Wednesday, September 28, 2016

ተቀምጠው የሰቀሉት
የኢራቅ ኩርዶች እንዲህ ይተርካሉ፤
አንዲት የልዑል ልጅ ነበረች፡፡ አንድ የምታፈቅረው ልጅም ነበረ፡፡ ታድያ ከአንድ የቤተ መንግሥቱ ጠባቂ ጋር ትመካከርና ይህንን ፍቅረኛዋን ክፍሏ ድረስ ታስገባው ነበር፡፡ የቤተ መንግሥቱ ጥበቃ የተወሰነ ገንዘብና ልብስ ትሰጠው ስለነበር በደስታ ምሥጢሩን ይደብቅ ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን ያልታሰበ ነገር ተከሰተ፡፡ ልዕልቲቱና ፍቅረኛዋ አፕል ቆርጠው እየተጫወቱ ይበሉ ነበር፡፡ ሁለቱም አፋቸውን ከፍተው የአፕሉን ቁራጭ አንዳቸው ወደሌላቸው አፍ ወርውሮ የማስገባት ጨዋታ ነበር የሚጫወቱት፡፡ 
እየተሳሳቁ የአፕል ቁራጭ ወደየአፎቻቸው ሲወረውሩ ልዕልቲቱ የወረወረችው የአፕል ቁራጭ ድንገት የፍቅረኛዋ ጉሮሮ ውስጥ ተቀረቀረ፡፡ ውኃ ብትሰጠው፣ ማጅራቱን ብትመታው ሊወርድለት አልቻለም፡፡ ኡኡ ብላ እንዳትጮህ ልጁ ማነው? እንዴትስ መጣ ? ለሚለው ጥያቄ የምትመልሰው የላትም፡፡ በዚህ መካከል ልጁ ትንፋሽ አጥሮት ሞተ፡፡

