Tuesday, June 14, 2016

የሦስት ደብዳቤዎች አዙሪትየአንድ ትልቅ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበረ ሰው ከደርጅቱ ሲለቅ ለተተኪው ሰው ሦስት ደብዳቤዎችን በሦስት ፖስታዎች አሽጎ በላያቸውም ላይ 1፣ 2 ና 3 ቁጥር ጽፎ ሰጠው፡፡ ተተኪውም ‹ምን ላድርጋቸው?› ሲል ጠየቀው፡፡ ‹ድርጅቱን በምታስተዳድርበት ጊዜ ችግር በገጠመህ ቁጥር በየተራ ከፍተህ አንብባቸው› አለና መለሰለት፡፡ ርክክቡም በዚህ ተጠናቀቀ፡፡

አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ሥልጣኑን እንደተረከበ ከያቅጣጫው ተቃውሞ በረታበት፤ በጉጉት ጠብቀውት የነበሩት ሁሉ ተስፋ ያደረጉትን ለውጥ በአጭሩ ማየት ስላልቻሉ መበሳጨትና ግፊት ማድረግ ጀመሩ፡፡ ‹ከበሮ በሰው እጅ ሲይዙት› እንደሚባለው ወንበሩ ላይ ሲቀመጥ የሞሰቡ መስፊያ ጠፋበት፡፡ የዘሐውንም ውል ማግኘት አልቻለም፡፡ ድርጅቱም በችግር ተወጠረ፡፡ ከዚህም ከዚያም ተበደልን፣ መብታችን ተረገጠ፣ ተገፋን፣ ተናቅን፣ የሚሉ ድምጾች በረከቱ፡፡ 
 
በዚህ ጊዜ ቁጥር አንድ የተጻፈበትን ፖስታ ከፈተና የተጻፈውን አነበበው፡፡ ‹ካንተ በፊት የነበረውን ኃላፊ ባገኘኸው አጋጣሚ ሁሉ ውቀስ› ይላል፡፡ የድርጅቱን ሠራተኞች ሰበሰበና ከእርሱ በፊት የነበሩት ኃላፊዎች ያጠፉትን ጥፋት፣ የሠሩትን ስሕተት፣ ያደረሱትን በደልና የፈጠሩትን ችግር መዘርዘር ጀመረ፡፡ አሁን ለተከሰተው ነገር ሁሉ ተጠያቂዎቹ እነርሱ መሆናቸውንና እርሱ የመጣው ችግሮቹን ጠራርጎ ለማስወገድ መሆኑን ደሰኮረ፡፡ በወደቀ ዛፍ ላይ ምሣር ማብዛት ቀላል በመሆኑ ሰውም አብሮ ወቀሰ፤ ኮነነ፤ አወገዘ፡፡ 

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በየሄደበት ቦታ ሁሉ ስለወደፊቱ ሳይሆን ስለትናንቱ ማውራትን ልማድ አደረገው፡፡ ራሱን በአካባቢው ከሚገኙ ሌሎች ኃላፊዎች ጋር ሳይሆን ካለፉትና ከሞቱት ኃላፊዎች ጋር ማወዳደር ጀመረ፡፡ ወንበር በቀየረ ቁጥር ‹ያለፉት ኃላፊዎች በእንጨት ወንበር ነበር ደርጅቱን የሞሉት፤ እኔ ግን የቆዳ ወንበር አስገዝቼላችኋለሁ› ይልና ያስጨበጭባል፡፡ ፀሐይ በማለዳ ከወጣች ‹በድሮ ኃላፊዎች ዘመን ፀሐይ ዘግይታ ነበር የምትወጣው፤ አሁን ግን ይሄው በማለዳ መውጣት ጀምራለች› ይላል፡፡ ቀን ዝናብ የዘነበ ጊዜ ‹የድሮ ኃላፊዎች ቤታቸው ከገቡ በኋላ ነበር ዝናብ የሚወርደው፤ አሁን ግን ይሄው በቢሮ ሰዓታችን ዝናብ መምጣት ጀመረ› ብሎ ይለጥፋል፡፡ አንዳንድ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞችም አድናቆታቸውን ይገልጣሉ፡፡ ያለፉት ኃላፊዎች በሠሩት ቤት እየኖረ ይወቅሳቸዋል፤ በገነቡት ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ እያዘዘ ያወግዛቸዋል፤ የገዙትን መኪና እየነዳ ያጣጥላቸዋል፡፡ ‹እማን ላይ ቆመሽ እግዜርን ታሚያለሽ› የሚባለውን አላወቀውም፡፡

