Wednesday, April 13, 2016

አራቱ የጠባይ እርከኖች

የሰው ልጅ አራት የጠባይ እርከኖች አሉት ይላሉ ትውፊታውያን ሊቃውንት፡፡ በነባሩ የኢትዮጵያ ትምህርት መሠረት ጠባይና ባሕርይ ይለያያሉ፡፡ ‹ባሕርይ› ማንነት ነው፡፡ በፍጥረትህ ታገኘዋለህ፡፡ ይዘህው ትኖራለህ፡፡ አትለውጠውም፤ አታሻሽለውም፡፡ ለምሳሌ ሰውነት ባሕርይ ነው፡፡ ሰው መሆንን፣ እንስሳ ወይም ዛፍ ወይም ውኃ በመሆን አትለውጠውም፡፡ ‹ጠባይ› ደግሞ በተፈጥሮ፣ በልምድ፣ በዕውቀት፣ በውርስ፣ የሚገኝ አስተሳሰብ፣ አመለካከት፣ ልማድ፣ አኳኋን፣ አነዋወር፣ አመል ነው፡፡ በትምህርት የጠባይ ለውጥ እንጂ የባሕርይ ለውጥ አይመጣም የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ የባሕርይ ለውጥ ማለት ጨርሶ ማንነትን መለወጥ ማለት ነውና፡፡ሰው ምንም እንኳ አንድ ዓይነት ሆኖ ቢፈጠር በትምህርቱ፣ በባህሉ፣ በልምዱ፣ በልምምዱ፣ በእምነቱ፣ በፍላጎቱና በምርጫው የተነሣ በተለያዩ የጠባይ ደረጃዎች ውስጥ ሊኖር ይችላል፡፡ እነዚህ የጠባይ ደረጃዎች አውሬነት፣ እንስሳነት፣ ሰውነትና መልአክነት ናቸው፡፡ ከአንደኛው ወደ ሌላኛው ማደግና መሻሻል የሚቻለውም አንደኛውን ተረድቶ፣ አርሞና ገርቶ ለሌላኛው ተገዥ በማድረግ ነው፡፡ ዝቅተኛው የጠባይ ደረጃ አውሬነት ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ መልአክነት ነው፡፡ የታችኛውን ሳይገሩና ሳይገዙ ቀጥሎ ያለውን ጠባይ ገንዘብ ለማድረግ የሚሞክሩ ሰዎች ለጊዜው እንደ ተዋናይ ይጫወቱ ይሆናል፡፡ ቆይቶ ግን ባላሰቡትና ባልፈለጉት ጊዜ ያልተገራውና ያልተገዛው ጠባይ ብቅ እያለ ይበጠብጣል፡፡ በተለይም በልዩ ልዩ ስሜቶች በሚናጡበት ጊዜ የደበቁት ጠባይ መገለጡና መጋለጡ አይቀርም፡፡ አንዳንድ ሰዎችም ሳያሸንፉና ሳይገዙ ሸፋፍነው የተውትን ጠባይ ይረሱታል፡፡ ‹ዝም ያለ የሌለ ይመስላል› እንዲሉ፡፡ በዐመድ እንደ ተዳፈነ የፍግ እሳት ይሆናል፡፡ እንዲህ ያለው የተዳፈነ ጠባይ በሰውነት ውስጥ ‹ሲስት› ሠርቶ እንደተቀመጠ ተሐዋሲ አመቺ ጊዜ ነው የሚጠብቀው፡፡ ‹እገሌን ሳውቀው እንዲህ አልነበረም፤ ስንጋባ ይኼ ጠባይ አልነበረውም፣ አብረን ስንሠራ እንዲህ ያለ ነገር አይቼባት አላውቅም፣ ድሮ ደኅና ሰው ነበረች› እያልን በምናውቃቸው ሰዎች ላይ ከምናዝንባቸው ምክንያቶች አንዱ ያልገሩትና ያልገዙት ጠባይ ብቅ ሲል አይተን ነው፡፡
 
