Thursday, July 30, 2015

ዝርዝርና ጥቅልል

ወንዶችንና ሴቶችን በተመለከተ ከተጻፉ መጻሕፍት መካከል ከርእሱ ጀምሮ የሚገርመኝ አንድ መጽሐፈ አለ፡፡ ‹‹why Men Don’t have a clue & Women always need more shoes›› ይላል፡፡ ባልና ሚስቱ የመጽሐፉ ደራስያን አላንና ባርባራ ፔዝ የወንዶችንና የሴቶችን ግንኙነት ጤናማና ሰላማዊ ለማድረግ አንዱ ዋናው መንገድ ሁለቱ በነገሮች ላይ ያላቸውን ልዩነት ጠንቅቆ ማወቅና በዚያ ላይ ግንኙነትን መመሥረት ነው ይላሉ፡፡ 
በመጽሐፉ ውስጥ ካነሷቸው አስገራሚ የወንዶችና ሴቶች የአነዋወርና አስተሳሰብ ልዩነቶች መካከል አንዱ ነገሮችን የሚያዩበት መንገድ ነው፡፡ ሴቶች ነገሮችን በዝርዝርና አበጥረው የማየት አዝማሚያና ተሰጥዖ አላቸው ይላሉ፡፡ ለምን? እንዴት? የት? ከዚያስ? እያሉ ነገሮችን ይፈተፍቷቸዋል፡፡ ወንዶቹ ‹ዝርዝር ኪስ ይቀዳል› በሚለው የአራዶች መመሪያ ተመርተው ነው መሰል ነገርን በጥልቁና በዝርዝሩ ከማየት ይልቅ ጠቅላላውን ነገር ስለሚመርጡ ስለ አንድ ጉዳይ በዝርዝር ሲጠየቁ ቁጥጥር የተደረገባቸው፣ ምርመራ የተካሄደባቸውና አለመታመን የተፈጠረባቸው መስሏቸው ቁጣ ይቀድማቸዋል፡፡ ነገሩ የመጣው ጉዳዮችን በዝርዝር በሚያየው የሴቶች ልቡናና ነገሮችን መጠቅለል በሚወደው የወንዶች ልቡና መካከል በተፈጠረ ልዩነት ነው፡፡ 

