Tuesday, June 28, 2016

መውጣትና መውረድ

ከቀናት በፊት ለሥራ ጉዳይ ባሕርዳር ነበርኩ፡፡ ከአንድ ወዳጄ ጋር ስንጨዋወት ማኅበረሰባችን ከሥልጣናቸው የሚወርዱ ሰዎችን በበጎ የመቀበል ልማድ አለው ወይ? የሚል ነገር አነሣ፡፡ እኔም ‹ከሥልጣን ወርደው በሰላም የኖሩም በመከራ ያሳለፉም ዐውቃለሁ› አልኩት፡፡ ዐፄ ካሌብ ሥልጣናቸውን ትተው አባ ጰንጠሌዎን ገዳም ሲገቡ በልጃቸው በገብረ መስቀል ዘመን የደረሰባቸው መከራ የለም፡፡ ምናልባት ግን ያን ጊዜ የክርስትናው ጣዕሙ ያልጠፋበት ዘመን በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ በጎንደር ዘመን ግን አድያም ሰገድ ኢያሱ ሥልጣናቸውን ትተው ገዳም ቢገቡ ተተኪዎቻቸው የመነኑበት ድረስ መጥተው ገድለዋቸዋል፡፡ ሁለቱም በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል፡፡
ወዳጄ ግን ‹ባህሉ ከሥልጣን ለወረደ ሰው ክብር የሚሰጥ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ሹምን ያበረታታል፡፡ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለውም የዚህ ምስክሩ ነው› አለና በሰሞኑ የገጠመውን ነገረኝ፡፡ ከባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች የአንዱ ዲን የነበረ ሰው  መኪናም፣ አበልም፣ ሥልጣንም፣ ክብርም ነበረው አለ፡፡ ሲወጣ ሲገባም እጅ ነሺው፣ ደጅ ጠኚውም ብዙ ነበረ አለ፡፡ በኋላ ታዲያ በአንዳንድ ጉዳዮች ምክንያት ከኃላፊነቱ እንዲነሣ ይወሰናል፡፡ ስብሰባው የተደረገው በዚያው እርሱ ይመራው በነበረው ኮሌጅ ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ በግቢው ውስጥም ሊወርድ ነው የሚል ጭምጭምታ ይወራል፡፡ ማታ ስብሰባው ሲጠራ እንደሚነሣ ሠራተኞቹ አምነዋል፡፡ እንዳመኑትም አልቀረ ኃላፊነቱን በቅርቡ ለተተኪው አስረክቦ ከቦታው እንዲነሣ ተወሰነ፡፡ ዲኑም ስብሰባውን ጨርሶ ወደ ቤቱ ለመሄድ መኪናው ውስጥ ገባ፡፡ ከግቢ ሲወጣ ጥበቃው አስቆመው፡፡ ከዚህ በፊት ይሰጠው የነበረው ሰላምታ ቀረና ‹ወዴት ነው?› አለ ጥበቃው፡፡ ዲኑ ተናድዶ ‹ከዚህ በፊት ወዴት ስለምሄድ ነበር የምትከፍተው› አለው፡፡ ‹ያ ሌላ፣ ይኼ ሌላ› አለ ጥበቃው፡፡ ‹አሁን ክፈተውና ልሂድበት› አለው ዲኑ፡፡ ‹የለም ጌታው እንደ ድሮው አይደሉምኮ፤ ወርደዋል፡፡ ከወረዱ ወዲያ መኪና ይዘው መሄድ አይፈቀድም፡፡ ማውጫ ያምጡ›› አለውና ዐረፈ፡፡ መኪናውን ይዞ ለመውጣት የቻለው ከእርሱ በኋላ የመጡት ሌሎች ኃላፊዎች በሰጡለት ትእዛዝ ነው፡፡ ታድያ ይህንን እያየ ማን ሞኝ ሥልጣኑን ይለቃል?
