Tuesday, January 31, 2017

ቃኘው ሻለቃ - የሚፍግ እሳት፣ የማይጠፋ ፋና - 2


እስከ 1956 እኤአ በኮርያ ምድር የቆዩት የቃኘው ሻለቃ አባላት ከአፍሪካ የሄዱ ብቸኛ ወታደሮች ነበሩ፡፡ የአፍሪካውያንን ጀግንነት የሚጠራጠሩትና የቀለም በሽታ ያልለቀቃቸው የአውሮፓና የአሜሪካ ወታደሮች ሊያሳዩዋቸው የሞከሩትን ንቀት በየግንባሩ በጀግንነት ባስመዘገቡት ገድል አፋቸውን አስይዘው የክብር ሰላምታ እንዲያቀርቡላቸው አድርገዋል፡፡ በኮርያ ምድር ከዘመቱ ምድቦች ሁሉ የተሰጣቸውን ሁሉንም ግዳጅ በድል የተወጡት የኢትዮጵያ ወታደሮች ብቻ ነበሩ፡፡ 238 ግዳጅ ተሰጥቷቸው ሁሉንም በድል ነበር የደመደሙት፡፡ ከዚህ በፊት ጥቁር ሰው አይተው የማያውቁት የሰሜን ኮርያ ወታደሮች የኢትዮጵያውያንን የድል በትር ሲቀምሱት ‹ልዩ ፍጡራን ናቸው› እስከማለት ደርሰው ነበር፡፡ እልከኞች ናቸው፡፡ መማረክን አይቀበሉም፡፡ ያለ ድል ለመመለስ ፈጽሞ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከፍ ብሎ ማየት የዘወትር ሕልማቸው ነው - ቃኘው ማለት ይህ ነው በቃ› እንግሊዛዊው የጦርነት ታሪክ ጸሐፊ ጆን ኬጋን፡፡ 

Monday, January 30, 2017

ቃኘው ሻለቃ - የሚፍግ እሳት፣ የማይጠፋ ፋና
የቃኘው አባላት በኮርያ

አሁን ከሴኦል ወደ ቹንቾን ከተማ እየተጓዝን ነው፡፡ በትዝታ ደግሞ ወደ ኋላ እንሄዳለን፡፡ እኤአ በሰኔ 1951 ዓም  የቃኘው ሻለቃ የመጀመሪያዎቹ ወታደሮች ከዚያ በፊት ኢትዮጵያውያን እምብዛም ስሙን ሰምተውት ወደማያውቁት የሩቅ ምሥራቅ ሀገር ተንቀሳቀሱ፡፡ በሰኔ ወር 1950 እኤአ የተጫረው የኮርያ ልሳነ ምድር ጦርነት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የመጀመሪያው ጦርነት ነበር፡፡ የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ኤል ሱንግ ደቡብ ኮርያን በመውረር የኮርያን ልሳነ ምድር አንድ የማድረግ ሕልሙን ሰሜን ኮርያ በነበረው የሶቪየት አምባሳደር በኩል ከፕሬዚዳንት ስታሊን ጋር መከረበት፡፡ በጉዳዩ የተስማማው ስታሊንና የታላቋ ቻይና መሪ የነበረው ማኦ ሴቱንግ ለኪም ኤል ሱንግ ቀኝ እጃቸውን ሰጡት፡፡ ሰሜን ኮርያም በሶቪየትና ቻይና እየተረዳች ደቡብ ኮርያን ወረረች፡፡

Saturday, January 28, 2017

ኮርያ ላይ ሆኜ አድዋን ሳስባት
በኮርያ ዋና ከተማ ሶኡል፣ ናምዮንግ ዶንግ፣ ዮንግሳን-ጉ (29 Itaewon-ro, Namyeong-dong, Yongsan-gu, Seoul) በሚገኘው የጦርነት መታሰቢያ ሙዝየም ግድግዳዎች ላይ በኮርያ ጦርነት ወቅት ከመላው ዓለም ተሰባስበው ሲዋጉ የተሠዉ ወታደሮች ስም ዝርዝሮች ተጽፈዋል፡፡ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ 121 ወታደሮቿን መሠዋቷ ተገልጧል፡፡ ከሁሉም ሀገሮች ብዙ ወታደሮችን ያሰለፈችውና ብዙ ወታደሮቿንም ያጣችው አሜሪካ ናት፡፡ የአሜሪካ ወታደሮች ዝርዝር በየግዛታቸው ረዥሙን ግድግዳ በሁለት እጥፍ ሞልቶታል፡፡
ይህን ሙዝየም ስጎበኝ ሁለት ነገሮች በሐሳቤ ይመጡ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን በታሪኳ እጅግ ብዙ ጦርነቶችን አድርጋለች፡፡ በጦርነቱ ተጎድተናል፤ በጦርነቱም ተጠቅመናል፡፡ የሕይወት ጥፋት፣ የንብረት ጉዳት ደርሶብን፣ ማኅበራዊ ቀውሶችንም በተሸክመን የተጎዳነውን ያህል ሀገራችንን ከጠላት ጠብቀን በማወቆየታችን ነጻነት የሚያስገኘውን መንፈሳዊና ቁሳዊ ጥቅምም አግኝተናል፡፡ በነጻነታችን ላይ ቆመን ሌሎች ነጻ እንዲሆኑም ታግለናል፡፡ ጦርነቶቻችን የዛሬዋን ሀገራችንንና የዛሬዎቹን ሕዝቦቻችንን አሁን ባሉበት መልክ ሠርተዋቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም የኢትዮጵያን የጦርነት ታሪክ የሚያሳይ አንድም የጦርነት መታሰቢያ ሙዝየም ግን የለንም፡፡

