Thursday, April 30, 2015

የተለመዱ የአማርኛ ስሕተቶችና መፍትሔያቸው

ዳንኤል ክብረት
ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓም
ባሕርዳር
ለባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋም ምሥረታ ማብሠሪያ ቀን የቀረበ የማሳሰቢያ ሐሳብ

ዩአን ሊ የተሰኘ ጃፓናዊ Breaking the message, በተሰኘው የ2006 ዓም መጽሐፉ ላይ እንዲህ ይላል፡፡ በኢንዶኔዥያ ገጠሮች ውስጥ በሠራባቸው 7 ዓመታት የታዘበው ትልቁ የሕዝብ ግንኙነት ችግር ለሕዝቡ መልእክት ለማስተላለፍ የሚመጡት ባለሞያዎች መልእክታቸው ተሟልቶ ወደ ሕዝቡ ለመድረስ አለመቻሉ ነው፡፡ ለዚህ ችግር መፈጠር ምክንያት ናቸው ያላቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው መልእክቱ ለሕዝቡ በሚመጥን መልኩ ተዘጋጅቶ አለመቅረቡ ነው፡፡ የሚተላለፈው መልእክት የአስተላላፊውን ማንነት፣ የዕውቀት ደረጃ፣ የፖለቲካ ጠገግ፣ የተማረውን የትምህርት ዓይነትና የአስተሳሰቡን መጠን የሚያሳይ እንጂ ለመልእክት ተቀባዩ ታስቦ በደረጃውና በመጠኑ የቀረበ አይደለም፡፡

‹‹ምንም እንኳን ሥጋ ሥጋ ቢሆንም ለሕጻንና ለዐዋቂ ግን በእኩል መጠንና ዓይነት አይቀርብም፡፡ ሕጻኑ ጥርሱና የምግብ ማዋሐጃ አካሉ ስላልጠነከረ በቀላሉ ሊፈጨው በሚችለው መጠን ሥጋው ደቅቆ መቅረብ አለበት፡፡ ለዐዋቂው ግን ሥጋው ጠንክሮና በቅመማ ቅመም ዳብሮ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ሥጋ ግን ሥጋ ነው›› ይላል ዩአን ሊ፡፡ መልእክት ሲቀርብም ከአቅራቢው በላይ የሚቀርብለትን ወገን ዐቅምና ችሎታ፣ ደረጃና ፍላጎት የመጠነ መሆን አለበት፡፡ ምንም የመልእክቱ ይዘት ባይቀየርም፡፡ 

ሌላው ለመልእክቱ መሰበር ምክንያት ነው ብሎ የታዘበው ነገር ምሁራኑና ሌሎችም ሕዝቡ በማይገባው ቋንቋ መናገራቸው ነው፡፡ አቅራቢዎቹ ለምዶባቸው ወይም እነርሱ የተማሩት በእንግሊዝኛ በመሆኑ ያለበለዚያም (እንደ እኛ ሀገር የኛ ሙሽራ ኩሪባቸው በእንግሊዝ አናግሪያቸው የሚለው ዘፈን እነርሱም ጋር አለ መሰል) እንግሊዝኛ መቀላቀል የዕውቀትና የደረጃ ማሳያ አድርገውት፣ እንግሊዝኛውን ከኢንዶኔዥያ ቋንቋ ጋር (በነገራችን ላይ ኢንዶኔዥያ 700 ሀገራዊ ቋንቋ የሚነገርባት ሀገር ናት፤ ብዙዉ ሰው ‹ባሐሳ ኢንዶኔዥያ› የተሰኘውን ብሔራዊ ቋንቋ ይናገረዋል፡፡) እየቀላቀሉ በሚያስፈልገውም በማያስፈልገውም ስለሚጠቀሙ መልእክቱ እየተሰበረ እንዲደርስ አድርገውታል፡፡

