Tuesday, May 17, 2016

ሶስና በኢትዮጵያ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ አስደናቂ የፍርድ ታሪኮች አንዱ የሶስና ፍርድ ነው፡፡ እሥራኤል ወደ ባቢሎን ተማርከው በነበሩ ጊዜ ኢዮአቄም እና ሶስና የተባሉ ባልና ሚስቶችም ተማርከው ነበር፡፡ የባቢሎን ሥርዓተ መንግሥት ከየሀገሩ የተማረኩ ፈላስያን የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ፈቅዶ ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ የራሳቸውን ፍርድ ቤቶች አቋቁመው የራሳቸውን ጉዳዮች ይዳኙ ነበር፡፡ በዚህ የእሥራኤል ዳኝነት አንድ ጉዳይ ቀረበ፡፡
ሶስና የምትባል በመልኳ ይህ ቀረሽ የማትባለው የኢዮአቄም ባለቤት በሞት በሚያስቀጣው የአመንዝራነት ወንጀል ተከሰሰች፡፡ በዚያ ዘመን በሀብት ሻል ያሉ የባቢሎን ሰዎች ቤታቸውን በኤፍራጥስ ወንዝ አቅራቢያ ሠርተው በወንዙ ዳር በሚገኙት የአትክልት ሥፍራዎች ውስጥ የገላ መታጠቢያዎችንና የመዋኛ ገንዳዎችን ያዘጋጁ ነበር፡፡ እነዚህ የመናፈሻ ሥፍራዎች በአጥር የታጠሩ ሆነው የራሳቸው በር ነበራቸው፡፡
ኢዮአቄምና ሶስና  ከፈላስያኑ ወገን በሀብትም በክብርም ላቅ ያሉ ስለነበሩ ይህ ሀብት ነበራቸው፡፡ ሀብት ክብር ብቻ ሳይሆን መዘዝም ያመጣል፡፡ በኢዮአቄም ቤት ለችሮታም፣ ለመጠለልም፣ ከባቢሎን ባለ ሥልጣናት ለመገናኘትም እያሉ የሚሰበሰቡ ብዙ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ መካከል ሁለቱ የተከበሩ የሕዝብ መምህራን ናቸው፡፡ ሕዝቡ በዐዋቂነታቸውና በወንበራቸው ያውቃቸዋል፣ ያከብራቸዋል፡፡ ‹በካባ ውስጥ ያለን ኃጢአት፣ በኮት ውስጥ ያለን ጽድቅ እግዜር ብቻ ነው የሚያውቀው› እንዲሉ እነዚህ ሁለት የተከበሩ ባለ ካባዎች ጠባያቸው እንደ ካባቸው አልነበረም፡፡ የኢዮአቄምን ሚስት ሶስናን ለመኝታ ይፈልጓት ነበር፡፡ ነገር ግን አመቺ ጊዜ አላገኙም፡፡


