Friday, February 17, 2017

ፓንክረስት ሞተ ይላሉ


ፓንክረስት ሞተ ይላሉ
አያፍሩም ደግሞ ይዋሻሉ፤
ታሪክን እንደነዳጅ ቆፍሮ
ለቅርስ እንደ ውርስ ተከራክሮ
ላልተወለደባት ምድር ከተወላጅ በላይ ለፍቶ
በደም ከወረሷት በላይ በፍቅር ልቧ ውስጥ ገብቶ
ከእናቱ እስከ ልጁ - ለጦቢያ ልቡን ሠውቶ
በትውልድ ማማ ላይ ቆሞ የጸናውን ጌታ
ሞቷል እያለ ይዋሻል ታሪክ የጠላ ቱማታ፡፡
ኢትዮጵያዊነት ቅኔ ነው
ብርቱ እንደ ፓንክረስት የሚነጥቀው
ሞኝ እንደ ከመዳፉ የሚቀማው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ጸጋ ነው
ልባም እንደ ዐሉላ የሚቀባው
ሞኝ እንደ ባንዳ የሚነሣው፤
ስንቱ ከማዕዘናተ ዓለም
እንደ ኦሎምፒክ ከትሞባት
ባተወለደባት ምድር
እትብቱን አምጥቶ ሲቀብርባት
ከደጁ ሞፈር ሲቆረጥ
ጅላጅል ቆሞ አንጎላጀ
ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ
ሐበሻ ሳይሆን አረጀ፡፡
እንዲህ ያለው ልብ አልባ
ልባሙን ሞተ ይለዋል
በትውልድ ማማ ላይ ያለ
መቼ ልብ ሰጥቶ ይሰማዋል፡፡
ፓንክረስትማ አልሞተም
በኢትዮጵያ ልብ ይኖራል
በዐጸደ ነፍስ ሆኖ
ጠላቷ ፍግም ሲል ያያል፡፡
የካቲት 10 ቀን 2009 ዓም

Monday, February 13, 2017

ነፍሰ ጡሮች በኮርያ

 
በኮርያ የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ስትጓዙ ፒንክ ቀለም ያላቸውና በእንግሊዝኛ ‹ፒ› የሚል ፊደል የተጻፈባቸውን መቀመጫዎች ታገኛላችሁ፡፡ የነዚህ መቀመጫዎች ዓላማ ነፍሰ ጡር ሴቶች ያለ ችግር ወንበር እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ እንዲያውም በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን የተጀመረ ፕሮጀክትም አላቸው፡፡ ነፍሰ ጡር ሴቶች ከብሉ ቱዝ ጋር የሚሠራ ነገር ይሰጣቸውና ወደ አውቶቡሱ ወይም ባቡሩ ሲገቡ በመቀመጫው አካባቢ ያለው ደወል ይጮኻል፡፡ ያን ጊዜ በነፍሰ ጡሮች ወንበር ላይ ተቀምጦ የነበረው ሰው ይነሣል፡፡
ይህንን ስመለከት የሀገሬ እናቶች ናቸው የታወሱኝ፡፡ በባቡሩ ውስጥ መጨናነቅ፣ በአውቶቡሱ ውስጥ መቆም፣ በታክሲው ወረፋና ግፊያ መከራ የሚያዩት ነፍሰ ጡሮች፡፡ ቀላል ባቡሩ በሥራ መውጫና መግቢያ ሰዓት ጨው እንደጫነ መኪና ይሞላል፡፡ በዚያ ነፋስ በማያሳልፍ ጭንቅንቅ ውስጥ እንኳን ነፍሰ ጡር ሴት የባቡሩም ሾፌር በመከራ ነው የሚደርሰው፡፡ አውቶቡሶቻችንም ቢሆኑ መስኮታቸውን ለመክፈት ሕዝቡ ብርድ የሚፈራባቸውና ሳንዱች በሚሠራ ሙቀት የተሞሉ ናቸው፡፡ የታክሲዎቻችን ሰልፍ እንኳን አይነሣ፡፡ ምንም እንኳን ለነፍሰ ጡር እናቶች ያለን ክብር ተንጠፍጥፎ ባያልቅም የሰልፉ ርዝመት ግን ለሌላ ቅድሚያ የሚያሰጥ አልሆነም፡፡ 

