Monday, July 13, 2015

የሚባላውን ጅብ ጥሪ


ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ በ1985 ዓም ታትማ በነበረቺው ውይይት መጽሔት(ቅጽ 2፣ ቁጥር 1) ላይ የዐፄ ኃይለ ሥላሴን ዘመንና የንጉሡን ሁለት መልክ የነበረው አመራር ገምግመው ነበር፡፡ መጀመሪያ ተራማጅ በኋላ ደግሞ ወግ አጥባቂ እየሆኑ የመጡት ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ከሃምሳ ዓመታት በዘለለው የንግሥና ዘመናቸው ለሀገሪቱ አስፈላጊ ከመሆን ተነሥተው አላስፈላጊ ወደመሆን የደረሱት ለምን ነበር? የሚለውን የምሁሩ ድርሳን በሚገባ ያሳየናል፡፡
ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ተፈሪ መኮንን ተብለው ሥልጣን በያዙባቸው የመጀመሪያ ዓመታት ሀገሪቱን በለውጥ ጎዳና የሚወስዱ ርምጃዎችን በመውሰድ፣ የሀገሪቱን ማዕከላዊ አስተዳደር በማጠናከር፣ ትምህርትን በማስፋፋት፣ በዐፄ ምኒሊክ ዘመን የተጀመሩ ዘመናዊ አሠራሮችን ሥር ይዘው እንዲጎለብቱ በማድረግ፣ የሀገሪቱን አዲስ ሕገ መንግሥት እንዲረቀቅና እንዲጸድቅ በማድረግ ተራማጅ መሪ ሆነው ብቅ ብለው ነበር፡፡ ለውጥ ይሻ የነበረው የዘመኑ አዲስ ትውልድም የተፈሪ መኮንን ደጋፊና ተባባሪ ሆኖ ተሰልፎ ነበር፡፡ ተፈሪ መኮንንን እንደ አዲሲቱ ኢትዮጵያ መሪ፣ የሥልጣኔ አራማጅ፣ ወደ አዲስ ዘመን አሸጋጋሪ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር፡፡ 


