Saturday, August 8, 2015

ራስ ዓምዱ፡- ከየመን እስከ አትሮንሰ ማርያም


በኢትዮጵያ ታሪክ ከሌላ ሀገር መጥተው እዚህ ሀገራችን ውስጥ ኖረው፤ ወልደውና ከብደው፣ ሁሉንም ነገሯን ወርሰው፣ ሀገሬው የሚደርስበት ደረጃ ደርሰው፣ ሀገር እንደሆነው ሆነው፣ ታሪክ የሠሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ዛሬ ዛሬ ጠባብነት በአያሌው አጥቅቶናል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎቻችንም አብረውን የኖሩትን፤ ነገር ግን በባሕል፣ በእምነትና ቋንቋ ከእኛ የሚለዩትን እንደ እንግዳ ፍጡር ማየት ቃጥቶናል፡፡ ከአንድ አካባቢ የመጣ ኢትዮጵያዊ በሌላ አካባቢ ባዕድነት ሲሰማው፣ ይህቺ ሀገር እንዲህ ሆና ተፈጥራ እንዲህ ሆና የኖረቺ ትመስለዋለች፡፡ ግን እንዲህ አልነበረቺም፣ እንዲህም አይደለቺም፣ እንዲህም አትኖርም፡፡

እንዲህ እንዳልነበረቺ ከሚያሳዩን ታሪኮቻችን አንዱ የራስ ዓምዱ ታሪክ ነው፡፡

በዛግዌ ሥርወ መንግሥት ጊዜ ከየመን፣ ከዮሴፍ ነገድ የሆነ ስሙም በነገዱ ስም ዮሴፍ የተባለ አንድ ኦይሁዳዊ ሰው ወደ አምሐራ ሀገር እላወዝ ወደሚባል ቦታ መጣ፡፡ ይህ ሰው እጅግ የተከበረና በጣምም ባዕለ ጸጋ ነበረ ይለናል በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም የሚገኝ አንድ መጽሐፍ(EMML no. 1768, fol. 88r,)፡፡ እርሱም በዚያ ሀገር መኖር ጀመረ፡፡ አምባ ናድንም ወለደ፣ አምባ ናድም ጎጃም ሰገድን፣ ጎጃም ሰገድም አምኃ ጽዮንን፣ አምኃ ጽዮንም ተስፋ ጽዮንን፣ ተስፋ ጽዮንም ገላውዴዎስን፣ ገላውዴዎስም ራስ ዓምዱን ወለደ ይለናል፡፡ ይኼ መሠረቱን ከቤተ አይሁድ (የመን) ያደረገ ቤተሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በፖለቲካና በወታደራዊ መስክ ወሳኝ ሚና ሲጫወት ነው የኖረው፡፡ በከታታ፣ በወጅ፣ በፈጠጋርና በትግራይ የዚህ ቤተሰቦች ትውልዶች ታላላቅ መሪዎችን አፍርቷል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎችም ራሳቸውን ከዚህ ቤተሰብ ጋር አያይዘው ትውልድ የሚቆጥሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህቺ ሀገር እንደ ዘሐ ዘጊ የተያያዘቺ አይደለች፡፡ እንዲያውም ይኩኖ አምላክ የዛግዌን መንግሥት እንዲያሸንፍ የረዱትና በኋላም ‹ሰሎሞናዊ› የሚለው ፖለቲካዊ ሽፋን በሰፊው ተሠራጭቶ ቦታ እንዲያገኝ ያደረገው ይኼው ቤተሰብ ነው ይባላል፡፡   