የመጀመሪያው የጠባይ ደረጃ አውሬነት ነው፡፡ አውሬነት ስግብግብነት፣ ጉልበተኛነት፣ ነውጠኛነት፣ ርኅራኄ ቢስነት፣ ለማንኛውም ችግር መፍትሔው ኃይል ነው ብሎ ማመን፣ አእምሮን የጥርስና ጉልበት ያህል አለማሠራት፣ በግዳይ መርካት፣ ከሌሎች ጋር ተግባብቶና ተስማምቶ ከመኖር ይልቅ ከልሎና አጥሮ መኖር፤ ማስደንገጥ፣ ማሸበርና ማስፈራረትን የሐሳብ ማስፈጸሚያ ማድረግ፤ በተለይ ጉልበትና ዐቅም በሌላቸው ላይ መጨከን ነው፡፡ አውሬነት ገንዘቡ የሆነ ሰው ምንም የተገራና የተገዛ ጠባይ አይኖረውም፡፡ ልምድ፣ እድሜ፣ ትምህርት፣ ተሞክሮ፣ ቅጣት፣ ሽልማት፣ ባህልና እምነት ያሻሻሉለት፣ የቀረጹለትና የለወጡለት ጠባይ አይኖረውም፡፡ ወይም ደግሞ በእነዚህ ለመሻሻልና ለመለወጥ ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ራሱንም አላዘጋጀም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህንን ጠባይ በውስጣዊ አእምሮው ውስጥ እንደ ሞተር ዋናውን ቦታ ሰጥቶ ነገር ግን በትምህርት፣ በባህል፣ በእምነትና በልምድ ያገኘውን ጠባይ በላዕላይ የእእምሮው ክፍል እያስቀመጠው የሚኖር አለ፡፡ አንዱ ካንዱ ጋር ሳይገናኝ፣ ሳይሟገትና ሳይሸራረፍ፣ በምንታዌ የሚኖር፡፡ እንዲህ ያለው ሰው ዕድል፣ ሥልጣን፣ ገንዘብና አጋጣሚ ሲያገኝ ያንን እንደ ሞተርና አስኳል በአእምሮው ውስጥ ዋና ቦታ ሰጥቶ ያስቀመጠውን የአውሬነት ጠባይ ያወጣል፡፡ 
 
ክፉ አምባገነኖች፣ ጨካኝ መሪዎችና አስቸጋሪ አለቆች የሚፈጠሩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በሀብት ውስጥ፣ በዕውቀት ውስጥና በዝና ውስጥ የተደበቀ አውሬነት የሚገኘው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የተማሩትን፣ የሠለጠኑበትን፣ ያመኑትንና ሲደሰኩሩበት የኖሩትን ትተው ከእነርሱ የማይጠበቅ የአውሬነት ሥራ ሲሠሩ የምናያቸው ‹ፊደላውያን›፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ባለሥልጣናትና ባለ ገንዘቦች በዚህ በሽታ የተጠቁ ናቸው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ መማራቸው፣ መሠልጠናቸውና በእምነት ውስጥ መኖራቸው አውሬነታቸውን እንዲገሩትና እንዲገዙት ከማድረግ ይልቅ ‹መልከ ጥፉውን በስም እንዲደግፉት› ያደርጋቸዋል፡፡ ለአውሬነታቸው የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የፍልስፍናና የዘር ስያሜ ይሰጡታል፡፡ መግደላቸው፣ መጨፍጨፋቸው፣ መዝረፋቸው፣ ማጥፋታቸውና ማውደማቸው ትክክል መሆኑን ለማስረዳት ሃይማኖትን፣ ፖለቲካን፣ ዘርንና ፍልስፍናን ሽፋን ያደርጓቸዋል፡፡ 
 
ሁለተኛው የጠባይ ደረጃ እንስሳነት ነው፡፡ እንስሳነት ከሆድ ያለፈ ነገር አለማሰብ፣ መዋሰብና መዋለድን ብቻ ገንዘብ አድርጎ መኖር፤ ወደነዱት መነዳት፤ ‹ቢጭኑት አህያ ቢለጉሙት ፈረስ› መሆን፤ በተፈቀደልን መስክ ብቻ መጋጥ፣ በተቀየደልን በረት ብቻ መኖር፤ ‹ሰብተዋል ልረዳቸው፣ ደርሰዋል ልጋልባቸው› ለሚለን ሁሉ እሺ ማለት፤ ማር ሠርተን ሌሎች እየቆረጡት፣ ወተት አግተን ሌሎች እየጠጡት መኖር፤ ከምንውልበት መስክና ከምናድርበት በረትና ጋጣ አርቆ አለማሰብ ነው፡፡ ምንም እንኳን እንደ አውሬነት ጠባይ ክፋትና ተንኮል፣ ንጥቂያና ዝርፊያ፣ ደም አፍሳሽነትና ጉልበተኝነት፣ ድንበርተኛነትና አምባገነንነት ባይኖሩም ‹ሆዴ ከሞላ፣ ደረቴ ከቀላ› ከዚህ በላይ ምን እፈልጋለሁ ብሎ መኖር የእንስሳነት ዋናው መገለጫ ነው፡፡ ‹እኔ ከሰው አልደረስ፣ ሰውን አላማ፣ የሰው ገንዘብ አልነካ፣ ሰው አላስቀይም፣ ከሰው አልጣላ› እያሉ የሚመጻደቁ ሰዎች ምን ጊዜም የሚያዩት በሰው ላይ ክፉ አለማድረጋቸውን ብቻ ነው፡፡ ዛፎችም፣ ተራሮችም፣ ወንዞችም፣ ሐይቆችም ይህንን ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ የሰው ዋና መለኪያው ምን አላደረገም? ሳይሆን ምን አደረገ? ነው፡፡ ምንም ባለማድረግማ ሙትንና ግዑዝን የሚስተካከለው አይኖርም፡፡  
 
