Tuesday, March 22, 2016

ሦስቱ ወዳጆችአንድ ሊቅ እንዲህ ይመክሩ ነበር፡፡ ሰው ለዕውቀት የተሰጠ፣ ለትግል የሠለጠ፣ ለመሪነትም የተመረጠ ይሆን ዘንድ ከሦስት ዓይነት ወዳጆች ጋር መዋል አለበት ይላሉ፡፡ አንድም ከእርሱ ከሚበልጡ፣ አንድም ከእርሱ ከሚስተካከሉ፣ አንድም ደግሞ ከእርሱ ከሚያነሱ፡፡
ለአንድ ሰው እነዚህ ሦስት ዓይነት ወዳጆች ወሳኞች ናቸው፡፡ ከሦስቱ አንዱ ሲቀር፣ ወይም ደግሞ ከሦስቱ የተወሰኑት ሲበዙ ችግር አለው፡፡ የሰውዬው የአእምሮ ጤንነት ይጓደላል ወይም ይዛባል፡፡ የሚኖረው ኑሮ፣ የሚጨብጠው ዕውቀት፣ የሚሰጠው ብያኔና የሚመራበት መርሕ ርቱዕ አይሆንም፡፡ ድቀተ ልቡና ያገኘዋል፡፡ ድቀተ ልቡና ማለት ልቡና የትክክለኛነትን መርሕ ስቶ ሲወድቅ ነው፡፡ ልቡና ለስሜትና ለግልብነት ተሸንፎ፣ ከ‹ፍትርት› ጎዳና ሲወጣ ድቀት አገኘው ይባላል፡፡ ‹ፍትርት› ማለትም ማመዛዘንን ገንዘቡ ያደረገ ቀና የሥልጡንነት አካሄድ ነው፡፡
ሰው ከእርሱ ከሚበልጡት ጋር የዋለ እንደሆነ ከልምዳቸው ይማራል፣ ከብስለታቸው ይቀስማል፣ ከእድሜ ጥጋባቸው ይቋደሳል፡፡ የሚደርስበትን ነገ ዛሬ አሻግሮ ለማየት ይጠቅመዋል፡፡  ዛሬ ላይ ሆኖም የነገውን ለማቀድ ያስችለዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች በእድሜም በዕውቀትም፣ በልምድም ከእርሱ የሚበልጡ ናቸውና ቢያጠፋ ለመገሠጽ፣ ቢሳሳት መንገድ ለማሳየት፣ ቢጎድልበት ለመሙላት፣ አያፍሩትም አይፈሩትም፡፡ የገና ዳቦ ከላይ በሚነድበት እሳት በስሎ እንደሚወጣው ሁሉ እርሱም በእነዚህ በበላዮቹ ምክርና ተግሣጽ ቁጣና ወቀሳ በስሎ ይወጣል፡፡ ከነውር ለመጠበቅ፣ ከሰሕተትም ለመራቅ፣ ራስንም ቀድሞ ለማረም ‹ሐፊረ ገጽ› አንዱ መሣሪያ ነው፡፡ ‹ሐፊረ ገጽ› ሰውን መፍራትና ማፈር ነው፡፡ የሚሠራው ነገር ለሰው ነውና ‹ሰው ምን ይለዋል?› ብሎ ቀድሞ ለማሰብ መቻል፡፡ ‹ሐፊረ ገጽ› ከአደጋው በፊት በማስጠንቀቂያው፣ ከሕመሙ በፊት በምልክቱ፣ ከእቶኑ በፊት በወላፈኑ፣ ለማረም መቻል ነው፡፡ 


