Monday, February 15, 2016

የጋማ ከብቶች

በቀደም ድሬዳዋ ላይ ዓሣ ዘነበ ብለን ከአንድ ወዳጄ ጋር ስናወራ ‹ባክህ ይሄ እንኳን የጋማ ከብቶች ወሬ ነው› አለኝ፡፡ እኔም አነጋገሩ ገርሞኝ ‹የጋማ ከብቶች ደግሞ እነማን ናቸው› ስል ጠየቅኩት፡፡
‹የማያመነዥኩ ናቸዋ› አለና አሳጠረው፡፡
‹እኮ ከድሬዳዋ ዓሣ ጋር ምን ያገናኘዋል› 
 
‹እኔ ድሬዳዋ እንኳን ዓሣ የዓሣ ፋብሪካ ቢወርድላት ችግር የለብኝም፡፡ ለምን፣ እንዴት፣ መቼ፣ ማን፣ ፊትና ኋላ፣ ቀኝና ግራ የሚባሉ ነገሮች ፋሽናቸው አለፈ እንዴ? አንድ ሚዲያ ‹ዓሣ ዘነበ› ከማለቱ በፊት በጋዜጠኛውና በሚዲያ ኃላፊዎች ላይ ‹ማመዛዘን› የሚባለው ነገር መዝነብ ነበረበት፡፡ ያንን የዘገበ ዘጋቢ ዓሣ ሊያዘንብ የሚችል ታሪካዊ፣ ሳይንሳዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ አየር ንብረታዊ፣ ሌላም ምክንያት መኖር አለመኖሩን ሳያጣራ፣ በየቦታው ተዘዋውሮ ሳያረጋግጥ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በኅሊናው መዝኖ ከግምት በላይ ሳያልፍ፣ እንዴት ለዘገባ ያበቃዋል፡፡ ይኼ የጋማ ከብትነት ይባላል፡፡
 
የጋማ ከብት ይበላል ግን አያመነዥክም፡፡ ያገኘውን መዋጥ ብቻ ነው፡፡ እስኪ የቀንድ ከብቶችን ተመልከት ቀን የበሉትን ማታ ጋደም ብለው በጽሞና ሲያመነዥኩት ታዳምጣለህ፡፡ ይፈጩታል፣ ይሰልቁታል፣ ያጣጥሙታል፣ ያወጡታል፣ ያወርዱታል፡፡ አንዴ ገባ ብለው እንዲሁ አይተውትም፡፡ ፊውዝ እንኳን የማይስማማው የኤሌክትሪክ ኃይል ሲመጣ አላሳልፍም ብሎ ራሱ ይቃጠላል፡፡ ብሬከር እንኳን በዐቅሙ የማይሆን ኤሌክትሪክ ሲመጣ ይዘጋል፡፡ እንዴት ሰው እንደ ጋማ ከብት የሰጡትን ሁሉ ይውጣል፡፡  

አሁን በየስብሰባውና በየሚዲያው ‹የመለስ ራእይ› ሲባል እንሰማለን፡፡ የመለስ ራእይ ምን እንደሆነ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት ብለህ ግለጠው ቢባል ስንቱ ያውቀዋል? የሆነ ቦታ ሲባል ስለሰማ ሳያመነዥክ እርሱም ይለዋል እንጂ፤ እውነት ይሄ ሁሉ ሰው ራእዩን ዐውቆት፣ ከዚያ ገብቶት፣ ከዚያም ተስማምቶበት ነው እያወራ ያለው፡፡ አንዱ፣ እገሌ የተባሉት ባለሥልጣን ሥራ የሚቀጥሩት በዘመድ ነው ሲባል ይሰማል፡፡ ጓደኞቹ ደግሞ ‹የአንተ አገር ሰውኮ ናቸው› ይሉታል፡፡ ይሄ ነገር ሲደጋገምበት ‹ለምን አልጠይቃቸውም› ብሎ ቢሯቸው ሄደ፡፡ ምናለ ቢያንስ - የት ሀገር፣ የት ቀበሌ፣ የት መንደር ናቸው የሚለውን እንኳን ቢያጣራ፡፡ ቢሯቸው ገብቶ የሀገራቸው ሰው መሆኑን ይገልጥና ሥራ ይለምናል፡፡ እርሳቸውም በመንደርና በጎጥ የጠበቡ ነበሩና ‹ለመሆኑ ሀገርህ የት ነው› ይሉታል ‹ከእርስዎ ሀገር› ይላል፡፡ ‹የኔ ሀገር የት ነው› ሲሉት ‹ከኛ ሀገር› አለ አሉ፡፡
 
