Tuesday, August 2, 2016

ደብተራ

click here for pdf

 


ከአንዳንድ ሰዎች ጋር የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት በተመለከተ ስንነጋገር ‹ደብተራ የጻፈው› ማለት ይቀናቸዋል፡፡ ይሄ ንግግራቸው ከሁለት ስሕተቶች የመነጨ ነው፡፡ አንደኛው ስለ ደብተራ ካለማወቅ ሲሆን ሁለተኛው ስለ መጻሕፍቱ ካለመረዳት የሚመጣ ነው፡፡ ‹ደብተራ› የሚለው ቃል ጥሬ ትርጉሙ ‹ድንኳን› ማለት ነው፡፡ ይህም ቢሆን ‹ሐይመት› ከሚለው ቃል ፍች ይለያል፡፡ ‹ሐይመት› ለማንኛውም አገልግሎት የሚውለውን ድንኳን ሲያመለክት ‹ደብተራ› ግን በዋናነት ለቤተ መቅደስነት የሚውለውን ድንኳን ያመለክታል፡፡ ‹ደብተራ ኦሪት› - የብርሃን ድንኳን እንዲል፡፡ 

በመካከለኛው ዘመን መጀመሪያ ላይ ነገሥታቱ ከሀገር ሀገር ሲጓዙ አብራቸው የምትጓዝ የጸሎት ታቦት ነበረቻቸው፡፡ ለዚህች ታቦት የምትሆን ድንኳን አዘጋጁ፡፡ ታቦቷ በቤተ መንግሥት ግቢ ተተክላ ትቀመጥና ንጉሡ ከቦታ ወደ ቦታ ሲንቀሳቀስ ተነቅላ ትንቀሳቀስ ነበር፡፡ በዚህች የቤተ መንግሥት የድንኳን መቅደስ ውስጥ ለአገልግሎት የሚመረጡት በዕውቀታቸውና በንጽሕናቸው የተመሰገኑ ነበሩ፡፡ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ አባት በዚህች ድንኳን ከሚያገለግሉ ካህናት ወገን ነበረ፡፡ አባ ጊዮርጊስም በዚህች የድንኳን ቤተ መቅደስ ውስጥ አገልግሏል፡፡ በዚህች ቤተ መቅደስ የሚያገለግሉት ካህናት አንዱ ሥራቸው ንጉሣውያን ቤተሰቦችን ማስተማር ስለነበር አባ ጊዮርጊስ የዐፄ ዳዊትን ልጆች ሲያስተምር ነበር፡፡ 

በዚህች የቤተ መንግሥት መቅደስ ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናት ‹በማደሪያው አዳሪው፣ በአዳሪውም ማደሪያው ይጠራል› በሚባለው መሠረት በደንኳኗ (በደብተራ) እነርሱም ‹ካህናተ ደብተራ› እየተባሉ መጠራት ጀመሩ፡፡ ቆይቶም ‹ካህናት› የሚለው ስም ተጎርዶ ‹ደብተራ› እየተባሉ ብቻ ተጠሩ፡፡ ከመነሻው ደብተራ ማለት በዕውቀትና በሕይወት ተመርጦ የቤተ መንግሥቱን የደብተራ ቤተ መቅደስ ለማገልገል የተሰየመ ሊቅ ካህን ማለት ነበር፡፡ 
ካህናተ ደብተራ ከንጉሡ ጋር የተሻለ ቀረቤታ በማግኘታቸው በኋላ ዘመን የርስትና የሹመት ተካፋዮች ሆኑ፡፡ ይህን ላለማጣት ሲሉም አንዳንዶቹ ቀኖናው ከሚያዛቸው ይልቅ ንጉሡ የሚያዛቸውን መቀበል ጀመሩ፡፡ በዚህ የተነሣም ካህናተ ደብተራ ለንጉሡ የሚያደሉና ለእውነት የማይቆሙ እየሆኑ በመምጣታቸው እንደነ አባ በጸሎተ ሚካኤል ያሉ አበው በድፍረት ወቅሰዋቸው ነበር፡፡ በኋላ ዘመን ደግሞ አንዳንዶቹ ከማኅበረሰቡ በተሻለ የተማሩ መሆናቸውን በመጠቅም ጥንቆላና አስማት እንችላለን በማለታቸው ‹ደብተራ› የሚለው ስም የምሁርነት ስም መሆኑ ቀርቶ ከጥንቆላና መተት ጋር የተያያዘ ስም እየሆነ መጣ፡፡

