Monday, April 18, 2016

ማኅደረ ማርያም - ማኅደረ ታሪክ

click here for pdf


ማኅደረ ማርያም

ሰሞኑን በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት በፋርጣ ወረዳ፣ ከደብረ ታቦር 28 ኪሎ ሜት ርቀት ላይ፣ በ2450 ሜትር ከፍታ ከባሕር ወለል በላይ፣ በቧኢት ተራራ ላይ ወደተተከለቺው ማኅደረ ማርያም ደብር ተጉዤ ነበር፡፡ የጉዞዬ ዋና ዓላማ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ለምሠራው ጥናት ተጨማሪ መረጃዎችን ፍለጋ ነው፡፡ ማኅደረ ማርያም ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ጋር ቅርበት ከነበራቸው የጎንደር አድባራት አንዷ ናት፡፡ ሁለት እጨጌዎችንም አበርክታለች፡፡ ከግራኝ ወረራ በኋላ ወዲያው ከተተከሉ አድባራት አንዷ በመሆኗ ከግራኝ በፊትና በኋላ ላለው የሀገራችን ታሪክ የመገናኛ ድልድይ ናት፡፡
በ1572 ዓም ዐፄ ሰርጸ ድንግል የመንግሥቱን መቀመጫ ከሸዋ ወደ ጎንደር ወስዶ የእንፍራንዝን ከተማ ቆረቆረ፡፡ በ1580 ዓም ደግሞ ወደ እስቴ ጉዞ አደረገ፡፡ በመንገዱ ላይ ጉማራ የተባለው ወንዝ ሞልቶ አዞ ሲዋኝበት ተመለከተ፡፡ በዚህም የተነሣ ከማኅደረ ማርያም በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት አርቦ ከተማን ከተመ፡፡ ባለቤቱ እቴጌ ማርይም ሥና ግን እነ አዝማች ዘሥላሴንና አዛዥ ዓምዴን ይዛ ወደ በጌምድር ተሻገረች፡፡


ጉዞ ማኅደረ ማርያም
እቴጌ ማርያም ሥና ወደ በጌምድር ስትሻገር ዛሬ ሸዋ ሰላሌ ከሚባለው ከአለታ ማርያም(ምናልባት ዓራተ ማርያም) ታቦተ ልደታ ለማርያምን ይዛ ነበር፡፡ በማኅደረ ማርያም የሚገኘው ድርሳነ ኡራኤል ‹ወትቤላ እግዝእትነ ማርያም ለሥነ ማርያም ንግሥት ሑሪ ኀበ ካልዕ ብሔር ወንሥኢ ታቦታትየ ዘሀለው ውስተ ኩሎን አድባራት ወኅድጊ ክልኤሆን ለአባ ኤልያስ ወይርእይኪ ለኪ ቅዱስ ራጉኤል መልአከ ብርሃናት መካን ኀበ ታነብሪ ታቦተ፤ ወኀበ ታሐንጺ ቤተ ክርስቲያን፡፡ ወትእምርተ ዛቲ መካን ዘሀለው በየማና ወበጸጋማ ክልኤቱ አፍላጋት፤ ወበታኅቴሃ ዐቢይ ባሕር ወትትበሃል ጎራማይ ዘውእቱ ጣና ወዘንተ ብሂላ ተሠወረት - እመቤታችን ማርያም ለንግሥት ሥነ ማርያም እንዲህ አለቻት፡- በሁሉም አድባራት የሚገኙትን ታቦቶቼን ይዘሽ ወደ ሌላ ሀገር ሂጂ፤ ለአባ ኤልያስም ሁለቱን ተዪለት፡፡ ታቦቱን የምታኖሪበትን፣ ቤተ ክርስቲያንም የምትሠሪበትን ቦታ መልአከ ብርሃናት ቅዱስ ራጉኤል ያሳይሻል፤ የዚያችም ቦታ ምልክቷ በግራዋና በቀኟ ሁለት ወንዞች አሏት፡፡ ጎራማይ የምትባል ታላቅ ባሕርም በሥርዋ ትገኛለች፡፡ ይህም ጣና ነው፡፡ ይህንንም ብላት ተሠወረች›› ይላል፡፡ 

