Monday, January 25, 2016

ከንብ ጋራ ኑሮ

በገድለ ወለተ ጴጥሮስ ላይ እንዲህ የሚል ታሪክ አለ፡፡ እምነ ወለተ ጴጥሮስ ወደ ዋልድባ ገዳም በገባች ጊዜ ለአንዲት እናት ረድእ ሆነች፡፡ እኒህ እናት ፈጽሞ ጠባይ የሚባል ያልፈጠረባቸው ነበሩ፡፡ አሁን የተናገሩትን አሁን ይሽሩታል፣ በሆነው ባልሆነው ይቆጣሉ፤ ከእርጅናቸው ብዛት የተነሣ ይነጫነጫሉ፤ ትእዛዛቸው ሁሉ ውኃ ቀጠነ ነው፡፡ በዚህ ዐመላቸው የተነሣ ማንም ከእርሳቸው ጋር ለመኖር ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ከእርሳቸው ጋር ለመኖር ፈቃደኛ ሆና ለረዥም ጊዜ ያገለገለቻቸው ወለተ ጴጥሮስ ነበረች፡፡
አንድ ቀን መነከሳዪያቱ ተሰባስበው ‹እንዴት ከእኒህ እማሆይ ጋር ለዚህን ያህል ዘመን አብረሽ ለመኖር ቻልሽ? እንዴትስ ታገሥሻቸው? እንዴትስ መሮሽ ጥለሽ አልወጣሽም? ሲሉ ጠየቋት፡፡ ወለተ ጴጥሮስም ‹ንብ ታውቃላችሁ? እኒህ እናት ንብ ናቸው፡፡ ከእርሳቸው የሚገኝ ብዙ ዕውቀት፣ ብዙ ጥበብ፣ ብዙ ልምድ፣ ብዙ ታሪክ፣ ብዙም ጸጋ አለ፡፡ ነገር ግን እናንተ መናደፋቸውን ብቻ ነው የምታዩት፤ ስለዚህም ማሩን ከእርሳቸው ልትቆርጡ አልቻላችሁም፡፡ ንብ ትናደፋለች፣ ነገር ግን ማር የሚገኘው ከምትናደፈው ንብ ነው፡፡ የማትናደፈው ዝንብ ቆሻሻ እንጂ ማር የላትም፡፡ እኔ ግን ከንብ ጋር እንዴት እንደሚኖር ዐውቃለሁ፤ ከንብ ጋር እየኖርኩም ማሩን እቆርጣለሁ› አለቻቸው ይባላል፡፡


