Tuesday, October 20, 2015

አቡነ ቴዎፍሎስ ‹ያላረፉት› ፓትርያርክ

 

ሰሞኑን የቀድሞው የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ የጻፉትንና ‹አብዮቱና ትዝታዬ› የተሰኘውን መጽሐፍ ሳነብብ ስለ አቡነ ቴዎፍሎስ አሟሟት የጻፉትን አገኘሁ፡፡ ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ እስካሁን ከጻፉት የቀድሞ ባለሥልጣናት በሁለት ነገር ተለይተውብኛል፡፡ የመጀመሪያው በቡድንና በጋራ ለሠሯቸው ስሕተቶች ይቅርታ መጠየቃቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሁሉም ወገኖች የተፈጠሩትን ያለፉትን ስሕተቶች ለማረም ያስችላል ያሉትን የጋራ መድረክ ሐሳብ ማቅረባቸው ነው፡፡
ምንም እንኳን በዘመነ ደርግ የተፈጠሩት ስሕተቶችና ጥፋቶች ደርግ ብቻውን ያደረጋቸው ባይሆኑም አንዱና ዋነኛው ተዋናይ ደርግ ነበርና ለተሠሩት ጥፋቶች ይቅርታ መጠየቃቸው ለሌሎች አካላትም አርአያነት ያለው ነው፡፡ ዋናው የደርጉ መሪ ያ ሁሉ ጥፋት ሲሠራ ‹እኔ አላውቅም ነበር›› ብለው በካዱበት ሁኔታ ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ የራሳቸውን ይቅርታ መጠየቃቸው ለሰማዩም ለምድሩም ጉዟቸው ምትክ አልባ ተግባር የሚሆን ነው፡፡ ክብር ይስጥልን፡፡

ያ ዘመን በተሻለ እንመራለን ብለው የተነሡ ፖለቲካዊ ኃይሎች እንደየዐቅማቸው ስሕተቶችን የሠሩበትና ጥፋቶችን ያጠፉበት ዘመን ነው፡፡ ሁሉንም ጥፋት ለደርግ በመስጠት እጅን መታጠብ አይቻልም፡፡ እርሳቸው እንዳሉትም የደርግን ባለ ሥልጣናት ብቻ ወደ ፍርድ ከማቅረብ ይልቅ የነበረው ጥፋት ከየአቅጣጫው የሚፈተሽበትና ሁሉም እንደ ጥፋቱ የሚከሰስበት ወይም የሚወቀስበት አለበለዚያም ደግሞ ይቅርታ የሚጠይቅበት መንገድ ቢመቻች መልካም ነበር፡፡ ችግሩንም በተቻለ መንገድ ሊፈታው የሚችለው ሁሉን አቀፍ የሆነው አካሄድ ነበር፡፡ አሁንም መሪ ተዋናዮቹ ከማለፋቸው በፊት ሁሉም እንደየድርሻው ኃላፊነቱን የሚወስድበትና ይቅርታ የሚጠይቅበት ሥርዓት ቢመቻች መልካም ነበር፡፡
ያ ካልሆነ ግን ሥርዓት በተቀየረና ሕጎች በተሻሻሉ ቁጥር ተከድነው የሚንተከተኩ ነገሮች እንደገና የመውጣታቸውና በመድረቅ ላይ ያሉ ቁስሎችን የማመርቀዝ ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ፕላስተር የተለጠፈበት ቁስል ሁሉ አይድንምና፡፡
ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ በጻፉት መጽሐፍ ላይ ግን ጥያቄ እንዳነሣ ያደረገኝ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን የተመለከተ፡፡ በመጽሐፉ ላይ የሚከተሉት ነገሮች ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መገደል ጋር ተያይዘው ቀርበዋል፡፡

1.      1. ቤተ ክህነት መሬቷ ስለተነጠቀ አብዮቱን እንደተቃወመች
እግዚአብሔር የለም ብሎ የሚክደው ኮሚንስታዊ መንግሥት ሲመጣ ቤተ ክህነት ባትቃወም ነበር የሚገርመው፡፡ በተለይም የመሬት ለአራሹ አዋጅ የጭሰኛውን የዘመናት ጥያቄ የመለሰ ቢሆንም የፈጠራቸውም ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተመሠረተው በመሬት ላይ በመሆኑ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማትም የመተዳደሪያ መሬት ነበራቸው፡፡ ልክ ዛሬ የመተዳደሪያ ሕንጻና ገንዘብ እንዳላቸው ሁሉ፡፡ ነገሥታቱና መኳንንቱ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ስለነበሩም ለቤተ ክርስቲያን የመሬት ስጦታ ሰጥተዋል፡፡ የመሬት ላራሹ ዐዋጅ ሲታወጅ ግን የካህናትንና የገዳማውያን ሁኔታ ግምት ውስጥ ሊያስገባ አልቻለም፡፡ እንደ አንድ በመሬት የሚተዳደር ኢትዮጵያዊ ዜጋ ካህናቱና መነኮሳቱ ለአንድ ገበሬ የተመደበውን መሬት እንዲያገኙ እንኳን አልተደረገም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ስም መኳንንቱ ይዘውት የነበረው  መሬት ከግምት ውስጥ አልገባም፡፡ ቢያንስ በቶፍነት ሥርዓት ውስጥ የነበሩትን ካህናት እንኳን አብዮቱ ሊያያቸው አልፈቀደም፡፡ ሲሆን ቅርስና ባሕል ጠባቂ እንደመሆናቸው በተለይ ገዳማቱ ተጨማሪ የጋራ መሬት ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ የወቅቱ የደርግ ባለሥልጣናት ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን ከመጀመሪያው በጠላትነት ስለፈረጁ የድርሻዋን እንኳን ለመስጠት አልቻሉም፡፡ በምዕራብ ሸዋ የነበረው ደብረ ጽሙና ገዳም መሬቱን ሙሉ በሙሉ አጥቶ ሊፈርስ ሲል ኮሎኔል ደበላ ዴንሳ በሰጡት መመሪያ ጥቂት መሬት አግኝቶ መትረፉን አረጋውያኑ ዛሬም ከምስጋና ጋር ያስታውሱታል፡፡
ገዳማትና አድባራቱ ከልክ በላይ የያዟቸው መሬቶች ከነበሩ መጠኑን መቀነስና በቂ ነው የተባለውን ያህል መስጠት እንጂ ያላቸውን በሙሉ ነጥቆ በድህነት እንዲማቅቁ ማድረግ በምንም መልኩ ፍትሐዊ ሊሆን የማይችል ነው፡፡ ‹‹ኮሚኒዝም ማለት ድህነትን እኩል ማካፈል ነው - an even distribution of poverty›› የተባለው ነው የተፈጸመው፡፡ ፍትሐዊነት ያላገኘውን አካል እንዲያገኝ አድርጎ እኩል ማድረግ እንጂ ያገኘውን እንዲያጣ አድርጎ በድህነት ማስተካከል አይደለም፡፡ ይኼንን የወቅቱ ቤተ ክህነት ብትቃወመውና ከአብዮቱ ጋር ለመጓዝ ቢቸግራት ተገቢ ነው፡፡ ያውም በበቂ ሁኔታ አልሄደችበትም፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ በ1967 ዓም ለዘመን መለወጫ ባስተላለፉት መልእክት ‹‹በጦር ኃይሉና በሕዝቡ የተጀመረው የተቀደሰ እንቅስቃሴ መልካም ውጤት እንዲያስገኝ ፈጣሪያችን ይርዳን›› ነበር ያሉት፡፡(ሐዲስ ሕይወት፣ ግንቦት 1፣ 1967 ዓም፣ ገጽ 17)፣ የዕድገት በኅብረት ዘመቻንም ፓትርያርኩ በበጎ ነበር ያዩት፤ ይህም ጥቅምት 3 ቀን 1967 ዓም በሰጡት መግለጫ ላይ ተመልክቷል፡፡(ገጽ 17)
ይኼ ጉዳይ በከተማ ቦታና ትርፍ ቤት ዐዋጁም ጊዜ ተከሥቷል፡፡ ብዙ ምእመናን ብጽዐት ገብተው እየሠሩ፣ ሲሞቱም እያወረሱ ለአድባራትና ገዳማት የሰጧቸው ቤቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ቤቶች በሀገር ቤት ብቻ ሳይሆን በኢየሩሳሌም ከተማ ሳይቀር ይገኙ ነበር፡፡ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት ዐዋጅ ሲታወጅ ግን ለአንድ ሰው የሚኖርበት የ500 ካሬ ሜትር ቦታና አንድ ቤት ሲፈቅድ ለአድባራትና ገዳማት ግን ምን አልተፈቀደም፡፡ በሙሉ ነው የተወረሰው፡፡ ራሳቸው ፍሥሐ ደስታ እንደመሰከሩት ዐዋጁ ጠላ ሽጣ፣ ማገዶ ቸርችራ ድኻዋ የሠራቺውን፣ ኮርያና ኮንጎ ዘምተው ባገኙት የደም ዋጋ መለዮ ለባሾች የገነቡትን ሁሉ ሀብት ከተትረፈረፋቸው ጋር እኩል በመውረሱ ‹‹ብዙዎች አብዮቱን የደገፉ ጭቁኖች ከበዝባዦች ጋር አብዮቱን ያጥላሉ ጀመር››(ገጽ 160)፡፡
ከነዚህ በዐዋጁ ከተጎዱት መካከል አብያተ ክርስቲያናቱ አንዱ ናቸው፡፡ ቢያንስ የተወሰነውን ቤት እንዲያገኙ መደረግ ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን ደርግ የተመለከተበት መነጽር ችግሩን እንዳያይ የሚጋርደው ነበር፡፡ ለዚህም ነው ቤተ ክህነት ለውጡን በበጎ ልታየው ያልቻለቺው፡፡ በርግጥ መንግሥት 4 ሚሊዮን ብር ምትክ ካሣ ሰጥቻለሁ ብሎ ነበር፡፡ በጎላ ወስዶ በጭልፋ መመለስ ማለት እንዲህ ነው፡፡ ያውም አራት ሚሊዮን ብሩ ሳይጨመር ሳይቀነስ በደርግ ዘመን ሁሉ የኖረ ነው፡፡
አቡነ ቴዎፍሎስ በ60ው ባለ ሥልጣናት የግፍ ግድያና በንጉሠ ነገሥቱ ሞት በእጅጉ አዝነው ነበር፡፡ የንጉሠ ነገሥቱን አስከሬን ወስደው በክብር ለመቅበር በነሐሴ 1967 ዓም ደርግን ጠይቀው አልተፈቀደላቸውም፡፡ ከዚህም አልፎ ለንጉሠ ነገሥቱ በይፋ የፍትሐት ጸሎት እንዳያደርጉም ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው(ፍሥሐ ደስታና ሌሎችም ቢዘሉትም)፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ ከዚህ በኋላ ነው ለውጡን በሥጋት ማየት የጀመሩት፡፡

