የሩቅ ምሥራቆቹ ጃፓኖች እንዲህ
የሚል ለዓለም የተረፈ ታሪክ አላቸው፡፡
በ17ኛው መክዘ ላይ በዓይን ሕመም
የሚሰቃይ ጎ- ሳይ የተባለ አንድ የጃፓን ንጉሥ ነበረ፡፡ በሀገረ ጃፓን የሚገኙ ሐኪሞችን ሁሉ ጠርቶ ለስቃዩ መድኃኒት እንዲፈልጉለት
ቢያዝም ሊያገኙ ግን አልቻሉም፡፡ በኮርያ፣ በቻይና፣ በሞንጎልያና በሩሲያ ሳይቀር ታዋቂ የሆኑ ባለ መድኃኒተኞችን እየጠራ፣ ገንዘብና
ሥልጣን ለመሸለምም ቃል እየገባ ሕመሙን ለማዳን ሞከረ፡፡ ግን አልተቻለውም፡፡ በመጨረሻም ሞንጎልያ ውስጥ በኡውስ ሐይቅ አጠገብ
ዑላንጎም በተባለ መንደር እጅግ የታወቀ ባለ መድኃኒት መኖሩ ተሰማ፡፡
ንጉሥ ጎ- ሳይም ኦይራት የተባሉትን
የሞንጎልያ ሲራራ ነጋዴዎች ይህን ባለመድኃኒት እንዲያመጡለት ወርቅ ሰጥቶ ላካቸው፡፡ ከአራት ወራት በኋላም ኦይራት የሚባሉት ሲራራ
ነጋዴዎች ባለመድኃኒቱን በድንክየዎቹና ፀጉራሞቹ ግመሎች ጭነው አመጡለት፡፡ ንጉሥ ጎ-ሳይ ባለ መድኃኒቱ መምጣቱን ሲሰማ የመዳን
ተስፋው ለመለመ፡፡
ሞንጎልያዊው ባለመድኃኒተኛ ወደ
ቤተ መንግሥቱ ገብቶ ንጉሡን አገኘው፡፡ ንጉሡም ከሚያሰቃየው የዓይን ሕመም ከፈውሰው የፈለገው ሁሉ እንደሚሰጠው ቃል ገባለት፡፡
ሞንጎልያዊው ባለመድኃኒተኛ የንጉሡን ሕመም ለማዳን የሚችል መድኃኒት እንዳለው ነገር ግን ንጉሡ መዳን የሚችለው አንድ ነገር ሲያሟላ
መሆኑን ተናገረ፡፡ ንጉሥ ጎ-ሳይ የተባለውን ሁሉ ለማሟላት ቃል ገባ፡፡ ሞንጎልያዊው ባለመድኃኒትም ‹‹ሐኩጋይ-ሻ› (ገዥ) ከሆንክ
አትድንም፤ ‹ሪዳ› (መሪ) ከሆንክ ግን ትድናለህ› ሲል ነገረው፡፡ ንጉሥ ጎ-ሳይ የባለመድኃኒቱ ነገር ስለገረመው በገዥና በመሪ
መካከል ያለውን ልዩነት ጠየቀው፡፡ ባለመድኃኒቱም ‹ገዥ ጉልበቱንና ሀብቱን ብቻ የሚጠቀም አለቃ ነው፤ መሪ ግን አእምሮውንና ክሂሎቱን
የሚጠቀም አለቃ ነው› ሲል በአጭሩ መለሰለት፡፡ ንጉሥ ጎ-ሳይም መሪ መሆኑን አረጋገጠለት፡፡