‹ደብተራ› የሚለው ስም አጠፋፍ ›ሐኪም› ከሚለው ስም አጠፋፍ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ‹ሐኪም› የሚለው ስም ትርጉሙ ‹ብልህ፣ ጠቢብ› ማለት ነው፡፡ ሙያን ሳይሆን ጥበብን የሚመለከት ነበር፡፡ ‹ወስመ መምህሩ ዘመሀሮ ጥበበ አርስጣጣሊስ ሐኪም› ይላል፡፡ ‹ጥበብን ያስተማረው መምህሩ ጠቢቡ አሪስጣጣሊስ ነው› ማለቱ ነው፡፡ በዐረብኛም ሆነ በእብራይስጥ ትርጉሙ ይሄው ነው፡፡ የእስልምና ወርቃማው ዘመን በሚባለው ጊዜ ‹ሐኪም› ማለት በእስልምና ሃይማኖት፣ በሳይንስ፣ በመድኃኒትና በፍልስፍና ሁለገብ ዕውቀት ያለው ጠቢብ ሰው ስያሜ ነበር፡፡ በዕብራይስጥ ቋንቋም ሁለገብ ዕውቀት ላለው የሃይማኖት መሪ የሚሰጥ ስም ነው - ሐኪም፡፡
በሀገራችን ‹ሐኪም› የሚለው ስም ለጠቢብ የሚሰጥ ስም ነበረ፡፡ በኋላ ግን ባሕላዊ መድኃኒት ለሚያውቅ ባለሞያ ሁሉ መሰጠት ተጀመረ፡፡ በየጋዜጣው ዛሬ የባሕል መድኃኒት ዐዋቂዎች ‹ሐኪም እገሌ› እያሉ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁት ለዚህ ነው፡፡ ዘመናዊ ሕክምና ሲጀመርም በሞያው የተሰማሩት በዚህ ስም ተጠርተዋል፡፡ ሐኪም ወርቅነህን ማስታወስ ለዚህ ይረዳል፡፡ አሁን አሁን ብዙዎቹ የባሕል መድኃኒት ዐዋቂዎች ይህንን ስም ስለሚጠቀሙት ስሙ እንደ ደብተራ ሁሉ ከጥበብና ሞያ ይልቅ ከጥንቆላ ጋር የመያያዝ ዕጣ እየገጠመው ነው፡፡

የደብተራም ዕጣው እንዲህ ነው የሆነው፡፡ ‹ዐዋቂ፣ ጠቢብ፣ የተመረጠ› ነበር ትርጉሙ፡፡ በኋላ ግን ግብር ስምን ያጠፋልና የአንዳንድ ‹ደብተሮች› ሥራ ስሙን አጠፋው፡፡ ያም ቢሆን ግን በነባሩ ማኅበረሰባችን ደብተሮች የተሻለ የትምህርት ደረጃ የነበራቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ እነ ደብተራ ዘነብንና እነ ደብተራ አሰጋኸኝን ከቀድሞው፣ እነ ደብተራ ኅሩይ ወልደ ሥላሴንና እነ ደብተራ ዮፍታሔ ንጉሤን ከቅርቡ ማስታወስ ይህንን ያጎላዋል፡፡

