Tuesday, October 4, 2016

ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት


አዋላጇ ጠፍታ ልጁም በእግሩ መጥቶ
እናቲቱ ሞተች ልጅዬውም ሞቶ

የሚል የልቅሶ ግጥም አለ። ነፍሰ ጡር እናት ስትወልድ ልጁ በእግሩ ከመጣ አደጋ ነው ይባላል። ጎበዝ አዋላጅ አግኝታ ልጁ በአናቱ እንዲመጣ ልታግዛት ይገባል። ያ ካልሆነ ግን ባልተስተካከለ መንገድ የመጣውን ልጅ ለመውለድ የምታምጠው እናት፣ ለረዥም ጊዜ በማማጧ የተነሣ ደክማ ለሞት ትዳረጋለች። ልጇም የመሞት ዕጣ ፈንታ ይገጥመዋል። መውለድ ደስታ የሚሆነው ልጁ በሰላም ተወልዶ፣ ለእናቱ ጤናና ደስታ ካመጣ ነው። መውለድ ካልተስተካከለ ማርገዝ ብቻውን ድካም ነው። ለዚህ ነው ነፍሰ ጡሮች በሕክምና እርዳታ ሲታገዙ ቆይተው፣ በሕክምና እርዳታ እንዲወልዱ የሚመከረው።ሀገር ለውጥን ልትወልድ የምትችለው የለውጥን ጽንስ በጤናማ መልኩ አርግዛ በጤናማ መልኩ እንድትወልድ የሚረዷትን ሐኪሞች ካገኘች ነው። ጽንሱ ጤናማ መሆኑን በየጊዜው የሚከታተሉ፤ ችግር ሲፈጠር ወዲያው መፍትሔ የሚሰጡ። ስትወልድም ልጁም እናቲቱም ጤንነታቸው በተጠበቀበት መንገድ እንድትወልድ የሚረዱ አዋላጅ ሐኪሞች ያስፈልጓታል። ይህ ሲጠፋ ልጁም እናቲቱም ለሞት ይዳረጋሉ።
ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ ለውጥን ፀንሳ ታውቃለች። ብዙ ጊዜ የማታገኘው ጎበዝ አዋላጅ ሐኪም ነው። በዚህ ምክንያትም ብዙ ጊዜ ልጇ ሞቶባታል። ያውም በእርሷም ላይ ከባድ አደጋ አድርሶ። ማኅፀኗን ጎድቷት ስለሚሄድ፣ ሌላ ልጅ ለመጸነስ ዘመናትን እንዲፈጅባት አድርጎ።

የቅርቡ ታሪካችንን እንኳን ብንመለከተው፣የልጅ ኢያሱን ዘመን ፀንሳ ነበር። ነገር ግን ካለፉት ዘመናት በተለየ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ሂደት ባለቤት እንዲሆን ከዘመኑ በቀደመ ሐሳብ የተነሣውን ወጣቱ ንጉሥ ሐሳቡን የሚያዋልድለትና ፅንሱ በእግሩ መጥቶ እናቱንም ራሱንም እንዳይገድል የሚያደርግ ሐኪም አጥቶ፣ ሀገሪቱ ያንን ዕድል አመከነችው። የተገኙት አዋላጆች ሳይሆኑ አምካኞች ነበሩ። ልክ ፈርዖን በግብጽ፣እሥራኤላውያን ላይ አሠማርቷቸው እንደነበሩት የአዋላጅ አምካኞች።

በ1953 ዓ.ም ኢትዮጵያ እንደገና ሌላ የለውጥ ልጅ ፀንሳ ነበር። ነባሩ ንጉሣዊ ሥርዓት ከመሠረቱ ሳይናጋ ነገር ግን ዘመኑ የሚጠይቀውን ሥርዓታዊ ለውጥ ለመውለድ ፀንሳ ነበር። አዋላጅ ግን አላገኘችም። ያንን ሐሳብ በሚገባ ፀንሳ በሚገባ እንድትወልድ የሚያደርጉ አዋላጆች ብታገኝ ኖሮ፣የጥንቱን ከዘመኑ ያጣጣመ ሥርዓት ገንብታ ለመጓዝ ትችል ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው፤ ጨነገፈ።