ትዳር ማለትም እንዲሁ ነው፡፡
‹አበባው አበበ ንቡም ገባልሽ
እንግዲህ አልማዜ ማር ትበያለሽ›
የሚለው የሠርግ ዘፈን ከዚህ ጋር ይስማማል፡፡ አፍንጅም ከጋብቻ በኋላ ያለውን ጫጉላ ‹ማር ጨረቃ› ሲለው ይኼ ታይቶት እንደሆነ እንጃ፡፡ አንዳንዶቹ የትዳር ንድፊያው ብቻ ስለሚታያቸው ወይ ትዳር ሳይመሠርቱ ወይም የመሠረቱትን ትዳር ሲፈቱ ይታያሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የትዳር በጎነቱን ብቻ ስለሚያውቁት እስኪገቡበት ሲጓጉ፣ ከገቡበት በኋላ ደግሞ
ስሳል እንዳልኖርኩኝ አስንቺን እስካገኝ
ካገኘሁሽ ወዲያ እላለሁ አውጣኝ
እያሉ ያንጎራጉራሉ፡፡
ምናልባትም ደግሞ በሠርግ ላይ የሚዘፈነው
ማን ፈርሚ አለሽ፣ ማን ፈርሚ አለሽ
በተወለወለው በአለንጋው ጣትሽ
የሚለው ዜማ ‹ትንቢት ይቀድሞ ለነገር› ዓይነት ሳይሆን አይቀርም፡፡
ትዳር ግን ሁለቱም ብቻ አይደለም፡፡ ትዳር ከንብ ጋር መኖር ነው፡፡ ንብ ሁለት ጠባይ አላት፡፡ አንዱ ያስደስታል፤ ሌላኛው ያስከፋል፡፡ አንዱ ጤና ይሆናል፣ ሌላኛው ግን ያማል፡፡ አንዱ ይጣፍጣል፤ ሌላው ግን ይመራል፡፡ አንዱን ይቆርጡታል፣ ሌላውን ግን ይከላከሉታል፡፡
ትዳርም እንዲሁ ነው፡፡ ሁለት ጠባይ አለው፡፡ አንደኛው ያስቃል አንዱ ያሰቅቃል፤ አንዱ ያስደስታል፣ ሌላው ያሳዝናል፡፡ አንዱ ግቡ ግቡ ሌላው ውጡ ውጡ ያሰኛል፡፡ አንዱ ይናደፋል፣ አንዱ ይጣፍጣል፤ አንዱ ጤና ሌላው ሕመም ይሰጣል፡፡ አንደኛው ግን ያለ ሌላው አይገኝም፡፡
ይኼን ለመድኃኒት፣ ለብርዝ፣ ለጠጅ፣ የምናደርገውን ማር የምትሰጠው ንብ ናት የምትናደፈው፡፡ ያቺ ስትናደፍ ፊት የምታሳብጠው፣ ውስጥን የምትመርዘው፣ የምትጠዘጥዘው፣ ንብ ናት ማሩን የምትሰጠው፡፡ በትዳርም ውስጥ ሁለቱም አሉ፡፡ ጭቅጭቁ፣ ንዝንዙ፣ ጠቡ፣ ኩርፊያው፣ አንዱ ለሌላው የግድ መታዘዙ፣ አንዱ የሌላው አገልጋይ መሆኑ፣ አንዱ ያለ ሌላው ለመወሰን አለመቻሉ፤ የሌላውን ጠባይ፣ የሌላውን ዐመል የግድ መታገሡ፤ ከሚታገሡት ሰው ጋር አብሮ መኖሩ፤ ይኼ ነው የንቧ ንድፊያ፡፡
ሰው የወለደውን አያገባም፡፡ ያሳደገውን አያገባም፣ የተዛመደውን አያገባም፡፡ የቤቱን ሰው አያገባም፡፡ ሰው ደግሞ በዐመልም፣ በፍላጎትም፣ በአመለካከትም ይበልጥ የሚቀራረበው አብሮት ከኖረና ካደገ ሰው ጋር ነበር፡፡ እምነቱና ባሕሉ ግን ጋብቻን እስከ ሰባት ቤት አርቆ ለባዕድ ይሰጠዋል፡፡ አብረነው ላልኖርነው፣ አብረን ላላደግነው አብረን ላልተወለድነው፣ ላልተዛመድነው ሰው፡፡ ከሌላ ተወልዶ፣ ሃያ ሠላሳ ዓመት ሌላ ቦታ ኖሮ፣ ከሌላ ጋር አድጎ፣ ሌላ ጠባይ ነሥቶ፣ በሌላ መንገድ መጥቶ ያገኘነውን ሰው ነው የምናገባው፡፡ ይኼንን ሰው ወይም ይህችን ሴትዮ በዕውቅ አላሠራናትም፣ አላሠራነውም፡፡ ዐመሉ እንዲህ፣ ሐሳቡ እንዲያ፣ መንገዱ እንዲህ፣ እምነቱ እንዲያ፣ ዕውቀቱ እንዲህ፣ ምግባሩ እንዲያ ብለን ዝርዝር ሰጥተን አላስመረትነውም፡፡ ‹ሬድ ሜድ› ነው ያገኘነው፡፡ ዓይተን እንመርጣለን እንጂ፣ መርጠን አናሠራም፡፡