2     2. አቡነ ቴዎፍሎስ የራሳቸውን ወገኖች በመሾም በአብዮቱ ላይ ውስጥ ውስጡን ሤራ እንደሠሩ
አቡነ ቴዎፍሎስ የራሳቸውን ሰዎች ሾሙ ያሰኛቸው ሦስት አባቶችን በጵጵስና መሾማቸው ነው፡፡ ደርግ መንግሥትና ቤተ ክርስቲያን ተለያይተዋል፤ እንዱ በሌላው ጣልቃ አይገባም ብሎ ዐወጀ፡፡ ፓትርያርኩ ይህንን ተከትለው ደርግን ሳይጠይቁ ሦስት አባቶችን ሾሙ፡፡ አቡነ ጳውሎስን፣ አቡነ ባስልዮስና አቡነ ጴጥሮስን፡፡ ሦስቱም አባቶች በነበራቸው ዕውቀት የተሾሙ እንጂ ለአቡነ ቴዎፍሎስ በነበራቸው ዝምድና አልነበረም፡፡ በሀገር ልጅነትም ሆነ በዝምድና አይገናኟቸውም ነበር፡፡ ደርግን ተደፈርኩ አስብሎ ፓትርያርኩን እንዲያሥር ያደረገው ይኼ የፓትርያርኩ ሳያስፈቅዱ መሾማቸው ነው፡፡ ያሠረውም ፓትርያርኩንና አዲስ የተሾሙትን ኤጲስ ቆጶሳትን ነው፡፡  
3  3. አቡነ ቴዎፍሎስን በተመለከተ የቤተ ክህነት ሰዎች ለመንግሥት አቤቱታ አቅርበው ነበረ ፡፡
  በሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ መጽሐፍ ላይ የቤተ ክህነት ሰዎች አቡነ ቴዎፍሎስን በተመለከተ ያቀረቧቸው ክሶችና አቀራረቡን ገልጠውታል፡፡ የመጀመሪያው ክስ አቡነ ቴዎፍሎስ አባ መልእክቱ ተብለው መነኩሴ እያሉ በአቡነ ጴጥሮስ ግድያ ላይ እጃቸው አለበት የሚለው ነው፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ ወደ አዲስ አበባ ከቤተሰቦቻቸው ጠፍተው የመጡት በ1920 ዓም ነው፡፡ የሄዱትም በአዲስ ዓለም ማርያም ወደነበሩት ሐዲስ ተክሌ ዘንድ ነው፡፡ ሐዲስ ተክሌ በቀለም አያያዛቸው ስለወደዷቸው አቀረቧቸው፡፡ አባ መልእክቱ ከአዲስ ዓለም ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው በ1930 መነኮሱ፡፡ ጣልያን ሀገሪቱን ሲወር እርሳቸው የመምህራቸው የሐዲስ ተክሌ ደቀ መዝሙር ሆነው በአዲስ አበባ ነበሩ፡፡
በወቅቱ የነበሩት አባቶች የጣልያን ወረራን በተመለከተ ሁለት ዓይነት ሐሳብ ነበራቸው፡፡ እንደ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል ያሉት ከዐርበኞች ጋር ሆነው ጣልያንን ለመፋለምና ሀገሪቱን ነጻ ለማውጣት ወሰኑ፡፡ ሌሎች አባቶች ደግሞ ሕዝቡ ያለ እረኛ መቅረት የለበትም የሚለውን ሐሳብ ደግፈው የሊቃውንት ጉባኤ በማቋቋም ወደ ሀገራቸው የሄዱትን  ግብጻዊውን አቡነ ቄርሎስን ተክተው መሥራት ጀመሩ፡፡
አቡነ ቴዎፍሎስ የአቡነ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር እንደመሆናቸው መምህራቸውን ተከትለው ከማገልገል ያለፈ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ በተፈጸመው ግፍ እጃቸው ነበረበት የሚል ምንም ዓይነት ማስረጃ እስካሁን አልቀረበም፡፡ ደግሞም በዚያ ጊዜ በነበራቸው ሁኔታ ይህንን ለመፈጸም የሚበቃ ሥልጣን አልነበራቸውም፡፡ የጠሉትን ሰይጣን፣ የወደዱትን መልአክ ማለት ልማድ ሆኖ ጠላቶቻቸው ለውጡን ተጠቅመው ለጥብስ አቀረቧቸው እንጂ ማስረጃ ሊያቀርቡበት የሚችሉበት ነገር አልነበረም፡፡ ደርግም ማስረጃ አልጠየቀም፤ ለማጣራትም አልሞከረም፡፡ ሌ/ ኮሎኔል ፍሥሐም አገላለጣቸው ‹ቤተ ክህነቱ ስለከሰሳቸው አሠርናቸው እንጂ ነገሩ ከኛ አልመጣም› ዓይነት ነው፡፡ የአቡነ ቴዎፍሎስን ሕይወት የቀጠፈው ግን ክሱ ሳይሆን ‹ከፍርድ በፊት ወንጀለኛ የሚያደርገው› የደርግ አሠራር ነበር፡፡ በዚያ ላይም ሳያስፈቅዱኝ ሾሙ ብሎ ደርግ ምክንያት ፍለጋ ላይ ነበር፡፡