‹‹በቴሌቭዥን ኳስ ስንከታተል›› ይላል ዩአን ሊ ‹‹የኳሱን ፍሰት ሳይቋረጥ መከታተል እንፈልጋለን፡፡ የቴሌቭዥን ጣቢያው  ይኼንን ትቶ በየመካከሉ ሙዚቃ እየጋበዘ ኳሱን ቢያስተላልፍልን የኳስ ጨዋታው ሙሉ ሥዕል አይኖረንም፡፡ ምናልባትም በመካከል ጎል ገብቶ፣ ተጨዋች በቀይ ወጥቶ፣ ግጭት ተፈጥሮ፣ ተጨዋች ተቀይሮ፣ አስደናቂ ወይም አሳዛኝ ክስተት ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህን ነገሮች አሳልፈን የምናየው ጨዋታ ግርታን ይፈጥራል እንጂ ደስታን አያመነጭም፡፡ በየመካከሉ ሕዝቡ የማይረዳውን ቋንቋ እየደባለቁ መልእክት ለማስተላለፍ መጣርም እንደዚሁ ነው፡፡ ድምፁን ለማስተላለፍ እንጂ መልእክቱን ለማስተላለፍ አይረዳም›› ይላል፡፡

እንዲያውም በአንድ በሰሜናዊ ኢንዶኔዥያ ክፍል ጥናት ሲያደርግ አንድ አዛውንት የነገሩትን እንደ ምሳሌ አስቀምጦታል፡፡ በዚያ መንደር ውስጥ አንድ የሕክምና ባለሞያ መጥቶ ለመንደሯ ሰዎች ስለ ኢንፍሉዌንዛ ገለጻ ያደርጋል፡፡ በገለጻው መካከል የአካባቢውን ቋንቋ ሱንዳኒዝንና እንግሊዝኛን እየደባለቀ ይናገር ነበር፡፡ መንደርተኞቹ ተቸገሩ፡፡ አንድ ሰውም ተነሡና ‹ልጄ፣ ወይ በእንግሊዝኛ ንገረንና ከመካከላችን ዕውቀቱ ያላቸው ይተርጉሙልን፤ ያለበለዚያ ደግሞ በአካባቢያችንን ቋንቋ በሱንዳኒዝ ንገረንና ያለ ችግር እንስማው›› ብለው አስተያየት ሰጡት፡፡ ከባለሞያው ይልቅ መንደርተኞቹ እንደሚቆራረጥ ስልክ መልእክቱ እየተሰበረ እንደደረሳቸው ገብቷቸዋል፡፡

አሁን አሁን በሀገራችን እየገጠመን ያለውም ልክ ዩአን ሊ በኢንዶኔዥያ የገጠመውን ዓይነት ነው፡፡ አማርኛን የሚናገር ሰው የጠፋ እስኪመስል ድረስ በአማርኛ መልእክት መለዋወጥ ከባድ እየሆነ ነው፡፡ የመልእክት ልውውጦቻችን በስሕተቶች የተሞሉ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ለእነዚህ ደግሞ ምክንያቶቻችን ሊሆኑ የሚችሉት አምስት ነገሮች ይመስሉኛል፡፡ የመጀመሪያው የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በሚገባ አለመሰጠቱ ነው፡፡ አማርኛ መማር የሚያውቁትን ነገር እንደገና መማር የሚመስላቸው የዋሐን ብዙዎች ናቸው፡፡ ለእንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና ጀርመንኛ ቋንቋዎች የሚሰጠውን ከበሬታ ያህል አማርኛን መማር ክብር አይሰጠውም፡፡ ዕውቀትም መስሎ አይታይም፡፡ ይህም በመሆኑም የአማርኛ  ንግግርና ጽሕፈት ክሂሎት ያለው ሰው ለማፍራት አልቻልንም፡፡ ወደፊት በዚሁ ከቀጠልን የምንፈጥራት ሀገር እንደ ጥቅመ ሰናዖር በማይግባቡ ሕዝቦች የተሞላች ትሆናለች፡፡  