አሁንማ የጋማ ከብቶች ወረሩንኮ፡፡ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው፣ ማኅበራዊ ሚዲያው፣ ሥልጣኑ፣ ኪነ ጥበቡ፣ ቤተ እምነቱ፣ ምሁርነቱ፣ ንግዱ፣ ፓርቲው፣ ምኑ ቅጡ በጋማ ከብቶች እየተሞላ ነው፡፡ እስኪ ከፈለግክ ‹እገሌ ሞተ› በልና ፌስ ቡክ ላይ ለጥፍ፡፡ ምንም ነገር ሳያጣራ ግማሹ ፕሮፋይል ፒክቸሩን ጥቁር ያደርጋል፣ ሌላው ‹አር. አይ. ፒ› ይላል፣ ሌላው ደግሞ ምናልባት ልቅሶ ተቀምጦ የዕድር ብር በልቶ ይሆናል፡፡ ‹በዓሉ ግርማ ዳጋ እስጢፋኖስ ተገኘ› ሲባል በአንድ ጀልባ ሮጦ ሊያጣራ የሚችለው የባሕር ዳር ነዋሪ አብሮ ‹ሼር› ና ‹ላይክ› ካደረገ ከዚህ በላይ የጋማ ከብትነት ምን አለ?
 
ወዳጄ፣ማመን ማለት ፈጽሞ አእምሮን መነሣት አይደለም፡፡ አእምሮ የፈጠረልህን ፈጣሪ ከሆነ የምታምነው ማመዛዘንን እምነት አይቀማህም፡፡ የቅዱስ እስጢፋኖስን በዓል አከብራለሁ ብሎ የሄደ ምእመን ‹ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወገረ› ሲሉት ‹እልልልልልል› ብሎ የሚያቀልጠው ከሆነ ዐጸዱ በጋማ ከብቶች ተሞልቷል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው የጋማ ከብትነት ነው ፓስተሮቻችንና አስተማሪዎቻችን ልብሳችሁን አውልቁ፣ ሣር ብሉ፣ መሬት እንዳይነካን አጎንብሱና እንቁምባችሁ ሲሉን ያለማመንዠክ እንድንቀበላቸው ያደረገን፡፡
 
ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን እናቱ ትምህርት ቤት ባስገባቺው ጊዜ መምህሩ የእብራይስጥን ፊደል ሲያስቆጥረው ‹አሌፍ› በል አለው፡፡ ‹አሌፍ› አለ፡፡ ‹ቀጥሎ ደግሞ ‹ቤት› በል አለው፡፡ ዝም አለ፡፡ መምህሩ ተናደደና ‹ለምን ቤት አትልም› ሲል ተቆጣው፡፡ ሕጻኑ ክርስቶስም ‹መጀመሪያ የአሌፍን ትርጉም ንገረኝና ከዚያ ቀጥዬ ቤት እላለሁ› አለው ይላል ተአምረ ኢየሱስ፡፡ ታድያ ምነው የእርሱ ተከታዮች መጠየቅንና መመዘንን ፈሩ? ለምንስ የጋማ ከብትነት በዛ?
 
