Wednesday, November 25, 2015

“በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጽሑፍ ቅርስ ላይ ከአለኝ ትዝብት”


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን

ኒው ዮርክ ከተማ

(የተራድኦ ድግስ ምሽትኅዳር ቀን ፳፻ . . = November 14, 2015)


ጌታቸው ኃይሌ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንድታገለግሉ የተመረጣችሁ የተከበራችሁ ካህናትና ዲያቆኖት፥ የመድኃኔ ዓለም አባላት እንድትሆኑ የሐዋርያትን ጥሪ ያከበራችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን እኅቶቼና ወንድሞቼ፥ በዚህ የበጎ አድራጎት ምሽት ላይ ተገኝቼ ለሥጋ ጣፋጩን የኢትዮጵያ ምግብ በስመጥር ጠጅ አያወራረድኩ እንድመገብና ስለመንፈስ አርኪው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሥነ ጽሑፍ ቅርስ ያሉኝን አንዳንድ ትዝብቶች እንዳጫውታችሁ ስለ ጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።

እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የትልቅ ታሪክ ችቦ ተሸካሞች ነን። ችቦውን መሸከም መስቀለ ሞቱን የመሸከም ያህል ይከብዳል፤ ግን የኩሩው ማንነት መታወቂያችን ስለሆነ ከባዱን ሸክም በደስታና በጸጋ እንሸከመዋለን። ስለችቦውና ስለ አቀጣጣዮቹ ተናገር ስላሉኝ ተደስቻለሁ። ቅዱስ ዳዊት “ተፈሣሕኩ እስመ ይቤሉኒ ቤተ እግዚአብሔር ነሐውር” (ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ስላሉኝ ተደስቻለሁ) ባለው አነጋገር ስለተጠቀምኩ መንፈሱ እንደማይወቅሰኝ እለምነዋለሁ።


ትልቁን ታሪካችንን በመመዝገብ የትልቅ ሕዝብ ቀጣዮች መሆናችንን የነገሩን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ናቸው። ባለውለታዎች ስለሆኑ፥ እናመስግናቸው፤ ቅዱሳን ስለሆኑ፥ እንዲጸልዩልን እንለምናቸው።
“ሊቃውንት አባቶቻችን ምን ምን መዘገቡልን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጥናቱ እንደቀጠለ ነው። በዚህ ጥናት ላይ የምዕራባውያን ምሁራን ተሳትፎ ከፍ ያለ ቦታ ይዟል፤ አድናቆትም አለኝ። የምዕራባውያን ምሁራን በምርምራቸው የሚያደርጉትን ስሕተት ሁሉ ከክፋታቸው እንደመነጨ አድርጌ አላየውም። ለምሳሌ በኪዳነ ወልድ ክፍሌ ስም የሚታወቀውን መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ የሚመጥን የግዕዝ መዝገበ ቃላት በኢትዮጵያ አልተጻፈም። የዚህ ድንቅ መጽሐፍ መሠረት ጀርመናዊው ዲልማን በላቲን ቋንቋ ያዘጋጀው የግዕዝ መዝገበ ቃላት ነው። እኔም ማስረጂያ ይዤ እንዲያርሙ የምጠይቃቸውን እርማት፥ በማልቀበለው ምክንያት እምቢ ያሉበትን ጊዜ አላጋጠመኝም።

የምዕራባውያን ምሁራን የግዕዝን ምንጮች ከሚመረምሩበት ምክንያት አንዱ፥ በዓለም ላይ የጠፉ የጥንት የክርስትና ሃይማኖት ምንጮች ኢትዮጵያ ገዳማት ውስጥ ይገኙ እንደሆነ ለማወቅ ነው። ክርስትና የዛሬውን መልክ እስኪይዝ ብዙ እንቅፋቶችን አልፏል። እንቅፋቶቹን ከፈጠሩት ምክንያቶች አንዱ ብዙ የክርስትናን ታሪክ ዘጋቢዎች መነሣት ነው። እዚህ ላይ በእኛ ዘንድ የተፈጸመውንና የታመነውን የሥራውን ዜና በሥርዐት ሊጽፉ የጀመሩ ብዙዎች ናቸው ያለውን የቅዱስ ሉቃስን ምስክርነት መጥቀስ ይቻላል። የጥንቶቹ ሊቃውንት ከውዝግብ ለመውጣት ሲሉ ጥቂቶቹን መጻሕፍት መርጠው የቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ መጻሕፍት አድርገው አወዛጋቢ ነገር ያለባቸውን ሌሎቹን ኮነኗቸው፤ አጠፏቸውም። ዛሬ የሃይማኖት ተመራማሪዎች እነዚህ የተኮነኑ መጻሕፍትና በሌላ ምክንያት የጠፉ ስለክርስትና ታሪክ የሚነግሩን ነገር ይኖራል በማለት ይፈልጓቸዋል።