አንድ ቀን ገላዋን ልትታጠብ ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ስትወርድ እነርሱም በድብቅ ወደ መታጠቢያው የአትክልት ሥፍራ ገቡና ተደበቁ፡፡ አገልጋዮቿ የመታጠቢያ ነገሮችን ሊያመጡ በኋላው በር ሲወጡ ከተደበቁበት ወጡና ያዟት፡፡ ከዚያም ‹ከአንቺ ጋር መተኛት እንፈልጋለን› አሉ፡፡ እርሷ ግን ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢል ፈቃዳቸውን ለመፈጸም እንደማትፈልግ በቁርጥ ነገረቻቸው፡፡ እንደዚያ ካልሆነ ‹ከጎረምሳ ጋር አይተናታል ብለን እኛ ምስክር ሆነን እንከስሻለን› አሏት፡፡ ነገሩ ምን ቢያስጨንቃት የእነዚህን ምግባረ ቢሶች ፈቃድ ከመፈጸም ሞትን መረጠቺና ጮኸች፡፡ ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል እንዲሉ እነዚያም ሰዎች አብረዋት ጮኹ፡፡ አንደኛውም ሮጦ የአጥሩን በር ከፈተው፡፡ የአካባው ሰዎች ጩኸቷን ሰምተው ሲመጡ እነዚያ ሰዎች ‹ሶስናን ከጎረምሳ ጋር ተኝታ በዚህ ቦታ አየናት፡፡ እርሱንም ልንይዘው ስንል ኃይለኛ ነበርና በሩን ከፍቶ አመለጠን› ብለው ተናገሩ፡፡ የተናገሩት ሰዎች የከበሩ መምህራን ስለነበሩ ሊጠራጠራቸው የቻለ ሰው አልነበረም፡፡
የሕዝቡ ሸንጎ በማግሥቱ ተሰብስቦ ጉዳዩን አየው፡፡ እነዚያ ሁለት መምህራን አይተናል ያሉትን ተናገሩ፡፡ ሰዎቹ የሚከበሩ በመሆናቸው ቃላቸውም ተከበረና በሶስና ላይ የሞት ፍርድ ተፈረደባት፡፡ ወደ ፍርድ መፈጸሚያው ሥፍራ ልትሄድ ስትል ግን ፍርዱን እንደገና ለማየት የሚያስገድድ ነገር ተፈጠረ፡፡ ነቢዩ ዳንኤል ‹እኔ በዚህ ፍርድ አልስማማም› አለ፡፡ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ያደረገውን ያውቁ ስለነበር ሕዝቡ ሁሉ ሊሰሙት ፈለጉ፡፡ ዳንኤል አንዱ ያንዱን ቃል ሊሰማ በማይችልበት ቦታ ሁለቱን ሰዎች ለየብቻ አቁሞ የትኛው ዛፍ ሥር ተኝታ እንዳዩዋት ጠየቃቸው፡፡ አንዱ በኮክ ዛፍ ሥር ሲል ሌላው በሮማን ዛፍ ሥር ነው አለ፡፡ ይህንን ሲመለከቱ የሕዝቡ ሸንጎ የሞት ፍርዱን እንዲከልስ ተገደደ፡፡ ሶስናን በነጻ አሰናብቶ በምስክሮቹ ላይ የቅጣት ውሳኔን አስተላለፈ፡፡
ሶስና ኢትዮጵያዊት ሆና፣ ድርጊቱ የተፈጸመው ዛሬ ቢሆን ኖሮ ግን የመትረፍ ዕድል አልነበራትም፡፡ ምንም ንጹሕ ብትሆን፣ ምንም ምስክሮቹ የሐሰት ምስክሮች መሆናቸው በኋላ ቢረጋገጥ፣ ምንም እንኳን ከፍርዱ ውሳኔ በኋላ የፍርዱን ውሳኔ የሚያስገለብጥ ማስረጃ ቢገኝ ሶስና ከመሞት ውጭ አማራጭ አልነበራትም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ በወንጀል ጉዳይ የተሰጠ ውሳኔ እንደገና የሚከለስበትን ዕድል ስለማይሰጥ፡፡ በታች ፍርድ ቤት የታየ ጉዳይ በይግባኝ በላይኛው ፍርድ ቤት ይታይ ይሆናል እንጂ አንድ የወንጀል ፍርድ ከተሰጠ በኋላ የቀረበው ማስረጃ ስሕተት ነበረ፣ የተፈረደበት ሰው በስመ ሞክሼ ነው፤ ተፈጸመ የተባለው ድርጊት አለመፈጸሙ ተረጋገጠ፣ የወንጀሉን ፍርድ ሊያስገለብጥ የሚችል ሌላ ማስረጃ ተገኘ ቢባል እንኳን የሀገራችን የወንጀል ፍርድ ‹ከፈሰሰ የማይታፈስ› ነው፡፡
