Thursday, July 7, 2016

ኤጲደቅስዮፊሳልጎስ የተሰኘዉና በ2ኛው መክዘ በእስክንድርያ ተጽፎ በ5ኛው መክዘ ወደ ግእዝ የተተረጎመው መጽሐፍ ‹ኤጲዲቅስዮ› ስለሚባል ዛፍ ይተርካል፡፡ ይኼ በሕንደኬ ሀገር የሚገኝ ዛፍ ሁለት ጠባይ አለዉ፡፡ አርጋብ የዛፉን ፍሬ ስለሚወዱት በእርሱ ላይ እየተሰበሰቡ ይመገቡታል ይላል መጽሐፉ፡፡ እንደ እባብ ላሉ እንስሳት ደግሞ ጥላዉ እንኳን ከነካቸዉ ይሞታሉ፡፡ ነገር ግን ለእባቦቹ ሌላ ዘዴ ለግሷቸዋል፡፡ ርግቦችን ለማጥመድ የሚመጡት እባቦች የፀሐይ ጥላ ባላረፈበት አቅጣጫ፣ ወይም ፀሐይ ስትጠፋ ወይም ደግሞ ደመና ሲጋርድ ወደ አካባቢዉ ይመጡና ያደፍጣሉ፡፡ ዛፉን ርግቦችም እባቦችም ይፈልጉታል፡፡  
 
ይህ ዛፍ በላቲኑ አምቢዴክትረስ(ambidextrous) ይባላል፡፡ ‹አምቢ› ማለት ‹ሁለቱም› ማለት ሲሆን ‹ደክስተር› ማለት ደግሞ ‹ትክክል› ማለት ነዉ፡፡ ‹አምቢዴክትረስ› ማለትም ‹በሁለቱም በኩል ትክክል የሆነ› ማለት ነዉ፡፡ የእንግሊዝኛው ቃል መጀመሪያ ተግባር ላይ የዋለዉ በሕግ ሰዎች ዘንድ ነዉ፡፡ አንተም ልክ ነህ፣ አንተም ልክ ነህ ብሎ ከከሳሽም ከተከሳሽም ወገን ጉቦ ለሚቀበል ዳኛ ነበር ቃሉ ጥቅም ላይ የዋለዉ፡፡ 
 


ርግቦቹ ወደ ኤጲደቅስዮ ዛፍ ሲመጡ ሁለት ነገር ተስፋ አድርገዉ ነዉ፡፡ በአንድ በኩል የዛፉን ፍሬ ጣፋጭነት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የርግቦች ዋና ጠላት የሆነዉ እባብ የዛፉን ጥላ በመፍራት ወደ አካባቢዉ አይደርስም ብለዉ በማመን፡፡ ኤጲደቅስዮ ዛፍ ግን ለርግቦቹ ምግብ እንደሚሆነዉ ሁሉ ለእባቦቹም የምግብ ምንጭ ነዉ፡፡ እባቦቹ እንዴት ከዛፉ ጥላ ማምለጥ እንደሚችሉ ጠንቅቀው ያዉቃሉ፡፡ 

ፀሐይ በምሥራቅ ስትወጣ በምሥራቅ፣ በምዕራብም ስትጠልቅ በምዕራብ ይመጣሉ፡፡ ያንንም ካልቻሉ እስክትገባ ጠብቀው ከች ይላሉ፡፡ ኤጲደቅስዮ ለርግብም ለእባብም የሚሠራ ዛፍ ነዉ፡፡ 
 