ራስ ዓምዱ አስተዳደጉ አስገራሚ መሆኑን የኅዳር 3 ቀን ስንክሳር ይተርክልናል፡፡ ወላጆቹ የዘመኑን ትምህርት አስተምረው በሚገባ ነው ያሳደጉት፡፡ የታወቀውን የኃላፊነት ቦታ የጀመረው በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ነው፡፡ በዘርዐ ያዕቆብ ዘመን የፈጠጋር መልከኛ ሆኖ ተሾሞ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላም በሹመት ላይ ሹመት እየጨመረ ከንጉሡ በታች ዋነኛውን ከፍተኛ ሥልጣን ራስነትን ደርሶበት ነበር፡፡ ስንክሳሩ ‹‹ውእቱኒ ነበረ በሢመት እም ዘርዐ ያዕቆብ እስከ እስክንድር ኢተሥዕረ -እርሱም ከዘርዐ ያዕቆብ እስከ እስክንድር ዘመን ድረስ ሳይሻር በሹመት ላይ ነበር›› ይላል፡፡ በዘርዐ ያዕቆብ፣ በበዕደ ማርያምና በእስክንድር ዘመንም ዋናው የጦር አዛዥ ነበር (EMML no. 5665, fol. 81r)፡፡
ራስ ዓምደ ሚካኤል ለድኾች የሚራራ፣ በፍርዱ ትክክለኛነት የታወቀ፣ ለእምነቱ ቀናዒ ነበር፡፡ እርሱ ማንንም አይጠላም፡፡ ነገር ግን የሚጠሉት ብዙዎች ነበሩ ይባላል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ የእርሱን ያህል ተሰሚና ተፈሪ ሰው አልነበረም፡፡ ሁን ያለው ይሆናል፡፡ ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ በኋላ በዕደ ማርያም እንዲነግሥ ወሳኙን ሚና የተጫወተው ራስ ዓምደ ሚካኤል ነበር፡፡ በዕደ ማርያም ሲያርፍ ልጁ እስክንድርና ራስ ዓምደ ሚካኤል በጦር ግንባር ላይ ነበሩ፡፡ ራስ ዓምደ ሚካኤል ሲመለስ ናዖድን በመንግሥቱ ላይ አገኘው፡፡ ነገር ግን መንግሥቱ ለእስክንድር ይገባዋል ብሎ ስላመነ ዐፄ ናዖድን አወረደና እስክንድርን አነገሠው(1471)፡፡ እስክንድር ኅዳር 12 ቀን 1487 ዓም ሲያርፍ ራስ ዓምደ ሚካኤል አሁንም ጦር ግንባር ነበረ፡፡ ሲመለስ አሁንም ናዖድን በመንበር ላይ አገኘው፡፡ ነገር ግን መንግሥት የሚገባው ለእስክንድር ልጅ ለዓምደ ጽዮን ነው ብሎ በማመን ናዖድን አወረደና በመንበሩ ዓምደ ጽዮን ሁለተኛን በልጅነቱ ዙፋን ላይ አስቀመጠው( ከግንቦት 13/1487-1488)፡፡ ዓምደ ጽዮን 2ኛ በወራት ጊዜ ውስጥ በማረፉ የተነሣ ሥልጣኑን ለመውረስ ትልቅ ሽኩቻ ተፈጠረ፡፡

ራስ ዓምደ ሚካኤል አያሌ አብያተ ክርስቲያናትን አሠርቷል፡፡ ራሱ እንደተማረው ሁሉ ልጆቹንም በዘመኑ ዕውቀት በሚገባ አስተምሯቸዋል፡፡ እንዲያውም መብዐ ጽዮን የተባለው የራስ ዓምዱ ልጅ በዐፄ ልብነ ድንግል ዘመን(1500-1533) ሃይማኖተ አበውን ከዓረብኛ ወደ ግእዝ ተርጉሞታል፡፡ ቤተሰቡ በየመን እያለ ያውቀው የነበረውን ዓረብኛ አላጠፋውም ማለት ነው፡፡ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ጥንት የዓረብኛ ቋንቋ ትምህርት እንዲሰጥ አንዱን አስተዋጽዖ ያደረገውም ይኼ ቤተሰብ ነበር፡፡
ራስ ዓምዱ ከእስክንድር ዘመን መጨረሻ አንሥቶ ጠላቶቹ በርትተውበታል፡፡ የቤተ መንግሥቱ ሽኩቻ መበርታትም ለጠላቶቹ ሁነኛ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል፡፡ እንዴት እንዳረፈ የሚነግሩን መረጃዎች ጥርት ያሉ አይደሉም፡፡ የደብረ ሊባኖስ አካባቢ መረጃዎች የተገደለው በንጉሥ እስክንድር መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ንጉሥ እስክንድር ራስ ዓምዱን በሐሰት የከሰሱትን ሰዎች ክስ ሰምቶ አጋዘው፡፡ በዚያ በግዞት እያለም ይጠሉት የነበሩት ሰዎች እውነቱ ታውቆ ከተመለሰ አያተርፈንም ብለው በድብቅ አስገደሉት፡፡ በኋላ ንጉሥ እስክንድር ክሱ ሐሰት እንደነበር ሲሰማ አዘነ፡፡ ደብረ ሊባኖስም መጥቶ ከእጨጌ መርሐ ክርስቶስ ዘንድ ተናዘዘ፡፡ ዐጽሙንም አምጥቶ ደብረ ሊባኖስ አስቀበረው፡፡ 

