Tuesday, January 31, 2017

ቃኘው ሻለቃ - የሚፍግ እሳት፣ የማይጠፋ ፋና - 2


እስከ 1956 እኤአ በኮርያ ምድር የቆዩት የቃኘው ሻለቃ አባላት ከአፍሪካ የሄዱ ብቸኛ ወታደሮች ነበሩ፡፡ የአፍሪካውያንን ጀግንነት የሚጠራጠሩትና የቀለም በሽታ ያልለቀቃቸው የአውሮፓና የአሜሪካ ወታደሮች ሊያሳዩዋቸው የሞከሩትን ንቀት በየግንባሩ በጀግንነት ባስመዘገቡት ገድል አፋቸውን አስይዘው የክብር ሰላምታ እንዲያቀርቡላቸው አድርገዋል፡፡ በኮርያ ምድር ከዘመቱ ምድቦች ሁሉ የተሰጣቸውን ሁሉንም ግዳጅ በድል የተወጡት የኢትዮጵያ ወታደሮች ብቻ ነበሩ፡፡ 238 ግዳጅ ተሰጥቷቸው ሁሉንም በድል ነበር የደመደሙት፡፡ ከዚህ በፊት ጥቁር ሰው አይተው የማያውቁት የሰሜን ኮርያ ወታደሮች የኢትዮጵያውያንን የድል በትር ሲቀምሱት ‹ልዩ ፍጡራን ናቸው› እስከማለት ደርሰው ነበር፡፡ እልከኞች ናቸው፡፡ መማረክን አይቀበሉም፡፡ ያለ ድል ለመመለስ ፈጽሞ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከፍ ብሎ ማየት የዘወትር ሕልማቸው ነው - ቃኘው ማለት ይህ ነው በቃ› እንግሊዛዊው የጦርነት ታሪክ ጸሐፊ ጆን ኬጋን፡፡ 


ከሁሉ አስደናቂ ሆነው የሚነገሩላቸው ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ የቃኘው ሻለቃ አባላት በጦርነት የተሠዉትን አባሎቻቸውን አስከሬን ለጠላት ጥለው አይሮጡም፡፡ ከላይ እንደ ሰዶም እሳት እየዘነበባቸው የጓዶቻቸውን ክቡር አስከሬን ተሸክመው ይወጣሉ፡፡ እንዲያውም አንድ የኢትዮጵያ ወታደር የቆሰለ ኮርያዊ ወታደርን እንደተሸከመ ተመትቶ ተሠውቷል፡፡ ዛሬም ኮርያውያን ለኢትዮጵያውያን ፍቅር እንደ ልዩ መግለጫ ያወሱታል፡፡ ጦርነቱ አብቅቶ የምርኮ ልውውጥ ሲደረግ ደቡብ ኮርያ 8343፣ አሜሪካ 4714፣ እንግሊዝ 977፣ ቱርክ 244፣ አውስትራልያ 26፣ ካናዳ 33፣ ፈረንሳይ 12፣ ግሪክ 3፣ ኮሎምቢያ 28፣ ታይላንድ 5፣ ኔዘርላንድ 3፣ ቤልጅየም 1፣ ፊሊፒንስ 97፣ ደቡብ አፍሪካ 9፣ ኒውዚላንድ 1፣ ኖርዌይ 3 ምርኮኛ ሲመለስላቸው ኢትዮጵያ ግን አንድም ሰው ያልተማረከባት ብቸኛ ሀገር ነበረች፡፡
የኮርያ ጦርነት እኤአ ጁላይ 27 ቀን 1953 ዓም ጦርነትን በማቆም ስምምነት ተጠናቀቀ፡፡ በቻይናና ሶቪየት ኅብረት በምትረዳው ሰሜን ኮርያና በአሜሪካና በሌሎች 15 ሀገሮች በተደገፈችው ደቡብ ኮርያ መካከል ድንበር ተሠመረ፡፡ ከድንበሩ ወደ ሰሜንና ደቡብ ሁለት ሁለት ኪሎ ሜትር ገብቶ 250 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ከወታደር ነጻ የሆነ ቀጣና (Demilitarized Zone – DMZ) ተመሠረተ፡፡ በዚህ ቀጣና ውስጥ የቃኘው ሻለቃ አባላት እልህ አስጨራሽ ውጊያ አድርገውበታል፡፡ የድል ጽዋንም ተጎንጭተውበታል፡፡ ግን ምን ያደርጋል ጦርነት አስቀያሚ ነውና አንድ ሕዝብ ለሁለት ተከፈለ፡፡ ቤተሰቦች በፖለቲካዊ ካርታ ተለያዩ፡፡ ኮርያውያን ይህንን ከወታደር ነጻ የሆነ ቀጣና ሲያዩ ‹ሰላምም፣ ጦርነትም የሌለበት ቦታ› ይሉታል፡፡ ከወታደር ነጻ በሆነው የደቡብ ኮርያ ቀጣና በኩል ሆኖ ሰሜን ኮርያን ማየት ይቻላል፡፡ ቀጣናው ከደቡብ ኮርያ ዋና ከተማ ሴኡል 35 ማይል ርቆ ይገኛል፡፡ 
ያልተዋሐደው የኮርያ ልሳነ ምድር