ሁለተኛው ክስ ‹በቤተ ክህነት ሤራና አሻጥር ይሠራሉ› የሚለው ነው፡፡ ምን ዓይነት ሤራና አሻጥር እንደሆነ አልተገለጠም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ በመጣ ቁጥር ሰውን የመክሰሻ ቀላሉ መንገድ ‹ለውጡን ይቃወማል፣ ያለፈውን ሥርዓት ይደግፋል፣ ውስጥ ውስጡን አድማ ይመታል› የሚሉት አቤቱታዎች ናቸው፡፡ ምግቡን ለበዪው እንዲስማማ አድርጎ ማቅረብ፡፡ ይህንን እንድገምት ያደረገኝ ክሱን ያቀረቡትን አካላት በተመለከተ ኮሎኔሉ የሰጡን መረጃ ነው፡፡ ‹ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ገዳማት ፈርመውበት ነበር›(ገጽ 199) ይላል፡፡
እጅግ አስገራሚ መረጃ ነው፡፡ ሳይበጠር ይከካ፣ ሳይለቀም ይፈጭ እንደነበር የሚያሳይ፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በ1972 ዓም ባካሄደው የሰበካ ጉባኤ ቆጠራ የኢትዮጵያ ገዳማት ቁጥር 1000 እንደነበረ ያመለክታል፡፡(ከ1966-1972 ባለው ጊዜ እንኳን አዲስ የሚቋቋምበት ያሉትም በፕሮፓጋንዳውና በለውጡ እየተንገዳገዱ ነበር) ያ ዘመን እንዳሁኑ መንገድ ያልተስፋፋበት፣ ሞባይል ስልክ የሌለበት ጊዜ ነው፡፡ ወቅቱም የግርግር በመሆኑ ገዳማውያን ከበኣታቸው እንዲወጡ የሚያበረታታ አይደለም፡፡ በዚህ ላይ ራሳቸው ፍሥሐ ደስታ እንደነገሩን ገዳማቱ ሁሉ መሬታቸውን ተወርሰዋል፡፡ እንዴት ሆነው ነው በአብዮቱ ቅር የተሰኙ 900 ገዳማት ተገናኝተው በአቡነ ቴዎፍሎስ ላይ ሊፈራረሙ የሚችሉት? በየቦታቸው ሆነው ፈረሙ ቢባል እንኳን ማነው በዚያ ዘመን ከዋልድባ እስከ ማንዳባ፣ ከደብረ ዳሞ እስከ ደብረ ወገግ፣ ከማኅበረ ሥላሴ እስከ ዝቋላ፣ ከደብረ ቢዘን እስከ ደብረ ሊባኖስ ተዘዋውሮ ገዳማቱን ሊያስፈርም የሚችለው(ያውም ያኔ የኤርትራንም ገዳማት ይጨምራል)፡፡ ገዳማቱ ያሉበት አስቸጋሪ አካባቢ፣ የገዳማቱ ብዛትና የወቅቱ ሁኔታ ተደምሮ 10 በመቶ ገዳማት እንኳን ሊፈርሙ አይችሉም፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ ናቸው የፈረሙት እንዳንል እንኳን እነርሱም ቁጥራቸው በ1972 ዓም ከ25 ሺ በላይ ነበሩ፡፡ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነው፡፡
የአቡነ ቴዎፍሎስ ሞትና አሟማት አሁንም ያልተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ በሞታቸውና አሟሟታቸው ሦስት አካላት የነበራቸው ሚና አሁንም በሚገባ መፈተሽ አለበት፡፡ ቤት ክህነት(ከጳጳሳት ጀምሮ)፣ ደርግና ሌሎች አካላት(ለምሳሌ አስያዛቸው የሚባለው ሰው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጎፋ አካባቢ ነበረ)፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የእኒህን አባት ሁኔታ በሚገባ ማጣራት ይኖርባታል፡፡ አንድም ዋና ተዋንያን የነበሩት የቤተ ክህነትና የቤተ መንግሥት ሰዎች መረጃውን ይዘውት ጨርሰው ከማለፋቸው በፊት፤ ሁለት ቤተ ክህነቱንም ሆነ ደርግን የሚያስወቅስ ያልተሰማ መረጃ ነገ ከመውጣቱና ማጣፊያው ከማጠሩ በፊት፡፡ ቤተ ክህነት አንድ አጣሪ አካል አቋቁማ ታሪኩ የተጣራ እንዲሆን ማድረግ አለባት፡፡ የአብዮቱን ዘመን ታሪክ የምትነግሩን አካላትም መጻፋችሁ የሚያስመሰግናችሁ ቢሆንም የምትሰጡን መረጃ ግን እውነትና ሊታመን የሚችል ቢሆን በታሪክ ውስጥ የሚኖራችሁን ሥፍራ ምቾት የሚሰጠው ይሆናል፡፡
የአቡነ ቴዎፍሎስን አሟሟት በተመለከተ ሻለቃ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስም ሆኑ ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ በሁለተኛው እትሞቻቸው የሚያብራሩት ነገር ሊኖር ይገባል፡፡ አዲስ እየጻፋችሁ ያላችሁም አስቡበት፡፡

38 comments:

 1. ዲ/ን ዳኒ
  እግዚአብሄር እድሜና ጤና ይስጥልን። ግን ጥያቄዉ ዲ/ን ዳኒ በዚህ ሰዉ በላ፤ ኢትዮጲያን ለማጥፋት መንገዱን ከሚጠርግ ስርዓት ምን ዓይነት እውነት ማን ይድፈር?

  ReplyDelete
 2. ሰላም ዲያቆን ዳኒ, ይህን ጊዜና ዕድል ለሰጣቹ አምላክ አመሰግናቹ እውነቱን ፅፋቹ ብታልፉ የታሪክ ተወቃሸነት አይኖርባቹም.የህሊና ዕረፍትም ይኖራቹዋል. እኛ ምናልባት የመፃፋቹ አድናቂዎች ልንሆንም ላንሆንም እንችላለን.ነገር ግን የአቤልን እውነት የፈለገ ዝም ያላለ አምላክ በግፍ የተገደሉትንም የአባታችንን እውነት ይጠይቃቹዋል. የተሳሳታቹትን አርማቹ እውነቱን እንድትፅፉልን እንጠብቃለን. ቤተክህነቱም በግፍ ሰለ ተገደሉት አባታችን የተሟላ መረጃ መሥጠት መቻል አለበት. ዲያቆን ዳኒ ,መድሃኒያለም ይጠብቅህ አሜን!!!

  ReplyDelete
 3. Where are the investigative journalists? Here’s a case study for journalism students!