በ1966 ዓ.ም ሌላ የለውጥ ልጅ ፀነሰች። ሀገሪቱን ወደተሻለ ሥርዓት ሊወስድ የሚችል ተስፋ የሰነቀ ልጅ። ምን ዋጋ አለው። አዋላጆች አላገኘችም። ልጁን ጤናማ ሆኖ እንዲወለድ ከማገዝ ይልቅ አዋላጆቹ እርስ በርሳቸው ሲጨፋጨፉና ሲቧቀሱ፣ ልጁ ‹ታሪክ የጣለብንን ኃላፊነት ለመወጣት› ብለው በተነሡ የወታደር አጨናጋፊዎች እጅ ወደቀ። አንዲት የገጠር ሴት ለመውለድ ደርሳ አዋላጅ ጠራች። የቀን ጎደሎ ሆኖባት የማይችል ሰው እጅ ወደቀችና እርሷም ልጇም ሞቱ። አልቃሽ፡-

እንዲህ ያል ክፉ ቀን ክፉ ሰው ላይ ጥሏት
እንኳን ልጅ ልታገኝ እርሷንም ገደሏት፤

ብላ ገጠመች ይባላል። ኢትዮጵያም በ66 እንዲህ ነው የሆነቺው። ሐኪሞች ልጆቿ፤ የራስዋን ልጅ ማዋለድና ማሳደግ ሲገባቸው፣ የማደጎ ልጅ ከሶቪየት አምጥተው ልጅሽ ይሄ ነው አሏት። በማኅፀንዋ የተፀነሰውን የራስዋን ልጅ ገድለው የሰው ልጅ አሳቀፏት። የአዋላጆቹ ጠብም ልጇን እንዴት እናዋልዳት? መሆኑ ቀርቶ፣የትኛውን ልጅ ትታቀፍ? የሚለው ላይ ሆነ። እንኳን አዲስ ልጅ ልትወልድ እርሷም በወሊድ ምክንያት በተከሠተ ሕመም ለዘመናት ትሰቃይ ጀመር።

ያ ዘመን አልፎ 1983 ዓ.ም መጣ። ሁሉንም ያሳተፈ፤ የኅብረተሰብም የሐሳብም ብዝኃነትን የተቀበለ፤ ሀገሪቱ ስትመኘው የኖረቺውን ልጅ ልትወልድ የምትችልበት ዕድል ገጠማት። አሁንም ግን አዋላጆች ጠፉ። ያንን ለውጥ በፖለቲካ ብስለት፣ በዕውቀትና በትዕግሥት፣ በአመራርና በጥበብ አዋልደው፣ሀገሬ ዴሞክራሲና ዕድገትን ከነ ቃጭሉ ዱብ እንድታደርግ የሚያስችሉ አዋላጆች ጠፉ። ሁሉም የራሱን ብቻ ሲሰማና ‹ልጁ እንዲፀነስ የታገልኩት እኔ ነኝና እኔ ብቻ ልወስን› ሲል ሀገሬ ልጇን አጣችው። እርሷ ለመፅነስ እንጂ ለመውለድ ሳትታደል ቀረች።

ከሕዝቡ አብራክ ተከፍሎ በኢትዮጵያ ማኅፀን የተፀነሰውን ያንኑ ልጇን ተባብሮ ከማዋለድና እርሱኑ ተከባክቦ ከማሳደግ ይልቅ አሁንም ኮሚኒዝሙን፣ ማኦኢዝሙን፣ ዴሞክራሲውን፣ ቀያይጠንን እንደ አሻንጉሊት ሰፍተን፣ ‹ልጅሽ ይሄ ነው› አልናት። የብሔረሰቦችን ጥያቄ ልንግባባበትና ሀገር ልንመሠርትበት በምንችለው መንገድ መፍትሔውን መውለድ ሲገባን፣ ዘወትር የሚያጣላንንና የሚያበጣብጠንን የማደጎ ልጅ አመጣን። ከራሳችን አብራክ በራሳችን ማኅፀን ለኛ የሚሆን የፌዴራሊዝም ልጅ ልንወልድ ሲገባን የማደጎ ልጅ አመጣን። ይኼው አሁን በሂደት ልጁ የኛ ልጅ አለመሆኑን፤ ኢትዮጵያ የወለደችው ልጅ አለመሆኑን እየነገረን ነው። ከኛ ፍላጎት፣ ባህል፣ አስተሳሰብና ታሪክ ጋር መኖር አቅቶታል። የገዛ ልጃችን ዕዳ ነው የሆነብን። ሀገሬ ልጅ አልወጣላትም።

