Monday, February 6, 2017

እዝራ በእዝራ መንፈስ


በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ገጥመውን ከነበሩት ፈተናዎች አንዱ የሚያውቁት አለመጻፋቸውና የሚጽፉት አለማወቃቸው ነው፡፡ ባሕረ ጥበባት የተባሉት ሊቃውንት ትምህርታቸውን በቃል ከማስተማር ባለፈ በጽሑፍ አስቀምጠው ለማለፍ ብዙም አልተጉበትም፡፡ በዚህ የተነሣም በድርሰቱ ዓለም የምንጠቅሳቸውን ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትን አንድ ሁለት ብለን በጣቶቻችን ለመቁጠር እንችላለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሥነ ጽሐፈቱን የተማሩት ፊደላውያን ወደ ሊቅነቱ ባሕር አልገቡም፡፡ በዚህ የተነሣ ገልባጮች ወይም ቃል ጸሐፊዎች ፊደል እያደባለቁ፣ እየጎረዱና እየለወጡ አልፈዋል፡፡ አንድን ድርሳን ለማወቅም ልዩ ልዩ ቅጅዎችን እንድናመሳክር ግዴታ ጥለውብናል፡፡ ለዚህ ነው ‹የሚያውቁት ሳይጽፉ፣ የሚጽፉት ሳያውቁ አለፉ› እየተባለ የሚነገረው፡፡