እስክንድር አስገድሎታል በመባሉ ራስ ዓምዱን የሚወደው ሕዝብ በንጉሡ ላይ ተነሣበት፡፡ እርሱም ሸዋን ትቶ ምሥራቅ ጎጃም መነነ፡፡ እዚያ እያለም በሰው እጅ ተገደለ ይላል(EMML 5403, 43r–44v)፡፡

ሌላው መረጃ ደግሞ በተደጋጋሚ እንዳይነግሥ የተከላከለው ዐፄ ናዖድ በበቀል ራስ ዓምዱን አስገድሎታል የሚለው ነው፡፡ ዐፄ ናዖድ ራስ ዓምዱን ከነ ሕይወቱ አስቀብሮ በላዩ ላይ በቅሎ፣ ላም በግ፣ ግመልና አህያ ነድቶበታል፡፡(EMML  1610,  12v, EMML  6536, 37v) መጀመሪያ በደብረ ሊባኖስ ተቀብሮ ነበር፡፡ ነገር ግን የዘወትር ተቀናቃኙ እቴጌ እሌኒ የራስ ዓምዱን ዐጽም ከዚያ አስወጥታ ሌላ ቦታ እንዲቀበር አድርጋ ነበር፡፡ በኋላ ግን ልብነ ድንግል ሲነግሥ በነገሥታት ወግ ራስ ዓምዱን በአትሮንሰ ማርያም አስቀበረው(I. Guidi, Le Synaxaire Ethiopien(mois de Sene),697)፡፡

ራስ ዓምዱ በምሥራቅ በኩል እያየለ የመጣውን የአዳል ጦር ከፈጠጋር እየተወረወረ በመመከት ተወዳዳሪ አልነበረውም፡፡ አዳሎች እየበረቱ የመጡት ከራስ ዓምዱ መሞት በኋላ ነው ብሎ ሕዝቡ አምኖ ነበር፡፡ ስንክሳሩም የእርሱን ሞት ሲሰሙ የአዳል ተዋጊዎች ደስ አላቸው፡፡ ከእንግዲህ የሚመክተን የለም አሉ ይላል፡፡ በተለይም በልብነ ድንግል ዘመን የምሥራቁ ግንባር ሲፈታ ሕዝቡ የራስ ዓምዱ ግፍ ነው ይል ነበር፡፡ ልብነ ድንግል በክብር እንዲያስቀብረው ያደረገው ይሄ የሕዝቡ ግፊት ነው፡፡ ለልጁ ለዐሥራተ ማርያምም ጉልት በመስጠት የቀድሞ ነገሥታትን በደል ለማስተሥረይ ሞክሯል፡፡ ሕዝቡ የፈራውም አልቀረም፡፡

ለሥልጣናቸው ብለው በራስ ዓምዱ ላይ ሤራ የሠሩት ሰዎች ሀገሪቱን ሰው አሳጥተው የምሥራቁ ግንባር ተፈታና በ1521 ንጉሡን ድል አድርጎ ወደ መካከል ገባ፡፡ ሀገሪቱም አይታው የማታውቀው ውድመት ውስጥ ገባች፡፡ ከራስ ዓምዱ ሞት በኋላ ሀገሪቱ በመመሰቃቀሏ ሕዝቡ በተለያየ መንገድ ቁጭቱን ገልጧል፡፡ መቼ እንደተገጠመለት ባላውቅም በደብረ ሊባኖስ ትውፊት

ትናንት እንደዋዛ ዓምዱን ሰብረውት
ፈረሰ ይሉናል አገር እንደቤት
የተባለው ለእርሱ መሆኑ ይነገራል፡፡ ታሪኩ በስንክሳር ተጽፏል፡፡ ፍልሰተ ዐጽሙም እንዲሁ(ሰኔ 23 ቀን)፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ብላዋለች፡፡ ሃይማኖተ አበው በተተረጎመ ቁጥርም ታሪኩ ይታወሳል፡፡ ቤተሰቡ ከየመን መጥቶ፣ ከዚህቺ ሀገር ደም ጋር ተዋሕዶ፡፡ ተባዝቶ ተራብቶ በየጎጡ ገብቶ፤ ዓምደ ሚካኤልን(ዓምዱን) ያህል ሰው አፍርቶ፤ እርሱም ንጉሥ አንጋሽ ድንበር ጠባቂ ሆኖ፡፡ ትልቁን መዓርግ ራስነትን ተቀዳጅቶ፡፡ እንደ ሀገሪቱ ጠባይ ኖሮ እንደ ሀገሪቱ ጠባይ ሞተ፡፡ 