እነዚህ ደብተሮች አንዳንድ ጊዜ የሕይወት መሰናክል ቢገጥማቸውም በዕውቀታቸው ግን የሚታሙ አይደሉም፡፡ አንዳንዴም ‹ዕውቀት ያስታብያል› እንዲል መጽሐፉ ወደ መሰናክሉ የሚወስዳቸው ዕውቀታቸው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ታሪከ ነገሥቱን፣ ዜና መዋዕሉንና ለቤተ መንግሥቱ የቀረቡ ድርሳናቱን የመጻፉ ዕድል የደብተሮች ሲሆን ከገዳማዊ ሕይወት ጋር የተገናኙ የጸሎት፣ የዝማሬ፣ የገድል፣ የመልክዕና የውዳሴ ድርሳናትን የመጻፍ ዕድል ደግሞ የገዳማውያኑ ሊቃውንት ነበረ፡፡ ሁለቱንም ሊቃውንት አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር በዘመኑ ዕውቀት የበለጸጉ መሆናቸው ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ቤተ መንግሥቱንም ገዳማዊ ሕይወቱንም የሚያውቁ ሊቃውንት ይገኛሉ፡፡ መነሻቸው አንደኛው ይሆንና ወደሌላው ይሄዳሉ፡፡ ከገዳሙ ወደ ቤተ መንግሥቱ (ልክ አንደ አባ ባሕርይ) ወይም ደግሞ ከቤተ መንግሥቱ ወደ ገዳሙ (እንደ ቅዱስ ያሬድ)፡፡

የቀድሞ ጸሐፍት አያሌ መጻሕፍትን ማገላበጥ ይወዱ ነበር፡፡ ከግራኝ ጦርነት ጥቂት ቀደም ብሎ ወደ ኢየሩሳሌም የሄደው የደብረ ብሥራት ዜና ማርቆስ መነኮስ አባ በኃይለ ማርያም በኢየሩሳሌም አደባባይ ባደረገው ክርክር ወቅት ከ30 በላይ መጻሕፍትን መጥቀሱን ስናይ ይህንን አባባል ያስረግጠዋል፡፡ በጎንደር ዘመን የነበሩት መምህር ኤስድሮስም በጣና ገዳማት ገብተው እስከ 3000 የሚደርሱ መጻሕፍን መመልከታቸውን የጉባኤ ቤት ትውፊት ይነግረናል[1]፡፡ 

የቀድሞ ጸሐፍትን የዕውቀት ልክ ሊነግሩን ከሚችሉ መረጃዎች መካከል የአባ ባሕርይ ‹መዝሙረ ክርስቶስ› የተሰኘው ድርሰት አንዱ ነው፡፡ ባሕርይ በዐፄ ርጸ ድንግልና ከዚያም ጥቂት ቀደም ብለው የነበሩ ሊቅ ናቸው፡፡ የተወለዱት በ1528 ዓ.. ነው፡፡ መጀመሪያ የነበሩት ጋሞ ውስጥ በአንድ ቤተ ክርስቲን አለቃ ሆነው ነው(የብርብር ማርያም አለቃ ነበሩ የሚሉ አሉ)፡፡[2] በኋላ ግን ኦሮሞዎች በአካባቢው እያየሉ ሲመጡ ወደ ጎንደር መጥተዋል፡፡ አባ ባሕርይ መዝሙረ ክርስቶስ የተሰኘውን በግጥም የቀረበ ድርሰት ያዘጋጁት ለመዝሙረ ዳዊት መመዘኛ (መለኪያ እንዲሆን) በመዝሙረ ዳዊቱ ልክ ነው፡፡ ዓላማቸውም መዝሙረ ዳዊትን የሚገለብጥ ሰው የመዝሙረ ዳዊቱን ልክ በእርሳቸው መዝሙረ ክርስቶስ በመለካት ሳያጓደል እንዲገለብጥ ለማድረግ ነው፡፡ ያዘጋጁት በ46 ዓመታቸው በ1574 ዓ.. መሆኑ በዚያው በመጽሐፉ ላይ ተገልጧል[3]፡፡ 