Tuesday, January 24, 2017

ብቻህን አይደለህምየቼሮቄ ጎሳዎች በደቡብ ምሥራቅ አሜሪካ የነበሩ ጥንታውያን የአሜሪካ ሕዝቦች ናቸው፡፡ የቼሮቄ ወጣቶች ለዐቅመ አዳም መድረሳቸውን የሚገልጡበት አንድ ከባድ ፈተና አላቸው፡፡ ወጣቱን አባቱ ይዞት ሊመሻሽ ሲል ወደ ጫካ ይሄዳል፡፡ ዓይኑን በጨርቅ ይታሠራል፡፡ ምንም ነገር ለማየት አይችልም፡፡ ያንን ጨርቅም ከዓይኑ ላይ ለማንሣት አይፈቀድለትም፡፡ አንድ ቦታ ላይ ይቀመጣል፡፡ ከተቀመጠበት ቦታም መንቀሳቀስ አይፈቀድለትም፡፡ ጨለማው አልፎ ፀሐይ እስክትወጣ ድረስ በዚያ ጫካ ውስጥ ለብቻው አንድ ቦታ ተቀምጦ ማሳለፍና ‹ወንድነቱን› መፈተን አለበት፡፡ አካባቢው ጸጥ ያለ ነው፡፡ ከአራዊት ጩኸትና ኮሽታ በቀር ሌላ የለበትም፡፡ ሰውም በአካባቢው አይደርስም፡፡ ምግብና ውኃ የሚያቀብለውም የለም፡፡ የልብ ምቱን እያዳመጠ ሌሊቱን በጸጥታ ያሳልፈዋል፡፡ ይህን ሌሊት ያለ ችግር ለማሳለፍ የቻለ ወጣት ለዐቅመ አዳም ደረሰ ማለት ነው፡፡ እንዴት እንዳሳለፈውና ምን እንዳጋጠመው ከእርሱ በታች ላሉት ልጆች ለመናገር አይፈቀድለትም፡፡ እያንዳንዱ ወንድ የራሱን ማንነት በባህሉ መሠረት መፈተሽ አለበትና፡፡
በዚህ ሥርዓት መሠረት አንድ የቼሮቄ ወጣት በምሥራቅ ቴነሲና በሰሜን ካሮላይና ወደሚገኘው የቼሮቄ ደን ተወሰደ፡፡ ፀሐይ እየጠለቀች መሆኑን እያየ ነው የተጓዘው፡፡ አባቱ የዓይን ማሠሪያውን ጨርቅ ይዟል፡፡ ሌሎች ሸኚ የጎሳ አባላት ደግሞ ይከተሉታል፡፡ ጥቅጥቅ ያለውን ደን አቋርጠው ከዛፎቹ ርዝማኔ የተነሣ ፀሐይን ለማየት ወደማይቻልበት ሆድ ውስጥ ገቡ፡፡ ሌሊቱን የማሳለፊያው ቦታ ተመረጠ፡፡ ወጣቱም ዓይኑን በጨርቅ ታሠረ፡፡ ታዛቢዎችም ዓይኑ በሚገባ የታሠረ መሆኑን አረጋገጡ፡፡ ከዚያም አንድ ቦታ እንዲቀመጥ ተደረገ፡፡ በመጨረሻም ሁሉም ሰዎች ተራ በተራ እየተሰናበቱት አካባቢውን ለቅቀው ሄዱ፡፡ ኮቴያቸው እየራቀው እየራቀው ሲሄድ ይታወቀዋል፡፡

Thursday, January 12, 2017

ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ

ሠፈራችን አንድ ሠርግ ቤት ውስጥ ልጃገረዶቹ ተሰባስበው
‹ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ
ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ
ይጠቀለላል እንደ ሠርዶ
ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ›
እያሉ ያስነኩታል፡፡ አንድ ሁለት ጊዜ እንዳቀነቀኑ እናትዬዋ ወገባቸውን እየሰበቁ ወጡና
‹‹አቁሙ፤ እርሱን ዘፈን አቁሙ›› አሉና ተቆጡ፡፡
‹‹ለምን እማማ?›› ልጃገረዶቹ ከዘፈን ትንፋሽ ባልወጣ ድምፃቸው ተንጫጩ፡፡
‹‹ምነው ሸዋ፤ የኔ ልጅ ከነ ፀጉሯ እንድትኖርልኝ እፈልጋለሁ ልጄ፤ ሐሳብ የለሽ ሁላ›› አሉ እማማ፡፡
‹‹ታድያ እኛ ዘፈንላት እንጂ ምን አረግናት›› ልጃገረዶቹ እየሳቁ ጠየቁ፡፡
‹‹እናንተ ምን ታደርጉ፡፡ ቴሌቭዥን አትከታተሉማ፤ ምን የዛሬ ልጆች ወይ ቃና ወይ ምርቃና ላይ ናችሁ፡፡››
‹‹ምን ተባለ ደግሞ እማማ፤ ተከለከለ እንዴ›› አለች አንዲት ወጣት አታሞውን እንደያዘች፡፡
‹‹ቻይናና ጃፓን ዶላር ሲያጡ የሴቶችን ፀጉር እንደሸጡ አልሰማችሁም›› እማማ በልጆቹ አለማሰብ ተናደዋል፡፡
‹‹ታድያ ቻይናና ጃፓን ቢሸጡ እኛ ምን አገባን፤ እንዝፈን ባካችሁ›› አለች ልጂቱ፡፡