Wednesday, March 8, 2017

የእንዳ ኢየሱስ ምሽግ፡- ከእቴጌ ጣይቱ እስከ ዶክተር ክንደያ


click here for pdf
የመቀሌው ምሽግ ጥንታዊ ፎቶ
የአድዋ ጦርነትና ድል ሲነሣ ምንጊዜም አብሮ የሚነሣ የኢትዮጵያውያን የጀግንነትና የብልሃት ዐውደ ውጊያ አለ፡፡ የመቀሌው ምሽግ ውጊያ፡፡
ጣልያኖች የመረብን ወንዝ ተሻግረው ወደ ትግራይ ሲገቡ ጠንካራ ምሽግ ከሠሩባቸው ቦታዎች አንዱ መቀሌ እንዳ ኢየሱስ ነበር፡፡ ምሽጉን ማጆር ቶዞሊ አስጀምሮት እርሱ በአላጌው ውጊያ ሲሞት ማጆር ጋልያኖ አጠናቅቆታል፡፡ ለመቀሌው ምሽግ መጠናከር ዋናው ምክንያት ጣልያኖች አላጀ ላይ በራስ መኮንን በሚመራው የኢትዮጵያ ጦር የገጠማቸው ሽንፈት ነው፡፡ ጄኔራል አርሞንዲ ኅዳር 28 ቀን 1888 ዓም የደረሰበትን የአላጌን ግንባር ሽንፈት ተከትሎ ወደ ኋላ በሸሸው የጣልያን ወታደር አማካኝነት ከባሕር ወለል በላይ በ2240 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘውን የእንዳ ኢየሱስ ምሽግ የበለጠ እንዲጠናከር አደረገ፡፡ በቦታው የሚገኘውን የኢየሱስን ታቦት አስወጥቶ ቦታውን ሙሉ በሙሉ ምሽግ አደረገው፡፡
እነ ፊታውራሪ ገበየሁ ታሪክ የሠሩበትና የኢትዮጵያውያንን ጥምር ክንድ ጣልያን በሚገባ በቀመሰበት በአላጌ ግንባር ማዦር ቶዜሊ በራስ ዐሉላ ብርጌድ ደረቱን ተመትቶ የወደቀበት ነው፡፡
አላጌ በሩ ላይ ሲወርድ ማዦር
እንደ ግራኝ ሁሉ በሰባት አረር - ተብሎለታል፡፡ 