የኢትዮጵያውያንን ክብር አግኝቶ፣ የኢትዮጵያውያንን ሞት ሞተ፡፡ በአኗኗሩ ብቻ ሳይሆን በአሟሟቱም ሁላችንንም መሰለ፡፡

ኢትዮጵያ እንዲህ ናት፡፡ ከየአቅጣጫው የመጡ ብዙ ዓይነት ሕዝቦች፣ ከየቦታው መርጠዋት የገቡ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች በመኖር ብቻ ሳይሆን በመሞትም የሠሯት፡፡ እንኳን ለራሷ ሰዎች ለሌሎቹም መኖሪያና መሞቻ የነበረች፡፡ አሁን የምናየው ሌላውን ወገን በባዕድ ዓይን የማየቱ አባዜ ይህንን ታሪክ እየዘነጋ እንዲጎመራ ከፈቀድንለት ደጃዝማች ዶክተር ዘውዴ ገብረ ሥላሴ እንዳሉት ‹‹ኢትዮጵያ ራስ የሸከም አንገት፣ ባለቤት የማይስገባ ቤት›› ትሆንብናለች፡፡


19 comments:

 1. ትናንት እንደዋዛ ዓምዱን ሰብረውት
  ፈረሰ ይሉናል አገር እንደቤት

  ReplyDelete
 2. lega malkam tafk egezabher amlk ytabekh eza ethiopiawian ababem melekach yhuleu zare magaza sanayaw gatachenn madahanitachinn yesses crestosen ytakabekem Israel the nebs tblen ymentaraw eza mhunachenn merst endalelaben bzer bnged mkafafl indllaben wlachinm Ethiopian ygara ageratchen mhonwan awken ymkafaflenn lebanachw endmleslachw atbekan ensaly egezabher ydingl maryamen yasrat agare ayresatem mherat ydarglnal atbken ensaly amen!!

  ReplyDelete
 3. ትንሽ ታሪኩ ደብለቅ ደብለቅለቅ ያለ ይመስላል፡፡ ሲጀመር ሰውዬው ለምን እንደመጣ ቢታወቅ ጥሩ ነበር፡፡ዮሴፍ ከሆነ መጀመሪያ የመጣው ስለዮሴፍ ማውራት ከራስ ዓምዱ በተሻለ ለማስተላለፍ የተፈከገውን መልእክት ያስረዳል ብዬ ገምታለሁ(ልክ ካልገመትኩ እታረማለሁ)፡፡ በዮሴፍና በራስ ዓምዱ መካከልም ብዙ ሰዎች አሉ ከራስ ዓምዱ ይልቅ እነሱ ለዮሴፍ ይቀርባሉና ራስ ዓምዱ ባሕላችንንና ጠባዩን ቢላበስ አይደንቅም፡፡ እኔግን ይዬ ከነገደ ዮሴፍ የመጣውና ስሙም ዮሴፍ ስለተባለው ሰውዬ በቂ መረጃ ቡገኝ ደስ ይለኛል፡፡ ለማንኛውም ጉድ ሳይሰማ መስከረም አልጠባምና ስብጥራችንን ከሰማኒያ በላይ በማብዛት እጅግ ድብልቅልቆች መሆናችን ለመቻቻል እንዲጠቅመን ለማድረግ የሚደረገው ጥረት መልካም ነው፡፡ ለካ ከውጭም ሰው መጥቶ ከኛ ጋር ሲጋባ ሚወለደው ሰው ነው፡፡ ያውም እስከ መንገስ የሚደርስ፡፡ ለምንድን ነው ታዲያ እኛ የመጣሁን ሁሉ አጎዛ አንጥፈን ስንቀበል በምንሔድበት ግን ስለትና ድናጋይ የሚጠብቀን?? እንድትጽፍ ላስቻለህ ምስጋና ይግባው፡፡

  ReplyDelete
 4. ቃለ ህይወት ያሰማልን ዲያቆን ዳኒ. አቤቱ አምላካችን ሆይ ኢትዮጵያን አሰባት .የቀደሙትን አባቶች በጎ ሥራቸውን የሚያሰብ ,የሚከተል መሪ እዘዝልን አሜን !ዲያቆን ዳኒ መድሃሂያለም ይጠብቅህ አሜን!

  ReplyDelete
 5. አሁን የምናየው ሌላውን ወገን በባዕድ ዓይን የማየቱ አባዜ ይህንን ታሪክ እየዘነጋ እንዲጎመራ ከፈቀድንለት ደጃዝማች ዶክተር ዘውዴ ገብረ ሥላሴ እንዳሉት እንዳይሆን

  ReplyDelete
 6. Silte Zone in my mind! Good Job.