አንድን ሰው በሥራው፣ በዕውቀቱ ወይም በውጤቱ ሳይሆን በሹመቱ የማክበር የቆየ ልማድ አለን፡፡ ከዓመት በፊት ወሎ ገጠር ውስጥ ገብቼ በእግር እየተጓዝን አንድ ወፍራም ዱላውን የያዘ፣ ቦላሌ ሱሪ ያጠለቀ፣ ምንሽሩንም የታጠቀን ገበሬ አላፊ አግዳሚው ሁሉ እጅ ሲነሣው አየሁ፡፡ አብሮኝ የነበረው ወዳጄም ለእኔ እንኳን አድርጎት የማያውቀውን መሬት ሊወድቅ ትንሽ እስኪቀረው ድረስ ነበር እጅ የነሣው፡፡ እንዲህ ሲያደርግ ያየሁት ቤተ ክርስቲያን ሲሳለም ብቻ ነበር፡፡ ገርሞኝ እልፍ ስንል ‹ሰዉዬው ምንድን ነው?› ስል ጠየቅኩት፡፡ አንድ የክልል ባለ ሥልጣን ስም ጠራና ‹የእርሱ ወንድምኮ ነው› አለኝ፡፡
እንኳን የሹም ሚስቱ፣ ወንድምና እኅቱ
ይኮራ የለም ወይ የሩቅ ጎረቤቱ
የሚል በደርግ ጊዜ የተገጠመ በሹም የመኩራትን ርቀት የሚያሳይ የጎጃም ሥነ ቃል ዐውቃለሁ፡፡ ይሄ በሹመትና በሹም ወዳጅ የመኩራት አባዜ በኋላ ላይ ከሹመት መሻርን፣ መውረድንና መልቀቅን በጸጋ እንዳንቀበለው የሚያደርግ ነው፡፡ ኩራቱ ከልክ ስለሚያልፍ ሐፍረቱም ከልክ ያልፋል፡፡
ኩራትና ትዕቢት የሞሉት አናት
ሰይፍና ጎራዴ የመቱት አንገት
አይገላገሉም እንዲህ በቀላሉ
ከመሬት ላይ ወድቀው ካልተንከባለሉ፡፡ እንዲል ደራሲ፡፡ በሀገራችን ሰው በሥልጣን ሲኖር ዘመድ ወዳጁን መጥቀሙን፣ ለሀገሩና ለአካባቢው ሰዎች መወገኑን፣ የቅርብ ዘመዶቹን ጥግ ጥግ ማስያዙን ባህሉ እንደ ነውር ሳይሆን እንደ ጨዋነት ነው የሚቆጥረው፡፡ በየአካባቢውና በየቢሮው ባለ ሥልጣናቱ ሲቀያየሩ ‹የገንፎ ምንቸት ውጣ፣ የጎመን ምንቸት ግባ› የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ሁሉም ባለ ሥልጣን አልጋውን የሚሸከሙ የራሱ ኪሩቤል፣ መንበሩንም የሚያጥኑ የራሱ ሱራፌል አሉት፡፡ በኛ ሀገር ባለ ሥልጣን ከሹመቱ ሲወርድ ብቻውን አይወርድም፡፡ ቤተሰቡ፣ ጓደኞቹ፣ ዘመዶቹ፣ ወዳጆቹ፤ ጎሳዎቹ፣ አብሮ አደጎቹ ሁሉ ናቸው ከሥልጣን የሚወርዱት፡፡ መውረድ ከባድ የሚሆነውም ለዚህ ጭምር ነው፡፡
ከሹመቱ የወረደ ዕለት ደግሞ፡-
ሹምና ቅቤ ቅል ሁለቱ አንድ ናቸው
የወደቁ ለታ የለም የሚያያቸው፡፡ ይባላል፡፡ በሀገራችን ቅቤ ቅል የተከበረ ነው፡፡ እንዲህ እንደዛሬው ‹ኮለስትሮል› የሚባል መጋኛ ከመምጣቱ በፊት ቅቤ መብላት የጌትነት መለኪያው ነበርና፡፡ የቅቤ ቅል ወዛም ነው፡፡ አይጥ እንዳይደርስበት ከፍ ብሎ ይቀመጣል፡፡ እንደ ሹም፡፡ ከወደቀ ግን መሠበሩ አይቀርምና ፈላጊ የለውም፡፡ ልክ እንደ ሀገራችን ሹም፡፡