በደርግ ዘመን ‹ጓድ መንግሥቱ እንዳሉት› እየተባሉ የሚነገሩት ጥቅሶች ሁሉ ብዙዎቹ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ራሳቸው የማያውቋቸው እንደሆኑ በኋላ ታውቋል፡፡ እንዲያውም በአንድ ስብሰባ ላይ ‹ሰውን ሰው ያደረገው ሥራ ነው› ብለዋል ጓድ መንግሥቱ ብሎ አንዱ ካድሬ ይጠቅሳል፡፡ ያውም ራሳቸው መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ባሉበት፡፡ እርሳቸው ራሳቸው ገርሟቸው ‹ኧረ ይሄን ነገር እኔ አልተናገርኩም› ይሉና ከስብሰባው በኋላ ያስጠሩታል፡፡ ‹ይህንን ንግግር የኔ መሆኑን ከየት አገኘኸው› ሲሉት ‹መቼም እንዲህ ያለ ንግግር ከእርስዎ አፍ ካልሆነ በቀር ከአድኃሪያን አፍ አይወጣም ብዬ ነው› አለ አሉ፡፡ ካድሬ ምን አለበት፤ ‹ነው› ከተባለ ነው፣ ‹አይደለም› ከተባለ፣ አይደለም ብሎ ይኖራል፡፡ 
 
በወዲህም ሆነ በወዲያ ቆመው ሚዲያውን የተቆጣጠሩት ወገኖቻችን ጥቂት ማመንዠክ ቢችሉ ኖሮ እኛን የአህያ ሆድ አድርገው አይቆጥሩንም ነበር፡፡ የሚበሉት እህል ይለያያል እንጂ ሁለቱም አያመነዥኩም፡፡ ሁለቱም ወዳጆቻቸው የነገሯቸውን ሳያመሰኩ ይውጣሉ፤ ሁለቱም ጠላት ከሚሏቸው የሚመጣውን አይቀበሉም፡፡ እነርሱን እስከ ደገፈና ጠላቶቻቸውን እስከ ተቃወመ ድረስ ሁለቱም ማንጠሪያ የላቸውም፡፡ 
 
በተለይ ደግሞ ዘረኝነትና ማይምነት ሲጨመሩበት የጋማ ከብትነት የከፋ ይሆናል፡፡ ዘረኞች ከራሳቸው ወገን የሚመጣውን ሁሉ እንዳለ ይውጡታል፡፡ ከዚያ ውጭ ያለው ሁሉ ሊያጠፋቸው፣ ሊቀማቸው፣ ሊያንቋሽሻቸው የሚመጣ አድርገው ስለሚመለከቱት ከወገናቸው ውጭ ማንንም አያምኑም፡፡ በባለሞያ ያልተቃኙ፣ በገለልተኝነት ያልተበየኑ፣ በማስረጃ የማይበጠሩ፣ ስሜትና እውነትን ያልለዩ፣ የታሪክ ድርሳናት በየቦታው ሲታተሙና ‹ለብሔረሰቡ› ሲሠራጩ ሃይ ባይ የላቸውም፡፡ ዘረኞች እውነትን በዘር መነጽር ነው የሚያዩዋት፡፡ ምን ተነገረ? ሳይሆን ማን ተናገረ? ነው ቁም ነገሩ? ቀጥሎ ደግሞ የኛ ወገን ነው ወይስ የነዚያ? ይባላል፡፡ የራስህ ወገን የነገረህን ዝም ብለህ መጋት ነው፡፡ ቢቻል ቢቻል ጀግና ነህ፣ ማራኪ ነህ፣ የሠለጠንክ ነህ፣ የዚህና የዚያ ምንጭ ነህ፣ ድንቅ ባህልና ምርጥ ታሪክ አለህ ይበልህ፡፡ ሳታመነዥክ ትጋተዋለህ፡፡ ይኼ ካልሆነ ደግሞ ተጨቁነህ፣ ተረግጠህ፣ ማንነትህ ተረስቶ፣ ከሰው በታች ሆነህ ነበር፤ እነ እገሌና እነ እገሊት ጠላቶችህ ናቸው ብሎ ሙሾ ያውርድልህ አሁንም ትጋተዋለህ፡፡ ማንጠር የሚባል ነገር የለም፡፡ 
 