በመጠኑም ቢሆን ተገኝተዋል። በጣም የታወቁትን ልተውና አንድ አሜሪካዊ ተማሪ በቅርብ ቀን ስላገኘው የጥንታዊ ድርሰት ብጣሽ (fragment) ልናገር። ሙሴና የፈርዖን ጠንቋዮች ታምራት በመሥራት ይወዳደሩ እንደነበረ እናስታውሳለን። አንድ ያልታወቀ ደራሲው ስለፈርዖን ጠንቋዮች የደረሰው ጥንታዊ ድርሰት ኖሯል። መኖሩ የታወቀው የድርሰቱ አንድ ብጣሽ በግሪክኛው ተገኝቶ ነው። ይህ ተማሪ ያገኘው የግዕዝ ብጣሽ ብራና ግሪክኛው ውስጥ ያለውን የሚመሰክርና የጐደለውን የሚያሟላ ነው። ተማሪው ከማግኘቱ በፊት እንዲህ ያለ ድርሰት በግዕዝ መኖሩን ማንም አያውቅም ነበር። ይቺ ብጣሽ የብራና ጽሑፍ መገኘት ያደረገው አስተዋጽኦ በብጣሹ መጠን የሚገመት አይደለም።

በግሌ ወደ አጋጠሙኝ ሁለት ጉዳዮች ልሻገር። አባ ባሕርይ መዝሙረ ክርስቶስን ሲደርሱ ከጠቀሟቸው ብዙ መጻሕፍት ውስጥ አንዱ ከሊላ ወድምና የሚባለው መጽሐፍ እንደሆነ ነግረውናል። እኔም ድርሰቶቻቸውን ስተች አንሥቼዋለሁ። መጽሐፉ በብዙ ቋንቋዎች ተተርጒሞ ሳለ በግዕዝ ስላልተገኘ፥ ሊቃውንቱ የመነኵሴውን ቃል መጠራጠር ጀምረው ነበር። ግን መጽሐፉ ራሱ ባይገኝም፥ የሐይቅ ገዳም መጽሐፉ እንደነበረው ማስረጃ አግኝቻለሁ፤ መዝገባቸው ከመዘገባቸው መጻሕፍት አንዱ ከሊላ ወድምና ነበረ። መጽሐፉን አይተውት ይሁን ወይም ስሙን ከመዝገብ ላይ አግኝተውት ይሁን ባይታወቅም፥ ሊቀ ጠበብት አክሊለ ብርሃን ከአዘጋጁት የመጻሕፍት መዝገብ ውስጥ አግብተውታል።


ሁለተኛው፥ ዮሴፍ ወአስኔት የሚባለውን መጽሐፍ የሚመለከት ነው። ይህም መጽሐፍ በብዙ ቋንቋዎች ተተርጕሞ ሲገኝ በግዕዝ አልተገኘም። ግን አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈ ምስጢር በሚባለው መጽሐፋቸው ውስጥ እመቤታችንን ንህብ ዘአስኔት (የአስኔት ንብ) ብለዋታል። አስኔት ንብ እንደነበራት የሚነግረን ምንጭ ዮሴፍ ወአስኔት ብቻ ስለሆነ ደራሲው አባ ጊዮርጊስ መጽሐፉ እንደነበራቸው--ኢትዮጵያ እንደነበራት--ታምኖበታል። እዚህም ላይ ትንሽ አስተዋፅኦ አድርጌያለሁ።

ከእኛ ሊቃውንትም ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴና ሊቀ ጠበብት አክሊለ ብርሃን ምን ምን መጻሕፍት እንዳሉን በዝርዝር ጽፈዋል። ግን በቂ አይደለም። ምርምሩ ይቀጥላል። ምኞቴ በዚህ በተቀደሰ ተግባር ብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን እንዲሰማሩ ነው። አባቶቻችንን የማደንቀው ለግዕዝ ያንን ሁሉ የሃይማኖት መጽሐፍ የመቀበያ ችሎታ ማስታጠቃቸው ነው። ይህ የሚያመለክተው ግዕዝ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት በፊት ዳብሮ እንደነበረ ነው። ለምሳሌ ግዕዝ ተቆጣ ለማለት ከአራት የማያንሱ ቃላት እንዳሉት በአጋጣሚ አይቻለሁ፤ መአከ (ተምእከ) መጐጸ (አመጐጸ) ተምዐ (ተምዕዐ) ተቈጥዐ

አማርኛ የሌለው አንዳንድ ቃላትም አጋጥመውኛል፤ ለምሳሌ፥ ሕልበት(nostril)ምንሀብ (factory). አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሕልበት መተርጐሚያ አማርኛ ቢያጡ፥ የአፍንጫ ጉንጭ አሉት።

የግዕዝን ችሎታ ብናውቅ ኖሮ፥ bank የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል አማርኛ ውስጥ አይገባም ነበር። ባንክ በመሠረቱ የገንዘብ መለዋወጫ ጠረጴዛ (bench)ነው። የሉቃስን ወንጌል ስናነብ ምዕራፍ ፲፱ ላይ ጌታችን የሰጠን አንድ ምሳሌ እናገኛለን። እንደምሳሌው፥ አንድ ጌታ ከአሽከሮቹ ለዓሥሩ ነግደው እንዲያተርፉለት ዓሥር ምናናት ከፋፍሎ ሰጥቷቸው ነበር። በመጨረሻ ሁሉም ገንዘቡን ከነትርፉ ለጌታቸው ሲያስረክቡ፥ አንዱ ብቻ የወሰደውን ሳይነግድበት ሳያተርፍበት እንዳለ ከትቶ እንዳለ ለጌታው መልሶ ሰጠው። ጌታው አዝኖና ተቆጥቶ እንዲህ አለው፤

