ይገርምሃል ወንድሜ በሕይወትህ ድል
አድርገህ ዋንጫ ወሰድክ ማለት እዚያው የልዕልና ማማ ላይ እንደተሰቀልክ ትቀራለህ ማለት አይደለም፡፡ አታየውም ቸልሲን መከራውን
ሲቀበል፡፡ አምና እርሱ ዋንጫ ሲበላ ያየ ሰው ዘንድሮ መከራውን ይበላል ብሎ ማን ገመተ? ብዙዎችኮ ሲወጡ መውረድን ይረሱታል፡፡
ለሚወጣ ሰው ግን መውረድ የጥላውን ያህል ቅርብ ነው፡፡ ‹እኖራለሁ ብለህ ሥራ እሞታለሁ ብለህ ኑር› ሲባል አልሰማህም? መውረድን
የረሳ ባለ ሥልጣን፣ ሕመምን የረሳ ጤነኛ፣ ድህነትን የረሳ ሀብታም፣ ሞትን የረሳ ነዋሪ፣ ድቀትን የረሳ ጻድቅ፣ ውርደትን የረሳ
ክቡር፣ ወደረሳው ነገር ለመጓዝ እንዴት ይፈጥናል መሰለህ? ድቅድቁ ጨለማ ያለው ከሻማው ሥር ነው፡፡
እነ እገሌ ካሉ፣ እነ እገሌ ቦታውን
ከያዙ፣ እነ እገሌ እዚያ ላይ ከወጡ፣ በቃ አይሳካልኝም አትበል፡፡ ሌስተርን ያየ እንዲህ አይልም፡፡ ለወትሮው የእንግሊዝ እግር
ኳስ ማንቸስተር ዮናይትድና ማንቸስተር ሲቲ፣ አርሴናልና ቼልሲ በእግራቸው ርግጥ፣ በእጃቸው ጭብጥ አድርገው የሚዘውሩት ይመስል ነበር፡፡
መቼም ዋንጫውን ከእነዚህ ከአራቱ አንዱ እንጂ ሌላው ይቀምሰዋል ተብሎ አይታሰብም ነበር፡፡ ‹ሙሴ በሩቁ ከነዓንን አያት እንጂ አልወረሳትም›
እንደሚባለው ሌሎቹ ቡድኖች ዋንጫውን በሩቁ ከማየት አልፈው ይወርሱታል ብሎ ማን ያስብ ነበር፡፡