
click here for pdf
ደጃዝማች አያሌው በ20ኛው መክዘ ከተነሡት ኃያላን መኳንንት አንዱ ናቸው፡፡ የራስ ብሩ ወልደ
ገብርኤል ልጅና የእቴጌ ጣይቱ ዘመድ ሲሆኑ የወገራ አውራጃ ሹም፣ የስሜን አውራጃ ገዥ፣ ልጅ ኢያሱ ከተያዙ በኋላ ደግሞ የንጉሠ
ነገሥቱ ጦር አዛዥ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ደጃዝማች አያሌው ብሩ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ከፍተኛውን ሚና ከተጫወቱት ሰዎች
መካከል ናቸው፡፡ መኢሶ ላይ ከልጅ ኢያሱ ጦር ጋር በተደረገው ጦርነት ተፈሪ መኮንን እንዲያሸንፉ ደጃዝማች አያሌው ከፍ ያለ
ሚና ነበራቸው፡፡ ራስ ጉግሣን ለመያዝ አንቺም ላይ በተደረገው ውጊያም የደጃዝማች አያሌው ጀግንነት ወሳኝ ነበር፡፡ እንዲያውም
በዚህ ጦርነት ለሚያበረክቱት ውለታ የራስነትን ማዕረግ እንደሚያገኙ ከንጉሥ ተፈሪ ቃል ተገብቶላቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን በአንድ
በኩል የእቴጌ ጣይቱ ዘመድ በመሆናቸው፣ በሌላ በኩልም ከቀድሞዎቹ የዐፄ ምንሊክ ባለ ሥልጣናት ወገን ስለሆኑ ተፈሪ ቃላቸው
አጠፉባቸው፡፡