ከቀናት በፊት ለሥራ ጉዳይ ባሕርዳር
ነበርኩ፡፡ ከአንድ ወዳጄ ጋር ስንጨዋወት ማኅበረሰባችን ከሥልጣናቸው የሚወርዱ ሰዎችን በበጎ የመቀበል ልማድ አለው ወይ? የሚል
ነገር አነሣ፡፡ እኔም ‹ከሥልጣን ወርደው በሰላም የኖሩም በመከራ ያሳለፉም ዐውቃለሁ› አልኩት፡፡ ዐፄ ካሌብ ሥልጣናቸውን ትተው
አባ ጰንጠሌዎን ገዳም ሲገቡ በልጃቸው በገብረ መስቀል ዘመን የደረሰባቸው መከራ የለም፡፡ ምናልባት ግን ያን ጊዜ የክርስትናው ጣዕሙ
ያልጠፋበት ዘመን በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ በጎንደር ዘመን ግን አድያም ሰገድ ኢያሱ ሥልጣናቸውን ትተው ገዳም ቢገቡ ተተኪዎቻቸው የመነኑበት
ድረስ መጥተው ገድለዋቸዋል፡፡ ሁለቱም በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል፡፡
ወዳጄ ግን ‹ባህሉ ከሥልጣን ለወረደ
ሰው ክብር የሚሰጥ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ሹምን ያበረታታል፡፡ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለውም የዚህ ምስክሩ ነው› አለና በሰሞኑ የገጠመውን ነገረኝ፡፡ ከባሕርዳር
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች የአንዱ ዲን የነበረ ሰው መኪናም፣ አበልም፣ ሥልጣንም፣
ክብርም ነበረው አለ፡፡ ሲወጣ ሲገባም እጅ ነሺው፣ ደጅ ጠኚውም ብዙ ነበረ አለ፡፡ በኋላ ታዲያ በአንዳንድ ጉዳዮች ምክንያት ከኃላፊነቱ
እንዲነሣ ይወሰናል፡፡ ስብሰባው የተደረገው በዚያው እርሱ ይመራው በነበረው ኮሌጅ ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ በግቢው ውስጥም ሊወርድ ነው
የሚል ጭምጭምታ ይወራል፡፡ ማታ ስብሰባው ሲጠራ እንደሚነሣ ሠራተኞቹ አምነዋል፡፡ እንዳመኑትም አልቀረ ኃላፊነቱን በቅርቡ ለተተኪው
አስረክቦ ከቦታው እንዲነሣ ተወሰነ፡፡