Tuesday, May 31, 2016

‹እኛና መንፈስ ቅዱስ› ማለት ሊቀር ነውን?

ቅዱስ ሲኖዶስ የፓትርያርኩን እንደራሴ ሹመት በተመለከተ ለመወያት የያዘው አጀንዳ የመንግሥት ተወካይ ባለበት እንዲታይ መወሰኑን ዛሬ ጠዋት ሰማን፡፡ ከብጹዐን ጳጳሳት በቀር ካህናትና ቆሞሳት እንኳን የማይገቡበት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አማኝ ይሁን ኢአማኒ፣ ሙስሊም ይሁን ክርስቲያን የማይታወቅ የመንግሥት ተወካይ እንዲገኝበት መጋበዙ የደረስንበትን የውርደት ደረጃ የሚያሳየን ነው፡፡
በአንድ በኩል የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ወሳኝ አካል መሆኑን ስናስበው፤ በሌላ በኩል የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የሚደረገው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ነው፤ ውሳኔውም በሐዋርያት ሥራ እንደተገለጠው ‹እኛና መንፈስ ቅዱስ› የሚባልበት ነው(የሐዋ. 15፣29) የሚለውን ስናየው ‹የመንግሥት ተወካይ ይኑርልን› የሚለውን ውሳኔ ኢሃይማኖታዊ ነው ያሰኘዋል፡፡ ለአንድ የሲኖዶስ ጉባኤ የመንፈስ ቅዱስ መገኘት አልበቃው ብሎ ነው የመንግሥትን ተወካይ የሚጋብዘው? ‹ሱባኤ ይዘን፣ ጸሎት አድርገን፤ አንድ ገዳም ወርደን፣ ከእግዚአብሔር ጋር መክረን› አይደለም ይሉን አባቶቻችን፡፡ ‹የመንግሥትን ተወካይ ጋብዘን› ነው ያሉን፡፡ እንዲያውም ቀኖናው የሊቀ ጳጳሳቱ(ፓትርያርኩ) ጉዳይ ሲታይ ‹በመቀመጫቸው መካከል አንድ ወንበር አስቀምጠው፣ ቅዱስ ወንጌሉን በዚያ ላይ አኑረው፣ ሊቀ ጳጳሳቱ በፊታቸው ተቀምጦ፣ አንድነት ተነሥተው በሩን ዘግተው ይጸልዩ፤ የተሰበሰቡበትንም ጉዳይ በሥውር(በኅቡእ) ይመርምሩ› ነው የሚለው(ፍ.ነ. ዐ.168)፡፡ እንዴት ተደርጎ ነው የመንግሥት ተወካይ ባለበት የሚታየው? አግዚአብሔር ያየናል የሚለው ጠፍቶ ታዛቢ ቢያስፈልግ እንኳን የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለታዛቢነት አይበቁም? ቅዱስ ጳውሎስ ‹በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን?› (1ኛቆሮ. 6፣5) ያለው ለዚህ ጊዜ አይሆነንም?

