Monday, February 13, 2017

ነፍሰ ጡሮች በኮርያ

 
በኮርያ የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ስትጓዙ ፒንክ ቀለም ያላቸውና በእንግሊዝኛ ‹ፒ› የሚል ፊደል የተጻፈባቸውን መቀመጫዎች ታገኛላችሁ፡፡ የነዚህ መቀመጫዎች ዓላማ ነፍሰ ጡር ሴቶች ያለ ችግር ወንበር እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ እንዲያውም በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን የተጀመረ ፕሮጀክትም አላቸው፡፡ ነፍሰ ጡር ሴቶች ከብሉ ቱዝ ጋር የሚሠራ ነገር ይሰጣቸውና ወደ አውቶቡሱ ወይም ባቡሩ ሲገቡ በመቀመጫው አካባቢ ያለው ደወል ይጮኻል፡፡ ያን ጊዜ በነፍሰ ጡሮች ወንበር ላይ ተቀምጦ የነበረው ሰው ይነሣል፡፡
ይህንን ስመለከት የሀገሬ እናቶች ናቸው የታወሱኝ፡፡ በባቡሩ ውስጥ መጨናነቅ፣ በአውቶቡሱ ውስጥ መቆም፣ በታክሲው ወረፋና ግፊያ መከራ የሚያዩት ነፍሰ ጡሮች፡፡ ቀላል ባቡሩ በሥራ መውጫና መግቢያ ሰዓት ጨው እንደጫነ መኪና ይሞላል፡፡ በዚያ ነፋስ በማያሳልፍ ጭንቅንቅ ውስጥ እንኳን ነፍሰ ጡር ሴት የባቡሩም ሾፌር በመከራ ነው የሚደርሰው፡፡ አውቶቡሶቻችንም ቢሆኑ መስኮታቸውን ለመክፈት ሕዝቡ ብርድ የሚፈራባቸውና ሳንዱች በሚሠራ ሙቀት የተሞሉ ናቸው፡፡ የታክሲዎቻችን ሰልፍ እንኳን አይነሣ፡፡ ምንም እንኳን ለነፍሰ ጡር እናቶች ያለን ክብር ተንጠፍጥፎ ባያልቅም የሰልፉ ርዝመት ግን ለሌላ ቅድሚያ የሚያሰጥ አልሆነም፡፡ 

በዚህ ሁሉ መካከል የሚሰቃዩት ነፍሰ ጡር እናቶች ናቸው፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎቶቻችን እንደኮርያውያን አላስታወሷቸውም፡፡ ቅብጠት ነው ብለው ትተዋቸውም ይሆናል፡፡ ‹ምንም ብቀጥን ጠጅ ነኝ› ይላልና የሀገሬ ሰው ምንም እንኳ የተብቃቃና የዘመነ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ባይኖረንም ባለን ዐቅም ላይ ሕግና ደግነት መጨመር ግን አያቅተንም፡፡ እነዚህ ነገሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጀመሩ አስቸጋሪ፣ ውስብስብና ለአፈጻጸም የማይመቹ ይመስላሉ፡፡ አጥብቀን ሥርዓቱንና ሕጉን ካስፈጸምነው ግን እየቆየ ባሕል ይሆናል፡፡
በታክሲዎቻችን ቢያንስ አንድ፣ በባቡሮቻችን ቢያንስ አራት፣ በአውቶቡሶቻችን ደግሞ ቢያንስ ሦስት ወንበሮችን ለነፍሰ ጡር እናቶች ለይተን ብናዘጋጃቸው፡፡ ልዩ የቀለም ምልክት ተሰጥቶ በላያቸው ላይ ብንጽፍባቸው፡፡ የእነዚህ ወንበሮች ዓላማ ነፍሰ ጡሮችን ብቻ መጠበቅ ሳይሆን ቅድሚያ ለነፍሰ ጡር እናቶች መስጠት ነው፡፡ እነርሱ በማይኖሩበት ጊዜ ሌሎች ተሳፋሪዎች ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ፡፡ የሚዘጋጀው ወንበር አየር በመስኮት ለማስገባት ምቹ በሆነበት አቅጣጫና ለመውረድና ለመውጣት በማያስቸግራቸው አካባቢ ቢሆን ደግሞ ይመረጣል፡፡
ከታክሲ ባለቤቶች፣ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ጋር ብንመክርበት ደግሞ ሐሳቡ ከውጤት በላይ ይሄዳል፡፡ መቼም እናቱን የማይወድ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ በርግጥ በእናቱ የሚሳደብ ባይጠፋም፡፡ በፍቅር ላይ ዕውቀት ሲጨመርበት ደግሞ ነገሩን የሠመረ ያደርገዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በታክሲ ፌርማታዎች ላይ ተራ የሚያስከብሩ ወገኖቻችን ሐሳቡን ‹ለእናቴ የማደርገው ነው› ብለው እንዲቀበሉት ከተደረገ እናቶቻችን ሰልፍ ይቀንስላቸዋል፤ ግፊያም ይቀርላቸዋል፡፡ ወንበር መስጠት ቢያቅተን ቆመው ከሚንቃቁ ድንጋይ ላይም ቢሆን ተቀምጠው ይጠብቃሉ፡፡ የትራፊክ ፖሊሶችና ሌሎች የፖሊስ አካላት ነገሩን ማስፈጸም አንዲችሉ ሐሳቡን ሕግ ሊደግፈው ይገባል፡፡ ያን ጊዜ እምቢ የሚለውን ጋጠ ወጥ ከእርግማን ባለፈ ሕግ ፊት ለማቅረብም ይቻላል፡፡
ወደ ክፍለ ሀገር በሚያመሩ አውቶቡሶች ላይ ይህን ብናደርግ ከአዲስ አበባ ይልቅ በክፍለ ሀገር የሚኖሩ እናቶችን እንጠቅማቸዋለን፡፡ በይበልጥም የአውቶቡስ መነሻ ባልሆኑ ትናንሽ ከተሞች ጎዳና ላይ ወጥተው አውቶቡስ እንዲጭናቸው እጃቸውን እያርገበገቡ የሚለምኑ ነፍሰ ጡር እናቶች የተሻለ ዕድል ያገኛሉ፡፡ እኛም ተሳፍረን የምንጓዘው ወዳጆቻቸው መብታቸውን ለማስከበር የሚያስችል የሕግ ዐቅም እናገኛለን፡፡
በተለመደው አሠራራችን ለሽማግሌዎች፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለእናቶች ቅድሚያ የመስጠት ባህል ያለን ይመስለናል፡፡ እነዚህ ነገሮች ግን በሕግ ካልተደገፉና ያልተከበረላቸው ለማስከበር፣ ያላከበሩ ለመቀጣት ካልቻሉ በሂደት መጥፋታቸው የማይቀር ነው፡፡አሁንም የምናየው ይህንን ነው፡፡ በብዙ ሀገሮች የሕግ አንቀጽ ተጠቅሶ ለእነዚህ አካላት ቅድሚያ እንዲሰጥ በግልጽ በአደባባይ ይጻፋል፡፡ አስፈላጊ ሲሆንም ልዩ መታወቂያ ይሰጣቸዋል፡፡ በመኪናቸው ላይ የሚለጠፍ ስቲከርም አላቸው፡፡ በዚህ ምክንያት የእነዚህ አካላት መብት እንዲከበር የሚሹ አጋሮች አብረዋቸው መብታቸውን ለማስከበር ይችላሉ፡፡ ሕግ የሚያስከብሩ አካላትም ሕግ ነውና በግድ እንዲከበር ለማድረግ ዐቅም ይሰጣቸዋል፡፡
እንደ ኮርያውያን ለሕጉ የማስፈጸሚያ አሠራር ስናበጅለት ደግሞ ሸጋ ይሆናል፡፡ እነርሱ ለነፍሰ ጡር እናቶች የሚሰጠውን ቦታ ቀለሙን ለይተው ብቻ ሳይሆን ነፍሰ ጡር ሴት እየመጣች መሆኑን የሚናገር የቴክኖሎጂ ሥርዓትም ዘርግተውለታል፡፡ እዚያ እስክንደርስ ድረስ እጃችን ባለው ነገር መጀመር እንችላለን፡፡
በተለይ ግን የአዲስ አበባ ታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶች እናንተው ራሳችሁ ተነጋግራችሁ በመወሰንና ተግባራዊ በማድረግ ለእናቶቻችሁ ያላችሁን ክብርና ፍቅር ማሳያ ብታደርጉት ሞገስ ይጨምርላችኋል፡፡