ብዙ ጊዜ የሌሎች አጃቢ፣ ተከታይና አድናቂ ሆነው የምናገኛቸው እነዚህን ነው፡፡ አይመዝኑም አያመዛዝኑም፣ አይገምቱም አያነጥሩም፤ የነገሯቸውን ሁሉ ያምናሉ፤ የሰጧቸውን ሁሉ ይቀበላሉ፤ ለምን፣ እንዴት፣ መቼ፣ ምን፣ የት፣ ወዴት ብለው መጠየቅ አይችሉም፣ አይወዱምም፡፡ ከሐሳብ ይልቅ በዘር፣ በዝምድና፣ በሀገር ልጅነት፣ አብሮ በመብላትና በመጠጣት፣ በመዋለድና በመጋባት ያምናሉ፡፡ ሐሳባቸውን ማሻሻል፣ ማዳበርና መለወጥ አይፈልጉም፡፡
ሦስተኛው ጠባይ ደግሞ ሰብአዊነት ነው፡፡ ማወቅ፣ ማመዛዘን፣ መለወጥ፣ መሻሻል፣መገመት፣ መመዘን፣ ከትናንት መማር፣ ስለ ነገ መተለም፤ ከአካባቢ፣ ከዘር፣ ከጎጥ፣ ከአጥንትና ጉልጥምት ወጣ አድርጎ ማሰብ፤ ራስን የሌላውም አካል አድርጎ ማሰብ፤ ለአእምሮ ትልቅ ቦታ መስጠት፤ ስሕተትን ለማረም፣ አዲስ ነገርን ለመቅሰም፣ ለመሠልጠን፣ ለመመርመርና ለመፈልሰፍ መትጋት፤ ለፍቅር፣ ለርኅራኄ፣ ለሰላምና ለወንድማማችነት ትኩረት መስጠት፣ በሥርዓትና በሕግ መመራት፣ ከስሜት ይልቅ ለመንፈስ፣ ከፍላጎት ይልቅ ለአቋም፣ ከጥቅም ይልቅ ለመርሕ መቆም ነው ሰውነት፡፡ አእምሮ(ዕውቀት)፣ ልቡና(መድሎት)፣ እና ኅሊና(መንፈስ) ያለው ሰው ብቻ ነው፡፡ አእምሮን ለማወቅ፣ ለመረዳትና ለማሰብ፤ ልቡናውን ባወቅና በተገነዘበው ላይ ተመሥርቶ ለማገናዘብ፣ ለለማስተያየትና ለማነጻጸር፣ ለመመዘንና ለመወሰን፣ ኅሊናውን ለማምሰልሰል፣ ለማሰላሰል፣ ወደኋላ ለማሰብ፣ ወደፊት ለመተንበይ፣ ወደላይ ለመንጠቅ፣ ወደ እመቃት ለመጥለቅ ከቻለ ነው አንደ ሰው ‹ሙሉ ሰው› ሆኗል የሚባለው፡፡  
 
ሰውነት ምንም እንኳን ከፍተኛው የሰብእና አካል ቢሆንም ጉድለቶች ግን አሉት፡፡ እንደ ዶክተር እጓለ አገላለጥ ለ‹ጽርየት› ትኩረት አይሰጥም፡፡ ‹ጽርየት› ማለት በግርድፉ ንጽሕና ነው፡፡ በዋናነት ግን የአእምሮ፣ የኅሊናና የልቡና ንጽሕናን ይመለከታል፡፡ ሰውነት በአንድ በኩል ሳይገራ ይዟቸው ከታችኞቹ ጠባያት ያመጣቸው እንከኖች፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሐሳብ፣ የእምነት፣ የፍልስፍና፣ የዘር፣ የባህልና የሥልጣኔ ልዩነቶችን ለመፍታት በሚወስዳቸው መፍትሔዎች ምክንያት ‹ዕድፈት› ያጋጥመዋል፡፡ ‹ዕድፈት› ማለት ጥበብን፣ ዕውቀትን፣ ሥልጣንን፣ ገንዘብንና ዝናን ለግላዊ ፍላጎት ለማዋል የሚሠራ ሰብአዊ ሤራ ነው፡፡ በተለይም ይኼ ሤራ ሳይገራና ሳይገዛ ከመጣ የአውሬነትና የእንስሳነት ‹ተረፈ ጠባይ› ጋር ከተቀላቀለ አደገኛ ነው፡፡ ለአውሬነትና እንስሳነት ጠባያት የዕውቀት፣ የጥበብ፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካና የፍልስፍና ስያሜ እየሰጡ የሰውን ልጅ የሚያስቸግሩ ሰዎች የሚከሠቱት በዚህ ዕድፈት ምክንያት ነው፡፡ 
 