“ወለምንት ኢያግባእከ ወርቅየ ውስተ ማእድ”
([ላለመነገድህ ምክንያት ካለህ] ታዲያ ገንዘቤን ለምን ከማእድ አላስገባህም?”
ምንጩ ግሪክኛው የሚለውም “ትራፔዛ” (ጠረጴዛ) ነው። ታዲያ የአማርኛው ትርጕም ከላይ እንዳመለከትኩት መሆን ሲገባው፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ትርጉም “ባንክ”፥ የኦርቶዶክሶቹ “ለዋጮች” ይላል። ግን ቀደም ብሎ “ማእድ” እንዳለ ከግዕዝ ወደ አማርኛ ቢተላለፍ ኖሮ “ባንክ” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ምንም ሳይጕድልብን ልናስቀረው እንችል ነበር።

የዮሐንስ ወንጌልን ሳነብና ምዕ 19 . 24 ላይ ስደርስ ደግሞ፥ ስለ ግዕዝ የቃላት ብልጽግናና ስለአባቶች ጥንቃቄ የገረመኝና እኛን ልጆቻቸውን የሚወቅስ ነገር አጋጠመኝ፤ ጥቅሱን እንዳለ ልጥቀሰው፤
 
ወሐራሰ ሶበ ሰቀልዎ ለኢየሱስ ነሥኡ አልባሲሁ ወረሰይዎ አርባዕተ ክፍለ ለአሐዱ ሐራ ክፍለ። ወክዳኖሂ እልታኀ ዘአልቦ ርፍአት ዘእምላዕሉ እኑም ኵለንታሁ። ወተባሀሉ በበይናቲሆሙ ኢንግምድ ወኢንስጥጥ አላ ንትፋሰስ ለዘረከቦ ይርከቦ። ከመ ይብጻሕ ቃለ መጽሐፍ ዘይቤ። ተካፈሉ አልባስየ ለርእሶሙ ወተዓፀው ዲበ ዐራዝየ።

ወታደሮቹ ኢየሱስን ከሰቀሉት በኋላ፥ ልብሱን ወስደው ለእያንዳንዱ ወታደር አንድ ክፍል እንዲደርስ አራት ቦታ ከፈሉት። መርፌ ስላልነካው ከላይ እስከታች አንድ ወጥ ሆኖ ስለተሠራው ስለ ፈርጅ ቀሚሱ ግን እርስ በርሳቸው (እንዲህ) ተባባሉ፥ “ዕጣ እንጣጣልና ለደረሰው ይድረሰው እንጂ አንቅደደው”። ይህም፥ “ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉት፤ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” ያለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።)
እንግሊዝኛውም እንደ አማርኛው ከሁለቱም ቦታ “ዕጣ ተጣጣሉ”(cast lots) ነው የሚለው።
. . . So they said to one another, Let us not tear it, but cast lots for it to see who will get it. This was to fulfill what the scripture says, They divided my clothes among themselves, and for my clothing they cast lots.

በግዕዝ ግን አነጋገሩ የተገለጠው በሁለት የተለያዩ ሐረጎች መሆኑን ልብ እንበል፤ ተፋሰሱ ተዐፀዉ ለምን እንዲህ ሆነ ብየ የግሪኩን ምንጭ ባየው፥ እውነትም ሁለቱ ሐረጎች በግሪክኛውም የተለያዩ ናቸው፡ lachomen እና ebalon kleeron


* * * * * * * *
ባሁኑ ሰዓት ጥሪየ አድርጌ የያዝኩት አባቶቻችን ከውጪው ዓለም ምን ተረጐሙልን፥ እነሱስ በተረጐሙት ላይ ምን አከሉበት የሚሉትን ሁለቱን ጥያቄዎች መመለስን ነው። አምሳያቸው እውጪ አገር ካለ ከውጪ የተተረጎሙ ናቸው ማለት አያስቸግርም። ደንቃራ የሆነብኝ አንዳንዶቹን የግዕዝ መጻሕፍት ከምዕራቡ ዓለምና ከመካከለኛው ምሥራቅ ጠፍተው ነው እንጂ፣ ትርጕም ናቸው የሚለው አነጋገር ነው። እርግጥ ከሌላው ዘንድ ጠፍተው እኛ ዘንድ የተገኙ አሉ። ይኸም ቢሆን አባቶቻችንና ቤተ ክርስቲያናችንን የሚያስመሰግን ነው።

ቢሆንም እኛ ተቀባዮች ብቻ ባንሆን እንመርጣለን፤ ለነገሩ ተቀባዮች ብቻም አይደለንም። ይኸንንም ለማሳየት ለዛሬው ንግግሬ ሁላችሁም በምታውቁት በመጽሐፈ ቅዳሴያችን ላይ አተኩራለሁ። 

የዶክተር ገብረ ጻድቅ ደገፉና የኔ መምህር ቄስ ማርቆስ ዳውድ የመጽሐፈ ቅዳሴውን እንግሊዝኛ ሲያሳትሙ፥ እመቅድሙ ውስጥ እንዲህ ብለው ጽፈዋል፤
 
It is said by the Ethiopian Church authorities that they received their liturgy of fourteen Anaphoras from the Church of Egypt. The Church of Egypt confirms this but has, unfortunately, lost most of the fourteen.
 
(በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣኖች ዘንድ ዓሥራ አራቱን የቅዳሴ መጻሕፍታቸውን ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን እንደወሰዱ ይነገራል። የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ይኸንን ታረጋግጣለች። ግን መጥፎ ዕድል ሆኖ ከዓሥራ አራቶቹ አብዛኛዎቹ ጠፍተውባታል።
 የግብፅ ቤተ ክርስቲያን የጠፉባት የቅዳሴ መጻሕፍት ቍጥር የሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት መጻሕፍት ቍጥር መሆኑ ነው። እንዲህ ከሆነ፥ ከዓሥራ አራት ሊበልጡ ነው። ምክንያቱም ቄሱ አልሰሙም እንጂ፥ ቅዳሴዎቹ ወደኻያ ይጠጋሉ። መምህሬ ቄስ ማርቆስ ዳውድ ይህን መቅድም ሲጽፉና ትርጕሙን ሲያሳትሙ እያወቁ ሁለት በደል ፈጽመዋል፤ (1) “የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ይኸንን ታረጋግጣለች” ያሉት ማስረጃ ሳይኖራቸው ነው። (2) መጽሐፈ ቅዳሴውን የተረጐመላቸው አብሮ አደግ ወዳጄና ጓደኛየ ዶክተር ገብረ ጻድቅ ደገፉ ነው። ግን እኝህ መንፈሳዊ አባትና መምህር ይኸንን ሐቅ ጨቁነውታል፤ የገብረ ጻድቅን ስም ለምስጋና እንኳን አላነሡትም።

ከታተመው መጽሐፈ ቅዳሴ ውስጥ ያሉት የቅዳሴ ጸሎቶች (አኰቴተ ቍርባን) ዓሥራ አራት የሆኑት ለኅትመት የተመረጠው የብራና ቅጂ ውስጥ ያሉት ዓሥራ አራት ስለነበሩ ነው። ካህናቱ እንደምታስታውሱት፥ ቅዳሴ ጎርጎርዮስ (ነአኵቶ ለገባሬ ሠናያት--ነአኵተከ እግዚኦን አይደለም) የሚያነሣው ሊቀ ጳጳሱን አባ ዮሐንስን (፲፮ኛው 1676-1718) እና ጳጳሱን አባ ሲኖዳን (1671-1693) ነው። የእትሙ ምንጭ የተቀዳው በነሱ ዘመን 1676 እና 1693 መካከል በነበረው ዘመን ነው ማለት ነው።

ያደረግሁት ምርምር ጥሩ ዕድል ሆኖ ከዓሥራ አራቶቹ አብዛኛዎቹ ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን የመጡ ሳይሆኑ፥ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ድርሰቶች መሆናቸውን አረጋግጦልኛል። አባ ጊዮርጊስ በአፄ ዳዊትና በአፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን የኖሩ ብዙ መጻሕፍት የደረሱ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ናቸው። ከድርሰቶቻቸው ውስጥ ኆኅተ ብርሃን፣ አርጋኖነ ውዳሴ (= አርጋኖነ ድንግል) ውዳሴ መስቀል፤ መጽሐፈ ብርሃን፣ ጸሎተ ፈትቶ፣ ፍካሬ ሃይማኖት፣ መጽሐፈ ምስጢር የሚባሉ መጻሕፍት ይገኛሉ።

ደራሲያቸው ያልተረጋገጠውን አኰቴተ ቁርባኖች የመረመርኩትና የጥናቴን ውጤት ለኅትመት የላክሁት እነዚህ መጻሕፍት የተጻፉበትን ስልት መሣሪያ በማድረግ ነው። ምርምሬን የጀመርኩት ውበቱን ምዕራባውያን በመሰከሩለት ድርሰታቸው አርጋኖነ ውዳሴ ነው። ግን መጀመሪያ አርጋኖነ ውዳሴ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንጂ፥ እንደሚታመንበት የአርመናዊው ጊዮርጊስ (Giorgis the Armenian) እንዳይደለ ማስመስከር ነበረብኝ። ያስመሰከርኩበት ጥናት የምዕራባውያን ሊቃውንት ቀንድ የሆነ ሊቅ፥ The erroneous dating of the Arganonä Wəddase . . . as well as its false attribution to un unknown Giorgis the Armenian have been conclusively refuted ሲል ፍርዱን መዝግቧል።