አንዳንድ ሰው ‹እህ› ብሎ የሚሰማው፣ ጎበዝ ብሎ የሚያደንቀው፣ ጀግና ብሎ የሚያጨበጭብለት፣ መሰንቆ ይዞ የሚዘፍንለት፣ አታሞ ይዞ የሚጨፍርለት እንጂ የሚገሥጸውንና የሚቆጣውን፣ ተው የሚለውንና የሚመክረውን አይወድም፡፡ በተለይ ደግሞ በሥልጣን ወንበር፣ በዕውቅና ማማ፣ በጥበብ ሠገነት፣ በሀብት ሠረገላ ላይ የተቀመጠ ሰው ‹ጨልጦ ገርኝቶ› እንዳያጠፋም ሆነ እንዳይጠፋ አንዱ ውሎው ከሚበልጡት ሰዎች ጋር መሆን አለበት፡፡ ሌሎቹ አፍረውትና ፈርተውት፣ ያለ ልክም አክብረውት ዝም ያሉትን እነዚህ ሰዎች በግልጽ ይነግሩታል፡፡ በሠገነት ላይ ከመሳሳቱ በፊት በእልፍኝ ያርሙታል፤ በአደባባይ ከማጥፋቱ በፊት በሹክሹታ ያቀኑታል፡፡ በእነዚህ ሰዎች ተተችቶ፣ ተፈትፍቶ፣ ተሞርዶ፣ ተወራርዶ የወጣ ነገር በውጩ ባሉት መሰሎቻቸው ዘንድ ቅቡልነት ያለው የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ በውስጥ ኦዲት የታረመ ለውጭ ኦዲት አያሠጋም፡፡
መኪና ማርሽ ብቻ ሳይሆን ፍሬንም ያስፈልገዋል፡፡ በመኪና ውስጥ የፍጥነት መጨመሪያ ብቻ ሳይሆን የፍጥነት መቆጣጠሪያም አለ፡፡ አንዳንድ ዘመናውያን መኪኖች እንዲያውም ሰውዬው ከልክ በላይ ሲያፈጥን በስክሪናቸው ላይ የሬሳ ሳጥን ምልክት ያሳያሉ፡፡ እንዲያውም መኪናን ለአደጋ የሚዳርገው ማፍጠኛው ሳይሆን ማቆሚያው አልሠራ ካለ ነው፡፡ ሰውም ማፍጠኛ ብቻ ሳይሆን ማቆሚያም ያስፈልገዋል፡፡ ከሚያጫውቱት ጓደኞቹ፣ ከሚያደንቁት የበታቾቹ ጋር ብቻ የሚውል ሰው የፍጥነት  መቆጣጠሪያ ሳይኖረው እንደሚጋልብ አሽከርካሪ ነው፡፡ አንድ ቦታ ተገልብጦ ይገኛል፡፡
ሰው መስማት ያለበት መስማት የሚገባውን ጭምር እንጂ መስማት የሚፈልገውን ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የጻፍከውን ድርሰት፣ የሠራኸውን ፕሮጀክት፣ ያቀድከውን ዕቅድ፣ የተለምከውን ዐቅድ፣ የቀረጽከውን ንድፍ፣ የወጠንከውን ትልም፤  በዕውቀትም፣ በጥበብም፣ በልምድም፣ በእድሜም በአመለካከትም ለሚበልጡህ ሰዎች ብታሳያቸው፣ ምናልባት የማትፈልገውን ትሰማ፣ የማትወደውን ታገኝ ይሆናል፡፡ ግን ትማራለህ፣ አዲስ መንገድ ታያለህ፣ ዕውቀትህ እንደ ምርት በነፋስ ይበራያል፣ ጥበብህ እንደ ወርቅ በእሳት ይፈተናል፣ ሐሳብህ እንደ ቅቤ ይነጥራል፣ ድርሰትህ እንደ እርሻ ይታረማል፡፡ በሀገራችን የእምነት መሪዎች፣ ባለ ሥልጣናት፣ ታላላቅ ነጋድያን፣ የጥበብ ሰዎች ከእኩዮቻቸውና ከአድናቂዎቻቸው ወይም ከተከታዮቻቸው አለያም ከጀሌዎቻቸው እንጂ ከሚበልጧቸው ጋር ውለው መማርን፣ መመከርን፣ መታረምን፣ መተቸትን፣ መነቀፍን፣ አዲስ መንገድ ማየትን፣ አይመርጡትም፡፡ በዚህም ምክንያት ስሕተትን ከነ ግሡ፣ ጥፋትንም ከነ ግሳግሱ፣ ድክመትን ከነሠራዊቱ፣ ወንጀልንም ከነ ኮተቱ ይዘውት አደባባይ ይወጣሉ፡፡ ካልወደቁ አይጸጸቱም፣ ካልሞቱ አይማሩም፡
ደግሞም ይኼ ቢባልም ሰው ከሚበልጡት ጋር ብቻ ሲውልም አደጋ አለው፡፡ ተግሣጽና ምክር፣ ቁጣና ወቀሳ ሲበዛ ሰውን ከማቅናት ይልቅ ያጎብጠዋል፡፡ እሳት ማብሰል ብቻ ሳይሆን ሊያሳርርም ይችላል፡፡ ከሚበልጡት ጋር ብቻ የሚውል ሰው ተቀባይ ብቻ ይሆናል፤ ሰሚ ብቻ ይሆናል፤ የበታችነት ብቻ ይሰማዋል፡፡ የሚበልጠው እንጂ የሚያንሰውና የሚተካከለው መኖሩን ይዘነጋል፡፡ እነ እንትና ያሉት ሁሉ ይሁን፤ ከነ እንትና በላይ ዐዋቂ የለም ማለት ይጀምራል፡፡  ከዚህ ሲከፋም እርሱ ለራሱ ተገቢውን ዋጋ እንዳይሰጥም ያደርገዋል፡፡ ከነዋሪነት ያኗኗሪነት፣ ከአሳቢነት የተላላኪነት ስሜት ያይልበታል፡፡ ሠሪ ሳይሆን ጠባቂ፣ መሪ ሳይሆን ታዛዥ፣ ወሳኝ ሳይሆን ተቀባይ ይሆናል፡፡ ለዚህ መድኃኒቱ ከእኩያም ከበታችም ጋር አብሮ መዋል ነው፡፡
ከእኩያ ጋር መዋል ሰውን ታጋይ፣ ተፎካካሪ፣ ተከራካሪ፣ ተሟጋች ያደርገዋል፡፡ ሳቂ፣ ተጫዋች፣ ነጻነትና ሰላም የሚሰማው ፍጡር ያደርገዋል፡፡ ማሸነፍንና መሸነፍን፣ መብለጥንና መበለጥን ይማርበታል፡፡ ያለ ፍርሃትና ያለ ሐፍረት ለመነጋገር የሚችልበት መድረክ ያገኛል፡፡ ቢላዋ በቢላዋ እንደሚሳል እኩያ በእኩያ ይሞረዳል፡፡ በእኩል ሜዳ፣ በተመጣጣኝ ዐቅም፣ በተቀረራቢ ዕድሜ፣ ውረድ እንውረድ ለማለት ያስችላል፡፡ የኛው መማሪያ ነው፤ ይኼኛው መታገያ፡፡ ያኛው መቅሰሚየ ነው፤ ይኼኛው መመርመሪያ፤ ያኛው ማግኛ ነው፣ ይኼኛው መፈተኛ፡፡
