ሰሞኑን ዶክተር አባ ኃይለ ማርያም
ኦርቶዶክሳውያን ካልሆኑ አካላት ጋር ያከናወኑትን ‹የጠበልና እምነት› ጉዳይ በተመለከተ አያሌ ጥያቄዎች ሲነሡ ነበር፡፡ ነገሩን
ከየምንጮቹ ብሰማቸውም በቅዱስ ጳውሎስ ዘመን የነበረው የቂሣርያው ገዥ ፊስጦስ ‹ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ለፊት ሳይቆም፣ ለተከሰሰበትም
መልስ ይሰጥ ዘንድ ፈንታ ሳያገኝ ማንንም ቢሆን አሳልፎ መስጥ የሮማውያን ሥርዓት አይደለም› (የሓዋ.25፣16) ብሎ የተናገረውን
መሠረት በማድረግ አባ ኃይለ ማርያም ለጉዳዩ የሚሰጡትን መልስና ማብራሪያ ጠብቄ ነበር፡፡ መልስና ማብራሪያውንም ሰጡ፡፡
አባ የድርጊቱን መከናወን አምነው
የክንውኑን ዓይነት ከተወራው የተለየ መሆኑን አብራሩልን፡፡
መልሳቸውን ስናጠቃልለው፡-
1. መርሐ ግብሩ ‹ውኃ ለሁሉም› በሚል
መርሕ እንደተዘጋጀ
2. ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳት እንደተገኙበት
3. ተበጥብጦ ከመጣው ውኃና እምነት
ጠቅሰው በተሳታፊዎቹ ግንባር ላይ ምልክት አንዳደረጉ
4. ሰውዬው ጣቱን አስጠጋ እንጂ አንዳልቀባቸው
መርሐ ግብሩ
‹ውኃ ለሁሉም በፍትሐዊነት እንዲዳረስ› ከሆነ እንዴት ነው እምነትና ውኃ በመበጥበጥ ውኃ ለሁሉም ሊዳረስ የሚችለው፡፡ ‹ውኃ ለሁሉም›
የሚለው ጉዳይ የዐውደ ጥናት፣ የምክክርና ምናልባትም የጸሎት ርእስ ሊሆን ይችላል እንጂ እምነትን በውኃ በጥብጦ በመቀባት ‹ውኃ
ለሁሉም› እንዴት ለማዳረስ ይቻላል? እምነት በውኃ በጥብጦ መቀባት
ለፈውስ ያገለግላል እንጂ እንዴት ከውኃ ፍትሐዊ አጠቃቀም ጋር ተገናኘ? ደግሞስ እኛ ከሌሎች እምነቶች ጋር አንድነታችንን ማምጣት
ያለብን በክርስቶስ እንጂ እምነት በውኃ በመበጥበጥ ነው እንዴ?