Monday, January 30, 2017

ቃኘው ሻለቃ - የሚፍግ እሳት፣ የማይጠፋ ፋና
የቃኘው አባላት በኮርያ

አሁን ከሴኦል ወደ ቹንቾን ከተማ እየተጓዝን ነው፡፡ በትዝታ ደግሞ ወደ ኋላ እንሄዳለን፡፡ እኤአ በሰኔ 1951 ዓም  የቃኘው ሻለቃ የመጀመሪያዎቹ ወታደሮች ከዚያ በፊት ኢትዮጵያውያን እምብዛም ስሙን ሰምተውት ወደማያውቁት የሩቅ ምሥራቅ ሀገር ተንቀሳቀሱ፡፡ በሰኔ ወር 1950 እኤአ የተጫረው የኮርያ ልሳነ ምድር ጦርነት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የመጀመሪያው ጦርነት ነበር፡፡ የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ኤል ሱንግ ደቡብ ኮርያን በመውረር የኮርያን ልሳነ ምድር አንድ የማድረግ ሕልሙን ሰሜን ኮርያ በነበረው የሶቪየት አምባሳደር በኩል ከፕሬዚዳንት ስታሊን ጋር መከረበት፡፡ በጉዳዩ የተስማማው ስታሊንና የታላቋ ቻይና መሪ የነበረው ማኦ ሴቱንግ ለኪም ኤል ሱንግ ቀኝ እጃቸውን ሰጡት፡፡ ሰሜን ኮርያም በሶቪየትና ቻይና እየተረዳች ደቡብ ኮርያን ወረረች፡፡
 
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በጁን 26 ቀን 1950 ዓም ባደረገው ስብሰባጠብ ጫሪነቱ በአስቸኳይ እንዲቆምወሰነ፡፡ ሰሜን ኮርያ ግን ውሳኔውን ቸል በማለት ወረራዋን ቀጠለችበት፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤትም ለዓለም ሰላም ሲባል ወረራው እንዲቀለበስ ወሰነ፡፡ በዚህም መሠረት ውሳኔውን የደገፉ አሥራ ስድስት ሀገሮች ወታደሮቻቸውን ለመላክ ወሰኑ፡፡ ከነዚህ አንዷ ሀገራችን ኢትዮጵያ ነበረች፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የቃኘው ሻለቃን ዝግጅት ሲመለከቱ
በነሐሴ 1948 ዓም ከዐሥር መድፈኛ ሻለቆች የተውጣጣ አንድ ሻለቃ ተመሠረተ፡፡ ስሙም ቃኘው ሻለቃ ተባለ፡፡ በእንግሊዝ አሠልጣኞች ጥብቅ የሆነ ሥልጠና ለስምንት ወራት ወሰደ፡፡ በመጨረሻም ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ባሉበት የቃኘው ሻለቃ አባላት አፕሪል 13 ቀን 1951 (እኤአ) ችሎታቸውን በመስክ አሳዩ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱምእነሆ በጋራ ደኅንነት መርሕ መሠረት እጅግ ቅዱስ ለሆነው ለዓለም ሰላም ዘብ ልትቆሙ የዓለምን ግማሽ የሚሆን ጉዞ ትጓዛላችሁ፡፡  ሂዱና ወራሪዎችን ድል ንሱዋቸው፡፡ በኮርያ ልሳነ ምድርም ሕግና ሥርዓትን አስከብሩሲሉ ልባቸውን በወኔ ሞሉት፡፡ ንጉሡ ይህንን ሲሉ ለአምስት ዓመታት በጣልያን ወረራ ተጋድሎ የቆየችው ኢትዮጵያ የነበሯት ወታደሮችና መሣሪያዎች ራስዋን ለመጠበቅ እንኳን የሚያስችሉ  አልነበሩም፡፡ ሀገርን ከፈጣሪ በታች የሚጠብቃት የሀገር ፍቅር ያለው ሕዝብ ነው ብለው የሚያምት ኢትዮጵያውያን ግን የወረራን ጽዋ ያውቁታልና በነርሱ የደረሰ በደቡብ ኮርያ እንዳይደርስ ሲሉ በተመረቁ በማግሥቱ በጀግንነት ዘመቱ፡፡

ቃኘው ሻለቃ ኮርያ፣ ቡሳን የወደብ ከተማ ሲደርስ
1122 የቃኘው ሻለቃ አባላት በኮሎኔል ከበደ ገብሬ መሪነት የመለየት ናፍቆት፣ የመተማመንም ጀግንነት በተሞላው መንፈስ ከአዲስ አበባ ተሸኝተው በባቡር ወደ ጅቡቲ ተጓዙ፡፡ ከጅቡቲ ደግሞ ቡሳን ወደተባለችው የኮርያ የወደብ ከተማ በመርከብ አቀኑ፡፡ 21 ቀናት በውቅያኖስ ላይ ከተንሳፈፉ በኋላ በሜይ 6 ቀን 1951 እኤአ ኮርያ ደረሱ፡፡ የደቡብ ኮርያ ፕሬዚዳንት ሲንግ ማንም በደስታ ተቀበሏቸው፡፡ 
 

የኮርያ ፕሬዚዳንት ሲንግ ማን ሲቀበሏቸው - የቃኘው አባላት ከመርከብ ሲወርዱ
 ከጥቂት ቀናት በኋላም ቶንግና ተዛውረው ለስድስት ሳምንታት ያህል ከአሜሪካ የጦር መሣሪያዎችና ከኮሪያ መልክዐ ምድር ጋር የሚያስተዋውቅ ሥልጠና ወስደው 85 መኮንኖችና 1037 ወታደሮች ጁላይ 11 ቀን በሰባተኛው የአሜሪካ ዲቪዚዮን ሥር ተሰለፉ፡፡ የቃኘው ሻለቃ ገድልም በሩቅ ምሥራቅ ተጀመረ፡፡
ይቀጥላል፡፡
ደቡብ ኮርያ  - ሴኦል

No comments:

Post a Comment