ሰው ትዝታውን፣ ታሪኩን፣ ገጠመኙን፣ ሊያውራ የሚችለው ከእኩያው ጋር ነው፡፡ የታሪክ ዝምድና ከሌለው ሰው ጋር ወግ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንተ ስለ ማይጨው ጦርነት ስታወራ እርሱ ስለ አድዋ ካስታወሰ መገናኛም የላችሁ፡፡ ተግባቦት በቋንቋ ብቻ አይመጣም፡፡ በትዝታ፣ በዕውቀት፣ በዘይቤና በዐውድ ጭምር እንጂ፡፡ እኩያ ስታጣ የሚከራከርህና የምትከራከረው ታጣለህ፤ እኩያ ስታጣ የምትቀልደውና የሚቀልድህ ታጣለህ፤ እኩያ ስታጣ የምትግባባውም ታጣለህ፡፡ እኩዮቻቸውን በስደትና በሞት የሚነጠቁ ሰዎች ኑሮን ከባድ የሚያደርግባቸው ይኼ ነው፡፡ ‹ትዝ ይልሃል ያኔ› ብለው የሚያወጉት ወዳጅ ያጣሉ፡፡ ‹እስኪ እንወራረድ› የሚሉት ሞጋች ያጣሉ፤ በምርጥ ሜዳ ላይ ያለ ተጋጣሚ ኳስ እንደመጫወት ይሆናል፡፡
ከእኩያ ብቻ የምትውል ከሆነ ደግሞ ጊዜህ በሙግትና በክርክር፣ በጨዋታና በትዝታ፣ በቀልድና በቧልት ያልቃል፡፡ የምትፈራውም የሚፈራህም ታጣለህ፡፡ ዓለም የትግል ብቻ ትመስልሃለች፡፡ የምትበልጠውም የሚበልጥህም ያለ አይመስልህም፡፡ ሁሉ እኩያህ ይመስልሃል፡፡ ብዙም የምትጨምረው ዕውቀት አይኖርም፤ አንዳንዴ ቢላዋው በደንብ እንዲስል ወደ ብረት አቅላጭ መውሰድም ያስፈልጋል፡፡ ሁሌ ከሌላ ቢላዋ ጋር ማፋጨቱ የቢላዋውን ስለት ቢጠብቀውም የተሻለ ስለት ግን አይሰጠውም፡፡
በሌላም በኩል ሐሳብህን ለማስረጽ፣ ትውልድን ለመቅረጽ፣ ሥራህን ለማሳለጥ፣ በጥቂት ሐሳብ ብዙ ሰዎችን ለማሰለፍ፣ ከእኩያ ጋር ብቻ መዋል ውጤታማ አያደርግም፡፡ ‹አንተ ማነህና፣ አናውቅህም እንዴ፣ ትናንት ከእኛ ጋር እንዲህ ሲያደርግ እንዳልነበር፣ የተነሣበትን የረሳ፣ ውለታ የበላ፣ እርሱ ከማን በልጦ ነው› የሚለው ሙግትና ክርክር የቀኑን መንገድ የዓመት፣ የሳምቱንም የክፍለ ዘመን ያደርግብሃል፡፡
ለዚህ ነው ካንተ ከሚያንሱት ጋር መዋል ያለብህ፡፡ ያልከውን ከሚሰሙ፣ በመንገድህ ከሚከተሉ፣ ሐሳብህን ከሚያደንቁ፣ መሪነትህን ከሚቀበሉ ሰዎች ጋር፡፡ ታስተምራቸዋለህ፣ ትመክራቸዋለህ፣ ያገኘህውን ታካፍላቸዋለህ፣ የአዲሱን ትውልድ ሐሳብ ታውቅባቸዋለህ፣ ሐሳብህን አሥርጸህ ቶሎ ወደ ተግባር ለመግባት ይጠቅሙሃል፡፡ አንተም ለውጥ ለማምጣት እንደምትችል ትፈትንበታለህ፡፡