ዘረኝነት ማንጠር የሚባለውን ሞያ አጥፍቶብናል፡፡ ቅቤን ከአንጉላው የሚለየው ማንጠር ነው፡፡ ሲነጠር ቅቤው ለብቻው አንጉላው ለብቻው ተለይቶ ቁጭ ይላል፡፡ ለአንጉላ ተብሎ ቅቤ አይጣልም፤ ለቅቤም ተብሎ አንጉላ አይበላም፡፡ ይነጠራል እንጂ፡፡ ያንተ ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና ቅርስ ስለሆነ ብቻ ዝም ብለህ አትዋጠው፤ አንጥረው፡፡ ዕውቀት ወደሚባል፣ ማስረጃ ወደሚባል፣ መረጃ ወደሚባል፣ ክርክር ወደሚባል፣ ተጠየቅ ወደሚባል፣ ኅሊና ወደሚባል፣ እሳት ላይ አውጣው፡፡ ይነጥራል፡፡ አንጉላው ከቅቤው ይለያል፡፡ ካልሆነ ግን በተለይ የማያመነዥኩ ሰዎች ሆድ ውስጥ ከገባ አደጋ ነው፡፡ 
 
እንክርዳድ እክርደድ የተንከረደደ
ስንዴ መስሎ ገብቶ ስንቱን አሳበደ፤ የተባለው ለዚህ አይደል፡፡ 
 
ማይምነትን በእናቶቻችን ቋንቋ ለመተርጎም ‹የማይለቅም፣ የማያነፍስ፣ የማያበጥር፣ የማይነፋ፤ እንዲሁ የሚያስፈጭና የሚበላ› ማለት ነው፡፡ እናቶቻችን እህሉን ከቆሻሻው ለመለየት የቻሉትን በእጅ ይለቅማሉ፣ ያልተቻለውን በሰፌድ ያነፍሳሉ፣ የተረፈውን በማበጠሪያ ወንፊት ያበጥራሉ፡፡ ተፈጭቶ ከመጣ በኋላ ደግሞ በጥቅጥቅ ወንፊት ይነፉታል፡፡ ይኼ ሁሉ ልፋት ዓይነተኛውን እህል ለማግኘት ነው፡፡ ዓይነተኛውን እውነት ለማግኘትም በመረጃና በማስረጃ፣ በዕውቀትና በብስለት፣ በተጠየቅና በመጠንቀቅ መልቀም፣ ማንፈስ፣ ማበጠርና መንፋት ያስፈልጋል፡፡

ምሁራኑ እንኳን በየዐውደ ጥናቱ ጥናታዊ ጽሑፍ ብለው የሚያቀርቡት ተዘጋጅቶና ተሰናድቶ የመጣውን ‹ዳታ›፣ ለበዓሉ የሚስማማውን ቀለም፣አየሩና ነፋሱ ሲለው የከረመውን እንጂ ዘወር ያለ፣ የተመዘነ፣የነጠረና፣የተመረመረ ነገር አይናገሩም፡፡ በዜና የሰማነውን በጥናታዊ ጽሑፍ ቅርጽ ያቀርቡታል፡፡ ሳያመነዥኩ ያቀርባሉ፤ ሳናመነዥክ እንበላለን፡፡
 