የኮርያ ጦርነት መጨረሻው አንድን ሕዝብ ለሁለት መክፈል፣ ሁለት ርእዮተ ዓለም ያላቸው ሁለት ሀገሮች መፍጠር፣ በሰሜን ቻይናና ሩሲያ፣ በደቡብ አሜሪካ በተልዕኮ የሚጎነታተሉበት የጦር ሜዳ ማዘጋጀት ሆነ፡፡ በተለይም ደቡብ ኮርያውያን ከሁለት ቦታዎች በስተቀር ሌላው ሀገራቸው በሙሉ ተወርሮ ስለነበር የነበረው እንዳልነበረ ሆኖባቸው ነበር፡፡ ጦርነቱ ሲጠናቀቅ የተበተኑትን መሰብሰብ፣ የፈራረሱትን መገንባት፣ የሕዝቡን የቆሰለ ልብ መፈወስ፣ ዳግም ወደ ስቃይ እንዳይገባ መጠበቅ ያስፈልግ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ ቃኘው ሻለቃ የሚመረጥ አልነበረም፡፡

የቃኘው ሻለቃ አባላት ከሚረዷቸው ልጆች ጋር
ዛሬም ኮርያውያንና የኮርያ መዛግብት የቃኘው ሻለቃ አባላትን በርኅራኄያቸው ያስታውሷቸዋል፡፡ በጦርነት ውስጥ ሆነው እንኳን ከምግባቸው እየቀነሱ የሚመግቧቸው ብዙ የተጎዱ ኮርያውያን ነበሩ፡፡ያሳደጓቸው ሕጻናት ዛሬ ኮርያን እየመሩ ነው፡፡ ትምህርት ቤትና የጤና ተቋማትን በገንዘባቸው ገንብተዋል፡፡ የጀግንነት ታሪካቸውን ተጠቅመው ሕዝቡ ተስፋ ሳይቆርጥ ኑሮን እንደገና እንዲጀምር አበርትተዋል፡፡ የዛሬዋ ኮርያ ወደ ዕድገቱ ጎዳና እንድትንደረደር መሠረቱ ሲጣል ስሚንቶ አቡክተዋል፣ ውኃ አቀብለዋል፣ እንዳይፈርስም ጠብቀዋል፡፡ 
ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ለቃኘው ሻለቃ ሰማዕታት ሜዳልያ ሲያበረክቱ
ከጦርነቱ በኋላ የቃኘው ሻለቃ አባላት 3 ዓመት ያህል እየተፈራረቁ በኮርያ ምድር በተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይል ሥር ሰላም እያስከበሩ ቆይተዋል፡፡ ከሙቀት ሀገር የመጡ የአፍሪካ ወታደሮች ወራሪውን ብቻ ሳይሆን ብርዱንና በረዶውን አሸንፈው ከብርዱ ሀገር ሰዎች በላይ ታሪክ ሠርተዋል፡፡ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ሕጻናት ሰብስበው አሳድገዋል፡፡
የቃኘው ሻለቃ አባላት ለመጨረሻ ጊዜ የኮርያን ልሳነ ምድር የለቀቁት በመጋቢት ወር 1956 ዓም እኤአ ነው፡፡ 121 ወታደሮች ተሠዉተው፣ 536 ወታደሮች ቆስለው ነበር፡፡ ዛሬ በእርጅናው የሚገኙ የዚያን ዘመን ኮርያውያን የቃኘው ሻለቃ ምድሪቱን ተሰናብቶ ሲወጣ ሕዝቡ በዕንባ እንዴት እንደሸኘው ያስታውሳሉ፡፡ ከዚህ በዕንባ ሲሸኙ ከወዲያ ደግሞ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ‹ጉሮ ወሸባየ› እያሉ ነበር የተቀበሏቸው፡፡ ዝናቸው በምድረ ኢትዮጵያ ናኝቷል፡፡ ገድላቸው የአፍ ማሟሻ ሆኗል፡፡ ከዐሥር ዓመት በኋላ የመጣው ደርግ ለሰሜን ኮርያ አድልቶ ደማቁ ታሪክ እንዲደበዝዝ ያደረገው ቢመስልም እነርሱ ያበሩት መብራት ግን የሚፍግ እሳት፣ የማይጠፋም ፋና ነው፡፡