በርግጥም እስከ ጣልያን ወረራ በነበሩት ዘመናት ተፈሪ መኮንን የታሰበላቸውን ያህል ባይሆንም ተራማጅና ለውጥ አራማጅ መሪ ለመሆን ሞክረው ነበር፡፡ ሕዝቡም አንዳንድ የለውጥ መንገዶች፣ የተራማጅነት ሐሳቦችና የሥልጣኔ ርምጃዎች በመመልከቱ በንጉሡ ላይ ተሥፋ ነበረው፡፡ እርሳቸውን መቃወምም የሀገሪቱን ዕድገት እንደመቃወም፣ በሥልጣኔ ላይም ዕንቅፋት እንደመሆን የሚቆጥሩ ወገኖች ነበሩ፡፡ እንደነ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም ያሉ የተማሩ ወጣቶችም ከተፈሪ መኮንን ጋር የተሰለፉት ንጉሡን በማፍቀር ሳይሆን ሀገራቸውን ለማዘመንና ለማሠልጠን የተሻሉት መሪ ተፈሪ መኮንን ናቸው ብለው በማመናቸው ነበር፡፡    
ከጣልያን ወረራ መልስ መንበራቸው ሳይናጋ ያገኙት ተፈሪ መኮንን የጀመሩትን የዝመናና የሥልጣኔ መንገድ ሀገሪቱ በምትፈልገው ፍጥነትና መጠን አላስኬዱትም፤የዴሞክራሲና የፖለቲካ ጥያቄዎችም በዘዴና በሥልጣን እንዲወገዱ ተደረጉ፡፡ ሀገሪቱ በመጀመሪያው የተራማጅነት ዘመን በተሠሩ ሥራዎች አደገች፣ የማኅበረሰቡ አስተሳሰብ ተለወጠ፣ የትምህርት ቤቶችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋት ኅሊናዊ ለውጥን በትውልዱ ላይ አመጣ፡፡ ምንም እንኳን እንዳሁኑ ቀልጣፋ የግንኙነት መንገድ ባይኖርም፣ ከቀደሙት ዘመናት በተሻለ ግን ሀገሪቱ ከውጭው ዓለም ጋር ተገናኘች፣ ይህም አዳዲስ አስተሳሰቦችና አሠራሮች እንዲገቡና ከነባሩ ጋር እንዲሟገቱ በር ከፈተ፡፡ የጣልያን የአምስት ዓመቱ ቆይታም ሕዝቡ ስለ ንጉሡ የነበረውን አመለካከት ለወጠው፡፡ ‹ንጉሥ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ› ከሚለው የጸና ብሂል ወጥቶ ‹የሸሸ ንጉሥ አይነግሥም፣ ያፈረሰ ቄስ አይቀድስም› ወደሚለው አዲስ አባባል ተሸጋገረ፡፡ በዚህም ምክንያት በተደጋጋሚ ንጉሡን መቃወም ተጀመረ፡፡
‹የት ከረሙ ሳንል ተቀብለን በወንበራቸው ብናስቀምጣቸው፤ ሊጋልቡብን አማራቸው› የሚለው  የበላይ ዘለቀ አስተሳሰብ ምንም እንኳን ከእርሱ መሰቀል ጋር የተገታ ቢመስልም መልኩን ቀየረ እንጂ ሐሳቡ አልሞተም ነበር፡፡ በቢትወደድ ነጋሽ የተመራው የመጀመሪያው ፀረ ኃይለ ሥላሴ አድማም ንጉሠ ነገሥቱ ተወግደው ሬፐብሊክ መመሥረት አለበት ብሎ ነበር የተነሣው፡፡ የ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥትም እነዚህን ተከትሎ የመጣ ነበር፡፡
እነዚህ ሁሉ የውድቀት ዋዜማ ከበሮዎች ቢደለቁም ንጉሡ ግን በልካቸው ከሰፉት ልብስ ውጭ ሌላ ለመልበስ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ የተለያዩ ምሁራንና ተራማጅ መኳንንት ያቀረቧቸውን የለውጥና የተሐድሶ ሐሳቦች ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ እጅግ የሚወዷቸው እነ ራስ እምሩ እንኳን ለየት ያለ ሐሳብ አምጥተው ንጉሡን ማሳመን አልተቻላቸውም፡፡
ለዚህ ሦስት ምንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡
የመጀመሪያው ተፈሪ መኮንን በ1909 ወደ ሥልጣኑ መንደር ሲመጡ የነበረቺው ኢትዮጵያ በግማሽ ምእተ ዓመት ጉዞ መለወጧ ነው፡፡ ከገጠሩ ማኅበረሰብ ጎን ለጎን በአነዋወር ሥርዓቱ የተለየ የከተማ ማኅበረሰብ ተፈጥሯል፡፡ በዘመናዊ ትምህርት ቤቶች በኩል ያለፈ አዲስ ትውልድ መጥቷል፡፡ የጣልያን ወረራ በሕዝቡ ዘንድ አስተዳደርን በተመለከተ አዲስ አመለካከት ፈጥሮ ሄዷል፡፡ ያለ ንጉሥ ሲመራ የነበረ ዐርበኛ የተባለ ማኅበረሰብ ተፈጥሯል፡፡ ዘመናዊ አስተዳደር በሀገሪቱ ተዘርግቷል፡፡ በመንግሥቱ ሥራ ውስጥም በባሕላዊ ትምህርትና በዘመናዊ ትምህርት ያደጉ ሁለት ዓይነት ትውልዶች ተሠማርተዋል፤ ማዕከላዊ የሆነና ዘመናዊ ሥልጠና ያገኘ ወታደራዊ ተቋም ተመሥርቷል፡፡ የግብርና የቀረጥ ሥርዓት በአብዛኛው ማዕከላዊ ሆኗል፡፡ በዐፄ ዮሐንስና በዳግማዊ ምኒሊክ ዘመን የነበሩት አካባቢያዊ አስተዳደሮች ቀርተው ማዕከላዊ ሥልጣን ተጠናክሯል፡፡
ተፈሪ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ለነበረቺው ኢትዮጵያ በቂ ነበሩ፡፡ ምናልባትም ደግሞ የተሻሉ ተራማጅ፡፡ ከግማሽ ምእተ ዓመት በኋላ ግን ለሀገሪቱ አነሱባት፤ ያሰፉላት ልብስ አልመጥናት አለ፡፡ አዲስ አስተሳሰብና አዲስ መንገድ ፈለገቺ፡፡ ተጨማሪ ነገር፣ ተጨማሪ አሠራርና ተጨማሪ ርምጃ ተመኘቺ፡፡ አንድ ሕጻን ልጅ ሲወለድ የእናቱ ጡት ብቻ ከበቂው በላይ ነው፡፡ በኋላ ግን ተጨማሪ ምግብ ይፈልጋል፤ ቀጥሎም ምን ቢወደው የእናቱን ጡት ይተወዋል፤ ሌላ ምግብም ያስፈልገዋል፡፡ እየቆየ ሲሄድ ደግሞ ጨው የሌለው፣ ስብ ያልበዛበት፣ ስኳር አልባ፣ አትክልት ብቻ፣ የተፈጥሮ፣ ቫይታሚን፣ ሚኒራል፣ ፕሮቲን፣ ካርቦሃይድሬት፣ እያለ አማርጦና ወስኖ መመገብ ይቀጥላል፡፡
አመራርም እንደዚሁ ነው፡፡ ሲጀመር ተወደደ ማለት እስከ መጨረሻው አይወደድም፡፡ ከነ ጣዕሙ በቃኝ ካላለ፡፡ ማንኛውም ነገር በሂደት ውስጥ ነው፡፡ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይወረዛል፣ ይጎረምሳል፣ ያረጃል፣ ይደክማል፣ ይሞታል፡፡ ይህንን ማምለጥ የሚቻለው በሁለት መንገድ ብቻ ነው፡፡ ወይ እንደ ንሥር ራስን በማደስ፣ አለያም ደግሞ ለአዲሱ ራስን በመልቀቅ፡፡ በተለያዩ ሀገራትና ድርጅቶች የመሪዎች የሥልጣን ዘመን እንዲገደብ የሚደረገው፣ በአንዳንድ ሀገሮችም ፓርቲዎችና መሪዎች ምንም መልካም ቢሠሩ በቃቸው ተብለው ድምጽ እንዲያጡ የሚሆኑት ሳያረጁና ወደማይፈለጉበት ደረጃ ሳይደርሱ ከነ ጣዕማቸው ለማኖር ሲባል ነው፡፡ ምን ብንወደው የልጅነታችንን ልብስ ስናድግ ልንለብሰው አንችልም፡፡ ካገኘን ተመሳሳዩን ጨርቅ ገዝተን በልካችን ሌላ እናሰፋለን እንጂ፡፡ ለዚህም ነበር በ1909 እንደ ተራማጅ ታይተው የተሞገሡት ተፈሪ በ1966 እንደ ችግር መታየት የጀመሩት፡፡ ሀገር እያደገች መሪ እያረጀ ሲሄድ ዕጣው ይኼው ነው፡፡ በ1964 ዓም አብዮቱ ሊፈነዳ 2 ዓመት ሲቀረው ንጉሡ 80ኛ የልደት በዓላቸውን ያከብሩ ነበር፡፡ በሃያዎቹ አጋማሽ ወደ ሥልጣን የመጡት ንጉሥ በ80 ዓመታቸው ፍላጎት ቢኖራቸው እንኳን ዐቅም ግን አይኖራቸውም፡፡ በዚህ እድሜ ዕንቅልፍን እንጂ የሀገሪቱን ችግር ማሸነፍ አይችሉም ነበር፡፡  አሥራ አራት ዓመት በአልጋ ወራሽነት፣ ሠላሳ ዘጠኝ ዓመት በንጉሠ ነገሥትነት  ቆዩ፡፡ ኢትዮጵያ አደገች፣ እርሳቸው ግን አረጁ፡፡ አዲሲቱ ሙሽራም አዲስ ባል ፈለገች፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ተፈሪ መኮንን