ይህንን ቀንበር እየሰበሩ እንደነ ቅዱስ ያሬድ፣ እንደነ አባ ጊዮርጊስ፣ እንደነ ርቱዐ ሃይማኖት፣ እንደነ አርከ ሥሉስ፣ እንደነ አባ ባሕርይ፣ እንደነ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ፣ እንደነ አባ ስብሐት ለአብ፣ እንደነ እጨጌ ዕንባቆም ያሉት የድርሰት ትሩፋት አቆይተውናል፡፡ በዘመናችንም ቢሆን እነ አቡነ ጎርጎርዮስን፣ እነ አቡነ መቃርዮስን፣ እነ አቡነ ጴጥሮስን፣ እነ መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬን፣ እነ አለቃ አያሌው ታምሩን፣ እነ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራን፣ እነ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየን፣ ወዘተ. እንጠቅስ እንደሆነ እንጂ ዝርዝሩ ሆድ አይሞላም፡፡ በድርሰቱ የምናስታውሰው ጳጳስ ከፈለግንማ ከጎርጎርዮስ አንዘልም፡፡ ወደ ሊቃውንቱ ስንገባም ከላይ ካነሣናቸው በቀር ሊቅነታቸው የሚመጥን ሥራ የሠሩትን ለማስታወስ ዳገት ይሆንብናል፡፡
የሊቀ ሊቃውንት እዝራ መንገድ በዚህ ረገድ ቀና እንድንል ከሚያደርጉን ወገን ነው፡፡ በጎንደር መድኃኔዓለም ደብር የሚያስተምሩትና የሚያስተዳድሩት የአራቱ ጉባኤያት ሊቅ ሊቀ ሊቃውንት እዝራ በቃል ከማስተማር ጎን ለጎን የሚያስተምሩትን ጽፈው እያሳተሙልን ነው፡፡ የርሳቸው መንገድ ከዘመነኞቻቸው ለየት የሚለው ሥራዬ ብለው ኅትመትን መሥራታቸውና ማከታተላቸው ነው፡፡ እርሳቸው ራሳቸው በሚያስተምሩት የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ ላይ እንደሚለው ወንጌላቱና መልእክታቱ የተጻፉት ደቀ መዛሙርት ‹በቃል ያለ ይረሳል፣ በጽሑፍ ያለ ይታወሳልና ጽፈሕ ስጠን› ብለው መምህራቸውን በመጠየቃቸው ነው፡፡ እርሳቸውም የሚያስተምሩትን ተከትለው ታላላቆቹን አብነት የሚሆኑ ድርሳናት በትርጓሜያቸው እያሳተሙ ይገኛሉ፡፡
·         ትርጓሜ ትንቢተ ኢሳይያስ  
·         ሃይማኖተ አበው ትርጓሜ
·         ድርሳነ ቄርሎስ
·         ጰላድዮስ
·         ተረፈ ቄርሎስ
·         መልክአ ሠለስቱ ምእት
የሚባሉትን መጻሕፍት በሊቅ ትርጓሜ ጽፈው አሳትመዋል፡፡
‹ሁሉም ሰው ትምህርት ቤት አይገባም፡፡ ሁሉም ትምህርት ቤት ቢገባም ሁሉም አንድ ዓይነት ትምህርት ቤት አይገባም፡፡ ሁሉም አንድ ዓይነት ትምህርት ቤት ቢገባም ሁሉም አንድ ዓይነት ትምህርት አይማርም፡፡ ሁሉም አንድ ዓይነት ትምህርት ቢማር እንኳን ሁሉም እኩል አይረዳውም› ይባላል፡፡ መጻሕፍት የሚያስፈልጉት ለዚህ ነው፡፡ከየሊቁ ዕውቀት ለመሰብሰብ፡፡ ከቅርስነታቸው ባሻገር፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከ200 ሺ በላይ የብራና መጻሕፍት ያሏት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለብዙዎቹ ደግሞ በቋንቋም፣ በቦታ ርቀትም ምክንያት ባዕድ ነን፡፡ እንዲህ እንደ ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ዓይነት ሊቃውንት ሲገኙ ግን ክፍተቱን በዕውቀትና በኅትመት ይሞሉልናል፡፡ ጎንደር ሳንሄድ ጉባኤ እንውላለን፡፡
ሊቀ ሊቃውን እዝራ ከሃይማኖተ አበው ትርጓሜ መጽሐፍ በኋላ ‹ድርሳነ ቄርሎስ ወጰላድዮስ ምስለ ተረፈ ቄርሎስ› የተሰኘ ባለ 833 ገጽ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ በአብነቱ መንገድ ለዕውቀት ፈላጊው ማኅበረሰብ ያበረከቱት ይህ አበርክቶ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ደቀ መዝሙር የተማረውን ያጠናበታል፤ ዕውቀት ፈላጊ ይመሰጥበታል፤ አጥኝ የሊቃውንቱን ትምህርት ይፈትሽበታል፡፡
እንደነዚህ ዓይነት ሊቃውንት ሲገኙ ማኅበረሰቡ ማበርታት አለበት፡፡ በሐሳባቸው ብንስማማም ባንስማማም ነባሩ ዕውቀት እንዳይጠፋ፣ ቅሩብ እንዲሆንና እንዲዳረስ የሚደረገውን ሥራ መደገፍ አለብን፡፡ እንዲጽፉ ማትጋት፣ ሲጽፉ ኅትመቱን መደገፍ፣ ሲያሳትሙ መግዛት፡፡ ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለአብያተ መጻሕፍት፣ ለአብነት ትምህርት ቤቶችና ለዕውቀት ማዕከላት ጭምር፡፡ ዕውቀት ማለት የምፈልገውና የምንስማማበት ብቻ አይደለምና፡፡ ሊቁ ሲሞት ‹ድጓ ተሸክሞ መጣልህ መምህር› እያልን ማልቀሱ ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ የሚያውቀውን ጽፎ፣ ለትውልድም አትርፎ እንዲሄድ ማበርታትና መርዳትም ይገባል እንጂ፡፡
ሊቀ ሊቃውንት እዝራ፣ በእዝራ ሱቱኤል መንፈስ ይቀጥሉ፤ እንዳይቆሙ፡፡      

9 comments:

 1. መልካም ሀሳብ ነዉ
  ዕድሜ ይስጥልን፡፡
  ግዜክስ

  ReplyDelete
 2. You are correct. We all have a responsibility. I wonder if these books available abroad. Thank you for idea. God be with you

  ReplyDelete
 3. Yes, but not only to have a book rather...
  "Behold, as the eyes of servants look unto the hand of their masters, and as the eyes of a maiden unto the hand of her mistress; so our eyes wait upon the Lord our God, until that he have mercy upon us."

  ReplyDelete
 4. Thank you!God bless you

  ReplyDelete
 5. AWOE YEMITSFU EJOCHIN YABIZALEN,YIHCH HAGER GENA BIZU MISTIR ALAT EDMIE YISTEN ENJI GENA BIZU ENAYALEN,Dn. danie God bless you!

  ReplyDelete
 6. ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንዴት አለህልኝ? ሰላምህን ፈጣሪ ያብዛልህ፡፡ እጅግ እናመሰግናለን፡፡ ሌላ ምን እንላለን፡፡ ልክ እንደ ባሮክና እንደ ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ "ኦ እግዚኦ ኢታርእየነ ሙስናሃ ለኢትዮጵያ" ማለት ብቻ እንጅ፡፡ ግራ የሚገባ ነገር ነው፡፡

  ReplyDelete