ጽርየትን ለማግኘት ወደ አራተኛው የሰብእና ደረጃ መግባት ያስፈልጋል፡፡ ጽርየት የሚገኘው ከመልአክነት ነው፡፡ መልአክነት ዋናዎቹ መገለጫዎቹ ሁለት ናቸው ‹ለሌሎች በሚደረግ መሥዋዕትነት በመርካት› እና ‹ምስጉን ህላዌ› ናቸው፡፡ ለሌሎች በሚደረግ መሥዋዕትነት መርካት ማለት ለሀገር፣ ለወገን፣ ለዓለም ሕዝብ፣ ከዚያም አልፎ ለእንስሳትና ለዕጽዋት፣ ለወንዞችና ለሐይቆች፣ ለአእዋፍና ለዓሦች፣ ለሰማዩና ለምድሩ በሚከፈል መሥዋዕትነት መርካት ማለት ነው፡፡ ‹የራስ ደስታ የሌሎችም ደስታ ነው› ብሎ ማሰብ ሰውነት ሲሆን ‹የኔ ደስታ ከሌሎች ደስታ ይመነጫል› ብሎ ማሰብ ግን መልአክነት ነው፡፡ መልአክነት በምግብና መጠጥ፣ በልብስና ጫማ፣ በክብርና ዝና፣ በሥልጣንና ገንዘብ፣ በውበትና ቁንጅና ሳይሆን ይህቺን ዓለም መልካም የሰው ልጆች መኖሪያ ለማድረግ፣ ነጻነትንና ፍትሕን፣ እኩልነትንና ርትዕን፣ ሰላምንና መልካም አነዋወርን ለማስፈን በሚከፈል መሥዋዕትነት መርካት ነው፡፡ 
 
ሰው በሚያገኘው ሳይሆን በሚሰጠው መደሰት፣ በሚዋልለት ሳይሆን በሚውለው፣ በሚደረግለት ሳይሆን በሚያደርገው፣ በሚከብረው ሳይሆን በሚያከብረው ነገር ይበልጥ መደሰት ሲጀምር ነው ጽርየት የሚገኘው፡፡
‹ምስጉን ህላዌ› ማለት ‹እያመሰገኑና እየተመሰገኑ መኖር› ነው፡፡ መላእክት እያመሰገኑና እየተመሰገኑ እንደሚኖሩት ሁሉ ሰውም ጽርየት ሲኖረው የሰዎችን መልካም ሥራ ለማየት፣ ከአድናቆት ለመጀመር፣ በስሕተታቸው ከመበሳጨት ይልቅ ከበጎ ሥራቸው ተነሥቶ ስሕተታቸውን ለማረም፣ በጉድለታቸው ከመናደድ ይልቅ ጉድለታቸውን ለመሙላት፣ ከጠማማው ግራር ታቦት ለመቅረጽ፣ ከእሾሃማው እንጨት ዕጣን ለመልቀም የሚተጋ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሰው የሚያጋጥመው ፈተና፣ የሚጋረጥበት ተግዳሮት፣ የሚደርስበት ችግር የለም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ደስታውን አይነጠቅም፡፡ መሥዋዕትነቱ የሚያመጣውን በጎ ውጤት እንጂ የደረሰበትን አያስበውምና፡፡ በእርሱ ድካም የሚበረቱትን፣ በእርሱ ቁስል የሚፈወሱትን፣ በእርሱ እሥራት የሚፈቱትን፣ በእርሱ ሕማም የሚድኑትን፣ በእርሱ ሥራ የሚጠቀሙትን፣ በእርሱ ሞት የሚወለዱትን ያስባልና ደስተኛ ነው፡፡ ለዚህ ነው አመስጋኝ የሚሆነው፡፡ ተመስገኝ ህላዌም ይኖረዋል፡፡ የሚሠራው ሥራ የሚጠፋ አይደለም፡፡ ለትውልደ ትውልድ የሚኖር ነው፡፡ ምናልባት በአንድ ዘመን የተሸሸገ ቢመስል እንኳን መሬት ውስጥ እንደተቀበረ እሳተ ገሞራ አንድ ቀን ራሱን መግለጡ አይቀርም፡፡ ታሪኩን የሚጽፍለት፣ ገድሉን የሚዘክርለት ባያገኝ እንኳን እውነት ራሷ አፍ አውጥታ ምስክር ትሆነዋለች፡፡ ስለዚህ የእርሱ ኑባሬ በሞት አይገታም፡፡ ሞት ቅርጹን ይቀይረዋል እንጂ ክብሩንና ህላዌውን አይቀይረውም፡፡ እንዲያውም በቆየ ቁጥር ጣዕሙ እንደሚጨምር የገጠር ጠላ ዘመናት ባለፉ ቁጥር የሚያስታውሱትና የሚያመሰግኑት እየበዙ ይሄዳሉ፡፡ የሚፈልጉትና የሚጠቀሙበት ይጨምራሉ፡፡ ለዚህ ነው ‹ምስጉን ህላዌ› አለው ያልነው፡፡ ሲመሰገን የሚኖር ህላዌ ማለት ነው፡፡
ጽርየትን ገንዘቡ ያደረገ ሰው ከወንጀል፣ ከጥመት፣ ከኃጢአት፣ ከጥቅመኛነት፣ ከአምባገነንነት፣ ከጥፋትና ከክፋት ጋር አይገጥምም፡፡ ይጸየፈዋል፡፡ እንዲህ ያሉትን ታግሦ፣ አቻችሎ፣ ተሸክሞ፣ እንዳላየ አልፎ፣ የራሱ ጉዳይ ብሎ፣ እኔን አይመለከተኝም ብሎ አያልፈውም፡፡ ድንግዝግዝ ሰብእና እንጂ ጽርየት እነዚህን አይታገሥምና፡፡  