እዚህ ላይ እንዲያውም አንድ ምሳሌ ያነሳሉ፡፡ በአንድ ግብዣ ላይ ወንዶችና ሴቶች በየጠረጲዛቸው ከብበው ሲጫወቱ ብታዩ ሴቶቹ ጋ ብዙ ማኅበራዊ፣ ቤታዊ፣ ልጃዊና ትዳራዊ ጉዳዮች እየተነሡ ሲበለቱና ሲተነተኑ ትሰማላችሁ፡፡ የማይተዋወቁት ሴቶች ከመተዋወቅ አልፈው የቤታቸውን ጓዳ ገላልጠው ሲወያዩበትና ሲማማሩበት ትመለከታላችሁ፡፡ ሴቶቹ ከስም አልፈው  መቼ እንዳገቡ፣ ስንት ልጆች እንዳሏቸው፣ የት እንደሚኖሩና ምን እንደሚሠሩ፣ ሌላው ቀርቶ የቤት ሠራተኞቻቸውን ጉዳይ ሳይቀር ተነጋገረዋል፡፡ ወዲያኛው ጠረጲዛ ያሉትን ከአንድ ሰዓት ጨዋታቸው በኋላ ብታዩዋቸው ግን እንደዚያ እየተሳሳቁና ድምጻቸውን ሞቅ አድርገው እየተጫወቱ የነበሩት ወንዶች፣ እንኳን የልጆቻቸውን ቁጥር የራሳቸውን ስም እንኳን እርስ በርስ ላይተዋወቁ ይችላሉ፡፡ ማነው? የት ነው የሚኖረው? ትዳር አለው ወይ? ትዳሩስ እንዴት ነው? የሚለው ፈጽሞ ላይነሣ ይችላል፡፡ ምናልባትም ስለ ስፖርት፣ ፖለቲካ ወይም ደግሞ ስለ ሰሞኑ የከተማው ወሬ እየተወራ ይሆናል፡፡ 
ሴቶቹና ወንዶቹ ከግብዣው በኋላ ወደየቤታቸው ሲሄዱ ‹እንትናኮ እንዲህ አለችኝ›› ትለዋለች ሚስቱ፡፡ ‹‹የቷ ናት እንትና›› ይላል እርሱም፡፡ ‹‹የእንትና ባለቤት›› ትልና አብሮት ሲጫወት የነበረውን ሰው ስም ትነግረዋለች፡፡ ሴቶቹ ስለ ራሳቸው ብቻ ሳይሆን የባሎቻቸውንም ማንነት ተዋውቀዋላ፡፡ ‹‹የቱ ነው እንትና›› ይላል፡፡እርሱ እቴ አብሮ ተጫወተ እንጂ ስሙን አያውቀው፡፡ ‹‹የትኛው ነበረ ባክሽ›› ከዚህ በኋላ ማስታወሱ መከራ ነው፣ ይላሉ አላንና ባርባራ ፔዝ፡፡
‹አንዴ› ይላሉ ደራሲዎቹ ‹ዩልያንና ሐና የሚባሉ ባልና ሚስት ነበሩ፡፡ የባልየው የድሮ ጓደኛ ራልፍ ከዓመታት በኋላ መጣና ጎልፍ ሜዳ ሊገናኙ ከዩልያን ጋር ተቃጠሩ፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲጫወቱ ውለው ዩልያን ወደ ቤቱ ሲመለስ የጠፋው የባሏ ጓደኛ ከብዙ ጊዜ በኋላ በመምጣቱ የገረማት ሚስት ‹‹ቀኑ እንዴት ነበር›› አለቺው ባሏን፡፡
‹‹አሪፍ ነበር›› አለ ዩልያንም፡፡
‹‹ራልፍስ ደኅና ነው››
‹‹ደኅና ነው››
‹‹ባለቤቱ ከሆስፒታል ከወጣች በኋላ እንዴት ናት›› አለቺው
‹‹አልጠየቅኩትም- እርሱም ምን ነገር አልነገረኝም›› አለ ዩልያን፡፡
‹‹አልነገረኝም? አንተም አልጠየቅከውም?››
‹‹አልጠየቅኩትም፡፡ ግን አንዳች ነገር ብትሆን ኖሮ ይነግረኝ ነበር››
‹‹ልጃቸውስ፣ ከአዲሱ ባሏ ጋር ተስማማች››
‹‹ምንም ነገር አላለኝም፡፡
‹‹የራልፍ እናት አሁንም ኬሞቴራፒውን እየወሰዱ ነው፤ ለመሆኑ የተለየ ነገር አለ?››
‹‹እኔ እንጃ››
‹‹ታድያ ቀኑን ሙሉ ምን ስታወሩ ነው የዋላችሁት?››
‹‹ጎልፍ ተጫወትን፣ ስንቀልድ ነበር፤ ሌሎች ጓደኞቻችንን መጡ፣ በቃ ስንጫወት ዋልን››