በድሬዳዋ የተጀመረውን ነገር ድሬዳዋ ላይ በተፈጸመ የጋማ ከብትነት እንዝጋው፡፡ መምህሩ ውጭ ቁጭ ብሎ ተማሪውን ይጠራውና ‹እዚያ ክፍል ሄደህ እኔ መኖሬንና አለመኖሬን አይተህ ንገረኝ› ይለዋል፡፡ ተማሪውም ቀጥ ብሎ ሄዶ በመስኮት ያይና ተመልሶ መጥቶ ‹የሉም› ይለዋል፡፡ ይሄኔ መምህሩ በጥፊ ተማሪውን መታው፡፡ ተማሪው የደረሰበትን ይናገርና አባቱን ይዞት ይመጣል፡፡ አባትዬውም እንደመጡ ‹እንዴት ልጄን ትመታለህ› ብለው ይፎክራሉ፡፡ መምህሩም ‹ታድያ ለምን ከክፍል ውስጥ የለም ይለኛል› አላቸው፡፡ አባት መለስ ይሉና ልጃቸውን ‹እንደዚህ ብለሃል› ይሉታል፡፡ ‹አዎ› ይላል ተማሪው፡፡ ‹መምህሩን ከክፍል ውስጥ የሉም አልክ› አባት አጽንቶ ጠየቀ፡፡ ‹አዎ ብያለሁ› ይላል ልጅ፡፡ አባትም ተናድዶ ‹ታድያ እርሳቸው ከሌሉ ማን እያስተማረህ ነው ተምሬ መጣሁ የምትለው› ብለው ልጃቸውን ጥፊ ደገሙት ይባላል፡፡ እንዲህ ነው የጋማ ከብትነት የመጣልህን መዋጥ፡፡

31 comments:

 1. ንተ ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና ቅርስ ስለሆነ ብቻ ዝም ብለህ አትዋጠው፤ አንጥረው፡፡ ዕውቀት ወደሚባል፣ ማስረጃ ወደሚባል፣ መረጃ ወደሚባል፣ ክርክር ወደሚባል፣ ተጠየቅ ወደሚባል፣ ኅሊና ወደሚባል፣ እሳት ላይ አውጣው፡፡ ይነጥራል፡፡ አንጉላው ከቅቤው ይለያል፡፡ ካልሆነ ግን በተለይ የማያመነዥኩ ሰዎች ሆድ ውስጥ ከገባ አደጋ ነው፡፡
  እንዲህ ነው የጋማ ከብትነት የመጣልህን መዋጥ፡፡

  ReplyDelete
 2. እንደ እሥካሁኑ ጥሩ እይታ ነዉ፡፡

  ReplyDelete
 3. Thanks Dn. Daniel K. well articulated; it's a good lesson for the equine!

  ReplyDelete
 4. መልካም ነው ዲ/ን ዳንኤል፣በመንግስትም በሃይማኖትም መሪቻችን የጋማ ከብት በዛ።

  ReplyDelete
 5. ዘረኝነት ማንጠር የሚባለውን ሞያ አጥፍቶብናል፡፡ ቅቤን ከአንጉላው የሚለየው ማንጠር ነው፡፡ ሲነጠር ቅቤው ለብቻው አንጉላው ለብቻው ተለይቶ ቁጭ ይላል፡፡ ለአንጉላ ተብሎ ቅቤ አይጣልም፤ ለቅቤም ተብሎ አንጉላ አይበላም፡፡ ይነጠራል እንጂ፡፡ ያንተ ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና ቅርስ ስለሆነ ብቻ ዝም ብለህ አትዋጠው፤ አንጥረው፡፡ ዕውቀት ወደሚባል፣ ማስረጃ ወደሚባል፣ መረጃ ወደሚባል፣ ክርክር ወደሚባል፣ ተጠየቅ ወደሚባል፣ ኅሊና ወደሚባል፣ እሳት ላይ አውጣው፡፡ ይነጥራል፡፡ አንጉላው ከቅቤው ይለያል፡፡ ካልሆነ ግን በተለይ የማያመነዥኩ ሰዎች ሆድ ውስጥ ከገባ አደጋ ነው፡፡

  ReplyDelete
 6. ፍቅር ፍቅር አለኝ!!! ዘረኝነት ውደቀት ነው! በሽታ ነው! መርዝ ነው! ልክፍት ነው! ካንስር ነው! ሃጢአት ነው! ጠባብነት ነው! ርሃብ ነው! እልቂት ነው! ስው ሆኖ ስው አለመሆን ነው! ድድብና ነው! እስኪ አስቡት 16-20 ዓመት ተምሩ በስፈር፣በጏጥ፣ በቀዬ፣ በደም፣ በአጥንት፣ ሲያስብ!! ጉድ ጉድ.....ጉድ.....አለ መፈጠር ይሻለኝ ነበር! የእኔ ምርጫ በሆነ ነበራ!!