አሁን አሁን በሀገራችን አስቸጋሪዉ አሠራር እንደ ኤጲደክስዮ ዛፍ ለሁለቱም ወገን ለመሥራት የሚጥረዉ አሠራራችን ነው፡፡ ለሕጋዊዉም ለሕገ ወጡም፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ቤቶችን በማፍረስና ባለማስፈረስ በተፈጠረ ግብ ግብ የሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ እጅግ አሳዛኝ ነዉ፡፡ እነዚህ የፈረሱ ቤቶች እንደ ሜክሲኮ የድንበር መተላላፊያ ዋሻ ምድር ውስጥ፣ እንደ ንጉሥ ሕዝብ ናኝ የምኞት ቤተ መንግሥት አየር ላይ የተሠሩ ቤቶች አይደሉም፡፡ በዚሁ በከተማችን ምድር ላይ የተሠሩ ናቸዉ፡፡ እንደ ታዴዎስ እርሻ በአንድ ቀን አልበቀሉም፡፡ ሲቆፈሩ፣ ሲገነቡ የኖሩ ናቸዉ፡፡ አካባቢዉ እንደ አንታርክቲካ መስተዳድር አልባ አይደለም፡፡ ክፍለ ከተማና ወረዳ አለዉ፡፡ ታድያ ለመሆኑ እነዚህ ሁሉ ቤቶች እንዴት ሊሠሩ ቻሉ? ይህንን ያህል ዘመንስ እንዴት ሊቆዩ ቻሉ? አነዚህ ሰዎች በአካባቢው ስብሰባ ሲኖር ሲጠሩ፣ መዋጮ ሲኖር ሲያዋጡ፣ ምርጫ ሲኖር ሲመርጡ የኖሩ ናቸዉ፡፡ 
 
ችግሩ ያለዉ እንደ ኤጲደቅስዮ ዛፍ ለሁለቱም ከሚሠሩ አካላት ነዉ፡፡ ነዋሪዎቹ ቤቱን ሲሠሩ አይተዉ አንዳላዩ በማለፍ ጥቅሙን ሲጋሩ የነበሩ፤ ምናልባትም ደግሞ በድብቅ እየፈቀዱ ገንዘብ ሲቀበሉ የኖሩ፡፡ በጊዜው ሕጉን ከማስከበርና ‹ይሆናል ወይም አይሆንም› የሚል ዉሳኔ ከመስጠት ይልቅ ነገሮችን በማዘግየት ከገንቢዎቹ ጋር ሲስማሙ የኖሩ አካላት ናቸዉ የችግሩ መነሻዎች፡፡ እነዚህ አካላት በአንድ በኩል የመንግሥት አካላት ሆነዉ ሕግ ያስከብራሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከነዋሪዎቹ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ የነዋሪዎቹ ቤት ሕገወጥ ነው ተብሎ እንዲፈርስ ሲደረግ አብረዉ መጠየቅ የነበረባቸው አካላት ነበሩ፡፡ የነዋሪዎቹን የቤት ችግር በጊዜ መፍታት ያልቻሉ፣ ነዋሪዎቹ ቤት እንዲገነቡ ውስጥ ለውስጥ የፈቀዱ፣ ቤቶቹ እየተገነቡ መሆኑን አይተዉ ዝም ያሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ እኩል ተጠያቂ የማይሆኑ ከሆነ ግን አሠራሩ እንደ ኤጲደቅስዮ ዛፍ ለእባቦች የበለጠ ይጠቅማል ማለት ነው፡፡ 
 
ነዋሪዎቹ እንደ ርግቦቹ በአንድ በኩል በቀላሉ ቤት ለመሥራት መቻላቸዉን አይተዉ፤ በየዘመኑ የሚቀያየሩት ኃላፊዎች የሚሰጧቸዉን ቃል እያመኑ ምንም አንሆንም ብለዉ ዘመናትን አስቆጥረዋል፡፡ ያላቸዉን ጥሪት አውጥተው ቤት ገንብተዋል፡፡ ልጅ ወልደዉ አሳድገዋል፡፡ የሥራ ኃላፊዎቹ ነገሩ ነገ ሊያስጠይቅ እንደሚችል ቢረዱም እንደ እባቡ እንዴት ከችግሩ ማምለጥ እንደሚችሉ ያዉቁበታል፡፡ በመጨረሻ የሚጎዱት ዛፍና ፀሐይዋን አምነዉ የተጠጉት ርግብ ቤት ገንቢዎች ናቸዉ፡፡
 