የልጁ የመውጫ ሰዓት ሲደርስ የጥበቃ ሠራተኛው መጣ፡፡ እንደቀድሞው ግን ልጁን ደብቆ ሊያስወጣው አይችልም፡፡ አሁን ያለው ሬሳው ነው፡፡ ‹እባክህን የምትችለውን ሁሉ አድርገህ ይህንን ሬሳ አውጣልኝ፤ የምትፈልገውን ነገር ሁሉ አደርግልሃለው› አለቺው፡፡ የጥበቃ ሠራተኛውም ‹ምንም ችግር የለውም፤ የምፈልገው ግን ገንዘብ ወይም ልብስ አይደለም› አላት፡፡ እርሷም ‹ምንም ችግር የለም፡፡ ብቻ በቶሎ አውጣልኝ› ብላ ለመነችው፡፡ የጥበቃ ሠራተኛው ሬሳውን ቆሻሻ አስመስሎ ደብቆ  አወጣው፡፡ እርሷም እፎይ አለች፡፡
የጥበቃ ሠራተኛው ተመልሶ መጣና ቃል በገባችው መሠረት የሚፈልገውን ነገር እንድታደርግለት ጠየቃት፡፡ ‹ምን?› አለች ልዕልቲቱ፡፡ ‹ካንቺ ጋር መተኛት ነው የምፈልገው› አላት፡፡ ፀሐይ እንደበዛባት ቅል ክው አለች፡፡ ተናደደች፡፡ ‹ምን ደፋር ነህ ከልዕልት ጋር ለመተኛት የምታስብ፤ አሁን ከዚህ ጥፋ› አለቺው፡፡ እሺ ብሎ ወጣና የፍቅረኛዋን አስከሬን ይዞላት መጣ፡፡ ይኼኔ የምታደርገው ግራ ገባት፡፡ ያላት አማራጭ የሰውዬውን ፈቃድ ማሟላት ብቻ ሆነ፡፡ ተሸነፈች፡፡ በአንድ ቀንም ሦስት ነገሮችን አጣች፡፡ ፍቅረኛዋን፣ ክብሯንና የወደፊት ተስፋዋን፡፡ ፍቅረኛዋን በሞት፤ ክብሯንም በአገልጋይዋ እግር ሥር በመውደቅ፤ የወደፊቱንም ተስፋዋን ድንግልናዋን በማጣት፡፡ 
በዚህ ብቻ አላበቃችም፡፡ ያ የጥበቃ ሠራተኛ እየመጣ ‹አጋልጥሻለሁ› ይላታል፡፡ ያን ቀን ሬሳውን ይዞ የመጣበትን ጆንያም ያሳያታል፡፡ እርሷም ትፈራለች፡፡ በፍርሃትም የማትፈልገው ሰው እግር ሥር ትወድቃለች፡፡ ከእርሱም ጋር ትተኛለች፡፡ ይህ ግን ሊያዛልቃት አልቻለም፡፡ ባርነት ሰለቻት፡፡ ችግሮችን ለመጋፈጥ ካልፈለግህ ችግሮችን እያነገሥካቸው ትሄዳለህ› ይላሉ ኩርዶች፡፡ ችግርን ካታለልከው መልሶ ይይዝሃል፤ ከተጋፈጥከው ግን ጥሎህ ይሸሻል የሚል አባባልም አላቸው፡፡ 
ልዕልቲቱ አሁንም ችግሩን መፍታት ሳይሆን ማምለጥ ፈለገች፡፡ አንድ ሌሊት የጥበቃ ሠራተኛው ተደብቆ ወደእርሷ ሲመጣ ለአባቷ የምታዘጋጀውን የልዑሉን ወይን አሰናድታ ጠበቀቺው፡፡ በደስታ እየደጋገመ ጠጣ፡፡ ከእርሷም ጋር ከተኛ በኋላ እንደ ተሸነፈ ቦክሰኛ በድካም ተዘረረ፡፡ አርሷም እየጎተተች ወስዳ በልዑሉ መኝታ በር ላይ አጋደመችው፡፡ ሊነጋጋ ሲል ጠባቂዎቹ አዩት፡፡ ጠጋ ብለው ሲያሸቱት አፉ የወይን ጠጅ ይሸታል፡፡ የወይን ጠጁ ሽታ የልዑሉ ወይን መሆኑን