የበላዮችህ ሲመከሩህ፣ አኩዮችህ ሲሞግቱህ የበታቾችህ ሲቀበሉህና ሲያደንቁህ የተመጠነ ሕይወት ይኖርሃል፡፡ ሰው በጠባዩ የሚሰማው፣ የሚመራለት፣ የሚከተለው፣ የሚያጨበጭብለት፣ አበጀህ ደግ አረግክ የሚለው ይፈልጋል፡፡  በእርሱ የተዘራውን የሚዘራበት መሬት ይሻል፡፡ መክሮ፣ ዘክሮ፣ አስተምሮ፣ አሳድጎ፣ ሐሳብ ሰጥቶ፣ ገንዘብ አውጥቶ፣ ዕቅድ አቅዶ፣ መንገድ ተልሞ ለውጤት ሲበቃ ማየት ደስ ይለዋል፡፡ ሰው የሚያንሰውን ስለሚወልድ እንጂ የሚበልጠውን ቢወልድ ኖሮ ትውልድ አይቀጥልም ነበር› የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ለዚህ ነው በዕውቀት፣ በሀብት፣ በእድሜ፣ በደረጃ፣ በልምድ፣ በሥልጣን፣ ከአንተ ከሚያንሱ ሰዎች ጋር መዋልና መጎዳኘት የሚያስፈልግህ፡፡
ከእነዚህ ሰዎች ከበሬታን ታገኛለህ፡፡ ከእነዚህ ሰዎች በትምህርትና በመድረክ የማይገኝ ዕውቀትም ትሸምታለህ፡፡ ‹የደኻ ምክር ጥሩ ነው የሚሰማው የለም፤ የሐምሌ ውኃ ንጹሕ ነው የሚጠጣው የለም› ከተባለው ወቀሳም ነጻ ትሆናለህ፡፡ ከሪፖርትና ከስታትስቲክስ ውጭ የሆነውን ሰውኛ ምላሽ የምታገኘው ከእነርሱ ነው፡፡ ከእነርሱ በምታገኘው ሞራልና ክብር ከእኩዮችህ ትሟገትበታለህ፣ ከበላዮችህ ትማርበታለህ፡፡ ባህላዊውንና አገርኛውን ዘይቤ በሚገባ የምታገኘው ከእነርሱ ነው፡፡
ከበታቾችህ ጋር ብቻ የምትውል ከሆነ ግን አሁንም በሽታ ነው፡፡ አንተ ብቻ ዐዋቂ፣ አንተ ብቻ ባለ ጸጋ፣ አንተ ብቻ መካሪ፣ አንተ ብቻ ዘካሪ፣ አንተ ብቻ ታላቅ፣ አንተ ብቻ መሪ የሆንክ ይመስሃል፡፡ ትታበያለህ፣ ከልክ ያለፈ ምስጋናና ውዳሴ ትለምዳለህ፡፡ ራስህን መለኪያ አድርገህ ትቆጥራለህ፡፡ እነርሱ ስላደነቁህ ዓለም ሁሉ ያደነቀህ፣ እነርሱ ስለወደዱህ ዓለም ሁሉ የወደደህ፣ እነርሱ ስለሚከተሉህ ዓለም ሁሉ ያንተ ተከታይ፣ እነርሱ ስለሚሰሙህ አንተ ብቻ መናገር ያለብህ ሊመስልህ ይችላል፡፡ ከበታች ጋር ብቻ መዋል ያልተፈለገ ንግሥናን ያመጣል፡፡ ናይጀሪያዎች ‹በዐላዋቂዎች መንደር ያለ የሆስፒታል ዘበኛ እንደ ዶክተር ይቆጠራል› እንደሚሉት፡፡
ለዚህ መድኃኒቱ ከእኩዮችህና ከሚበልጡህ ጋርም መኖር ነው፡፡ ሦስቱም እንደየ አግባቡ ያስፈልጉሃል፡፡ አንዱ ሲጎድል ትዕቢተኛ፣ አንዱ ሲጎድል ዝቅተኛ፣ አንዱም ሲጎድል ብቸኛ ያደርግሃል፡፡ 
     