Thursday, May 26, 2016

ሺአውያን

በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2000 ዓም ጥቂት ዘመናት ቀደም ብለው የተወለዱትንና በአሁኑ ዘመን እስከ 30ዎቹ እድሜዎች ያሉትን ትውልዶች ሺአውያን(Millennials) ብለው ይጠሯቸዋል፡፡ በአሜሪካ ሻውያን(ሺአውያን) እጅግ የተጠኑና ብዙ የተወራላቸው ትውልዶች መሆናቸው ይነገራል፡፡ አንዳንዶችም በዲጂታል ቴክኖሎጂ ውስጥ ተወልደው፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ውስጥ አድገው፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ውስጥ ለወግ ለማዕረግ የሚደርሱ ትውልድ ይሏቸዋል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያና ትሥሥር መንደሮችን ሁሉ ባዳረሰበት፣ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች ግለሰባዊ ተደራሽነትን በያዙበት፣ ወላጆች ለትምህርት ይበልጥ ትኩረት በሰጡበት ዘመን የተፈጠሩ ትውልዶች በመሆናቸው እነዚህ ነገሮች በአስተሳሰባቸው፣ አነዋወር ዘያቸውና ፍልስፍናዎቻቸው ላይ ተጽዕኖ አሳድረውባቸዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ የሴቶች፣ የሕጻናት፣ የእንስሳት፣ የተመሳሳይ ጾታ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የአካል ጉዳተኞች፣ ጉዳዮች በሚቀነቀኑበት ዘመን የሚገኙ ናቸውና የእነዚህ ነጸብራቅ ይታይባቸዋል፡፡ ዓለም ተያያዥና በቀላሉ ተደራሽ በሆነችበት የሉላዊነት ወቅትም ስለሚገኙ ክፉውንም ሆነ ደጉን የመካፈል ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ልጅን ተገንዝቦና አስገንዝቦ እንጂ ጠብቆ ማዳን የማይቻልበት ዘመን ነው፡፡ 
በሀገራችን ጥናት ባይደረግም በምዕራቡ ዓለም ግን ሻውያን አጥለቅላቂው ትውልድ ተብሎላቸዋል፡፡ በአሜሪካና በእንግሊዝ የተደረጉ ጥናቶች ሻውያን ከቀደምት ትውልዶች ይልቅ ብዛትና ስብጥር እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ የ2012(እኤአ) ጥናት 80 ሚሊዮን ሻውያን በአሜሪካ፣ 14.6 ሻውያን ደግሞ በእንግሊዝ መኖራቸውን ያመለክታል፡፡ በ2015 ይሄ ትውልድ ‹ፍንዳታ›(baby boomers) የተባለውን ትውልድ ተክቶ በአሜሪካ ዋናው የሥራ ኃይል እንደሚሆን በአሜሪካ ቆጠራ ቢሮ( U.S. Census Bureau) ጥናት ተመልክቶ ነበር፡፡ በ2048 እኤአ ደግሞ ከመራጩ ሕዝብ መካከል 39 በመቶውን እንደሚይዙ ተተንብዮአል፡፡ እኤአ በ2008 ዓም በነበረው የባራክ ኦባማ ምርጫ ወቅት ሻውያን ወሳኝ ድርሻ እንደነበራቸው ታምኗል፡፡

Tuesday, May 17, 2016

ሶስና በኢትዮጵያ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ አስደናቂ የፍርድ ታሪኮች አንዱ የሶስና ፍርድ ነው፡፡ እሥራኤል ወደ ባቢሎን ተማርከው በነበሩ ጊዜ ኢዮአቄም እና ሶስና የተባሉ ባልና ሚስቶችም ተማርከው ነበር፡፡ የባቢሎን ሥርዓተ መንግሥት ከየሀገሩ የተማረኩ ፈላስያን የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ፈቅዶ ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ የራሳቸውን ፍርድ ቤቶች አቋቁመው የራሳቸውን ጉዳዮች ይዳኙ ነበር፡፡ በዚህ የእሥራኤል ዳኝነት አንድ ጉዳይ ቀረበ፡፡
ሶስና የምትባል በመልኳ ይህ ቀረሽ የማትባለው የኢዮአቄም ባለቤት በሞት በሚያስቀጣው የአመንዝራነት ወንጀል ተከሰሰች፡፡ በዚያ ዘመን በሀብት ሻል ያሉ የባቢሎን ሰዎች ቤታቸውን በኤፍራጥስ ወንዝ አቅራቢያ ሠርተው በወንዙ ዳር በሚገኙት የአትክልት ሥፍራዎች ውስጥ የገላ መታጠቢያዎችንና የመዋኛ ገንዳዎችን ያዘጋጁ ነበር፡፡ እነዚህ የመናፈሻ ሥፍራዎች በአጥር የታጠሩ ሆነው የራሳቸው በር ነበራቸው፡፡
ኢዮአቄምና ሶስና  ከፈላስያኑ ወገን በሀብትም በክብርም ላቅ ያሉ ስለነበሩ ይህ ሀብት ነበራቸው፡፡ ሀብት ክብር ብቻ ሳይሆን መዘዝም ያመጣል፡፡ በኢዮአቄም ቤት ለችሮታም፣ ለመጠለልም፣ ከባቢሎን ባለ ሥልጣናት ለመገናኘትም እያሉ የሚሰበሰቡ ብዙ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ መካከል ሁለቱ የተከበሩ የሕዝብ መምህራን ናቸው፡፡ ሕዝቡ በዐዋቂነታቸውና በወንበራቸው ያውቃቸዋል፣ ያከብራቸዋል፡፡ ‹በካባ ውስጥ ያለን ኃጢአት፣ በኮት ውስጥ ያለን ጽድቅ እግዜር ብቻ ነው የሚያውቀው› እንዲሉ እነዚህ ሁለት የተከበሩ ባለ ካባዎች ጠባያቸው እንደ ካባቸው አልነበረም፡፡ የኢዮአቄምን ሚስት ሶስናን ለመኝታ ይፈልጓት ነበር፡፡ ነገር ግን አመቺ ጊዜ አላገኙም፡፡

