ሀገር ሰላም እንድትሆን፤ ሰላም
ሆናም በብልጽግና ጎዳና እንድትራመድ ከታሰበ ሁለት ነገሮች የግድ ያስፈልጓታል፡፡ ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥትና መንግሥትን የሚያዳምጥ
ሕዝብ፡፡ ማዳመጥ ከመስማት ይለያል፡፡ መስማት ጆሮ ለተፈጠረለት ሁሉ የሚቻል ነው፡፡ ይህን ጽሑፍ ስናነብ እንኳን ስንትና ስንት
ድምጾችን ፈልገንም ሳንፈልግም እንሰማለን፡፡ ማዳመጥ ግን ሦስት ነገሮችን ይፈልጋል፡፡ ይሁነኝ ብሎ መስማት፣ ሰምቶ ማስተዋል፣ አስተውሎም
መመለስ፡፡
ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት ስንልም
ይሁነኝ ብሎ ሕዝቡን የሚሰማ፣ ሰምቶ ሕዝቡ ምን እንዳለው የሚያስተውልና ከዚያም አስተውሎ መልስ የሚሰጥ መንግሥት ማለት ነው፡፡
ለሕዝብ የመናገር ነጻነት ብቻውን ምንም አያደርግለትም፡፡ የመደመጥ መብት ከሌለው በቀር፡፡ ሰሚ ከሌለ እንኳን ሕዝብ ፈጣሪ አይናገርም፡፡
ቢናገርም ጥቅም የለውም፡፡ ለዚህም ነው ሊቃውንቱ እንደሚነግሩን መላእክት እስኪፈጠሩ ድረስ ፈጣሪ ፍጥረታትን በአርምሞ ብቻ የፈጠረው፡፡
ለምን? ቢሉ ሰሚ ሳይኖር መናገር ምን ያደርጋል ብሎ፡፡ መላእክት ከተፈጠሩ በኋላ ግን ‹ብርሃን ይሁን› ብሎ ሲናገር እንሰማዋለን፡፡
አሁን ሰሚ ተገኝቷልና መናገር ዋጋ አለው፡፡
ሕዝብም መናገሩ ብቻ ጥቅም የለውም፡፡
የተናገረውን የሚያዳምጠው መንግሥት ያስፈልገዋል፡፡ ሕዝብ የሚያዳምጠው ሲያጣ ጩኸቱን የሚያዳምጠው አጥቶ ቤቱ እንደተዘረፈበት ውሻ
‹ነባህነ ነባህነ ከመ ዘኢነባህነ ኮነ
- ጩኸን ጩኸን እንዳልጮኽን ሆን› ብሎ አይቀመጥም፡፡ ራሱን በራሱ ማዳመጥ ይጀምራል፡፡
የልቤን መከፋት ሆዴ እያዳመጠ
ሊመረው ነው መሰል ነገር አላመጠ
የሚል የቆለኛ ፉከራ አለ፡፡