ይኼ ጉዳይ በሁለቱ ጓደኛሞች መካከል ብቻ አይደለም የሚፈጠረው፡፡ በባልና ሚስቱም መካከል ጭምር እንጂ፡፡ ሚስቶቹ ነገሮችን በዝርዝርና አንድ በአንድ መነጋገር፣ ማወቅና መረዳት ይፈልጋሉ፡፡ ባሎቹ ደግሞ ስለ ጉዳዩ ከሰሙ በቂያቸው ነው፡፡ አንድ ሰው እንዲያውም ‹ወንዶች ሟች ማን እንደሆነ ሳያውቁ ልቅሶ መድረስ ይችላሉ›› ብሏል፡፡ እዚያ ልቅሶ ቤትም ሄደውም ካርታ መጫወት፣ የሰሙኑን ፖለቲካና የስፖርት ወሬዎችን መሰለቅ ካልሆነ በቀር ለቀስተኞችን ቀርበው ላይጠይቋቸው፣ ምን ሆኖ ሞተ? ሕክምና ወስዶ ነበር ወይ? ከዚህ በፊት ታምሞ ነበር ወይ? ላይሉም ይችላሉ፡፡
ወንዶቹ ነገሮችን ጠቅልሎ የማየት አዝማሚያ አላቸው፡፡ ለወንዶች ወጡ ወጥ ነው፡፡ አንድ ድስት ወጥ፡፡ ለሴቶቹ ግን ወጡ ብዙ ነገር ነው፡፡ ሽንኩርት፣ ቅመም፣ ዘይት፣ እህል፣ እሳት፣ ድስት፣ ማማሰያ፣ ሞያ ነው፡፡ ወንዶቹ ‹‹ወጡ አይጣፍጥም›› ነው የሚሉት፡፡ ሴቶቹ ግን ‹ጨው አንሶታል፣ ሽንኩርቱ በደንብ አልተቁላላም፣ ቅመም በዝቷል፣ በርበሬው አርሯል›› ብለው ይተነትኑታል፡፡ ለወንዶች ዋናው ድምር ውጤቱ ነው፤ ለሴቶች ግን ዋናው ድምሩን ያመጡት ቅንጣቶች ናቸው፡፡ 
አለንና ባርባራ ይኸ ጉዳይ ለምን መጣ? ለሚለው ጥያቄ የሚያቀርቡት አንዱ ምክንያት የሰው ልጅ አነዋወሩን ቀየረ እንጂ የማሰቢያ ንጥረ ነገሩን አልቀየረም የሚለውን ነው፡፡ ሰው በምድር ላይ ኑሮ ሲጀምር የመጀመሪያ ሥራው አደን ነበር፡፡ ወንዶቹ ሊያድኑ ይወጣሉ፡፡ ሴቶቹ ልጆቻቸውን ይዘው ቤት ይሆናሉ፡፡ የሰው ልጅ የማሰቢያ መንገድ የተቀረጸው ያኔ ነው፡፡ አሁንም በአደን መንገድ ነው እያሰበ የሚኖረው ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ወንዶች አንድ ቦታ ሰብሰብ ብለው፣ ነገር ግን ሁሉም ዝም ብለው በየራሳቸው ዓለም ሲጓዙ ታዩ ይሆናል፡፡ በዚያው ወቅት ግን ሴቶቹ አንድ አካባቢ የቀለጠ ወሬ ይዘዋል፡፡ ነገሩ የተፈጠረው ወንዶች ዝምተኛ ሴቶች ደግሞ ወሬኞች ስለሆኑ አይደለም፡፡
በአደን ዘመን ወንዶቹ ለአደን ይወጣሉ፡፡ ግዳይ እስኪያገኙ ድረስ ወጥመዳቸውን አጥምደው አለያም ደግሞ መሣሪያቸውን አነጣጥረው ይጠብቃሉ፤ ይሸምቃሉ፣ያደባሉ፡፡ አደን አንድ ከፍተኛ ክሂሎት ይጠይቃል፤ በግዳዩ ላይ በጥንቃቄ ማነጣጠር፡፡ ስለዚህም ወንዶቹ አንድ ቦታ ቢከብቡም እንኳን ሁሉም ግን በዝምታ ግዳያቸው ላይ ማነጣጠር ይፈልጋሉ፡፡ በተቃራኒው ሴቶቹ ባሎቻቸው ከወጡ ሰንብተዋል፡፡ በሰላም ይመለሱ ይሆን? የሚለው ሥጋት አለ፡፡ ሥጋቱን ማቃለል የሚችሉት እርስ በርስ በመነጋገርና በመጽናናት ነው፡፡ ከዚያም በላይ ቀኑን የሚሳልፉት በቤት ሥራ ነው፡፡ የሚመጣውን ችግር ለመወጣትም በአንድ አካባቢ ይሆናሉ፡፡ ይነጋገራሉ፣ ይወያያሉ፤ መፍትሔ ይወራረሳሉ፤ ለዝርዝሮች ጊዜ ያገኛሉ፡፡ ወንዶቹ ከግዳይ በኋላ ወደ ቤት ሲመለሱ እንኳን እሳት ከብበው ዝምታን ሊመርጡ ይችላሉ፡፡ የአራዊቱ ሁኔታ፣ ጫካው፣ የአደኑ ቅደም ተከተል፣ ከሞት ያመለጡበት አጋጣሚ፣ የቀጣዩ ጊዜ አደን በዝምታ ይታሰባል፡፡ 
ለወንዱ ጉዳዩ ‹አንበሳ ገዳይ›› የሚለው ላይ ያልቃል፡፡ ዋናው አንበሳ መግደሉ ነው፡፡ ለሴቶቹ ደግሞ እንዴት? መቼ? ለምን? የሚለው ሁሉ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ያ፣ ከእንዲህ ይበልጥ እንዲያ ለምን አልሆነም? የሚለውም ወሳኝ ነው፡፡ ይህንን ግን ወንዶቹ እንደ ጭቅጭቅና ንዝንዝ ያዩታል፡፡   
