Thursday, April 20, 2017

ለሕዝብ ያልታወቀ - ከሕዝብ የራቀ


መቅደላ ላይ ጀግናው ዐፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን የሠዉበትን ቦታ ለማየት ጎብኚዎች ተራራውን ይወጣሉ ይወርዳሉ፡፡ እልፍ ብሎ ደግሞ አንድ የመቅደላ ገበሬ በትሩን ተደግፎ ቆሞ የሚሆነውን በአግራሞት ያያል፡፡ ይህንን የታዘበ ጋዜጠኛ ካሜራውን አነጣጥሮ፣ መቅረጸ ድምጹንም ወድሮ ጠጋ አለውና ‹ዐፄ ቴዎድሮስ የተሠዉበት የመቅደላ አካባቢ ነዋሪ በመሆንዎ ምን ይሰማዎታል› ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ገበሬውም በትሩን ተደግፎ ባሻገር መቅደላን እያየ ‹ተወኝ ባክህ፤ ካላጣው ቦታ እዚህ መጥቶ ሞቶ እህሌን ያስጠቀጠቅብኛል› አለና መለሰለት ይባላል፡፡
ይሄ ገበሬ በመቅደላ ዙሪያ የሚኖር ገበሬ ነው፡፡ ለእርሱ ከመቅደላ አምባ በላይ የእርሻ ቦታው የመኖርና ያለመኖር ጉዳዩ ነው፡፡ ያ ሁሉ ሕዝብ መቅደላን ለመጎብኘት በመሄዱ ገበሬው ያገኘው ትሩፋት የለም፡፡ እንዲያውም ተጓዡ መንገድ ፍለጋ በእርሻው ላይ ሲሄድ ሲመጣ የሚያደርሰው ጉዳት ያሳስበዋል፡፡ ለእርሱ ያ ሁሉ ወጭ ወራጅ ‹ዓለምኛ› ነው፡፡ ቤሳ ቤስቲኒ ጠብ አያደርግለትም፡፡ ለምን እንደሚወርዱ፣ ለምንስ እንደሚወጡ የነገረው ያለም፡፡ እርሱ የወረዳ ካቢኔ፣ የፓርቲ ካድሬ፣ የዞን መስተዳድር፣ የክልል ባለ ሥልጣን፣ የ‹ወርክ ሾፕ› ተሳታፊ፣ የመስክ ጎብኚ፣ የኮንፈረንስ ተካፋይ አይደለ፡፡ ማን ይነግረዋል፡፡ እርሱ ‹ሕዝብ› ነው፡፡
መብት ዕድልን ካላስቀደመ ዋጋ የለውም፡፡ የማወቅ መብት የማወቅ ዕድልን ማስቀደም አለበት፡፡ ፍትሕ የማግኘት መብት የፍትሕ አካላትን በቅርበትና በነጻነት የማግኘትን ዕድል ማስቀደም አለበት፡፤ ሐሳብን በነጻነት የመግለጥ መብት ነጻና ገለልተኛ ሐሳብ የመግለጫ መንገዶችን በቅርበት የማግኘት መብትን ማስቀደም አለበት፡፡ ትምህርት ቤቶች በሌሉበት የመማር መብት፣ የማምለኪያ ቦታዎች በሌሉበት የማመን መብት፣ አመቺና ተደራሽ የመጓጓዣ መንገዶችና ዘዴዎች በሌሉበት የመዘዋወር መብት፣ ደመና እንጂ ዝናብ አይሆኑም፡፡