  Find out the truth, before white lie and liars cover the face of Ethiopia! Expose the facts of the matter, so the future has a true base, not a shaky one that every generation criticizes and escapes from.

  No matter how eager one become to start a new life, it should admit the facts of the past /bitter or sweet/ and learn a good deal out of it. Isn't this the core of Repentance?

  May the light of Almighty GOD and the guidance of our Lady Virgin Mary bring us ALL to such life, a one that starts with Repent!

  ReplyDelete
 4. "የአቡነ ቴዎፍሎስን አሟሟት በተመለከተ ሻለቃ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስም ሆኑ ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ በሁለተኛው እትሞቻቸው የሚያብራሩት ነገር ሊኖር ይገባል፡፡ አዲስ እየጻፋችሁ ያላችሁም አስቡበት፡፡"
  ዲ/ን ዳንኤል ቃለ ሕይወት ያሰማልን!

  ReplyDelete
 5. Dani really,really,really you are our icon especially for us !!!

  ReplyDelete
 6. ‹‹ኮሚኒዝም ማለት ድህነትን እኩል ማካፈል ነው
  an even distribution of poverty›› የተባለው ነው።
  ዳኒ ቃለ ህይወትን ይሰማልን ።

  ReplyDelete
 7. ቤተክርስቲያናችን እኮ ያጣችው እንደዚህ ለአባቶቻቸው የሚቆረቆሩትን ነው፡፡ እንደአንተ አይነቱን ለአባቱ፣ ለሀገሩ፣ለሐይማኖቱ ለህዝቡ የሚቆረቆር ወንድሞችን ያብዛልን፡፡ ከላይ አስተያየት እንደሰጡት ወንድሞቼ የእኔም አስተያየት ነው፡፡ እውነቱን እየገለፃችሁ እናንተ እንኳን ባትጨርሱት ተረካቢው ትውልድ እንዲያጠናቅቀው ማድረግ ስለሚቻል ጅማሬው ጥሩ ነው በርቱ፡፡ምን እላለሁ ዳኒ፡፡ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡

  ReplyDelete
 8. የእውነተኛ ደም ዘላለም ይጮሃል ለዛነው ዛሬ ላይ ይሄንን ለማለት ያደፋፈራቸው እውነቱን ከነሱ የበለጠ የሚያውቅ ስለሊለተ ንስሃ ቢገቡ ጥሩ ነው

  ReplyDelete
 9. lega egezabher ytabkhe!! abatachen ytgadalwebeten ewentwen bnegerun nesh begabew melkam new leneswem lkerewem tweled llgachewm egezabher amelk yker endlenn bgef ylferd ygadlwechw dem endabal bget fet hwle geza eych new ewntwen tngerw zmeblow yweshat yekert ylam egzabhern matlel aychalm egezabher lnesh mot ybkach lelewch kenant tmerew ktfat endktabw btaeregw ylafaw bbak malkam naw ewnt menagar hatyat aydalam ewentwen tnagarew egezabher lnesh ystachen edma tskmebt !! yedengle Maryam yasret leg andew amen!!