አባ ባሕርይ ይህንን መጽሐፍ ሲያዘጋጁ ምንጭ የሆኗቸውን መጻሕፍት አስቀድመው በመቅድሙ ላይ አስፍረዋል፡፡ ማስፈር ብቻም ሳይሆን ከያንዳንዱ መጽሐፍ ምን ያህል ጥቅሶችን እንደወሰዱም ይገልጣሉ፡፡
1.      ከኦሪት ዘልደት - 17
2.     ከኦሪት ዘጸአት - 17
3.     ከኦሪት ዘሌዋውያን  - 7
4.     ከኦሪት ዘኊልቈ - 2
5.     ከኦሪት ዘዳግም - 11
6.     ከመጽሐፈ መሳፍንት - 2
7.     ከመጽሐፈ ኦሪት ዘሆሴዕ - 1
8.     ከመጽሐፈ ኩፋሌ - 2
9.     ከመጽሐፈ ሄኖክ - 7
10.   ከመጽሐፈ ኢዮብ - 1
11.     ከመጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ - 7
12.    ከመጽሐፈ ነገሥት ዳግማዊ - 2
13.    ከመጽሐፈ ነገሥት ሣልስ - 9
14.   ከመጽሐፈ ነገሥት ራብዕ - 2
15.    ከመዝሙረ ዳዊትና ከሰሎሞን ምሳሌያት- 8
16.   ከመጽሐፈ ተግሣጽ- 3
17.    ከመጽሐፈ ጥበብ - 17
18.   ከመጽሐፈ መክብብ - 8
19.   መኃልየ መኃልይ - 2
20.  ከመጽሐፈ ሲራክ - 10
21.    ከትንቢተ ኢሳይያስ - 18
22.   ከትንቢተ ኤርምያስ - 7
23.   ከትንቢተ ሕዝቅኤል - 5
24.  ከትንቢተ ዳንኤል - 13
25.   ከመጽሐፈ እዝራ - 4
26.  ከመጽሐፈ መቃብያን - 2
27.   ከራእየ ኤልያስ - 1
28.  ከትንቢተ ሆሴዕ - 3
29.  ከትንቢተ አሞጽ - 2
30.  ከትንቢተ ሚክያስ - 3
31.    ከትንቢተ ኢዩኤል - 1
32.   ከትንቢተ ዮናስ- 1
33.   ከትንቢተ ዕንባቆም - 2
34.  ከትንቢተ ዘካርያስ - 4
35.   ማቴዎስ፣
36.   ማርቆስ፣
37.    ሉቃስ፣
38.   ዮሐንስ (ከአራቱ ወንጌላውያን በድምሩ) - 103
39.  ከመቅድመ ጳውሎስ - 1
40.  ከሮሜ መልእክት - 27
41.   ከቀዳማዊ ቆሮንቶስ - 10
42.  ከዳግማዊ ቆሮንቶስ መልእክት - 7
43.  ከገላትያ መልእክት - 7
44.  ከኤፌሶን መልእክት - 10
45.  ከፊልጵስዩስ መልእክት - 2
46.  ከቆላስይስ መልእክት - 7
47.  ከቀዳማዊ ተሰሎንቄ መልእክት -  2
48.  ከዕብራውያን መልእክት - 15
49.  ከያዕቆብ መልእክት - 7
50.  ከአንደኛው የጴጥሮስ መልእክት - 7
51.    ከሁለተኛው የጴጥሮስ መልእክት - 4
52.   ከቀዳማዊ የዮሐንስ መልእክት
53.   ከዳግማዊ ዮሐንስ መልእክት
54.  ከሣልሳዊ ዮሐንስ መልእክት (በድምሩ ከሦስቱ መልእክቶች)  - 5
55.   ከሐዋርያት ሥራ - 7
56.  ከዮሐንስ ራእይ - 9
57.   ከመጽሐፈ ሲኖዶስ - 2
58.  ከዲድስቅልያ - 8
59.  ከመጽሐፈ ኪዳን- 15
60.  ከመጽሐፈ ቀሌምንጦስ - 1
61.   ከባስልዮስ - 12
62.  ከአትናቴዎስ ሐዋርያዊ - 9
63.  ከሃይማኖተ አበው - 3
64.  ከዮሐንስ አፈወርቅ - 7
65.  ከመጽሐፈ ሠለስቱ ምእት ርቱዐነ ሃይማኖት- 7
66.  ታሪክ - 7
67.  ፍትሐ ነገሥት - 1
68.  ጎርጎርዮስ - 2
69.  ኤጲፋንዮስ - 2
70.  ያዕቆብ ዘእልበረዲ - 2
71.    መጽሐፈ ባሕርይ - 2
72.   ረድእ ወመምህር - 1
73.   ስንክሳር - 7
74.  ኤፍሬም ሶርያዊ - 11
75.   ያዕቆብ ዘሥሩግ - 1
76.  ድርሳነ አባ ብንያሚ - 3
77.   ድርሳነ አባ ሕርያቆስ - 3
78.  ሳዊሮስ ዘእስሙናይ - 11
79.  አረጋዊ መንፈሳዊ - 2
80.  ፊልክስዮስ - 2
81.   ተአምረ ኢየሱስ - 4
82.  ዜና አይሁድ - 1
83.  ፈላስፋ - 7
84.  ከሊላ ወድምና - 3
85.  ፊሳልጎስ - 5
86.  በረላም - 3
87.  ዜና አበው - 5
88.  ተአምረ እግዝትነ - 1
89.  መጽሐፈ ምሥጢር - 1
90.  አክስማሮስ - 2 

