Saturday, October 31, 2015

ላስቬጋስ - ጎንደር


አሜሪካ ስመጣ ሦስት ቦታ ያለው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይማርከኛል፡፡ ላስቬጋስ  ኪዳነ ምሕረትና ቅዱስ ሚካኤል፣ ዴንቨር መድኃኔዓለምና ሚነሶታ ቅድስት ሥላሴ፡፡ ሃይማኖታቸውን የተረዱ፣ ለአገልግሎት የተጉና ምራቃቸውን የዋጡ ክርስቲያኖች ያሉበት ቦታ፡፡ ወደነዚህ ቦታዎች ስመጣ ከማስተምረው የምማረው ይበልጣል፡፡ በአስቸጋሪው የአሜሪካ ኑሮና ፈተና ውስጥ የቤተ ክርስቲያን እምነትን፣ ሥርዓትና ትውፊትን ጠብቆ፣ ጊዜንና ገንዘብን ሠውቶ፣ የቤተ ክርስቲያንንም አንድነት ጠብቆ ለማገልገል የሚደረገው ተጋድሎ እንኳን የኔ ቢጤውን ሊቃውንቱንም የሚያስደምም ነው፡፡ በተለይ የወጣቶቹ አገልግሎት ጎላ ሚካኤል፣ ተምሮ ማስተማር፣ መርካቶ ተክለ ሃይማኖት ወይም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ያላችሁ ነው የሚመስላችሁ፡፡


ላለፉት አምስት ሳምንታት ላስቬጋስ ነበርኩ፡፡ ‹‹የኃጢአት ከተማ›› እያሉ አሜሪካኖች የሚጠሯት የቁማር ከተማ ውስጥ፡፡ ከቅዳሜና እሑድ ይልቅ ረቡዕና ኀሙስ የዕረፍት ቀን በሆነባት ከተማ፡፡ ከሚፈቀደው ይልቅ የማይፈቀደውን ኃጢአት መዘርዘር በሚቀልባት ከተማ፡፡ ክረምቱ ሲመጣ ሙቀቷ እንደ ገሃነም በሚያቃጥልባት ከተማ፤ ዙሪያዋን በተራራ ታጥራ መሐሏ እንደ ድስት ጎድጉዶ፣ ቁማር ላይ የተጣደች ድስት በምትመስለው ከተማ፡፡ በታዋቂው የኔቫዳ በረሃ ውስጥ በምትገኘው ከተማ፡፡ ከተመሠረተች 110 ዓመት በሆናት ጎልማሳዋ ከተማ፡፡ የመጀመሪያዋን ባለቁማር ሆቴል (ጎልደን ጌት ሆቴልን) እኤአ በ1906 በተከለች ከተማ፡፡ በዓመት ከ41ሚሊዮን በላይ ጎብኝ በምታስተናግደዋ ጭንቅንቅ ከተማ፡፡ በየዓመቱ ከ22ሺ በላይ ስብሰባና ትርዒት በምታስተናግደው ውክቢያም ከተማ፡፡ 


ቅዱስ ጳውሎስና አባ ኤፍሬም አንድ ሆነው ‹ኀጢአት በበዛችበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች› እንዳሉት ሆነና ብርቱዎቹ ክርስቲያኖች መሬት ገዝተው በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ሠርተዋል፡፡ ላስቬጋስ ኪዳነ ምሕረት ወቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፡፡ ያውም ወጭው ሙሉ በሙሉ ከፍለው ያለ ዕዳ፡፡
እዚህ የመጣሁት ለአንድ ወር የሚቆይ ሥልጠና ተዘጋጅቶ ነው፡፡ መታዘዝ ከመሥዋዕትነት ይበልጣል ብዬ እንጂ በቀለጠቺው የላስቬጋስ ከተማ፣ ዕረፍት በሚነሣው የአሜሪካ ሩጫና ጊዜ ጠየቅ በሆነው ልጆችን የማሳደር ኃላፊነት ውስጥ ያንን ያህል ቁጥር ያለው ሰው ሥልጠናውን ይወስዳል የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ 