ኢትዮጵያንና ራሳቸውን የማይነጣጠሉ አድርገው ማየታቸው ነው፡፡ እርሳቸው ከሌሉ ሀገሪቱ እንደ ሀገር የምትኖርና የምትቀጥል አትመስላቸውም፡፤ ትወድቃለቺ፣ ትበታተናለቺ፣ ህልውናዋም ያቆማል ብለው አመኑ፡፡ ከእርሳቸው በፊት ስንት የመከራና የድል ዘመናትን እንዳጣጣመቺ፣ እርሳቸው ትተዋት በሄዱበት የመከራ ጊዜ እንኳን እየታገለቺ መቀጠል እንደቻለቺ፣ እርሳቸውንም ወደ ሥልጣን ያመጣቺ እርሷ እንደሆነቺ፣ የስንት ታላላቅ ታሪክ ባለቤት እንደሆነቺ ዘነጉት፡፡ አመራራቸው ‹ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ› ሆነ፡፡
በአንድ ወቅት ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም የኢትዮጵያን ስም ደጋግመው ሲያነሡባቸው ‹‹አንተ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የምትለው ኢትዮጵያ ያለ እኔ ምንም አይደለቺም፤ ዕድልዋ ከእኔ ጋር የተሣሠረ ነው፤ እኔ ነኝ የማደርሳት፤ ካለኔ ትኖራለቺ ብለህ አታስብ›› ብለው ነበር በቁጣ የመለሱላቸው፡፡ ተፈሪ መኮንን ኢትዮጵያ ያለ እርሳቸው እንዳልተፈጠረቺ፣ ያለ እርሳቸውም እንደማትኖር ያምኑ ነበር፡፡ የእርሳቸው ዘመን ሲያበቃ የኢትዮጵያም ዘመን አብሮ እንደሚያበቃ፤ የህልውናዋም ዋልታ እርሳቸው እንደሆኑ ይናገሩ ነበር፡፡ ይህ ግን ከታሪካዊው ሐቅ ውጭ ነበር፡፡ እርሳቸው ለኢትዮጵያ ሠርተዋል፤ ኢትዮጵያ እንድትሠለጥንና እንደትዘምን አድርገዋል፤ ሀገሪቱን ወደ አንድ ምዕራፍ ለማሻገር ችለዋል፡፡ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ፈጣሪዎች ከሚባሉት ተርታ ተሰልፈዋል፡፡ ነገር ግን አገሪቱን አልፈጠሯትም፤ አያኖሯትም፤ አይበትኗትምም፡፡ ኢትዮጵያ ነበረቺ፣ ትኖራለቺም፡፡ መልኳ ሊለወጥ፣ ታሪኳ ሊቀየር፣ መንገዷ የተለየ ሊሆን፣ አሠራርዋ ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ ሀገሪቱ ግን ትቀጥላለቺ፡፡ ደግሞም ‹ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ› እንደተባለው ተፈሪ ቢሞት ሌላ ይመጣል፡፡
ይኼ የኢትዮጵያን ዕጣ ከራስ ዕጣ ፋንታ ጋር የማያያዝ፣ የኢትዮጵያን ህልውና ከራስ ህልውና ጋር የማስተሣሠር፣ የኢትዮጵያንም ጉዞ ከራስ ጉዞ ጋር ብቻ የማቆራኘት አባዜ እስከዛሬም አልለቀቀንም፡፡ ከንጉሡ በኋላ ይህቺን ሀገር የመሩ ሰዎችና ድርጅቶችም እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ አትኖርም፤ሰማይዋን ያለ ዋልታ፣ ምድሯን ያለ መከታ ያቆምነው እኛ ነን ይላሉ፡፡ ሀገሪቱ ሥጋ ናት፣ ነፍሷ እኛ ነን ብለው ያስባሉ፡፡ ‹‹ፀሐይ ጠዋት ጠዋት የምትወጣው እኔ በማለዳ ስጮኽ እየቀሰቀስኳት ነው›› ብሏል አውራ ዶሮም፡፡ እርሱ ለፋሲካ ሲታረድ ፀሐይ መውጣቷን እንደምትቀጥል ማን በነገረው፡፡
ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ነገሩን ሁሉ የመጠቅለል አባዜ ነው፡፡ አባ ጠቅል እንደስማቸው ሥልጣኑን ሁሉ ጠቀለሉት፡፡ ተራማጅ ሐሳብ የነበራቸውን፣ የተለየ ሐሳብ የሚያስቡትን ሁሉ ገሸሽ እያደረጉ፣ መሳፍንቱን ሁሉ ገንድሰው ገንድሰው ሀገሪቱን የራሳቸው ብቻ አደረጓት፡፡ ለኢትዮጵያ ከእኔ የተሻለ የሚያስብላት የለም ብለው ስላመኑ እርሳቸው የሚናገሩትና የሚሠሩት ባቻ ሳይሆን እርሳቸው ራሳቸውም እውነትና ትክክል ሆኑ፡፡ መለኪያውም ራሳቸው ሆኑ፡፡ የሚሰጧቸውን የለውጥ ሐሳቦች ከመቀበል ይልቅ አሳቢዎቹን ማግለልን መረጡ፡፡