ይኸ በራሱ አንድ አስደሳች የድካም ውጤት ነው። እርግጥ በኛ ዘንድ አርጋኖነ ውዳሴ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መሆኑን የሚጠራጠር የለም። ግን የኢትዮጵያ ታሪክ በምዕራቡ ዓለም በሰፊው ስለሚጻፍ፥ ልጆቻችንም እነሱ ዘንድ ስለሚማሩ፥ ታሪካችንን በተገኘበት ቦታና ጊዜ ሁሉ ማስተካከል ግዴታችን ነው። ከቅዳሴዎቹ አብዛኞቹ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መሆናቸውን ለማሳየት የምጥረውም ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን የመጡ ናቸው ተብሎ በሀገራችን ሳይቀር ተቀባይነት ያገኘውን የተሳሳተ እምነት ለማስቀረት ነው። አርጋኖነ ውዳሴ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መሆኑ ከተረጋገጠ የአጻጻፋቸው ስልት ምን እንደሚመስል ላሳይ። በድርሰቶቻቸው ላይ ሁሉ በተለይ ከዚህ በታች ያሉት ባሕርዮች ጎልተው ይታያሉ፤
1. ይዞታቸው እንደ መጽሐፈ ምስጢር ነገረ መለኮት ማስተማሪያ ናቸው፤
2. በጀመሩበት ቃል ብዙ አረፍተ ነገሮች ያከታትሉበታል፤
3. በአረፍተ ነገሩ መጀመሪያ ሐረግ ላይ ያለውን ሐሳብ በሁለተኛው ሐረግ ያጠነክሩታ፤
4. በአረፍተ ነገሩ መጀመሪያ ሐረግ ላይ ያለውን ሐሳብ በሁለተኛው ሐረግ ያፈርሱታል፤
5. አረፍተ ነገሮቹ ቤት የሚመቱ የማይመቱም ቅኔዎች ናቸው፤
6. ካለው ግስ ላይ አዳዲስ ቃላት ይፈጥራሉ፤
7. ለኛ ባልታወቁ የውጪ ቃላት ይጠቀማሉ፤

እነዚህ የአጻጻፍ ባሕርዮች በብዙዎቹ ቅዳሴዎች ላይ ይታያሉ።
ቅዳሴ በመሠረቱ ከጸሎተ ሃይማኖት አልፎ ነገረ መለኮት መተቻ አይደለም። ብዙዎቹ ቅዳሴዎቻችን ግን እንደ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ድርሰቶች እንደ መጽሐፈ ምስጢር እና እንደ ፍካሬ መለኮት መለኮትን በሰፊው ይተቻሉ። ሁሉንም የአባ ጊዮርጊስን የአጻጻፍ ባሕርዮች ለማሳየት ከሁሉም ምሳሌ መስጠት መጽሐፈ ቅዳሴውን መገልበጥ ይሆናል። ግዕዝ የማያውቀውንም ያሰለቸዋል። ሆኖም ከዚህ በታች ያሉትን ብቻ እንመልከት፤

ከአርጋኖነ ውዳሴ ለምሳሌ
ኪያኪ፡ ረከብኩ፡ ምጒያየ፡ እሙስና፡ (ከብልሸት መሸሻ አንቺን አገኘሁ ፡)
ኪያኪ፡ ረከብኩ፡ ምጒያየ፡ እምአፈ፡ አናብስት፡ (ከአንበሶች አፍ መሸሻ አንቺን አገኘሁ፡)
ኪያኪ፡ ረከብኩ፡ ምጒያየ፡ እምአፈ፡ ተኵላተ፡ ዐረብ፡ (ከዐረብ ተኵላ አፍ መሸሻ አንቺን አገኘሁ፡)
ኪያኪ፡ ረከብኩ፡ ምጒያየ፡ እምቃለ፡ ዘይጽዕል፡ (ከተሳዳቢ ቃል መሸሻ አንቺን አገኘሁ፡)
ኪያኪ፡ ረከብኩ፡ ምጒያየ፡ እምእደ፡ ኵሎሙ፡ ጸላእትየ፡ (ከጠላቶቼ ሁሉ እጅ መሸሻ አንቺን አገኘሁ፡)

(1) ከቅዳሴ ማርያም፤

አኮ ዘቦቱ ለመለኮት ክበብ . . . አላ መንክር. . . (መለኮቱ ክበብ የለውም . . . አስደናቂ እንጂ . . .።)
አኮ ዘቦቱ ለመለኮት ግድም ወኑኅ . . . አላ ምሉእ . . . (መለኮቱ አግድሞሽና ርዝመት የለውም . . . በሁሉም ዘንድ የሞላ ነው እንጂ . . .)
አኮ ዘቦቱ ለመለኮት ምስፋሕ . . . አላ ውስተ ኵሉ . . (መለኮቱ መስፋፊያ ቦታ የለውም . . ግዛቱ በሀገሮች ሁሉ ነው እንጂ . . .)
አኮ ዘቦቱ ለመለኮት ዘበላዕሉ ጠፈር . . . አላ ጠፈር ውእቱ . . . (መለኮት በላዩ ጠፈር የለበትም . . . እሱ እራሱ ጠፈር ነው ኢንጂ . . .)