እንዲህ እያለ አንድ ዓመት ያህል ተቀመጠ፡፡ ሠራተኛውም ያለፈውን እየወቀሰ፣ ለሚመጣውም የተስፋ ቀብድ እየተቀበለ፤ የችግሩ ሁሉ መነሻና መድረሻ የቀደሙት ናቸው የሚለውን እየደገመ ከረመ፡፡ እየሰነበተ ሲሄድ ግን ያለፉት ኃላፊዎች የሠሩት እየፈረሰ፤ አዲስ ይሠራል የተባለውም የሕልም እንጀራ እየሆነ ሲመጣ ሠራተኛውም እንደገና ማጉረምረም ጀመረ፡፡ ችግሮቹም አየተባባሱ ብቻ ሳይሆን እየተወሳሰቡም ሄዱ፡፡ ያለፉትን ኃላፊዎች የኮነነበትን ሁሉ እርሱ ራሱ እየደገመ መሥራት ጀመረ፡፡ ‹የድሮ ኃላፊዎች ሠራተኛ ሲያባርሩ በደብዳቤ ነበር፤ አሁን ግን በኢሜይል ሆኗል› ተብሎ ለውጡ ተነገረ፡፡ የድሮ ኃላፊዎች ሠራተኛ ሲቀጥሩ በዘመድ ነበር፤ አሁን ግን ተሻሽሎ በዘር ሆነ፡፡ ነገሩ ግን እየባሰ እንጂ እየተሻለ ሊመጣ አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ሥራ አስፈጻሚው ሁለተኛውን ፖስታ ከፈተ፡፡

ሁለተኛው ፖስታ ውስጥ የተጻፈው ነገር ‹ድርጅቱን እንደገና አዋቅረው(Restructure the organization)› ይላል፡፡ ይህንን ተቀብሎ እንዳለ ድርጅቱን ገለባበጠው፡፡ አንድ የነበሩትን ተቋማት ሁለት፤ ሁለት የነበሩትን አንድ፤ ድርጅት የነበሩትን አጀንሲ፤ ዋና ክፍል የነበሩትን ዳይሬክቶሬት፤ የክፍል ኃላፊ የነበሩትን የሥራ ሂደት ባለቤት፤ ኮሚቴ የነበሩትን አንድ ላምስት አደረጋቸው፡፡ ከፊሎቹ ሠራተኞች ተባረሩ፤ ከፊሎቹ ተዛወሩ፤ ከፊሎቹ ተሾሙ፤ ሌሎች ደግሞ ተቀጠሩ፡፡ አዳዲስ መመሪያዎች ተዘጋጁ፣ አዳዲስ ሕንጻዎች ተከራዩ፤ ቢል ቦርድ ተዘጋጀ፤ ራእይና ተልዕኮ ተጻፈ፤ የደረት ባጅ ተጀመረ፤ የመሥሪያ ቤቱም ስም ተቀየረ፤ መግለጫ ተሰጠ፡፡ ድግስም ተደገሰ፡፡ የሠራተኛውም ሥራ ሥልጠና፣ ስብሰባ፣ ተሞክሮ ልውውጥ ሆነ፡፡ 