 
  

26 comments:

 1. ናይጀሪያዎች ‹በዐላዋቂዎች መንደር ያለ የሆስፒታል ዘበኛ እንደ ዶክተር ይቆጠራል› እንደሚሉት፡፡

  ReplyDelete
 2. kalehiywet yasemalin.

  ReplyDelete
 3. Thank you for your time, suggestion and money.

  ReplyDelete
 4. ‹የደኻ ምክር ጥሩ ነው የሚሰማው የለም፤ የሐምሌ ውኃ ንጹሕ ነው የሚጠጣው የለም›

  ReplyDelete
 5. ahunim tebarek tibebun yabzalih. endante aynet shi yihunulin

  ReplyDelete
 6. እግዚአብሔር ይሥጥልኝ፡፡

  ReplyDelete
 7. ውድ ወንድማችን ዲ/ን ዳንኤል
  ጥሩ አስተማሪ ጽሁፎችን ስለምትመግበን እግዚአብሔር እድሜና ጤና ከሙሉ ሰላም ጋር ይስጥልን፡፡ ይህም እንደ ሌሎቹ ጽሁፎችን በጣም አስተማሪ ነው፡፡ የሐምሌን ውሃ ምሳሌ ግን እኔ ከማውቀው ተለይቶብኛል፡፡ ሰሚ ቢያገኝ ምክር ከድሃ ጠጪ ቢያገኝ የጥቅምት ውሃ ሲባል ነበር የምሰማው፡፡ የሐምሌ ውሃ እኮ የክረምቱ መጀመሪያ ስለሆነ እንኳን ለመጠጥ ለመታጠቢያም ይከብዳል፡፡ ግን እንደ ክረምቱ አገባብና እንደየ ሀገሩ ሊለያይ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ከሆነ ግን የጥቅምቱ ውሃ ነው ኮለል ብሎ የሚጠራው፡፡ የድሃ ምክርና የሐምሌ ውሃ አብሮ የሚሄድ አይመስለኝም፡፡

  ReplyDelete
 8. I really thank you very much, Dani. As usual, the article is so much educative, esp. for those like me: the ones who do not know whom to live with.

  ReplyDelete
 9. በህይወታችን ልንከተለው የሚገባ ልዩ እይታ ነው!!!እናመሰግናለን

  ReplyDelete
 10. ሦስቱም እንደየ አግባቡ ያስፈልጉሃል፡፡ አንዱ ሲጎድል ትዕቢተኛ፣ አንዱ ሲጎድል ዝቅተኛ፣ አንዱም ሲጎድል ብቸኛ ያደርግሃል፡፡ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፣ ጸጋውን ያብዛልህ

  ReplyDelete
 11. Dear Daniel, I agree with the idea you raised which I use to live it . Above all the way you tried to simplify the main point so that all parts of social status can read ,understand and see themselves using it as a mirror .
  There is one known saying in the past which you mention it ‹የደኻ ምክር ጥሩ ነው የሚሰማው የለም፤ የሐምሌ ውኃ ንጹሕ ነው የሚጠጣው የለም› In the present world, I think it is not only the poor who knows good advice but also the rich ,the middle callas,the scholars like you from different types of skills , the politicians, elders,very few matured youths and etc . The same is true for the water which was known as Yetekimet wuha not Yehamle ; in the 21st century people use water from any sources in what ever month as much as it is treated and distrusted well . So let us change our old way of thinking and try to govern ourselves by valuing the result of humankind's brain development and growth which God gave us through life and think big by marching forward with the rest of the world .

  ReplyDelete
 12. E n a m e s e g n a l e n . . .

  ReplyDelete
 13. good idea thank you..... we you should work together

  ReplyDelete
 14. መልካም ምክር ልብ እንደመስጠት ነው

  ReplyDelete
 15. በዐላዋቂዎች መንደር ያለ የሆስፒታል ዘበኛ እንደ ዶክተር ይቆጠራል›

  ReplyDelete
 16. በዐላዋቂዎች መንደር ያለ የሆስፒታል ዘበኛ እንደ ዶክተር ይቆጠራል›

  ReplyDelete
 17. ወንድም ዳኒ እግዚአብሔር እድሜና ጤና ይስጥህ። ጊዜህንም አብዝቶ ይባርክልህ።

  ReplyDelete
 18. YALTEGEBERKUT GIN METEGBER YEMIYASFELIGEN EYITA NEEW

  ReplyDelete
 19. ግሩም ነዉ ... አስተማሪ አያሳጣን!! እግዚአብሔር ረጂም እድሜ፣ ጤናና ሰላም ይስጥህ::

  ReplyDelete
 20. Egziabher Yistln Wendmachn!!!!!!!

  ReplyDelete
 21. እግዚያብሔር ረጅም እድሜ ከጤና ጋር ይስጥህ፡፡ እንደዚህ ለህይወት መንገድ የሚሆኑ ምክሮችህ አይለዩን፡፡

  ReplyDelete