ሥልጠናው ሲጀመር ግን የኔን ፍርሃት የሚንድ፣ የላስቬጋሶችን ቆራጥነት የሚያሳይ ነገር መከሰት ጀመረ፡፡ ረቡዕ ከምሽቱ 12 ሰዓት(6 pmበምዕራብ አሜሪካ ሰዓት) እስከ 2 ሰዓት(8 ሰዓት)፣ ኀሙስ ደግሞ ከምሽቱ 11 (5 pm በምዕራብ አሜሪካ ሰዓት) እስከ 1(7 pm  በምዕራብ አሜሪካ ሰዓት) ነበር ሥልጠናው የሚሰጠው፡፡ ከእነዚህ ጊዜያት በተጨማሪ ኀሙስ ጠዋትና እሑድ ጠዋት ቅዳሴ አለ፡፡ እሑድ ከቅዳሴ በኋላ ደግሞ ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው መጥተው የልጆች መርሐ ግብር ይካሄዳል፡፡
ሥልጠናው ሦስት ክፍሎች ነበሩት፡፡ ትምህርት፣ የቤት ሥራና አቅርቦት፡፡ ከአንድ ተኩል እስከ ሁለት ሰዓታት የሚፈጅ ትምህርት አለ፡፡ ትምህርቱን መሠረት ያደረገ የቤት ሥራ ይሰጣል፡፡ የቤት ሥራው ቅዱሳት መጻሕፍትን ማገላበጥና አባቶችን መጠየቅን የግድ ይላል፡፡ የተሠራው የቤት ሥራ በቀጣዩ ቀን በድንገት በተመረጡ ሠልጣኞች ለሕዝብ ይቀርባል፡፡ ይሄ ራሱ ጊዜ ጠየቅ ነው፡፡ ከሥራ፣ ከልጆች፣ ከምግብ ማብሰልና ከቤት ጽዳት በሚተርፍ፣ ከዕንቅልፍ በሚቀማ ጊዜ የሚከናወን፡፡  

ክርስቲያናዊ ቤተሰብ›፣ ‹የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት›፣ ‹ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን›ና ‹መንፈሳዊ አገልግሎት› የትምህርቶቻችን ርእሶች ነበሩ፡፡ ትምህርቱን ለመከታተል ከአንድ መቶ ሰው በላይ በሰዓቱ ይገኝ ነበር፡፡ ትምህርቱ ከተጀመረ ከ10 ደቂቃ በኋላ በሩ እንደሚዘጋ ሕግ ስለወጣ ሁሉም ተሯሩጦ በሰዓቱ ነበር የሚገኘው፡፡ ከድካምና ከዕንቅልፍ ጋር እየታገሉ መማር፣ ልጆችን ይዞ መጥቶ እየጠበቁ ሥልጠና መከታተል ከባድ ነበር፡፡ ላስ ቬጋሶች ግን በሚደንቅ ጽንዐት ተወጡት፡፡ በችግር ወይም በሥራ ምክንያት የቀሩትም ስልካቸው ከፍተው ባሉበት ይከታተላሉ፡፡ ያለበለዚያም ጓደኞቻቸው ቀድተው ይወስዱላቸዋል፡፡ የቤት ሥራውን ግን ይሠራሉ፡፡
ብዙዎች የማዕድ ቤት ሥራ እንጂ የቤት ሥራ ረስተዋል፡፡ ምንም እንኳን ትምህርቱ ታትሞ ቢሰጥም ማስተዋሻ መያዝ ግን የግድ ነበር፡፡ ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ አባቶችና እናቶች በትጋት ትምህርቱን ሲከታተሉ፣ የቤት ሥራቸውን ሲሠሩና የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት አገላብጠው የተሰጣቸውን ሠርተው ሲመጡ እንደማየት በአሜሪካ ምን ተአምር አለ፡፡ 

ሥልጠናው የተጠናቀቀው የእመቤታችንን ስደት በማስመልከት በካሊፎርንያ ግዛት ወደሚገኘው የአባ ሙሴ ጸሊምና አባ እንጦንስ የግብጽ ገዳም በተደረገ ጉዞ ነበር፡፡ ከ300 በላይ ምእመናን በ6 አውቶቡሶች ተሣፍረው መንፈሳዊ ውይይት እያደረጉ ነበር የተመሙት፡፡ የግብጹ ገዳም ጉብኝት ቅዳሴ፣ ትምህርትና የአንድነት ምግብ(አጋፔ) የታከሉበት ነበር፡፡ እጅግ አስደናቂው ነገር ደግሞ በዚህ ጉዞ ለመሳተፍ ከ4 ሰዓት በላይ ተጉዘው የሳንድያጎ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ምእመናን አብረውን መኖራቸው ነው፡፡ 