ዓለም የጣፈጠቺውና የምትጣፍጠው፣ በአጭሩ እድሜያችን ብዙ ነገር እንድናይ ያደረጉን፣ የሰው ልጅ ድካም ቀልሎ፣ የሰው ልጅ ሕማም ድኖ፣ የሰው ልጅ ጉድለት ሞልቶ፣ የሰው ልጅ ሥልጣኔ መጥቆ፣ የሰው ልጅ ሥርዓት ሠምሮ የምናየው በእነዚህ መልአካውያን አስተዋጽዖ የተነሣ ነው፡፡ ክፋቱ ቁጥራቸው ጥቂት ነው፡፡ ሥራቸው ግን ‹ከተባረከ ይበቃል አንዱ› እንደተባለው ነው፡፡ እነዚህ መልአካውያን በአውሬነት፣ በእንስሳነትና በሰውነት ውስጥ ያሉ ክፉ ዐመሎችን ሁሉ ገርተው፣ ቀጥተውና ገዝተው ልዕልናን ያገኙ ናቸው፡፡ በአእምሮ ሳይሆን በልዕለ አእምሮ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ማንም እንደ ባዶ ኮምፒውተር የፈለገውን ፕሮግራም አይጭናቸውም፤ አይቀይዳቸውም፤ በሳጥን አስገብቶ አይወስናቸውም፡፡ እነርሱ በሐሳብ ልዕልና፣ በመንፈስ ንጽሕና ይራመዳሉ፡፡ ድንበሮችና አጥሮች፣ ቋንቋዎችና እምነቶች፣ ባህሎችና ልማዶች፣ ጎሳዎችና ጎጦች ሊገድቧቸው አይቻላቸውም፤ እነርሱ ‹መልዕልተ ኩሉ ሥጋውያን› ናቸው፡፡ በጥቅምና በገንዘብ፣ በክብርና በዝና፣ በሥልጣንና በርስት መደለል አይቻልም፡፡ እነዚህን ሁሉ ዐውቀው፣ ንቀው፣ ልቀው፣ መጥቀው፣ ከፍ ባለው የሰው ልጅ ክብር ‹መልአክነት› ላይ ደርሰዋል፡፡ እነዚህን ለሌሎች በመለገስ ይደሰታሉ እንጂ ለእነርሱ በማግኘት አይደሰቱም፡፡ 
 
ዓለም በዚህ ዘመን የተቸገረቺው እነዚህን መልአካውያን እያጣች አውሬዎቹን እያበዛች፣ እንስሳቱን እያበረታታች፣ ሰብአውያኑንም ከጽርየት እየገታች በመሄዷ ነው፡፡ 
 
    

35 comments:

 1. dani betam des yilal erasen ayichebetalehu! amlak erejim edime yistih!

  ReplyDelete
 2. የሰው ዋና መለኪያው ምን አላደረገም? ሳይሆን ምን አደረገ? ነው፡፡ ምንም ባለማድረግማ ሙትንና ግዑዝን የሚስተካከለው አይኖርም!!!
  Dani,Edmena tena yadlih!

  ReplyDelete
 3. እንዲህ ያለውን ጽሁፍ አለምስጋና አያልፉትም።

  ከልብ አመሰግናለው።

  እግዚአብሔር ይጠብቅህ

  ReplyDelete
 4. ጥሩ እይታ ነው ። በርታ ጻፍ ዕድሜ ከጤና ይስጥህ።

  ReplyDelete
 5. Danii)
  -hulem - iske ilfete hiwetih /yeteshale/ yetemesegene/ irken lay ALLAH YANURIh..

  ReplyDelete
 6. መልአካውያን በአውሬነት፣ በእንስሳነትና በሰውነት ውስጥ ያሉ ክፉ ዐመሎችን ሁሉ ገርተው፣ ቀጥተውና ገዝተው ልዕልናን ያገኙ ናቸው፡፡ በአእምሮ ሳይሆን በልዕለ አእምሮ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ማንም እንደ ባዶ ኮምፒውተር የፈለገውን ፕሮግራም አይጭናቸውም፤ አይቀይዳቸውም፤ በሳጥን አስገብቶ አይወስናቸውም፡፡ እነርሱ በሐሳብ ልዕልና፣ በመንፈስ ንጽሕና ይራመዳሉ፡፡ ድንበሮችና አጥሮች፣ ቋንቋዎችና እምነቶች፣ ባህሎችና ልማዶች፣ ጎሳዎችና ጎጦች ሊገድቧቸው አይቻላቸውም፤ እነርሱ ‹መልዕልተ ኩሉ ሥጋውያን› ናቸው፡፡ በጥቅምና በገንዘብ፣ በክብርና በዝና፣ በሥልጣንና በርስት መደለል አይቻልም

  ReplyDelete
 7. ዮሐንስ አድገህApril 14, 2016 at 9:09 AM

  ለአንተ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፤ ለእኛ ደግሞ መልዓካውያንን ካልተቻለ እንኳ ሰብአውያንን ያብዛልን፡፡

  ReplyDelete
 8. Complete!!! It should be translated to English language so that world knows it. LONG LIVE DANIEL!