በየጊዜዉ የሚወሰኑ ውሳኔዎችም ቢሆኑ ፍናፍንት የሆኑ ውሳኔዎች ናቸው፡፡ ሕገ ወጥ ግንባታ ነዉ ተብሎ ቤታቸዉ የሚፈርስባቸዉ አካላት እንዳሉ ሁሉ ሕገወጥ ብትሆኑም ሕጋዊ እናደርጋችኋለን የሚባሉ አካላት አሉ፡፡ እንዴት ተደርጎ ነዉ ሁለቱ ነገሮች በአንድ ጊዜ ትክክል የሚሆኑት፡፡ ዉሳኔዉ ሁለት የሚቃረኑ ‹ትክክል› ነገሮችን ለመሥራት የሚሞክር ነዉ፡፡ አንድ ሕግ የጸና ሕግ የሚሆነዉ በመቼዉም ጊዜ፣ ለሁሉም ዓይነት ዜጎች በማንኛዉም ሁኔታ እኩል ተግባራዊ ሲሆን ነዉ፡፡
በጥንቱ የኢትዮጵያ የውትድርና ሥምሪት ወታደር ደመወዝና ቀለብ ስላልነበረዉ በሄደበት ሀገር በመንደር ተመርቶ ጠይቆም ቀምቶም እየበላ ነበር የሚኖረዉ፡፡ በዚህ ዘመን ብዙ ግፍ ተፈጽሟል፡፡ ቤት ንብረት ይበረበራል፤ ከብት ይታረዳል፣ ሴት ልጆችና ሚስቶች ይደፈራሉ፡፡
ከሰዉ እኖር ብዬ፣ ልጀ አሳድግ ብዬ
ለባሻ ዳርኩለት ሚስቴን እቴ ብዬ
የተባለዉ በዚህ ዘመን ነበር፡፡ ታድያ በአንድ ወቅት በአንድ መንደር ወታደር ይሠራል፡፡ አንዱ ወታደር ወደ አንዱ ገበሬ ቤት ሲገባ ቆንጆ የሆነች ሚስቱን ያያል፡፡ ይዤ እሄዳለሁ ሲል ከባል ጋር ይጋጫል፡፡ ግርግሩን የሰሙ ሌሎች ወታደሮች  ይመጡና ገበሬዉን የፊጥኝ ያሥሩታል፡፡ ሌላው ወታደር ደግሞ ሌላ ቤት ሲገባ ባሏ የታሠረባትን ሴት ያገኛል፡፡ አብሮ ያድራል፡፡ ያቺም ሴት አስተዛዝና ባሏን እንዲፈታላት ትለምነዋለች፡፡ ሀገሩን ለቅቀው ሲሄዱ ፈትቶ ይሰድላታል፡፡ ታድያ ይህንን ሁለቱን ታሪክ ያየ የሠፈር እረኛ፡፡
አይ ዉበት አይ ዉበት አይ ዉበት ቁንጅና
አንዱን ያሳሥራል አንዱን ያስፈታና
ብሎ ገጠመ ይባላል፡፡
መሬት ማግኘት ለአንዳንዶች ጠጠር እንደማግኘት ሲቀልል፤ ለአንዳንዶች ደግሞ ነዳጅ እንደማግኘት ይከብዳል፤ ሕጋዊ ያልሆነ መሬት ይዞ ሕጋዊ መሆን ለአንዳንዶች እንደ ቅል ቀላል፣ ለሌሎች እንደ ዱባ ከባድ ነዉ፡፡ ከጉምሩክ ዕቃ ማውጣት ለአንዳንዶች ከኤቲኤም ብር እንደማዉጣት ሲቀል፣ ለሌሎች ደግሞ ዶላር እንደማዉጣት የከበደ ነዉ፡፡ አንዳንዶች በጊዜ አልገነባችሁም ተብለዉ መሬት ሲነጠቁ፣ ሌሎች ደግሞ በዘመናት ውስጥ ባይሠሩም የሚመጣባቸዉ ነገር የለም፡፡ ለአንዳንዶች የውጭ ምንዛሪ ከማግኘት ዝርዝር ሳንቲም ማግኘት ይከብዳቸዋል፡፡ ለአንዳንዶች ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ከማግኘት ዉጭ ሀገር ሄዶ መሬት መግዛት ይቀላቸዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን በአንዲት ሀገር ይኖራሉ፡፡ በአንድ ሕግ ግን አይተዳደሩም፡፡  
 
