በገድለ ወለተ ጴጥሮስ ላይ እንዲህ
የሚል ታሪክ አለ፡፡ እምነ ወለተ ጴጥሮስ ወደ ዋልድባ ገዳም በገባች ጊዜ ለአንዲት እናት ረድእ ሆነች፡፡ እኒህ እናት ፈጽሞ ጠባይ
የሚባል ያልፈጠረባቸው ነበሩ፡፡ አሁን የተናገሩትን አሁን ይሽሩታል፣ በሆነው ባልሆነው ይቆጣሉ፤ ከእርጅናቸው ብዛት የተነሣ ይነጫነጫሉ፤
ትእዛዛቸው ሁሉ ውኃ ቀጠነ ነው፡፡ በዚህ ዐመላቸው የተነሣ ማንም ከእርሳቸው ጋር ለመኖር ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ከእርሳቸው ጋር
ለመኖር ፈቃደኛ ሆና ለረዥም ጊዜ ያገለገለቻቸው ወለተ ጴጥሮስ ነበረች፡፡
አንድ ቀን መነከሳዪያቱ ተሰባስበው
‹እንዴት ከእኒህ እማሆይ ጋር ለዚህን ያህል ዘመን አብረሽ ለመኖር ቻልሽ? እንዴትስ ታገሥሻቸው? እንዴትስ መሮሽ ጥለሽ አልወጣሽም?
ሲሉ ጠየቋት፡፡ ወለተ ጴጥሮስም ‹ንብ ታውቃላችሁ? እኒህ እናት ንብ ናቸው፡፡ ከእርሳቸው የሚገኝ ብዙ ዕውቀት፣ ብዙ ጥበብ፣ ብዙ
ልምድ፣ ብዙ ታሪክ፣ ብዙም ጸጋ አለ፡፡ ነገር ግን እናንተ መናደፋቸውን ብቻ ነው የምታዩት፤ ስለዚህም ማሩን ከእርሳቸው ልትቆርጡ
አልቻላችሁም፡፡ ንብ ትናደፋለች፣ ነገር ግን ማር የሚገኘው ከምትናደፈው ንብ ነው፡፡ የማትናደፈው ዝንብ ቆሻሻ እንጂ ማር የላትም፡፡
እኔ ግን ከንብ ጋር እንዴት እንደሚኖር ዐውቃለሁ፤ ከንብ ጋር እየኖርኩም ማሩን እቆርጣለሁ› አለቻቸው ይባላል፡፡