እያረጁና እየደከሙ ሲሄዱ፣ ዐቅም ሲያንሣቸው ለአልጋ ወራሹ አልጋውን ከመልቀቅ ወይም የፖለቲካ ሥርዓቱን ከማላሻሻል ይልቅ ጠንካራ መስለው ለመታየት እንዲችሉ በየጊዜው ድግስ መደገስና በዓሎቻቸውን ማክበር፣ የሀገር ቤቱ ሰው አላደንቅ ሲል ወደ ውጭው ዓለም እየሄዱ አድናቆትን መሰብሰብ ጀመሩ፡፡ እርሳቸው ሥልጣኑን በጠቀለሉትና ለለዘብተኛና ጥገናዊ ለውጦች ዕድል በነፈጉ ቁጥር ተቃዋሚዎቻቸው ወደ ከረረ ተቃውሞ ውስጥ ገቡ፡፡ ባሕሩ ዘውዴ እንዳሉትም ‹‹ለለዘብተኛ ተቃውሞ ሥፍራ የማይሰጥ ሥርዓት ራሱን ለከረረ ተቃውሞ መዳረጉ የማይቀር ነው፡፡››
ከግርማሜ ንዋይ በፊት የነበሩት የንጉሡ ተቃዋሚዎች ጥገናዊ ለውጥ፣ የፖለቲካ ሥርዓት መሻሻል፣ አስተዳደራዊ ዘመናዊነት፣ የብዙኃንን ተሳትፎ በማረጋገጥና የሀገሪቱን መሠረታዊ ችግሮች በማላቀቅ ጥያቄዎች ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ ንጉሡ ለእነዚህ ለዘብተኞች ቦታ ሲነፍጓቸው ንጉሡንና መሳፍንቱን ማስወገድ ያስፈልጋል የሚሉ የከረሩ ሐሳቦች ቦታ እያገኙ መጡ፡፡ ግርማሜ ንዋይ የዚህ አዲስ የከረረ ተቃውሞ ጀማሪ ነው፡፡ በኋላ የመጡት ተማሪዎች ደግሞ ግርማሜንም በለዘብተኛነት ፈረጁት፡፡ ለንጉሡም ሆነ ለሥርዓቱ ትዕግሥት አጡ፡፡ ሀገሪቱን ከፍላ ወደማትጨርሰው ዕዳ ውስጥ ወደሚከት ጽንፈኛ ተቃውሞም ገቡ፡፡ ጥገናዊ ለውጥን ለማጤን ልብ ያለው ተቃዋሚ ጠፋ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የበሽታው መጠንከር ነው፡፡ የንጉሡ የሥልጣን ቁጥጥርና ጉልበት መጠንከር ተቃውሞው በአመክንዮ ሳይሆን በአብዮት እንዲመራ አደረገው፡፡ መድኃኒቱ እንደ በሽታው ይጠነክራልና፡፡
ንሥር ማርጀቱን ራሱ ዐውቆ ለራሱም ጊዜ ሰጥቶ ራሱን ያድሳል፡፡ መጀመሪያ ግን ማርጀቱን ማመን አለበት፡፡ ማመን ብቻም ሳይሆን የሚምንበት ጊዜ ለመታደስ በሚችልበት እድሜው ላይ መሆን አለበት፡፡ ንሥር ለመታደስ የሚችልበትን ጊዜ ካሳለፈው በኋላ ራሱን ለማደስ አይቻለውም፡፡ ያለው አማራጭ ራሱን በራሱ እያየ ሞትን መቀበል ብቻ ነው፡፡ ራስን በራስ እንደ ንሥራ ለማደስ ካልተቻለ  ደግሞ እንደ ኢምፓላ አዲሱ ዘመን ለሚፈልገው አዲስ አስተሳሰብ ቦታን መልቀቅ ነው፡፡ እንደ ጎበዝ የእግር ኳስ ተጨዋች፡፡ በጊዜ የስታድዮም ደጋፊዎቹ የቁልምጫ ስማቸውን ወደ ስድብ ሳይቀይሩት፣ ባገባው ጎል እጥፍ ጎል ሳይገባበት ጫማውን በጊዜ እንደሚሰቅል ጎበዝ ተጨዋች፡፡ በጊዜ የሚቻለውን ሠርቶ፣ ከራሱ የተሻለ ሰውና ሥርዓት ተክቶ በጊዜ ወንበርን መስቀል፡፡ ተፈሪ ሁለቱንም ማድረግ ስላልቻሉ በ80 ዓመታችው ዓይናቸው እያየ የማይፈልጉት ነገር ሁሉ ሆነ፡፡ አገሪቱንም ራሳቸውን ዕዳ ውስጥ ከተቱ፡፡ የሚጮኸውን ውሻ አባረው የሚባላውን ጅብ ጠሩት፡፡
አስደናቂው ነገር ከዚህ የዘመናችን ታሪክ አሁንም አለመማራችን ነው፡፡ በፓርቲ፣ በመንግሥት፣ በድርጅት፣ በማኅበር፣ ያሉት መሪዎቻችን አሁንም በእነዚህ ሦስት የጥፋት መንሥኤዎች ላይ ሆነው ራሳቸውን የሚበላ አብዮት በመጥራት ላይ ናቸው፡፡
      