  ReplyDelete
 10. በአማን ነጸረOctober 21, 2015 at 2:47 PM

  ዳኒ ሕመማችንን ቀሰቀስክ፡፡ብትተወን ጥሩ ነበር፡፡እኔ ስለእኒህ አባት በተነሳ ቁጥር እታመማለሁ፡፡ፀፀት ይበላኛል፡፡አንተ ደግሞ እንዚህን ተነሳሒ ልቡና የሌላቸው ሰዎች አምነህ ይበልጥ ሆድ ታስብሰኛለህ፡፡እንግዲህ ፈቃድህ ከሆነ ከዚህ ቀደም በፌስገጽ ላሉ ጓዶቼ ከተጋራሁተ መጣጥፍ ልቆንጥር…
  ሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ!!
  1. ልደት፣ትምሕርት፣ሹመት!!
  1.1. ሚያዚያ 16 ቀን 1902 ዓ.ም በጎጃም ክ/ሀገር በደብረ ማርቆስ አውራጃ ደብረ ኤልያስ በተባለ ሥፍራ ከአባታቸው አቶ ወ/ማርያም ውቤና ከእናታቸው ወ/ሮ ዘርትሁን አደላሁ ተወለዱ፡፡የዓለም ስማቸው መልእክቱ ተባለ፡፡
  1.2. በተወለዱበት ደብር ንባብና ዳዊት ከመሪጌታ ረዳኸኝ፣ዜማ ከግራ ጌታ ሣህሉ ተማሩ፣ከታዋቂው የወለጋ ተወላጅ ሊቅ የኔታ ገ/ሥላሴ ቅኔ ተምረው ተመረቁ፡፡የቅዳሴ፣የውዳሴ ማርያምና የወንጌል ትርጓሜ ከእኚሁ ሊቅ አጠኑ፡፡
  1.3. በ1920 ዓ.ም አ/አ መጥተው ከታዋቂው ሊቅ ሐዲስ ተክሌ(ንቡረ ዕድ ተ/ሃይማኖት ኋላ አቡነ ዮሐንስ) መጻሕፍተ-ሐዲሳትንና የፍትሐ-ነገሥትን ትርጓሜ አጠኑ፡፡በተራቸው ወንበር ዘርግተው አስተማሩ፡፡
  1.4. በ1930 ዓ.ም ደ/ሊባኖስ ሄደው መዓርገ-ምንኩስና ተቀበሉ፡፡
  1.5. በ1934 ዓ.ም ን፡ነ፡ቀኃሥ ከቤ/ክ ምሑራን 20 ሰዎችን በገነተ ልዑል በዛሬው አ.አ.ዩ እንዲማሩ ሲያደርጉ አባ መልእክቱ እድሉን ተጠቅመው የእንግሊዝኛ ቋንቋ አጠኑ፡፡
  1.6. በ1935 ዓ.ም የመካነ ሥላሴ አለቅነትን መምህር ተብለው ተሾሙ፡፡መካነ ሥላሴ ተሰርቶ መንበረ ጸባኦት ቅ/ሥላሴ ካቴድራል ሲሰኝ በ1938 ዓ.ም የመጀመሪያው አለቃ በመሆን ሊቀሥለክጣናት ተብለው ተሾሙ፡፡
  1.7. ሐምሌ 18 ቀን 1940 ዓ.ም ለመዓርገ-ጵጵስና ተመርጠው በካይሮ ቅ/ማርቆስ ካቴድራል ከተሾሙት 5 ጳጳሳት አንዱ ሆኑ፡፡በኤጲስ ቆጶስነት የሐረርን ሀ/ስብከት መሩ፡፡
  1.8. በ1953 ዓ.ም የመጀመሪያው ፓ/ክ የብ/ወቅ/አቡነ ባስልዮስ እንደራሴ ሆነው በመሾም እስከ 1963 ዓ.ም ድረስ በተለይ የውጭውን ጉዳይ ሓላፊነት ተሸክመዋል፡፡
  1.9. ግንቦት 1 ቀን 1963 ዓ.ም የኢ/ያ ፓትርያርክና ዕጨጌ ዘመንበረ-ተ/ሃይማት ሆነው በኢ/ያ ምድር ተሹመዋል፡፡በዚህም በኢ/ያ ምድር የተሾሙ የመጀመሪያው ፓ/ክ ሆኑ፡፡
  1.10. የካቲት 9 ቀን 1968 ዓ.ም በደርግ መንግሥት ከመንበረ-ፓትርያርካቸው ወርደው ለእስር ተዳረጉ፡፡
  1.11. ሐምሌ 7 ቀን 1971 ዓ.ም በልዑል አስራተ ካሳ ቤት በገመድ ታንቀው ተገደሉ፡፡
  1.12. ሚያዚያ 23 ቀን 1984 ዓ.ም አጽማቸው ከመቃብር ወጥቶ የእሳቸው ስለመሆኑ ነፍሰኄር አቡነ መቃርዮስ አረጋግጠው ወጣ፡፡ቅ/ማርያም ቆየ፡፡ከዛም ሐምሌ 3 ቀን 1984 ዓ.ም በቅ/ሥላሴ ካቴድራል ፍትሐት ተደርጎላቸው ሐምሌ 4 ቀን 1984 ዓ.ም ባሰነጹት ጎፋ ገብርኤል ቤ/ክ አጽማቸው ዐረፈ፡፡
  2. የአቡነ ቴዎፍሎስ ቋሚ አስተዋጽኦ ለኢኦተቤክ!!
  2.1. የደርግ የመሬትና የከተማ ትርፍ ቦታዎች ይዞታ አዐዋጅን ተከትሎ የመጣብንን ኢኮኖሚያዊ ፈተና ያለ1965ቱ ቃለዓዋዲ ማለፍ እና ካሕኑ አሁን ላለበት የኑሮ ሁኔታ መብቃት አይታሰብም፡፡ይህ ቃለዐዋዲ ደግሞ የቴዎፍሎስ ሐውልት ነው፡፡ያስጠራቸዋል፡፡
  2.2 ቃለዐዋዲው የፈጠራቸው የሰበካ ጉባኤና የሰ/ት/ቤት አደረጃጀቶች የፓ/ኩ አርቆ አሳቢነት ጠቋሚዎች ናቸው፡፡አሁንም ድኩምነቱ ባይለቀውም የቤ/ክህነት አስተዳደር እጅና እግር ያወጣውም በዚህ ቃለዐዋዲ ነው፡፡
  2.3 በ1949 ዓ.ም በባሌ ጠ/ግዛት በስብከተ-ወንጌል ተዘዋውወረው 24 ሺህ ሰዎችን አሳምነው አጥምቀዋል፡፡
  2.4 በሐረር የካሕናት ማሰልጠኛ አቋቋሙ፣ት/ቤቶች ከፈቱ፣12 አብ/ክናት አሰሩ፣ማኅበራት አቋቋሙ፡፡
  2.5 አቡነ ጳውሎስንና አቡነ ገሪማን ጨምሮ ብዛት ያላቸው ደቀመዛሙርትን ወደ ውጭ እየላኩ አስተማሩ፡፡
  2.6 የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንን ታህሣሥ 26 ቀን 1964 ዓ.ም አቋቋሙ፣የ1966ቱን የወሎ ረሀብ ተከትሎ የህጻናትና የቤተሰብ ኮሚሽንን መሰረቱ፡፡የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርን ጨምሮ እነዚህ ተቋማት ዛሬ የኢኦተቤክንን የሚያስመሰገን ግዙፍ ሰብአዊ አገልግሎት እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
  2.7 ኪራያቸው ለገዳማት፣ለአብነት ት/ቤቶች እና ለካህናት የሚሆን ሕንጻዎችን አሰሩ፡፡የተወለዱበትን ደብረ ኤልያስ አሳደሱ፡፡ጎፋ ገብርኤልን ሰሩ፡፡በጎፋ ተግባረዕድ ከፍተው ተቋሙ እስካሁን በስራ ላይ ነው፡፡
  2.8 አቡነ ጳውሎስን ጨምሮ 9 ሊቃነ ጳጳሳትን ሾሙ፡፡
  2.9 ከምስረታው፡ገና አባ መልእክቱ ሳሉ በሊ/መንበርነት የመሩትን የቅ/ሥላሴን ኮሌጅ አጠናከሩ፡፡
  2.10 በእንደራሴነታቸው ዘመን ጀምሮ በያዙት የውጭ ግንኙነት የሰጡት አገልግሎት እጅግ የተመሰገነ ነበር፡፡በተለይ የምስራቅና የኦሪየንታል አብ/ክናት ጋር የነበራቸው ግንኙነት ጥብቅ ነው፡፡ሲበዛ ዓለምአቀፋዊ ፓ/ክ ነበሩ፡፡ለዚህ ነው መሰዋዕትነታቸውን ተከትሎ እነ አቡነ ሺኖዳ የተቆጡትና ከኢኦተቤክ ጋር እስከ ዘመነ አቡነ ጳውሎስ ድረስ ግንኙነታቸውን ያቋረጡት፡፡