[አባ ኤልያስ በእንጦጦ ይኖር የነበረ ባሕታዊ መነኮስ ነው፡፡ የግራኝን ዘመን ተሻግሮ አያሌ መዛግብትን ያተረፈልን አባት ነው፡፡ ገድሉ ብዙ ታሪካዊ መረጃዎችን ይዟል፡፡ በኋላ ዘመን ታኩ ተረስቶ ለነቢዩ ኤልያስ ተሰጠ እነጂ በእንጦጦ የነበረው የኤልያስ ቤተ ክርስቲያን የጻድቁ አባ ኤልያስ ነበር፡፡] እቴጌ ማርያም ሥና ለአባ ኤልያስ ታቦቱን አስይዛ ወደ በጌምድር ስትመጣ ማኅደረ ማርያም ተራራ ላይ ስትደርስ ‹ዛቲ ይእቲ ማኅደረ ማርያም መቃብረ ሀገርኪ - የመቃብርሽ ሥፍራ ማኅደረ ማርያም ይህቺ ናት› ብሎ ቅዱስ ራጉኤል አመለከታት፡፡ ንግሥት ማርያም ሥና አምባው ውኃ ገብ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኑን ለመሥራት ተቸግራ ነበር፡፡ በኋላ ግን ከሸዋ የመጡት ጠቢባን አምባውን በድንጋይ እየገነቡ ሠሩት፡፡ አዛዥ ዘሥላሴም ውኃውን ለማድረቅ 500 ጊደሮችን ከእንደርታ(ትግራይ) አስመጡ፡፡ 