  ReplyDelete
 7. ፍቅር ፍቅር አለኝ!!! ዘረኝነት ውደቀት ነው! በሽታ ነው! መርዝ ነው! ልክፍት ነው! ካንስር ነው! ሃጢአት ነው! ጠባብነት ነው! ርሃብ ነው! እልቂት ነው! ስው ሆኖ ስው አለመሆን ነው! ድድብና ነው! እስኪ አስቡት 16-20 ዓመት ተምሮ/ተምራ በስፈር፣በጏጥ፣ በቀዬ፣ በደም፣ በአጥንት፣ ሲያስብ!! ጉድ ጉድ.....ጉድ.....አለ መፈጠር ይሻለኝ ነበር! የእኔ ምርጫ በሆነ ነበራ!!

  ReplyDelete
 8. ፌስቡክ፣ቫይበር፣ሴልፎን፣ኢንተርኔት፣ዲሽ ካለን አዋቂ ነን። ይህ ሁሉ መዘበራረቅ፣መደበላለቅ ያደነቆረን እኮ ምሑር ወይም መሪ ስለጠፋ አይደለም። ቴክኖሎጂውን የተጠቀምንበት ወይም የጠቀመን መስሎን ስለጠፋንበት ነው። ኢቲቪ፣ፋና፣ኢቶፒካ ሊንክ በደረቅ ፕሮፓጋንዳ፣በሕልም ዓለም (ድራማ) ፣በመዝናኛ ስም በምዕራባውያን የሴሰኝነትና የሱስ ትረካ ካደነዘዘን፣ ካደነበዠን ሕዝቦች የሚጠበቀው ሌላ ሊሆን አይችልም። የራሳችን መገለጫ የሆነውን ባሕላችንን፣ታሪካችንን፣ወጋችንን መርምረን፥ የተዛባውን አቃንትን፣የተሳሳተውን አርመን፣በጎውን አጠናክረን እንዳንሄድ፤ እድሜ ለወያኔ እርሱን እስካቆየው ትውልዱን በድንቁርና ቸነፈር መፍጀት ዓላማው ነውና የማናውቀውን ያስግተናል። ደንቆሮዎች በዘመኑበት አገር ሕዝብ ይማራል ማለት ዘበት ነው።

  አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ሞት i
  የእድገትና ትራንስፎርሜሽናችን እቅድ ይሳለጣል i
  ሙሰኞች ይጋለጣሉ፥ የተፈቀደላቸው ይናጥጣሉ i
  ጠባቦች እንዲሰፉ፥ ትምክሕትኞች እንዲጠፉ እንጋደላለን i
  11 በመቶ እንመነደጋለን፥ ወደዱም ጠሉ በ2020 መካከል እንገባለን i
  አፍ እንጂ ጆሮ አያስፈልገንም i
  የኢቲቪ ድራማ ከሚቀር ዝናቡ ይጠንቀር i
  ሌላም … ሌላም … ሌላም…