የሀገራችን ሰው ‹ሥጋ ሰጥቶ ቢላ መንሣት› የሚለው ብሂል አለ፡፡ በጥንቱ ባህል ግብዣ ላይ ቁርጥ ሥጋ ሲቀርብ የሰላ ቢላዋ ከሌለ፣ ሥጋው ለዓይን እንጂ ለሆድ ምግብ ሊሆን አይችልም፡፡ የአዲስ ዓለም ማርያም ቤተ ክርስቲያን በ1898 ዓም ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር ፈረስ የሚያስጋልብ ዳስ ተጥሎ፣ ሥጋው ቅጠል በተረበረበ አልጋ ላይ ተጋድሞ፣ ተጋባዡ ዓላማ እንዳየ ወታደር ተሰድሮ ይረበረብ ነበር ይባላል፡፡ ምን ዋጋ አለው፡፡ የቀረበው ሥጋና የመጣው ቢላዋ አልጣጣም ብሎ ብዙው ተጋባዥ ሥጋ አግኝቶ ቢለዋ ሳይደርሰው ቀረ፡፡
ይህን ያየ ተጋባዥ ‹ሥጋ ሰጥቶ ቢላ መንሣት› ሆነበትና የዳሱ ማገር የተሠራበትን ሸንበቆ እየሳበ፣ እንደ ቢላዋ እየጠረበ ሥጋውን ይቆርጠው ጀመር፡፡ ይህንን የተመለከተ ገጣሚ
ብርንዶው ባንድ አልጋ
ጮማውም ባንድ አልጋ
በማገር ይበላል እንዲህ ያለ ሥጋ፡፡ ብሎ ገጠመ ይባላል፡፡
አንድ ነገር ለሕዝብ ተብሎ መሠራቱ፣ መቅረቡና መገዛቱ ብቻ ጠቃሚ አያደርገውም፡፡ ሕዝቡ ያንን ነገር የሚያውቅበት፣ ዐውቆ የሚወስንበት፣ ወስኖ የሚያስከብርበት ዐቅም እንዲያዳብር መደረግ አለበት፡፡ የሐኪሙ ፍቱን መድኃኒት ከማዘዝ በላይ የበሽተኛው የመድኃኒቱን ጥቅምና አጠቃቀም ተረድቶ መውሰዱ የበለጠ አስፈላጊ ነው፡፡ ደርግ በወደቀ ጊዜ ገበሬው ለምን የገበሬ ማኅበርን ደን እንደቆረጠ አንድ ባለሞያ የተናገሩት እዚህ ላይ ቢጠቀስ ሸጋ ነው፡፡ ‹የዚያ ዘመን አብዮተኞች ሕዝቡ በታሪኩም በተረቱም ሰምቶት የማያውቀውን ኮሙኒዝም የሚባል ዛር አመጡበት፡፡ የት እንዳለ፣ ምን እንደሚመስል፣  ግብሩ ምን እንደሆነ፣ ማርከሻው በምን እንደሆነ የማይታወቅ ዛር ነው ይዘውበት የመጡት፡፡ በሥዕል አያውቀውም፣ በተረት አልተነገረውም፣ በዘፈን አልሰማውም፣ በድርሳንም በተአምርም አንብቦት አያውቅም፡፡ ጠበል ላይም ሲለፈልፍ አልሰማም፡፡ ለዚህ ለማያውቀው ዛር ሲባል ብዙ መከራ ተቀብሏል፡፡ ውትድርና ዘምቷል፣ ዛፍ ተክሏል፣ እርሻ አርሷል፣ መዋጮ ገፍግፏል፡፡ በመጨረሻ ደርግ ሲወድቅ ኮሙኒዝምን ቢፈልግ ቢፈልግ አላገነውም፡፡ ያገኘው ዛፉን ነው፡፡ ዛፉ ኮሙኒዝም መሰለውና ቆረጠው፡፡ የዛፍ መትከልን አስፈላጊነትና ጥቅም ከማስረዳት፣ ከማሳመንና አምኖ እንዲሠራበት ከማድረግ ይልቅ ‹ባይገባውም ዋናው ዛፉ ነው› ተብሎ በቅጣት የተሠራው ሥራ ዛፉ ኮሙኒዝ እንዲሆን አደረገው› ነበር ያሉት፡፡
ማስገደድና ማዘዝ ሥልጣንንና ጉልበትን እንጂ ዐቅምን አያመለክቱም፡፡ በአእምሮ ዐቅማቸው የማይተማመኑ ሁሉ ሐሳብን፣ ዕውቀትንና ተዋሥኦን ይፈሩታል፡፡ ተናግረው እንደማይሰሙ፣ ተንትነው እንደማያሳምኑ፣ ተከራክረው እንደማይረቱ ልባቸው ያውቀዋል፡፡ ስለዚህም ከሰውነት ተርታ ይወርዳሉ፡፡ እንስሳነት ሜዳ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደ እንስሳትም ጉልበትና ሥልጣንን ብቻ ይጠቀማሉ፡፡ መመሪያቸው ‹የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው› ነው፡፡ የዱቄቱ ጥራት ግን እንደተፈጨበት ቦታ እንደሚወሰን አያውቁም፡፡ በሚሸረክት ወፍጮ የተፈጨ ዱቄት እንዴት ዳቦ ይሆናል? ንጽሕና በሌለው ወፍጮ የተፈጨ ዱቄትስ እንዴት ጤና ይሆናል፡፡ ውጤት ያለ ሂደቱ ብቻውን ቅዱስ ሊሆን አይችልም፡፡