 
በዚህ ጦርነት አምስት ካፒቴኖች፣ ዐሥር የመቶ አለቆችና ሁለት ምክትል መቶ አለቆች በጦርነቱ ተገደሉ፡፡ ሁለት ሺ የሚደርሱ የኢጣልያ ወታደሮችም አለቁ፡፡ ራስ መኮንንም የጣልያኖቹን ሬሳ ከየቦታው አስለቅመው በቤተ ማርያም አስቀበሩት፡፡ ይህም ጣልያኖች መቀሌ ላይ ጠንካራ ምሽግ  እንዲሠሩ አደረጋቸው፡፡ ጄነራል አርሞንዲ የመቀሌው ምሽ በተመለከተ የሚዋዥቅ ሐሳብ ነበረው፡፡ ትቶ ለመሄድም አስቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን ማድረግ የጣልያንን ክብር መንካት ነው ብሎ ያመነው፣ ከዚህም አልፎ የኢትዮጵያን ጦር የሚንቀው ጋልያኖ የመቀሌው ምሽግ ላለማስደፈርና ተዋግቶ ለመሞት ቆረጠ፡፡ 
በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ጊዜ መልሶ የተሠራው የመቀሌው ምሽግ
ጳውሎስ ኞኞ እንደሚለው ‹የመቀሌ ምሽግ በደቡብ በኩል 3 ሜትር ስፋት ያለው ግንብ እየሆነ ተገነባ፡፡ ምሽጉ ዙሪያ ክቡን ካለው አጥር ሌላ ከግንቡ 30 ሜትር ያህል ራቅ ብሎ በጣም የሾሉ እንጨቶች በምሽጉ ዙሪያ በብዛት ተተከሉ፡፡ ካንዱ ሹል እንጨት እስከ አንዱ ሹል እንጨት ያለው ርቀትም 20 ሳንቲ ሜትር ያህል ነበር፡፡ እነኚህ ሹል እንጨቶች ከመሬት በላይ ያላቸው ከፍታ 30 ሳንቲ ሜትር ነው፡፡ ከሹል እንጨቶቹ አልፎ ደግሞ እሾካማ ሽቦ እየተድቦለቦለ በምሽጉ ዙሪያ እየተተከለ ተከምሯል፡፡ ከሽቦው ውጭ ደግሞ ጠርሙስ እየተሰበረ እንዲነሰነስ ተደረገ› ይላል፡፡
ጣልያኖች ይህንን ያደረጉት የኢትዮጵያ ወታደሮች ባዶ እግራቸውን ናቸውና ይህን አደገኛ እሾሃማ አጥር ተሻግረው ለመግባት ይከብዳቸዋል ብለው በማሰባቸው ነበር፡፡ እንዳሉትም ምሽጉን ለመስበር በተደጋጋሚ የተደረጉ ሙከራዎች ሊሳኩ አልቻሉም፡፡
ጣልያኖች ከምሽጉ ሥራና አጥር በተጨማሪ በምሽጉ ውስጥ ጠንካራ ጦር መሽጎ ነበር፡፡ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ እንደሚሉት  በጋልያኖ የሚመራው አንድ ባታልዮን ጦር 21 የጦር መኮንኖችን፣ 176 ነጭ ለባሾችን፣ 1150 የሀገር ተወላጅ ወታደሮችን እና አንድ መድፈኛ ጦር የያዘ ነበር፡፡ ጳውሎስ ኞኞም የመቀሌ ምሽግ 20 ከፍተኛ መኮንኖች 13 ዝቅተኛ መኮንኖች፣ 150 ባለ ሌላ ማዕረግ ወታደሮችና አንድ ሺ ጥቁር ወታደሮች ነበሩበት ይላል፡፡
በራስ መኮንን የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር የአላጀን ድል ተከትሎ ወደ መቀሌ ገሰገሠ፡፡ ኦገስት ዋይልድ የራስ መኮንን ጦር ኅዳር 30 ቀን 1888 ዓም የመቀሌውን ምሽግ ከብቦ መቀመጡን ጦርነቱንም ታኅሣሥ 18 ቀን መጀመሩን የሚገልጡ አሉ፡፡ ጳውሎስ ኞኞ ግን ጦርነቱ የተጀመረው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ መቀሌ ከገቡ በኋላ ታኅሣሥ 30 ቀን መሆኑን ይናገራል፡፡
ዐፄ ምኒሊክ መቀሌ ሲገቡ የመቀሌው የእንዳ ኢየሱስ ምሽግ ዙሪያውን ተከበበ፡፡ ጦሩ ከጣልያን መድፍ ርቀት ውጭ ሆኖ በጨለቆት በኩል የንጉሠ ነገሥቱ ጦር፣ የራስ መኮንንና የፊታውራሪ ገበየሁ ጦር፤ በደብሪ በኩል የሸዋ ጦር፤ በምሥራቅ በኩል የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትና የራስ መንገሻ ጦር፤  በገምበላ በኩል የራስ መንገሻ አቲከም እና የራስ ወሌ ጦር እንዲሠፍር ተደረገ፡፡ ሊቀ መኳስ አባተ ቧ ያለውና በጅሮንድ ባልቻ ደግሞ መድፎቻቸውን ይዘው በስተ ምሥራቅ በኩል አመቺ ሥፍራ ያዙ፡፡ 