በኤጲዲክቅዮ ዛፍ አሠራር እባቦች አይጎዱም፡፡ ‹እንደ እባብ ብልህ› የተባሉትም ለዚህ ነዉ፡፡ የዛፏን ጥላ አቅጣጫ ያውቁታል፡፡ የሚጎዱት ርግቦቹ ናቸዉ፡፡ አሁንም የመንግሥትን ስስ ልብ የሚያዉቁት አይጎዱም፡፡ ሕግ እንዴት እንደሚወጣ፣ አሠራር እንዴት እንደሚቀየር፣ መመሪያ ከየት እንደሚመነጭ፣ ችግር ቢፈጠር እንዴት ማምለጥ እንደሚቻል፣ መሥዋዕትነት ቢከሰት የትኛዉን ፍየል መሠዋት እንደሚቀል አቅጣጫዎቹን ያውቋቸዋል፡፡ ድሮ በሀገራችን የእግር መንገድ የሚያዉቅ ሰዉ ይፈለግ ነበር፡፡ አቋራጩን መንገድ መርቶ እንዲያደርስ፡፡ ዛሬ የሚፈለገዉ የእጅ መንገድ የሚያዉቅ ነዉ፡፡ 
 
በጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ዘመን አንድ የአካባቢ ሹም አንዱን ገበሬ ከስሶ ለንጉሡ ችሎት ያደርሰዋል፡፡ የተከሰሰበት ወንጀል ደመኛዉን ገድሏል ተብሎ ነዉ፡፡ ከሳሹ ነገሩን ሲያስረዳ ‹በየጊዜዉ ሲዝት ነበር፣ አንተን አያርገኝ ሲለዉ ነበር፣ መሣሪያ ጠይቆን ሰጥተነዋል› ብሎ ይናገራል፡፡ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትም ‹ሲዝት ካየኸው፣ ለምን መሣሪያ ሰጠኸዉ› ይሉታል፡፡ እርሱም ‹ሲለምነኝ እንዴት እምቢ ልበለዉ› አለ፡፡ ንጉሡም ‹ሰዉዬውን የገደለው እርሱ ቢሆንም ያስገደልከዉ ግን አንተ ነህ፡፡ ወይ ብትመክረዉ ወይ ያኔ ከስሰህ ብታሣሥረው ይህ ሁሉ አይመጣም ነበር› ብለው በከሳሹም በተከሳሹም ላይ ፈረዱ ይባላል፡፡ ርትዕ ማለት ይህ ነዉ፡፡ ፍትሕ ለሁሉም በትክክል ሲያገለግል፡፡ እያንዳንዱ የሥራዉን ሲያገኝ፡፡ ርትዕ ከሌለ ፍትሕ ብቻዉን ዋጋ አይኖረዉም፡፡ ፍትሕ ዳኝነት፣ የሕጉም ሥርዓት ነዉ፡፡ ርትዕ ግን ይህንን ሥርዓት ለሁሉም በሚዛናዊነት መፈጸም ነዉ፡፡ ፍትሕን ርትዕ ካልተከተላት የኃያላን ማጥቂያ መሣሪያ ትሆናለች፡፡ ደካሞች ተገቢዉን ፍትሕ እንዲያገኙ የሚያደርጋቸዉ ርትዕ ነዉ፡፡ በሀገራችን የሕግና የሕግ ማስከበር ሥርዓትም አንዱ ጉድለት ርትዕ መጥፋቱ ነዉ፡፡ ርትዕ በሌለበት ሕጎች፣ የሕግ መስከበር ሂደቶችና አሠራሮች ኤጲደክስዮ ዛፍ ይሆናሉ፡፡ ከርግቦች ይልቅ ለእባቦች የተመቹ፡፡


16 comments:

 1. ዳኒ ወርቅ ትንታኔ ነው ኤዺደቅስዮ የተባለውን ዛፍ ግን ምን እናርገው?

  ReplyDelete
 2. ዳኒ ወርቅ ትንታኔ ነው ኤዺደቅስዮ የተባለውን ዛፍ ግን ምን እናርገው?

  ReplyDelete
 3. Thanks Dani le,baboch bicha yetemech hig.

  ReplyDelete
 4. wuy daniye nebs ekoneh!!! ERE HOD YIFIJEWU................