በድንጋጤው ብዛት በጥይት የተመታውን ቁስል እንደሚረሳ ወታደር ከትርምሱ የተነሣ ችግሩ የተፈታ መሰለ፡፡ አዲስ ሕንጻ ሲከራዩ፣ አዲስ ወንበር ሲገዙ፣ አዲስ ስም ሲይዙ፣ አዲስ ቢል ቦርድ ሲያሠሩ፣ አዲስ ሐሳብ ያመጡ መሰላቸው፡፡ ሁሉም ከትርምሱ እንደገና ተስፋ ሰነቀ፡፡ ነገር ግን መኪናዋ ኮፈኗ ብቻ ነበር እንጂ ሞተሯ አልተቀየረም ነበር፡፡ ቀለሟ ነበር እንጂ ውስጧ ያው ነበር፡፡ ይህም ለጥቂት ጊዜ ማመካኛ ሆነ፡፡ ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር ‹ከአዲሱ አሠራር ጋር ባለመላመድ የመጣ ነው፤ መሥሪያ ቤቱ ኮምፒውተራይዝድ እየሆነ ነው፤ ካለፈው አሠራር ለመላቀቅ በሽግግር ላይ ስለሆንን ነው፤ ኅብረተሰቡ አዲሱን አሠራር ስላላወቀው ነው፤ ቢሮ ሲቀየር ፋይል ስለጠፋ ነው፤ ዳታ ቤዙ ስላልተስተካከለ ነው፤ ኔት ወርክ ስለሌለ ነው› ይባል ጀመር፡፡

ደንበኛውም ሠራተኞቹ ሲለምዱ፣ የጠፋው ፋይል ሲገኝ፣ ሽግግሩ ሲያበቃ፣ ኮምፒውተራይዜሽኑ ሲጠናቀቅ፣ ችግሩ ይፈታል ብሎ እንደገና ታገሠ፡፡ የተስፋ ቀብድም ተቀበለ፡፡ እየቆየ ሲያየው ግን ተዋንያኑ ቢቀየሩም የፊልሙ ‹ስክሪፕት› ተመሳሳይ ሆነበት፡፡ ‹ቁንጮን ሲያታልሏት ፓንክ ብለው ጠሯት› እየሆነ ታየው፡፡ ፈሰስም ተጋቢኖም ያው ሽሮ ነው ማለት ጀመረ፡፡ እንደገናም በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ችግር ተፈጠረ፡፡

በዚህ ጊዜ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሦስተኛውን ፖስታ ከፈተ፡፡ እንዲህ ይላል ‹አሁን አንተም ለተተኪህ ሦስቱን ፖስታዎች አዘጋጅ›፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቁጭ ብሎ ሦስቱን ፖስታዎች አዘጋጀ፡፡ በሰም አሽጎ ቁጥር ጻፈባቸው፡፡ እርሱ አሽጎ ሲጨርስ የስንብቱ ደብዳቤ መጣለት፡፡ እርሱም በተራው ለተተኪው እነዚያን ሦስት ፖስታዎች ሰጠው፡፡ ተቀባዩም በተራው ‹ምን ላድርጋቸው?› ሲል ጠየቀ፡፡ መላሹም በተራው ‹ድርጅቱን ስትመራ ችግር ከገጠመህ በየተራ እያወጣህ ተመልከታቸው› ሲል መከረው፡፡ አዙሪቱም እንደገና ቀጠለ፡፡ 