መውሰዳቸውን ይነግሩናል፡፡ እነዚህን መጻሕፍትም በጠቀሱባቸው ቦታዎች ላይ ሲደርሱ በጎን ኅዳግ ላይ ምንጮቹን አሥፍረዋቸዋል፡፡   

አባ ባሕርይ ለማስረጃነት የጠቀሷቸውን መጻሕፍት ብዛትና ዓይነት በአራት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡
1.      ከብሉይና ሐዲስ
2.     ከሊቃውንት መጻሕፍት
3.     ከጠቢባን መጻሕፍትና
4.     ከታሪክ መጻሕፍት ናቸው፡፡ 

አባ ባሕርይ በመቅድማቸው ላይ ‹ለዚህ ድርሳነ መዝሙር የሚሆኑ ምስክሮችን ከመጻሕፍተ ኦሪት፣ ከወንጌላውያን፣ ከነቢያት ትንቢት፣ ከሐዋርያት መልእክታት፣ ከሊቃውንት ድርሳናት፣ ከጥንት ጠቢባን ምሳሌዎች ወስጃለሁ፡፡ በቃላቸው ጣዕም የኔ ንግግር ጣዕም እንዲያገኝ ብዬ፡፡ የያንዳንዳቸው ኅብር እንደ ዕንቁዎች ጌጥ እንዲሆን፡፡ የአንድ ኮከብ ብርሃን የሰማይን ሰፊ ሰሌዳ አያስጌጠውም፡፡ የአንድ ዕንቁ ውበትም ብቻውን አንድን ቤት አያሳምረውም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የአንድን ሰው መጽሐፍ ብቻ ማንበብ መጽሐፍን አያሳምረውም፡፡ ነገርም በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ካልሆነ በቀር ጸንቶ አይቆምም[4]› ይላሉ፡፡ በዚህ አባባላቸውም አንድ መጽሐፍ ለማዘጋጀት አያሌ መጻፍትን ማገላበጥና ምስክር ማበጀት አስፈላጊ መሆኑን አጽንተው ተናግረዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት የደረሷቸው እንዲህ በላዕያነ መጻሕፍት የሆኑ ደባትር ናቸው፡፡ 
[1] በዚህ ረገድ እኔ ያየኋቸው ሊቅ አቡነ ዘካርያስ ናቸው፡፡ ከ5 ዓመታት በፊት በአሜሪካ ቺካጎ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተደርጎ በነበረ ጉባኤ ላይ አቡነ ዘካርያስ ባስተማሩት የ30 ደቂቃ ትምህርት ውስጥ ብሉይና ሐዲሱ ሳይቆጠር ከሊቃውንትና ከጠቢባን ብቻ 30 መጻሕፍትን መጥቀሳቸውን በአድናቆት ተመልክተን ነበር፡፡ መጽሐፈ በርለዓምን በአደባባይ ሲጠቅሱት ያየሁት አቡነ ዘካርያስንና መምህር ደጉ ዓለም ካሣን ነው፡፡
[2] ምናልባ ብርብር ማርያም( ጌታቸው ኃይሌ፣ የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፣1995፣ 35)
[3] የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፣ 46
[4] EMML 3473 (መዝሙረ ክርስቶስ), 3a