በ1997 ዓ.ም ሀገሬ ሌላ ልጅ ፀንሳ ነበር። ዴሞክራሲን። የአስተሳሰብ ብዙኅነትን ልትወልድ ነበር። እኛም ትወልዳለች ብለን የገንፎውንና የአጥሚቱን እህል አዘጋጅተን ነበር። ግን ምን ያደርጋል፤ ሐኪም አላገኘችም። ‹እኔ ብቻ› የሚል ሐኪም ገጥሟት፤ የዛሬውን እንጂ የነገውን የማያይ ስግብግብ አዋላጅ ገጥሟት፤ ምንጊዜም በሆስፒታሉ ውስጥ ‹ብቸኛው ስፔሻሊስት ሐኪም› እየተባለ መኖር የሚወድ ራስ ወዳድ ሐኪም ገጥሟት፤ ጊዜያዊ ችግሮችን ለዘላቂው ጥቅም ሲል መታገሥ የማይችል ሐኪም ገጥሟት፤ ወይ ‹ሁሉን ማግኘት አለያም ሁሉን ማጣት› የሚባል የማዋለጃ መሣሪያ የያዘ ሐኪም ገጥሟት ሀገሬ ልጇ ሞተባት።

እርሷም ትፀንሳለች እኛም እንፈጫለን
ለልቅሶ ነው እንጂ ለእልልታ አልታደልን፤

አለ አሉ፤ ኀዘን የጎዳው ባል። ሚስቱ በፀነሰች ቁጥር ለአራሷ የሚሆን እህል በቤቱ ይፈጫል። ነገር ግን ወለደች ተብሎ እልል ሳይባል፣ ሞተባት ተብሎ ይለቀሳል። ይሄ ነበር ባልን እንዲህ እንዲያንጎራጉር ያደረገው። ሀገሬም እንዲህ ነው የሆነቺው።

አሁንም ሀገሬ ፀንሳለች። እኛም ሊያግባባንና ሊያስማማን የሚችል ሥርዓተ መንግሥት፤ የብዙኃኑን ውክልና የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ሂደት፤ የትብብር መነሻ የሚሆን፣ ከአጥር ይልቅ ድልድይ የሚገነባ ፌዴራሊዝም፣ ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያከብርና የሚጠብቅ የፖለቲካ ምኅዳር ትወልዳለች ብለን ተስፋ እያደረግን ነው። ይህ እንዲሆን ግን ማዋለድ ያስፈልጋል። ኃይልና ጉልበትን፣ ዘረኝነትና ጽንፈኝነትን፣ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀልና እኔ ብቻ ዐውቅላችኋለሁን፣ እኔን ምን አገባኝና እኔ የለሁበትምን፣ አግላይነትንና ጠቅላይነትን፣ ጥገናዊነትንና ጊዜያዊነትን ትተን ሀገሬ ለሁላችንም የሚሆን፣ ሁላችንም እልል ብለን የምንቀበለው፤ ሁላችንም የአራስ ጥሪ የምናመጣለት፣ ሁላችንም በመወለዱ ገንፎ የምንበላበት፣ ሁላችንም ልደቱን የምናከብርለት፣ ከሩቅ ያሉት እንደ ሰብአ ሰገል ገሥግሠው፣ ከቅርብ ያሉት እንደ እረኞቹ ነቅተው ሄደው የሚያመሰግኑት ልጅ እንዲወለድልን ማዋለድ አለብን። ምሁራኑ፣ የፖለቲካው ልሂቃን፣ ደጋፊዎች፣ ተቃዋሚዎች፣ የእምነት መሪዎች፣ የሚዲያ ተዋንያን፣ ነጋድያን፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወታደራዊ አለቆች፤ ሀገራችን የፀነሰቺውን ልጅ በሰላም እንድትገላገል እንርዳት። አንዱ እግሩን፣ አንዱ እጁን፣ አንዱ ጆሮውን፣ አንዱ ጭንቅላቱን እየሳበ፣ ለራሱ ብቻ የሚጠቅመውን የየራሱን ልጅ ለማዋለድ ቢጥር ልጁ ይሞታል እንጂ ልጅ አይሆንም። ሀገሬም ፀንሳ በወለደች ቁጥር እየተጎዳች፣ እየደከመች ትሄዳለች።

