Saturday, October 31, 2015

ላስቬጋስ - ጎንደር


አሜሪካ ስመጣ ሦስት ቦታ ያለው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይማርከኛል፡፡ ላስቬጋስ  ኪዳነ ምሕረትና ቅዱስ ሚካኤል፣ ዴንቨር መድኃኔዓለምና ሚነሶታ ቅድስት ሥላሴ፡፡ ሃይማኖታቸውን የተረዱ፣ ለአገልግሎት የተጉና ምራቃቸውን የዋጡ ክርስቲያኖች ያሉበት ቦታ፡፡ ወደነዚህ ቦታዎች ስመጣ ከማስተምረው የምማረው ይበልጣል፡፡ በአስቸጋሪው የአሜሪካ ኑሮና ፈተና ውስጥ የቤተ ክርስቲያን እምነትን፣ ሥርዓትና ትውፊትን ጠብቆ፣ ጊዜንና ገንዘብን ሠውቶ፣ የቤተ ክርስቲያንንም አንድነት ጠብቆ ለማገልገል የሚደረገው ተጋድሎ እንኳን የኔ ቢጤውን ሊቃውንቱንም የሚያስደምም ነው፡፡ በተለይ የወጣቶቹ አገልግሎት ጎላ ሚካኤል፣ ተምሮ ማስተማር፣ መርካቶ ተክለ ሃይማኖት ወይም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ያላችሁ ነው የሚመስላችሁ፡፡

Tuesday, October 27, 2015

የወታደሮቻችን ነገር


አፕሪል 12፣ 1868 የተጻፈ
click here for pdf
የመቅደላው ጀግና ዐፄ ቴዎድሮስ በመጨረሻዋ ሰዓት ለጄኔራል ናፒየሪ በጻፉት ደብዳቤ አበክረው የጠየቁት ነገር ከሁለት ቀናት በፊት በተደረገው ውጊያ የወደቀውን የወዳጃቸውንና የጦር መሪያቸውን የፊታውራሪ ገብርዬን አስከሬን ለመቅበር እንዲፈቀድላቸው ነበር፡፡ ‹‹ፊታውራ ገብርዬን የኔን ወዳጅ ሳላነሣው ያደርኩ ከሞትኩኝ ሁሉንም አብረው ይቅበሩኝ ብየ ነበር፡፡ ቁሜ ከዋልኩ ግን ልቅበረው ይፍቀዱልኝ›› ይላል ደብዳቤው፡፡ ለሀገሩና ለወገኑ በክብር የተሠዋ አስከሬኑም የክብር ዕረፍት ይሻዋልና፡፡
አሜሪካኖችና አውሮፓውያን የተሰጣቸውን ግዳጅ ለመወጣት የዘመቱ ወታደሮቻቸው ሲሠው በክብር አስከሬናቸውን ወደ ሀገር በማምጣት በብሔራዊ ሥነ ሥርዓት የመቅበር ያልጠፋ ልማድ እንዳላቸው በየጊዜው ሚዲያው ያሳየናል፡፡ እነዚህ ወታደሮች ሀገራዊ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የዘመቱ በመሆኑ መሥዋዕትነታቸውም ሀገራዊ ሆኖ መታሰብ አለበት፡፡
በኢትዮጵያ የቅርብ ዘመን ታሪክ የተሠዉ ወታደሮችን በክብር የመዘከር፣ በክብር የመቀበልና በክብር የመቅበር ሥነ ሥርዓት አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ በኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት የተሠዉ ስንት ወታደሮች ናቸው? የተሠዉትስ ወታደሮች መርዶ እንዴት ተነገረ? የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውስ እንዴት ተከናወነ? ሚዲያውስ ለዚያ ምን ዓይነት ሽፋን ሰጠው? የሁል ጊዜ ጥያቄዬ ነው፡፡ እኔ ሳልሰማና ሳላውቅ ተከናውኖ ካልሆነ በቀር፡፡ ለምንስ አስከሬናቸው በወታደራዊ ሥነ ሥርዓት ታጅቦ፣ ሰንደቅ ዓላማ ለብሶ፣ ብሔራዊ መዝሙር እየተዘመረ፣ ሕዝቡ ወደ አደባባይ በነቂስ ወጥቶ አላከበርናቸውም? እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡

Tuesday, October 20, 2015

አቡነ ቴዎፍሎስ ‹ያላረፉት› ፓትርያርክ

 

ሰሞኑን የቀድሞው የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ የጻፉትንና ‹አብዮቱና ትዝታዬ› የተሰኘውን መጽሐፍ ሳነብብ ስለ አቡነ ቴዎፍሎስ አሟሟት የጻፉትን አገኘሁ፡፡ ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ እስካሁን ከጻፉት የቀድሞ ባለሥልጣናት በሁለት ነገር ተለይተውብኛል፡፡ የመጀመሪያው በቡድንና በጋራ ለሠሯቸው ስሕተቶች ይቅርታ መጠየቃቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሁሉም ወገኖች የተፈጠሩትን ያለፉትን ስሕተቶች ለማረም ያስችላል ያሉትን የጋራ መድረክ ሐሳብ ማቅረባቸው ነው፡፡
ምንም እንኳን በዘመነ ደርግ የተፈጠሩት ስሕተቶችና ጥፋቶች ደርግ ብቻውን ያደረጋቸው ባይሆኑም አንዱና ዋነኛው ተዋናይ ደርግ ነበርና ለተሠሩት ጥፋቶች ይቅርታ መጠየቃቸው ለሌሎች አካላትም አርአያነት ያለው ነው፡፡ ዋናው የደርጉ መሪ ያ ሁሉ ጥፋት ሲሠራ ‹እኔ አላውቅም ነበር›› ብለው በካዱበት ሁኔታ ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ የራሳቸውን ይቅርታ መጠየቃቸው ለሰማዩም ለምድሩም ጉዟቸው ምትክ አልባ ተግባር የሚሆን ነው፡፡ ክብር ይስጥልን፡፡

Saturday, October 3, 2015

የዘመናችን ‹አጥማቂዎች›፡- የሐሳዊ መሲሕ መንገድ ጠራጊዎች


click here
(ክፍል ሁለት)

1.   ተአምራት ማድረግ የምን ውጤት ነው? ተአምራት ማድረግ ከሁለት ነገሮች ሊመጣ ይችላል፡፡ ከመንፈሳዊ ብቃትና ከሰይጣን አሠራር፡፡ በክርስትና ሕይወቱ የበረታ ሰው መንፈሳዊ ብቃቱ በሕይወቱ በሚገለጡ ተአምራት ሊታወቅ ይችላል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን የምናገኛቸው ቅዱሳን በገድል ተቀጥቅጠው፣ ሰማዕትነት ከፍለው፣ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በሚገባ ተጉዘው ዲያብሎስን ድል ሲነሡት በሕይወታቸው ውስጥ ተአምራት ይገለጣሉ፡፡ ይህም ማለት ተአምራት የመንፈሳዊ ብቃት መገለጫ ነው ማለት ነው፡፡ የተአምራት ስጦታ እንዲሁ በድንገት አይገለጥም፡፡ በዚያ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ እያደገ፣ እየተገለጠና እየተመሰከረለት በሚመጣ መንፈሳዊ ዕድገት ምክንያት እንጂ፡፡ ለዚህ ሁለት ምሳሌዎች እናንሣ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስና አቡነ ተክለ ሃይማኖት፡፡