  ReplyDelete
 9. Betam denk Eyetanew bedmena tena ytebekehe.

  ReplyDelete
 10. Kbur mehuze tibebat dn. Daniel kibret wowwwwww biyalew. ye ewunet betam astemari tsihuf new,,,, tebarek rejim edime ena tena yistih!!!!!!!!!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 11. እዚህ ሶስተኛና አራተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ ምን እናድርግ? ሁሉም ሰዉ መድረስ ይችላል? ወይስ እንደ አባቶቻችን በእግዚአብሔር መመረጥ አለብን? ሃሳቡን ከዚህ በፊት ከፍልስፍና መጻህፍት አንብቤዋለሁ መንገዱን ግን ሁሉም ይደብቁታል ወይም አያዉቁትም፡፡

  ReplyDelete
 12. ሰው በሚያገኘው ሳይሆን በሚሰጠው መደሰት፣ በሚዋልለት ሳይሆን በሚውለው፣ በሚደረግለት ሳይሆን በሚያደርገው፣ በሚከብረው ሳይሆን በሚያከብረው ነገር ይበልጥ መደሰት ሲጀምር ነው ጽርየት የሚገኘው፡፡

  ReplyDelete
 13. ሰው በሚያገኘው ሳይሆን በሚሰጠው መደሰት፣ በሚዋልለት ሳይሆን በሚውለው፣ በሚደረግለት ሳይሆን በሚያደርገው፣ በሚከብረው ሳይሆን በሚያከብረው ነገር ይበልጥ መደሰት ሲጀምር ነው ጽርየት የሚገኘው፡፡

  ReplyDelete
 14. በዚህች አለም መልአክ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ይሆን? አምላክ መልአክ በዚህ ምድር ያሳየን አሜን::

  ReplyDelete
 15. ከፍባለው የሰው ልጅ ክብር(መልአክነ ላይ)ደርሰዋል እነዚህ ለሌሎችበመለገስ ይድሠታሉ እንጂ ለእነርሱ በማግኘት አይድሰቱም እግዚያብሔር ያደላቸው፡፡

  ReplyDelete
 16. Enameseginalen! Hulachinim bezih tsihuf mestawotinet rasachinin mayet alebin.Tebayachin ende awre new weys ende ensisa weys sebiawi nen...Tilku neger ene endih aynet tebay alegn bilo yerasin tikikilegna maninet mermiro mawoku ena mamenu yimesilegnal betikikil manininetachinin kawekin ena kamenin metsesetachin aykerimina tseset degimo lemeshashal beminadergew tigil yemejemeriaw new!

  ReplyDelete
 17. Enameseginalen! Hulachinim bezih tsihuf mestawotinet rasachinin mayet alebin.Tebayachin ende awre new weys ende ensisa weys sebiawi nen...Tilku neger ene endih aynet tebay alegn bilo yerasin tikikilegna maninet mermiro mawoku ena mamenu yimesilegnal betikikil manininetachinin kawekin ena kamenin metsesetachin aykerimina tseset degimo lemeshashal beminadergew tigil yemejemeriaw new!

  ReplyDelete
 18. Reading your article helped me bring a great idea [Plato] from the back of my mind .Plato in his book The Republic raised, somewhat, a similar idea. His [Plato’s] theory of soul put souls into three categories: Appetitive, Spirited and Rational/Logical. According to this ingenious theory those with appetitive dominant soul lead their life with a voracious intention to quench their trust for sex, food , shelter etc. These people according to him are closer to wild beasts because they wake up every morning with satisfaction of these beastly needs in mind. Those ruled by spirit are people who are courageous [warlike], cowards etc. These are people who basically are run by their emotions. These are people who act without giving a second though to the likely implications of their actions. The third category are those he referred to as philosopher kings, people who use their head before acting, people whose souls are governed by reason. Philosopher kings keep their appetitive and spirited natures, always in check. His [Plato] build his theory of justice from this perspective. For him a man will do justice to himself when his flesh is governed by reason. Similarly, a state will do justice only when citizens are given the chance to serve the state in accordance with the inclination of their souls- Appetitive souls should be producers, spirited souls should hold military positions and those governed by reason [philosopher kings] should hold the scepter.
  This fascinating theory of the soul, even though was the brain child of Plato, was also the focal point of his [Plato] contemporary [Aristotle] who presented his idea of it as vegetative, animal and rational.

  ReplyDelete
 19. Thank you so much.