እናት በተደጋጋሚ ልጆች ሞተውባት በስተመጨረሻ ተወልዶ የሚያድግላትን ልጅ ‹ማስረሻ› ትለዋለች። ያለፈውን መከራና ስቃይ ሁሉ የሚያስረሳ ማለቷ ነው። ሀገሬ ማስረሻ የሆነ ልጅ ትፈልጋለች። እልህና ኃይለኝነት አልጠቀመንም። ዘረኝነትና መከፋፈል አልፈየደልንም፣ ጥላቻና ሽኩቻ አላሳደገንም፤ ግዴለሽነትና ራስ ወዳድነት አላራመደንም። አሁን ሰከን ብሎ፤ ከስሜታዊነትም ወጥቶ፣ሀገሬ የፀነሰቺውን ልጅ እንዴት በሰላም ልትገላገል እንደምትችል መነጋገር፣ መመካከርና መተባበር ያስፈልጋል። ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት፤ ኑ፡፡ እስከ መቼ ልጅ ይሙትባት?

ካልጋሪ፣ ካናዳ

23 comments:

 1. እስከ እስከ መቼ ልጅ ይሙትባት ?
  በእውነት ከልብ እግዚአብሔር ይጠብቅህ ሥራህንም ያቅናልህ / እኛም ከዘር ከጎሳ ከቋንቋ ከክልልና ከጠባብ አስተሳሰብ ተላቀን የአንድ እናት ብዙ ልጆች መሆናችንን ተገንዝበን ለበላዮቻችን በፍቅር የምንገዛ የምንታዘዝ የበላዮቻችንም ሁላችንን ያለ አድሎ ያለ ልዩነት እንደሚገባ የሚመሩበት ይልቁንም ምዕራባዊያን የሰው ስብዕና አክብረው አስከብረው ወደ እንስሳት መብት ማክበር እንደደረሱ የእኛም መሪዎች ክቡሩን የሰው ልጅ እንደሚመሩ ሊረዱ ተረድተውም ሊተገብሩ ይገባል ።
  የአንድን ሕዝብ የመብት ጥያቄ በመሳሪያ አፈሙዝ ማፈን መጨቆን ለጥቂት ጊዜ ሊቻል ይችላላል ለዘመናት ግን በፍጹም አይቻልም ። ለምን መሪዎቻችን ከጎረቤቶቻችን አይማሩም በሌሎች ሃገራት የደረሰው በእኛ እስከሚደርስ ዝም ብለን እንመለከታለን ? ሀገር ጥሩ ልጅ እንድታፈረ ጥሩ አዋለጅ እንሁን እከመቼስ ልጅ ይሙትባት /
  ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን እግዚአብሔር ይስጥልን ።

  ReplyDelete
 2. እናመሰግናለን ወንድማችን!

  ከሚረብሽ የትርምስ ዜና እንዲህ ተስፋ የሚታይበት ፅሁፍ ማንበብ እንዴት መልካም ነው።

  ReplyDelete
 3. እርሷም ትፀንሳለች እኛም እንፈጫለን
  ለልቅሶ ነው እንጂ ለእልልታ አልታደልን፤
  ምሁራኑ፣ የፖለቲካው ልሂቃን፣ ደጋፊዎች፣ ተቃዋሚዎች፣ የእምነት መሪዎች፣ የሚዲያ ተዋንያን፣ ነጋድያን፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወታደራዊ አለቆች፤ ሀገራችን የፀነሰቺውን ልጅ በሰላም እንድትገላገል እንርዳት። አንዱ እግሩን፣ አንዱ እጁን፣ አንዱ ጆሮውን፣ አንዱ ጭንቅላቱን እየሳበ፣ ለራሱ ብቻ የሚጠቅመውን የየራሱን ልጅ ለማዋለድ ቢጥር ልጁ ይሞታል እንጂ ልጅ አይሆንም። ሀገሬም ፀንሳ በወለደች ቁጥር እየተጎዳች፣ እየደከመች ትሄዳለች።
  ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት፤ ኑ፡፡ እስከ መቼ ልጅ ይሙትባት?