  ReplyDelete
 11. በአማን ነጸረOctober 21, 2015 at 2:48 PM

  3. ብሂለ-ቴዎፍሎስ….ፈገግ ከሚያሰኙ ንግግሮቻቸው!!
  3.1 አንድ ታላቅ ሊቅ ቅኔ በሰንበት አደረጉላቸው፡፡ግን ሊቁ ዜማ(ሪትም እንበለው) ሰብረዋል፡፡ጎናቸው ያለውን ሰው እረ ዜማውን አርምላቸው ይሉታል፡፡ሰውየው የሊቁን ታላቅ ሰው መሆን አይቶ አንገቱን ደፋ፡፡ከዛ አቡነ ቴዎፍሎስ “በል ተወው በሰንበት አይታረምም ብለህ ነው” ብለው አሳቁት፡፡
  3.2 ቀኃሥ እንግዳ ይዘው ሥላሴ መጡ፡፡ቅዳሴውን አሳጥሩ እንግዳው እንዳይሰለች አሉ፡፡አቡነ ቴዎፍሎስ ሥርዓቱ በሚያዘው ይሄዳል እንጅ ለእርስዎ እንግዳ ተብሎ አያጥርም አሉ፡፡ቀኃሥ ተቆጥተው…እንዲህ ከሆነ እዚህ ቤ/ክ ተመልሰን አንመጣም…አሉ፡፡የቴዎፍለስ መልስ…”ግርማዊ ጃንሆይ!ማን ሊጎዳ??” የሚል ነበር፡፡
  3.3 አንድ ግለሰብ ለአቡነ ቴዎፍሎስ ቅኔ ለማድረግ ወረፋ በዝቶ ይከለከላሉ፡፡ኋላ ለምን ተከለከልኩ ብለው አቤቱታ መጡ፡፡አቡኑ “ወቀሳውን ትተህ ቅኔውን አምጣ-ያንጊዜም እኛ፣አሁንም እኛ” አሉት ይባላል፡፡
  3.4 በጣም ስማቸውን የሚያጠፋና የማይወዳቸውን ሰው የውጭ የትምህርት እድል አመቻችተው ላኩት፡፡ሰዎች እንዴት እሱን ይልካሉ ሲሏቸው መልሳቸው… “የሚሳደበው እኮ ስላተማረ ነው፣ከተማረ አይሳደብም” የሚል ነበር፡፡
  3.5 በእንደራሴነታቸው ዘመን ፓ/ኩን አቡነ ባስልዮስን የሚያማ ሰው አጋጠማቸው፡፡ተቆጡት፡፡አድጦኝ ነው አለ፡፡ “ታዲያ ሰው ባይሆን ወደ ታች እንጅ እንዴት ወደ ላይ ያድጠዋል??” አሉት፡፡
  4. ደርግ ለአቡነ ቴዎፍሎስ ግድያ የዘረዘራቸው 5 ድኩማን ምክንያቶች!!
  4.1 አንዳንዴ ሁለንተናዊ ታሪካችንን አይና …ኢትዮጵያዊ ማለት ባርነትን አጥብቆ የሚጠላ ነገር ግን ነጻነትን ለመሸከም አቅም የሌለው ድኩም ሕዝብ….ማለት ነው ብየ እደመድማለሁ፡፡ከግብጽ መንፈሳዊ ባርነት ለመውጣት ለክፍለ ዘመናት በተካሄደው ትግል ወገንና ብሄር ሳንለይ ባንድነት ቆምን፡፡ታገልን፡፡ነጻነቱ በተገኘ በ12 አመት ግን ከየትኛው ብሄር፣ከየትኛው መደብ ፓትርያርክ መሾም እንዳለበት እርስ በርስ መግባባት አቃተን፡፡ጅቡን አባረው ሲመለሱ እርስ በርስ እንደሚናከሱቱ-እንደ ከለባቱ ሆን!!ነጻነታችንን መሸከም አቃተን፡፡አቡነ ቴዎፍሎስ የዚህ ነጻነትን ያለመሸከም ርግማን ሰለባ ሆኑ፡፡
  4.2 ትናንት! ብፁዕነታቸው፣ቅዱስነታቸው ሲል የነበረው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለቤተ-ክህነትና ለካሕናት ያሰበ መስሎ የፈበረከውን፣ደካማ ካሕናት በነገር አቀባይነት ያገለገሉበትን፣የደርግን በሃይማኖት ጉዳይ ከነ ከስክስ ጫማው መዘፈቅ የሚያሳየውን የቅዱስ ፓትርያርኩን አበሳ፣ሰበቡን፣5ቱን ድኩማን ምክንያቶቹን “ሲጠበቅ የቆየው ፍርድ” በማለት መዘርዘር ጀመረ እንዲህ እያለ፡………….(1) ለፓትርያርክነት የበቁት የንጉሡ ወዳጅ ስለነበሩ በጥቂት መራጮች ድምጽ ብቻ ነውና ከስልጣን ይውረዱ፡፡(2) ከሕገ ቤ/ክ ውጭ በካፒታሊስት መንፈስ በመነሳት ሕንጻ እያሰሩ በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት አካብተዋል፡፡(3) 20 የተለያዩ የሂሳብ ቁጥሮች በግል ስማቸው ከመክፈታቸውም በላይ በግል አሽከሮቻቸውና ወዳጆቻቸው ስም ብዙ የሂሳብ ቁጥሮች ከፍተው ባሁኑ ጊዜ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ብር 4,029,350 ያንቀሳቀሳሉ፡፡(4) በግል ፈቃዳቸውና ሥልጣናቸው 3 ጳጳሳትን ሾመዋል፡፡(5) ከታሪክ ሲሸሹ የወደቁ፣የወንጌልን ሥራ ትተው ወደ ጎን ገሸሽ ያደረጉ፣የወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበራትን ያፈረሱ፣ቤ/ክ የቅርስ ደሃ ስትሆን ዝም ብለው የሚመለከቱ፣ከቤ/ክ ሥርዓት ውጭ ሥጋ-አምላክን በማቀበል ሕገ ቤ/ክ ያፈረሱ ናቸው ተባሉ፡፡
  4.3 ፓ/ኩ አልፈጸሙዋቸውም እንጅ ፈጸሙዋቸው ቢባል እንኳ ከላይ የተዘረዘሩት ክሶች በአብዛኛው መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው በመሆናቸው በደርግ ዓደባባይ የሚታዩበት የሕግ ምክንያት አልነበረም፡፡
  4.4 እናም ከ10 አመት በላይ የእንደራሴነት አገልግሎት ልምድ ያላቸው፣ሕንጻ እያሰሩ በኪራዩ ቤ/ክንን ራስ ለማስቻል የደከሙት፣ከ144 መራጭ የ123ቱን ድምጽ ያገኙት፣የብራና መጻህፍትን በማይክሮ ፊልም ያስቀረጹት፣በሲኖዶስ ፈቃድ ጳጳሳትን የሾሙት፣ወጣቶችን ወደ ቤ/ክ የሳቡት፣ያመኑ ጃማይካውያንን በድንኳን አስቀድሰው ያቆረቡት አባት እነዚህ ድርጊቶች በወንጀልነት ተቆጥረውባቸው፣እንደ አንድ ተራ የፊውዳል ተቀጽላ ታይተው፣በደረቅ ተላጭተው፣የሚጸልዩበትን መስቀልና ስዕል ተነጥቀው፣በባዶ እግራቸው እንዲሄዱ ተገደው፣ተንበርክከው፣በእጃቸው ካቴና-ባንገታቸው ገመድ ገብቶ፣በሁለት ኮማንዶዎች ግራና ቀኝ እየተሳቡ ትንፋሻቸው ተቋጨ-ምዕራፋቸው ተዘጋ!!ከምንኩስና እስከ ፕትርክና ያበቃቻቸው ቤ/ክ እንደተራ ምዕመን እንኳ ፍትሃት ለመፈጸም ፈራች፡፡እንደ አረማዊ፣እንዳልተጠመቀ፣እንዳ ኢ-አማኒ ከቤ/ክ ገረገራ ውጭ ተጣሉ!!ይሄ ሁሉ የሆነው ከግብጽ ቤ/ክ ነጻ በወጣን በ17ኛ አመታችን ነው፡፡ነጻነትን መሸከም አለመቻል!!ከ50 አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ፋሽስት በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የፈጸመውን በቴዎፍሎስ ላይ በመፈጸም ፋሽስትነት በቆዳ ቀለም እንድማይወሰን አረጋገጥን!!
  4.5 ኋላም አመታትን ጠብቀን፣አጽማቸው ወጥቶ፣በፊርማቸው ሞታቸውን በማጽደቃቸው በጸጸትና በኃዘን ተኮራምተው የሸበቱት አባቶች ወደማረፊያቸው ወደ ጎፋ ቅ/ገብርኤል ካቴድራል ተረፈ-አጽማቸውን ተሸክመውት ሲገቡ አይተን ለአመታት በውስጣችን ያቆርነውን ዕንባ አፈሰስነው፡፡የምር አለቀስን፡፡የሚያውቋቸው አለቀሱ፡፡ደርሰን ባናይም ታሪኩን የሰማንም አለቀስን፡፡የፈረሙባቸውም አለቀሱ፡፡በደላችንን በዚህ እንኳ ቢሽርልን!!የቴዎፍሎስን አሟሟት ባሰብኩት ቁጥር ዕንባየን መቆጣጠር አልችልም-በዚች ቅጽበት እንኳ!!