  ReplyDelete
 7. እርግጥ ኢትዮጵያ እንደዛሬው ሕዝቦቿን በሚያራርቅ ዘረኛ እና መንደርተኛ አስተሣሠብ ተተብትባ አታውቅም። በሀገር ውስጥ ቆለኛው ወደ ደጋ፣ ደገኛው ወደ ቆላ፣ የምስራቁ ወደ መሐል ፣ደቡብ ፣ ምዕራብ ፣ ወይም ሰሜን ፤የመሐል ፣ የሰሜን ፣ የምዕራብና የደቡቡም እንዲሁ ወደ ሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ያለ ከልካይ ተንቀሳቅሰው ነባሩ እንግዳውን ፊት ሳይነሣው ተጋብተው ተዋልደው ፣ የሌላውን ባህልና ልምድ ተጋርቶ እና አክብሮ የኖረባት፤ ከውጭ ተሳቱ ቅዱሳን ከአውሮፓ ፣ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከላኛው ግብጽ፣ቤተ እሥራኤል ከመካከለኛው ምስራቅ ፣ በርካቶች ፣ ከተለያዩ የአረብ ሀገራት ከህንድና ከአርመን መጥተው የህዝቡን ቋንቋ ተምረው ተናግረው፣ ፊደሉን አጥንተው ጽፈው ደጉሰው፣ ባህሉን ተምረው ኑረውበት ትግሬ ፣ አማራ፣ ኦሮሞ ወይም ሌሎችን ብሔረሰሰቦች በጥቅሉ ባዕድነት ሳይሰማቸው ኢትዬጵያዊ ሆነው ኑረው ኢትዬጵያዊ ሆነው አልፈዋል። ይህ ኢትዮጵያዊነት ድር እና ማግ ሆኖ እንደ ጥበብ ሸማ የተሰራበት የመቻቻል ፣ የመከባበርና እና የፍቅር አብሮነት በኢትዮጵያዊያን እንዲፈርስ ሲነቀነቅ ማየት ኢትዬጵያና ኢትዬጵያዊነትን ለሚያከብር ሁሉ ከባድ ነው። ይህን ህብረ ውበት ሊያጠፉ ባዕደን በቀደመው ዘመን ጥረዋል ነገር ግን በኢትዬጵያዊያን የአብሮነት ጽናት እና በእግዚአብሔር ቸርነት ተጠብቆ ዛሬ ላይ ደርሧል። ዛሬ ልዩነቱ ይኸንን ደማቅ ህብር ለማፍረስ የሚጥሩት ኢትዬጵያን ፣ ኢትዬጵያዊያንን እና ኢትዪጵያዊነትን ከኛ በላይ ወዳጅ የለም በሚሉ ኢትዬጵያዊያን መሆናቸው ነው። ሆኖም ኢትዬጵያዊያን ይህን ውበት ጠልተው የዚህ ጥፋት ተባባሪ ስለማይሆኑ እግዚአብሔርም ኢትዬጵያን ስለማይተዋት አረሙ አስተሳሰብ ተነቅሎ ኢትዬጵያዊነት እንደሚቀጥል ተስፋ አለኝ።

  ReplyDelete
 8. dear Dn Dani. Thanks for your details as usual. To me the message didnot much with the details. It is completely different with the current political situation in the country. Rather you are narrow from this particular article point of view. 1. Ras Amdu is Ethiopian since he is seventh generation descendant fro Yemen. 2. He was born from Ethiopian mother. So you are trying to convince us as Ras Amdu was not Ethiopian. What criterion should some body fulfill to be Ethiopian fro your side?

  ReplyDelete
 9. ለማስቃኘት የሞከርከው ታሪክ ዳን ዳንኤል ከባህር በጭልፋ የተቀዳ የጥምረታችን አንዲት ጠብታ ይሆናል፥ግን ደግሞ ስለኛ ብዙ ይናገራል። ዛሬ መንገዳችን ሁሉ ምን ያህል ከቀደሙት አበው የተቃረነ እንደሆን የሁላችንም የቤት ስራ ነው አርግጥ በፖለቲካ በሀይማኖት ይልቁንም ደግሞ በዲሞክራሲ ጭንብል ተክልለው የታሪክን ሚዛን ያዛቡ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን በሰው ዘር ላይ የዘሩ እንደነበሩ ሁሉ ዛሬም ይኖራሉ፥ይህ ሁሉ ስግብግብነት የወለደው የሰናኦር ግንብ የቅጣት ውጤት ነው ብዬ አምናለሁ ፥የስው እድሜ ሁሉ ጥንት እንደነበረው ቢሆን ኖሮ ምን ይሆን ነበር ይህ ትውልድ? ?በሀገር በወገን በመንደር በዘር ቢሰላ ምን ያህል ይኖር ነበር 'ባቢሎን 'ባቢሎናዊያን' መጥፋትሽ ይሆንንንን????