ብዙዎቻችን እንደሚመስለን የኢትዮጵያ ጦር ወደ አድዋ ሲዘምት ኋላ ቀር መሣሪያ ብቻ አልያዘም፡፡ የኢትዮጵያን ጦር ለውጤት ያበቁት ጠንካራ የሀገር ፍቅር፣ ተገቢ የሆነ ዝግጅትና አደረጃጀት፣ የሁሉም ሕዝብ ሁለገብ ተሳትፎ፣ የዐፄ ምኒልክና የጦር ጄኔራሎቻቸው የአመራር ጥበብ፣ ከዚያ በፊት ከውጭ ወራሪዎች ጋር በተደረጉ ውጊያዎች የተቀሰሙ ልምዶች እና ትክክለኛ የጦርነት ምክንያት ናቸው፡፡
ዐፄ ምኒልክ ለማይቀረው ጦርነት ቅድመ ዝግጅት አድርገውበታል፡፡ ሀገሪቱ ጠብቃ ባቆየቻቸው መሣሪያዎች ላይ ከፈረንሳይ ተገዝተው በጅቡቲ በኩል የገቡትና በየዐውደ ውጊያው የተማረኩት ዘመናዊ መሣሪያዎችም ለጦርነቱ ውለዋል፡፡ ኦገስት ዋይልድ ይህንን ሁኔታ ሲገልጠው ‹the Hotchkiss quick firing guns with a longer range …were of a caliber of about two inches, firing both solid and percussion shell, and their range and accuracy were much superior to the muzzle-loading mountain guns of the Italians.> ይላል፡፡ ተክለ ጻድቅ መኩሪያም ‹ከፈረንሳይ ሀገር ተገዝቶ የመጣውና በኢትዮጵያውያን እጅ ያለው የመድፍ ጥይት እስከ 4500 ሜትር ድረስ ሄዶ የሚመታ ሲሆን የኢጣልያኖች ግን 3800 ሜትር የሚሄድ ነበር› ይላሉ፡፡ በዚህ መሣሪያ ላይ እነ ሊቀ መኳስ አባተ ቧ ያለውና በጅሮንድ ባልቻ አባ ነፍሶ ያሳደጉት ፈረስ ያህል ተክነውበታል፡፡
ኢትዮጵያውያን በመድፎቻቸው እየተረዱ ምሽጉን ሰብረው ለመግባት በተደጋጋሚ ሙከራ አድርገው ነበር፡፡ መሰላል አምጥተው ወደ ምሽጉ ከታች ወደ ላይ በድፍረት ለመውጣትም ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን ምሽጉ ከነበረበት ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ አንጻር ሊሳካ አልቻለም፡፡
በመጨረሻ ግን የእቴጌ ጣይቱ መላ በአጭር ጊዜ ምሽጉ እንዲለቀቅ አደረገ፡፡ 
ማይ አንሽቲ ምንጭ
 እቴጌ ጣይቱ ሊቀ መኳስ አባተ ቧ ያለው ጋር መክረው ‹ተዋግተው ለተረፉት ደስ የሚያሰኝ የክብር ሽልማት እሰጣለሁ፣ ለሞቱትም ተዝካራቸውን አወጣላቸዋለሁ› ብለው ብለው የላኳቸው በዝቅተኛ መኮንኖች የተመሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች ከምሽቱ በ11 ሰዓት ገብረ ጊዮርጊስ ድል ነሤ እና ሸዋዬ የሚባሉ አሽከሮች ሶስት ሦስት መቶ ወታደሮች ይዘው ወደ ማይ አንሽቲ ምንጭ ወረዱ፡፡ ምሽጋቸውንም ሠሩ፡፡ እቴጌይቱ ሌሊቱን ሙሉ ‹አምላኬ ሆይ አታሳፍረኝ እርዳኝ› እያሉ ሲጸልዩ ማደራቸውን ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ዐፄ ምሊክና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጽሐፍ ላይ ይገልጣሉ፡፡ 

