Tuesday, December 8, 2015

ኢዛናና የነገረ ክርስቶስ እምነቱ


በኢትዮጵያ ታሪክ ክርስትናውን በይፋ ያወጀው ንጉሥ ኢዛና ነው፡፡ ኢዛና ክርስትናውን በይፋ በማወጅ ብቻ ሳይሆን በድንጋይ ላይ የጦርነት ታሪኩን መዝግቦ በማቆየትም ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳን የታሪክ ሊቃውንት በኢትዮጵያ ክርስትና የተሰበከበትን ጊዜ ከ4ኛው መክዘ ቢጀምሩትም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ግን ከጃንደረባው መጠመቅ አንሥተው ይቆጥሩታል፡፡
በኢትዮጵያ የክርስትና ትምህርት ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም ኦፊሴላዊ እምነት የሆነውና መሠረት ባለው ጽኑ ዐለት ላይ የተተከለው ግን በ4ኛው መክዘ የፍሬምናጦስን ስብከትና ሹመት፣ የኢዛናንም ወደ ክርስትና መመለስ ተከትሎ ነው፡፡ ንጉሥ ኢዛና ከክርስትና ጋር የነበረውን ታሪክ በተመለከተ የሚነግሩን አራት ዓይነት የድንጋይ ላይ ጽሑፎች አሉ፡፡ ሁለቱ በግሪክና በግእዝ፣ ሦስተኛው በግእዝ ብቻ፣ አራተኛው ደግሞ በግሪክ ብቻ የተጻፉ ናቸው፡፡
የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ኢዛና በመንግሥቱ ላይ ያመጹ ሕዝቦችን(ቤጃዎችን) ለመውጋት ያደረገውን ዘመቻ የያዙ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ሲሆኑ ሁለቱ ጽሑፎች[1](ግሪኩና ግእዙ) ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸው ናቸው፡፡ ይሄ የኢዛና የድንጋይ ላይ ጽሑፍ በአንዱ ገጽ በግሪክ የተጻፈ ሲሆን በሌላው ገጽ ደግሞ በግእዝና በሳባውያን(ግእዝን በሳባውያን ፊደል) የተጻፈ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ላይ ኢዛና በአምልኮ ጣዖት ውስጥ እንደነበረ ያሳያል፡፡ ራሱንም የሚጠራው ‹ወልደ መሕረም ዘኢይትመዋዕ ለጸር - ለጠላቱ የማይደፈረው የመሕረም ልጅ› ብሎ ነው፡፡ ሦስተኛው የድንጋይ ላይ ጽሑፍ በኖባ ሕዝቦች ላይ ስለተደረገው ዘመቻ የሚገልጥ ሲሆን[2] በዚህ ጽሑፍ ላይ ኢዛና አምላኩን የሚጠራው ‹በኀይለ እግዚአ ሰማይ፣ ዘበሰማይ ወምድር መዋኢ - በሰማይና በምድር አሸናፊ በሆነው በሰማዩ ጌታ ኀይል› ብሎ ነው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ‹በኀይለ እግዚአ ኩሉ - የሁሉ ጌታ በሆነው ኀይል› ይለዋል፡፡