  ReplyDelete
 10. ኢትዮጵያ እማማ እዲህ ናት የሰው ፍጡር ለሆነ የማታዳላ እደፈጣሪዋ ትእዛዝ የምትኖር እናት ነበረችን ትኖርመሰለች ።ሁሉም ያልፋል ዳኒ እ/ግ ይስጥህ ይህን መልእክትህን ሳነብ እያለቀስሁ ነው የጨረስሁት በርታ እ/ግ ካተ ጋ ይሁን ሌላ ምንም ቃል የለኝም ሰዎች ከየቦታው መጠው ኢትዮጵያውያንን መስለው ኑረው ሞታቸውም እኛን መልለው ተከብረው ነው ያለፉት የዛሬው ኢትዮጵያዊ የት ነው ያለ በባህር በበረሀ እየታረደ በማንነቱ እዲያፍር አገቱን ደፍቶ እዲኖር በዘመናዊ ባርነት ተሽጦ ያለ ነውና ኢትዮጵያዊው ማንነቱን እዲያውቅ ይረዳዋልና ።እንኳን ለራሳችን ለሰው እንተርፍ ነበር እሄን አዲሱ ትውል እዲያውቅ ይጠቅማልና ።ብርታቱን ይስጥህ ቃለ ህይወት ያሰማህ ምን እላለሁ ስላተ ምንም ።ማድነቅና ከመደሰት በቀር እናት መክና እዳልቀረች ሳይ ደስታየ ወሰን የለውም ።ምን እንላለን እዳለ ሐዋርያው ግሩም ነው ።ሰላም ጤና ይስጥልኝ ።ከበላይ ነኝ።ቸር እንሰነብት።

  ReplyDelete
 11. ኢትዮጵያ በታሪክ ብዙ እንግዶችን የተቀበለች የመቻቻልና የጎጠኝነት ስሜት ያልኖረባት ለማለት ባያስደፍርም እንዲህ እንደዛሬው ያገጠጠ ያፈጠጠ በታሪክ ያማይታወቅ ጥላሽት አልነበራትም ፡፡ መማርና ማወቅ የምንመርጠው ለመሻል ሆኖ እያለ ጥፋታችንና መልካምነታችን እየጠፋብን በጎነት እየሰለቸን አላውቅበት ብለናል፡፡ እንዲያው ብናስተውል እንኳ በራስ ላይ እዲደረግብን ማንፈቅደውን ነገር በሌላው የማድረጉ ነገር እየበዛ ነው፡፡ ትንሽ ቢታሰብበትስ ስደተኞች ሁነንም የምናደርገው በኛ ለይ እንንዲደረግብን ማንፈልገውን ነው የምናደርገው ፡፡ የፍየልንና የበግን በጠጥን መለየት ለንንስ አስፈለገን ??? ብንችል ከፍብለን አዳምን ዝቅ ብለንም ሞትን ብናስብ ይህን ሁሉ ባዕድ ሐሳብ እንደማይኖረን እርግጠኛ ነኝ .... ዳኒ ለእንተም ለመልካም አቀራረብህ እግዚያብሔር ይበርክህ በርታልን እግዚያብሔር ኢትዮጵይን ይካርክ፡፡

  ReplyDelete
 12. ኢትዮጵያ በታሪክ ብዙ እንግዶችን የተቀበለች የመቻቻልና የጎጠኝነት ስሜት ያልኖረባት ለማለት ባያስደፍርም እንዲህ እንደዛሬው ያገጠጠ ያፈጠጠ በታሪክ ያማይታወቅ ጥላሽት አልነበራትም ፡፡ መማርና ማወቅ የምንመርጠው ለመሻል ሆኖ እያለ ጥፋታችንና መልካምነታችን እየጠፋብን በጎነት እየሰለቸን አላውቅበት ብለናል፡፡ እንዲያው ብናስተውል እንኳ በራስ ላይ እዲደረግብን ማንፈቅደውን ነገር በሌላው የማድረጉ ነገር እየበዛ ነው፡፡ ትንሽ ቢታሰብበትስ ስደተኞች ሁነንም የምናደርገው በኛ ለይ እንንዲደረግብን ማንፈልገውን ነው የምናደርገው ፡፡ የፍየልንና የበግን በጠጥን መለየት ለንንስ አስፈለገን ??? ብንችል ከፍብለን አዳምን ዝቅ ብለንም ሞትን ብናስብ ይህን ሁሉ ባዕድ ሐሳብ እንደማይኖረን እርግጠኛ ነኝ .... ዳኒ ለእንተም ለመልካም አቀራረብህ እግዚያብሔር ይበርክህ በርታልን እግዚያብሔር ኢትዮጵይን ይካርክ፡፡