እስኪ ሁለት ነገሮች እናንሳና የመቅደላውን ገበሬ የሚያስታውሰንን ጥያቄ እንጠይቅ፡፡ በየስብሰባውም፣ በየሚዲያውም፣ በየሰሌዳውም ‹ዕድገትና የትራንስፎርሜሽ ዕቅድ› ይባላል፡፡ ለመሆኑ ይህ ዕቅድ የት ነው ያለው? እንደ ግማደ መስቀሉ ተቀብሮ? ወይስ እንደ ታቦተ ጽዮን ተሠውሮ? ለመሆኑ ስንት ገጽ አለው? የተጻፈውስ በምን ቋንቋ ነው? ‹የዕድገትና ትራንስፎርሜሽ ዕቅዱን ለማሳካት እንዲህና እንዲያ እናደርጋለን› የሚሉት ሰዎች ምን ያህል አንብበውታል? ምን ያህልስ ተረድተውታል? ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ልባቸውን ሞልተው ደረታቸውን ነፍተው ስለ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽ ዕቅዱ የሚናገሩት ጋዜጠኞችስ እውነት አንብበውታል? አንድ ቅጅስ በእጃቸው ይገኛል? ወይስ ‹ሳያዩ የሚያም› የሚለው ለዚህም ይሠራል? በየመድረኩ የሚያስፎክሩን ሰዎችስ ‹ዕድገት›ና ‹ትራንስፎርሜሽን› ስለሚሉት ሐሳቦች ተመሳሳይ ግንዛቤ አላቸው?
አዲስ አበባ መሪ ዕቅድስ? የዕቅዱ ባለቤት ሕዝብ ነው፤ በዕቅዱ ላይ ከሁለት መቶ ሺ ሕዝብ በላይ ተሳትፎበታል ተብሏል፡፡ ሕዝቡ ግን በእጁ ቅጅው አለው? መጠየቅ ይችላል? በዕቅዱ መሠረት ተፈጽሟል፣ በዕቅዱ መሠረት አልተፈጸመም ለማለት የሚያስችለው መዝገብ በእጁ አለ? በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ የሚማሩ ወጣቶች አንብበው ሊረዱት፣ መምህራንም ከዚያ አውጥተው የቤት ሥራ ሊሰጡበት የሚችሉበት ቅጅ አለ?  
በሌላው ዓለም የሆነ እንደሆነ የማወቅ መብትን ለማረጋገጥ እንዲቻል የሚታወቅበት መንገድ ወሳኝ ነውና ‹የሕዝብ ቅጅ (Popular Version)› የሚባል ኅትመት ይዘጋጃል፡፡ የሕዝብ ቅጅ የሚባለው ሞያዊ በሆኑ ቃላት የተሞላውን፣ ውስብስብ የሆነውንና እልፍ በሆኑ ገጾች የተዘጋጀውን መዝገብ ሦስት ነገሮችን አሟልቶ እንዲዘጋጅ ለማድረግ መቻል ነው፡፡ በቀላል ቋንቋ፣ ዋና ዋና ሐሳቦችንና ጉዳዮችን ይዞ፣ በተመጠኑ ገጾች የሚዘጋጅ ነው የሕዝብ ቅጅ፡፡ የኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሚጎድለው አንዱ ዋነኛ ነገር ይሄ ነው፡፡ ዕቅዱ የሚታሰብ እንጂ የሚነበብ አልሆነም፡፡ ዕቅዱ ስለ እርሱ የምንሰማለት እንጂ እርሱን ራሱን የምንሰማው አልሆነም፡፡ ዕቅዱ መኖሩን በእምነት እንጂ በመንካት ልናረጋግጠው አልቻልንም፡፡ ስለ ዕቅዱ እናውቃለን እንጂ ዕቅዱን አናውቀውም፡፡ ለምን?
የሕዝብን የማወቅ መብት የሚያስከብር የሕዝብ የማወቂያ መንገድ አልተዘጋጀምና፡፡ የመቅደላው ገበሬ ከመቅደላ አምባ ይልቅ የእርሱ እርሻ ነገር ያሳሰበው፣ መቅደላ ላይ ምን እየተደረገ እንዳለ የሚነግረው ስላላገኘ ነው፡፡ ለተራራው ቅርብ ቢሆንም ለጉዳዩ ግን እጅግ እንዲርቅ ተደርጓል፡፡ የሁለቱ ሀገራዊ መዛግብት ዕጣ ፈንታም እንዲሁ ነው፡፡ ስለ ፈጣሪ የሚነግሩን ቅዱሳት መጻሕፍት እንኳን ለሕዝብ በሚገባው ቋንቋ በቀላሉ ሕዝብ እጅ እንዲደርሱ፣ ጳጳሱና ምእመኑ፣ ዑለማውና ሙእሚኑ እኩል እንዲጠቅሱዋቸው በተደረገበት ዘመን፤ ለሀገር የወጣ ዕቅድ ምነው እንደ ሰማይ ራቀ፣ እንደ ነፍስ ረቀቀ?  
  