ሥዕለ እግዝእትነ ማርያም ዘማኅደረ ማርያም
የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን የተሠራበት እንጨት የመጣው ከዝዋይ ነው፡፡ ከሸዋ የመጡት አሽከሮች የሠፈሩበት ቦታ ዛሬም ‹ተጉለት›፣ ‹ዳሞት›፣ ‹መንቺንግ› እየተባለ ይጠራል፡፡ ግንባታው 9 ዓመት ፈጅቶ የተጠናቀቀው በ1589 ዓም ነው፡፡ ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር ንጉሥ ሰርጸ ድንግል፣ ንግሥት ማርያም ሥና፣ አቡነ ማቴዎስና እጨጌ ዮሐንስ ተገኝተዋል፡፡ ንጉሡም ከጣና እስከ ተከዜ፣ ከመተራይ እስከ ሬብ ወንዝ የደረሰ ርስት ሰጧት፡፡ ስሟም ማኅደረ ማርያም ተባለ፡፡ ከጎጃም፣ ከላስታ፣ ከትግራይ፣ ከኤርትራ፣ ከጎንደርና ከሸዋ፣ ከየአቅጣጫውም አያሌ ሊቃውንት ወደ ማኅደረ ማርያም ተሰበሰቡ፡፡ በተለይም ከጉራጌ ምድር የሄዱት ሊቃውንት በጎንደር ታሪክ ውስጥ እጅግ የታወቁ እንደነበሩ የማኅደረ ማርያም ታሪክ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡
እቴጌ ማርያም ሥናና ሦስቱ ልጆቻቸው(አመተ ሚካኤል፣ ቀሱሳዊትና ወለተ ሥላሴ) የተቀበሩት በማኅደረ ማርያም ነው፡፡ እቴጌ ማርያም ሥና ያረፈቺው በ1600 ዓም ሲሆን ዐፄ ሱስንዮስ ለእቴጌዋ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በማኅደረ ማርያም አስቀብሯታል፡፡ እቴጌ ማርያም ሥና የተቀበሩት በቅድስቱ መሆኑንና ለዚህም ቤተ ክርስቲያኑ ሲታደስ የመቃብር ግንብ፣ ዐጽምና የመጻሕፍት ቅሬቶች መገኘታቸውን የሚጠቅሱ አሉ፡፡
ንጉሥ ሱስንዮስ ለሥልጣኑ ላገዙት የኦሮሞ ጦረኞች መሬት ለመስጠት በነበረው ዕቅድ የመጀመሪያ ዒላማ የሆነቺው ማኅደረ ማርያም ነበረች፡፡ ንጉሡ ከፊሉን ርስቷን ነጥቆ ለጦረኞቹ ሰጠ፡፡ የኦሮሞ ወታደሮችንም በማኅደረ ማርያም አሠፈረ፡፡ በዚህም የተነሣ ከአካባቢው ሕዝብ ጋር ተጋጨ፡፡ እርሱ ወደ ካቶሊክነት ገባ ሲባልም በ1614 ዓም አያሌ ካህናትና ሊቃውንት በማኅደረ ማርያም ተሰብስበው ተቃወሙት፡፡ በ1615 ዓም ንጉሥ ሱስንዮስ ካቶሊክነቱን በይፋ ሲያውጅ እነ እምነ ወለተ ጴጥሮስ ተቃውሟቸውን የጀመሩት በማኅደረ ማርያም ነበር፡፡ ንጉሡ ተቃውሞው ለማብረድ ወደ ማኅደረ ማርያም መጥቶ ከተማውን አቃጠለ፡፡ ቤተ ክርስቲያንዋም አብራ ተቃጠለች፡፡ ዐፄ ዮሐንስ ከደርቡሽ ጋር ሲዋጉ
ቤተ ክርስቲያንዋ ተመልሳ የተሠራቺው በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን (1682-1706) ነው፡፡ አድያም ሰገድ ኢያሱ በ1689 ዓም ወደ ማኅደረ ማርያም መጥተው ደብሯን መልሰው ከሠሯት በኋላ ርስቷን መለሱላት፡፡ ዛሬ ድረስ የሚታየው የግንብ አጥሩም የተሠራው ያኔ ነው፡፡ በዕለቱም አቡነ ማርቆስና እጨጌ ቃለ ዐዋዲ ተገኝተው ነበር፡፡ ከእርሳቸው በኋላ ዐፄ በካፋና ዐፄ ተክለ ጊዮርጊስ ለማኅደረ ማርያም ርስት ሰጥተዋል፡፡
በዘመነ መሳፍንት ማኅደረ ማርያም የመማጸኛ ከተማ ነበረች፡፡ አያሌ መሳፍንትና መኳንንት ደወል ደውለው በመግባት ከጠላቶቻቸው ጥቃት ተርፈውባታል፡፡ ንጉሥ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ራስ ጉግሣ ወሌና ደጃዝማች ወንድ ወሰን ካሣ በደብርዋ የገዳም ቤት ነበራቸው፡፡ አቤቶ ኃይሉም ከንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስ ተጋጭተው ጎጃም ቡሬ ታሥረው ሲኖሩ ከዚያ አመለጡና ማኅደረ ማርያም ገብተው ደወሉ፡፡ በዚያም ለአራት ዓመታት ኖረዋል፡፡ አቤቶ ኃይሉ እሸቴ በማኅደረ ማርያም በኖሩበት ዘመን በየገዳማቱና አድባራቱ የነበራቸው ተሰሚነት ተጠቅመው አያሌ መጻሕፍትን በማሰባሰብ የሀገሪቱን ታላቁን ታሪከ ነገሥት ጽፈዋል፡፡ አቤቶ ኃይሉ እሸቴ አቤቶ አበጋዝ በተባለው ጸሐፊ እጅ መስከረም 1778 ዓም መጠናቀቁን ታሪከ ነገሥቱ ይገልጣል፡፡ አቤቶ አበጋዝ ከሸዋ የሄደ ጸሐፊ ነው፡፡
ይሄ የደጃዝማች ኃይሉ እሸቴ መጽሐፍ በፓሪስ ቤተ መጻሕፍ በቁጥር 143 ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ መጽሐፉ እያንዳንዱ አራት ዓምዶች ያሉት ባለ 370 ገጽ ነው፡፡
ራስ ዓሊጋዝ ከበጌምድሩ ገዥ ራስ ወልደ ገብርኤል ጋር ተጣልተው ማኅደረ ማርያም ገብተው ደውለው ነበር፡፡ ራስ ወልደ ገብርኤልም ወደ ማኅደረ ማርያም መጥተው ራስ ዓሊጋዝን ለመውሰድ ቢጠይቁ ካህናቱ ‹ማርያምን የተማጸነው ወደ ውጭ አናወጣውም› ብለው እመቢ አሏቸው፡፡ ራስ ወልደ ገብርኤልም በኃይል ገብተው ራስ ዓሊጋዝን አሥራው እዚያው በዘበኛ አስጠበቋቸው፡፡ ራስ ወልደ ገብርኤል ወደ መርሐ ቤቴ ዘምተው በሄዱ ጊዜ ካህናቱ ራስ ዓሊጋዝን ፈትተው ሰደዷቸው፡፡ 