  ReplyDelete
 4. አሜሪካ ከጥቅሟ ጉዳቷ የሚያመዝን ሀገር ነች!!! ታዲያ ምን እናድርግ?

  ብዙዎች አሜሪካን ሲማጸኑ ስመለከት እጅግ ያሳስበኛል። የወደፊቱ ዕጣችን ጭምር። በዓለም ላይ በአሜሪካ ዕርዳታ ዲሞክራሲን ሰላምን እና ዕድገትን ያገኘ አንድም የ3ኛው ዓለም ሀገር የለም። አሜሪካ ለሰው ህይወት ደንታ የሌላት ግን በማታለል በሴረኝነት ወደር የሌላት፤ ከሰለጠኑት ሀገራት ጋርም ሆነ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰውን አንገት እያረደ ከሚገድል ሳኡዲ አረብያ ያሉ ሃገራትም ጋር ትሰራለች። ዲሞክራሲን እና ሰላምን በተመለከተ በፍጹም አንድ አቋም የሌላቸው፡ ለእንቅስቃሴዋ ሁሉ ስሌቱ የራስ ጥቅም ብቻ ነው።

  የኛ ቢጤ አላዋቂ ህዝቦች ለለውጥ የሚያደርጉትን ትግል ታዳምጥ ታዳምጥ እና ህዝቦች ወደአሸናፊነት ሲመጡ አጅባ በመግባት ቀጣዩ መንግስት የሷ አሻንጉሊት እንዲሆን አድርጋ ታቋቁማለች። በወያኔ መንግስት የተፈጸመው ይኸው ነው።

  ነፍሰ ገዳይም ሆንክ ወይም ጻድቅ ለነሱ ልዩነት የለውም። ዋናው አሸናፊ ከሆንክ አንተን የራሳቸው አሻንጉሊት ለማድረግ ያላቸውን ሁሉ ይጠቀማሉ።
  ዛሬ አሜሪካን አሜሪካን የሚሉ የፖለቲካ አስተባባሪዎች፡ ነገ ለውጥ ቢመጣ በተራቸው ሀገራችንን የአሜሪካ አሻንጉሊት ላማድረግ ከወዲሁ ልባቸውን የሰጡ ናቸው።

  ስለዚህ ድል ማሸነፍ መመንጨት ያለበት ከውስጣችን ነው፤ካራሳችን ብቻ። በየቀበሌው ያለውን፤ በየአቅራቢያችን ያለውን ወያኔ እና ተላላኪ ሁሉ በሃይል ብናስወግድ፤ንብረቱን ብናወድም፤ ማህበራዊ መገለል ብናውጅበት፡ መንግስት በአጭር ጊዜ ሀገር ጥሎ ይጠፋል። ከዚህ በኋላ የሚመጣ አስተዳደር የህዝብን ሃይል ስለሚረዳ ዳግም አይቀልድም።

  ከታች ወያኔን ከህዝቡ ጋር የሚያገናኙትን ካስወገድን፤ ግፈኛው መንግስት ያከትምለታል። ከዚያ የራሱ ወታደር ባለስልጣኖቹ ላይ መሳሪያውን ያነሳል።

  እኛ በውስጥ ማሸነፋችን ሲታወቅ አሜሪካ እንደልክስክስ ውሻ አጃቢ ሆና እንደገና ልትታበቅብን ትሯሯጣለች። ያንጊዜ እውን የሀገር ፍቅር ካለን፤ የራሳችንን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ግንኙነት ማድረግ እንችላለን። ጠንካራ ከሆንን አሜሪካንን መቋ ቋምም እንችላለን።