  ReplyDelete
 20. እንደ ማር ጥሞ እንደ ወይራ የሚያበረታ መልዕክት … እናመሰግናለን፤እግዚአብሔር ይስጥልን፡፡

  …እንዲህ ያሉትን ታግሦ፣ አቻችሎ፣ ተሸክሞ፣ እንዳላየ አልፎ፣ የራሱ ጉዳይ ብሎ፣ እኔን አይመለከተኝም ብሎ አያልፈውም፡፡ ድንግዝግዝ ሰብእና እንጂ ጽርየት እነዚህን አይታገሥምና፡፡ …

  … መልአካውያን በአውሬነት፣ በእንስሳነትና በሰውነት ውስጥ ያሉ ክፉ ዐመሎችን ሁሉ ገርተው፣ ቀጥተውና ገዝተው ልዕልናን ያገኙ ናቸው፡፡ በአእምሮ ሳይሆን በልዕለ አእምሮ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ማንም እንደ ባዶ ኮምፒውተር የፈለገውን ፕሮግራም አይጭናቸውም፤ አይቀይዳቸውም፤ በሳጥን አስገብቶ አይወስናቸውም፡፡ እነርሱ በሐሳብ ልዕልና፣ በመንፈስ ንጽሕና ይራመዳሉ፡፡ ድንበሮችና አጥሮች፣ ቋንቋዎችና እምነቶች፣ ባህሎችና ልማዶች፣ ጎሳዎችና ጎጦች ሊገድቧቸው አይቻላቸውም፤ እነርሱ ‹መልዕልተ ኩሉ ሥጋውያን› ናቸው፡፡ በጥቅምና በገንዘብ፣ በክብርና በዝና፣ በሥልጣንና በርስት መደለል አይቻልም፡፡ እነዚህን ሁሉ ዐውቀው፣ ንቀው፣ ልቀው፣ መጥቀው፣ ከፍ ባለው የሰው ልጅ ክብር ‹መልአክነት› ላይ ደርሰዋል፡፡ እነዚህን ለሌሎች በመለገስ ይደሰታሉ እንጂ ለእነርሱ በማግኘት አይደሰቱም፡፡ …

  ReplyDelete
 21. I like the article and reading it brought a great idea from the back of my mind and made me realize how the points you raised are similar with theory of souls proposed by two ingenious philosophers-Plato and his contemporary Aristotle. Plato, in his theory of souls identified three categories;[of soul]-Appetitive, Spirited and Rational/Logical. According to him [Plato] people ruled by appetitive soul are those who wake up every morning having the satisfaction of elementary needs (sex, food and shelter) in mind and those governed by spirit, to Plato, are the courageous /warlike and the cowards. The last category, which he identified as the philosopher kings, are those with a soul run by reason/logic. He [plato] proposed this theory to explain his understanding of justice. A person is said to be just when and if he has his appetitive and emotional/spirited aspect of his soul in check by logic and/or reason. He said if reason does not reign and appetitive aspects take over a person’s soul that person will be no better than a wild beast and if spirit/emotion rule over a soul a person will rather be a being that never give deep thoughts to the implications of his/her actions. Plato applied this same theory to explain a just state. According to him a state is just only if it assign, to its citizens, what they are due-appetitive souls will be the producers, the spirited will be the soldiers and the reasonable/logical soul will be the philosopher king with the specter.

  ReplyDelete
 22. ‹የኔ ደስታ ከሌሎች ደስታ ይመነጫል› ብሎ ማሰብ ግን መልአክነት ነው፡፡

  ReplyDelete
 23. Kale Hiwot Yasemalin! Semtan irasachinin indinayibet yargilin!

  ReplyDelete
 24. እንደ መዕላካውያኑ እንድንኖር ይርዳን አሜን !!!

  ReplyDelete
 25. ዓለም በዚህ ዘመን የተቸገረቺው እነዚህን መልአካውያን እያጣች አውሬዎቹን እያበዛች፣ እንስሳቱን እያበረታታች፣ ሰብአውያኑንም ከጽርየት እየገታች በመሄዷ ነው፡፡
  God bless u
  ዓለም በዚህ ዘመን የተቸገረቺው እነዚህን መልአካውያን እያጣች አውሬዎቹን እያበዛች፣ እንስሳቱን እያበረታታች፣ ሰብአውያኑንም ከጽርየት እየገታች በመሄዷ ነው፡፡
  Egnanem rasachenen endenemeremer ena guzoachinen wed melaekt edenadereg endihum enesun endenaberetata egziabeher yirdan

  ReplyDelete
 26. እንደ መዕላካውያኑ እንድንኖር ይርዳን አሜን !!!