የዐፄ ሰርጸ ድንግል አልጋ
ራስ ዓሊ ሥልጣን ሲይዙ እናታቸው እቴጌ መነን መኖሪያቸው በማኅደረ ማርያም አድርገው ነበር፡፡ የደብሯ የመማጸኛ ከተማነትም እንደገና ጸና፡፡ ከቅዳሜ ገበያ እስከ ደብሩ ያለው ቦታም መማጸኛ ተባለ፡፡ እቴጌ መነን ደብሩን እንደገና በውጭና በውስጥ አስጌጡት፡፡ በአይሻል ጦርነት ሰኔ 22 ቀን 1846 ዓም ዐፄ ቴዎድሮስ ራስ ዓሊን ድል ሲያደርጉ ራስ ዓሊ ማኅደረ ማርያም ገብተው ደወሉ፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስም ተዋቸው፡፡ በኋላም በማኅደረ ማርያም ጥቂት ጊዜ ቆይተው ራስ ዓሊ የጁ ወደሚገኙት ወገኖቻቸው ሄዱ፡፡ 
በ1850 ዓም አቡነ ሰላማ ወደ ማኅደረ ማርያም መጥተው ታቦተ ቅዱስ ማርቆስን አስገብተዋል፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ በነበራቸው የመሬት ፖሊሲ ምክንያት አያሌ የማኅደረ ማርያምን ርስት ነጠቁ፡፡ ከካህናቱም ጋር ተጋጩ፡፡ ደብረ ታቦርን ካቃጠሉ በኋላ ወደ ማኅደረ ማርያም መጥተው ከለቻ በተባለው ሜዳ ላይ ሕዝቡንና ሊቃውንቱን ሰበሰቡት፡፡ ካህናቱንም ‹ራስ ዓሊን ለምን አሳልፋችሁ አልሰጣችሁኝም› ብለው ወቀሱ፡፡ በመጨረሻም የተሰበሰቡትን ካህናት፣ ሊቃውንትና ምእመናን በዕለተ ስቅለት አስፈጇቸው፡፡ አልቃሽም፡-
ምንኛ ሰፊ ነው ከለቻ መሬቱ
አራት መቶ ሃምሳ የታረደበቱ፣
መከራ ወረደ በዕለተ ስቅለት
ጌታውን መሰለ ይህ ሁሉ ፍጥረት፣
ካደረግከው ላይቀር ዓርብ መከራውን
እንድትደግመው ይሁን እሑድ ትንሣኤውን› ብላ አለቀሰች፡፡


የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅርስ ተዘረፈ፡፡ በመቅደላ ጦርነት ወደ እንግሊዝ ከሄዱት መዛግብትና ቅርሶች መካከል አያሌ የማኅደረ ማርያም መጻሕፍትና ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ ዐፄ ዮሐንስ በ1869 ዓም ዐፄ ቴዎድሮስ የነጠቋትን ርስት መልሰውላታል፡፡ የደብሯንም ሥዕል በታዋቂው ሰዓሊ በአለቃ ዘዮሐንስ ያሳሉት ዐፄ ዮሐንስ ናቸው፡፡[አለቃ ዮሐንስ ከማኅደረ ማርያም በኋላ አዲስ አበባ የእንጦጦ ራጉኤልንና በኣታ ለማርያም አጠገብ ያለቺውን የሥዕል ቤት ኪዳነ ምሕረትን ሥለዋል፡፡ በሥዕላቸው ሥር ‹ዘከመ ተማኅጸነ ኀበ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰዓሊሁ አለቃ ዘዮሐንስ ዘማኅደረ ማርያም› ይላል፡፡] እቴጌ ጣይቱ ብጡልም በማኅደረ ማርያም ተቀምጠው ዳዊት ደግመዋባታል፡፡ በጣልያን ወረራ ጊዜ ከተማው ቢቃጠልም ደብሯ ግን ተርፋለች፡፡ 