ኀሙስ ከቅዳሴ በኋላ ትምህርታቸውን በሚገባ ያለ ቀሪ የተከታተሉ፣ የቤት ሥራቸውን የሠሩና ያላረፈዱ ሠልጣኞች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ነበር፡፡ የብዙዎቹ ምእመናን ጥያቄ ወደፊት ሊቃውንቱን ጋብዘን ጠንከርና ጠለቅ ያለው የቤተ ክርስቲያን ወደ መማር መጓዝ አለብን የሚል ነበር፡፡ በቀጣይም ሊቃውንቱ ተገኝተው ትውፊታዊውን ጉባኤ የሚያስተምሩበትን መንገድ ለማዘጋጀት ነው የወሰኑት፡፡ ይበል ነው፡፡ ድካም፣ የቤት ውስጥ ሥራ፣ ልጆችን መከባከብና የዕንቅልፍ እጦት የማይበግራቸው የላስ ቬጋስ ካህናትና ምእመናን ያደርጉታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ብቻ እድሜ ይስጠን፡፡ እድሜ ለሰጠው ላስቬጋስ ጎንደር ትሆናለች፡፡ ‹ለእመ አእመረ ባቲ፣ ጎንደርሰ ዋልድባ ይእቲ› አይደል የሚባለው፡፡

18 comments:

 1. ሰላም ዲያ ቆን ዳኒ ,አገልግሎትህን መድሃኒያለም ይባርክልህ. የቬጋሥ ካህናቶችም የተሰጣቹን አላፊነት እሰከ መጨረሻው እንድትጠብቁት እመብርሐን አትለያቹ አሜን! ለህዘብ ክርሰትያኑም እንዲሁም ለሰበካ ጉባሔ አባላቶቹም በተለያየ መንገድ እናት ቤተክርሰትያናችንን የምትረዱ ሁሉ ደስ ይበላቹሁ ዋጋቹሁን በሰማይ የሚከፍል አምላክ ሥራቹሁን ያያል .በርቱ በፈተና ፅኑ !የእግዚሃብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን !!

  ReplyDelete
 2. ደግ ፥ይበል የሚያስብል መልካም ዜና ነው።ቤተ ክርስትያን በዚያች የ'ሀጢያት ከተማ' መገንባቱ የትውልዱ የወንጌል ፍሬ ስለሆነ በቤቱ ያጽናችሁ ያስብላል።ሆኖም ግን በዚህች ከተማ እንደ ዴማስ የጠፉ ወገኖች ነበሩ ዛሬም አሉ፥ ስንት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፈረሰ መሰለክ? ብቻ ቤት ይቁጠረው፥ ስንት ጋብቻ ፈረሰ በቬጋስ?ከዚህ ጋር መታየት ያለበት ትውልዱን በቅድስት ቤተ ክርስትያን ትምህርት የማነጽና የማዳን ስራ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።ከዚህ ጋር ላነሳው የሚገባው ትልቁ ስራ ቤተ ክርስትያን ያለ ተተኪ እንዳይቀር ሊታሰብበት ይገባል የዛሬ 50 አመት አንድ በኒዮርክ ያለ የአይሁድ ምኩራብ ዛሬ የሚረከብ ትውልድ በማጣቱ ወደ ንግድ ተቕምነት አዘንብሎዋል።አበቃሁ የቀድሞ የቬጋስ ነዋሪ ነኝ፥ ስለሁሉም ነገር ግን ዳ ዳንኤል እግዚአብሔር ይመስገን።

  ReplyDelete
 3. አገር ቤቶች በእጅ ያለ ወርቅ ሆኖብን በተኛንበት ዘመን

  ReplyDelete
 4. ለእመ አእመረ ባቲ፣ ጎንደርሰ ዋልድባ ይእቲ›

  ReplyDelete
 5. Hi, Dani- sometimes I am confused when I read your blog, because I don’t like when you write your opinion or what you like. I feel all Deacon, Priest and preacher are our religion leader so even if you accept it or not, I feel you are my leader because of this when I read something from you I want read general topic, comment or suggestion not specific. What I want to say is you shouldn’t mention three churches while we have more than 119 churches in USA. I know most of the churches have big problem but you have to write something that help them to improve their leader ship. Especially in some churches the Sunday school students are work hard to satisfy us so don’t hurt their feeling.

