Sunday, September 27, 2015

የዘመናችን አጥማቂ ነን ባዮች፡- የሐሳዊው መሲሕ መንገድ ጠራጊዎች

  click here for pdf
ክፍል አንድ
በዚህ ዘመን በተደጋጋሚ ከሚነሡ መንፈሳውያን ጥቄዎች መካከል አንዱ የጥምቀትና አጥማቂዎች ጉዳይ ነው፡፡ ጥምቀት(የክርስትና ጥምቀትን አይመለከትም) በብሉይና በሐዲስ ኪዳን ምእመናን ፈውሰ ሥጋ ፈውሰ ነፍስ እንዲያገኙባቸው ከእግዚአብሔር ከተሰጡ ጸጋዎች አንዱ ነው፡፡(2ኛ ነገሥት 5፤ ዮሐ. 5፣ዮሐ. 9)፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ውስጥ በልዩ ልዩ ገድላተ ቅዱሳን ላይ እንደምናነበው በጠበል ሕዝቡን ሲፈውስ ኖሯል፡፡ ሕዝብ ፈውስ የሚያገኝባቸው እንደ ሰሊሆምና እንደ ቤተ ሳይዳ የታወቁ የቃል ኪዳን ቦታዎችም ነበሩ፡፡
አሁን በያዝነው ዘመን አያሌ ‹አጥማቂ> የሚባሉ ሰዎች ተነሥተዋል፡፡ ክብራቸውን የሚገልጥ ማስታወቂያ ያስነግራሉ፣ መቁጠሪያ ይሸጣሉ፣ ቅባት ይቀባሉ፣ አዳራሽ ከፍተው ወይም ሕዝብ በሜዳ ሰብስበው እንፈውሳለን ይላሉ፤ ሰይጣን ተናገረ የሚባለውን በካሴት ቀድተው ይሸጣሉ፡፡ ከዚህ ቀጥዬ በማቀርባቸው አሥር ምክንያቶች እነዚህን ሐሳውያን መቀበል የለብንም ብዬ አምናለሁ፡፡

Monday, September 21, 2015

እህል ወይስ አረም ?


click here for pdf
አሁን ባለንበት ዘመን ያለን የኢትዮጵያ ትውልድ የሀገራችንን ታሪክ፣ የሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነትና የመሪዎቻችንን ሁኔታ ስንነጋገርና ስንጽፍ በአብዛኛው አሉታዊውን ነገር ይበልጥ ጎልቶ እንዲወጣ፣ ጥላቻ እንዲበቅል፣ ቂም እድሜ እንዲያገኝ፣ ልዩነት እንዲሰፋ፣ ጠብም ሥር እንዲሰድ በማድረግ ላይ የተመሠረተ ሆኖ ይታያል፡፡ ርግጥ ነው በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተፈጠሩ የመስተጋብር ችግሮች ሁሉ በኛም ሀገር ተፈጥረዋል፡፡ በኛ ሀገር የተፈጠሩትም በሌሎች ይገኛሉ፡፡ በዓለም ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ የኩራትም የውርደትም፣ የፍቅርም የጠብም፣ የሰላምም የጦርነትም፣ የእኩልነትም የጭቆናም፣ የመረዳዳትም የመጠፋፋትም፣ የሥልጣኔም የስይጣኔም ታሪኮች አሉ፡፡ እንኳን በአንድ ሀገር የሚኖሩ የተለያየ ዘውግ፣ ቋንቋ፣ እምነትና የኑሮ ደረጃ ያላቸው ቀርተው በተመሳሳይ ቋንቋ፣ ባሕልና የኑሮ ደረጃ የሚገኝ የአንዲት ሀገር አንድ ወጥ ሕዝብ እንኳን በውስጡ ጽጌረዳም እሾህም አለው፡፡ 

Tuesday, September 15, 2015

‹አርቲስቶቹ›ን ወይስ ጠቅላይ ሚኒስትሩንአንድ ጆሮና ጊዜ የገጠሙለት ሰው ነበር አሉ፡፡ ሰውዬው የተማረው ትምህርት የለውም፡፡ ሁለት ችሎታ ግን ነበረው፡፡ ሲባል የሰማው እውነትም ይሁን ስሕተት ልቅም አድርጎ ይይዝና ሌላ ቦታ ሄዶ የተማረው ያህል ያንደቀድቀዋል፡፡ ሁለተኛው ችሎታው ደግሞ አፈ ጮሌ ስለሆነ ነገር በምላሱ ይቆላል፡፡ ያንንም ይኼንንም እያቆላመጠ ከተማሩትና ከተመራመሩት በላይ ከብሮና ታፍሮ ይኖራል፡፡ አንድ ቀን የማያውቀውን ቀለም ሲያዜም የሰሙት ሊቅ አፍረው አቀረቀሩ፡፡ እርሱ ግን ከዕውቀት የደነገለ ነበርና አልገባውም፡፡ በኋላ ቀረብ ብሎ ‹ደኅና ነዎት የኔታ› አላቸው፡፡ እርሳቸውም ‹ደኅና ነህ›› ብለው ዝም አሉት፡፡ እርሱም ያላወቁት ስለመሰለው ‹አላወቁኝም መሰል መሪጌታ እኮ ነኝ› አላቸው፡፡ሊቁም ‹ዐዉቄሃለሁ› አሉት፡፡ እንዳቀረቀሩ፡፡ ‹ታድያ ምነው ካወቁኝ ከነ ማዕረጌ ሳይጠሩኝ ቀሩሳ› አላቸው፡፡ ‹አንተን አከብራለሁ ብዬ ሞያውን እንዳልሰድበው ፈርቼ ነው›› አሉት ይባላል፡፡
እኔም ‹እርቲስቶቻችን› የሚለው ቃል በትእምርተ ጥቅስ ያደረግኩት ሊቁ የፈሩትን ፈርቼ ነው፡፡ እንዳልተውባቸው ደግሞ ምን ብዬ እንደምጠራቸው ግራ ገብቶኝ፡፡ የአዲስ ዓመት ዋዜማውን መርሐ ግብር በዕለቱ ለማየት ስላልቻልኩ ቪዲዮውን ነው የተመለከትኩት፡፡ ሊነግሩን የፈለጉት ስለ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ፣ ስለ ሀገራችን ዕድገት፣ ስላለፈው ስኬታችን ቢሆንም እንኳን የቀረበው ዝግጅት ግን አደገች የምትባለውን ኢትዮጵያን የማይመጥን፣ ጥበብ ዞር ብላ ያላየቺው፣ ከንግግር ከፍ፣ ከፉከራ ዝቅ ያለ፤ ከፕሮፓጋንዳ ወረድ፣ ከዲስኩር ራቅ፣ ከድንፋታ ጠጋ ያለ ወለፈንዲ ሆኖ ነው የታየኝ፡፡ 