በፍትሐ ብሔር መሥመሩ እንደገና ሊታይ የሚችልበት ዕድል በመጠኑም ቢሆን ገርበብ ብሎ ተከፍቷል፡፡ በወንጀል ሕጉ ግን የተከረቸመ በር ነው፡፡ ከወጣ ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ የሆነው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጋችን በዚህ ሁሉ ዘመን በሩን እንደዘጋው ይገኛል፡፡
ሰሞኑን ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሄጄ በነበረ ጊዜ ሁለት ‹የሶስና ፍርዶችን› ሰምቼ መጣሁ፡፡ አንደኛው ሰውዬ ሰው ገደልክ ተብሎ ይከሰሳል፡፡ ምስክርና ማስረጃ ይቀርብበታል፡፡ ሰውዬው አልገደልኩም ብሎ ቢከራከርም በመጨረሻ በሰባት ዓመት ጽኑ እሥራት ይቀጣል፡፡ እርሱም ወኅኒ ወርዶ ፍርዱን ማድረስ ይቀጥላል፡፡ ለሁለት ዓመታት ያህል ከታሠረ በኋላ ግን ሞተ የተባለው ሰው ወደ መንደሩ ይመጣል፡፡ በእርሱ ምክንያት ሰው መታሠሩንም ይሰማል፡፡ ሰውዬውም ወደ ፍርድ ቤቱ ይመጣና ‹ተገደልኩ የተባልኩት ሰው አለሁ፤ ገደለኝ የተባለውን ሰው ፍቱልኝ› ይላል፡፡ ልክ በሞገደኛው ነውጤ ላይ አበራ ለማ እንደጻፈው፡፡ ዳኞቹ ሁኔታውን ሲያጣሩ በርግጥም ሞተ የተባለው ሰው ይህ ከፊታቸው የቆመው ነው፡፡ አሁን ችግሩ ‹ቀጥሎ ምን ይደረግ?› የሚለውን የሀገራችን የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ አለመመለሱ ነው፡፡ በወንጀል የተሰጠን ፍርድ እንደገና ለመከለስ የሚያስችል ዕድል የለም፡፡ በዚህ የተነሣ አለመግደሉ የተረጋገጠው ሰው የእሥር ጊዜውን ከመጨረስ ያለፈ ውሳኔ ሊያገኝ አልቻለም፡፡
ይህን የተዘጋ በር እስከዛሬም ብዙዎችን ንጽሕናቸው እንዳያድናቸው፣ ዘመን በወለደውና ጊዜ በወደደው ሰው እጅ እንዲወድቁ፣ በአንድ ወቅት በተፈጠረ ስሕተት በተሰጠ ፍርድ እንዲማቅቁ አድርጓቸዋል፡፡ የዚህን በር መከፈት በመቃወም የሚከራከሩ ወገኖች የሚያነሡት ሁለት ጉዳይ ነው፡፡ አንደኛው የወንጀል ፍርድ እንዴትና በማን ነው ሊከለስ የሚችለው? ሁሉም የወንጀል ችሎቶች ይህ ሥልጣን ከተሰጣቸው ላልተገባ ተግባር የመዋል ዕድል አይኖረውም ወይ? የሚል ነው፡፡ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ጉዳዩ መጀመሪያ ለቀረበበት ችሎት ነው የሚቀርበው፡፡ የወንጀል ጉዳዮች ሀገርንና ማኅበረሰብን የሚመለከቱ ስለሆኑ ይህንን ነገር ሊያዩ የሚችሉ ችሎቶችን መመደብ ወይም ከፍ ያለ ሥልጣን ለተሰጠው የፍርድ አካል መስጠት ይቻላል፡፡ በሌላም በኩል አንድ ንጹሕ በስሕተት ከሚታሠር ዐሥር ወንጀለኞች ቢለቀቁ ይሻላል የሚለውን የሕግ ምክር ተግባራዊ አድርጎ መጠቀም ነው፡፡
ሌላው የሚነሣው ጉዳይ ደግሞ የካሣ ጉዳይ ነው፡፡ ‹በስሕተት ነው የታሠርከው› የተባለ ሰው ለተፈጸመበት ነገር ምን ሊደረግለት ይችላል? መንግሥትስ ለእነዚህ ሰዎች ካሣ ለመክፈል ኢኮኖሚያዊ ዐቅም አለው ወይ? የሚለውን የሚያነሡ አሉ፡፡ በስሕተት የተፈረደበት ሰው ኢኮኖሚያዊ፣ ሞራላዊና ማኅበራዊ ኪሣራ ያገኘዋል፡፡ ከሥራው ይወጣል፣ ንግዱ ይበላሻል፣ በሞያው ያፈራቸውን ደንበኞች ያጣል፡፡ ወንጀለኛ ተብሎ ስለተፈረደበት በማኅበረሰቡ ዘንድ ይገለላል፣ ስሙ ይጠፋል፣ ክብሩ ይቀንሳል፡፡ በእነዚህ ሁለት ምክንያቶችም ሞራሉ ይነካል፡፡ የፍርዱ ዘመን ረዥም ከሆነም የማይተካው እድሜው ይወሰድበታል፡፡