ደብረ ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን
ማኅደረ ማርያም ላይ ሆኖ ፋርጣ፣ ደራና ፎገራ ይታያል፡፡ የጣና ሐይቅም በሩቁ ተዘርግቷል፡፡ አካባቢ በትርጓሜ መጻሕፍትና በድጓ ትምህርት የተጌጠ ነው፡፡ እንዲያውም የፋርጣን ሰው ‹ድጓ ታውቃለህ› ተብሎ አይጠየቅም ይባላል፡፡ የአካባቢው ሰዎችም ‹የፋርጣ ድንጋይ ቢፈነቀል ‹ወለቡ› ይላል› እያሉ ይተርታሉ፡፡ ከእንደርታ የመጡ ትግራዮች፣ ከሸዋ የሄዱ ጠቢባን፣ ከጉራጌ የሄዱ ሊቃውንት፣ ከኦሮምያ የሄዱ ወታደሮች እዚያው ሠፍረው የቀሩባት ትንሽዋ ኢትዮጵያ ናት፡፡ የማኅደረ ማርያም ካህናት በደብሩ የተማጸነውን ተጠቂ፣ ጉልበት ላለው ባለ ሥልጣን አሳልፈው ላለመስጠት ያሳዩትን ቆራጥነትና የከፈሉትን መሥዋዕትነት እያሰብን የዛሬዋን ቤተ ክህነት እንታዘባለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከሞጣ ወደ ደቡብ ጎንደር የሚሄደው መንገድ በማኅደረ ማርያም አልፎ እየተሠራ በመሆኑ ለጉብኝትም ለመሳለምም ለሚሄድ ሰው ቀና ሆኗል፡፡ ከማኅደረ ማርያም ደብር በቅርብ ርቀት በዐፄ ዓምደ ጽዮን ዘመን የተተከለቺው ‹ደብረ ጽዮን ማርያም› ትገኛለች፡፡ ታቦቷ ‹ዝ ጽላት ዘማኅደረ ማርያም ጽዮን ዘወሀባ ዓምደ ጽዮን ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ› ይላል፡፡ በደብሩ በ15ኛው መክዘ የተጻፉ ጥንታውያን መዛግብት አሉ፡፡  
 

የማኅደረ ማርያም ጉብኝታችን እንዲሳካ ያደረጉትን ዲያቆን ሙሉቀን ዘጎንደርን፣ መምህር ናሁ ሠናይ ጌጡን፣ ለስብከተ ወንጌልና ለቤተ ክርስቲያን ቅርስ ያላቸው ቅናትና ትጋት ከፊታቸው የሚነበበው፣ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዮሐንስ መዝገቡ፤ ከ1974 ዓም እስካሁን ደብሯን እያረሱና እያስተማሩ የሚያገለግሏትን፣ ሊቁ የሐዲሳትና የሊቃውንት መምህር፣ የድጓ፣ የአቋቋም፣ የዝማሬና የቅኔ ዐዋቂ፣ ትኅትናን ከዕውቀት አስተባብረው የያዙት የማኅደረ ማርያም ደብር አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ብሩኅ አምሳሉ፤ የማኅደረ ማርያም ካህናትና የሰበካ ኡባኤ አባላት እግዚአብሔር ዋጋችሁን ይክፈላችሁ እላለሁ፡፡   

19 comments:

 1. ሠላም ዳኒ!!ሥለ አቡነ ተክለሀይማኖት ብዙ መርጃ ሥለያዘችው ምሥካቤ ቅዱሣን ገዳም ታውቅ ይሆን??እርሣም በደቡብ ወሎ ቦረና ደንቆሮ ደን ጥግ የአማራ ሣይንቶቹ ተድባበማሪያም እና አትሮንሰ ማሪያም አዋሳኝ ናት፤በገዳሙ አባታችን ለብዙ አመት የፀለዩበት የተፈለፈለ ዛፍ እሥካሁን በህይወት አለ።ጌታ ካንተ ጋ ይሁን!!!