  ReplyDelete
 13. ዝርዝር ያለ ባይሆንም..አሪፍ ቅኝት ነው

  ReplyDelete
 14. አይጋጭም ወይ?????
  እስክንድር ኅዳር 12 ቀን 1487 ዓም ሲያርፍ ራስ ዓምደ ሚካኤል አሁንም ጦር ግንባር ነበረ፡
  vs
  ንጉሥ እስክንድር ራስ ዓምዱን በሐሰት የከሰሱትን ሰዎች ክስ ሰምቶ አጋዘው፡፡በኋላ ንጉሥ እስክንድር ክሱ ሐሰት እንደነበር ሲሰማ አዘነ፡፡ ደብረ ሊባኖስም መጥቶ ከእጨጌ መርሐ ክርስቶስ ዘንድ ተናዘዘ፡፡ ዐጽሙንም አምጥቶ ደብረ ሊባኖስ አስቀበረው፡፡

  ReplyDelete
 15. I LOVE YOU MAMA Ethiopia; despite I am one who has no where to claim as my village. I was born in region different from my families region. Now I don't feel any belongingness to any region. What a stranger am I in front of today's Ethiopia? I am willing to die for my country despite every thing. I love you mama Ethiopia and you will free yourself of this generation.

  ReplyDelete
 16. እግዚያብሔር ይበርክህ በርታልን እግዚያብሔር ኢትዮጵይን ይካርክ፡፡

  ReplyDelete
 17. በዛግዌ ሥርወ መንግሥት ጊዜ ከየመን፣ ከዮሴፍ ነገድ የሆነ ስሙም በነገዱ ስም ዮሴፍ የተባለ አንድ ኦይሁዳዊ ሰው ወደ አምሐራ ሀገር እላወዝ ወደሚባል ቦታ መጣ፡፡ ይህ ሰው እጅግ የተከበረና በጣምም ባዕለ ጸጋ ነበረ ይለናል በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም የሚገኝ አንድ መጽሐፍ(EMML no. 1768, fol. 88r,)፡፡ እርሱም በዚያ ሀገር መኖር ጀመረ፡፡ አምባ ናድንም ወለደ፣ አምባ ናድም ጎጃም ሰገድን፣ ጎጃም ሰገድም አምኃ ጽዮንን፣ አምኃ ጽዮንም ተስፋ ጽዮንን፣ ተስፋ ጽዮንም ገላውዴዎስን፣ ገላውዴዎስም ራስ ዓምዱን ወለደ ይለናል፡፡ ይኼ መሠረቱን ከቤተ አይሁድ (የመን) ያደረገ ቤተሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በፖለቲካና በወታደራዊ መስክ ወሳኝ ሚና ሲጫወት ነው የኖረው፡፡
  የኔ እይታ ደግሞ አንደሚከተለው ነው፡- ከ እኔ በላይ አዋቂ እንደሆንክ ምንም ጥርጥ የለኝም እንዲያውም በአንድ ወቅት ስል leeder ship ስልጠና ሰተኀኛል፡፡ እኔ ግን በኦርቶዶክስ ሀይማኖትን ተከክ በማድርግ በሀገራችን ከፍተኛ የሆነ የታሪክ ማፈለስ አሁን ለደረስንበት ውድቀት ተጠያቂ የሚሆን የታሪክ ባለድርሾች እንዳሉ ታውቃለህ፡፡ እዚህ ላይ ከዮሴፍ ነገደ የመጣው …….ለኢትዮጵያ እና ለሀይማኖታችን ያመጡት ጥቅም ምንም አይታየኝም እዚህ ላይ ልትመልስልኝ ትችላለህ የፍቅሬ ቶሎሳ መፅሀፍን አንብብ!!! እንዲሁም ሌሎችን መጽሀፍ በደንብ ስለምታነብ እውነታውን ታውቀዋለህ፡፡የማንነት ቀውስ ውስጥ ነው የከተቱን አኩሪ ታሪካችንን በነሱ በረዙብን ገና ለገና የአይሁድ ደም አለብን ዕያሉ በገራችን ከፍተኛ የሆነ የርስ በርስ ጦርነት እየከተቱን እና ገናና የነበረውን አኩሪ ታሪካችን ላይ አሉታዊ ሚና የተጫወቱት የግብጽ ኦርቶዶክስ እና ዓይሁዳውያን እንደሆኑ በደንብ ታውቀዋለህ፡፡ታዲያ በዚህ ሁኔታ ላይ እንዴት ነው ጠቀመሙን የምነለው ሐይማኖት አስፋፉ ከተባለ የትኛውን ሐይማኖት እንዲውም በተቃራኒ ካልሆነ…..ብቻ በየዋህነት ብዙ ነገር አታንል መጫውቻ እና መሳለቂያ እንድንሆን አደረገውናል፡፡ በጣም አከብርሃለሁ ግን ይህ ሰው ከየመን ወደ ኢትዮፕያ የመጣው ሀይማኖትን ለማስፋፈት ሳይሆን ድብቅ የአይሁድ አጀንዳውን ለማዳበል እና ለማቆርቆዝ ነው……