  ReplyDelete
 12. በአማን ነጸረOctober 21, 2015 at 2:52 PM

  5. አቡነ ቴዎፍሎስን ለሞት ያበቋቸው እውነተኛ ምክንያቶች!!
  (5.1) በወቅቱ የነበረው ጸረ-ሃይማናተኛነት አቋም በተለይም የኢኦተቤክንን መንበረ-ፓትርያርክ ከንጉሣዊ ሥርዓት አስተሳስሮ በ‘ተራማጅ’ ልሂቃንና ወታደራዊው መኮንኖች የተካሄደው የሃይማኖት ጥላቻ የተጫነው ፖለቲካ፣
  (5.2) የካሕናቱ በብሄርና በፍርሃት ተከፋፍሎ ያለልዩነት፣ያለተዐቅቦ፣በሙሉ ድምጽ የፓትርያርኩን ግድያ በፊርማ ማጽደቅ፣
  (5.3) የሕዝቡ መንጋ ሆኖ ‘ስቅሎ-ስቅሎ’ ማለት፣
  (5.4) ደርግ ለተቋሙ ካለው የተዛባ አመለካከት የተነሳ ያቋም መለሳለስ ያሳያል ተብሎ ባይጠበቅም ፓ/ኩ ራሳቸው ደርግ ከቤተመንግሥቱ ተሻግሮ የቤተክሕነት ኃላፊዎችን ማሰርና መግደል ሲጀምር ትርጉም ያለው ተቋማዊ ተቃውሞ አለማድረጋቸው፣
  (5.5) በ60ዎቹ ለተወሰደው የሞት እርምጃ ድጋፍ ተጠይቀው እምቢተኛ መሆናቸው፣
  (5.6) ግንቦት 1 ቀን 1967 ዓ.ም በወጣው የቤተክሕነቱ ‘አዲስ ሕይወት’ መጽሄት “አዲሱ ሥርዓት መላው የኢ/ያ ሐረዝብ የሚሳተፍበት እንጅ ለወታደር ብቻ የሚተው አይደለም” ማለታቸው፣
  (5.7) በዚሁ መጽሄት የደርግን ታታሪ ነጋዴን ከፊውዳል ያልለየ የከተማ ትርፍ ቤቶች የውርስ አዋጅ “ሊሰራ የማይወድ አይብላ” ከሚለው የወንጌል ሕግ ጋር ይጋጫል ሲሉ መተቸታቸው፣
  (5.8) መጋቢት 1 ቀን 1967 ዓ.ም ለወታደራዊው መንግሥት በኢኦተቤክ ላይ በደርጉ ሊወሰዱ ይችላሉ ባሉዋቸው ጉዳዮች ተመስርተው በቅድሚያ ያቀረቧቸው ባለ-7 ነጥብ የመብት ጥያቄዎች በደርግ አለመወደዳቸው፣
  (5.9) የንጉሡን አስከሬን ስጡንና ፍትሃት ፈተን እንቅበረው ማለታቸው፣
  (5.10) አቡነ ጳውሎስ የተካተቱበትን የ3 ጳጳሳት ሲመት ቅ/ሲኖዶሱን አስጸድቀው ነገር ግን ለደርግ ሳያሳውቁ ማከናወናቸው፡፡
  6 ዝክረ ቴዎፍሎስን የደርግ አያያዝ ያላማራቸው ወዳጆቻቸው ወደ ውጭ እንዲሸሹ ሲመክሯቸው አቡኑ በመለሱት መልስ እናሳርገው!!
  “…..አባቶቼ ሐዋርያትና ሰማዕታት ስለ እውነትና ስለ ቀናች ሃይማኖታቸው ሲሉ በሰይፍ ተቆርጠው፣በገመድ ታንቀውና በእሳት ተቃጥለው በሰማዕትነት ተሰውተዋል፡፡እኔም እንደነርሱ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ክብር ሲባል እስከ ሞትም ድረስ ቢሆን መከራና ሥቃይ ከመቀበል በቀር ወደ ኋላ የምልበት ምክንያት የለም፡፡ቀደም ሲል በእነ አቡነ ጴጥሮስ ላይ የደረሰውን የሰማዕትነት ሞት እኔም የነርሱን ጽዋ ቆርጨ እንድቀበል እንጅ እንድሸሽ አይገፋፋኝም፡፡….በብዙ ድካም የተገኘውን የቤተክርስቲያን ክብር ሕይወቴን ለማትረፍ ስል አላዋርድም፡፡ባንገቴ ስለት እያንዣበበ እንደሆነ ይታወቀኛል፡፡ቢሆንም ከዚሁ ሆኜ የሚመጣብኝን መከራ ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ ስለሆንሁ በምንም ተአምር አልሸሽም፡፡”
  7. በነገራችን ላይ ዳኒ፡-
  ስለዘረኛነት አጥብቀው የሚናገሩና የሚኰንኑ ባገር ውስጥና በውጭ ያሉ ጸሐፍት አቡነ ቴዎፍሎስን በዘረኛነት እየከሰሱ የጻፉባቸውን አይተኸው እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ካላየኸው የአባ ኪዳነማርያም ጌታሁንን ‹‹የሐሰት ምስክርነት›› መጽሐፍ ተመልከተው፡፡እንዲያው ለማዘን ከፈለክ ብዬ ነው፡፡እኔ በግሌ ደርግ ከወደቀ ከ11 ዓመት በኋላ በ1994 ዓ.ም አንድ ታላቅ ሊባሉ የሚችሉ ሰው የአባታችንን አቡነ ቴዎፍሎስን ስም ኪዳን ላይ በጸሎተ-ማርያም ስናነሳ ‹‹ቤ/ክ ወዲያ አውጥታ የጣለችውን ሰው አታንሱ›› ብለው ሲሳደቡ ሰምቻለሁ፡፡ተናጋሪው በመምህርነት ደረጃ ያሉ ዐይነስውር ነበሩ፤በወቅቱ የምመራቸው እኔ ነበርኩ፡፡ይመስለኛል የየት አካባቢ ተወላጅ እንደሆንኩ አላወቁም፡፡የአቡ ቴዎፍሎስን የትውልድ ክፍለ-ሀገርም ነው ደርበው የሚነቅፉት፡፡በጊዜው ሕመሙ ቢሰማኝም አረጋዊነታቸውን ዐይቼ ስድቤን ከአቡነ ቴዎፍሎስ ጋር ተጋርቼ ዝም አልኩ፡፡አንድ ሌላ አረጋዊ ሰው ግን የዐይነስውሩን ንግግር ሰምተው ኖሮ ‹‹እርስዎ አነሱት አላነሱት የቴዎፍሎስ ስም በመስዋዕትነት የከበረ ነው›› ብለው ዝም አሰኙዋቸው፡፡የእኔን በፍራቻ የታሰረ ቁስል አጠገጉልኝ!አቡነ ቴዎፍሎስ ኖረውም አልፈውም ጠላቶቻቸው ያልተኙላቸው እድለ-ቢስ አባት ስለሚመስሉኝ ያሳዝኑኛል!እንኳንስ ደርጎቹ በቃለዐዋዲ ድንጋጌ ፔሮል ተክለው ከ1967 ዓ.ም የአብዮት ማዕበል ያዳኗቸው ካሕናት እንኳ የእሳቸውን ስም በክፉ ለማንሳት አቅም አላቸው!
  ዝክረ-ቴዎፍሎስን በቅ/ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለዓመታት በሐዲስኪዳን መምህርነት ያገለገሉት መመህር ደጉዓለም ካሳ አንድ ወቅት ለቅዱስነታቸው ባበረከቱት ሕንጼሃ ቅኔ እናሳርገው፡፡
  ሕንጼሃ!!
  ቴዎፍሎስ ላሕም ዘኢይትሄየል በቀርኑ፣
  ምስለ ሰዋዒሁ ወዐለ አኮኑ፡፡
  ትርጉም፡- በቀርኑ (በቀንዱ) የማይበረታታው የዋሁ በሬ ቴዎፍሎስ ካራጁ (ከሚሰዋው) ጋር ዋለ፡፡ምስጢር፡- የአቡነ ቴዎፍሎስ አጋር የነበሩት የቅ/ሲኖዶስ አባላት አባታችንን ለደርግ ገመድ ፈርመው ሰጧቸው ማለታቸው ነው ሊቁ (መጋቤሐዲስ) የኔታ ደጉዓለም ካሳ!!ባጭሩ፡- በሬ ካራጁ ይውላል ማለት ነው!
  የአባታችን የአቡነ ቴዎፍሎስ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን!!
  ዳግም አባቶችን በግፍ ወደ መቃብር ከማውረድ ይጠብቀን!!

