool.Good reading Dani. God be with you.

  ReplyDelete
 10. ዋናው መሥዋዕትነቱ አይደለም፡፡ አቀራረቡ ነው፡፡ ሰውኮ ድስቱን ሳይሆን ወጡን ነው የሚፈልገው፡፡

  ReplyDelete
 11. Minwagaw TemesgenMay 10, 2017 at 2:56 PM

  ዳኒ፣ ጽሑፍህ መቼስ ግሩም እኮ ነው! “አያልቅበት” የሚባል የሰው ስም ሰምተህ ታውቃለህ? አያልቅበት ማለት እንግዲህ አንተ ነህ ባይ ነኝ! ለነገሩ “ሙሐዝ” ማለትም ምሥጢሩ ያው መሰለኝ፡፡ በነገራችን ላይ ዳኒ፣ የድስቱንና የሰሐኑን ነገር በተለየ መንገድ ብናየውስ ምን ይመስልሃል?


  ድስት በእሳት ተለብልቦ የሠራውን ወጥ፣ ጭልፋ ጠልቆ ሰሐኖችም መውሰጃ ሆነው ለሰዎች ባያደርሱት ኖሮምኮ ችግር ነበር፡፡ መቼም ድስት ወጥ መሥሪያም፣ መጨለፊያም፣ ወጥ ማቅረቢያም ሊሆን አይችልም፡፡ እርሱ ሥራውን ሠራ፤ እነዚያም የድርሻቸውን አከናወኑ፡፡ ባለፈው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል መቀሌ ላይ ሲከበር ያሬድ ሹመቴና መሰሎቹ፣ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ፣ አንተና ሌሎችም ያደረጋችሁትኮ የሰሐኖችን ሥራ ነው፡፡ አባቶቻችን የሠሩትን ወጥ በጭልፋ ጠልቃችሁ በሳሐን አደረጋችሁትና ወደሰው አፍ አደረሳችሁት፡፡ በእውነት ደስ የሚል የሰሐንነት ሥራ ነው!


  ዐፄ ምኒልክ ድስት ሆነው የአድዋ ድል ወጥን ሠሩ፡፡ በጦርነቱ መሥዋዕት ሆነው የተሰውት አርበኞች ደግሞ የእንጨትነቱን ሥራ ሠሩ፤ እሳቱ መከራቸው ነው፡፡ ምክክራቸውና ውይይታቸው ደግሞ ማንኪያውን ሆኖ ወጡ ሳያር ጣፍጦ እንዲወጣ አደረገ፡፡ በዚያ ላይ ሀገር መውደድ የሚባል ጨውን ጣል ሲያደርጉበት ጊዜ ይኼው መላ አፍሪካን “ድገሙን! ድገሙን!” እንዲል አደረጉት፡፡ እንዲህ ሆኖ የተሠራው ወጥ ግን ለብዙ ዘመናት ሰሐንና አሳላፊ አልነበረውም፡፡ አብዛኞቹ ሰሐኖችና አሳላፊዎች የውጭ ሰዎች ስለነበሩ፣ ወጡ ቀምሰው ወደሚያጣጥሙት አልደረሰም ነበር፡፡ ያው እንደምታውቀው ወጡ በእኛ አባቶች ተሠርቶ በላተኛው ግን ሌላ ነበር፤ በአሳላፊዎች ችግር ምክንያት፡፡


  አሁን ግን ሰሐኖች እናንተ ደረሳችሁና ይኼው ወጡ እየተቀመሰ ነው፡፡ ለዚህም ፈጣሪን እናመሰግነዋለን፡፡ በነገራችን ላይ ወጥ ተሠርቶ ካልተበላ ምን ዋጋ አለው፡፡ ወጥ እንዲሠራ እንጨት ያስፈልጋል፤ ክብሪት ያስፈልጋል፡፡ እሳትና ፍምም ያስፈልጋሉ፡፡ ለማማሰያነት ማንኪያም ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ብቻቸውን ግን ያለድስት ምንም ሊሠሩ አይችሉም፡፡ ድስትም ቢሆን ያለሌሎች ዋጋ የለውም፡፡ ለጨለፍም ጭልፋ ያስፈልጋል፡፡ የወጥ ማቅረቢያ ሰሐንም እንዲሁ፡፡ እኔ ድስትና ሰሐን እኩል ያስፈልጋሉ ባይ ነኝ፤ አንዳንድ ጊዜ ድስት ሲጠፋኮ በሰሐንም ወጥ ይሠራል፡፡ ምን የጣፈጠ ወጥ ቢሠራ ሰሐን ከሌለስ አሳላፊዎች በየመሶቡ ድስቱን ይዘው መዞር እንዴት ይቻላቸዋል?