ንብን እኛ ብናሠራት ኖሮ የርሷን መናደፍ ለዝንብ ሰጥተን የዝንብን ጠባይ ለንብ በመለስንላት ነበር፡፡ ግን ንብን እንዲሁ ሆና አገኘናት፣ አላመድናት፣ ወደ ቀፏችን አስገባናት እንጂ አንድም አልፈጠርናት፣ አንድም አላስፈጠርናት፡፡ ንቧን ማርና ንድፊያ እንደያዘች ነው ያገኘናት፡፡ ሰው በውስጡ ማርና ንድፊያ አለው፡፡ የተገዛ የሱፐር ማርኬት ማር የሚበላ ልጅ ንብ የምትባለውን የሚያውቃት በጣሳው ላይ ባለው ሥዕል ነው፡፡ መልኳን እንጂ ንድፊያዋን አያውቀውም፡፡ እርሱ እድሜ ልን በንብ እየተነደፈ ለጌቶቹ ማር ቆርጦ የሚሰጥ ገባርም ንብ እንደምትናደፍ እንጂ ማር እንደምትሰጥ አያውቅም፡፡ ‹ጌቶች ምን ምን ቢላቸው ነው ይህን የቀፎ እንጀራ የሚያስገፈግፉኝ› አለ የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡
አንዳንዶች በሠርግ ዘፈን፣ በተረት፣ በሠርግ ሥነ ሥርዓት፣ በስብከት፣ በድራማና በፊልም ትዳርን ሲያዩ ምናልባት ማሩ ይሆናል የሚታያቸው፡፡ ያገኛቸውም ሰው ሁሉ ‹ምነው አንተ አታገባም እንዴ› ይላቸዋል እንጂ ተገብቶ ምን እንዳለ አይነግራቸውም፡፡ ‹የዛሬ ዓመት፣ የዛሬ ዓመት፣
የእንትናዬ አባት
ሲወለድ ማሞ፣ ሲወለድ ማሞ
እንመጣለን ደግሞ፤
ያሉት ሰዎች ደግመው ላይመጡ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶችም ማሞ ሲወለድ እንደማይመጡ እያወቁት የሚዘፍኑት ዘፈን ነው፡፡ ‹የዛሬ ዓመት የእንትናዬ አባት› መሆን ለሁሉ ያልተሰጠ መሆኑን የሚናገርም የለም፡፡ ይኼ ያልተነገራቸው የዋሐንም ናቸው ልጅ የለም ብለው የሚፋቱት፡፡
ሌሎች ደግሞ ትዳር ሲባል የንቧ ንድፊያ ነው ትዝ የሚላቸው፡፡
‹ታሠረች አሉ በትዳር፣
ከንግዲህ ቀረ መሽርቀር› የሚለው ዘፈንም ውስጠ ዘ አለበት፡፡
ትዳር ምን ዕዳ ነው ትዳር ምን ዕዳ ነው
ጉልቻው ስሙኒ ምጣዱ ብር ነው
የሚለው ባሕላዊ ዜማ የምጣዱና የጉልቻው ዋጋ ዛሬ ሰማይ በነካበት ጊዜ ቀርቶ ትናንትም በርካሹ ዘመን ትዳርን ‹ዕዳ› ነው እያለ የንቧን መናደፍ እየነገረን ነው፡፡