መንግሥት ለእነዚህ ነገሮች ሦስት ካሣዎችን ማዘጋጀት ይችላል፡፡ የሞራል፣ የማረሚያና የገንዘብ፡፡ የሞራል ካሣው ሰውዬው በስሕተት እንደታሠረ የሚገልጥ ማስረጃ(የምስክር ወረቀት) በመስጠት፣ አመቺ በሆነው ሚዲያ ወይም በአካባቢው ሊለጠፍ በሚችል ማስታወቂያ በስሕተት የታሠረ ንጹሕ ሰው መሆኑን በመግለጥ መካስ ይቻላል፡፡ የማረሚያ ካሣ ደግሞ ወደ ሥራው እንዲመለስ፣ በመታሠሩ ምክንያት ያጣቸው ጥቅሞች እንዲከበሩለት፣ የተወሰደበት እንዲመለስለት፣ ያለፉት ነገሮች ካሉ እንዲሟሉለት ማድረግ ይችላል፡፡ የሀገሪቱ ዐቅም በሚፈቅደው መጠንም የገንዘብ ካሣ መስጠት ነው፡፡ መንግሥት በፍርድ ሂደት የሚያገኛቸው ገቢዎች አሉ፡፡ ከገንዘብ መቀጮዎች፣ ከውርሶች፣ ወዘተ፡፡ ከእነዚህ ሸረፍ አድርገው ሙሰኞቹ ከሚወስዱ ንጹሐኑ ቢካፈሉ ምን አለ?
አንዳንድ ልሂቃን ‹የተወሰኑ የሕግ አካላት በሠሩት ስሕተት እንዴት መንግሥት ይቀጣል?› የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ መንግሥት ድሮውንም በሰዎች የሚመራ መዋቅር ነው፡፡ መንግሥት የሾማቸው ሰዎች ለሚሠሩት ስሕተት አንዱ ተጠያቂም ራሱ መንግሥት ነው፡፡ ለዚህም ነው በሌሎች ሀገሮች የበታች አካላት ለሠሩት ስሕተት ከፍተኛ ኃላፊዎች ሥልጣን እስከ መልቀቅ የሚደርሱት፡፡
ይህ በር እንደተዘጋ ከቀጠለ ግን ከባድ ማኅበራዊ ኪሣራ ያመጣል፡፡ ሰዎች ንጽሕናን እንዲጠየፉ ያደርጋል፡፡ ዘመኑ በተራቀቀበት በዚህ ወቅት ማስረጃዎችን መፈብረክ ቀላል ነውና አያሌ ንጹሐን ለዚህ በተዘጋጁ ማስረጃ ፈብራኪዎች እጅ እንዲወድቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ያለ ሥራቸው ወንጀል ሠርታችኋል የተባሉትንም ለበቀል ያነሣሣል፡፡
ሁለተኛውን ታሪክ እዚህ ላይ ላውጋችሁ፡፡ ሰውዬው በነፍስ ግድያ ተከሰሰ፡፡ በርግጥ ተኩሶ ሰው መትቷል፡፡ ሲተኩስም ሰዎች አይተውታል፡፡ በተኮሰበት ቦታም ደም ፈስሷል፡፡ ይህንን ሰውዬውም አልካደም፡፡ ምስክሮችም መስክረዋል፡፡ የሟች አስከሬን ግን ሊገኝ አልቻለም፡፡ ከተኩሱ ቦታ በታች ዝንጀሮ ብቻ የሚወርደው ገደል አለ፡፡ እዚያ ውስጥ ስለገባ ሊገኝ አልቻለም ተባለ፡፡ ተኳሹ ግን ‹በርግጥ ተኩሻለሁ ግን አልገደልኩትም› ብሎ ተከራከረ፡፡ ፍርድ ቤቱ የምስክሮችንና የማስረጃውን ነገር መዝኖ አምስት ዓመት ፈረደበት፡፡ ከዓመታት በኋላ ሞቷል የተባለው ሰው ሌላ መንደር እንደሚኖር ተሰማ፡፡ የታሣሪው ዘመዶችም ሄደው አረጋገጡ፡፡ ሰውዬው በጥይት ተመትቶ ነበር፡፡ ሲመታ ቢያውቀው ገደል ተንከባልሎ ገባ፡፡ በጋቢው ቁስሉን አሥሮ ገደል ለገደል ተንኳቶ ሌላ ሀገር ተደበቀ፡፡ እዚያ ጥይቱን አስወጥቶ ታክሞ ዳነ፡፡ ወደ መንደሩ ለመመለስ ስለፈራ ሌላ ቦታ ጎጆ ቀልሶ ተቀመጠ፡፡ ታሪኩ ይሄ ነው፡፡
ታሣሪው ሰው ይህንን ሲሰማ አልተናደደም፡፡ እንዲያውም ደስ አለው፡፡ ‹ለማንም አትናገሩ› ብሎ ዘመዶቹን አስጠነቀቀ፡፡ አምስት ዓመቱን ጨረሰና ከወኅኒ ቤት ወጣ፡፡ ጠመንጃውን ወለወለ፣ ጥይቱን አቀባበለ፡፡ ‹ሟች› ይኖርበታል ወደተባለው ሥፍራ ሄደና ሰው በተሰበሰበበት ቦታ ተኩሶ ገደለው፡፡ ሲገድለው ሰው አይቷል፡፡ እርሱም አልተደበቀም፣ ቤቱ ነው የተቀመጠው፡፡ ፖሊስ ግን እንዴት ይክሰሰው፡፡ አንድ ሰው ሁለት ጊዜ ሊሞት አይችልምና፡፡ በፍርድ ቤት ውሳኔ አሁን የተገደለው ሰው ከሞተ አምስት ዓመት አልፎታል፡፡ ይፈረድበት ቢባልም በአንድ ወንጀል ሁለት ጊዜ ፍርድ የለም፡፡ የተዘጋ የፍትሕ በር ዕዳው ይኼ ነው፡፡