ይመሰክራል፡፡ የልዑሉን ወይን ሰርቆ ጠጥቷል ብለው በአደባባይ ሰቅለው ገደሉት፡፡ ነገሩም በዚህ የተቋጨ መሰለ፡፡ ነገር ግን የዕብድ ቀን አይመሽም፡፡ ኩርዶች እንዲህ ይላሉ፡፡ የምትሠራው በር ምንጊዜም ልትሄድበት የምትችል መሆኑን አረጋግጥ፡፡ ለአንድ ጊዜ መውጫ ብለህ በሩን ከሠራኸው ከበሩ በኋላ ወዴት እንደምትሄድ ግራ ይገባሃል፡፡ በሩን ከነ መንገዱ አስበው፡፡ መንገዱን ከነ መዳረሻው፤ መዳረሻውንም ከነመቆያው፤ መቆያውን ከነ መክረሚያው፡፡ 
የጥበቃው ሠራተኛ በአደባባይ ሲሰቀል፤ የወይኑ ጣዕም አፉ ላይ ቀርቶ ስለነበር እየደጋገመ ከንፈሩን ይልስ ነበር፡፡ የዚህ ምክንያቱ የጠጣው የወይን ጠጅ ጣዕም ነው ተብሎ ተወራ፡፡ ይህንን ወሬ የሰማ የሌላ ልዑል ልጅም ይህንን ወይን ያዘጋጀቺውን የልዑሉን ልጅ ለማግባት ፈለገ፡፡ እናም ወደ ልዕልቲቱ አባት ሽማግሌዎች ላከ፡፡
ይህ ዜና ለአባቷ የምሥራች ለልዕልቲቱ ግን መርዶ ነበር፡፡ ድንግልናዋን አጥታለች፡፡ በኩርድ ደግሞ ድንግል ያልሆነቺውን ልጅ እንኳን ልዑላን ተራዎቹ ሰዎች አያገቡም፡፡ እስካሁን ችግሩን ከመጋፈጥ እየሸሸች፣ ነገር ግን አንዱን ችግር በሌላ ችግር እያለፈች መጥታለች፡፡ አሁን የመጋፈጫው ሰዓት ደረሰ፡፡ ችግርን በመፍትሔ መፍታትና ችግርን በሌላ ችግር ማለፍ ይለያያሉ፡፡ ችግርን በችግር ካለፍከፈው ጊዜ እየገዛህ ነው፡፡ ችግርን በመፍትሔ ካለፍከው ደግሞ ልብ እየገዛህ ነው፡፡ ይላሉ ኩርዶች፡፡ 
የልዕልቲቱ አባት ጋብቻውን መቀበሉን ስትሰማ እንደተለመደው ልዕልቲቱ አንድ ዘዴ ቀየሰች፡፡ አንዱን ታማኝ አገልጋይዋን ጠራችውና አንድ እፍኝ ወርቅ ሰጥታ እንዲህ ስትል አዘዘችው ‹በመላዋ ኢራቅ ዙር፡፡ በመልክም፣ በቁመትም፣ በጠባይም እኔን የምትመስል ልጅ ፈልገህ ለደንገጡርነት አምጣልኝ›፡፡ ሰውዬውም ለወራት ያህል ከቦታ ወደ ቦታ ዞረ፡፡ በመጨረሻም አንዲት ልጅ አገኘ፡፡ ልዕልቲቱ ስታያት ቁርጥ እርሷን ትመስላለች፡፡ እንዲህ አለቻት ልጅቱን፡፡ አሁን አንቺ ልዕልት ሆነሻል አሉ፡፡ የልዑሉንም ልጅ ታገቢያለሽ፡፡ የጫጉላውንም ጊዜ አብረሽው ታሳልፊያለሽ፡፡ እኔም ያንቺ ደንገጡር ሆኜ አንቺንና ልዑሉን ለጊዜው እታዘዛለሁ፡፡ ልክ የጫጉላው ጊዜ እንዳለፈ ግን ትቀይሪኛለሽ፡፤ እንቺ ወደ ደንገጡርነትሽ እኔም ወደ እመቤትነቴ እመለሳለሁ፡፡ ለዚህ ውለታሽም ለጥሎሽ የሚመጣውን ሀብት ሁሉ ትወስጃለሽ› አለቻት፡፡ ልጂቱም በደስታ ተፍነከነከች፡፡ 
