Tuesday, May 2, 2017

አራቱ መስተፃርራን


click here for pdf 
ኢትዮጵያ ውስጥ ለአንድ ሕዝብ የሚሠሩ፣ በአንድ መንግሥት የሚተዳደሩ የማይመስሉ ለመሥራት ተመሥርተው በማፍረስ የተጠመዱ አራት መስተፃርራን አሉ፡፡ እርስ በርሳቸው የሚቀዋወሙ፡፡ አንዱ የሠራውን ሌላው ካላፈረሰ የሠራ የማይመስለው፡፡ ዋና ተልዕኳቸው የሌላውን ማፍረስ እንጂ የራሳቸውን መሥራት ያልሆነ፡፡ መዝገበ ቃላታቸውን - ናደው፣ ደምስሰው፣ አፍርሰው፣ ቆፍረው፣ ጉረደው፣ ቁረጠው፣ ገልብጠው - በሚሉ ቃላት የተሞሉ፡፡
አንድ ነገር ሲያምር ያየሁት እንደሆን
ያንን ካላጠፋሁ ከቶ ምንም ቢሆን
ዕረፍት አላገኝም እንቅልፍ አይወስደኝም
ቅን ነገር አይቼ እኔ አያስችለኝም፡፡ የሚለው መዝሙር ብሔራዊ መዝሙራቸው የሆነ - አራቱ መስተፃርራን፡፡
እነዚህ አራቱስ እነማን ናቸው ቢሉ - ውኃና ፍሳሽ፣ ቴሌ፣ መንገዶች ባለሥልጣንና መብራት ኃይል ይባላሉ፡፡ አንዱ የሌላውን መኖር ቢያውቅም፣ አንዱ ግን ከሌላው ጋር ለመተባበር አይፈልግም፡፡ ወዳጅ እንዳንላቸው የሀገር ሀብት ሲያፈርሱ ምንም አይመስላቸው፤ ጠላት እንዳንላቸው የምንሠራ ለሀገር ነው ይላሉ፡፡   