22 comments:

 1. ሠላምታ። ለጥያቄዎት ሦሥት መልስ አሉኝ። የመጀመሪያው፣ ለግዜ ቁጠባ ሲባል ሕዝብን አለማማከር፡ ዋናው ዓላማ ኤኮኖሚዉን ማዳበር ማለትም በተቻለ መጠን በፍጥነት ገንዘብ መሥራት ነውና። ሁለተኛ፣ ሕዝብን መምከር የገንዘብ ወጪ ነው። በተጨማሪም ሕዝቡ ዕቅዱን ሊቃወም ይችላል። ይህ ከሆነ የገንዘብና የግዜ ብክነት ይፈጠራል። ሦሥተኛው ምክንያት የህሊና ግድፈት የተቀላቀለበት ነው። (በንቀት) ሕዝቡ መሐይም ነው ስለዚህም አላማክረውም በማለት፣ (ሥርቆት) ዕቅዱ ሊያመጣ የሚችለውን ትርፍ ለሕዝብ አለመግለፅ፡ የተወሠነ ገቢ ለማሸሽ የያመቻል።

  የመጀመሪያ ግዜ ነው ፅሑፎን ሣነብ። ልዩ ነው።
  "ከፈረንሣይ"

  ReplyDelete
 2. well-articulated ... thank you Dn. Daniel K.

  ReplyDelete
 3. ማስገደድና ማዘዝ ሥልጣንንና ጉልበትን እንጂ ዐቅምን አያመለክቱም፡፡ በአእምሮ ዐቅማቸው የማይተማመኑ ሁሉ ሐሳብን፣ ዕውቀትንና ተዋሥኦን ይፈሩታል፡፡ ተናግረው እንደማይሰሙ፣ ተንትነው እንደማያሳምኑ፣ ተከራክረው እንደማይረቱ ልባቸው ያውቀዋል፡፡ ስለዚህም ከሰውነት ተርታ ይወርዳሉ፡፡ እንስሳነት ሜዳ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደ እንስሳትም ጉልበትና ሥልጣንን ብቻ ይጠቀማሉ፡፡

  ReplyDelete
 4. ግሩም ዕይታ ነው :: እነሆኝ ምስጋና::

  ReplyDelete
 5. Well thought ideas are identified. Sure the documents have to be more accessible to people in terms of content through different mechanisms as you said. Since the document comprises several topics and areas of plan each has to be explained to the people in a clear manner.

  ReplyDelete
 6. ተው እንጅ ዳኒ እንደወረደ ተቀበሉ ያሉንን እንደወረደ እኛም እናውርደው እንጂ ሌላ ጣጣ ደግሞ .....

  ReplyDelete
 7. በየመድረኩ የሚያስፎክሩን ሰዎችስ ‹ዕድገት›ና ‹ትራንስፎርሜሽን› ስለሚሉት ሐሳቦች ተመሳሳይ ግንዛቤ አላቸው?

  ReplyDelete
 8. ለዚህች ሀገረ እኔ ብቻ አውቅልሻለሁ የሚል እንጂ እናንተም ታውቃላችሁ የሚል ስሌለለ የማያዉቁላት ሰዎች የማይታወቅ ቁሳዊ እቅድ እያወጡ አስተሳሰብ ላይ ሳይሰልጡ በስማ በለው ያደነቁሩናል፡፡ እቅድ አዘጋጆች እነሱ ፤ አውጪዎች እነሱ ፤ ገምጋሚዎች እነሱ ፤ ከሁሉ በፊት የአስተሳሰብ ትራንስፎርሜሽን እቅድ ያስፈልገናል ካልሆነ ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ ነው የሚሆነው፡፡