  አንተ እንደነገርኸን ሌሎቹ ሀገራት ያልተሠራ ወጥ ያቀርባሉ፡፡ “የምድር ወገብን ጎብኝቼ የምስክር ወረቀት ተሰጠኝ” ማለትህን አስታውሼ ነው፡፡ ግሪካውያን ደግሞ የመናፍስትን መኖሪያ ያስጎበኛሉ፡፡ አየህ! እነርሱ ድስትና ወጥ ሳይኖራቸው በጭልፋና በሰሐን ብቻ እንግዳ ተቀብለው ይሸኛሉ፡፡ እኛ ግን ድስቱም ወጡም እያለን በጭልፋና በሰሐን እጦት ምክንያት ይኼው አሁንም በረሀብ አለንጋ እንገረፋለን፡፡ ችግሩ ድስትና ወጥ ስለሌለን ሳይሆን ጭልፋና ሳህን መሆን ስላልቻልን ይመስለኛል፡፡ ዋናው ችግራችን ወጡን ከነድስቱ እንጂ በሰሐን ማቅረብ አንችልበትም፡፡


  እናም ዳኒ፣ አንተ እንዳልኸው ድስቱን የሚጠርጉት ሰዎች በዝተዋል፡፡ ድስቱን ከጉልቻው ላይ አንስተው አመድ ላይ የሚጥሉት ብዙ ናቸው፡፡ ትክክል ነህ! ለድስትም ሆነ ለጭልፋና ለሰሐን ያለን አያያዝ ትክክል አይደለም መስተካከል አለበት፡፡ ድስትነትን ብቻ አጉልተን ሰሐንነትን ካኮሰስን አሁንም አደጋ አለው፡፡ ደግ ደጉን ያስመልክተን፤ አሜን!


  ሰላም ሁን!

  ReplyDelete
  Replies
  1. አምስት ጣቶች አንድ ለይ ሲጣመሩ....

   Delete
 12. selam dani zare yayegebet angle teru behonim 'Minwagaw Temesgen'yayebet angle gin kenew ga temesasay naw .enam sehan ena chelefa kelele man yakabelen yetewodros yeminilik tarik jebed ena kurat kalabeleun desetochma eko yerasachewun sera sertewale yegn cheger yehonaw beante eyeta becherash desetochun reseten chelefa ena sehanochun mezekerachin manekolepapesachin naw enji lelaw ema deg neber aseb axumn yakom lalibelan yetereb yanene tewuled resten zare surie selekeded tsegure selefereze manenetun bebad bahele gare tedebaleko yalew ewenetun zekare manenetien gelach defare yehon sehan ena chelefa selatan naw desetu bechawun alamawun ayemetam woy babeselaw esat lay yedefale woyim yare ena yederekale ya degmo lela tefat yehonale gin yamare sehan ena chelefa selale alamawun yemetale even sehanu bayetreg ena netsuh bayehon yelefatu wutiet yekenesale dani.

  ReplyDelete
 13. እዚህ ሀገር እንደ ጠረጲዛ አበባ ፊት  ሆኖ የሚታየውን እንጂ፣ እንደ ጄነሬተር ከኋላ ሆኖ የሚሠራውን የሚያየውና የሚያከብረው የለም ማለት ነው?›› አለ፡፡