መንገዶች ባለ ሥልጣን ይመጣና አካባቢውን ቆፍሮ፣ ንዶ፣ ቤት አፍርሶ፣ ዛፍ ገንድሶ፣ አጥር ጠርምሶ፣ ምሶሶ ነቅሎ፣ መንገድ እሠራለሁ ይላል፡፡ የቴሌን ገመድ ሲበጥሰው፣ የውኃውን መሥመር ሲተረትረው፣ የፍሳሹን ቱቦ ሲዘጋው፣ የመብራቱን እንጨት ሲያግድመው ትንኝ የነካ እንኳን አይመስለውም፡፡ አካባቢው ይታመሳል፣ ይተራመሳል፡፡ ለጥቂት ጊዜ ችግሩን ቻሉት እንባልና የአፈር እንጀራ እንበላለን፣ የአቧራ ውኃ እንጠጣለን፡፡ ልክ ጠጠሩ ተደላድሎ አስፓልቱ ሲነጠፍ፣ አካፋና አዷማ የያዙ ጎልማሶች አካባቢውን ይወሩታል፡፡ ያሠምራሉ፣ ይለካሉ፣ ይቆርጣሉ፡፡ ምንድን ነው? ስንላቸው ‹የቴሌ መሥመር ልንዘረጋ ነው› ይሉናል፡፡ ‹እስካሁን የት ነበራችሁ› ያልናቸው እንደሆን መልሱን የሚሰጡን ጉድጓዱን እየቆፈሩ ነው፡፡ ‹የተሠራ ሳናበላሽ፣ የተገነባ ሳንንድ አታውለን› ብለው ጸልየው የመጡ ናቸውና ያሉትን ሳያደርጉ አይመለሱም፡፡ እኛም
የተመኘሁትን አንድ ቀን ሳላይ
ያልፍልኛል ስለው ሊያልፍብኝ ነወይ 
ያለችውን ሴትዮ እንጉርጉሮ እንዳንጎራጎርን እንከርማለን፡፡ የደኻ ምርኩዙ ተስፋ ነውና ቴሌ ጨርሶ ሲሄድ ሠፈራችን ያልፍለታል ብለን ደግሞ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የተሠራውን አስፓልት ንደው፣ የተደለደለውን ጎድጉደው፣ በሬንጁ ምትክ አፈር፣ በአስፓልቱ ምትክ ጠጠር ሞልተው፣ የአህያ ሻኛ ቁስል የመሰለ የአስፓልት ላይ ቁስል ትተው ቴሌዎች ይሄዳሉ፡፡ እኛም
ለማይሰማው ስልክ ለሚቆራረጠው
እንደ ገላውዴዎስ መንገዴን ቆረጠው
እያልን እያዜምን እንቀራለን፡፡ እንደ ገላውዴዎስ የተባሉት ዐፄ ገላውዴዎስ ናቸው፡፡ መጋቢት 27 ቀን 1551 ዓ.ም. ሐረር አካባቢ ከሐረሩ አሚር ከኑር መሐመድ ጦር ጋር በተደረገ ጦርነት ዐፄ ገላውዴዎስ ተገደሉ፡፡ ራሳቸውንም ቆርጠው ወደ ሐረር ከተማ ወሰዷቸው፡፡ 
ቴሌ በቆፈረው ጉድጓድ እየተንገጫገጭን፣ ጉድጓዱ በያዘው ውኃም እየተንቦራጨቅን ኑሯችንን ስንገፋ፡፡ ሦስተኛው ፀር ይመጣል፡፡ ‹መንገዱ የፍሳሽ ማስወገጃ የለውም፤ አሮጌውም የውኃ መሥመር ይቀየራል› የሚል መፈክር ያሰማል፡፡ ምነው ሲሆን መንገዱ ሳይሠራ፣ ካልሆነም ቴሌ ሲቆፍረው አትመጡም ወይ? ያልናቸው እንደሆን ‹እኛ በወንድነት ከነማን አንሰን ነው ሌላ በቆፈረው ጉድጓድ የምንሠራ፡፡ እኛም የራሳችን ቆፋሪ ክፍል አለን፣ የመቆፈሪያ በጀት አለን፣ የማስቆፈሪያ አበል አለን፡፡ እጃችን ሙቅ ይዟል እንዴ? እንንደዋለን እንጂ፡፡ እንኳን ይኼንን ኮረትና አፈር የለበሰ ጉድጓድ፣ ምን የመሰለውን  አውራ አስፓልትም ዕጢ እንደሚወጣለት ሆድ ስንተረትረው ባያችሁ› ይሉናል፡፡
ገና እናፈርሳለን
ገና እንንዳለን
በጀት እስካስፈቀድን፣ ዕቅድ እስካወጣን
ገና እንቆፍራለን፣ ገና እናፈርሳለን፡፡
የሚለውን መዝሙር እያቀነቀኑ ያን የፈረደበት አስፓልት ይተረትሩታል፡፡ አማርኛ የሚናገሩ ደርቡሾች፡፡ ስትፈርስ ስትሠራ የምትኖር አገር ናት፣ መቼም ፈርዶባታል ብለን እኛም ዝም አልን፡፡ ዝምታችንም እንደፍርሃት ስለተቆጠረ ሦስቱ ጨረሱና አራተኛው መጣ፡፡ ‹ለአዲሱ መንገድ የኤሌክትሪክ ምሶሶ እንተክላለን› የሚሉ አፍራሾች መቆፈሪያቸውን እንደሳንጃ ወድረው፣ አካፋቸውን እንደ ጦር አሹለው አሰፈሰፉ፡፡ የተስተካከለውን የእግረኛ መንገድ እንደተጣመመ ጥርስ እየነቀሉ፣ የተደላደለውን ጎዳና እንደ ወርቅ ፈላጊ እየፈነቀሉ የበልግ እርሻ አስመሰሉት፡፡ ይባስ ብለው ወደ ምሶሶ የሚገባው የኤሌክትሪክ ገመድ እንደ ፈልፈል በምድር ውስጥ ነውና የሚሄደው እኛም በተራችን መንገድ እንቆርጣለን - አሉና ተነሡ፡፡ እኛም
በመንደሩ መሐል አንድ ዋርካ ቢኖር
ያም መጥቶ ያም መጥቶ ይፈልጠው ጀመር
የሚለውን ነጠላ ዜማ ለቀቅን፡፡ ሠፈራችንን ከመልቀቅ ነጠላ ዜማ መልቀቅ ይሻላል ብለን፡፡ ይኼው ከተማችንም አራቱ መስተፃርራን እንደ አራቱ ወቅቶች እየተፈራረቁ ሲያፈርሷት፣ እርሷም ሳያልፍላት እኛም ሳያልፍልን እንኖራለን፡፡ በዚህ የጠላትነት አዙሪት ውስጥ መግባታችን የሚታወቀው ደግሞ ውኃና ፍሳሽ የዘረጋውን፣ መብራት ኃይል የቀበረውን፣ ቴሌ የደለደለውን መንገዶች ባለ ሥልጣን እንደገና አፈርሰዋለሁ ብሎ መነሣቱን ስናይ ነው፡፡ መንገዱ ይሰፋል፣ ደረጃው ይሻሻላል ብሎ ባልተወለደ አንጀቱ ያ ሁሉ ብር የፈሰሰበትን አስፋልት ጅብ እንዳገኘው የአህያ ሆድ ዘረገፈው፡፡   
የአቦላን ተራራ ያክላል ጡትሽ
ወይ ባል አላገባሽ ወይ አልመነኮስሽ
እንዴው ልጃገረድ ይባላል ስምሽ
እንዳለው ክራር ገራፊ፡፡ ከተማችንም ገጠር አይሏት ሕንጻዎቿ እንደ ጡት አጎጥጉጠው፤ ወይ ሁነኛ የመንግሥት ባል አላገባች፣ ወይ እንደ ፈረሰች ከተማ ጨርሶ አልመነኮሰች - እንደ መንደር ምግብ ቤት ድስት አሥር ጊዜ ስትወጠወጥ ትኖራለች፡፡ የሀገሬ ህዳሴ የሚጀምረው መቼ ነው ብለው ለሚጠይቁ - መልሱ - እነዚህ አራቱ መስተፃርራን የታረቁ ጊዜ ነው፡፡  
         