ይህ ጥቅስ (1)ነገረ መለኮት ነው፤ (2) አረፍተ ነገር በጀመረበት ቃል (አኮ) አረፍተ ነገር ይደጋግማል፤ (3) በመጀመሪያው ሐረግ ውስጥ ያለውን ሐሳብ በሁለተኛው ሐረግ ያፈርሰዋል (አላ)

(2) ከቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፤

አልብከ ጽንፍ ወአልብከ ማኅለቅት፤ (ዳርቻ የለህም፥ መጨረሻም የለህም፤)
አልቦ ዘረከቦ ወአልቦ ዘይረክበከ፤ . . . (ያገኘው የለም፥ የሚያገኝህም የለም . . .፤)
አልብከ ጥንት . . . (መጀመሪያ [origin] የለህም. . .፤)
ፈጠርከ፡ ኵሎ፡ እንዘ፡ ኢትትቀነይ፤ (ሳትገዛ ሁሉን ፈጠርክ፤)
ትጸውር፡ ኵሎ፡ እንዘ፡ ኢትደክም፤ (ሳትደክም ሁሉን ትሸከማለህ፤)
ትሴሲ፡ ለኵሉ፡ እንዘ፡ ኢታሐጽጽ፤ (ሳታጓድል ሁሉን ትመግባለህ፤)
ትሔሊ፡ ለኵሉ፡ እንዘ፡ ኢታረምም። (ዝም ሳትል ለሁሉ ታስባለህ፤)
ትሁብ፡ ለኵሉ፡ እንዘ፡ ኢትቀብል (ሳትጐድል ለሁሉ ትሰጣለህ፤)
ታረዊ፡ ለኵሉ፡ እንዘ፡ ኢትነጽፍ፤ (ሳትጠግ ሁሉን ታጠጣለህ፤) 8

ትዜከር፡ ኵሎ፡ እንዘ፡ ኢትረስዕ። (ሳትረሳ ሁሉን ታስታውሳለህ፤)
ተዐቅብ፡ ኵሎ፡ እንዘ፡ ኢትነውም፤ (ሳትተኛ ሁሉን ትጠብቃለህ፤)
ትሰምዕ፡ ኵሎ፡ እንዘ፡ ኢትጸመም፤ (እምቢ ሳትል ሁሉን ትሰማለህ፤)
ተኀድግ፡ ለኵሉ፡ እንዘ፡ ኢትነሥእ። (ሳትወስድ ለሁሉ ትተዋለህ።)
በተለይ እነዚህን ቀጥሎ የጠቀስኳቸውን ሁለት ጥቅሶች ብናስተያያቸው ሁሉም ከአንድ ሰው አእምሮ የወጡ ከመሆናቸው ላይ እንደርሳለን፤

() ከዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፤
ነሥአ፡ ኅብስተ፡ በእደዊሁ፡ ቅዱሳት፡ ወብፁዓት፡ ሕፄሃ፡ ለመርዓትከ፡ ወኅዳጋቲሃ፡ ለእንተ፡ ኀደጋ፡ ምኵራብ።
(በቅዱሳትና ብፁዓት እጆቹ ኅብስት አነሣ። [ኅብስቱ] ለሙሽራህ [ለምእመናንህ/ለቤተ ክርስቲያንህ] ማጫ፥ ለፈታሃት ለምኵራብ መፋቻ ሆኗል።)

() ከውዳሴ መስቀል፤
መስቀል፡ ዘኮነ፡ ሕፄሃ፡ ለመርዓትከ፡ ወኅዳጋቲሃ፡ ለእንተ፡ ደኃርካ፡ በምኵራብ።
(መስቀል የሙሽራህ [የቤተ ክርስቲያንህ] ማጫ በምኵራብ ለፈታሃት [ለሕዝበ አይሁድ] መፍቻ ሆኗል።)

() ከዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፤
ኅሩም፡ አንተ፡ ወሀሎከ፡ አብ፡ ቅዱስ።
ኅሩም፡ አንተ፡ ወሀሎከ፡ ወልድ፡ ቅዱስ።
ኅሩም፡ አንተ፡ ወሀሎከ፡ መንፈስ፡ ቅዱስ።

() ከመጽሐፈ ምስጢር፤
ኅሩም፡ አብ፡ ዘኢያስተርኢ፡ በህላዌሁ፡ ዘእንበለ፡ ዳእሙ፡ በራእየ፡ ትንቢት፡ ለነቢያቲሁ።
ኅሩም፡ ወልድ፡ ዘኢያስተርኢ፡ በመለኮቱ፡ ዘእንበለ፡ ዳእሙ፡ በትስብእቱ።
ኅሩም፡ መንፈስ፡ ቅዱስ፡ ዘኢያስተርኢ፡ በካልእ፡ ግርማሁ፡ ዘእንበለ፡ ዳእሙ፡ በንጻሬ፡ ዘይትፈቀድ፡ በዘይረድኦሙ፡ ለቅዱሳን።