ትዳር ግን ሁለቱም ብቻ አይደለም፡፡ ትዳር ከንብ ጋር መኖር ነው፡፡ ለማሩ ስንል ንድፊያውን መታገሥ፡፡ ቆይተህ ደግሞ ንድፊያውን መልመድ፡፡ ገበሬ ቀፎ ሰቅሎ ንብ ሲያንብ ንብ እንደምትናደፍ ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም፡፡ የማትናደፍ ንብ ከፈለገ በየደጁ ቆሻሻ ፍለጋ የምትጓዘው ዝንብ ነበረችለት፡፡ ዝንብ ምን ጠባይዋ ሸጋ ቢሆን፤ ጠብ የሚላት ግን ሌላ ነገር ነው፡፡ ይህን ያውቃል ገበሬው፡፡ እያወቀም ንብ ያንባል፡፡ ማነብ ብቻ ሳይሆን ከንብ ጋር እንዴት መኖር እንደሚቻልም ያውቃል፡፡ ንብ ትናደፋለች፤ ግን እንዳትናደፍ ማድረግም ይችላል፡፡ የምትወደውና የማትወደው ሽታ አለ፡፡ ስትቀርብህ ምን ማድረግ እና ምን አለማድረግ እንዳለብህ ገበሬው ያውቃል፡፡ በሀገራችን ንብ አትገደልም፡፡ ነውር ነው፡፡ ብትነድፍም አትገደልም፡፡ የንቧን ማር ለመውሰድም ንቧን ገድሎ፣ አጥፍቶ፣ ጎድቶ ወይም አሰቃይቶ ሳይሆን በጭስ ራሱን እየተከላከለ፣ ፊቱን በጨርቅ ሸፍኖ፣ ወደ ንቧ ቀፎ ገብቶ ነው ማሩን የሚቆርጠው፡፡ ንቧም ሳትጎዳ፣ ማሩም ሳይጠፋ፣ እርሷም ሳትናደፍ፡፡
ትዳርም እንዲህ ነው፡፡ አኗኗሩን ነው ማወቅ፡፤ የንቧን ንድፊያ የመቀነሻውን መንገድ ነው ማወቅ፣ የማሩን አቆራረጥ መንገድ ነው ማወቅ፡፡ ደግሞምኮ አስገራሚው ገበሬው የሚከባከበው ይህቺኑ የምትናደፈውን ንብ መሆኑ ነው፡፡ የምትቀስመው አበባ ትፈልጋለች፣ ንጹሕ አካባቢ ትፈልጋለች፣ ከጉንዳንና ከአውሬ ነጻ የሆነ ቀፎ ትፈልጋለች፡፡ ግን ትናደፋለች፡፡ ደግሞም ማር ትሰጣለች፡፡ ትዳር አስደሳች ነገር ብቻ ሳይሆን አስመራሪ፣ አንገብጋቢ፣ አስጠሊታ፣ ጨጓራ አንዳጅ፣ አንጀት ቆራጭ፣ ልብ አቃጣይም ክፍል አለው፡፡ ይናደፋል፡፡ ግን ደግሞ ክብካቤም ይፈልጋል፡፡ ንጹሕ ልብ፣ ታማኝ ኅሊና፣ ቻይ አንጀት፣ ታጋሽ ሆድ፣ ጠቢብ አእምሮ፣ አሳላፊ ልቡና ይፈልጋል፡፡ ለምን ቢሉ? ማር ይሰጣልና፡፡
አንዳንዶች ቤት ካለችው ወይም ካለው ንብ ይልቅ ውጭ ያቺውን ወይም ያለው ዝንብ ሲያደንቁ ይሰማል፡፡ መቼም ከቀፎ ውጭ ምን እንደሚኖር የታወቀ ነው፡፡ ንብ ትናደፋለች ብሎ ንብ የማያነባ ገበሬ ስንፍናውን እንጂ የንቢቱን ክፋት ማንም አይረዳለትም፡፡ ጥበብ አልባ መሆኑን፣ ትዕግሥት አልባ መሆኑን፣ ተሸናፊነቱን እየተናገረ እንጂ የንቧን ጠባይ እየተናገረ አለመሆኑን ሁሉም ያውቅለታል፡፡ የትዳርን ችግር ብቻ የሚያወራ፣ በትዳር ተመርሮ ከቀፎው ውጭ የሚሄድም ስንፍናውንና ዐቅመ ቢስነቱን እንጂ የቀፎውን ችግር እየተናገረ አይምሰለው፡፡ ቀፈ ውስጥ ማር የምትሠራው ን እንዳለች ሁሉም ያውቃልና፡፡ ሌላው ቀርቶ ውጭ ያለቺው ዝንብም ይኼንን ታውቃለች፡፡   
አንዳንዶች ከንብ ጋር የመኖር ጥበብ ሲያንሳቸው የማትናደፍ ንብ ፍለጋ ይኳትናሉ፡፡ የማትናደፍ ንብ መፈለግ ከመረቁ አወጡልኝ ከሥጋው ጦመኛ ነኝ እንደማለት ነው፡፡ ወይም የማትዞር መሬት እንደመፈለግ፡፡ የመትናደፍ ንብ ከፈለግክ ከዝንብ ጋር ተጋባ፡፡ 
ይህ ጽሑፍ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የወጣ ነው፡፡