ሀገራችን በዚህ አዙሪት ውስጥ ናት፡፡ ያለፈውን መኮነንና ማውገዝ፤ ከዚያም የነበረውን እንዳልነበረ አድርጎ ›ለሥር ነቀል ለውጥ› መነሣት፤ በመጨረሻም ሌላውን አዙሪት አዘጋጅቶ መሄድ፡፡ እስኪ አስቡት? ሥር ተነቅሎ ለውጥ እንዴት ይመጣል? ከመጣም ለውጡ መድረቅ ነው፡፡ መጨረሻ ላይ ጣል የተደረገ ቅቤ፣ ሲቁላላ ጀምሮ የነበረውን ሽንኩርት አንዴት ያወግዛል፡፡ መጀመሪያ ካንተ በፊት ለሠሩት ዋጋና ክብር ስጥ፤ ከዚያም የተሳሳቱትን በብቃት አርም፤ በመጨረሻም በመሠረቱ ላይ ግድግዳውን፣ በግድግዳው ላይ ድምድማቱን፤ በድምድማቱም ላይ ጣሪያውን እያስቀመጥክ ሂድ፡፡ ሰውዬው ራስ አለው ብለህ ሳትስማማ እንዴት ፀጉሩ መስተካከል አለበት ትላለህ? ያለፈውን በደንብ አለማወቅ ያለፈውን ስሕተት በባሰ ሁኔታ እንድትደግመው ያደርግሃል፡፡
ጨለማውን ደጋግመህ ስላወገዝከው መብራቱ አይበራልህም፡፡ አንድ ሻማ ብትለኩስ ግን ጨለማውን መግፈፍ ትችላለህ፡፡ ልጅ ምንም አዲስ ፍጡር ቢሆን ከእናትና ከአባቱ የሚወስደው ነገር አለ፡፡ በየቀኑ ልጅ እንጂ አዳም አይፈጠርም፡፡ ካለፉት ምንም ያልወሰደ አዳም ብቻ ነው፡፡ ሌሎቻችን ግን ካለፉት የሆነ ነገር ወስደን፣ አዲስ ነገር ጨምረን ነው አዲስ ትውልድ የሆንነው፡፡ ካለፉት ምንም ሳይወርስ ሰው ለመሆን የቻለ ማነው? ሁሉንም አፍርሰን፣ ሁሉን አዲስ አርገን፣ ሁሉንም ለውጠን አንችለውም፡፡ ካለፈው እንነሣለን፣ ዛሬ ላይ እንሠራለን፤ ወደፊት እንሄዳለን፡፡ ይሄው ነው፡፡ 

ያለበለዚያ ግን በሦስቱ ፖስታዎች አዙሪት ውስጥ እንወድቃለን፤ መላ ዘመናችንንም ዘይት እንደሚጨምቀው ግመል እንዞራለን፤ ግን አንራመድም፡፡ እንደክማለን፣ ግን ፈቀቅ አንልም፡፡ አዙሪት ውስጥ ስንገባ እንዲህ ነው፡፡     

36 comments:

 1. Yes I agree with your idea. It is better said and practiced "MESERETAWI MASHSHAYA" than "sere nekel lewete" as it has not been seen practical as politicians manifest it so. Yealemat hullu fetari YEHONEW AMLAKACHEN EGZIABEHEREM EKO ENGANE SIASTEMERE "ORITEN LADESE ENJI LESHIRE ALMETAHUME "NEW YALEW.

  ReplyDelete
 2. እግዚአብሔር አብዝቶ ይስጥህ ፡ ልቦና ኖሯቸው ይህን አንብበው ቢጠቀሙበት ደስ ይል ነበር፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅልን፡፡

  ReplyDelete
 3. ዳኒ……. እግዝያብሄር ይባርክህ ግሩም እይታ ነዉ አስተማሪ ነዉ … በሚገርም ሁኔታ ደጋግሜ አነበበኩት …. እረጅም እድሜ ከመላዉ ቤተሰብህ ይስጥህ…………

  ReplyDelete
 4. ዳኒ……. እግዝያብሄር ይባርክህ ግሩም እይታ ነዉ አስተማሪ ነዉ … በሚገርም ሁኔታ ደጋግሜ አነበበኩት …. እረጅም እድሜ ከመላዉ ቤተሰብህ ይስጥህ…………

  ReplyDelete
  Replies
  1. በላይ ሙላትJune 20, 2016 at 9:54 AM

   እዉነት የሚናገር አፍ ምን አይነት ጥበበኛ ነዉ.! ለኔ ከሰለሞናዊ ዙፋን ላይ እንደተቀመጠ ያክላል!!! ዲ/ን ዳንኤል በቃ አንተ ጥበበኛ ነህ ጥበብህ ግብ እንዲመታ እግዚአብሄር ይርዳህ!!! በነገራቺን ላይ ገጣሚ ነበርሁ….. ምናል በዚህ ጥበብህ ግጥሜን ነፍስ በሰጠህልኝ.!!! በስሜት ሆኘ ነዉ የጻፍሁልህ…. ዳኒ !!! በላይ ሙላት