  … አይ ኢትዮጵያ ሃገሬ i

  ተስፋዬ

  ReplyDelete
 9. መምህሩ ውጭ ቁጭ ብሎ ተማሪውን ይጠራውና ‹እዚያ ክፍል ሄደህ እኔ መኖሬንና አለመኖሬን አይተህ ንገረኝ› ይለዋል፡፡ ተማሪውም ቀጥ ብሎ ሄዶ በመስኮት ያይና ተመልሶ መጥቶ ‹የሉም› ይለዋል፡፡ ይሄኔ መምህሩ በጥፊ ተማሪውን መታው፡፡ ተማሪው የደረሰበትን ይናገርና አባቱን ይዞት ይመጣል፡፡ አባትዬውም እንደመጡ ‹እንዴት ልጄን ትመታለህ› ብለው ይፎክራሉ፡፡ መምህሩም ‹ታድያ ለምን ከክፍል ውስጥ የለም ይለኛል› አላቸው፡፡ አባት መለስ ይሉና ልጃቸውን ‹እንደዚህ ብለሃል› ይሉታል፡፡ ‹አዎ› ይላል ተማሪው፡፡ ‹መምህሩን ከክፍል ውስጥ የሉም አልክ› አባት አጽንቶ ጠየቀ፡፡ ‹አዎ ብያለሁ› ይላል ልጅ፡፡ አባትም ተናድዶ ‹ታድያ እርሳቸው ከሌሉ ማን እያስተማረህ ነው ተምሬ መጣሁ የምትለው› ብለው ልጃቸውን ጥፊ ደገሙት ይባላል፡፡ እንዲህ ነው የጋማ ከብትነት የመጣልህን መዋጥ፡፡ ታዲያ አንድ ትውልድ ጠፍቶ የለ እንዴ ያለእውቀት ልበርታ ያሉት ደግሞ እንደዚህ አይነት ናቸው ምን ታረገዋለህ

  ReplyDelete
 10. ውድ ወንድሜ ዳ/ን ዳኒ
  ወቅታዊ ቅኔ ነው፡፡ እጅግ ወድጄዋለሁ፡፡ ግን እኮ ከብቶች አንድ ጊዜ የጋማ ከብት ከሆኑ ራሳቸውን ለማየት ስለማይዘጋጁ ወደ ቀደመ ከብትነታቸው ለመስተካከል ከመሞከር ይልቅ እንዴት የጋማ ከብት ተባልን ብለው ነው ቱግ የሚሉት፡፡ የጋማ ከብቶቹም የእርሱው ፍጥረት ናቸውና እርሱ ማመንዠኪያ ይፍጠርላቸዋ!

  ReplyDelete
 11. trew blhale lega yltmngga ware yzaw ymrotew nachew ahewn yscgarewen egezabher amlek klek isk dakik yaleweten lebone ystelen!! ydengl Maryam yasrat agare Ethiopian kn orthiodix thwedew ementwa ytabeklen aman!!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 12. Thank you so much however I don’t like his reason. When you work in media you have to address hot news for people. All investigation will come after the news. That is police responsibility. Your friend told you that in Dira Dewa fish came with rain. It is fact and Ethiopian broadcast told us. What kind research requires telling us about this news? They have video and photo evidence but they are not God to prove the fact. It may take 20 to 30 years to prove the reason. As your friend suggests us we have to wait the next 30 years to hear about this news. Shame on him!!!

  ReplyDelete
 13. It has good message but I don’t like the title and your friend idea. It is so difficult to prove everything. For example we don’t have any prove who wrote the Bible but we trust our church reason to accept the bible.

  ReplyDelete
 14. Hi, Daniel – Did you write this or someone use your blog. Shame on you if you did it.

  ReplyDelete
 15. እንዲህ ነው የጋማ ከብትነት የመጣልህን መዋጥ፡፡ ማስተዋል ይስጠን፣ ዳኒ እናመሰግናለን እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛልህ፡፡

  ReplyDelete
 16. ኢትንአዶ ... ዘእንበለ ተፍጻሜ ርእዮቱ ይባላል መሰለኝ እንጂ ብሩህ አእምሮ እንዳለህ ጽሑፍህ ያሳብቃል። ያም ሆነ ይህ አስተያየት የሚጽፉ አንባቢዎችህ እንዳለ አንተ የጻፍከውን እንደ ገደል ማሚቶ መልሰው ሲለጥፉ ከተራ ቲፎዞነት ያለፈ ትርጉም አይኖረውም። አስተያየት (comment) መሆኑ አልገባቸው ይሆን? አሳላፊዎቹስ (moderator) ለምን ይሄን ይፈቅዳሉ? በዚህ ጉዳይ ላይ ትንሽ ብታስተምረን አመስጋኞች ነን።
  ፫፻፲፰ ዘብሔረ ኢትዮጵያ

  ReplyDelete
 17. AHUNIM TEKAME MEREJAWOCHIN -POST ADIRIGILIN.ENAMESGNALEN.