22 comments:

 1. በጣም ይገረማል… እናመሰግናለን፡፡

  ReplyDelete
 2. yemigerm milketa be ewunet betam tenkara yezemenu dink tsehafi

  ReplyDelete
 3. D/N Daniel, yemtanesachewu hasaboch min yahl woktawi endehonu lemezerzer kalat yatrugnal. Bicha gin Egziabher Amlak lantem tenawun ystih leftih akalatim mastewalun ystachew. Lik ahun yanesahew neger begna beteseb lay dersual. 1 sew ba'akababiachin bedulana bechubie tedebdbo ygedelal. 3 sewochim be muachu mskrnet meseret tyazu. huletu tikiklegna gedyoch neberu (tilkna tinish wondmamachoch nachew) sostegnaw gin bebotaw alneberem. neger gin kemuach gar yekoye kim sleneberachewuna drgitu yetefetsemwum bechelema slehone muach sostunm debdbewugnal, endiawum bechubie yewegagn ya bebotawu yalneberewun sew new bilo endetenagere betemeta be 5 gnaw ken mote. sostum taseru. Frd betum be 3tum lay ekul 13 amet tsnu eserat feredebachew. Lezon, lekelel ena lefederalu seber ygbagn binlim semi altegegnem esrun atsenabet. Honom gin lefrd betu baymesekrum gedayouch rasachew liju endalnebere lezemedochachewuna leguadegnochachew eyetenageru new. ke huletu wondimamachoch beteley tilku bicha bedula metito endetalewuna kewedekem behuala bechubie nedewegaw ynageral. Yewgabetun chubie yzo sirotm be'akababiw yeneberu milishawoch yzewut neber bewektu almesekerum enji. Aydelem ye akababiw sew yeyazut polisoch rasu liju endalnebere aregagtewal, honom gin ahun endetebalew mejemeria negeru tebelash kezia memelesha mataria yemibal neger yelem abeka. Lijum yalesraw wohnibet tasrual!

  ReplyDelete
 4. የሜገርም ታሪክ አነበብን ፣ለመሆኑ የሕግ ምሁራን በዚህ ሕግ ዙሪያ ምን ቢሆን ይሻላል ትላላችሁ?