አንድ ሌላ ባለሞያ ይህንን ነገር ‹በወንዶች አእምሮ ውስጥ በየራሳቸው የተቀመጡ ልዩ ልዩ ሳጥኖች አሉ፡፡ የሴቶች አእምሮ ግን እርስ በርሳቸው በተገናኙ ሽቦዎች የተሞላ ነው፡፡ ለወንዶች አንድ ጉዳይ ማለት አንድ ሳጥን ነው፡፡ ከሌላው ሳጥን ጋርም ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ አንዱ ሳጥን ሲከፈትም ሌሎች ይዘጋሉ፡፡ ነገሮችን ሳጥን በሳጥን ማየት ይመርጣሉ፡፡ አያገናኟቸውም፡፡ ለሴቶች ግን ነገሮች እርስ በርሳቸው የተገናኙ ናቸው፡፡ በየራሳቸው እየተነተኑና እያያያዙ ማየትንም ይመርጣሉ፡፡ ከወንዶች ሳጥን ውስጥ የሚገርመው ‹ባዶ ሳጥን› የሚባለው ነው፡፡ አንድን ወንድ ዝም ብሎ ቁጭ ብሎ ብታገኙትና ‹‹ምን እያሰብክ ነው?›› ብትሉት ‹‹ምንም›› ሊላችሁ ይችላል፡፡ እየደበቃችሁ አይደለም፡፡ ምንም ሳያስብ ለረዥም ጊዜ ዝም ማለት የሚችለው ‹ባዶ ሳጥኑ›› ሲከፈት ነው፡፡ እዚያ ውስጥ ምንም የለም፡፡ የሴቶች አእምሮ ግን የተጠላለፈ ሽቦ በመሆኑ አንድን ነገር የሚያስቡት ከሌላ ነገር ጋር አያይዘው ነው፡፡ ወንዶች ሴቶች የተጠራጠሩ ወይም የሚመራመሩ የሚመስሏቸው ነገሮችን አያይዘው ስለሚያዩ ነው፡፡  
‹‹ይኼንን ነገር ነው ዛሬም የምናየው›› ይላሉ ባለሞያዎቹ፡፡ ‹አንበሳ ገዳይ› በሚለው አስተሳሰብ ለተቃኘው ወንድ የሚገዛ ነገር ዝርዝር ይዞ፣ ገበያ ወርዶ፣ አማርጦና ተከራክሮ መግዛት ከባድ ነው፡፡ የልብስና ጫማ ገበያ ገብቶ ሳይሰለች እየተዘዋወረ ቃኝቶ መግዛት ምጥ ነው፡፡ ዋጋ ለማወዳደር፣ በየገበያው ገብቶ ማነጻጸር ሸክም ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ በመሰለው ዋጋ አንዱን ገዝቶ ሳይከራከርና ሳያማትር መውጣትን ይመርጣል፡፡ አንድ መረጃ እንደጠቆመውም ቤታቸውን በሚያሠሩ ባለትዳሮች ዘንድ ሚስቶች የሚያሠሯቸው ቤቶች ባሎች ከሚያሠሯቸው ቤቶች ይልቅ ዋጋቸው ቢያንስ 40% ይቀንሳል፡፡ አንድ ወዳጄ እንዲያውም ‹አንበሳ መግደል› የሚለው ብሂል ይሆን እንዴ አትክልት ተራና ዕቃ ተራ ሄደው ከመግዛት ይልቅ በሬ ተራና በግ ተራ ወርደው መግዛት የወንዶች ሆኖ የቀረው? ብሎኛል፡፡  
በወንዶችና ሴቶች ግንኙነት ውስጥ ጤናማ ከባቢን ለመፍጠር አንዱ መንገድ ልዩነቶቻችን ዐውቀን፣ በልዩነቶቻችን ውስጥ እንዴት እንደምንኖር፣ ከልዩነቶቻችንም እንዴት እንደምናተርፍ አስበን መኖር ነው፡፡ ለምን እንዲህ አይሆንም ? ብሎ ከመጨቃጨቅ ይልቅ እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ? እንዴትስ እንዲያ እንዳይሆን ማድረግ ይሻላል? የሚለውን መረዳቱ ይበልጥ ይጠቅመናል፡፡ ባልና ሚስት ሆነን የምንኖርበት ምክንያቱ ጉድለቶችን ለመሟላት ነውና በጎደለው ላይ ከመናደድ ይልቅ የጎደለውን መሙላቱ ቤቱን ‹ሙሉ› ያደርገዋል፡፡