  ReplyDelete
 18. ዲ/ን ዳኒኤል በጣም ደስ የሚል ምክር ነው፤ እንደዛ ነው ያለው ማመንዠክና ትክክለኛው መለየት በብዛት ኣይታይም፤ ብዙ ሰውም እገሌ ደህና ሰው ነው በሚል ኣመለካከት እርሱ ስለተናገረው ያመጣለትን መቀበል ብሎም ሳያጠና የመዋጥ ሁኔታዎች ይታያል። ኣንድ ወረዳ ላይ ተቀጥሬ ስሰራ ነበር። መስማማት ኣልቻልኩም፤ እንድያውም ኣንዳንዴ እንደ ወፈፌም ያደርገኝ ነበረ ሲበዛብኝ..ምክንያቱም ሁሉን እንድትቀበላቸው የሚፈልጉ ኣሉና ካልሆነም ማግለል..ሌላም፤ በቃ ምንም የሚናገሩት እይዋጥልህ ይለኛል፤ኣንድ ምሳሌ ላቅርብ "በዛ ሰሙን ነው ምርጫ ቀን ለኣንድ ሰሞን ተራዘመ ብለው ተቃዋሚዎች ተናገሩ ህዝቡን ኣወናበዱ ኣሉን ሰብስበው ያውም መንግስት ሰራተኞች ስብስበው፤ ኣካባቢው ሌሎች ፓረቲዎች ደጋፊዎች የሚያገኙበት ቦታ ነው።ማን ኣለ?ማን ተናገር ኣልሁ?የኣሁኑ ሰው እንደሚያስቀጣ እያወቀ እንደዚህ ኣይልም ያስጠይቀዋልና ካልሆነም ያለው ሰው ኣምጡልን ኣልኩኝ፤ በቃ ይህ ሌሎቹ ወገኖች ስም ለማጥፋት የተደረገ መስሎ ታየኝ። ሌላው ኣብዛኛው ተሰብሳቢው ተቀበለውና ተቃዋሚዎች ወራዳዎችና ወንጀሎኞች ናቸው ብሎ ደመደመ፤ለእኔም ለምን ኣትቀበለውም ሃሳቡ ለምን ትጋጫለህ?እንዴት ኣንተ ኣመራርን የተናገረው፣መንግስትን ኣጥንቶ ያመጣውን ኣትቀበልም ኣሉኝ ...ኣልሆነልኝም...ኣንዳንድ የምንቀራረብ ልጆች...ኣዎ በል ጥሩ ኣይደለም ኣሉን....ዝበሉካ ግበረሎም ወይ ዓዶም ልቐቐሎም ተብሎ በእኔ ፊት ተመሰለለኝ...ተገለልለኩኝ...በቃ....ማሰብ ነበረብኝ...ኣሰብኩኝ...ኣእምሮየ ያው ነው በማስረጃ ያሳምኑህ ኣለኝ፤ መረጃ የለም.. ገረመኝ.....በቃ ተቃዋሚዎች እንዲህ ኣደረጉ ተብሎ እስካሁን ይወራል...እውነት ቢሆን ግን ምርጫ ቀን ተቀየረ ያለ ኣካል አባስፈረዱበት ነበር....ዝምብሎ የተባለውን መቀበል ችግር ነው"

  ReplyDelete
 19. Replies
  1. e/r yisteh d/n dani btam tiru timheret new ysethen legnam asitway libona e/r ysten

   Delete
 20. ዲ/ን ዳኒኤል በጣም ደስ የሚል ነው፤ እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛልህ፡፡

  ReplyDelete
 21. "አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር በምትወርሳት ርስትህ የቀደሙ ሰዎች የተከሉትን የባልንጀራህን የድንበር ምልክት አትንቀል።"አውቀው ያደርጋሉ ብዬ ባላምንም የርስዎ ሃላፊነት ስለሆነ እባክዎ ማድረግ ይችላሉና ቸል አይበሉት

  ReplyDelete