  ReplyDelete
 5. ስንት ህግና ደንብ በየግዜዉ በየ አዋጁ እየተሻሻለ እንዳልከዉ ለንፅህና ዋጋ መስጠት አለብን የሚለዉን ሃሳብህን ለመተግበር ህጉን ማሻሻል ለምን እንደከበደ ፍልስፍናዉን የህግ ባለሞያዎች ቢያስቀምጡት ጥሩ ይመስለኛል:: ችግሩ የፍልስፍና ሳይሆን ያለ ማሰብ ከሆነ ግን ማፈር ይገባናል::

  ReplyDelete
 6. ohhhhhhhh ya hulu awaki sew eyale yh yderegal.mn aynet neger new. ere negeru bitay elalehugn. ta yemecheresha tarik eyayen eyeseman zm malet mn malet new.hgus endet endih yhonal

  ReplyDelete
 7. YE EWNET BEYE FIRDIBETU BINHED YALEW YIHE NEEW....BEMIN AYNET MENGED MEKEYER ENDEMICHAL AYGEBANIM....AND YALTEMARE LIFETAW YEMICHILEW YEWENJEL KIS BETEMARU SEWOCH YEFIRD MAZABAT SELAMAWIW SEEW WEHNI SIWERD EMITAYIBET ZEMEN NEEEW....WENJELEGNA ANGETUN KENA ADRO YEMIHEDIBET ZEMEN LAY DERSENAL...

  ReplyDelete
 8. dani aferku betam aferku ejig betam aferku! amanuel hoy diresilin!

  ReplyDelete
 9. "senegirut yalisema sekelibut yekesale....."

  adane from hawassa

  ReplyDelete
 10. Well Stated Dear. Much appreciated.

  ReplyDelete
 11. ante aydeleh Memhir Girman yasaserk ??

  yemetal qen

  be adebabay enkomalen

  ReplyDelete
 12. Civile law is worst compare to common law.
  All countries who speak English languge use common law others including Ethiopia uses civel law.
  Anyways Dn. Daniel thanks for your perception.

  ReplyDelete
 13. ምንጊዜም ከታሪክ ተነስተህ የአሁን ትንታኔህ ይደንቀኛል። ታላቅ ነህና ዘመንህ ይባረክልን!!!

  ReplyDelete
 14. እንዴት ልብን ይነካል! ከዚህ ጥፋት ያመልጥ ዘንድ ማን ያስተዋለ ማን አለ? ግለሰቦችና የድርጅት ኃላፊዎችም እኮ የዚህ ዓይነቱ ስህተት ተጋሪዎች ናቸው። እስኪ በሀሰት የተወራን ወሬ ማን ያቆመዋል?ማናችን እውነታውን ለማወቅ የግላችንን ጥረት እናደርጋለን? ከዚህ ይልቅ ለመታለል የተዘጋጀን ነው የምንመስለው። ኃላፊዎችን አስተውላችኋል ብዙ ጊዜ ቀድማችሁ ንገሯቸው እንጂ እውነት አካል ገዝቶ ቢመጣ አይቀበሉትምኮ። ነቢዩ ዳንኤል ያስፈልገናል ወደ እውነት ወደ ቅን ፍርድ ወደ ፍርድ አደባባይ የሚመልሰን። በማንኛውም ጊዜ ፍርድ በተጓደለበትም በሞላበትም ሶስናን መሆን መታደል ነው። ቃለ ሕይወት ያሰማልን ወንድማችን!ማስተዋሉን ያድለን።

  ReplyDelete
 15. ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ።

  ReplyDelete
 16. I have kept mindly silent because I was amazed of the countries situation.

  ReplyDelete
 17. ምንጊዜም ከታሪክ ተነስተህ የአሁን ትንታኔህ ይደንቀኛል። ታላቅ ነህና ዘመንህ ይባረክ !!

  ReplyDelete
 18. ውድ ወንድማችን ዲያቆን ዳንኤል !!! በብዙ ምክርና ትምህርት ለወገኖችህ እና ለኃያሉ እግዚአብሔር አገልግሎት የምትሰጥ ወንድማችንን በምን አይን አዩብን ? ስለ ቅዱስ አባታችን ያልከው እውነት እንደሆነ ሁሉም ምእመን ያውቃል፡፡ እናት ልጅዋን በአደባባይ የምትከስበት ጊዜ ላይ በመድረሳችን እያንዳንዳችን በንስሐ ወደ አምላካችን ተመልሰን ልናዝንና ልናለቅስ ይገባል፡፡ በእውነት የምትቆምለት እሱ ባለቤቱ መድኃኔ ዓለም ይቁምልህ አሜን !!!