Thursday, September 10, 2015

የዕብድ ኀሙስ


የታደለ አገልጋይ የበላዩን ከስሕተት ይጠብቃል፡፡ ‹አማካሪ የሌለው ንጉሥ ያለ አንድ ዓመት አይነግሥ› እንዲሉ፡፡ አክዓብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከክርስቶስ ልደት በፊት(871-852 ቅልክ) የነበረ ንጉሥ ነው፡፡ የሚስቱን የኤልዛቤልን ቃል ሰምቶ ነቢያተ እሥራኤልን ሊያጠፋ ተነሣ፡፡ ብዙዎች በሰይፉ ጠፉ፣ ብዙዎችም አገር ጥለው ተሰደዱ፡፡ በአክአብ ቤተ መንግሥት ውስጥ ግን አብድዩ የተባለ ልብ ያለው ባለሟል ነበር፡፡ ንጉሡን ከጥፋቱ ማዳን ቢያቅተው በንጉሡ ስሕተት ባለመስማማቱ 100 ነቢያትን በሁለት ዋሻ ውስጥ ደብቆ የቤተ መንግሥቱን ምግብ እየመገበ ከአክዓብ ጥፋት አድኗቸው ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ነቢያት የእሥራኤል የዕውቀትና የእምነት መሪዎች ናቸው፡፡ የእሥራኤል ባህል፣ ታሪክ፣ ትውፊትና ዕውቀት የሚተላለፈው በነቢያት ትውፊት ነበርና፡፡ ነቢያቱን ማጥፋትም ሀገሪቱን ያለ ታሪክ፣ ዕውቀት፣ ባህል፣ ሥርዓትና ቅርስ ማስቀረት ነበር፡፡ ለዚህ ነው አብድዩ የንጉሡን ዐዋጅ ማስቀየር ቢያቅተው ነቢያቱን ደብቆ እየመገበ ሀገሪቱን ከከባድ ጥፋት የታደጋት፡፡ 

Monday, September 7, 2015

3ኛው የበጎ ሰው ሽልማት ተካሄደ

click here for pdf
የምርጫ ሂደቱ ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ ሲከናወን የቆየው የበጎ ሰው ሽልማት ለሦስተኛ ጊዜ ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓም በአኩስም ሆቴል ተከናወነ፡፡ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ተሸላሚዎች፣ የተሸላሚ ቤተሰቦች፣ ዕጩዎች፣ የክብር እንግዶችና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት በተገኙበት ተከናውኗል፡፡ በዕለቱ ለዕጩዎች የዕጩነት የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ለአሸናፊዎች ደግሞ የክብር ሽልማት ተበርክቷል፡፡
ከቀረቡት ዕጩዎች መካከል በዳኞች የተመረጡት የዚህ ዓመት የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊዎች የተመረጡባቸው ዋነኛ መሥፈርቶች ሦስት ሲሆኑ እነርሱም በዘመናቸው ካገኙት ዕድል በመነሣት በሞያቸው የተጓዙበት ርቀት፤ አርአያ በመሆን ወይም ፈር በመቅደድ፣ ወይም ችግርን በመፍታት ወይም ደግሞ አዲስ መንገድ በመቀየስ፣ ወይም በጎ ተጽዕኖ በማሳረፍ ወይም ሌሎችን በማፍራት ያበረከቱት አስተዋጽዖ፤ እና ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ያላቸው አበርክቶ የሚሉት ናቸው፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ ሌሎች ዝርዝር መመዘኛዎች ታይተዋል፡፡ 

Tuesday, September 1, 2015

የበጎ ሰው ሽልማት ፕሮግራም አዳራሽ ተቀየረ
ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓም በካፒታል ሆቴል ሊደረግ የነበረው የበጎ ሰው ሽልማት ፕሮግራም በቦታ መደራረብ ምክንያት ወደ አኩስም ሆቴል ተዛውሯል፡፡ ለተፈጠረው ነገር ይቅርታ እየጠየቅን መልእክቱን ለማስተላለፍ ትብብራችሁን እንጠይቃለን፡፡ ሰዓቱ አልተለወጠም፡፡