የሠርጉ ቀን ደረሰ፡፡ ደንገጡሯዋ የሙሽራ ልብስ ለበሰች፡፡ እመቤቲቱ ደግሞ የአገልጋይ ልብስ ለበሰች፡፡ ማንም ሊለያቸው የቻለ የለም፡፡ ልዑሉ መጣ፡፡ ሙሽራዋን ይዞ ሄደ፡፡ አገልጋይዋም ተከትላ ሄደች፡፡ በልዑሉ ቤት የነበረው ድግስ ሲያልቅ ልዑሉና ሙሽራዋ ወደ ጫጉላ ቤት ገቡ፡፡ አገልጋይዋም ከውጭ ቀረች፡፡ ታስበዋለች፡፡ ይህ ዕድል የእርሷ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን አይደለም፡፡ አሁን እርሷ ነበረች እዚያ ውስጥ መሆን የነበረባት፤ ግን ችግርን ለማለፍ ብላ በፈጠረችው ችግር ምክንያት ውጭ ቆማለች፡፡ እዚህ ደረጃ ሳትደርስ ነገሮችን አስተካክላ በክብር ልትወጣ ትችል የነበረባቸውን ዕድሎች ታስታውሳለች፡፡ ዕድሎች ሁሉ አምልጠዋታል፡፡ ችግሮችን በሌላ ችግር በመተካት ዕድሎችን አምክናቸዋለች፡፡ ስለዚህም ክብሯን ለሌላዋ አሳልፋ ሰጠቻት፡፡ ሕዝቡ ጫጉላ ቤት ያለቺው እርሷ መስላቸዋለች፡፡ ግን አይደለችም፡፡ የተመረጠችው እርሷ፣ ወደ ሠገነት የወጣችው ሌላዋ፡፡ የተዳረችው እርሷ፣ ያገባችው ሌላዋ፡፡
የጫጉላዎቹ ቀናት አለፉ፡፡ ልጂቱ ግን ወደ አገልጋይነቷ ልትመለስ አልቻለችም፡፡ አንድ ቀን መታጠቢያ ቤት ውስጥ እመቤትና ደንገጡር ተገናኙ፡፡ ደንገጡሯም ‹አሁን በቃሽ ወደቦታሽ ተመለሽ፡፡ ለውለታሽ ያዘጋጀሁትን ስጦታሽን ውሰጅ; አለቻት፡፡ እመቤቲቱም ‹የዋሕ ነሽ፡፡ ላየው የማልችለውን አሳየሺኝ፤ ላገኘው የማልችለውን ሰጠሽኝ፤ ልደርስበት የማልችለው ቦታ አደረሽኝ፡፡ ያኔ እሺ ስልሽ ይህንን ሁሉ አላውቅም ነበር፡፡ አልጋው እንዲህ የሚመች መሆኑን አልቀመስኩም ነበር፡፡ ክብሩ እንዲህ የሚያጓጓ መሆኑን አላውቅም ነበር፡፡ ምቾቱ እንዲህ ልብ የሚለሰልብ መሆኑን አላውቅም ነበር፡፡ ላንቺ ከደንገጡርነት ወደ እመቤትነት መምጣት ቀላል ይሆናል፡፡ ለእኔ ግን ከእመቤትነት ወደ ደንገጡርነት መውረድ ከባድ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ነገር ከቀመስኩ በኋላ ትተውልኛለች ብለሽ ማሰብሽ ሞኝነትሽ ነው፡፡ አልጋ አንዲህ በቀላሉ የሚተው አይደለም፡፡ ሀብቱ ሁሉ የእኔ መሆኑን እያየሁ ያንቺ ስጦታ የሚያጓጓኝ ይመስልሻል› አለቻት፡፡ 
›እነሆ› ይላሉ ኩርዶች፡፡ እነሆ በዚህ የተነሣ አገልጋይቱ እመቤት፣ እመቤቲቱም አገልጋይ ሆነው ኖሩ፡፡ ተቀምጣ የሰቀለቺውን ቆማ ማውረድ አቅቷት፡፡ 
ኤድመንተን፣ ካናዳ