ማይ አንሽቲ ከእንዳ ኢየሱስ ምሽግ 150 ክንድ ርቀት ላይ ይገኝ ነበር፡፡ ወታደሮቹ በሌሊት ገሥግሠው ምንጩን ከበቡት፡፡ ምንጩ የሚገኘው ከእንዳ ኢየሱስ ምሽግ ወረድ ብሎ ገደል ሥር ነበር፡፡ የእቴጌ ጣይቱ ወታደሮች ከምንጩ በ15 ክንድ ርቀት ላይ አድፍጠው ተቀመጡ፡፡ ጣልያኖች ምንጩ ለምሽጉ ቅርብ ስለነበር ይያዛል ብለው አልገመቱም፡፡ ውኃው በኢትዮጵያውያን መያዙን ሲያውቁ ምንጩን ለመቆጣጠር መድፎቻቸው ጎትተው አውጥተው በተደጋጋሚ ጥረት አደረጉ፡፡ ቦታው ከምሽጉ በኩል ለሚደረግ የመድፍ ምት ምቹ አልነበረም፡፡ ለፊት ለፊት ውጊያም ከጣልያኖች ይልቅ ለኢትዮጵያውያን የተመቸ ነበር፡፡ ምንጩን ለመቆጣጠር ጣልያኖች ያደረጉትን ጥረት የኢትዮጵያ ወታደሮች አደናቀፉት፡፡ ሊቀ መኳሽ አባተና በጅሮንድ ባልቻም የጣልያን መድፎችን በመነጽር አይተው ደበደቧቸው፡፡ ከዚያም አልፈው የጣልያኖችን መድፍ በመድፍ አፉን መትተው ሥራ አስፈቷቸው፡፡ በዚህም ምክንያት
አባተ አባ ይትረፍ ነገረኛ አዋሻኪ ሰው
ይህን መድፍ ከዚያ መድፍ አቆራረጠው - ተብሎ ተገጥሞላቸዋል፡፡
የጦርነቱ ጊዜ እየጨመረ ሲመጣ የጣልያኖቹ ውኃ እያለቀ መጣ፡፡ መጀመሪያ በራሽን ውኃ መታደል ጀመረ፡፡ በመቀጠልም ችግሩ ከጣልያን ወታደሮች ዐቅም በላይ ሆነ፡፡ እቴጌ ጣይቱ ግን ለምሽጉ ጠባቂዎች በየቀኑ ስንቅ ይልኩ ነበር፡፡   
ጣልያኖቹ ቀሪ ዕጣ ፈንታቸው ሞት መሆኑን ሲያውቁት ከ45 ቀን ከበባ በኋላ በድርድር እጃቸውን ለመስጠትና ምሽጉን ከነ መሣሪያው ለቀው ለመውጣት ወሰኑ፡፡ ጥር 21 ቀን በድርድሩም መሠረት ምሽጉ ተለቀቀ፡፡ ጣልያኖች መሣሪያቸውን አስረክበው ወጡ፡፡ ዐፄ ምኒልክም በሰላም ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ሸኟቸው፤ ዳግም በውጊያ ካገኟቸው እንደማይምሯቸው አስጠነቀቋቸው፡፡ ይህንን ውጤት ያመጣው እቴጌ ጣይቱ የዘየዱት መላ ነው፡፡ አስቀድመው ለጣልያኑ አምባሳደር ለአንቶኒሊ እስንዳስጠነቀቁት ጦርነቱን አልፈለጉትም ነበር፡፡ በሀገር ላይ ሲመጣ ግን ‹እዚያው የጦሩ ዐውድማ ላይ እንገናኛለን› ነበር አንቶኖሊን ያሉት፡፡ እቴጌ ጣይቱ ያሉት አልቀረም ለአድዋው ድል በር ከፋች የሆነውንና የካቲት 23 ቀን ለሚዋጋው ሠራዊት የሞራል ከፍታ የፈጠረውን ድል አስመዘገቡት፡፡ 
ለጎብኝ እንዲያመች ሆኖ የተጠገነው ምሽግ የግቢው መግቢያ
 እቴጌ ጣይቱ ታሪኩን ለመሥራት ሳይከብዳቸው ለ121ኛው የዐድዋ ድል በዓል አከባበር አድዋ ላይ የተገኙት ‹አርቲስቶች› ስማቸውን ማንሣት ከበዳቸው፡፡ ‹ኢትዮጵያውያን በፈጠሩት ዘዴ› ብለው ያለፉት ይህንን የጣልያን መዛግብት ሳይቀሩ በድንቅ የሚያነሡትን የእቴጌ ጣይቱን ታላቅ ጥበብ ነው፡፡ ዐድዋን እያከበሩ ምኒሊክንና ጣይቱን አለማንሣት ማለት አሜሪካን ከመከፋፈል ታድጎ ወደ አንድነት ያመጣትን ‹የአሜሪካ የርስበርስ ጦርነት› የሚባለውን ዘመቻ ታሪክ አንሥቶ አብርሃም ሊንከንን መዝለል ማለት ነው፡፡ የዶጋሊን ድል አንሥቶ ዐሉላ አባ ነጋን መዘንጋት፣ የሕወሐትን የመቀሌ እሥር ቤት ሰበራን ታሪክ አንሥቶ ኃየሎም አርአያን መተው ማለት ነው፡፡ በዐድዋው በዓል ላይ የዐፄ ምሊክ ስም ያነሡት ሁለት ተናጋሪዎች ብቻ ነበሩ፡፡ የደቡብ አፍሪካው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ታቦ ኢምቤኪና የጉዞ አድዋ አስተባባሪ ያሬድ ሹመቴ፡፡ ለእናንተ ኮፍያችንን በክብር እናነሣለን፡፡ 
 