  ReplyDelete
  Replies
  1. ከብክለት ነፃ ለሆነው መረጃዎ እና አስተያየትዎ አመሰግናለሁ።

   Delete
  2. ወንድሜ አማን እግዚአብሔር ይባርክህ፣ሰላምና ጤናህን ያብዛልህ፣ብዙ ነገሮችን በተጨማሪ አጋርተህናል፡፡ ከእይታችን የራቁ ብዙ የተደበቁ ታሪኮች እንዳሉን ይሰማኛል፣ነገር ግን ከአለፈዉ እንድንማርና ስላለፍት አባቶቻችን እንድናዉቅ በእንዲህ ዓይነት መልኩ ሊያቀርብልን የሚችል ልበ ሙሉ ሰዉ ግን ያሻናል፡፡ እግዚአብሔር ህዝቦቿን ይባርክ! አሜን፡፡

   Delete
  3. ወንድሜ አማን እግዚአብሔር ይባርክህ፣ሰላምና ጤናህን ያብዛልህ፣ብዙ ነገሮችን በተጨማሪ አጋርተህናል፡፡ ከእይታችን የራቁ ብዙ የተደበቁ ታሪኮች እንዳሉን ይሰማኛል፣ነገር ግን ከአለፈዉ እንድንማርና ስላለፍት አባቶቻችን እንድናዉቅ በእንዲህ ዓይነት መልኩ ሊያቀርብልን የሚችል ልበ ሙሉ ሰዉ ግን ያሻናል፡፡ እግዚአብሔር ህዝቦቿን ይባርክ! አሜን፡፡

   Delete
  4. አባታችን በአማን ጥልቀት ስላለው መረጃወ እናመሰግናለን።እኔ ዳኒን ላመሰግን ለመጻፍ ስል የርስወን ጽሁፍ አይቸ ለዳኒም ያሰብኩትን ምስጋና ቦነስ አድርጌ ሰጠሁሆት።ሑላችሁንም እግዚአብሄር ያኑርልን።

   Delete
  5. ወነድም አማን በእዉነት ተደብቆ የኖረዉን ነገር ስላጋራሃኝ እጅግ አመሰግናለሁ፡፡ ከብር ለሰማእታት ለእምነታቸው ስለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ አነደ በግ ለታረዱ አባቶች ይሁንልን፡፡ እዉነት ብትቀጥንም አትበጠስም

   Delete
 13. ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ማን ናቸው? open the following link
  http://www.andadirgen.org/2013/02/blog-post_21.html

  ReplyDelete
 14. ፓትርያርኩ ስለ እምነታቸው የከፈሉት ዋጋ

  open the following link

  http://andadirgen.blogspot.com/2013/12/blog-post_30.html

  ReplyDelete
 15. It is better to ask Abune Markorios.

  ReplyDelete
 16. Dn.daniel ye Abatachinin tarik amuamuatachewn chemireh lemetsaf betemokir mereja masebasebu min yahil aschegari yimeselehal weys begileseb dereja mesratu adegawn kebad yadergew yihon?

  ReplyDelete
 17. ለአንድ ብፁዕ አባት የግፍ አገዳደል ምድራዊ ፍትህ እንዲያገኝ መጣር የእርሳቸውን ዋጋ ማሳነስ ነው። በመንፈሳዊ ተጋድሎ ያለፉ አባቶች አሟሟት ማጣራት የቤተክርስቲያን ተግባር ሊሆን እንዴት ይችላል መምህር? አለም የፈለገውን ቢያወራ እርሳቸውን ቤተክርስቲያን መዘከሯ በቂ ይመስለኛል። የክርስትና ህይወትን እና የፖለቲካ ቀውስን ለማስታረቅ ባትሞክር ጥሩ ነው። ወይ ለያይተህ ፈርጃቸው።

  ReplyDelete
 18. ምነው ጸሐፊው ማንበብ አትችልም ወይንስ አንብበህ
  መረዳት ከላይ እስከ ታች በሶስት ቦታ ተከፍሎ እኮ
  ስለእሣቸው ሥራና መስዋዕት መሆን ነበር እኮ
  የሚያስነብብህ ወይንም የገለጸልህ የማስተዋል ችሎታ ያድልህ

  ReplyDelete
 19. Aman Nsara!!Abat lble lega gerra gabaz ewntwen stnagerw slewent stmsakerw bmesmata !! bzhe zamen ytanew ewnte tngerow ltweledwe ymystamer thafe btam teket nachaw enswenm ketrache bztale blew !!egezabher amlek ytabkew ergem yaglglowet gzan edmna tana yestlen amen!!

  ReplyDelete
 20. tanks beaman e-nesere for today info of Abatachn, Most time your comment is crtisizing but you did job1 today.
  please use your knowldge like this to shrare for brothers and sisters.

  ReplyDelete
 21. ለተከበሩ በአማን ነጸረ
  አለማወቅ እንጂ ደጉ ሰላም የሚያሳድር ማወቅማ መከራ ነው ሲያስለቅስ ያኖራል፡፡ ብዙ ባለሥልጣናት እኮ አዋቂዎችን አርቀው ጨዋዎችን የሚሰበስቡት በማይወቅሰው ህሊናቸው ያዘዟቸውን ሁሉ እንዲፈፅሙላቸው እኮ ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት 21 ኪሎ መዝነው ነው ያረፉት፣ በእግራቸው ጫማ ሳያደርጉ ነው የኖሩት፣ ከደመወዛቸው የዳቦና የሻይ ብቻ ተጠቅመው ቀሪውን አሳዳጊ ላጡ ሕጻናት መርጃ ያውሉታል ወዘተ ሲባል እየሰማሁ እገረም ነበር፡፡ ለካ የተቀመጡበት መንበር የሰማዕቱ መንበር ስለሆነ ነበር!!! ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ዛሬ ነው ያወቅኋቸው፡፡ ቃለ ሕይወት ያሰማልኝ፡፡ ግን እኛ ምን ዓይነት ያልታደልን ትውልዶች ነን!? እንዴት ባለ ግፍ ላይ ተቀምጠን ነው የምንኖረው? ይህ ግፍስ በስንት ትውልድ ይጸዳ ይሆን? ደጉ ቀን መቼ መጥቶ የቤተ ክርስቲያንን ትንሣኤ ያሳየን ይሆን? አምላከ ቴዎፍሎስ፣ አምላከ ተክለሃይማኖት ይህችን ቤተ ክርስቲያን ጭርሱኑ እንዳይተዋት እያለቀስን ከመጠባበቅ በቀር ምን እንላለን! አምላከ ቅዱሳን ይፈውሰን፤ አሜን፡፡

  ReplyDelete
 22. ከዋናዉ ጭብጥ ጋር ባይሄድም ‹‹ኮሚኒዝም ማለት ድህነትን እኩል ማካፈል ነው
  an even distribution of poverty›› ይህንን አለምን ያናወጠ ትልቅ አስተሳሰብ(THEORY) በዚህ መንገድ ቢገለፅም አንተም መድገምህ ቅር አሰኝቶኛል::

  ReplyDelete
 23. I couldn't understand your view- Daneil, is it critique or suggestion. you are trying to enforce the previous regime Colonels to write your interest. "ye kes mist awoksh awokish siluat-------"

  ReplyDelete
 24. ABUNE THEWOFELOSEN YEGEDELEW EHAPA NEW

  ReplyDelete
 25. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ዛሬ ነው ያወቅኋቸው፡፡ ቃለ ሕይወት ያሰማልኝ፡፡

  ReplyDelete
 26. it is excellent feed back for fesseha deseta.

  ReplyDelete