ከሁለት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ
አየር መንገድን የሆድ ዕቃ የመጎብኘት ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ አየር መንገዱ ያስመረቀውን ዘመናዊ ኮሌጅ በማስመልከት የአየር መንገዱን
ነገረ ሥራ እንድንጎበኝ ተጋብዘን ነበር፡፡ የጥገና ቦታውን፣ የካርጎ ማዕከሉን፣ አዳዲስ እያስፋፋቸው የሚገኙ የካርጎና የጥገና ቦታዎችን
አይተናል፡፡ የአየር መንገዱን የሆድ ዕቃ ለሚመለከት ሰው ከጥንት ጀምሮ እየካበት፣ እየተሳለጠና እየሠለጠነ የመጣውን ይህን ታላቅ
ሀገራዊ ድርጅት እስከ ጀርባ አጥንቱ ድረስ ለመረዳት ያስችለዋል፡፡ እንዲያውም እኛ ሀገር እንደ አበሻ መደኃኒት ሁሉም ነገር ምሥጢር
ስለሚሆን ነው እንጂ ልጆቻችን በጉብኝት ፕሮግራሞች የአየር መንገዱን የሆድ ዕቃ የማየት ዕድሉ ቢኖራቸው ኖሮ አየር መንገዱንም እንዲወዱ
የፈጠራ ፍልጎታቸውም እንዲጨምር ያደርገው ነበር፡፡
በጥገና ክፍሉ የጀመረው ጉብኝት
በካርጎ ክፍሉ በኩል አድርጎ በአዳዲስ የማስፋፋያ ፕሮጀክቶቹ በኩል ሲጠናቀቅ ዓይኔ አንድ ነገር ላይ ዐረፈ፡፡ ነገሩ የተጻፈው በአየር
መንገዱ የጥገና ክፍል ግድግዳ ላይ ነው፡፡ ለእኔ ከጥገና መሣሪያዎች፣ ከጠጋኞቹ ብቃትና ለጥገና ብቃቱ የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች
ከሰጡት ዕውቅና ባልተናነሰ የሳበኝ በየግድግዳው የተለጠፉት የደኅንነት ማሳሰቢያዎቹ ናቸው፡፡