የግቢው ንጣፍ በብርጭቆ ስብርባሪ ተነጥፏል
እንደ ንጉሡ አጎንብሱ ብለው ጣልያን ዐድዋ ላይ የሠራውን ስሕተት በደገሙት አርቲስቶቻችንና አርቲስቶቹ ታሪክ ዘለው ታሪክ እንዲያጠለሹ መመሪያ በሰጡት አለቆቻቸው እያዘንን 121ኛውን የዐድዋ ድል ልናከብረው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ሲረዳን ግን የእንዳ ኢየሱስ ምሽግ እንደገና እንዲያዝ ያደረገውን ታሪክ የካቲት 26 ቀን 2009 ዓም መቀሌ ላይ አየን፡፡ 
የዛሬ 2 ዓመት የአድዋ ተጓዦ ወጣቶች በእንዳ ኢየሱስ በኩል ሲያልፉ ምሽጉ ፈራርሶ፣ ተንቆና ተረስቶ፣ በዚያ ላይ የተሠዉት ኢትዮጵያውያን መቃብር ክብሩ ተዋርዶ፣ ዐጽማቸው የትም ወዳድቆ ተመለከቱ፡፡ አዘኑ፡፡ ዐፄ ምኒልክ ያልቻልክ በኀዘንህ እርዳኝ እንዳሉት፡፡ አዝነው ግን ዝም አላሉም የመቀሌ የኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ክንደያ ገብረ ሕይወት ይህንን ነገር እያዩ ለምን ዝም አሉ? ሲሉ ጠየቁ፡፡ ያሬድ ሹመቴ ስሜት የሞላበት ግልጽ ደብዳቤ ጻፈ፡፡ ሌሎችም ያንን ጩኸት አስተጋቡት፡፡ ‹መቼ ተነሡና የወዳደቁት› የሚለው የእጅጋየሁ ሺባባው ቃል እውነት ሆኖ አየነው ብለን ኀዘናችንን ገለጥን፡፡
ምሽጉ እንዳይፈርስ የተገነባው የመጠበቂያ ግንብ
 ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰማ ባለ ሥልጣን፣ ሰምቶም የሚፈጽም ባለ ሥልጣን በሥዕለት ከሚገኙ ነገሮች መካከል ናቸው፡፡ ዶክተር ክንደያና አመራራቸው ግን ሰሙ፡፡ ሰምተውም ቅርስን የሚመለከተውን የዩኒቨርሲቲውን የትምህርት ክፍል ጠሩ፡፡ከዩኒቨርሲቲው የግንባታ ክፍል ጋር በመሆን ታሪኩንና ቅርሱን የሚጠብቅ ዲዛይን እንዲዘጋጅ አዘዙ፡፡ የዲዛይኑን ዝግጅትም ራሳቸው ተከታተሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲው በጀትና የሰው ኃይል የእንዳ ኢየሱስ ምሽግ እንዲጠገን፣ አካባቢው እንዲጸዳ፣ ለጎብኚዎች በሚሆን መልኩ እንዲዘጋጅ፣ ዐጽሞቹ በክብር እንዲሰበሰቡና በልዩ ሥነ ሥርዓት እንዲቀበሩ አስደረጉ፡፡
የምሽጉ ጥገና ሥራ ተፈጽሞ ባለፈው እሑድ የካቲት 26 ቀን ተከብሯል፡፡ ጣልያን አድርጎት እንደነበረው ዙሪያውን በሽቦ ታጥሯል፡› መንገዱ ጣልያን ኢትዮጵያውያንን ለመከላከል አድርጎት እንደነበረው የብርጭቆ ስብርባሪ ተነስንሶበታል፡፡ በመቃብሩ ላይ ታሪኩን የሚዘክሩ ማስተዋሻዎችን ለማድረግ ተመቻችቷል፡፡ ከመንገዱ መጨረሻ ያለውን መቃብር በንጹሕ ሣር ለማሣመር ተሰናድቷል፡፡ ከመከራው መንገድ በኋላ ለስላሳ መስክ ይጠብቀናል፡፡ ከዐርበኞቹ ተጋድሎ በኋላ ያገኘነውን ነጻነት ለማስታወስ ነው፡፡ 
 