መውረድ ሁለት ቦታ የሚገኙ ጥቅሞችን ያሳጣል፡፡ በአንድ በኩል በወንበር የሚያገኙትን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በወንበሩ ክብርና ሥልጣን ምክንያት የሚያገኙትን፡፡ በዕውቀት፣ በውድድር፣ በጥረት፣ በገንዘብ፣ የማይገኙ በሥልጣን ብቻ የሚገኙ ጥቅሞች በሀገራችን ብዙ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ በሚያገኙት ደመወዝ መኪና ለመግዛት ዕድሜያቸውን ሙሉ የሚፈጅባቸው ሰዎች በቀላሉ መኪና የሚያገኙት ከተሾሙ ነው፡፡ በሀገራችን ሊቅ ከተናገረው ይልቅ ባለ ሥልጣን የተናገረው ዜና ስለሚሆን ታዋቂነት በቀላሉ የሚገኘው በሹመት ነው፡፡ ውጭ ሀገር በቀላሉ የሚኬደው በሹመት ነው፡፡ ቤት በቀላሉ የሚገኘው በሹመት ነው፡፡ ጉዳይ በቀላሉ የሚፈጸመው በሹመት ነው፡፡ ሀብት በቀላሉ የሚገኘው በሹመት ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች በትምህርት፣ በጥረት፣ በውድድርና በልቀት ደረጃ የሚገኙ ቢሆኑ ኖሮ አንድም የሹመትን ፍቅር፣ አለያም ደግሞ የመውረድን ሥጋት መቀነስ በተቻለ ነበር፡፡ ትምህርት ቤት ለመመዝገብ እንኳን የሹም ልጅ ነው ከተባለ ነገሩ ያልቃል፡፡ የእምነት ባለ ሥልጣናት እንኳን የሚኮሩት በሚያውቁት አምላክ ሳይሆን በሚያውቁት ባለ ሥልጣን ነው፡፡
ሹመት በወንበሩ ብቻ ሳይሆን ስለ ወንበሩ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች አሉት፡፡ ሳይንቲስቱን ሥራ በዛበት ብሎ የዕድር ልቅሶ ይቅር አይለውም፡፡ ባለ ሥልጣኑን ግን ይቅር ይለዋል፡፡ ‹እርሳቸው ስብሰባ ይበዛባቸዋል› ይባላል፡፡ አንተ ድንኳን ውስጥ ወለህ ማደርህን የሚያይለህ የለም፡፡ እርሳቸው ለደቂቃ ልቅሶ ሲመጡ ግን ‹ከሌላቸው ጊዜ አጣበው› ተብሎ ይደነቅላቸዋል፡፡ አንተን ሳይሆን ወንበርህን የሚያከብረው ሰው መቀመጥ ባትፈልግም ‹ነወር› ይልሃል፡፡ ያንተን ጸሎት እግዜር በቅርበት መስማት ያለበት ይመስል ቤተ ክርስቲያን ስትገባ እንኳን ከፊት ትቆማለህ፡፡ ይህንን እያሰበ ነው ሹሙ ሁሉ መውረድን እንደ ገሃነም የሚፈራው፡፡ ‹ፔንዱለም የሚመለሰው በሄደው መጠን ነው› እንደሚባለው፡፡ የሹመቱ ክብርህ እንደ ተራራ ስለሚነፋ፣ የሽረቱ ውርደትህም እንደ እንጦሮጦስ ይወርደል፡፡ ብርሃኑ ድንቄ እንደጻፉልን በንጉሥ በካፋ ጊዜ ሹም የነበሩት ሊቅ ተሽረው ታሥረው ውኅኒ እያሉ ፈቃጅ ቢያጡ ‹አልቦ ዘመድ ጊዜ ተዋርዶ - በተዋርዶ ጊዜ ዘመድ የለም› ብለዋል፡፡
ሹም እንደ ሰው እንዴት ነው የሚኖረው? የሚለውን ባህላችን የቀረጸው አይመስለኝም፡፡ ‹ዕሩቅ ብእሲ› የሆነ ሹም፡፡ ሽሙጥ፣ ንቀትና ግልምጫ ሳይደርስበት እንዴት ነው መኖር የሚችለው? ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ትርጓሜያችን ‹በሰጠሁበት አገር ለምኜ፣ በተሾምኩበት ሀገር ተዋርጄ አልኖርም ብሎ ሀገር ጥሎ ጠፋ› የሚለን፡፡ ዛሬ ዛሬ ዩኒቨርሲቲዎች በዝተዋል፡፡ በቁጥራቸው ልክ ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሹሞች ሲወርዱ የት ነው የሚሄዱት? ሲሰግድ የነበረ ጥበቃ ‹አሁንማ ወርደሃል› እንደሚላቸው ያውቁታል፡፡ ስንቱን የተሻረ ሹም አምባሳደር አድርገን አንዘልቀዋለን፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ‹በሰጠሁበት ሀገር ለምኜ፣ በተሾምኩበት ሀገር ተዋርጄ› የሚለው የቆየ ብሂል ይመስለኛል የቀድሞ ሹመኞችን አምባሳደር አድርጎ ከሀገር የሚያወጣቸው፡፡
የሹመት ዘመን ሲያበቃ የኖሩበትን አካባቢ ጥሎ መሄድ የቆየ ታሪካችን አካል ነው፡፡ የመጨረሻው የዛግዌ ንጉሥ በይኩኖ አምላክ ሲሸነፍ የዛግዌ የጦር መሪዎችና መሳፍንት አስቀድሞ የዛግዌ ነገሥታት የንግሥናቸው ቦታ ላስታን ትተው ጠንካራ ድጋፍ ወደነበረበት ወደ ሰሜን(ኤርትራ) ሄደዋል፡፡ በዛግዌና በአድከመ መልጋ(ኤርትራ) አካባቢ፣ ሸዋ ላስታን በወረረ ጊዜ የመጡ እንደሆኑ የሚናገሩ ሕዝቦች አሉ፡፡ እነዚህ በዛግዌ ነገሥታት ከተሾሙት የአካባቢ መሪዎች ጋር በመሆን ይኩኖ አምላክን ለተወሰነ ጊዜ ተቋቁመውት ነበር፡፡ በ1261ዓም ለደብረ ሊባኖስ ዘሺምዛና የተሰጠው የርስት ስጦታ እንደሚያመለክተው የዛግዌ ወገኖች ድላንዳ የተባለ ንጉሥ አንግሠው ነበር፡፡ ስድስት ወታደራዊ መሪዎች ያሉበት ምክር ቤትም ነበራቸው፡፡ በ1263 ዓም ንጉሥ ኩዊናት በተባለ ንጉሥ አማካኝነት ሌላ ርስት ስጦታ እናያለን፡፡ በዚህ ጊዜ የተዘረዘሩት አለቆችም ሌሎች ናቸው፡፡ ይህም የዛግዌ ዘመን በይኩኖ አምላክ የንግሥና ጊዜም ቢሆን ለተወሰነ ዘመን መቀጠሉን የሚያሳይ ነው፡፡ ዘመነ መሳፍንት ሲያልቅም የመጨረሻዎቹ ራሶች ደብረ ታቦርን ለቅቀው ወደ የጁ ነው የሸሹት፡፡
በሀገራችን ታሪክ የሹም ዘመድ ብቻ ሳይሆን የሹም በቅሎ፣ ፈረስ፣ ውሻ፣ ከብት ይፈራል፡፡ ይከበራል፡፡ በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን ቢላዋና ድቁስ በአንገቱ ላይ አሥሮ የሚዞር ጠቦት ነበረ እየተባለ የሚነገረው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ማን ይነካዋል? ነው ነገሩ፡፡ እንደ ክፍለ ዮሐንስ ያለ የዕውቀትም የሞራልም ሊቅ ካልሆነ በቀር፡፡ ‹አትንኩኝ የሹም ዶሮ ነኝ› የሚለው አባባል ዝም ብሎ አልመጣም፡፡ የሹም ዶሮ ስጦ ብትበትን፣ ጓሮ ብትፈልስ የሚናገራት ስለሌለ ነው፡፡ እንኳን ከብቱ የሹም ዛፍ እንኳን ልዩ ክብር አለው፡፡
ትሆነኝ ነበረ ሞፈርና ቀንበር
የሹም ዛፍ ሆንክና ይበላሃል አፈር
ያለው ገበሬ የነገረን ይሄንን እውነት ነው፡፡ 
እናም ሹሞቹ ሆይ፤ እናንተም ስትወጡ ዕወቁበት፡፡ እኛም ስትወርዱ እንወቅበት፡፡