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ግዴለሽት ነው፡፡ ለጽሑፍና ለንግግር መጠንቀቅ እየቀረ ይመስላል፡፡ ከአነጋገር ይፈረዳል ከአያያዝ ይቀደዳል ተብሎ ከተተረተ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ እንዳመጣ መናገር፣ እንደወረደ መጻፍ የማያሳፍርበት ደረጃ ላይ መደረሱ ይገርማል፡፡ ያልተማረው ሕዝብ ሳይቀር ለአነጋገሩ ተጨንቆ በዘይቤ፣ በተረትና ምሳሌ፣ በሰምና ወርቅና በአባባል እያዋዛ በሚናገርበት አገር ከተሜውና ተማረ የሚባለው ወገን ግን በገዛ ቋንቋው መናገር ሲያቅተው መመልከት ግዴለሽነቱ የደረሰበትን የካንሰር ደረጃ ያሳየናል፡፡

በአንድ ወቅት የጎጃም ጠቅላይ ግዛት ሲባል ደብረ ማርቆስ በሚገኘው የጠቅላይ ግዛቱ ፍርድ ቤት አንድ ሰው የፍርድ ቤት የጥሪ ደብዳቤ ይደርሳቸዋል፡፡ አቶ ሠረቀ ብርሃን ይባላሉ፡፡ ስማቸው በደብዳቤው ላይ የተጻፈው በእሳቱ ‹ሰ› ስለነበር በቀጠሮ ቀን ሳይቀርቡ ቀሩ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ደብዳቤ ቢጻፍላቸውም ቀሩ፡፡ በመጨረሻ በፖሊስ ተይዘው ቀረቡ፡፡ ዳኛው ‹ይኼ ደብዳቤ ደርሶዎታል› ብሎ ጠየቃቸው፡፤ ‹አዎን› አሉ፡፡ ‹‹ታድያ ለምን በቀጠሮ አልመጡም›› አላቸው ዳኛው ‹‹የተጠራሁት እኔ ስላልሆንኩ›› አሉ፡፡ ስምዎ ‹ሰረቀ ብርሃን አይደለም›› አለ ዳኛው›› ‹‹ነው›› አሉ ሰውዬው፡፡ ‹‹ታድያ ለምን ስሜ አይደለም አሉ›› ‹‹የእኔ ስም በንጉሡ ሠ እንጂ በእሳቱ ሰ አይጻፍም፡፡ እኔ የብርሃን ሌባ አይደለሁም›› ሲሉ ዳኛው ደነገጡና ይቅርታ ጠየቁ እየተባለ ይወራ ነበር፡፡       

በንጉሡ ጊዜ በንጉሣዊ አገዛዙ የተማረረ አንድ ሰው  ነበር፡፡ በአደባባይ ጉባኤ ላይ አንዲት ሴትዮ ‹ንጉሡ ሺ ዓመት ይንገሡ› ብላ ስትናገር ‹‹እኔ ለሃምሳ ዓመቱ መርሮኛል አንቺ ሺ ዓመት ትያለሽ›› ብሎ ተነሥቶ በጥፊ ይመታታል፡፡ ሕዝብ በተሰበሰበበት የተደረገ ነበርና ምስክር ተቆጥሮበት ይከሰሳል፡፡ ዳኛው ‹‹አድርገሃል ወይ›› ሲሉት ‹‹አዎ ተማትቻለሁ› አለ፡፡ ‹‹ለምን›› ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹ታድያ እኒህን የመሰሉ ንጉሥ ዘለዓለምስ ቢገዙ ምን ገዷት ነው በሺ የምትገድባቸው ብዬ ነው›› በማለቱ በነጻ ተለቀቀ ተብሎ ይወራል፡፡ ንግግር ዐዋቂ የሚባለው እንዲህ ያለው ነበር፡፡

በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ‹ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ግርማዊት ከእቴጌ መነን ጋር በተገኙበት› በሚለው ዜና ላይ ‹ገ› ተቆርጣ አርታዒው ሳያያት በመታተሙ ‹ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከእቴጌ መነን ጋር በተኙበት› ተብሎ ወጣ፡፡ በዚያ ሰበብ ብዙ ሰው እንደተቀጣ ይነገራል፡፡ ይኼ ሁሉ የተተረከው ያለ ጥንቃቄ የሚጻፉና የሚነገሩ ነገሮች የሚያስከፍሉትን ዋጋ ለማሳየት ነው፡፡ አስቦ፣ ቃላት ያላቸውን ዋጋና የሚያስከትሉትን ውጤት ገምግሞ፣ ተዘጋጅቶና መርጦ በአማርኛ የሚጽፍና የሚናገር ሰው እንደ ስሜን ዋልያ እየመነመነ መጥቶ በሙዝየም የምናይበት ዘመን መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥኮ በአጻጻፍ ስሕተት ብቻ ሁለት አየር መንገዶች ተፈጥረዋል፡፡ አንደኛው ሕግ የሚያውቀው ‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ› ሲሆን ሁለተኛው ስሑት ጸሐፊ የፈጠረው ‹ቦሌ አየር መንገድ› ነው፡፡ በቦሌ መንገድና በቀለበት መንገድ ላይ ‹ቦሌ አየር መንገድ› የሚል ታነባላችሁ፡፡ የሌለ አየር መንገድ፡፡ 
ሦስተኛው ደግሞ አንግሊዝኛ መቀላቀል የልምድም የክብርም ጉዳይ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡ እንግሊዝኛ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ለመግባባት የሚያስችል፣ ብዙ ቴክኖጂ የተሠራበትና የሚሠራበት፣ ዕውቀት በሰፊው የተጻፈበት፣ በብዙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርት የሚሰጥበት ቋንቋ ነው፡፡ አጥርቶና አርትቶ ማወቁ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ከጤፍ መካከል የተገኘ ስንዴ አረም እንደሚሆነው ሁሉ ከአማርኛ ጋር እንዴው ያለ ቦታውና ያለ አስፈላጊነቱ ሲደባለቅ ሥራው መልእክት መስበር ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ‹አባየ› አሳፍሮን ‹ዳዲ› የተመረጠው፡፡ ‹ፋዘሬ ማዘሬ› የዚሁ ውጤቶች ናቸው፡፡ ‹ባለሥልጣን› የሚለውን ቃል አስወጥቶ በ‹ኤጀንሲ› የተካው የሀገራችን መዋቅርም የዚህ ውጤት ነው፡፡ ‹ፈንድ› የሚል ተቋም በመጣበት ዘመን በየስብሰባው ‹ፈንዱ እንዲህ አድርጎ፣ ፈንዱ እንዲህ ሠርቶ› ሲባል ‹ኧረ ምን በወጣን እንፈነዳለን፣ የሚፈነዳ ይፈንዳ እንጂ› ያሉት ሰዎቹ ወደው አልነበረም፡፡