   Delete
 5. ካንተ በፊት ያለውን ባገኘከው አጋጣሚ ውቀሰው። ደምስሶ መቅዳት

  ReplyDelete
 6. be ewunetu yihenen neger debdabewu yemimeleketachew yanebut yihone. enaja lemangnawum gen ejig betam des yilal. tenantna derge yastekelew tsed endalneber eyehone eyetekorete eyekere new debre markos mewucha lay yemigegn derg yastekelewun tsed benwosed kettekorete kehulet amet belay honewu gen hulet zaf enkua naltetekelem bemitku . tariken lematfat yimeslal. lalochem tru bsrawoch alu matfat enji beneberachewu lay sichemer alayenem.

  ReplyDelete
 7. ዲ/ን ዳንኤል እግዚር ያክብርልኝ፡፡

  ReplyDelete
 8. እግዚሄር ያክብርልኝ

  ReplyDelete
 9. እግዚሄ ያክብርልኝ

  ReplyDelete
 10. Dear Daniel. thank you for the piece. it is insightful. I wonder why it took you so long to write it, I am sure you have observed this phenomenon a long time ago. in any case, it is good that you write about it now. may be it is time and May be someone from 'the concerned' will read it and take note. the cyclical movement is too boring and tiresome and I think it is foolish to think that one (even if it is a government in office)can get away with fooling others indefinitely. it stops somewhere, as everything else. it is wise to pause, and watch, and learn, and act.

  ReplyDelete
 11. ጨለማውን ደጋግመህ ስላወገዝከው መብራቱ አይበራልህም፡፡
  አንድ ሻማ ብትለኩስ ግን ጨለማውን መግፈፍ ትችላለህ፡፡

  110% Right!!!

  ReplyDelete
 12. Hi DIAKON DANIEL! I always appreciate your views. I read a book entitled "YOU CAN WIN: A STEP BY STEP TOOLS FOR TOP ACHIEVERS". Wrote by SHIV KHERA. In this book I read similar views. It says, a retiring president of a company gave two envelopes marked No. 1 and No. 2 to the incoming president, He directed him to open those envelopes turn by turn when he comes to management crises. When these envelopes opened: the first envelope says "Blame your predecessor" and second envelope says "Prepare two envelopes to your Successor". What I appreciate is you have presented this view diffenetly. You have added envelope No. 3. to blame structural adjustment, BPR, etc. which have helped presidents to stay on their authority get more time to blame. Lastly Iwould like to appreciate you for doing things differently.
  Getnet Geremew

  ReplyDelete
 13. ብልህ ሰው ታናሹንም ይሰማል ///

  ReplyDelete
 14. Dear Daniel!
  FYI!
  it is a question of elaboration !
  Even though, in my opinion, your 'script' is general and not specific, many of the audienc, make a direct claim to their political view. Infact, still they are preparing additional envolopes to their successor generation. These envolopes could be said, message of racisim, subjective to class superiority, rent seeking, extremisim, agenda of intolerance, distinction, authocracy, subpression, anti co-existence, and specifically it is the interest of few left-overs claiming the recovery of in-human governance.
  So please, for the respondants, let us leave with tolerance, co-existence, common interest.and contribute for to historically ignited renaissance and development of our blessed land!.
  So we should believe that we are at the eve of bright, precious, developed federal democratic republic country. Meaning that stop dreaming the edge of total distinction. No one, of the doomy claimers, is calculating the current insight of the nations nationalities and peoples of Ethiopia is having great honor for the federation, democracy, republic values. And maturely assume that , their language, identity, fair justice and governance, common economic and social interests is never negatiable. This is for the historical lessens taught Us, these basic, rational, and critical values earned thruogh the veteran patriots blood is not marketable in the arena of few, sabotage, extremist, zero sum political groups.

  VIVA EFDR!!!
  VIVA BLESSED ETHIOPIA!!!
  VIVA OUR NATIONS NATIONALITIES AND PEOPLES!

