ወንዶችንና ሴቶችን በተመለከተ ከተጻፉ
መጻሕፍት መካከል ከርእሱ ጀምሮ የሚገርመኝ አንድ መጽሐፈ አለ፡፡ ‹‹why Men Don’t have a clue &
Women always need more shoes›› ይላል፡፡ ባልና ሚስቱ የመጽሐፉ ደራስያን አላንና ባርባራ ፔዝ የወንዶችንና የሴቶችን
ግንኙነት ጤናማና ሰላማዊ ለማድረግ አንዱ ዋናው መንገድ ሁለቱ በነገሮች ላይ ያላቸውን ልዩነት ጠንቅቆ ማወቅና በዚያ ላይ ግንኙነትን
መመሥረት ነው ይላሉ፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ ካነሷቸው አስገራሚ
የወንዶችና ሴቶች የአነዋወርና አስተሳሰብ ልዩነቶች መካከል አንዱ ነገሮችን የሚያዩበት መንገድ ነው፡፡ ሴቶች ነገሮችን በዝርዝርና
አበጥረው የማየት አዝማሚያና ተሰጥዖ አላቸው ይላሉ፡፡ ለምን? እንዴት? የት? ከዚያስ? እያሉ ነገሮችን ይፈተፍቷቸዋል፡፡ ወንዶቹ
‹ዝርዝር ኪስ ይቀዳል› በሚለው የአራዶች መመሪያ ተመርተው ነው መሰል ነገርን በጥልቁና በዝርዝሩ ከማየት ይልቅ ጠቅላላውን ነገር
ስለሚመርጡ ስለ አንድ ጉዳይ በዝርዝር ሲጠየቁ ቁጥጥር የተደረገባቸው፣ ምርመራ የተካሄደባቸውና አለመታመን የተፈጠረባቸው መስሏቸው
ቁጣ ይቀድማቸዋል፡፡ ነገሩ የመጣው ጉዳዮችን በዝርዝር በሚያየው የሴቶች ልቡናና ነገሮችን መጠቅለል በሚወደው የወንዶች ልቡና መካከል
በተፈጠረ ልዩነት ነው፡፡