8 comments:

 1. በተለይ ግን የአዲስ አበባ ታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶች እናንተው ራሳችሁ ተነጋግራችሁ በመወሰንና ተግባራዊ በማድረግ ለእናቶቻችሁ ያላችሁን ክብርና ፍቅር ማሳያ ብታደርጉት ሞገስ ይጨምርላችኋል፡፡

  ReplyDelete
 2. work yehonk sewuye edewu min ladirgh!!! amlak erejim edme yistih!!!

  ReplyDelete
 3. thank you so much Dn.Daneal,It is 100%true.I even saw it. in India also there are good experience that we can share on transportation specially for senior citizens, children and ladies the bus gives priority.

  ReplyDelete
 4. አይ ዳኒ ዘንድሮ እኮ ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ የሚባልበት ጊዜ ላይ ነን እንኳን ወንበር ሊሰጡህ ወረፋ ላያስጠብቁህ እርጉዝ ሴትንና ልጅ የያዘችን ሴት አንዳንዴም አረጋውያንን መጫን በፍፁም አይፈልጉም ለምን እንደሆነ ታውቃለህ ትርፍ ለመጫን አይመቸንም የሚል ራስ ወዳድ የሆነ አስተሳሰብ የሰፈነበት ጊዜ ላይ ነን ይህን ስል ግን እንደ ቤተሰብ ተንከባክቦ እተፈለገበት ቦታ ድረስ ጨዋነትን ከነ ሙሉ ክብሩ አሟልተው የሚያገለግሉ እንዳሉም ለመግለፅ እፈልጋለሁ ለማንኛውም አንተ ይህን በማለትህ እንድሜና ጤና ይስጥልን እያልኩ የነበረንን መልካምነት እንደያዝን ብንቀጥል ነገን የተሻለ ማድረግ እንችላለን እላለሁ፡፡

  ReplyDelete
 5. አሁን ህብረተሰቡ በራሱ አቅም የጀመረው የመረዳዳት መንፈስ እጅግ የሚያስመሰግን ነው፡፡ በተለይም የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ትብብር ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም ስለሆነም የተጀመረው ሥራ የሚቀጥልበት እንዲሁም የመረዳዳት መንፈስን የሚያጎለብቱ የማህበራዊ ሙከራ ሥራ (Social Experiment) እየተከናወነ ለሚቀጥለው ተውልድ የአባቶች፣ የእናቶች፣ የአካል ጉዳተኞች እና ወገኖቻችን ክብር የምንሰጥበትና የምንረዳበት የለውጥ ሥራዎች ተበራክተውና ተጠናክረው መሰራት አለባቸው እላለው፡፡ ለዚህ ጉዳይ በርካታ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት አሉ፡፡

  ReplyDelete
 6. thank you very much, dear Dn. Daneil ki. this is very interesting and relevant advice specially for this generation youth and for me too.

  ReplyDelete