  ReplyDelete
 15. ዳንኤል ጽሁፎችህ በጣም አንብባቸው ያሰኛሉ፡፡ በጣም አስተማሪና ገላጭ ነው! ለሚገባው !.... በርታ…በርታ…

  ReplyDelete
 16. ‹ቁንጮን ሲያታልሏት ፓንክ ብለው ጠሯት›


  ካለፉት ምንም ሳይወርስ ሰው ለመሆን የቻለ ማነው? ሁሉንም አፍርሰን፣ ሁሉን አዲስ አርገን፣ ሁሉንም ለውጠን አንችለውም፡፡ ካለፈው እንነሣለን፣ ዛሬ ላይ እንሠራለን፤ ወደፊት እንሄዳለን፡፡ ይሄው ነው፡፡

  ReplyDelete
 17. Thank you Daniel K. I enjoyed your insightful article.

  ReplyDelete
 18. Thanks!Wishing you more success in your life!

  ReplyDelete
 19. እስኪ አስቡት? ሥር ተነቅሎ ለውጥ እንዴት ይመጣል? ከመጣም ለውጡ መድረቅ ነው፡፡

  ReplyDelete
 20. bewnetu yetsafkew hasab lemirda sew enquan degmmo mesrat yilk bebalefew yemyatsetst new.you are genius man!!!!.egziabher yitebkh.edmihn yarzmew.

  ReplyDelete
 21. i like it very much.thank you very much Dn Dani....

  ReplyDelete
 22. It is difficult to get a person like U...I fear ...4 future generation..... a person who can talk about Us....

  ReplyDelete
 23. It is difficult to get a person like U...I fear ...4 future generation..... a person who can talk about Us....

  ReplyDelete
 24. I like it. keep it up! thank you Dani.

  ReplyDelete
 25. ለሚያስተዉልና ለሚመረምር የጻፉት ትልቅ ምክርም ሀገርንም የማዳን ስራ ነበር ። ዳሩ ግን ሰሚና በዕዉቀት የሚመራ ህዝብና አመራር ቢኖር ኖሮ ምክርዎ እጅግ ማለፊያ ነዉ ። እግዚያብሔር ዘመንዎን ይባርክ ። እግዚያብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ።

  ReplyDelete
 26. እግዚአብሔር ያከበረውን ማን ያዋርደዋል? እግዚአብሔር የቀደሰውን ማን ያረክሰዋለ? እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠረውን ማን ያቃልለዋል? በሰዎች መካከል ልዩነትን የሚሰብክ ካለ ጠቡ ከሰው ጋር ሳይሆን ከባለቤቱ ከእግዚአብሔር ጋር ስለሆነ ልዩነት ለሚፈጥሩ እግዚአብሔር ልቦና ይስጣቸው
  አንተን ግን እግዚአብሔር እድሜና ጤና ይስጥልን

  ReplyDelete
 27. እግዚአብሔር ያከበረውን ማን ያዋርደዋል? እግዚአብሔር የቀደሰውን ማን ያረክሰዋለ? እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠረውን ማን ያቃልለዋል? በሰዎች መካከል ልዩነትን የሚሰብክ ካለ ጠቡ ከሰው ጋር ሳይሆን ከባለቤቱ ከእግዚአብሔር ጋር ስለሆነ ልዩነት ለሚፈጥሩ እግዚአብሔር ልቦና ይስጣቸው
  አንተን ግን እግዚአብሔር እድሜና ጤና ይስጥልን

  ReplyDelete
 28. ye Ethiopian liyuuu sitota neh. Ye matusalan endimie yistilin .... abatachin Egziabher tibebun abzito abzito yistih.

  ReplyDelete
 29. ደስ እሚል ጽሁፍ ነው። እግዚአብሔር እድሜና ጤና ይስጥልን።

  ReplyDelete
 30. የእውነት ግልፅና እውነት የሆነ ፅሁፍ እግዚአብሔር ያበርታህ

  ReplyDelete
 31. አንድ ሻማ ብትለኩስ ግን ጨለማውን መግፈፍ ትችላለህ፡፡

  ReplyDelete