29 comments:

 1. ቆይ ኤኔ የሚገርመኝ ዲ/ን ዳኒ በየ ቀኑ አርቲክል ትጽፈለህ ደግሞ መጽሐፍትን ታዝጎደጊዳቸዋለህ(ታሳትማለህ) ደግሞ ያልተነገሩ ሌሎች ስራዎችህ ግን በምን ሰዓት እንዴት ባለ ጸጋስ ነው፡፡እድሜ ይስጥልን፡፡የኔ ብሮውዘር ላይ ግና ዲ ሲጻፍ ዲ/ን የሚለውን ክብር በውስጡ አሽጎ daniel kibret views የሚለው ገጽ default ነው፡፡የ እኛ ዲፎልት ግን ምንድን ነው? ያንተን ጽሁፍ ለማንበብ ሁልጊዜ እንጠማለን፡፡ደግሞ በርታ ሂድ...ሂድ...ጻፍ...ጻፍ

  ReplyDelete
 2. ትሆነኝ ነበረ ሞፈርና ቀንበር
  የሹም ዛፍ ሆንክና ይበላሃል አፈር

  ReplyDelete
 3. "ሁሉም ባለ ሥልጣን አልጋውን የሚሸከሙ የራሱ ኪሩቤል፣ መንበሩንም የሚያጥኑ የራሱ ሱራፌል አሉት"so expressive article....

  ReplyDelete
 4. የእምነት ባለ ሥልጣናት እንኳን የሚኮሩት በሚያውቁት አምላክ ሳይሆን በሚያውቁት ባለ ሥልጣን ነው፡፡ D/Dani you are absolutely right, they rely on empowered person instead of God,

  ReplyDelete
 5. "Neguse teru sera kesera zafser mader yechelale"she zayede
  saw bahulum geze egziabehere besetew gezena sat malkam sera maseratu lanege yetekemewal malkam meserat larase naw

  ReplyDelete
 6. Dear Dani I like all your whiten Thank you

  ReplyDelete
 7. ከስልጣኑ ወርዶ ያሳየን ባለስልጣን ሲጀመር የለም፤ ከማን ያየውን ነው የሚወርደው፤ በተጨማሪም ከስልጣን የወረደው እኮ ተገምግሞ ወይም ለፖሊቲካው ታማኝ ስላልሆነ እንጂ ከሱ የተሻለ ሰው ስለተገኘ ወይም በአዲስ ኃይል ለማሰረት አይደለም፡፡ ይህን ከሰሞኑ ዜና ከእንጊሊዙ ጠ/ሚንስቴር ዳቪድ ካሚሮን መማር ያስፈልጋል፡፡ እናም ቢከበር ባይከበር አይገርምም፡፡ በተጨማሪም የትኛው ባለስልጣን ነው መጀመሪያ ለህዝብ ብሎ የተሸመው፣ ቤት ይቁጠረው፡፡

  ReplyDelete
 8. "ሹሞቹ ሆይ እናንተ ስትወጡ እወቁበት እኛም ስትወርዱ እንወቅበት" የሁልጊዜ ሃሳቤ ነው።ኑርልን የህይወት መምህራችን ደ/ን ዳንኤል።

  ReplyDelete
 9. ሹሞቹ ሆይ፤ እናንተም ስትወጡ ዕወቁበት፡፡ እኛም ስትወርዱ እንወቅበት፡፡

  ReplyDelete
 10. ሹሞቹ ሆይ፤ እናንተም ስትወጡ ዕወቁበት፡፡ እኛም ስትወርዱ እንወቅበት፡፡

  ReplyDelete
 11. የበውቀቱን ግጥም አስታወስከኝ። ቃል በቃል ስነቃሉን ባላስታውሰውም በግርድፉ ...
  "ወድ ላይ ከፍ፥ በደንብ ከፍ
  ሲወድቅ እንዳይተርፍ።"

  ReplyDelete
 12. Hi, Dani plese say something about the people lost their home and they are homeless now. I saw some photo htat show me about the TPLF bad learship we put him to lead us but he killed us.