  ReplyDelete
 2. ጌታ ካንተ ጋ ይሁን!

  ReplyDelete
 3. አሜን!! ቃለህይወት ያሰማልን የአገልግሎት ዘመንህን እግዚአብሔር ይባርክ

  ReplyDelete
 4. ዕድሜና ጤና ሁሌም ለአንተ ዲ/ን ጥሩ እይታ ነው ማኀደረ ማርያም ማኀደረ ታሪክ በእውነት ነው ደቡብ ጎንደር ገና ብዙ ያል ተዳሰሱ የታሪክ ቦታዎች አሉ

  ReplyDelete
 5. ዕድሜና ጤና ሁሌም ለአንተ ዲ/ን ጥሩ እይታ ነው ማኀደረ ማርያም ማኀደረ ታሪክ በእውነት ነው ደቡብ ጎንደር ገና ብዙ ያል ተዳሰሱ የታሪክ ቦታዎች አሉ

  ReplyDelete
 6. Amlake Mikael anten yanurelen, yetebekelen, gena bezu sera alebeh!

  ReplyDelete
 7. እናመሰግናለን፡፡ ግን ምነው ስለተድባበ ማርያም የሚዘግብ ሚዲያ ጠፋ?

  ReplyDelete
 8. የሚረዳህ እግዚአብሔር፣ ረድኤቱን አያጉድልብህ፡፡ በእውነት በረከተ ቅዱሳንን ያድልህ!  ReplyDelete
 9. ማኅደረ ማርያም - ማኅደረ ታሪክ... እ/ር ካንተ ጋር ይሁን! … ነገር ግን ፎቶ ላይ አንተ ብቻ ተለየህ.

  ReplyDelete
 10. thanks D/danel. I need you need to wrrite 2 more things based on This.
  1.prophete Elias church &ethipian LIk ELIAS.
  2.Oromo population soupperting susniyos. I.E are they catholich at z time?
  3.Abune tekile hayimanot canged souther ethiopia especially wolita and gurage.NO any history on this part?
  4.a lot of source shaws Abune Tekile haymanot 12 ephis komosat in wolita,your book shaws from GUrage is true or false?
  4.Abune petros martry from wolita but they wrotte from fiche .he is not only adimistrator of otona mariam.
  YANete bier ewunetun abetro endtsf enfeligalen. minm kirstnan metedadria badergu kahinat mikinat yeakebawn sew ensu eyayu menafikan zare bicherisum ewnetaw leela newnna . yihen comment gin enditiletif etyikalehu.

  ReplyDelete
 11. እግዚአብሔር ፀጋህን ያብዛው።

  ReplyDelete
 12. አሜን !!! እግዚአብሔር ያገልግሎት ዘመናችሁን ይባርክልን ፤ ያርዝምልን !!! ወንድማችን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ምን እነደምልህ አላውቅም ውዳሴ ከንቱ ይሆንብኛል !!! ብቻ እግዛብሔር ከዚህ የበለጠውን እውቀትና ሚስጥሩን ይግለፅልህ አሜን !!!

  ReplyDelete
 13. አርቶዶክስ ተዋህዶ
  በኢዮብ ቀናው
  ሚያዚያ 5/2008 ዓ.ም
  እውነት ናት አርነት ታወጣችኋለች
  መንገድ ናት ሳትጠራጠሩ ተጓዙባት
  ህይዎትናት ኑሩባት
  አንዲት ሃይማኖት ናት ጠብቋት
  ውበትናት አጊጡባት
  ፍቅር ናት ውደዷት
  ሰላም ናት በፍቅር ያዟት
  በረከት ናት አክብሯት
  አሜን፡፡

  ReplyDelete