እነዚህ () እና () የተጠቀሱ ኀይለ ቃሎች ከአንድ ሰው እንጂ ከተለያዩ ሰዎች አእምሮ የወጡ አይደሉም።

(3) ከአትናቴዎስ ቅዳሴ፤

ሰብእሰ፡ እንዘ፡ ክቡር፡ ውእቱ፡ . . . (የሰው ልጅ ክቡር ሆኖ ሳለ . . . )
ሰብእሰ፡ እንዘ፡ ንጉሥ፡ ውእቱ፡ . . . (የሰው ልጅ ንጉሥ ሆኖ ሳለ . . . )
ሰብእሰ፡ እንዘ፡ ባዕል፡ ውእቱ፡ . . . (የሰው ልጅ ሀብታም ሆኖ ሳለ . . . )
ሰብእሰ፡ እንዘ፡ ልቡስ፡ ውእቱ፡ . . . (የሰው ልጅ ብርሃን የለበሰ ሆኖ ሳለ . . . )
ሰብእሰ፡ እንዘ፡ መላኪ፡ ውእቱ፡ . . . (የሰው ልጅ ገዢ ሆኖ ሳለ . . . )
ኦአዳም፡ ምንተኑ፡ ረሰይናክ፡ . . . (አዳም ሆይ ምን አደረግንህ . . .?)
ኦአዳም፡ ምንተኑ፡ ረሰይናክ፡ . . . (አዳም ሆይ ምን አደረግንህ . . .?)
ኦሔዋን፡ ምንተኑ፡ ረሰይናኪ፡. . . (ሔዋን ሆይ ምን አደረግንሽ . . .?)
ኦአዳም፡ ወሔዋን፡ እስመ፡ አኮ፡ . . . (አዳምና ሔዋን ሆይ ልንነቅፋችሁ አይቻልም. . .)
ኦአዳም፡ ወሔዋን፡ አንትሙሰ፡ . . . (አዳምና ሔዋን ሆይ እናንተስ . . .)
ኦአዳም፡ ወሔዋን፡ አንትሙሰ፡ . . . (አዳምና ሔዋን ሆይ እናንተስ . . .)
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ ቀዳማዊት፡ ይእቲ፡ ወአኮ፡ ደኃራዊት፡ . . .
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ ደኃራዊት፡ ይእቲ፡ እንተ፡ ትሰፍን፡ ለዓለም።. . .
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ ለአብርሃም፡ ተከሥተት፡ . . .
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ ለሙሴ፡ በደብረ፡ ሲና፡ ተከሥተት፡ . . .
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ በነቢያት፡ ተዐውቀት፡ . . .
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ ቅድስቱ፡ ለአብ፡ ቡርክቱ፡ ለወልድ፡ ልዕልቱ፡ መንፈስ፡ ቅዱስ።
ኦ፡ ባዕዳት፡ ዕለታት፡ እንተ፡ ባቲ፡ ተአመርክን፡ . . .
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ እንተ፡ ባቲ፡ ብሊት፡ ተፀርዐት፡ ወሐዳስ፡ ጸንዐት።
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ እንተ፡ ባቲ፡ ሙቁሓን፡ ተፈትሑ፡ ወአግብርት፡ ግዕዙ።
ኦ፡ ዛቲ፡ ዕለት፡ እንተ፡ ባቲ፡ ምዝቡር፡ ተሐንጸ፡ ወሰይጣን፡ ተኀጕለ።

(4) ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ፤

አልቦ፡ ጥንት፡ ለህላዌሁ፤ (አነዋወሩ መጀመሪያ የለውም፤)
ወአልቦ፡ ማኅለቅት፡ ለክዋኔሁ፤ (አኳኋኑም መጨረሻ የለውም፤)
አልቦ፡ ኍልቍ፡ ለመዋዕሊሁ፤ (ዘመኑ ቍጥር የለውም፤)

ወአልቦ፡ ሐሳብ፡ ለዓመታቲሁ። (ዓመቶቹም ልክ ቍጥር የለውም፤)
ወአልቦ፡ ርስዓን፡ ለውርዛዌሁ፤ (ጕልምስናውም እርጅና የለውም፤)
ወአልቦ፡ ድካም፡ ለጽንዐ፡ ኃይሉ፤ (የኀይሉ ጥንካሬ ድካም የለውም፤)
ወአልቦ፡ ሙስና፡ ለመልክኡ፤ (መልኩም ብልሹነት የለውም፤)
ወአልቦ፡ ጽልመት፡ ለብርሃነ፡ ገጹ። (የፊቱም ብርሃን ጨለማ የለውም፤)
አልቦ፡ ድንጋግ፡ ለባሕረ፡ ጥበቡ፤ (የጥበብ ባሕሩ ዳርቻ የለውም፤)
ወአልቦ፡ መስፈርት፡ ለሣህለ፡ ትእዛዙ፤ (የትእዛዙም ምህረት ልክ የለውም፤)
አልቦ፡ ዐቅም፡ ለስፍሐ፡ መንግሥቱ፤ (የመንግሥቱ ስፋት መጠን የለውም፤)
ወአልቦ፡ ወሰን፡ ለራኅበ፡ ምኵናኑ። (የግዛቱም ስፋት ወሰን የለውም፤)