26 comments:

 1. አስደናቂው ነገር ከዚህ የዘመናችን ታሪክ አሁንም አለመማራችን ነው
  መሪዎቻችን አሁንም በእነዚህ ሦስት የጥፋት መንሥኤዎች ላይ ሆነው ራሳቸውን የሚበላ አብዮት በመጥራት ላይ ናቸው፡፡

  ReplyDelete
 2. ‹‹ፀሐይ ጠዋት ጠዋት የምትወጣው እኔ በማለዳ ስጮኽ እየቀሰቀስኳት ነው›› ብሏል አውራ ዶሮም፡፡ እርሱ ለፋሲካ ሲታረድ ፀሐይ መውጣቷን እንደምትቀጥል ማን በነገረው፡፡

  ReplyDelete
 3. አስደናቂው ነገር ከዚህ የዘመናችን ታሪክ አሁንም አለመማራችን ነው፡፡ በፓርቲ፣ በመንግሥት፣ በድርጅት፣ በማኅበር፣ ያሉት መሪዎቻችን አሁንም በእነዚህ ሦስት የጥፋት መንሥኤዎች ላይ ሆነው ራሳቸውን የሚበላ አብዮት በመጥራት ላይ ናቸው፡፡

  ReplyDelete
 4. Welcome back after long time absence. Very nice opinion!

  ReplyDelete
 5. ዲ/ን፣ ይህም ድንቅ ነው፣ የሚሰማ ከተገኘ።
  ኧረ በስልጣን ላይ ያለኸው፣ እባክህ የሚባላው ጅብ ሳይመጣ፣ የሚጮኸውን ውሻ ስማው!

  ReplyDelete
 6. አረ ጉድ ነው ለአንተና ለቤተ ሰብህ እግዚአብሔር አአምላክ ሙሉ ጤናና ረጅም ዕድሜ ይስጣችሁ በተለይ ለባለቤትህ ከእያንዳንዱ ታላላቅ ሰዎች በስተ ጀርባ ሌሎች ታላላቅ ሰዎች አሉና ባለቤትህ ጊዜና ፍላጐት ሰጥታ ከጐንህ ቆማ በመገኘቷም ጭምር ነው የተሳካልህ ልትመሰገን ይገባታል በተለየ ሁኔታ ነው የዛሬዋ ጦማርህ (እለ ትነብሩ ተንሥኡ ወእለ ታረምሙ አውሥኡ) ማለት አሁን ነው ደወሉ ለሥጋም ለነፍስም ጆሮ የሚሰማ ነውና ።(ጆሮ ላለው ማለቴ ነው) አክባርህ ነኝ እስኩ ድግሙ ከጀርመን

  ReplyDelete
 7. ቃለ ህይወት ያሰማልን፡
  ቅን አስተሳሰብ ያለው አስተዳደር እንዲሰጠን አምላክ ይርዳን፡ ሰምቶ የሚታረም መሪዎች ይስጠን፡፡
  ግዚክስ


  ReplyDelete
 8. በእውነት እግዚአብሔር አስተዋይ ልብና አስተማሪ አይምሮ ሰጥቶሃል። ለመሸንገል ወይም በከንቱ ለማወደስ ሳይሆን ሥራና ተግባርህ ይመሰክራል። የሚሰማ ጀሮና የሚያይ ልብ ካላቸው እያንዳንዱን አካል የሚቀሰቅስና በጊዜ የተሻለውን እንዲያደርጉ የሚያሳያቸውን የፊት መሥተዋት ነው በጽሑፍህ ያሥቀመጥህላቸው።
  በእውነት እግዚአብሔር ይጠብቅህ። ካንተ ብዙ የምንማረው ይኖራልና ጨምረህ አሥተምረን።

  ReplyDelete
 9. ዳኒ እ/ግ ይስጥህ ካንተ እንኳን ተምሮ እደንስር እራስን ማደስ ጊዜው ካለፈ ደሞ አደማይሆን አውቆ ሞቱን መጠበቅ ።ግን አልታደለችምና ኢትዮ እማማ ሀገራችን መፍትሄው አሁንም አልታወቀም እ/ግ ሀይልይሁናት ።እጂግ ጠቃሚ ትምህርት ነው ቃለ ህይወት ያሰማልን ።ጀሮ ያለው ይስማ ።ኡ ኡ ኡኡ ኡኡ።