Tuesday, May 10, 2016

‹ፌስዳቢ›እነሆ በሀገራችን አዲስ ጎሳ መፈጠሩ ተሰማ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ሰዎች የጎሳ ማንነታቸውን ለማስከበር፣ ባህላቸውንና ታሪካቸውን ለመግለጥ ሲታገሉ ነበር የምናየው፡፡ ታሪክ የማያልቅባት ኢትዮጵያ የነባር ጎሳዎችን መብት ማስከበር ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ጎሳዎችንም መመሥረት አለብኝ ብላለች፡፡ በርግጥ በሕገ መንግሥቱ ላይ ነባር ጎሳዎችን በተመለከተ እንጂ አዲስ ጎሳ እንዴት እንደሚመሠረት፣ ቢመሠረትም እንዴት ዕውቅና እንደሚያገኝ የተጻፈ ነገር የለም፡፡
ይሄ አዲስ ጎሳ ‹ፌስዳቢ‹ ይባላል፡፡ ትርጉሙም ‹በፌስ ቡክ በኩል ተሳዳቢ› ማለት ነው ሲሉ የጎሳው ዋና መሪ ፌስ ቡከኛ ጨርግደው በቀደም ዕለት መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ የዚህ ጎሳ መገኛ ክልል ‹ፌስቡክ› የተባለው አካባቢ ሲሆን የጎሳው ቋንቋ  ደግሞ ‹ስድብ› ይባላል፡፡ ‹ስድብ› በተባለው ቋንቋ ወግ መሠረት አማርኛን ሆነ ትግርኛን፣ ኦሮምኛንም ሆነ ሶማልኛን፣ እንግሊዝኛንም ሆነ ዐረብኛን መጠቀም ይቻላል፡፡ ዋናው የቋንቋው ሰዋሰው ሕግ የሚያዘው በእነዚህ ሁሉ ፊደላትም ሆነ ቋንቋዎች ‹ስድብ› መተላለፉን ነው፡፡ ‹ስድብ› የተባለው ይህ የ‹ፌስዳቢዎች› ቋንቋ አምስት አካባቢያዊ ዘዬዎች እንዳሉት በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ልክ አማርኛ የጎጃም፣ የጎንደር፣ የሸዋ፣ የወሎ እየተባለ በዘዬ እንደሚከፈለው ማለት ነው፡፡  አምስቱ ዘዬዎች ናቂ ስድብ፣ ጨርጋጅ ስድብ፣ ባለጌ ስድብ፣ ተንኳሽ ስድብና ፈጥሮ አደር ስድብ ናቸው፡፡
‹ናቂ ስድብ› የሚባለው ዘዬ ማኅበረሰቡን የናቀ፣ ያዋረደና ለዕውቀትና ለኅሊና ቦታ የሌለው ዘዬ ነው፡፡ ‹እገሊት ባኞ ቤት ውስጥ ራቁቷን ሆና የሆነ ነገር እየሠራች ናት፡፡ ሙሉውን ለማየት ላይክና ሼር አርጉኝ› በሚለው አባባሉ ይታወቃል፡፡ መንግሥት በየመሥሪያ ቤቱ ኪራይ ሰብሳቢ እዋጋለሁ ሲል እዚህ ፌስቡክ ላይ ደግሞ ‹ላይክና ሼር ሰብሳቢዎች› ተፈጥረዋል፡፡ ናቂ ስድብ እነዚህ ላይክና ሼር ሰብሳቢዎች የሚግባቡበት የስድብ ዓይነት ነው ፡፡ ናቂ ስድብ አሠሥ ገሠሡን እያቀረቡ ማኅበረሰቡን ለማበሳጨትና ፌስቡክ ከሚባለው ክልል ጨዋዎችን ለማፈናቀል፣ ብሎም  ፌስቡክ የተባለው ክልል  በ‹ፌስዳቢዎች› ለመሙላት የሚጥሩ የጎሳው አባላት የሚጠቀሙበት ቋንቋ ነው፡፡ በእነዚህ ‹ናቂ ስድብ› ዘዬ ተጠቃሚዎች ምክንያት ብዙ ዐዋቂ ፌስቡከኞች ከክልሉ ወጥተው ወደሌላ ክልል ለመሄድ ተገድደዋል፡፡ ‹እስኪ እነዚህን ቆንጆዎች ተመልከቷቸው? ዐሥር ሺ ላይክና ሼር ይገባቸዋል› የሚለው የዚህ ዘዬ ታዋቂ ተረቱ ነው፡፡