  አሜሪካ ሃገራችን ስላልሆነች ምንም ልንጠብቅ አይገባም። ለሰብአዊ መብት ቢጨነቁ ኖር ሃገራቸው ያለውን ዘረኝነት ባስወገዱ ነበር ወይም . ሶርያውያን እንዲህ ባላለቁ ነበር።

  ከአሜሪካ የምንናገኘው ብቸኛ ጥቅም ለመናገር ለመደራጀት የተመቸ መሆኑ ብቻ ነው። ከዚህ ያለፈ ግን አሸናፊዎች ካልሆንን በስተቀር ጠብ የምትል ነገር የለችም፤ ብናሸንፍም ቀዳሚ ዓላማቸው እኛን በነጻ የነሱ አሽከር ማድረግ ነው። የነሱ ጥቅም ይከበር እንጂ እኛ በነርሱ ምክንያት ከአካቢያችን ሀገራት ጋር ያማያቋርጥ ግጭት ውስጥ ብንገባ ጉዳያቸው አይደለም።

  ከጠነከርንባቸው ግን ትንሽ ተመጣጣኝ ክፍያ ለማድረግ ይገደዳሉ። በቃ አሜሪካ ይኸው ነው።
  የሀገር ፍቅር ይኑረን እንጂ ያለአሜሪካ እገዛ ጠንካራ ፍትህ ሰላም እኩልነት የሰፈነባት ሀገር መመስረት እንችላለን። በብሄረሰቦችም ሆነ በዕምነቶች መካከል ሰላም ሊያሰፍን የሚችል ሀገር በቀል የሆነ አኩሪ ትሥሥር አለን። በውጭ ግንኙነትም በኩል አሜሪካን እና አውሮፓውያንን የራሳችንን ጥቅም ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ባስጠበቀ መልኩ ብቻ ግንኙነት እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል። ሀገሩን የሚወድ እና የገባው ትውልድ ብቻ ያስፈልጋል።

  ያኔ የአሜሪካን ተላላኪ ሆኖ ሶማሌን የሚወጋ ወታደር አይኖርም። ያኔ ለአሜሪካ ገብጋባ ካፒታሊስቶች ገንዘብ ብለን የምናፈናቅለው ደሃ ወገናችን አይኖርም። ያኔ ህዝባችን የአውሮፓውያን እና የአረብ ሃገራት የቻይና የማይጠቅሙ፤ ለጤናም ጠንቅ የሆኑ ሸቀጥ ማራገፊያ አይሆንም። ጥንካሬያችን ከውስጥ ከመነጨ ብቻ!!!!!!

  አቦ ወገን እንንቃ ሌሎችንም እናንቃ። የአሜሪካን ጥቁሮች ህይወት ያየ፤ ኢራቅን፤ አፍጋኒስታንን፤ ሶርያን ያየ፤ የነሳኡዲ አረብያን የአሜሪካ ልብ ወዳጅነት ያየ፤ አሜሪካ የጥፋት፤ እንጂ የዲሞክራሲ የሰላም ምሳሌ ልትሆን እንደማትችል ፍንትው ብሎ ይታየዋል።