  ReplyDelete
 10. ዴኒ ወዴት ጠፍተህ ነው ሳስብህ ነበር አሁን ደስ አለኝ
  በዚ ዘመን ዘረኛው ጉጠኛው አጥብቦ አሳቢዎች በበዙበት በይበልጥ በስደት ላለን ያንተ እይታዊና ድንቅ ማንነትን ሳይዘነጉ ለመኖር
  በጠቅል አሽከሮች ተጠቅልሎ ተሳቢ ከመሆን ያድናል እና ብርታቱን ያድልህ እናነባለን እናስነብባለን በርታልን

  ReplyDelete
 11. Well come back Dn.Dani. Great idea!!

  ReplyDelete
 12. No more words to say, you said it all

  ReplyDelete
 13. Wonderful....Well written

  ReplyDelete
 14. እያስተዋልክ ማለቂያ በሌለው ነገር ውስጥ አትግባ ለልጆችህ ብትኖር ጥሩ ነው እግዚአብሄር ይጠብቅህ አሁንም ከሚበላ ጅብ ይሠውርህ

  ReplyDelete
 15. ጽሑፉ ባነሳው መባያ ጉዳይ መልእክቱ ድምጸት አለው፡፡ ለዚህም ጸሐፊው ይመሰገናል፡፡ ሆኖም ግን በዚህ የጡመራ ገጽ የሚወጡ ታሪክ ቀመስ ጽሑፎች ነገ በጦማሪው መጽሐፍ ስለሚደረጉ ፤ የታሪክ ሁነቶችና እውነቶች ሲጻፉ ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለምንጭነት ሰዎችም ይጠቀሟቸዋል፡፡ ስለሆነም ጸሐፊው እንደገና ቢያያቸው ያልኳቸውን ሦስት ነጥቦች ላንሳ፡፡
  1. በንጉሠ ነገሥትነት 39 ዓመት የሚለው ስህትት ነው፡፡ ትክክለኛው 44 ዓመት ነው፡፡ (ከ1923ዓ.ም - 1967ዓ.ም)
  2. ተፈሪ ብዙ ሥራዎችን የሠሩት ድኅረ ጣሊያን ወረራ ነው እንጂ ፤ከወረራው በፊት አልነበረም፡፡
  3. የመጀመሪያው ፀረ ኃይለ ሥላሴ አድማ የተመራው በቢትወደድ ነጋሽ አይደለም፡፡

  ReplyDelete
 16. ሰላም ዲያቆን ዳኒ ,ቃለ ህይወት ያሰማልን! መቼም ቢሆን ተሰፋ አንቆርጥም አንድ ቀን የእዝቧን ጬኅት የሚሰማ ፈሪሃ እግዚሃብሔር ያደረበት መሪ ይሰጠናል. ይብላኝ ለነሱ የሰላም እንቅልፍ ሳይተኙ ለሚኖሩ. ለሁላችንም ትንሥሔዋን ያሳየን አሜን. ዲያቆን ዳኒ ,መድሃሂያለም ባለህበት ይጠብቅህ አሜን!!!

  ReplyDelete
 17. ሰላም ዲያቆን ዳኒ ,ቃለ ህይወት ያሰማልን! መቼም ቢሆን ተሰፋ አንቆርጥም አንድ ቀን የእዝቧን ጬኅት የሚሰማ ፈሪሃ እግዚሃብሔር ያደረበት መሪ ይሰጠናል. ይብላኝ ለነሱ የሰላም እንቅልፍ ሳይተኙ ለሚኖሩ. ለሁላችንም ትንሥሔዋን ያሳየን አሜን. ዲያቆን ዳኒ ,መድሃሂያለም ባለህበት ይጠብቅህ አሜን!!!

  ReplyDelete
 18. it is hard to advice old people or parties until they are driven away to their end by the next person or party who may get the chance through peaceful way of straggle or revolution like the former once .Your opinion is positive and educative thank you for your clear idea .