  ReplyDelete
 27. Dn.Dani Egziabher yistih bizu temrebetalehu

  ReplyDelete
 28. ዳኒየ በእውነት ደስስ የሚል ምልከታ ነው ፡፡" የኔደስታ ከሌሎች ደስታ ይመነጫል ብሎማሰብ መልአክነት ነው " እንደኔ እምነት ይሄ ደስታ የሰዋሰው ስህተት አለበት ብየ አምናለሁ ምክንያቱም ደስታ በ2 ይከፈላልና፡፡ 1ኛ joy(ከውስጣችን ዝም ብሎ ያለምንም ምክንያት ደስስ የሚል ስሜት ነው፡፡ለምሳሌ ህፃናት ብዙ ጊዜ ያለምክንያት ፍንድቅድቅ ብለው ይስቃሉ፡፡ 2ኛ pleasure(ይሄ ደግሞ conditioned ወይም ነገሮች ተመርኩዞ የሚመጣ ደስታ ነው እንደ ባህላችን,እንደ ሀይማኖታችን... ....ይለያያል እቁብ ሲወጣለት የሚደሰት ሰው አለ....ሰወችን በመርዳቱ የሚደሰት አለ... ምን ለማለት ፈልጌ ነው እውነተኛው ደስታ(joy) ምርኩዝ አያስፈልገውም ሰዎችን ብንረዳም ባንረዳም እቁብ ቢደርሰንም ባይደርሰንም እኩል ደስተኛ መሆን መቻል አለበት ሰውን በመርዳት መደሰት ሰውኛ ባህሪ እንጂ መልአካዊ ባህሪ አይመስለኝም፡፡ ሰዎችን  ብዙ ጊዜ ስለማንረዳቸው አንድ ቀን ሞልቶልን ስንቸር (ስንለግስ)ለራሳችን መደነቅን አግራሞትን ይፈጥርብናል፡፡ያስደስተናልም፡፡ ከሌላው ጊዜ በበለጠ ሰዎች ደስ ሲላቸው አየን አ፡፡ ምናልባትም እኮ አንድን ሰው ረድተነው የሆነ ጥሩ ያልሆነ ምላሽ ቢሰጠን በመርዳታች እንዲያውም እንፀፀት ይሆናል፡፡የኔ ደስታ የሚመነጨው ከእኔ ከራሴ እንጂ ከሌሎች ጓዳ ሊሆን አይችልም፡፡ ሌላ  1 ነገር ልጨምር የሰው ልጅ ከቃላቶች ሁሉ በላይ መሆን ይችላል ፡፡ ለምሳሌ የዘወትር የዕለተ አርብ የዘወትር ጸሎት ላይ እመቤታችንን አንቺ ..... .ከሀሳቦችም ሁሉ ትበልጫለሽ፡፡ ይህም ማለት አንድ ሰው እመ አምላክን ቢቃወም ለምን ተቃወመኝ፡ እንዴት ይቃወመኛል፡ ንቆኛል፡ .....እያለች አትብከነከንም ፡፡ ይልቁንም ስደቷን፡ጥማቷን.....እያሳሰበች ልጄን ማርልኝ ትላለች እንጂ::ደግሞ የምን ቃል ብትሉ ሰውን ስንረዳው የሚያስደስተን መርዳታች አይደለም ይልቁንስ እኛ ለነገሩ የምንፈጥረው story ነው፡፡ማለትም በመርዳታችን የሚሆነውን ነገር ስንስለው ደግሞ ለstory ማን ብሎን! ደራሲውም ተዋናዪም....እኛው ለምሳሌ ላስረዳ :- እኔና አንድ ቢሊየነር 100,000,000 ብር ሎተሪ ቢደርሰን አኔን ጮቤ ሊያስረግጠኝ ይችላል ቢሊየነሩ ግን ላይገርመውም ይችላል፡፡ስለዚህ እዚህ ላ ይ እኔን ያስደሰተኝ ብሩ ሳይሆን ከብሩ ባሻገር የድህነትን ተራራ አንዴት እንደማፈርሰው ብዙ የሀሳብ ፊልሞችን ስለማይ ነው፡፡ያ ቢሊየነር ግን ብር ብቻ ነው የደረሰው እንጂ በግማሹ ቤት ሰርቼ ፡ በዚህ ይሄንን አደርጋለሁ ብሎ የሚፈጥረው ታሪክ ስለሌለ ነው፡፡እኛን የማስደሰትም የማበሳጨትም አቅም ያላቸው ብር...ግዑዝ ነገሮች ሳይሆኑ እኛው ራሳችን ለራሳችን የምንፈጥረው (happy happy story or unhappy unhappy storyዎች ናቸጸው፡፡ ይሄ ደሞ እውነተኛ ደስታ አይደለም፡፡ማለትም በሌሎች ደስታም መደሰት ሰውኛ እንጂ መልአካዊ ባህሪ አይመስለኝም፡፡ይሄንንማኮ ሰዎችም ሌሎች ሲደሰቱ ደስ ይለናል፡፡ደግሞም እነርሱ ሁሌም ደስተኞች ናቸው ምክንያቱም They have got joy. እኛ እራሱ ልጅ እያለን ነበረን በሇላ ግን በmedia,school,family,culture በአንድ ላይ እንደሚፈልጉት shape ስላደረጉን ነው፡፡እንጂ ስንወለድ እኮ ስድብ ምን እንደሆነም አናውቅም ክፋት ምን እንደሆነ አናውቅም፡፡ሰውን መርዳት ያስደስት አያስደስት አናውቅም ግን ስናጠፋም ጥሩ ስንሰራም እንደሰት ነበር፡፡ሁሌም በክፋት እደተሸፈነ እንጂ ደስታ በውስጣችን አለ፡፡ዳኒየ ከምን አንግል እንዳየሀት በጥቂቱ ብታካፍለኝ፡፡አመሰግናለሁ፡፡

  ReplyDelete
 29. Thank you Brother Dani, may God bless you more and more.

  ReplyDelete