የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን
ኒው ዮርክ ከተማ
(የተራድኦ ድግስ ምሽት፥ ኅዳር ፬ ቀን ፳፻፰ ዓ. ም. = November 14, 2015)
ጌታቸው ኃይሌ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንድታገለግሉ የተመረጣችሁ የተከበራችሁ ካህናትና ዲያቆኖት፥ የመድኃኔ ዓለም አባላት እንድትሆኑ የሐዋርያትን ጥሪ ያከበራችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን እኅቶቼና ወንድሞቼ፥ በዚህ የበጎ አድራጎት ምሽት ላይ ተገኝቼ ለሥጋ ጣፋጩን የኢትዮጵያ ምግብ በስመጥር ጠጅ አያወራረድኩ እንድመገብና ስለመንፈስ አርኪው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሥነ ጽሑፍ ቅርስ ያሉኝን አንዳንድ ትዝብቶች እንዳጫውታችሁ ስለ ጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የትልቅ ታሪክ ችቦ ተሸካሞች ነን። ችቦውን መሸከም መስቀለ ሞቱን የመሸከም ያህል ይከብዳል፤ ግን የኩሩው ማንነት መታወቂያችን ስለሆነ ከባዱን ሸክም በደስታና በጸጋ እንሸከመዋለን። ስለችቦውና ስለ አቀጣጣዮቹ ተናገር ስላሉኝ ተደስቻለሁ። ቅዱስ ዳዊት “ተፈሣሕኩ እስመ ይቤሉኒ ቤተ እግዚአብሔር ነሐውር” (ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ስላሉኝ ተደስቻለሁ) ባለው አነጋገር ስለተጠቀምኩ መንፈሱ እንደማይወቅሰኝ እለምነዋለሁ።