  ReplyDelete
 5. wow Grium Eyeta May God bless you Daniel

  ReplyDelete
 6. የኢትዮጵያ መንግሥት የብቃት ጉድለት እንደጥላ ሲከተለው ይኖራል።

  ከሁሉም የሚያናድደው በዐይናቸው ውስጥ ያለውን ምሰሶ ሳይሆን በሰዎች ውስጥ ያለን ጉድፍ ለመንቀፍ በሚሞክሩ፣ የዓሥራ ሦስት ዓመት ወጠጤ ይመስል እንደግለሰብ እንጂ እንደማኅበረሰብ መኖር በተሳናቸው፣ ሳይረዱ በተሾሙበት ሥልጣን የስንት ቤተሰብ የእለት ጉርስ ሊነሱ እንደሚችሉ ባልተረዱ ብቻ ሣይሆን ሊረዱም በማይችሉ፣ ማኅበረሰብአዊ ሥነ፡ምግባር በተለያቸው ግለሰቦች መሞላቱ፣ ሕይወት ለሱ ወይም ለሷ በዛሬ ማታ የተወሰነች የሚመስለውን/ላትን ባለሥልጣን የሚያፈራ አስተዳደር ሆኖ መቅረቱ ነው።

  ተስፋ ስለማልቆርጥ አንድ ቀን ቢያንስ ከችግሮቻቸው አንዱን ይፈቱታል ብዬ ተስፋ አደርጋለው።

  እይታህ ብቻ ሣይሆን ጸሎትህም ይታከልበት።

  ReplyDelete
 7. “Laws are spider webs through which the big flies pass and the little ones get caught.”
  ― Honoré de Balzac

  ReplyDelete
 8. ድርጊቱ ቢዙ ሰው አሳዝኗል በተለይ ሰብአዊነት የጎደለው መሆኑን የሚያሳየው አፈጻጸሙ ባልጠፋ ጊዜ በክረምት ላይ ሆኗል
  ቤተሰብ ልጆቹን የት ያስገባል

  ReplyDelete
 9. መሬት ማግኘት ለአንዳንዶች ጠጠር እንደማግኘት ሲቀልል፤ ለአንዳንዶች ደግሞ ነዳጅ እንደማግኘት ይከብዳል

  አንድ መንግስት ለሀገሩ ዜጎች መሰረታዊ ነገሮች ከሆኑት አንዱ የሆነውነን መጠለየያ የማማላት ግዴታ የለበትምን; ከ30000 በላይ ቤቶች ያለሰነድ የተገነቡት ለምንድንን ነው መንግስት መሬቱን በህጋዊ እና ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ ባለመቻሉ አይደለምን; ነው ወይስ ከጥቂት አስርት አመታት በሃላ ኢትዮጵያችንን አሁን ሸጠን እኛ በግዛ እጃችን እና ሀገራችን ባርነት እንድናድር እቅድ አለ

  በፈረሱት ቤቶች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች አብዛኛው ቢያንስ ሁለት ልጆች ያላቸው ናቸው፡ እንካን የቤት ኪራይ ከፍለው ሊያድሩ በነበሩባት ጎጆ እያሉ በቀነን ሁለት ጊዜ ልጆቻቸውን ለመመገብ የሚቸገሩ ዜጎች ነበሩ፡፡ አሁን ያሉበትን ሁኔታ ማሰብ ነው፡፡ ኢትየጵያ የጎዳና ተዳዳሪ ሳያንሳት የቀረ አልመሰለኝም፡፡ ሊየውም በራሱ መንግስት ተገፍተው የሚወጡ፡፡

  ReplyDelete
 10. the injustice starts in thinking that government can do anything at anytime without any consideration to public wellbeing. Thank you for raising this issue Daniel. the absence of any sense of humanity in bulldozing thousands of homes, which were built under the watchful eyes of the so called 'local government officials' is simply astounding and to do it during the rainy season, is just pure evil. some of the homes are over 40 years old. I am sure they are going to blame the past regime for illegal settlements as well.
  I think it is really important for our 'government' to answer this question. where people have no alternatives for building homes other than a few sentences in the law book which none of the implementers take a look at let alone read, do you find the public guilty for finding a way to fend for themselves and sheltering their families? this is not an issue only in Addis Ababa. you can witness such injustice on daily basis in every other regional state; the snakes having their way all the time because they know how to manipulate, or because they know how to bend the law, to be exact.