25 comments:

 1. .....ባልና ሚስት ሆነን የምንኖርበት ምክንያቱ ጉድለቶችን ለመሟላት ነውና በጎደለው ላይ ከመናደድ ይልቅ የጎደለውን መሙላቱ ቤቱን ‹ሙሉ› ያደርገዋል፡፡

  ReplyDelete
 2. በጎደለው ላይ ከመናደድ ይልቅ የጎደለውን መሙላቱ ቤቱን ‹ሙሉ› ያደርገዋል፡፡

  ReplyDelete
 3. ለወንድ የሚገዛ ነገር ዝርዝር ይዞ፣ ገበያ ወርዶ፣ አማርጦና ተከራክሮ መግዛት ከባድ ነው፡፡ የልብስና ጫማ ገበያ ገብቶ ሳይሰለች እየተዘዋወረ ቃኝቶ መግዛት ምጥ ነው፡፡ ዋጋ ለማወዳደር፣ በየገበያው ገብቶ ማነጻጸር ሸክም ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ በመሰለው ዋጋ አንዱን ገዝቶ ሳይከራከርና ሳያማትር መውጣትን ይመርጣ ስለዚህ ባልና ሚስት ሆነን የምንኖርበት ምክንያቱ ጉድለቶችን ለመሟላት ነውና በጎደለው ላይ ከመናደድ ይልቅ የጎደለውን መሙላቱ ቤቱን ‹ሙሉ› ያደርገዋል ጥሩ ፅሁፍ ነው ተባረክ

  ReplyDelete
 4. ዳኒ ለእኔ የፃፍኸው ነው የመሰለኝ ብዙ ጥያቄዎች ተመለሱልኝ፡፡
  እድሜ ከ ጤና ጋር ይስጥልኝ
  ሁልጊዜም ምርጥ ዜጋ ነህ፡፡
  ግዜክስ

  ReplyDelete
 5. You are one who live in small house but your thinking ability is not blocked by your small house rather you revolve all over the world

  ReplyDelete
 6. ለወንዶች ወጡ ወጥ ነው፡፡ አንድ ድስት ወጥ፡፡ ለሴቶቹ ግን ወጡ ብዙ ነገር ነው፡፡ ሽንኩርት፣ ቅመም፣ ዘይት፣ እህል፣ እሳት፣ ድስት፣ ማማሰያ፣ ሞያ ነው፡፡ ወንዶቹ ‹‹ወጡ አይጣፍጥም›› ነው የሚሉት፡፡ ሴቶቹ ግን ‹ጨው አንሶታል፣ ሽንኩርቱ በደንብ አልተቁላላም፣ ቅመም በዝቷል፣ በርበሬው አርሯል›› ብለው ይተነትኑታል፡፡ ለወንዶች ዋናው ድምር ውጤቱ ነው፤ ለሴቶች ግን ዋናው ድምሩን ያመጡት ቅንጣቶች ናቸው፡፡

  ReplyDelete
 7. በጣም ጥሩ ዕይታ ነው። ጉዳዩ እውነት መሆኑን በኔም ቤት አይቼዋለው። ለነገሮች ዝርዝር ግድ አለመስጠቴ ራሴንም እንዲሰማኝ ያደርገኝ ነበር። ጥሩነቱ ዩልያንን ሆኜ ስመጣ ባለቤቴ እኔነቴን ተረድታ መኖሯ ለኔ ትልቅ ስጦታዬ አድርጌ እንዳያት ያደርገኛል። በርግጥ ዩልያንን ሆኖ መኖር እንዴት አይነት ደካማነት ነው፧ የሐናን ጥያቄ አሟልቶ ባይመልስ እንኳን ጤንነትን የመሰለ ቁምነገር መዘንጋት ጥሩ አይደለም።