  ReplyDelete
  Replies
  1. Well, as anyone he has full right to write, comment .... based on what he smells. If you really get a chance to read carefully and understand well about his point, I assure you wouldn't say that. God bless you.

   Delete
 6. Des yemilina arayanet yalewu ageligilot

  ReplyDelete
 7. በዚህ ሁሉ ነገር መካከል ሆነው ለሀይማኖታቸው የሚሰጡ ቦታና ጊዜ ለብዙዎቻችን የመንፈሳዊ ሕይወት መፈተሸሻ ማስተማሪያ ነው ዲያቆን ዳንኤል ቃለ ሕይወት ያሰማል የነሱንም ብርታትና ጥንካሬ ይስጠን አሜን

  wtbmhg

  ReplyDelete
 8. "በእጅ ያለ ወረቅ ከመዳብ ይቆጠራል"እዲሉ እዚህ ሀገር ውሰጥ ያለን ጉባኤ አዘጋጅተና ኑና እግዚአብሔር የሚነግራችሁን ስሙ ወንድሞቻችሁን እህቶቻችሁን ጋብዙ ስንባል ምንም አይመስለንም አንዳንዱ ጉባኤማ ቤተክርስቲያኑ በአጥቢያው ነዋሪም ያለው አይመስልም አንድም ሆነ ሁለትም ሆናችሁ በስሜ ብትሰባስቡ እኔ በመሐከላችሁ እገኛለሁ ያለው ቃል ቢኖርም ካለን የህዝብ ብዛት አንፃር ሲታይ እጅግ አናሳ አየሆነ ነው በተለይ በሀገር ውስጥ የስጋ ነገራችን እየሳሳ በመንፋሳዊ ነገር በቤተክርስቲያን ነገር መሰባሰባችን ካለው የህዥብ ቁጥር አንፃር ቀፅሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያነሰ ነው ለዚህ ታዲያ ከላስቬጋስ ነዋሪዎች ምን እንማራለን፡፡

  ReplyDelete
 9. Glory to be God for the support,courage & initiation of such programs I hope others may take a lesson from this.Thank you so much Danie.

  ReplyDelete
 10. ወንድም ዳኒ በአሁኑ ስአት በአገራችን ርሃብ ወገኖቻችንን እየተፈታተነ ይገኛል፤ስለሆነም በዮኒቨርስቲ ያለው ተማሪ ከሚበላው ቀንሶ ፣አርቲስቶች በሙያቸው ሁሉም እንደ እያቅሙ የሚችለውን እንዲያደርግ ባለህ አቅም ጥሪህን አስተላልፍ፤ዲያስጶራውም የበኩሉን እንዲያደርግ ምከር፤ይህን በማድረጋችን እንባረክበታለን ብቻ ሳይሆን አገራዊ አንድነታችንን ያጠናክራል፤በህዝቡ መካከል የመተሳሰብ ባህልን ያጎለብታል...ወዘተ።ቤተክርስትያናችን ይህን ሃዋርያዊ ተግባር በቀዳሚነት ትፈጽም ዘንድ በየ ሰንበት ትምህርት ቤቱ እና አውደ ምህረቱ እንቅስቃሴ እንዲጀመር ለማድረግ እንሞክር።

  ReplyDelete
 11. ታላቅ ቆራጥነት የሚታይበት ምዕመን ነው እግዚአብሔር ፀጋውን ያብዛላቸው፡፡

  ReplyDelete
 12. Thank you brother.
  God bless you much!

  ReplyDelete
 13. እጅግ የሚገርም ጽሁፍ 

  ReplyDelete
 14. እኔ ራሴ እንቅልፋም ሁኜለሁ!!!

  ReplyDelete
 15. መልካም ነው የመንፈስ ወንድማችን።

  ReplyDelete
 16. God bless you brother. Thank you for reporting how the holy spirit is work in a place like Las Vegas and continue to bless us with a good new and wisdom words. God bless!!!!

  ReplyDelete