  ReplyDelete
 18. በዛግዌ ሥርወ መንግሥት ጊዜ ከየመን፣ ከዮሴፍ ነገድ የሆነ ስሙም በነገዱ ስም ዮሴፍ የተባለ አንድ ኦይሁዳዊ ሰው ወደ አምሐራ ሀገር እላወዝ ወደሚባል ቦታ መጣ፡፡ ይህ ሰው እጅግ የተከበረና በጣምም ባዕለ ጸጋ ነበረ ይለናል በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም የሚገኝ አንድ መጽሐፍ(EMML no. 1768, fol. 88r,)፡፡ እርሱም በዚያ ሀገር መኖር ጀመረ፡፡ አምባ ናድንም ወለደ፣ አምባ ናድም ጎጃም ሰገድን፣ ጎጃም ሰገድም አምኃ ጽዮንን፣ አምኃ ጽዮንም ተስፋ ጽዮንን፣ ተስፋ ጽዮንም ገላውዴዎስን፣ ገላውዴዎስም ራስ ዓምዱን ወለደ ይለናል፡፡ ይኼ መሠረቱን ከቤተ አይሁድ (የመን) ያደረገ ቤተሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በፖለቲካና በወታደራዊ መስክ ወሳኝ ሚና ሲጫወት ነው የኖረው፡፡

  የኔ እይታ ደግሞ አንደሚከተለው ነው፡- ከ እኔ በላይ አዋቂ እንደሆንክ ምንም ጥርጥ የለኝም እንዲያውም በአንድ ወቅት ስል leeder ship ስልጠና ሰተኀኛል፡፡ እኔ ግን በኦርቶዶክስ ሀይማኖትን ተከክ በማድርግ በሀገራችን ከፍተኛ የሆነ የታሪክ ማፈለስ አሁን ለደረስንበት ውድቀት ተጠያቂ የሚሆን የታሪክ ባለድርሾች እንዳሉ ታውቃለህ፡፡ እዚህ ላይ ከዮሴፍ ነገደ የመጣው …….ለኢትዮጵያ እና ለሀይማኖታችን ያመጡት ጥቅም ምንም አይታየኝም እዚህ ላይ ልትመልስልኝ ትችላለህ የፍቅሬ ቶሎሳ መፅሀፍን አንብብ!!! እንዲሁም ሌሎችን መጽሀፍ በደንብ ስለምታነብ እውነታውን ታውቀዋለህ፡፡የማንነት ቀውስ ውስጥ ነው የከተቱን አኩሪ ታሪካችንን በነሱ በረዙብን ገና ለገና የአይሁድ ደም አለብን ዕያሉ በገራችን ከፍተኛ የሆነ የርስ በርስ ጦርነት እየከተቱን እና ገናና የነበረውን አኩሪ ታሪካችን ላይ አሉታዊ ሚና የተጫወቱት የግብጽ ኦርቶዶክስ እና ዓይሁዳውያን እንደሆኑ በደንብ ታውቀዋለህ፡፡ታዲያ በዚህ ሁኔታ ላይ እንዴት ነው ጠቀመሙን የምነለው ሐይማኖት አስፋፉ ከተባለ የትኛውን ሐይማኖት እንዲውም በተቃራኒ ካልሆነ…..ብቻ በየዋህነት ብዙ ነገር አታንል መጫውቻ እና መሳለቂያ እንድንሆን አደረገውናል፡፡ በጣም አከብርሃለሁ ግን ይህ ሰው ከየመን ወደ ኢትዮፕያ የመጣው ሀይማኖትን ለማስፋፈት ሳይሆን ድብቅ የአይሁድ አጀንዳውን ለማዳበል እና ለማቆርቆዝ ነው……

  ReplyDelete