  ReplyDelete
 19. ይሄ ጉዳይ እኛ ሀገር አዲስ አይደለም እኔ የማውቀውን የሀሰት ፍርድ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
  ልጁ በዚህ በአዲስ አበባ የሚኖር ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነው የግል ሥራ አለው በቤተክርስቲያን ልጅነቱ በቤተክርስቲያን የሚሠራውን የገንዘብ ምዝበራ በመቃወም በማስረጃ እያስደገፈ በድምፅ፣ በምስል መረጃዎችን እየያዘ የዕዝ ሰንሰለቱን ተከትሎ ችግሩ እንዲወገድ እና እንዲፈታ በወረዳ ቤተክህነት ኃላፊዎች የደብሩን ኃላፊዎች ይሞግት ጀመር ደብሯ አዲስ እንደመሆኗ የወረዳ ቤተክህነት ኃላፊዎች ጉዳዩን የሚፈቱ መስለው ነገር ግን የወረዳ ቤተክህነት ኃላፊዎች ልጁን ይዘው በመሄድና ችግሩን እንደሚፈቱ በማስመሰል ለደብሩ ኃላፊዎች ጠላታችሁ ይሄ ነው በሚል መልኩ ያስጠናሉ ችግሩን ላያስወግዱና ላይፈቱ ፡፡
  የደብሩ ኃላፊዎች ከክፍለ ከተማ የፀጥታ ኃላፊ እና ከወረዳ የመንግሥት ባለስልጣኖች ጋር በጋራ አቅደው ለልጁ ወንጀል ይፈጠርለታል፣ የሀሰተኛ ምስክሮች በሃይማኖታቸው ሙስሊሞች የሆኑ ተፈልገው ይዘጋጃሉ የተፈጠረው ክስ ከአንድ አመት በፊት 2006 e.c ከሚሠራበት ሥራ ላይ ህፃናት ወንዶችን አስገድደህ ደፍረሃል በሚል 2007e.c. የሀሰት ክስ ተከሶና በሀሰተኛ ምስክሮች ተመስክሮበት ለ33 ዓመት ከኖረበት መኖሪያ ቤቱ እና እዛው ግቢው ላይ ከ10 ዓመት በላይ ሠርቶ ከሚተዳደርበት ሥራ፣ ከአንድ ልጁ እና ከባለቤቱ እንዲሁም ከደካማ አሮጊት እናቱ አይናቸው እያየ በጥይት እያስፈራሩ ነጥለው በመውሰድ ፖሊስ ለሌላ ሰው መያዣ በወጣ መጥሪያ ስሙን ሰርዞና ደልዞ የልጁን ስም በማስገባት ለእስር ዳርጎት ምንም በማያውቀው ለ15 አመት ተፈርዶበታል፡፡ ቤተሰቡ ተበታትኗል፡፡

  ReplyDelete
 20. ጉድ ነው! ከቀኃስ ዘ/መንግሥት ጀምሮ እስካሁን ድረስ እንዲህ ዓይነቱን ፍርደ ገምድል አሠራር የሚያቃና ሰው የለንም ማለት ነው?

  ReplyDelete
 21. በተጨማሪ ስለሌባ ሻይ ያነበብኩትን አስታወሰኝ። ቀደምት አባቶቻችን ምን ይህል የዋህ ነበሩ ብዬ ተደንቄ ነበር... ግን ለካስ አሁንም ብዙ የሚቀረን አለ? ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሚሆነው መንግሥት ሆን ብሎ እስረኞችን ለአውጫጪኝ የሚያሰቃየው ነው። በተለይ የፖለቲካ እስረኞችን። ስንቱ ያለኃጢአቱ ፍዳውን ያያል። ጥፋተኛ መሆኑ ቢረጋገጥስ በቁጥጥሩ ሥር ያዋለውን ሰብአዊ ፍጡር መንግሥት ለምን ያሰቃያል?
  ደርግ ቢያሰቃይ ሥልጣንን በአድማና በማታለል ስለያዘ ከፍርሃት የተነሣ ሊሆን ይችላል። የአሁኖቹ ግን ፲፯ ዓመት ተፋልመው እየወደቁ እየጣሉና እየተነሡ ሥልጣን ከያዙ ለምን እንደ ፈሪ እስረኛ ያሰቃያሉ? በጥላቻስ ምክንያት ከሆነ ከ፳፭ ዓመት በኋላ የማይበርድ ምን ዓይነት ጥላቻ ነው? እግዚአብሔር ወደ ልባችን ይመልሰን፡፡

  ReplyDelete