21 comments:

 1. ሆ… አንተ አታውቀኝም፡፡ በዚህ ፅሁፍህ ግን እኔን ከሆነ መጥፎ ነገር አድነሀኛል፡፡ አመሰግናለሁ፡፡ (በሀገራችን ንብ አትገደልም፡፡ ነውር ነው፡፡ ብትነድፍም አትገደልም፡፡ የንቧን ማር ለመውሰድም ንቧን ገድሎ፣ አጥፍቶ፣ ጎድቶ ወይም አሰቃይቶ ሳይሆን በጭስ ራሱን እየተከላከለ፣ ፊቱን በጨርቅ ሸፍኖ፣ ወደ ንቧ ቀፎ ገብቶ ነው ማሩን የሚቆርጠው፡፡ ንቧም ሳትጎዳ፣ ማሩም ሳይጠፋ፣ እርሷም ሳትናደፍ፡፡)

  ReplyDelete
 2. የዛሬ ዓመት፣
  የዛሬ ዓመት፣
  የእንትናዬ አባት
  ሲወለድ ማሞ፣
  ሲወለድ ማሞ
  እንመጣለን ደግሞ፤

  ReplyDelete
 3. Well said...!!!ቀፈ ውስጥ ማር የምትሠራው ን እንዳለች ሁሉም ያውቃልና፡፡ ሌላው ቀርቶ ውጭ ያለቺው ዝንብም ይኼንን ታውቃለች፡፡ ...A...