16 comments:

 1. This is a great article. Because the message is very wide, it is hard to interpret in a defined certain way. Is this about the current situation in Ethiopia? i.e TPLF is a king and the Ethiopian people is a servant. Because the Ethipipian people ushered TPLF to their powerful seats...lol

  ReplyDelete
 2. i have no words to say thanks dani.Go ahead wiith this motive

  ReplyDelete
 3. ፋሺስትን ለማሸነፍ ጸሎት ብቻ በቂ ነው ቢሉ ኖሮ ጣሊያን አቡነ ጴጥሮስን አና አቡነ ሚካኤልን ባልገደለ ነበር
  አውሮፓያውያን ወራሪዎች አፍሪካን፤ሰሜን እና ደቡብ አሜሪካን ለመያዝ ሲመጡ ሚሲዮናውያንን( ወንጌል ሰባኪ ነን ባዮችን) ከፊታቸው በማስቀደም የህዝቡን ስነልቦና ለመስለብ፤ የሚደርስበት ሁሉ በሀጢአቱ ብቻ ስለሆነ፤ እርስበርሱ ያስተሳሰረን ባህሉን ልምዱን እንዲጠላ፤ዕድሉ በሰማያዊው እንጂ በዚህ ምድር እንዳልሆነ፤ ሁሉን አሜን ብሎ መቀበል እና መጸለይ ብቻ እንዳለበት በመስበክ ፍጹም ፀጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ አድርገውበታል።
  እውቁ የነጻነት ታጋይ ጆሞ ኬንያታ፤ አውሮፓውያን አይናችሁን ጨፍናቹ ጸልዩ አሉን፤ ዓይናችንን ስንጨፍን መሬታችንን ወሰዱት ማለቱ፤ ላቲን አሜሪካውያን፤ የጦር መሳሪያ ካደረሰብን ጉዳት፤ መጽሐፍ ቅዱስ ያደረሰብን ጉዳት ይበልጣል ማለታቸው ይህንኑ ሊያስረዳ ይኸው በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። አንብቦ ለመረዳት ለሚፈልግ ሁሉ።
  ታዲያ ይህች ዘዴያቸው፤ አልሰራ ያለችው ኢትዮጵያ ሲመጡ ነበር። የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶች፤ ክርስትና ራስን፤ሀገርን፤ ዕርስትን ለመከላከል የሚደረግን ብሎም ነጻነትን የማስከበር የሚደረግን ትግል ትደግፋለች በማለት ህዝቡን አንድ አደረጉ፤ እና አርበኛውን እያበረታቱ፤ አብረው ዱር በገደል እየዞሩ ጸሎት በማድረግ፤ ሁሉም ለሀይማኖቱ ለሀገሩ እንዲቆም፤እንኳን ሰው እና ምድሪቷም ለአረመኔዎች እንዳትገዛ በማለት የጠላትን ፍጻሜ እና የሀገርን ነጻነት ትንሳኤ አፋጠኑት።
  ለዚህም ነው አቡነ ጴጥሮስ አና አቡነ ሚካኤልን በሰማዕትነት ያረፉት እንጂ…እንደ ሌሎች ዓለም ወንጌላውያን ነን ባዮች ጸሎት እና ዝምታ ይበቃል ቢሉ ጣልያን እነሱንንም አይገድል፤እኝም አሁን የምንናገርበትን የነጻነት አንደበት ባልነበረን።
  ታዲያ ዛሬ ዛሬ እንሰብካለን የሚሉ፤ ሳይገባቸው በአባቶች መንበር የተቀመጡ ፍርሃትን፤ዝምታን፡ ፀሎትን ብቻ በማለማመድ፤የ ጨቃኞችን ዕድሜ እና የህዝቡን መከራ ዘመን ያራዝማሉ።
  ደግነቱ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መቼ ምን መደርግ እንደሚገባው የሚፈቅደው ሥርዓቷ በጽሁፍም፤ በመላው ህዝበ ክርስቲያን ልቡና ውስጥ ተቀምጧል። ለዚህ አስታዋሽ ባንፈልግም፤ ህዝቡን በወንጌል እንመራለን እያሉ ሳይገባቸው የቤተክርስቲያንን አንደበት ይዘው ዝምታን የመረጡ ሁሉ ግን ወየሁላቸው። ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዳግም ታበራለች፤ እነሱ ገን ተዋርደው ያልፋሉ።
  እግዚአብሐር አምላክ ሁሉም በክብር በእኩልነት እንዲኖር እንጂ አንዱ ወገን አሳዳጅ ሌላ ደግሞ ደም እየገበረ እንዲኖር አይፈቅድም። ስለሆነም ሰዎች እግዚአብሔር በተፈጥሮ ላደላቸው ነጻነት እኩልነት የሚያደርጉትን ትግል የፈቅዳል፤ይባርካልም። ቅዱስ ዳዊትን ጨምሮ እሥራኤላውያን እግዚአብሐርን አጋዥ በማድረግ በየዘመኑ ያደረጉት ተጋድሎዎች፤ በሀገራችንም የእግዚአብሐርን ታቦት ተሸክመው አድዋ ላይ አባቶቻችን ያደረጉት ተጋድሎ ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው።
  ታዲያ ዛሬ ከመካከላችን ከመብቀላቸው በስተቀር ከፋሽስት የበለጠ ግፍ በመስራት በቤተክርስቲያን ላይ፤ በምዕመናኖቿ ላይ አስቃቂ ጥቃት ለሚያደርሱም ጠላቶች ዛሬም ታሪካዊው የተዋህዶ ጥሪ ያስተጋባል። በያለህበት፤ በዱር በገደል፤ ለሀይማኖትህ ለሀገርህ፤ለክብርህ የምታደርገው መዋደቅ ከቡር ነው ይላል።
  ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዘረኝነትን አጥብቃ ትቃወማለች። በፋሺስት ጊዜ አማራውን፤ኦሮሞውን፤ትግሬውን፤ ጉራጌውን ወላይታውን… ሁሉንም አንድ አድርጋ ሀገርን ባለድል፤እኛንም ነጻ ህዝቦች አሰኝታናለች። ዛሬም ለሚያስተውል ሁሉ ይህ ጥሪዋ ያስተጋባል።
  ይህች የህዝቦችን የነጻነት ትግል የምትደግፈው ፡ፀት ለጥ ብሎ ከመገዛት ይልቅ ብረት አንስቶ ፤የሌለውም በጦር በጎራዴ ለነጻነቱ የሚሰዋውን የምታከብረው እውነተኛዋ ተዋህዶ ናት፡ ፋና ወጊነቷ ከአፍሪካ እስከ ደቡብ አሜሪካ ያስተጋባው፡ አውሮፓውያኖችን ያሸማቀቀው፡ ግብጾችን፤ሱዳኖችን ፤ሶማልያን አደብ ያስገዛው። ታዲያ ከፋሺስት የበለጠ ዘረኝነትን የሚያስፋፋ፡ ልጇን ገድሎ በሬሳው ላይ የወለደች እናቱን አስቀምጦ የሚደበድብ ፡ ጳጳሳትን ባዕታቸውን ሰብሮ የሚደበድብ፡ ምንም ያማያውቁ ህጻናትን በአልሞ ተኳሽ ደማቸውን ለሚያፈስ፡ ለጭካኔው ልክ ለሌለው ወያኔ ተዋህዶ ዝም ትበል? በፍጹም ዛሬ መንበሯን የቀበሮ ባህታውያን አባ ጵውሎስ፤አባ ማትያስ ፤ እና የዘመናችን አፈ ጮሌ ቃላት አሳማሪ ሰባኪያን መሳዮችተቆጣጥረውት ልሳን አልባ ብትመስልም የተዋህዶ ጥሪ ግን በዝምታም በትውልዱ ያስተጋባል።