Monday, February 6, 2017

እዝራ በእዝራ መንፈስ


በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ገጥመውን ከነበሩት ፈተናዎች አንዱ የሚያውቁት አለመጻፋቸውና የሚጽፉት አለማወቃቸው ነው፡፡ ባሕረ ጥበባት የተባሉት ሊቃውንት ትምህርታቸውን በቃል ከማስተማር ባለፈ በጽሑፍ አስቀምጠው ለማለፍ ብዙም አልተጉበትም፡፡ በዚህ የተነሣም በድርሰቱ ዓለም የምንጠቅሳቸውን ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትን አንድ ሁለት ብለን በጣቶቻችን ለመቁጠር እንችላለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሥነ ጽሐፈቱን የተማሩት ፊደላውያን ወደ ሊቅነቱ ባሕር አልገቡም፡፡ በዚህ የተነሣ ገልባጮች ወይም ቃል ጸሐፊዎች ፊደል እያደባለቁ፣ እየጎረዱና እየለወጡ አልፈዋል፡፡ አንድን ድርሳን ለማወቅም ልዩ ልዩ ቅጅዎችን እንድናመሳክር ግዴታ ጥለውብናል፡፡ ለዚህ ነው ‹የሚያውቁት ሳይጽፉ፣ የሚጽፉት ሳያውቁ አለፉ› እየተባለ የሚነገረው፡፡

ለሊዮ ቶሎይስቶይ የተጻፈ ደብዳቤ (እውነተኛ የሰሙኑ ገጠመኝ)


click here for pdf
አንድ ወዳጄ ከሳምንታት በፊት አንድ ቴአትር ይጽፍና በአዲስ አበባ ከተማ ካሉት ቴአትር ቤቶች ወደ አንዱ ይሄዳል፡፡ ድርሰቱን ለግምገማ እንዲያስገባ ይነገረዋል፡፡ አስገባ፡፡ በቀደም ዕለት የግምገማውን ውጤት ለማየት ወደ ቤተ ተውኔቱ ያመራል፡፡ መዝገብ ቤቶቹም ‹የግምገማው ውጤት ደርሷል፡፡ መታወቂያዎትን አሳይተው ፈርመው መውሰድ ይችላሉ› ይሉታል፡፡ ከደረት ኪሱ መዥለጥ አድርጎ መታወቂያውን ሰጣቸው፡፡ የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ መታወቂያውንና ደብዳቤውን አስተያየና ‹እርስዎ መውሰድ አይችሉም፤ መውሰድ የሚችለው ደራሲው ነው› ይሉታል፡፡ እርሱም ደረቱን ነፍቶ ‹የድርሰቱ ባለቤት እኔ ነኝና ልውሰድ› ይላል፡፡ መዝገብ ቤቶቹም ‹እዚህ ላይ የተጻፈው ግን የእርስዎ ስም ሳይሆን የደራሲው ስም ነው› ይሉታል፡፡ ግራ ገባው፡፡ እዚህ ቴአትር ቤት ይህንኑ ድርሰት ይዞ የመጣ ሌላ ደራሲ ይኖር ይሆን? ብሎ አሰበ፡፡ የትርጉም ሥራዎች አንዱ ችግር ይህ ነው፡፡ የተለያዩ ሰዎች አንድን ሥራ ያውም በተመሳሳይ ጊዜ ተርጉመው ሊያቀርቡት ይችላሉ፡፡
‹የተጻፈውን ደብዳቤ ማየት እችላለሁ› ይላል ወዳጄ የተጻፈለትን ሰው ስም ለማየት ጓጉቶ፡፡
‹መውሰድ አይችሉም እንጂ ማየትስ ይችላሉ› አለው የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ፡፡
ወዳጄ ወደ ማኅደሩ አንገቱን ልኮ ሲመለከተው ግን ክው ብሎ ነበር የቀረው፡፡

Wednesday, February 1, 2017

የቹንቾን ሐውልታችን


የቃኘው ሻለቃ መሥዋዕትነት መታሰቢያ ሐውልት

ዛሬ ከሴኡል ከተማ 75 ኪሎ ሜትር ርቀን ቹንቾን(Chuncheon) ወደምትባል የኮርያ ከተማ እንጓዛለን፡፡ በታሪክ ላይ በእግራችን ለመራመድ፡፡ በበረዶ በተሸፈኑት የኮርያ ተራሮች መካከል እያለፍን በኮርያ የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት ጸጥ ባለው ጎዳና ላይ እንበራለን፡፡ ዛፎቹ ቅጠሎቻቸውን ሸኝተው ግንዶች ብቻቸውን የብርዱን ወቅት ሊጋፈጡት ቆርጠዋል፡፡ መሬቱ ነጭ ሥጋጃ ለብሷል፡፡ ደግነቱ ጎዳናው እንደ ካናዳና አሜሪካ በረዶ አልለበሰም፡፡