  ReplyDelete
 11. ዳኒ እይታህ በጣም ልዩ ነው እናመሰግንሀለን

  ReplyDelete
 12. በጣም ግሩም አስተያየት እና ምክር ነው በርታልን

  ReplyDelete
 13. ምነው ዛሬ የ“ው” እና “ዉ” አጠቃቀም ?

  ReplyDelete
 14. Joro yalew mesimatin yisma
  Neger gin EPRDF yemiawerabet af enji yemiayibet ayin yemiastewulibet libuna yemisemabet joro yalew ayimesilegim
  EPRDF kechaka silemeta le erisu sew malet kechaka yemimetana chekagn aremene bicha new.
  le enersu sew megidel chaka wusit ayit megidel new
  EPRDF beteleyayu hageroch sewoch beasheberi simotu azinenal bilew megilecha siawetu ensemachewalen
  Behagerachin gin bizu sewoch mebitachin yikeber bilew siteyiku kechaka bemetu sewoch megedel yetelemede eyehone metitual andim ken gin azinenal silu alisemanachewn
  Yelikunim mediaw be ejachew silehone bicha yemotu sewochin betifatachew endehone sikoninuachew yisemal
  Bicha Egiziabiher ye Ethiopian tifatuan gin ayasayen
  D/n Daniel Egiziabher Yabertah

  ReplyDelete
 15. ለነገሩ ከኦሮሚያ ገበሬዎች በሰፊው ሊዘርፉ ያሰቡት ባልጠበቁት መልኩ ተሰነካከለባቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች እኮ ከጅብም ብሰዋል፤ ትክክለኛነቱን ባላውቅም ጅብ ሁኔታዎች ከተመቻቹለት ጓደኛውን ከድቶ ይበላል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ሰው ለሆነና አእምሮ ላለው ሰው ሕጋዊ ይሁንም አይሁንም እንዴት የሰውን ልጅ ያህል ክቡር ፍጡር ለዚያውም በክረምት ወራት ለጎርፍና የጅብ ይጣላል?እነርሱ ከቶ ከሰው አልተወለዱምን? በነሱ ልጆች ላይ ቢሆን ይቀበሉታልን? ለአንክሮና ተዘክሮ የተፈጠሩ ነፍሳትና አእዋፋት እንደ ጉንዳንና "eagle" ያሉት እንኳን የክረምቱን ዝናብና ብርድ ከባድ እንደሆነ በማወቅ ክረምቱ እስከሚያልፍ ራሳቸውን ይደብቃሉ፡፡ ከእባቦች ደረጃማ በጣም ከፍ ብለዋል፡፡ በሰው ልጆች እንባ፣ለቅሶ፣ ዋይታ፣ሰቆቃ፣መከራ፣ውርደት፣ኢፍትሃዊነት፣ግድያ፣ዘረፋ፣ስደትና አፈና እንዲሁም ቅጥ ያጣ ዘረኝነት እጅግ በጣም ወፍረው ዘንዶ ሆነዋል እኮ! ትግሉ ከሰው ጋር ሳይሆን ከደለበና አደገኛ ከሆነ ዘንዶ ጋር በመሆኑ፣ አቅም ያለው በጉልበቱ፣አቅም የሌለው በጸሎቱ ተረዳድቶ ዘንዶውን አጥፍቶ ሀገርንና ወገንን ነፃ ማውጣት ነው ብቸኛው አማራጭ፡፡ ዘንዶው እስካለ ድረስ ወገንን ሁሉ በልቶ ጨርሶ ምድሪቱን ባዶ አስቀርቶ ለባዕዳን ቻይና፣አረብና ሕንድ ጨርሶ እንደሚሸጣት የታመነ ነው፡፡ዘንዶው አፉን ከፍቶ አሁንም ደሃዎችን ለመዋጥ በእጅጉ እየተዘጋጀ ነው፡፡ "ከተባበርን ዘንዶውን እናጠፋለን፣ከተከፋፈልን በልቶ ይጨርሰናል፡፡" ስለዚህ ዘንዶው(ሕወሃት) ጨርሶ ሳያጠፋን አሁን በመንገዳገድ ላይ ስለሆነ በተባበረ ክንዳችን ገፍተን ወደ ጥልቁ መቃብር እንክተተው! ለዚህም አምላክ ይርዳን፡፡ አሜን!