  ReplyDelete
  Replies
  1. ወንድሜ ምናልባት አልሰማህ እንደሆን እንጅ ከሁሉም አስቀድሞበደፋሮችና እውነትን ብቻ በያዙ ወንጌላውያን አማኞች እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ደብዳቤ በመጻፍም ሆነ በሚዲያ እየሆነ ያለውን ተቃውመውና እግዚአብሔር ያመለከታቸውን አድርሰዋል። በዚህ ወቅት ደግሞ እንደ አንድ ሀገር ልጆች የጋራ ጠልትን መጋፈጥ እንጅ የሃይማኖት ልዩነትን እያራገቡ ለችግሩ አለመፈታት ተጨማሪ እንቅፋት መሆን አይጠበቅብንም። እግዚአብሔር ለሁላችንም ልቦናችንን ያብራ።

   Delete
 4. Don't go around by talking teret teret. Speak up the truth, but you have no willingness.
  Preaching is business for persons like you.
  The truth of our time does not need middle standers when speak calculated statement so that they can live with whomever staying or coming. The truth needs clear standard. ...we need direct stand like that of Abune Abraham or Ananni Sorri. We don't want smart person, we need innocent and truthful. You are smart, but not smarter than anyone else.

  ReplyDelete
  Replies
  1. dedeb neh!!! you have no any room for logic and understanding!!!
   @daniel kibret I wish you long life God bless you!!!

   Delete
 5. ችግርን በመፍትሔ መፍታትና ችግርን በሌላ ችግር ማለፍ ይለያያሉ፡፡ ችግርን በችግር ካለፍከፈው ጊዜ እየገዛህ ነው፡፡ ችግርን በመፍትሔ ካለፍከው ደግሞ ልብ እየገዛህ ነው፡፡

  ReplyDelete
 6. ችግሮችን ለመጋፈጥ ካልፈለግህ ችግሮችን እያነገሥካቸው ትሄዳለህ›
  ችግርን ካታለልከው መልሶ ይይዝሃል፤ ከተጋፈጥከው ግን ጥሎህ ይሸሻል

  ReplyDelete
 7. ወይ ግሩም ፧ እኛ ኤድመንተን ላይ ቁም ስቅልህን ስናሳይህ ነው የከረምከው፤ በየትኛው ቀን ግዜ አግኝተህ ነው ይህን ሁሉ የምትፅፈው፤ በእውነት እኔ ቢዚ ነኝ የሚለውን ቃል ለራሴ መጠቀም ያሳፍረኛል፤ እግዚአብሔር አገልግሎትህን ይባርክ ። Fish..

  ReplyDelete
 8. Thank you Dn Daniel as always. this will happen to our Government very soon they never try to find a solution to the problem they created,they never prepare them self to exit from a situation like this.if the know the gate they should leave the sit to the next one with their legacy.they will pay back for what they did just like the princess did.even we the people got a heart to mercy them God will judge them because he is a loving dad he also care for each of his children,more than any thing he is a fairly judge.God bless Ethiopia and our nation for ever.

  ReplyDelete
 9. Great Idea!! thank you dani.

  ReplyDelete
 10. Don't go around by talking teret teret. Speak up the truth, but you have no willingness. 
  Preaching is business for persons like you. 
  The truth of our time does not need middle standers when speak calculated statement so that they can live with whomever staying or coming. The truth needs clear standard. ...we need direct stand like that of Abune Abraham or Ananni Sorri. We don't want smart person, we need innocent and truthful. You are smart, but not smarter than anyone else.

  WHO ARE YOU TALKING ABOUT. I DON'T UNDERSTAND.

  ReplyDelete
 11. i love you dani God bless and save you.

  ReplyDelete
 12. ችግርን በመፍትሔ ካለፍከው ደግሞ ልብ እየገዛህ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሁላችንም ልቦናችንን ያብራ።

  ReplyDelete