  ReplyDelete
 19. Daniyee,you are our idol! you are our voice ! God be with you and with your great family .Danny for President.Yeslasea baria yedengil Mariam ashker Dereje Jote.Love you

  ReplyDelete
 20. ዲ/ዳንኤል፡- ስለ ንጉሡ በአጭሩ የጻፍከውን ሃሳብ በአብዛኛው አልቀበለውም፡፡ ምክንያቱም አንተን በመንፈሳዊ መምህርነት ስለማስብህ የተጠቀምካቸው ቃላት፡- 1. አዲሲቱ ኢትዮጵያ፣ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ፣ ለውጥ ፈላጊ ህዝብ፣ልብስን በልክ መስፋት፣ኢትዮጵያ ነበረቺ፣ ትኖራለቺም፣ወዘተ. ከዘመኑ ካድሬ ~ን~ ጋር አንድ ስለሆነ" ለውጥ ፈላጊ ህዝብና አዲሲቱ ኢትዮጵያ ምን እንዳገኙና ምን እንዳጡ በመንፋሳዊና በሥጋዊ ዕይታ ብትገልጽ በተለይም ከንጉሡ በኋላ ቢያንስ የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ መሪ እስካሁን ስላላየን" 2. የውድቀታቸውን ምክንያት ስትጠቅስ ከእግዚአብሔር አንጻር ያለውን ሁኔታ ማለትም ለእግዚአብሔር የማይመቹ ነገሮች ወደ ሀገሪቱ የገቡት በሳቸው ጊዜ በመሆኑ የሥልጣን ባለቤት ስለሻራቸው እንጂ ስላረጁ ወይም ለውጥ ፈላጊ ስለበዛ ወይም በሌላ ምክንያት አይደለም፡፡ ሀገር በአንድ ሰው ምክንያት ትጸናለች/ትፈርሳለች፡፡ ንጉሡ ከኢትዮጵያ አልፈው ለአፍሪካ አባት ነበሩ፡፡ ግንድ ሲወድቅ መጥረቢያ ይበዛበታልና ዛሬ ሁሉም ሰው ነገስታቱን ሲነቅፍ ያሳዝናል፡፡ በርግጥ ሰው እንደመሆናቸው ብዙ ሥህተቶች ሠርተው ይሆናል"የኢትዮጵያ ዙፋን ግን ‘ፍሬ አይገኝብህ’ ተብሎ ተረግሞ ይሆን? የምዕራባውያን ዲሞክራሲ ለሰይጣን ወይስ ለእግዚአብሔር ተመቸ? አንድ ታላቅ አባት(አቡነ ዲዮስቆሮስ ዘወሊሶ) ‘የፈረንጅ ወዳጅ የለንም’ እንዳሉት ንጉሡ የፈረንጅ ወዳጅ መሆናቸውና የኢትዮጵያ ብቻ የሆነውን ማንነት ለምሳሌ የመንፈሳዊ ትምህርት(የቆሎ ትምህርት) በአስኮላ መተካት፣የያሬድን ዜማ በሙዚቃ(ዘፈን) መተካት የቅዱስ ያሬድን ስም ለዓለማዊ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መሰየም፣ የቅዱስ ጊዮርጊስን ስም ለቢራ መሰየም፣ወዘተ. የአመጻ ሥራ እንዲስፋፋና ሃማኖትና ምግባር እንዲዳከም በመደረጉ ይህም ከእግዚአብሔር ጋር የማይድ በመሆኑ ንጉሡን ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱንና ትውልዱን ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ለመሆኑ አንተስ ዲ/ዳንኤል የአቡነ ጎርጎርዮስ ተማሪ የነበርከው ዓላማህ ምንድነው? ለዚህ ትውልድ ወንጌልን ማስተማር ወይስ…..

  ReplyDelete
 21. dn dani nice view but i expect to write about Obama coming

  ReplyDelete
 22. "እለ ትነብሩ ተንሥኡ ወእለ ታረምሙ አውሥኡ.........!!!"

  ReplyDelete
 23. ዳን እግዚአብሔር ጥበቡን አብዝቶ ይጨምርልህ፤ የሚበላውን ጅብ ጥሪ ‹‹ፀሐይ ጠዋት ጠዋት የምትወጣው እኔ በማለዳ ስጮኽ እየቀሰቀስኳት ነው›› ብሏል አውራ ዶሮም፡፡ እርሱ ለፋሲካ ሲታረድ ፀሐይ መውጣቷን እንደምትቀጥል ማን በነገረው፡፡ የሚገርመኝ በዚህ ዘመንም እንደዚህ ዓይነት መንግስትና አስተሳሰብ ያላቸው ትውልዶች መፈጠሩ በጣም የሚገርም ነው፡፡ የቱ ጋር ይሁን የእኛ ስልጣኔ? እኔ የዚህን ሀገር ስልጣኔ ያየሁት ሆድ የባሰው መንገድና በሙስና የተጥለቀለቁ ፎቆችን ማየት ነው ስልጣኔ?

  ReplyDelete