  በዚህ አጋጣሚ እኔም በምሰራበት መስሪያ ቤት እንደተገነዘብኩት ባለሙያዎችም እንደሚያሰምሩበት ሴቶች ክሌሪካል የሆነ ዝርዝር ጥንቃቄ የሚያስፈልገውን ስራ ከወንዶች በተሻለ ይሰሩታል። አሁን እውነት እንነጋገር፣ ወንዶች ወይስ ሴቶች ገንዘብን አብቃቅተው ይጠቀማሉ፧ ገበያ የማብዛት ችግራቸው እንዳለ ሆኖ በጥቅሉ ሴቶች ለገንዘብ ትልቅ ግምት ይሰጣሉ፣ ለሴት ልጅ አሥር ብር መቶ ብሯ ነው ለወንድ ልጅ ግን መቶ ብሩ አሥር ብር እንኳን አይሆንም።
  በርቱልን ሚስቶቻችን። እግዚአብሔር ይስጥህ ዲያቆን ዳንኤል

  ReplyDelete
  Replies
  1. አቤት አንተ እንዴት የተባረክ ሰው ነህ ለሚስቶች ትልቅ ክብር ያለህ ሰው በመሆንህ እጅግ አድርጌ አመሰግንሃለሁ ሁሉም እንዳንተ ነገሮች ቶሎ ቢገባቸው ምን ነበር ደካማነታቸው ሲያሸንፋቸው ቤታቸውን ማፍረስ መፍትሄ ለሚመስላቸው ሰዎች ትልቅ ትምህርት ነው ዲን ዳን ለአንተም መልካም የሥራ ዘመን ይሁንልህ

   Delete
 8. ባልና ሚስት ሆነን የምንኖርበት ምክንያቱ ጉድለቶችን ለመሟላት ነውና በጎደለው ላይ ከመናደድ ይልቅ የጎደለውን መሙላቱ ቤቱን ‹ሙሉ› ያደርገዋል፡፡

  ReplyDelete
 9. ወንዶቹ አንድ ቦታ ቢከብቡም እንኳን ሁሉም ግን በዝምታ ግዳያቸው ላይ ማነጣጠር ይፈልጋሉ፡፡

  ReplyDelete
 10. This comment has been removed by the author.

  ReplyDelete
 11. ይህ መጣጣፍ ከኢትዮጵያ ብዙሃን ከሆነው አርሶ አደር ጋር ምን ያህል እውነት አለው??ፈረንጅ ያለው ሁሉ እውነት ከተባለ እኔ የለሁበትም።በአገሬ ጥናት ያልተርጋገጠ፣እውቀቱና እውነቱ ያልተበራየ፣ከአገሬ ህልውና ጋር ያልተያያዘ ጅምላ ግምት አልተዋጠልኝም።ሌላ ፈረጅ የጻፈው እውነታ ደግሞ እንዲህ ይላል "all generalization is wrong".

  ReplyDelete
 12. ለነገሮች ክብድት ስቶ ማውራት መስማትና መናግር ለንግሩ ካለ ፍላጎት እንጂ ከወንድ እና እሴት ጋር ይገናኝል።

  ReplyDelete
 13. ‹አንበሳ ገዳይ› በሚለው አስተሳሰብ ለተቃኘው ወንድ የሚገዛ ነገር ዝርዝር ይዞ፣ ገበያ ወርዶ፣ አማርጦና ተከራክሮ መግዛት ከባድ ነው፡፡ የልብስና ጫማ ገበያ ገብቶ ሳይሰለች እየተዘዋወረ ቃኝቶ መግዛት ምጥ ነው፡፡

  ReplyDelete
 14. i like the explanation but it need other explanation difference b/n men and women.

  ReplyDelete
 15. It provides insights to understand each other provided the interference of personal behavior of an individual.

  ReplyDelete
 16. It provides insights to understand each other provided the interference of personal behavior of an individual.

  ReplyDelete
 17. HI ! Dani. Manbeb endet des yilal !!! Ante zimbileh tsaf egnam enanbib eninebabebim. Lehulachinim rejim edime yisten.