  ReplyDelete
 14. ድስትም አፈጣጠሩ እንዲህ ነውና ይሁን። ሳህንም እንዲሁ። ግን ክፋቱ ሁሉም አንዱ ያንዱን ድርሻ እየረሳ ብቻውን ክብሩን ሽልማቱን ለመውሰድ አንዱ ለሌላው ክፋ መሆኑ ነው። ሃገር: ማህበረሰብ እንዲህ ነው የሚመሰረተው። ግማሹ ድስት ግማሹ ሳህን ሌላው ማንኪያ ወይም ጭልፋ ሆኖ ነው። ያገሬ ገበሬ ድስት ነው። ሁልጊዜ በመከራ ያለ። ክብሩን ያጣ ዋጋው ያልተከፈለው ባተሌ አመድ ላይ የተጣለ። ያገሬ መምህራን ድስቶች ናቸው። ምግብ አብሰለው ግን የተረሱ: በጠብታ ውሃ እርኩ የተባሉ። ያስተማሩትን ተማሪ እርጣባን እንዲያወሩ የተፈረደባቸው። ስለመኪና አሰራር የሚያስተምሩ ግን በህይወት ዘመናቸው የመኪና መሪ መዘወር በፍጹም በፍጹም የማያስቡ። 7 ዓመት የተማረ ሃኪም 12ኛ ክፍል የወደቀ ጓደኛው የደላላ ሃብታም ሆኖ ሲቆየው ከተመረቀ በኋላ የቤት ኪራይ መክፈል አቅቶት ከደላላ ጓደኛው ብድር የሚቀበል በኛ ሃገር ድስት የሆነ።
  ስንቱ መከረኛ ድስት ስልጣን በሳህኖችና ጭልፋዎች በመወረሩ ወይም የድስቶችን ዋጋ ብቻቸውን በግፍ ነጥቀው ሃገር ተስፋ ቢስ እንድትሆን የሆነ። ጭልፋዎች ብቻቸውን ስልጣን ከነጠቁ ሃገር ይበላሻል። ራስ ወዳድነት: ዘረኝነት: ሙስና: ነውራቸውን ክብራቸው ያደርጋሉ። ድስቶችም ብቻቸውን አያምርባቸውም።
  ዲያቆን አንድ ቀን ከሌሎች ስህተት መማር ባንችልም: ጅሎች ስለሆንን በሚደርስብን እና አየኖርነው ባለነው የችጋር ዘመን ቆይተንም ቢሆን መማራችን አይቀርም። በርታ። ያለምክንያት አንተ አልተነሳህም: ድስት ሆነህ ጠቁረህም ይሁን አስተምር። ብዙ የተራበ አለና ምግብ መስራትህን ቀጥል።
  አምላክ እድሜህን ያለመከራ ያብዛ።
  ይሄ የኔ ሃሳብ ነውና ቅር ያለው ካለ ይቅርታ።

  ReplyDelete
 15. የዚህ ዘመን ወጣት ምን ይገባዋል ምስጢር ….በግልጽ ድስቱ እገሌ ነው ሰሀኑ እገሌ ነው ከ ሳህኑ ይልቅ ድስቱ ክብር ይገባዋል ብለህ ብታወራው እጅግ መልካም ይሆን ነበር፡፡

  ReplyDelete
 16. ስንቶች በወደቁበት ሌሎች ይነሳሉ ስንቶች በተረቡበት ሌሎች ይጠግባሉ ስንቶች በተሰደዱበት ሌሎች ይኖራሉ
  ስንቶች በሞቱበት ሌሎች ይኖራሉ ለዚህም ይመስላል
  ሃገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ
  የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ ባለ
  የተባለው ቀና እይታ ነው

  ReplyDelete
 17. አንተ የተናገርከው እውነቱን ነው፡፡ እኔ የምነግርህ የሚያዋጣውን ነው.......uffffff this is the whole truth about our times, country and us. ewunetu Yamal. Thank u Dani

  ReplyDelete
 18. እንድ የሌላ ዜጋ የትምህርት ቤት ጉዋደኛየ፣ እኔ ሁለት ወር የደክምኩበትን የግሩፕ ፕሮጀከት በመጨረሻ እኔ ላቅርበው ብሎ ሙዝዝ አለ። ምክንያቱን ብጠይቀው፣ አይ እናንተ ኢትዮጵያውያን ተጨንቆ መስራት እንጅ ነገር አፍታቶ መናገር አይሆንላችሁም እና ፕሮጀክቱን ትገድለዋለህ አለኝ፤ እኔም ተስማምቸ ፣ አሳምሮ አቀረበው። እና ሁለታችንም አገኘን።
  ድስቱም የሚችለውን ሰራ ፣ (በዚያ ድስት ለማዕድ ቢቀርብ ??) ሰሃኑም የሚችለውን ሰራ እናም በሁለቱ ትብብር ወጡ ጣፈጠ አላማው ግቡን መታ! ሁሉም እንደ አቅሙ እና ችሎታው ቢተባባር ፣ ተቃርኖው ቢኖርም ፣ ችግር ግን አይመሰለኝም።

  ReplyDelete
 19. kale hiwet yasemalgn muhaze tibebat

  ReplyDelete
 20. ድስቱም ‹እዚህ ሀገር እንደ ጠረጲዛ አበባ ፊት ሆኖ የሚታየውን እንጂ፣ እንደ ጄነሬተር ከኋላ ሆኖ የሚሠራውን የሚያየውና የሚያከብረው የለም ማለት ነው?›› አለ፡፡

  ReplyDelete