ከዚያ ይህ ይቀጥላል፤
ሥውር፡ ውእቱ፡ (ሥውር ነው)
ወምጡቅ፡ ውእቱ፡ (ምጡቅ ነው)
ነዋኅ፡ ውእቱ፡ (ረጂም ነው)
ቀላይ፡ ውእቱ፡ (ጥልቅ ባሕር ነው)
ልዑል፡ ውእቱ፡ (ልዑል ነው)
ወእሙቅ፡ ውእቱ፡ (ጥልቅ ነው)
ጽኑዕ፡ ውእቱ፡ (ጠንካራ ነው)
መዋዒ፡ ውእቱ፡ (አሸናፊ ነው)
ጠቢብ፡ ውእቱ፡ (ጥበበኛ ነው)
ማእምር፡ ውእቱ፡ (ዐዋቂ ነው)
ኃያል፡ ውእቱ፡ (ኀይለኛ ነው)
ተባዕ፡ ውእቱ፡ (ጀግና ነው)
ክቡር፡ ውእቱ፡ (ክቡር ነው)
ከሀሊ፡ ውእቱ፡ (ቻይ ነው)
ዋሕድ፡ ውእቱ፡ (አንድዬ ነው)
ወብሑት፡ ውእቱ፡ (ብቸኛ ነው)
መንክር፡ ውእቱ፡ (አስደናቂ ነው)
ከዚህ በታች ያለውን በማነጻጸ የእግዚአብሔርን አገላለጽ እንመልከት፤
ኄር፡ ዘእንበለ፡ እከይ፤ (ክፋት የለለበት ደግ፤) 11

ወየዋህ፡ ዘእንበለ፡ በቀል፤ (በቀል የሌለበት የዋህ፤)
ወዕጉሥ፡ ዘንበለ፡ መዓት፤ (ቁጣ የሌለበት ታጋሽ፤)
ጻድቅ፡ ዘእንበለ፡ ኃጢአት፤ (ኀጢአት የሌለበት ጻድቅ፤)
ወንጽሕ፡ ዘእንበለ፡ ርስሐት፤ (እድፍ የሌለበት ንጹሕ፤)
ወራትዕ፡ ዘእንበለ፡ ጥውየት፤ (ጠማማነት የሌለበት ቅን፤)
ወሃቢ፡ ዘእንበለ፡ ክልአት፤ (ንፍገት የሌለበት ሰጪ፤)
ወጸጋዊ፡ ዘእንበለ፡ ደንፅዎ፤ (ስስት የሌለበር ለጋሽ፤)
ሠራዬ፡ ኃጢአት፡ ዘእንበለ፡ በቀል፡ ወቂም፤ (በቀልና ቂም የሌለበት ኀጢአት ይቅር ባይ፤)
መጽያሕት፡ ዘእንበለ፡ ማዕቀፍ፤(እንቅፋት የሌለበት ጥርጊያ ጎዳና፤)
ወዐሠር፡ ንጹሕ፡ ዘእንበለ፡ አሥዋክ። (እሾኽ የሌለበት ንጹሕ ፈለግ፤)

ቅዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ የአባ ጊዮርጊስ ድርሰቶች ለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ቅዳሴ ያዕቆብ ዘሥሩግና ቅዳሴ ቄርሎስም የሳቸው ሳይሆኑ አይቀሩም።

ሌላው የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሥራ መታወቂያ ካለው ግስ ላይ አዳዲስ ቃላት ይፈጥራሉ። በቅዳሴ ማርያም ውስጥ የሚገኙ ቃላት “አማዕበለ” (ማዕበል አነቃነቀ) “መስግዲ” (አሰግድ) “መትሐቲ” (ዝቅ አርጌ) “መቅንዪ” (አስገዥ) የአባ ጊዮርጊስ ፍጥረቶች ናቸው።

ለኛ ባልታወቁ የውጪ ቃላት ይጠቀማሉ ብያለሁ። በሥነ ጽሑፍ ውስጥ ፒላስ” (ድንኳን) የሚለው ቃል የተገኘው ሦስት ቦታ ብቻ ነው፤ 1. በመጽሐፈ ምስጢር፤ 2. በአርጋኖነ ውዳሴ፤ 3. በቅዳሴ ቄርሎስ፤

 
ሜሎስ (እሳታዊ) የሚለው ቃል የተገኘው ሦስት ቦታ ብቻ ነው፤ 1. በመጽሐፈ ምስጢር፤ 2. በቅዳሴ ያዕቆብ ዘሥሩግ፤ (3) በቅዳሴ ቄርሎስ፤

እመቤታችን ታቦት ዘዶር/ ታቦተ ዶር የተባለችው 1. ቅዳሴ ማርያም 2. በመጽሐፈ ምስጢር ውስጥ ብቻ ነው።

የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ቅርሳችን ተዝረክርኳል። እስካሁን የደረሱለት ምዕራባውያን ብቻ ናቸው። የኛ ዝምታና ቍጭት- አልባነት ባለማወቅና አስታዋሽ በማጣት ይመስለኛል። ቢያውቅና አስታዋሽ ቢያገኝ ቍጥሩ ከአምሳ ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ የማንነቱ መታወቂያ ቅርሱ ሲወድም ዝም ብሎ አያይም። ሳንውል ሳናድር የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ቅርስ ድርጅት ማቋቋም አለብን።