ምሽጉ ከውጭ ሲታይ
ዩኒቨርሲቲው በቀጣይነት እቴጌ ጣይቱ በብልሃት ያስያዙትን ታሪካዊውን የማይ አንሽቲ ምንጭ ታሪካዊነቱን ጠብቆ አገልግሎቱን እንዲቀጥል ለማድረግ መወሰኑን በዕለቱ ገልጧል፡፡
ታሪካዊ ቅርሶች ጠባቂና ተከባካቢ ካላገኙ ወደ ተረትነት መቀየራቸው የማይቀር ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ‹ዩኒቨርሳል› ነገሮችን ከማጉላት ይልቅ ‹መንደራዊ› ነገሮችን ወደ ማቀንቀን ከሚወርዱ እንዲህ ያሉ ሥራዎችን በመሥራት ታሪክ ዐውቆ፣ ታሪክንም ጠብቆ፣ ታሪክ የሚሠራ ትውልድ እንዲያፈሩ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ችቦውን ከፍ አድርጎታል፡፡ 

16 comments:

 1. ታሪካዊ ቅርሶች ጠባቂና ተከባካቢ ካላገኙ ወደ ተረትነት መቀየራቸው የማይቀር ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ‹ዩኒቨርሳል› ነገሮችን ከማጉላት ይልቅ ‹መንደራዊ› ነገሮችን ወደ ማቀንቀን ከሚወርዱ እንዲህ ያሉ ሥራዎችን በመሥራት ታሪክ ዐውቆ፣ ታሪክንም ጠብቆ፣ ታሪክ የሚሠራ ትውልድ እንዲያፈሩ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ችቦውን ከፍ አድርጎታል፡፡

  ReplyDelete
 2. እቴጌ ጣይቱ ታሪኩን ለመሥራት ሳይከብዳቸው ለ121ኛው የዐድዋ ድል በዓል አከባበር አድዋ ላይ የተገኙት ‹አርቲስቶች› ስማቸውን ማንሣት ከበዳቸው፡፡ ‹ኢትዮጵያውያን በፈጠሩት ዘዴ› ብለው ያለፉት ይህንን የጣልያን መዛግብት ሳይቀሩ በድንቅ የሚያነሡትን የእቴጌ ጣይቱን ታላቅ ጥበብ ነው፡፡ ዐድዋን እያከበሩ ምኒሊክንና ጣይቱን አለማንሣት ማለት አሜሪካን ከመከፋፈል ታድጎ ወደ አንድነት ያመጣትን ‹የአሜሪካ የርስበርስ ጦርነት› የሚባለውን ዘመቻ ታሪክ አንሥቶ አብርሃም ሊንከንን መዝለል ማለት ነው፡፡ የዶጋሊን ድል አንሥቶ ዐሉላ አባ ነጋን መዘንጋት፣ የሕወሐትን የመቀሌ እሥር ቤት ሰበራን ታሪክ አንሥቶ ኃየሎም አርአያን መተው ማለት ነው፡፡ በዐድዋው በዓል ላይ የዐፄ ምሊክ ስም ያነሡት ሁለት ተናጋሪዎች ብቻ ነበሩ፡፡ የደቡብ አፍሪካው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ታቦ ኢምቤኪና የጉዞ አድዋ አስተባባሪ ያሬድ ሹመቴ፡፡ ለእናንተ ኮፍያችንን በክብር እናነሣለን፡፡