16 comments:

 1. Good read Daniye deep as well.Thank you once again for you and for your family Keep up the good work Boss.

  ReplyDelete
 2. ‘’እዩት ደብተራ ቅኔ ሲመራ’’ ሲባል የሊቅነት ደረጃን ያሳያል፡፡ይሁን እንጂ ከስንዴ መሐል እንክርዳድ እንደማይጠፋ አንዳንድ የቤተክህነት ትምህርት ወስደው ቤተክርስቲያንን ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ እንደይሁዳ በሰይጣን የተወሰዱ አሉ፡፡እነርሱም ጠንቅዋይ የሚል ስያሜ ያገኙ ሲሆኑ የጥንቆላ መጽሐፍ አላቸው፤እኔም አንዱ ጠንቋይ ጋ ሄጄ የታዘብኩት ነገር ነው ሰይጣንን በሌሊት ጠርተው መብራት ጠፍቶ በጨለማ ውስጥ ሰዎች በአካል ከመጣው ሰይጣን(ዛር) ጋር እንዲነጋገር ያደርጋሉ እኔም ያለፍኩበት ተሞክሮ ነው፤ይህ ዓይነቱ ደብተራ አደገኛና ሰይጣንን በሰው ላይ የሚያቆራኝ ሲሆን ለማስመሰል ቤ/ክ ሄዶ ይጸልያል፡፡እኔ ግን እዚያ በመሄዴ ብዙ ዘመን በሽተኛ ሆኜ በቅዱሳን ጸሎት አሁን እየተሻለኝ ነው፡፡ ስለዚህ ደብተራ የሚለው ስም ለጠንቋይ ተሰጥቶ የቀረው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
  በጥንቆላ የብዙ ሰው ህይወት እንደሚሰናከል በየጸበሉ ከምናየው በተጨማሪ በየገድላትና ድርሳናት ተጽፏል፡፡ለምሳሌ በነገረ ማርያም ላይ መጥቁል የሚባል አጋንንትን የሚልክ ጠንቋይ÷በአቡነ ተ/ሃይማኖት ገድል ላይ ያሉት÷በሐዋርያት ሥራ ላይ÷ወዘተ. በየዘመኑ በአጋንንት ወጥመድ ተይዘው ሌሎች ሰዎችን በሚያጠፉ ሰዎች ይህ ሥራ እስከምጽአት ሲሠራ ይኖራል፡፡ይህን የሰይጣን ሥራ የምናሸንፋው ተግተን በመጸለይ ነው፤ለምሳሌ በስንክሳር መጽሐፍ የተጻፈው ዮስቴና የተባለች የአንዲት ድንግል ታሪክ ስናይ እንድ ሰው ውበ~ን አይቶ ለማግባት አስቦ ሊያገኛት ባለመቻሉ ጠንቋይ ጋ ሄዶ አጋንንትን ሲልክባት ልጅ~ በገዳም ውስጥ በጸሎት ተወስና ስለምትኖር ሰይጣን ሊጠጋት አልቻለም፡፡ስለዚህ ሰይጣን የወሰደው አማራጭ መንገድ ዮስቴናን መስሎ በምትሐት ለሰውዬው በመተየት ለለማስመሰል ወደሰውየው ሄደ፤ሰውየውም በምትሐት የተገለጸለትን ሰይጣን እውነት መስሎት እመቤቴ ዮስቴና መጣሽ ብሎ ሊቀበል ሲል ሰይጣኑ ‘ዮስቴና’ የሚለውን ስም ሲሰማ እንደጢስ በኖ ጠፋ፡፡ከዚህ የምንረዳው በጸሎት የተጋ ሰው ከሰይጣን ሥራ የሚያመልጥ ብቻ ሳይሆን ስሙ እንኳን አጋንንትን የማባረር ኃይል እነደሚኖረው ነው፡፡