14 comments:

 1. Yihuna!

  Keep up the good work our Big Brother!

  ReplyDelete
 2. A hiden truth from Government and peoples

  ReplyDelete
 3. መልሱ - እነዚህ አራቱ መስተፃርራን የታረቁ ጊዜ ነው፡፡ dn dani it is very funny.thank you as usual.

  ReplyDelete
 4. ewunethin new diyakon dani yelben tenagerkilgn!!! ahun degmo atikilt enji enante wuha atetum teblen yetine yet meseleh wuha hiden minameta!! koy gn dani yewuch hagerat eko endezih ayinet eyitawochin betam new mitekemubachew yegnawoch min nekachewu weys endene yemanbeb beal yelachewum???

  ReplyDelete
 5. ወንድማችን ዲ/ን ዳንኤል በርታ ያንተን ጽሑፍ ተከትሎ አንዳንድ ለውጦች ሲደረጉ ማየት ያበረታታልና እግዚአብሔር ብርታቱን ይስጥህ፡፡ በዚህ የጡመራ መድረክ የተለጠፉ ጽሑፎችን ተከትሎ ካልተሳሳትኩ ትዝ የሚሉኝ ሁለት ለውጦች አይቻለሁ
  1. የእንዳ እየሱስ ምሽግ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ አማካኝነት መጠበቅ እና ለጎብኚዎች ክፍት መሆን
  2. በተለምዶ ኢቦላ (ፐብሊክ ሰርቪሲ) የተባለው አውቶቡስ ላይ ለአቅመ ደካሞች፣ ለነፍሰጡሮችና ለአካል ጉዳተኞች የሚሆኑ ወንበሮች መዘጋጀት
  ሰባት ዓመት ሙሉ ጽፎ ሁለትም ቢሆን ለውጥ ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥራህን ይባርክልህ

  ReplyDelete
 6. dn dani condominium(Yewel Bet) lay new teru yetayew.Thank you.

