በኢትዮጵያ ታሪክ ከሌላ ሀገር መጥተው
እዚህ ሀገራችን ውስጥ ኖረው፤ ወልደውና ከብደው፣ ሁሉንም ነገሯን ወርሰው፣ ሀገሬው የሚደርስበት ደረጃ ደርሰው፣ ሀገር እንደሆነው
ሆነው፣ ታሪክ የሠሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ዛሬ ዛሬ ጠባብነት በአያሌው አጥቅቶናል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎቻችንም አብረውን የኖሩትን፤
ነገር ግን በባሕል፣ በእምነትና ቋንቋ ከእኛ የሚለዩትን እንደ እንግዳ ፍጡር ማየት ቃጥቶናል፡፡ ከአንድ አካባቢ የመጣ ኢትዮጵያዊ
በሌላ አካባቢ ባዕድነት ሲሰማው፣ ይህቺ ሀገር እንዲህ ሆና ተፈጥራ እንዲህ ሆና የኖረቺ ትመስለዋለች፡፡ ግን እንዲህ አልነበረቺም፣
እንዲህም አይደለቺም፣ እንዲህም አትኖርም፡፡
እንዲህ እንዳልነበረቺ ከሚያሳዩን
ታሪኮቻችን አንዱ የራስ ዓምዱ ታሪክ ነው፡፡
በዛግዌ ሥርወ መንግሥት ጊዜ ከየመን፣
ከዮሴፍ ነገድ የሆነ ስሙም በነገዱ ስም ዮሴፍ የተባለ አንድ ኦይሁዳዊ ሰው ወደ አምሐራ ሀገር እላወዝ ወደሚባል ቦታ መጣ፡፡ ይህ
ሰው እጅግ የተከበረና በጣምም ባዕለ ጸጋ ነበረ ይለናል በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም የሚገኝ አንድ መጽሐፍ(EMML no. 1768, fol. 88r,)፡፡ እርሱም በዚያ ሀገር መኖር ጀመረ፡፡ አምባ ናድንም ወለደ፣ አምባ ናድም ጎጃም ሰገድን፣ ጎጃም ሰገድም
አምኃ ጽዮንን፣ አምኃ ጽዮንም ተስፋ ጽዮንን፣ ተስፋ ጽዮንም ገላውዴዎስን፣ ገላውዴዎስም ራስ ዓምዱን ወለደ ይለናል፡፡ ይኼ መሠረቱን
ከቤተ አይሁድ (የመን) ያደረገ ቤተሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በፖለቲካና በወታደራዊ መስክ ወሳኝ ሚና ሲጫወት ነው የኖረው፡፡
በከታታ፣ በወጅ፣ በፈጠጋርና በትግራይ የዚህ ቤተሰቦች ትውልዶች ታላላቅ መሪዎችን አፍርቷል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎችም ራሳቸውን ከዚህ
ቤተሰብ ጋር አያይዘው ትውልድ የሚቆጥሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህቺ ሀገር እንደ ዘሐ ዘጊ የተያያዘቺ አይደለች፡፡ እንዲያውም ይኩኖ
አምላክ የዛግዌን መንግሥት እንዲያሸንፍ የረዱትና በኋላም ‹ሰሎሞናዊ› የሚለው ፖለቲካዊ ሽፋን በሰፊው ተሠራጭቶ ቦታ እንዲያገኝ
ያደረገው ይኼው ቤተሰብ ነው ይባላል፡፡