በኮርያ ምድር ስትዘዋወሩ ልባችሁ ሞቅ ይላል፡፡ እዚህም እዚያም የጀግኖቻችሁን ገድል በመዛግብቱ፣ በሐውልቱ፣ በሙዝየሞቹ አሸብርቆ ታዩታላችሁ፡፡ የሚነገርላቸው ሁሉ ድንቅ፣ መሳጭና እንኳን ልጃቸው ሆንኩ የሚያሰኝ ነው፡፡ ምናልባት ግን እነርሱ የሞቱላት ኮርያ ባለፉት 61 ዓመታት አድጋና ተመንድጋ በብልጽግና ማማ ላይ ስትቀመጥ፣ የእነርሱ ሀገር ኢትዮጵያ ከችግር አለመውጣቷ እነዚያን ጀግኖች ልባቸውን ሳይሰብረው አይቀርም፡፡   

6 comments:

 1. በጽሑፉ መግቢያ ላይ ከአፍሪካ የተሳተፈችው ኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነች ተገልጾ ወረድ ብሎ ደግሞ የምርኮኞችን ዝርዝር ሲገለጽ ከደቡብ አፍሪካ 9 ምርኮኞች እንደነበሩ ተገልጿል፡፡ ሁለቱ አሳቦች አይጋጩም ወይ?

  ReplyDelete
  Replies
  1. ደቡብ አፍሪካ የሕክምና ባለሞያዎች ነው የላከችው እንጂ በጦርነቱ አልተሳተፈችም፡፡

   Delete
 2. ”የእሳት ልጅ አመድ“ አሉ አበዉ ሲተርቱ。ድሮ አባቶቻችን ከራሳቸዉ አልፈው እንዲህ ለሰው ይደርሱ ነበር ዛሬ ግን ያ ሁሉ ቀርቶ እኛ መደፈር ጀመርን。ንጹህ ወገኖቻችን በየመነገዱ፣በየበርሃዉ ወድቀዉ ይገኛሉ ታዲያ ይህን እነሱ ቢያዩ ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን?

  ReplyDelete
 3. ሃገራችን ምን ያክል ታላቅ ነበረች እና ኢትዮጵያዊን ለራሳችን ብቻ አልኖርንም ለሌሎችም እንኖራለን ለዓለም ሰላም ፍቅር በጸሎታችን ሰላምን በማሰከበር ሁሉ ኖረናል እንዴት ደስ ሲል ኢዮጵያ በኮሪያ ምድር ያደረገችው ተጋድሎ እኔስ በአባቶቼ እኮራለሁ

  ReplyDelete
 4. Good read Danny ! my dad was one of them.He represented his country and his people with bravery heart.He was fortunate to back home safley and he was a proud dad for the rest of his life.One again Thank you you pumped me to visit this great country with God willing.Peace be with you Boss.

  ReplyDelete
 5. እልከኞች ናቸው፡፡ መማረክን አይቀበሉም፡፡ ያለ ድል ለመመለስ ፈጽሞ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከፍ ብሎ ማየት የዘወትር ሕልማቸው ነው - ቃኘው ማለት ይህ ነው በቃ› እንግሊዛዊው የጦርነት ታሪክ ጸሐፊ ጆን ኬጋን፡፡

  ReplyDelete