  ReplyDelete
 3. በጣም ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡ ብዙዎቻችን የደብተራ ትርጉምን ሳንረዳ ያልተገባ ትርኋሜ ለምንጥ ሰዎች በቂ ምላሽ ይሰጣል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ስለሆነም ከዚህ ጽሑፍ ብዙዎቻችን ከስህተታችን እንደምንማርበትም ተስፋ አለኝ፡፡ ዲ.ዳንኤል ይህን ትውልድ ለማስተማር እንደተጋህ ሁሉ፣ ዋጋህን እግዚአብሔር ይክፈልህ፡፡ ረጅም ዕድሜና ጤና ይስጥህ፡፡

  ReplyDelete
 4. በዚህ ሰዓት ስለዋልድባ ብትፅፍ ደስ ይለኝ ነበር::

  ReplyDelete
  Replies
  1. http://www.danielkibret.com/2012/03/blog-post_18.html
   @ Mehari he wrote about Waldba March 18,2012.
   No need to repeat.

   Delete
 5. ዲ.ዳንኤል ዋጋህን እግዚአብሔር ይክፈልህ፡፡ ረጅም ዕድሜና ጤና ይስጥህ፡፡

  ReplyDelete
 6. ግሩም እይታ ነው ጌታ ዘመንህን ይባርክልህ!!ሠዎች ከእውቀት በታች ሢሆኑ ደብተራ በሚል ብሂል አለመቀበልን ይመርጣሉ!!

  ReplyDelete
 7. ዲ. ዳንኤል ጥሩ መረጃ ነው፡ ነገር ግን አሁን እንዳሸን በዝተው ህዝቡን እያታለሉ (አውቀውም ይሁን ሳያውቁ፡ ብዙዎቹ ሳያውቁት ነው) በመናፍስት የሚጨርሱትን ደብተራዎች በመለየት የቤተ ክርስቲያን ሚና ምን መሆን እንዳለበት ሓሳብ ብትሰጥልን የበለጠ ይሆናል፡፡ ይህንን ጉዳይ ደፍሮ የሚናገር አባት መጥፋቱ ያሳዝናል በመሆኑም ከአስማት ሥራ ጋር የተያያዙ የሚቸበቸቡት መጽሓፍት መለየት ቢቻል በበለጠ ደግሞ እውቀት እየመሰላቸው ለሚታለሉት አገልጋዮች ጠቃሚ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ቁልፍ ቦታ ላይ ተቀምጠው ለቤተ ክርስትያንና ለሀገር ሳንካ የሚሆኑ አባቶች የበዙትና ህዝባችን በረከት አልባ የሆነው በዚህ መንገድ የመጠለፍ አንዱ ምክንያት ይመስለኛል፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. ወንድሜ/እህቴ አስማት ማለት ምንድን ነዉ;

   Delete
 8. May God be with you,Daniel.Kibret

  ReplyDelete
 9. ብዙ ኃላፊነት እንድንጭንብህ የሚያደርግ የምርምር ስራዎችን እያቀረብክ ነዉ::ዲ.ዳንኤል አገራችን ካንተ ብዙ ትጠብቃለች እግዚአብሔር ረድቶህ የምትወደዉን ስራ እየሰራህ ነዉና በዚሁ ቀጥል:: በአሁኑ ግዜ ብዙ የኛ ነገሮች እየተዘነጉና እየተተዉ ስለሆነ እባክህ ብዙዉ የአገራችን ታሪክ በቤተክርስቲያናችን ጉያ ዉስጥ ስላላለ እየፈለክና እየቆፈርክ ለልጆቻችን አስተላልፍልን::እግዚያብሔር ዕድሜና ጤና እንዲሰጥህ እመኝልሃለሁ አመሰግናለሁ::

  ReplyDelete
 10. ASTEHATSEBKU TOMARIKE ESME YIKEWUN SEB KEME HALO BEWUSTE SEMAY....

  ReplyDelete