  ReplyDelete
 9. ለዚህች ሀገረ እኔ ብቻ አውቅልሻለሁ የሚል እንጂ እናንተም ታውቃላችሁ የሚል ስሌለለ የማያዉቁላት ሰዎች የማይታወቅ ቁሳዊ እቅድ እያወጡ አስተሳሰብ ላይ ሳይሰልጡ በስማ በለው ያደነቁሩናል፡፡ እቅድ አዘጋጆች እነሱ ፤ አውጪዎች እነሱ ፤ ገምጋሚዎች እነሱ ፤ ከሁሉ በፊት የአስተሳሰብ ትራንስፎርሜሽን እቅድ ያስፈልገናል ካልሆነ ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ ነው የሚሆነው፡፡

  ReplyDelete
 10. ሠላምታ። ለጥያቄዎት ሦሥት መልስ አሉኝ። የመጀመሪያው፣ ለግዜ ቁጠባ ሲባል ሕዝብን አለማማከር፡ ዋናው ዓላማ ኤኮኖሚዉን ማዳበር ማለትም በተቻለ መጠን በፍጥነት ገንዘብ መሥራት ነውና። ሁለተኛ፣ ሕዝብን መምከር የገንዘብ ወጪ ነው። በተጨማሪም ሕዝቡ ዕቅዱን ሊቃወም ይችላል። ይህ ከሆነ የገንዘብና የግዜ ብክነት ይፈጠራል። ሦሥተኛው ምክንያት የህሊና ግድፈት የተቀላቀለበት ነው። (በንቀት) ሕዝቡ መሐይም ነው ስለዚህም አላማክረውም በማለት፣ (ሥርቆት) ዕቅዱ ሊያመጣ የሚችለውን ትርፍ ለሕዝብ አለመግለፅ፡ የተወሠነ ገቢ ለማሸሽ የያመቻል።

  የመጀመሪያ ግዜ ነው ፅሑፎን ሣነብ። ልዩ ነው።
  "ከፈረንሣይ"

  ReplyDelete
 11. Nice view! You nicely put it that the fate of all things done without making the public aware is a failure at last!

  ReplyDelete
 12. Good read Danny!Thank you.

  ReplyDelete
 13. Great piece. Berta Dani.

  ReplyDelete
 14. I appreciate the idea you raised. I have been thinking over such issue. As professional, I read GTP II and AGP which is an excellent document. But does not consider the reality in the ground . Dani for sure most of the implementer does not know the plan in reality. I am working with them. they are against plan unknowingly and lack of understanding in different sectors. The plan is Top down, not Down to Top just for the sake of politics and funding. Our people are sick, need medication. You raised the sickness. If they do have ear and hear, they have to prepare medication. But they are knowingly deaf.Therefore it will die as the communist idea of planting tree. Even though the idea is nice it needs community consent. Politicians should listen before they speak like eko.

  ReplyDelete
 15. ለሀገር የወጣ ዕቅድ ምነው እንደ ሰማይ ራቀ፣ እንደ ነፍስ ረቀቀ?

  ReplyDelete
 16. Des yilal.Arso aderu tikikil nachew

  ReplyDelete
 17. እግዚአብሄር ይስጥልኝ ሚሰማ የለም እንጂ

  ReplyDelete
 18. ሕዝብ አለቃ ቢሆን ኖሮ የተባለውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ሕዝብ አለቃ አይደለም እየጮሀ እንዳያስቸግር ብቻ ይመስላል አንዳንድ ስራዎች የሚሰሩት፡፡ ሕዝብ ቢፈራ (ፈ›ን ጠበቅ) ኖሮ እንኳን በእርሱ ስም፤ ለሱ፤ በርስቱ ላይ ስለሚሰራው ነገር ቀርቶ በጎረቤቱ ስለሆነው፤ በአየሩ ስለነፈሰው ነገር ሁሉ ቶሎ ብለው ያሳውቁታል! ምክንያቱም ጌታና ፈላጭ ቆራጭ ነዋ ሕዝብ! እዚህ ሀገር ግን ሕዝብ ተንቋል፡፡ አንድና አንድ ጠመንጃ እስከታያዘ ድረስ ሕዝብን ማክበር፤ መፍራት ጥቅሙ አይታይም፡፡ ወድያውም አንዲያ ለመሆን መጀመርያ ብዙ የቤት ስራ ይቀራል፡፡

  ReplyDelete