  ReplyDelete
 3. Dani bexam enameseginalen tariku be migeba sila kafelken le Dr. Kindeyim misgana yigebachewale ,la yarede ena le adwa teguazochim hullachihunem enameseginalen ye tarike ambasaderochachine nachihu bezaw mexen yalebunen chigeroch befexenete enefetachew adwa sinesa etege xayitu ena emiye minilek mersate yelebachewum bayi nenye

  ReplyDelete
 4. Endeme ena Tena kememegnet lela min elalehu,ke kalat belay Egizeabher yisitih

  gizax

  ReplyDelete
 5. እግዚአብሔር ይስጥልን! ቆንጆ ቁምነገር ነው፡፡ ታሪክን ትውልድ ይጠብቀዋል፡፡ ለታሪክ የሚቆረቆር ባለታሪክ ትውልድ ያስፈልጋልና! ዶ/ር ክንደያ ክብር ይግባቸው! የ1888 የአድዋ ድላችን የማንነታችን መገለጫ ሆኖ ሳለ ታሪክን ለማንበብ እና ለማወቅ በሰነፉ የሚዲያ ሰዎች የታዛባ ሐሳብ መቅረቡን ነቅሶ ማሳየት ተገቢ ነው፡፡

  ReplyDelete
 6. እግዚአብሔር ይስጥልን! ቆንጆ ቁምነገር ነው፡፡ ታሪክን ትውልድ ይጠብቀዋል፡፡ ለታሪክ የሚቆረቆር ባለታሪክ ትውልድ ያስፈልጋልና! ዶ/ር ክንደያ ክብር ይግባቸው! የ1888 የአድዋ ድላችን የማንነታችን መገለጫ ሆኖ ሳለ ታሪክን ለማንበብ እና ለማወቅ በሰነፉ የሚዲያ ሰዎች የታዛባ ሐሳብ መቅረቡን ነቅሶ ማሳየት ተገቢ ነው፡፡

  ReplyDelete
 7. አይ ዲ/ን ዳኒዩ፡ ባለታሪኮቹን ስማቸውን ባለማንሳታቸው አትውቀሳቸው፡፡ የት ያውቋቸዋል ለመናገር እኮ እውቀት ይጠይቃል፡፡

  ReplyDelete
 8. ብዙዎቻችን እንደሚመስለን የኢትዮጵያ ጦር ወደ አድዋ ሲዘምት ኋላ ቀር መሣሪያ ብቻ አልያዘም፡፡ የኢትዮጵያን ጦር ለውጤት ያበቁት ጠንካራ የሀገር ፍቅር፣ ተገቢ የሆነ ዝግጅትና አደረጃጀት፣ የሁሉም ሕዝብ ሁለገብ ተሳትፎ፣ የዐፄ ምኒልክና የጦር ጄኔራሎቻቸው የአመራር ጥበብ፣ ከዚያ በፊት ከውጭ ወራሪዎች ጋር በተደረጉ ውጊያዎች የተቀሰሙ ልምዶች እና ትክክለኛ የጦርነት ምክንያት ናቸው፡፡

  ReplyDelete
 9. Daniel GOD might keep you in the heaven. You are the only person that may teach our historian,scholars, and unjustic and corrupted gov'tal authorities.

  ReplyDelete
 10. የሚሰሙ ጆሮዎች እና የሚያዳምጡ ልቦች ቢኖሩን ሁሌ ታሪክ ከመዘከር አልፈን ዳግም ታሪክ እንሰራ ነበር፡፡ ለዛሬ መኖራችን የኋሎቻችንን ማሰብ አለብን፡፡

  ReplyDelete
 11. የሚሰሙ ጆሮዎች እና የሚያዳምጡ ልቦቸ ቢኖሩን ሁሌ ታሪክ ከመዘከር አልፈን ዳግም ታሪክ እንሰራ ነበር፡፡ ለዛሬ መኖራችን የኋሎቻችንን ማሰብ አለብን፡፡

  ReplyDelete
 12. Guys, this was excellent event and I really all those participated in the event and the University. I managed the presentation sessions and everything was more than what we all are commenting

  ReplyDelete
 13. በጣም ጥሩ እይታ ነው::

  ReplyDelete
 14. በጣም ጥሩ እይታ ነው::

  ReplyDelete