የኢራቅ ኩርዶች እንዲህ ይተርካሉ፤
አንዲት የልዑል ልጅ ነበረች፡፡
አንድ የምታፈቅረው ልጅም ነበረ፡፡ ታድያ ከአንድ የቤተ መንግሥቱ ጠባቂ ጋር ትመካከርና ይህንን ፍቅረኛዋን ክፍሏ ድረስ ታስገባው
ነበር፡፡ የቤተ መንግሥቱ ጥበቃ የተወሰነ ገንዘብና ልብስ ትሰጠው ስለነበር በደስታ ምሥጢሩን ይደብቅ ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን ያልታሰበ
ነገር ተከሰተ፡፡ ልዕልቲቱና ፍቅረኛዋ አፕል ቆርጠው እየተጫወቱ ይበሉ ነበር፡፡ ሁለቱም አፋቸውን ከፍተው የአፕሉን ቁራጭ አንዳቸው
ወደሌላቸው አፍ ወርውሮ የማስገባት ጨዋታ ነበር የሚጫወቱት፡፡
እየተሳሳቁ የአፕል ቁራጭ ወደየአፎቻቸው
ሲወረውሩ ልዕልቲቱ የወረወረችው የአፕል ቁራጭ ድንገት የፍቅረኛዋ ጉሮሮ ውስጥ ተቀረቀረ፡፡ ውኃ ብትሰጠው፣ ማጅራቱን ብትመታው ሊወርድለት
አልቻለም፡፡ ኡኡ ብላ እንዳትጮህ ልጁ ማነው? እንዴትስ መጣ ? ለሚለው ጥያቄ የምትመልሰው የላትም፡፡ በዚህ መካከል ልጁ ትንፋሽ
አጥሮት ሞተ፡፡