  ReplyDelete
 16. ዲ / ዳንኤል ኤጲደቅስዮ በሚለው ባወጣኸው ጽሁፍ አንድ እናቴ ነገረችኝ ብዬ የላኩልህ ጹፍ ነበር ባለማውጣትህ ቅር እያለኝ እንደገና ልላክልህ፡፡ ሳይደርስ ቀርቶ ሊሆን ይችላል

  የተናገረው የመንዝ ገበሬ አሁን ላለው ሁኔታ እንደ ትንቢት ነው ብላ በሰሞኑ ጉዳይ ከእናቴ ጋር ስንጨዋወት አንድ እውነተኛ የሆነ ታሪክ ነገረችኝ፡
  በአበባ ጃንሆይ ጊዜ ነው በትክክል ጊዜውን ባታውቀውም በ60 ዎቹ መጀመሪያ እንደሆነ ትገምታለች፣ አንድ በመንዝ ሀገር የሚኖር ገበሬ መሬቱን ያለ አግባብ ተወስዶበት እንዲመለስለት ብዙ ቢደክምም ፍትህ ባለማግኘቱ ጃንሆይ ይፈረዱልኝ ይሆናል ብሎ በማሰብ ጃንሆይን በግልጽ የሚገኙበትን ጊዜ አስልቶ ወደ አዲስ አበባ ይመጣል ፡፡ የመጣው የቅዱስ ሚካአል ክብረ በዓል በሚሆንበት ቀን፡ ጃንሆይ የቅዱስ ሚካኤልን የንግሥ በዓል የሚያከብሩት በየካ ሚካኤል በመሆኑ በዚህ ቀን በዋዜማው ይደርስና አንድ ትልቅ ሾላ ዛፍ ነበረ (ዛፉን እኔም ደርሼበታለሁ) እዛ ላይ ይወጣና ጀንሆይ ጠዋት ሲመጡ ድምጹን ከፍ አድርጎ፡ እንዲህ አለ አለችኝ
  የጅብ ገበሬ
  የአህያ በሬ
  የጦጣ ዘር አቀባይ
  የዝንጀሮ ጎልጓይ
  ሁሉም እንብላ ባይ
  ሺህ አውሉ ከሚሞት
  ሺው ይሙት ብሎ
  ከዛም ባለሟሎች ገበሬውን ለማዋከብ ሲሞክሩ ጃንሆይ እንዲተውትና ምን ማለት እንደፈለገና ችግሩን እንዲናገር ሲጠየቅ ሁሉም ባለ ሹም የድሀን ንብረት እንደሚነጥቅና ጉቦ እንደሚበላ፣ሹሞች እርስ በርስ በጉገቦ እንደሚጠቃቀሙ ህዝብ ግን እየደሀየ እየነጣ እና እያለቀሰ እንደሆነ ባቃላይ ፍትህ እንደተዛባበት ተናግሮ ፍትህ ከእሳቸው እንደሚፈልግ አስራዳ፡ ጃንሆይም ንገሩ ተመርምሮ ፍትህ እስኪሰጠው ድረስ በቤተ መንግስት ተቀምጦ ጉዳዩን እንዲከታተልና አስረድተው በቀጣዮቹ ቀናት ጉዳዮ ለጃንሆይ ቀርቦ ተበይኖለት ወደ ሀገሩ እንዲመለስ አደረጉ አለችኝ፡፡ ታዲ በዚህ ዘመን ተመሳሳይ ነገር አልሆነም ትላላህ፡፡
  ሰው ችግሩን እንጂ የሚመለከተው ህግ በመጣሱ አንድ ቀን ችግር ውሰጥ እንደሚገባ ማገናዘብ አቁሟል፣ ህግ አስከባሪው (የሚመለከተው ባለስልጣን ወይም ሠራተኛ ከህዝብ ላይ የሚገባውን ቦጭቆ ተረኛውን አስቀምጦ እንደጨዋ ዞረ ማለት እንጂ ለሚፈጠረው ቀውስ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ማሰብ አይፈልገም ስለዚህ ዘመናችንን የመበላላት አደረጓት ያሳዝናል፡፡

  ReplyDelete