  ReplyDelete
 7. እየሳኩ እና እየተገረምኩ ነበር ያነበብኩት።በጣም
  ደስ ይላል። በሚገባ አስተውለህ አይተሀቸዋል።

  ReplyDelete
 8. መቻል ነዉ እንግዲ ምን ይደረግ ብለህ ነዉ ወንድሜ ዳንኤል.
  በዚህ ዘመን በተለይ በኛ ሀገር፡-
   ታታሪነት ና መቸኮል
   ትግስት ና አድር ባይነት
   ማስተዋል ና ስንፍና
   ጥበብ ና መሰሪነት(ተንኮል)
   ዘመናዊነት ና ድንቁርና
   መሰልጠን ና መሰይጠን
   ነፃነትና ና ህገወጥነት
   ሰላም ማስከበር ና ህዝብን ማፈን
   መብት ና ግዴታ
   ልባዊ ተግባር ና አስመሳይነት
  የሚባሉት የህይወት መሰረታዊ ነገሮች እንደ ህዝብም እንደ መንግስትም ተምታተዉብን ስለምንኖረ
  በዚች ለምንም ለማንም በማትራራ ሁከትና ግርግር በማይለያት ዉስብስብ አለም ዉስጥ፤ ህይወት እንዲህ ናት፤ ይህም ያልፋል እያልን እንኖራለን፡፡

  ReplyDelete
 9. አራቱንም ሊያስታርቅ የሚችለው የከተማው መስተዳድር ሥራውን እየሰራ ስላልሆነና መካከል ገብቶ መስራትና እንደ ድልድይ መሆን ባለመቻሉ፤ እንዲሁም በማስተር ፕላን መመራት ያልቻለች ከተማ ስላለን ነው ሁሌ ቁፈራና ግንባታ፤ ማፍረስና መስራት የማያቋርጡ ጓደኛሞች ሆነው የሚሄዱት::
  ከመካከላቸው ትልቅ ገደል እያለ ምን ያድርጉ ድርጅቶቹ ወቅታዊውን የደንበኛቸውን ችግር ለመፍታት መቆፈር ያለበትን ይቆፍራሉ መለጠፍ ያለበትን ይለጥፋሉ ብቻቸውን እንዳሉ እንጂ ሌላውን አያስቡም

  ReplyDelete
 10. ለምሳሌ ያህል አዲሱ የሜክሲኮ መንገድ ከተሰራ ወር አይሆነውም ይህው ዛሬ እድሜ ለእነ እንቶኔ እንዳልበረ አዳረጉት ...

  ReplyDelete
 11. በደንብ አስተዉለዋል ። ችግሩ የተከሰተዉ በዕቅድ ስለማንመራና የጋራ መናበብ ስሌለን ነዉ ።ይህ ደግሞ ምንጩ በዕዉቀት ላይ ያልተመሰረተ ሰዎች ስለሚመሩት ነዉ ። ችግሩን ለመፍታት ለሀገሩ የሚያስብ በሙያዉ ዕዉቀት የተካነ ሲመደብ ያኔ ሀገራችን ሀገር ትሆን ይሆናል ። እግዚያብሔር ዘመንዎን ይባርክ እግዚያብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ ።

  ReplyDelete
 12. ስትፈርስ ስትሠራ የምትኖር አገር ናት፣ መቼም ፈርዶባታል ብለን እኛም ዝም አልን፡፡
  ReplyDelete
 13. ስትፈርስ ስትሠራ የምትኖር አገር ናት፣ መቼም ፈርዶባታል ብለን እኛም ዝም አልን፡፡

  ReplyDelete