  ReplyDelete
 13. Our leaders do not display personal humility, good will and discipline while they are in power (regardless of how big). They do not see the power and the responsibility that comes with it as larger and more enduring than themselves.

  ReplyDelete
 14. Edage
  የእምነት ባለ ሥልጣናት እንኳን የሚኮሩት በሚያውቁት አምላክ ሳይሆን በሚያውቁት ባለ ሥልጣን ነው፡

  ReplyDelete
 15. Dn.Daniel berta

  ReplyDelete
 16. ዲ/ን እግዚአብሔር ብርታቱን ይስጥህ

  ReplyDelete
 17. "መሰላል ሲወጡ በብልሀት
  የታቹን ረግጦ የላዩን ጨብጦ
  ሲወርዱ ግን ያስቸግራል
  የረገጡትን ያስጨብጣል"

  ያለችውን ገጣሚ አስታወስከኝ።
  የዛኛው ዘመን ባለቅኔና ባለስነቃል አባቶቻችን ብቻ ሳይሆኑ ፣የዘመናችንም ገጣሚያንም ለዚህ አባዜ ያላቸውን ፍራቻ የገለጡበትን ስንኝ.

  እግዜር ይስጥልን ዲ.ን

  ReplyDelete
 18. Thank you for this article, Daniel. this is one of the downsides of our political culture. I often wonder why we don't see ex-politicians living amongst us, sharing their experience and knowledge, or advising current leaders in office. yes I agree with what you said but what were the reasons why this culture developed in the first place? why is it that political leaders wish to stay in power for posterity? and this is true in every other developing nation. but why? I think one of the reasons is because our political system is based on fear. in this country political career (if there is such a thing in Ethiopia) is developed not because people have the initiative or the will to serve people or improve the situation of the masses. no, people go into politics as a survival mechanism because as you mentioned in your article it is the easiest way to access every possible comfort and opportunity not only for oneself but also for others. there is also the fulfillment of the psychological need of being recognized and respected by everybody around with lavish attention flowing on you like sunlight. of course, no body wants to lose that but this greed for power is a nurtured attitude, continuously fed by public thinking and response and as such can be altered.
  you can be sure that the Americans are not going to kill President Obama or throw him to jail after he completes his term. or the Brits are not going to remove D. Cameroon from any political participation. these people will remain influential for the rest of their lives because they once shouldered the responsibility of making a decision on behalf of the entire nation. That role, whether the decision is right or wrong, commends respect.

  ReplyDelete
 19. የዳግማዊ ዳንኤል አምላክ ቅዱስ እግዚብሔር የተመሰገነ ይሁን

  ReplyDelete
 20. የዳግማዊ ዳንኤል አምላክ ቅዱስ እግዚብሔር የተመሰገነ ይሁን

  ReplyDelete
 21. Dear Deacon please see the following link (http://www.copts-united.com/English/Details.php?I=1703&A=25396) and search for additional information if this restoration of Der-Sultan is really beneficial for Ethiopian Orthodox Church in Israel? I am sure you do have better access and acquaintances than us. Let the almighty God help you in your endeavor.

  ReplyDelete
 22. እናም ሹሞቹ ሆይ፤ እናንተም ስትወጡ ዕወቁበት፡፡ እኛም ስትወርዱ እንወቅበት፡፡

  ReplyDelete
 23. Dear My Bro.
  In our case it is difficult to say we have government. It has died. The existing one are the dead body of the already died government. It has tried to rule the country with the spirit of dead leader for about 3 years to song here and there. Now it has fully dead. If some part of their body is alive the leader are focused on snatching the country’s resource here and there as well as on killing people’s life. I do not think they have the courage and the capacity to lead by giving their heart and mind people’s voice.

  ReplyDelete
 24. እንደዚህ በእውቀት እንደመንበሽበሽ መታደል ነው፡፡ እውነቴን ነው የምለው ኢትዮጵያ እንዳተ ያለ መሪ( እውቀት ያለው ቢኖራት) የት በደረስን፡፡

  ReplyDelete