  ReplyDelete
  Replies
  1. የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የፖለቲካ ጥልፍልፍና ልፊያው በደንብ የገባው ይመስላል፡፡ በግሌ አንድም ቀን ዋይት ሐውስና ካፒቶል ፊት ለፊት በሰልፍ ስም ድዴን አስጥቼ አላውቅም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንተ ያልከው ነው፡፡ አሜሪካኖቹም ሆኑ እንግሊዞች ሁሉንም ያውቃሉ፡፡ ገንዘብ የሚሰጡት፣ መተኮሻውን የሚሰጡት፣ ጥይቱን የሚያቀብሉት፣ ሥልጠናውን የሚሰጡት፣ ባቀረቡት አረር ኢትዮጵያዊ ሲሞት ከማንም በፊት ቀድመው ስንት፣ መቼ፣ የት፣ እንዴት እንደሞተ እንኳን የተሟላ መረጃ ያላቸው እነርሱ ናቸው፡፡ ታዲያ ለቀባሪው ለማርዳት፤ ወይም በገዛ ምድራችን እያሳረዱን ያሉትን ኃያላን መንግሥታት "ታደጉን" ብሎ ጩኸት፤ ረብ ያለው አይደለም ለእኔ፡፡ አሜሪካኖቹ የሚመኩበት ትልቅ የሊደርሺፕ ፍልስፍና አላቸው The strategic leadership environment components, strategic thinking and future orientation. በእግጥም ይህ የዘላቂ ህልውናና ጥቅም አመራር መርህ ጥልቅና ዛሬ ታላላቆቹ አገራት አሜሪካንን ጨምሮ ራሺያ፣ቻይና፣ሕንድ፣ደቡብ ኮሪያ፣ ወዘተ አገራቸውን የሚመሩበት ፍልስፍናቸው ነው፡፡ ይህ ፍልስፍና በተለምዶ አጠራር ማኔጅመንት ከምንለው የትምህርት ዘርፍ ውስጥ የሚገኝ ቢመስልም ፍልስፍናው ጥልቅና የራሱ የልህቀት ፍልስፍና ያለው ነው፡፡ ይህንን የአመራር ፍልስፍና በቅጡ ያልተገነዘበውን እንጭጭ የፖለቲካ ጎራ አሜሪካ በስቴት ዲፓርትመንቷ አማካይነት እየጠራች እያወያየች ነው፡፡ አስተያየት ሰጪው እንዳሉት አሜሪካኖቹ የጨዋታው ሚዛን ወደየት እያደላ መሆኑን በማወቃቸው እንደ ውሻ እየተልከሰከሱ የኢትዮጵያን ዘላቂ ህልውናና ዘላቂ ጥቅም ከላይ በገለጽኩት መርህ መሠረት ለማስጠበቅ የማይችሉ በቂ ልምድ፣ጥልቅ አሳቢነት፣ የጋራ ርእይ የሌላቸውን ቡድኖች እየሰበሰቡ እያነጋገሩ ይገኛል፡፡ የስትራቴጂክ ሊደርሺፕ አስተምህሮ ከማኔጅመንት መርሆ ይለያል፡፡ (for Management - Managers are not made but born ሲል for Leadership - Experiential attributes are essential to goal achieving decision making) ሊደርሺፕ ለመሪነት የሚጠይቀው መሥፈርት ከማኔጅመን በእጅጉ ይለያል፡፡ ማኔጅመንት በተዘጋጀ ቦይ ውስጥ፣ በመዋቅር በተጠረ ሜዳ ውስጥ የመጫወት ያህል ነው፡፡ ሊደርሺፕ ደግሞ ጥልቅ እሳቤን ይፈልጋል፤ ሜዳውን ከማዘጋጀት ጀምሮ የማዋቅሩን ዋልታና ማገር ከኀልዮ አፍልቆ መሬት ላይ መተግበርን የሚጠይቅ በጣም ፈታኝ ተግባር በመሆኑ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን አሁንም የአሜሪካንን ጥቅም ብቻ አስጠባቂ ቡችሎችን ለመቀበል ያረገዘ ለውጥ በራችንን እያንኳኳ መሆኑን ሳስብ የኢትዮጵያውን ወገኖቼ እየከፈሉት ያለው መስዋእትነት ከንቱ መሆኑ በጣም ያማል፡፡
   ተስፋዬ

   Delete
 5. እልህና ኃይለኝነት አልጠቀመንም። ዘረኝነትና መከፋፈል አልፈየደልንም፣ ጥላቻና ሽኩቻ አላሳደገንም፤ ግዴለሽነትና ራስ ወዳድነት አላራመደንም።

  ReplyDelete
 6. ማርያም ማርያም ማለቱንም አንርሳው!!!

  ReplyDelete
 7. ሀገሬ ማስረሻ የሆነ ልጅ ትፈልጋለች

  ReplyDelete
 8. ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት፤ ኑ፡

  ReplyDelete
 9. Dani, you should take this responsibility.

