click here for pdf
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገርሙኝ ዘፈኖች አንዱ ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› የሚለው ነው፡፡ እሥራኤላዊና ጂፕሲ ይህንን ቢሰሙ ምን
ይሉ ይሆን? እላለሁ፡፡ አይሁድ በመላው ዓለም ለ1900 ዓመታት ያህል ተበታትነው ሲኖሩ በየአካባቢው ሰው ነበራቸው፤ያውም እንደ ብረት የጠነከረ ማኅበረሰብ፤ ሀገር ግን አልነበራቸውም፡፡ ሀገር ማለት ሰው ከሆነ አይሁድ ሀገር ፍለጋ ከሺ ዓመታት በላይ መኳተን አልነበረባቸውም፡፡ በአውሮፓ የሚኖሩት ጂፕሲዎች የታወቀ ማኅበረሰብ አላቸው፡፡ ነገር ግን ሀገር የላቸውም፡፡ ሀገር ማለት ሰው ቢሆን ኖሮ ጂፕሲ የሚባል ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ጂፕሲ የሚባል ሀገርም ይኖር
ነበር፡፡ ግን የለም፡፡
በአሜሪካ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ‹በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን› የምትባል ሀገር ግን የለቺም፡፡
1.3 ሚሊዮን የሚደረሱ ግሪኮች በአሜሪካ ይኖራሉ፡፡ ‹የአሜሪካ ግሪኮች› የምትባል ሀገር ግን የለችም፡፡ ‹ግሪክ ሲሠራ አሜሪካ
ይኖራል፣ ሲያረጅ ግሪክ ይጦራል› የተባለው ሀገር ሰው ብቻ ስላልሆነ ነው፡፡
ሰዎች ተሰብስበው ሀገር ሊመሠርቱ አይችሉም፡፡ በየሀገሩ የተሰበሰቡ ማኅበረሰቦች ‹ኮሙኒቲ› ይባላሉ እንጂ ሀገር አይባሉም፡፡
ሀገር ሀገር ለመሆንና ለመባል ከሰው በተጨማሪ የምትፈልገው ብዙ ነገር አላትና፡፡ ሀገርን ሀገር ለማስባል መሬትም ያስፈልጋል፤ መሬት
ሳይኖርህ ሰው ስለሰበሰብክ ብቻ ሀገር ልትሆን አትችልም፡፡ ያውም የእኔ የምትለው፣ የምትሞትለትና የምትለፋለት ታሪካዊ መሬት ያስፈልግሃል፡፡
አይሁድ በ1930 አካባቢ በኡጋንዳ ኡዋሲን ጊሹ (Uasin Gishu County) በተባለ ቦታ እንዲሠፍሩና
ሀገር እንዲኖራቸው ታስቦ ነበር፡፡ እንደ ቴዎዶር ኸርዝል ያሉ ታላላቅ የጽዮናዊነት መሪዎችም ለጊዜውም ቢሆን ተስማምተውበት ነበር፡፡ ብዙኀኑ አይሁድ ግን ‹ሀገር ማለት የሆነ መሬት አይደለም፡፡ ታሪካዊ መሬት ነው› ብለው ተቃወሙት፤ ሀገር ማለት የሆነ መሬት ብቻ ቢሆን ለአይሁድ ከዛሬዋ እሥራኤል ይልቅ በአየር ንብረትና በተፈጥሮ
ማዕድን፣ ብሎም በአቀማመጥ ኡጋንዳ ትሻላቸው ነበር፡፡