  ReplyDelete
 4. ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡

  ReplyDelete
 5. "አንዳንዶች ከንብ ጋር የመኖር ጥበብ ሲያንሳቸው የማትናደፍ ንብ ፍለጋ ይኳትናሉ፡፡ የማትናደፍ ንብ መፈለግ ከመረቁ አወጡልኝ ከሥጋው ጦመኛ ነኝ እንደማለት ነው፡"

  ReplyDelete
 6. ይህ አጀንዳ ሰፊና ሁልጊዜ ልንወያይበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በትዳር ውስጥ ያለፈ ሁሉም ሰው የየራሱ ተሞክሮ አለው፡፡ ዝም ብሎ የሚኖር ሰው እንዳለ ሁሉ የህይወት መርህ ያለው ሰው አለ፡፡ ለትዳርና ለልጅ ያለን አመለካከት ካለን የህይወት መርህ ይመነጫል፡፡ አንዳንዱ ትዳርን ሲመሠርት ፈተና እንዳለው ሳያውቅ ደስታን ብቻ ይጠብቃል፡፡ ልጅን መውለድ(ዘር መተካት) የግድ ነው ብሎ ያስባል፡፡ የራሴን ተሞክሮ ላንሳ፤ ሥራ ይዤ ዝም ብዬ እኖር ነበር፤የኔ ዓላማ እ/ርን መከተል ብቻ ነው፤ጥዋትና ማታ ወደ ቤ/ክ መሮጥ፤የሚያስደስተኝ ይሄ ነው፤በኋላ የርሱ ፈቃድ ሆኖ በተክሊል አገባሁ፤ጋብቻ ምን እንደሆነ አየሁ፤አስደሳቹንና አሳዛኙን ገጽታዎች በዝርዝር አየሁ፤የሰይጣንን አመጣጥ የምከታተል ሆንኩኝ፤በጸሎት መታገልና ማሸነፍ አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን ተረዳሁ፤በአብዘኛው ተሳክቶልኛል፤በታገስኩኝ ቁጥር ኑሮዬ ጣፋጭ ሆነ፤ይሁን እንጂ የልጅ ጉዳይ ከባዱ ፈተና ሆነ፤እኔ በዚህ ዓለም ስኖር ልጅ ለመውለድ ያለኝ ፍላጎት ዜሮ ነው፤ ከማህረሰቡ በተቃራኒው ማለት ነው፤እኔ የምፈልገው መመኪያዬ እ/ርን አመስግኜ መኖርና በዚች ክፉ ዓለም ላይ ልጅ አምጥቼ ለምን ላሰቃይ የሚል አመለካከት ነው ያለኝ፤ሰው ደግሞ ዘር አለመተካት መረገም ነው ብሎ ያስባል፡፡የሚገርመኝ ለራሱ የሚበላ እንኳን የሌለው ልጅ ይመኛል፡፡ ወደ 3 ዓመት ያለልጅ እንደኖርኩኝ ባለቤቴ(እናትዋን ጨምሮ) በየቀኑ መጨቃጨቅ ሆነ፡እኔ ደግሞ ልጅ አልለምንም የሚል አ~ሜን ይዤ ነበር፤ልጅ ስላልሰጠኝም አመሰግነው ነበር፡፡ይህ በንዲህ እንዳለ ከትዳር ትምህርት ቤት በአራት ዓመት ተመረቅን፤ከማረፍዋ በፊት ብዙ ስለመሞትዋና ስለመለያየታችን ብዙ ነገር አይቼ ነበር፡፡ ዛሬ በሃይማኖት ጸንቶ መሞት የት ይገኛል፡፡ለብቻዬ መኖርን እንደገና ሀ ብዬ ጀመርኩ፡፡ለብቻ መኖርም ፈተናው ብዙ ነው፡፡ ከ2 ዓመት በላይ ከቆየሁ በኋላ አዘዘልኝ፤ወዲያው ጸነሰች፡፡የጌታ ፈቃድ ይሁን ብዬ ዝም አልኩ፡፡ አሁን የአንድ ልጅ አባት ነኝ፤ የመጀመሪያና ምናልባትም የመጨረሻ ልጅ፡፡ልጅ መውለድ ትልቅ ኃለፊነት መሆኑን አየሁ፤ልጅ ቤት ያሞቃል፤ያስደስታል፤ወዘተ.ግን ያ ልጅ የዚህን ዓለም ፈተና አሸንፎ ለመንግሥተ ሰማይ ይበቃል ወይ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል እንጂ ዘር ልተካ፤ሀብቴን ይውረስ፤ይጡረኝ፤ስሜን ያስጠራ፤ወዘተ.የሚባሉ ከንቱ አስተሳሰቦች በየሰዉ ልቦና ተዘርተው ከንቱ ትውልድ እበዛ የመጣ ይመስለኛል፡፡ ሀብት ያለው ሰው ልጅ አጣሁ መከንኩ ብሎ ከሚጨነቅ ጎዳና የወደቁትን ልጆ አንስቶ የጽድቅ ሥራ ቢሠራስ? ሌላው ልጅ ወልዶ ለስጋው የሚያስፈልገውን ብቻ ማሰብና ለነፍሱ አለመጨነቅ ጎድቶናል፡፡ ሌላው ልጅ አጣሁ ብለው የሚያዝኑ ሰዎች ይገርሙኛል፡፡ይህንን ዘመን ካለማወቅ የመነጨ ሊሆን ይችላል፤የወሊድ መከላከያም ሌላው መወያያ አርዕስት ነው፤እኔ እስከዛሬ በኪነጥበቡ ጠብቆኛል ወደፊትም እርሱ ያውቃል ይህንን ነገር በጣም እጠላለሁ፡፡ ትውልዱ በዚህ ጉዳይ ጥርት ያለ ነገር አላገኘም፡፡ ይሄ ነገር ከእ/ር ጋር መጣበቅን ይጠይቃል፤መጀመሪያ ስጋችንን መግራት/ለነፍሳችን ማስገዛት/ የተፈቀደም ቢሆን የባልና የሚስት የመኝታ ግንኙነት ስርዓቶች አሉት፤ለምሳሌ የሰንበትና በዓለት ቀን አይፈቀድም፡፡ሥጋችን ከጠገበ ፍትወቱ ስለሚጨምር በጾምና በጸሎት ማድከም አለብን፡፡ለምሳሌ አንድ ሰው ሲያወራ ከሴት ጋር ከተኛሁ የግድ ግንኙነት መፈጸም አለብኝ ብሎ ነበር፡፡ክፉና አመንዝራ ትውልድ ያሰኘውም እንዲህ ዓይነቱ ነው፡፡ከትዳር ዓላማዎች አንዱ ፍትወትን ለመቆጣጠር ቢሆንም ያለአግብብ መጠቀምም ተገቢ አይሆንም፡፡ብቻ ይህ አጀንዳ ሰፊና በሚዲያም ጭምር ውይይት የሚፈልግ ነው፡፡ የህዝብ ብዛት ጉዳይ በመንፈሳዊና በስጋዊ ዕይታ ያላቸው እንድምታና ህዝቡ ልጅ ለመውለድ ያለው አመለካከት ምን መሆን እንዳለበት የሚያወያይ መድረክ ቢኖር ጥሩ ነው፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. Thank you for sharing! I have the same believes in general in life in his world's meaning for us.

   Delete
  2. Thank you for sharing! I have the same believes in general in life in his world's meaning for us.

   Delete
  3. Nice way of viewing marriage.God bless you both.

   Delete
 7. በተዋህዶ ሀይማኖት ውስጥ ትዳርን የሚያፈርስ ትክክለኛ ምክንያቶች ምን ምን ናቸው ?
  ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 8. ድንቅ አገላለጽና አቀራረብ። መምህራችን ዳኒ በእውነት ቃለ ሕይወት ያሰማልን!!!