  ReplyDelete
 10. ድሮ…
  ነፍሰ―ጡር…
  የአባትነት ክብር
          የቤተሰብ ተድላ
  ፅንስ ስትሸከም
          ማህፀን ሲላላ
  በምጥ ስትጨነቅ
          "እናቴን! እናቴን!"
  ጥሩልኝ ትላለች
        የምጥ ታሪክ ካላት
  ምክር እየሻተች።
  ባለተራው አባት
        ከወለደው ሰምቶ
         ቀበቶ ያላላል
     በምክር ቀለበት
          ህይወት ይቀጥላል።
           አዲስ ይወለዳል።
  ይሔስ አዲስ ትውልድ?
  ከተጨናገፉ ብዙ ፅንሶች መሀል
             ለዘር የተረፈው
  (በማላላት ፋንታ)
  በአዲስ ፅንሰ ሀሳብ
  ከታሰረ ወገብ
           አፈትልኮ የወጣው
  ይሔስ አዲስ ትውልድ?
            ሀገር ያክል ነገር
  አርግዞ ሲጨነቅ
          ከማን ይማከራል?
          ማንን ይጠይቃል?
                                                          ነሐሴ ፪፻፰
                                                               ሰደ

  ReplyDelete
 11. That's exactly I am feeling about Ethiopia & so much worried about the possibility of having a stolen revolution for the 3rd time in my life.
  May God help us to have true governance that will create a country for all of us to live in true democracy, equality, justice, freedom...

  ReplyDelete
 12. አመተ ምህረት ወይስ ዓመተ ምኅረት።
  ሁሉን በአግባቡ መጠቀም መልካም ነው።

  ReplyDelete
 13. እግዚአብሔር በምህረቱ ይጎብኘን፣ አስተዋይ ልቦና ይስጠን፡፡

  ReplyDelete
 14. ሁላችንም እልል ብለን የምንቀበለው፤ ሁላችንም የአራስ ጥሪ የምናመጣለት፣ ሁላችንም በመወለዱ ገንፎ የምንበላበት፣ ሁላችንም ልደቱን የምናከብርለት፣ ከሩቅ ያሉት እንደ ሰብአ ሰገል ገሥግሠው፣ ከቅርብ ያሉት እንደ እረኞቹ ነቅተው ሄደው የሚያመሰግኑት ልጅ እንዲወለድልን ማዋለድ አለብን።

  ReplyDelete
 15. እኛም ሊያግባባንና ሊያስማማን የሚችል ሥርዓተ መንግሥት፤ የብዙኃኑን ውክልና የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ሂደት፤ የትብብር መነሻ የሚሆን፣ ከአጥር ይልቅ ድልድይ የሚገነባ ፌዴራሊዝም፣ ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያከብርና የሚጠብቅ የፖለቲካ ምኅዳር ትወልዳለች ብለን ተስፋ እያደረግን ነው። ዶ/ር ዲ/ን ዳንኤል ክብረት እግዚአብሔር አምላክ ይባርክኸ፡፡

  ReplyDelete
 16. እልህና ኃይለኝነት አልጠቀመንም። ዘረኝነትና መከፋፈል አልፈየደልንም፣ ጥላቻና ሽኩቻ አላሳደገንም፤ ግዴለሽነትና ራስ ወዳድነት አላራመደንም።

  ReplyDelete
 17. melkam new memihr, huliem yemitinagerachew astaraki hasaboch nachew. long life for u.

  ReplyDelete
 18. Dn Daniel, Kale hiwot yasemalen"እናት በተደጋጋሚ ልጆች ሞተውባት በስተመጨረሻ ተወልዶ የሚያድግላትን ልጅ ‹ማስረሻ› ትለዋለች። ያለፈውን መከራና ስቃይ ሁሉ የሚያስረሳ ማለቷ ነው። ሀገሬ ማስረሻ የሆነ ልጅ ትፈልጋለች። እልህና ኃይለኝነት አልጠቀመንም። ዘረኝነትና መከፋፈል አልፈየደልንም፣ ጥላቻና ሽኩቻ አላሳደገንም፤ ግዴለሽነትና ራስ ወዳድነት አላራመደንም። አሁን ሰከን ብሎ፤ ከስሜታዊነትም ወጥቶ፣ሀገሬ የፀነሰቺውን ልጅ እንዴት በሰላም ልትገላገል እንደምትችል መነጋገር፣ መመካከርና መተባበር ያስፈልጋል። ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት፤ ኑ፡፡ እስከ መቼ ልጅ ይሙትባት?"

  ReplyDelete