  ReplyDelete
 18. ሰላም ለሁላችን ይሁን
  በእውነት መልካም እይታ ነው። ግን የኔ እይታ ደግሞ ትንሽ ለየት ይላል። እርግጥ ነው በፆታ ልዮነት የሚመጣ ልዮነት ቢኖርም፤ በዝርዝርና ጥቅል ጉዳይ ግን እኔ ወሳኙ ከፆታ ልዩነት ይልቅ “ለነገሮች ያለን አትኩሮት” ይመስለኛል። የእይታዬ አመክንዮ የሚመነጨው ከዚሁ እይታ ላይ ነው። ዳኒም ሆነ የእይታው መነሻ የሆኑት ደራስያን አላንና ባርባራ ፔዝ ስለተቃራኒው ኃሳብ ያሉት ነገር የለም። ማለትም ወንዶቹ ለሴቶቹ ( እንደጽሁፉ) ስለ ፖለቲካው ዝርዝር ቢጠይቋቸው ሴቶቹ ምላሻቸው ከወንዶቹ ምላሽ በተመሳሳይ “ማነው ደሞ እሱ?” የሚል ይሆናል። ስለሆነም ለእኔ ዋናው ጉዳይ አትኩሮት የምንሰጠው ጉዳይ ዓይነት ይመስለኛል።
  እንዲያውም አንዳንዴ ሳስብ የሰው ልጆች የአትኩሮት አቅጣጫ ለምን በፆታ ተወሰነ ብዬ አስባለው። ዳኒ ስለዚህ ያለህን እያታ ብታካፍለን ደስ ያለኛል።
  እንዳለ ነኝ ፣ከ አዲስ አበባ via amelmest@hotmail.com

  ReplyDelete
 19. ዳኔ ፣ ስለትዳር በሰፌው በመጻፍ ብዙ እየሞከርክ ነው ።እኔም እንደሌሎች አመሰግንህ አለሁ ። ሁኖ ግን ዘመኑ ይሁን እኛ አላውቅም ትዳርን ደምጽ በለለው መሣሪያ በመዋጋት ላይ ያለን ይመስለኛል ።አንድ ያስተዋሉ እናት እንዲህ ሲሉ ሰማሁ ልጆች ሁሉን ቆም አርጉና መፀለይ ይበጃል ፣የዘንድሮ ሰይጣን እንደሆነ በትዳርና በቤተክርሰረትያን ውስጥ ነው ያለ አሉ ። ስለዚህ መፍትሔው ቤቻል የዳኔ ምክር ሰምቶ ተቻችሎ መኖር ፣አልያም መስቀሉን ላሸከመ አምላክ አጥብቆ መፀለይ ነው ።፣አግዚአብዘሔር ብርታቱን ይስጥ ።

  ReplyDelete
 20. ዳን እናመሰግናለን፤ባልና ሚስት ሆነን የምንኖርበት ምክንያቱ ጉድለቶችን ለመሟላት ነውና በጎደለው ላይ ከመናደድ ይልቅ የጎደለውን መሙላቱ ቤቱን ‹ሙሉ› ያደርገዋል፡፡

  ReplyDelete
 21. "ወንዶቹ ነገሮችን ጠቅልሎ የማየት አዝማሚያላቸው፡፡ አለወንዶች ወጡ ወጥ ነው፡፡ አንድ ድስት ወጥ፡፡ ለሴቶቹ ግን ወጡ ብዙ ነገር ነው፡፡ ሽንኩርት፣ ቅመም፣ ዘይት፣ እህል፣ እሳት፣ ድስት፣ ማማሰያ፣ ሞያ ነው፡፡ ወንዶቹ ‹‹ወጡ አይጣፍጥም›› ነው የሚሉት፡፡ ሴቶቹ ግን ‹ጨው አንሶታል፣ ሽንኩርቱ በደንብ አልተቁላላም፣ ቅመም በዝቷል፣ በርበሬው አርሯል›› ብለው ይተነትኑታል፡፡" Wedijewalehu

  ReplyDelete
 22. Dani,It is great observation! Many of us
  have spoiled our years spent relationship or marriage because of not knowing this natural difference. So it is a good lesson for all of us. Keep on writing, keep on observing the unobservable.

  ReplyDelete