  ReplyDelete
 9. ‹ንብ ታውቃላችሁ? እኒህ እናት ንብ ናቸው፡፡ ከእርሳቸው የሚገኝ ብዙ ዕውቀት፣ ብዙ ጥበብ፣ ብዙ ልምድ፣ ብዙ ታሪክ፣ ብዙም ጸጋ አለ፡፡ ነገር ግን እናንተ መናደፋቸውን ብቻ ነው የምታዩት፤ ስለዚህም ማሩን ከእርሳቸው ልትቆርጡ አልቻላችሁም

  ReplyDelete
 10. እውነት ነው...ትዳር ከባድ ነገሮች ቢኖሩትም ማሩ የበለጠ ይጣፍጣል...የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑንም አንርሳ...ሁሌም የእርሱ ስጦታ ለእኛ መልካም ነው፡፡

  ReplyDelete
 11. ይቅርታ! ይሄ ጽሁፍ ፣ በአይዶል ዳኞች ቛንቛ ይሄን ጦማር ' እይመጥንም! እላለሁ።
  የንብ ምሳሌው ጥሩ ሆኖ፣በአንድ ዓርፍተነገር ማልቅ ሲችል፣ ትዳርን ያለ-ተፈጥሮው ከንብ ተግባራት ጋር ለማመሳሰል የተደከመው ፤ የተፈለሰመው አካሄድ፣ ምን ነካቸው ብየ እንዳስብ አድርጎኛል። ባይሆን ዳንኤል፣ በተባ ብዕርህ አንድ ቀን ፣ ትዳር ከክርስቲያናዊ ምግባር ወይም ከእግዚአብሄር አይን አንጻር ምን ማለት እንደሆን አንድ ቀን ጥሩ ጽሁፍ ትጽፍ ይሆናል ብየ እጠብቃለሁ።

  ReplyDelete
 12. እግዚያብሔር ፀጋሕን ይጠብቅልሕ በደንብ ገልጸኸዋል።

  ReplyDelete
 13. ቃለ ህይወት ያስማልን!

  ReplyDelete
 14. እውነት ነው ማትናደፍ ንብ ከፈለግህ ከዝብ ጋ ተጋባ ።ትልቅ አባባል ነው እንኳን ኢትዮ ወንድሜ ሆንህ በዚህ ቃል ቡዙ አስተምረከኛልና አመሰግናለሁ ዳኒ ዝርዝር ኪስ ይቀዳል እዲሉ አይደል የምትለኝ ።እድሜና ጤና ይስጥህ።ከበላይ ነኝ ቸር ይግጠመን።

  ReplyDelete
 15. Dn.Daniel Kiberet Kale hiwot yasemalene.Ewunete new Marun Mengest semayate ena zelalemawi hiwoten lemkedajete. Yihichen tenadafiwuan Nibuaen Alem Betegise betibeb ena beblihat menore aleben. Yihe neger betirewu sel gabicha bicha sayihone Bezi midir nurache rasu gabicha mehonun new yasayen. Silizi Alem lemashenef bitinadefem Marune Zelalemawi Hiwote endeneworse. Ye Kidusan Amelake Yiradan.


  ReplyDelete
 16. ወይ ዲያቆን ዳንኤል አንተ እግዚአብሔር የባረከህ!!!!!አንዳንዶች ቤት ካለችው ወይም ካለው ንብ ይልቅ ውጭ ያቺውን ወይም ያለው ዝንብ ሲያደንቁ ይሰማል፡፡ መቼም ከቀፎ ውጭ ምን እንደሚኖር የታወቀ ነው፡፡......ቀፈ ውስጥ ማር የምትሠራው ን እንዳለች ሁሉም ያውቃልና፡፡ ሌላው ቀርቶ ውጭ ያለቺው ዝንብም ይኼንን ታውቃለች፡፡
  አንዳንዶች ከንብ ጋር የመኖር ጥበብ ሲያንሳቸው የማትናደፍ ንብ ፍለጋ ይኳትናሉ፡፡ የማትናደፍ ንብ መፈለግ ከመረቁ አወጡልኝ ከሥጋው ጦመኛ ነኝ እንደማለት ነው፡፡ ወይም የማትዞር መሬት እንደመፈለግ፡፡ የመትናደፍ ንብ ከፈለግክ ከዝንብ ጋር ተጋባ፡፡

  ReplyDelete
 17. ቃለ ሕይወት ያሰማልን!

  ReplyDelete