ብዙ ሰዎች በአዳራሽ፣ በስብሰባ ቦታዎች፣ በሚዲያ፣ ሌላው ቀርቶ በእምነት ተቋማት ሳይቀር እንግሊዝኛን እየቀላቀሉ መናገር፣ ልማድም፣ የዕውቀት ማሳያም አድርገውታል፡፡ ዐዋቂነት የሚሆነው ግን ወይ በአማርኛ ወይ በእንግሊዝኛ መናገሩ ነበር፡፡
አራተኛው ምክንያት ደግሞ ፖሊሲ ወይም አሠራር አለመኖሩ ነው፡፡ በሕዝባዊ ቦታዎች፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በአደባባይ በሚነገሩና በሚጻፉ ነገሮች፣ እንዴት ባለ መልኩ መናገርና መጻፍ እንደሚገባ ሀገራዊ ፖሊሲ ወይም አሠራር ሊኖር ይገባ ነበር፡፡ ለምሳሌ በሚዲያ የሚቀርቡ መልእክቶች የሚቀርቡበትን ቋንቋ በተመለከተ የሚዲያ ፖሊሲው ቁልጭ አድርጎ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ያ አሠራርም ባሕል እንዲሆን መደረግ አለበት፡፡ ባለሥልጣናት ለሕዝብ ንግግር ሲያደርጉ ወይም መግለጫ ሲሰጡ ሊከተሉት ስለሚገባ የቋንቋ ሥነ ምግባር ወጥ የሆነ አሠራር መኖር ነበረበት፡፡ በአደባባይ የሚለጠፉ መልእክቶችና ማስታወቂያዎችን በተመለከተም የቋንቋ አጠቃቀም መርሕ ሊወጣ ይገባ ነበር፡፡ ይኼ ባለመሆኑ ግን አሁን የምናየው ዝብርቅርቅ ነገር ተፈጥሯል፡፡ በአዲስ አበባ በአንድ ጥንታዊና ታዋቂ ምግብ ቤት ‹ምላስና ሰንበር› የሚለው ምግብ ‹ታንግ ኤንድ ሰንበር› ተብሎ ተጽፎ ነበር፡፡  
አምስተኛው ምክንያት ደግሞ አዳዲስ ሐሳቦች ወደ ቋንቋው ሲመጡ ስያሜ ቃላት የሚያዘጋጅ ወይም በፕሮፌሰር ባየ ይማም ቋንቋ ለመናገር ‹በቋንቋ ሥርዓት መሠረት ቃላትን የሚያዋልድ› አካል ወይም ተቋም አለመኖሩ ያስከተለው ጣጣ ነው፡፡ ከሰባ ዓመታት በፊት እግር ኳስ አዲስ ሐሳብ ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ እነ ይድነቃቸው ተሰማና ፍቅሩ ኪዳኔ መጀመሪያ ያደረጉት ነገር ለዛሬ ሥራችን ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ የእግር ኳስን ሕግ ወደ ኢትዮጵያ ሲያመጡ ለአያሌ የእግር ኳስ ሐሳቦች የአማርኛ አቻ ትርጉም ነው የፈጠሩት፡፡ ቡድን፣ በረኛ፣ ፍጹም ቅጣት ምት፣ የማዕዘን ምት፣ የመሥመር ውርወራ፣ ዳኛ፣ የመሥመር ዳኛ፣ አማካይ፣ አጥቂ፣ ተከላካይ፣ የመሳሰሉት ቃላትና ሐረጎች ያኔ የመጡ ናቸው፡፡ የሚያሳዝነው ያ ሁሉ እንዳልተለፋበት የዛሬ የስፖርት ጋዜጠኞች ‹ፔናሊቲ፣ ፔናሊቲ ቦክስ፣ ሪፈሪ፣ ዲፌንደር፣ ስኳድ፣ ቲም› እያሉ ወደ ኋላ ሲመለሱ መሰማታቸው ነው፡፡     
‹ለኢትዮጵያ ታሪኳ ነው መልኳ› በሚለው መጽሐፍ ንጉሤ አክሊሉ እንደሚተርከው ‹ከዛሬ ሃምሳ ዓመታት በፊት አፈ ሊቅ አክሊሉ ወልደ ቂርቆስ በማስታወቂያ ሚኒስቴር የአዲስ ዘመን ዋና ክፍል ሲሠሩ አዲስ ዘመን በእንግሊዝኛ ይወጡ እንደነበሩት ጋዜጦች ‹ኤዲቶርያል› አልነበረውም፡፡ በኋላ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ነጋሽ ገብረ ማርያም አፈ ሊቅ አክሊሉን ‹ይኼን ኤዲቶርያል የሚባል ቃል በአማርኛ ምን እንበለው?› ብለው ቢጠይቋቸው ‹አንቀጸ ትምህርት፣ አንቀጸ ጾም፣ አንቀጸ ምጽዋት፣ አርእስተ አንቀጽ፣ ርእሰ አንቀጽ የሚለውን ጠቅሰው የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ የሚጽፈው ዐቢይ መልእክት የሚሠፍርበት በመሆኑ ‹ርእሰ አንቀጽ› ብንለው በማለት የሰጡት ስያሜ ይኼው ዛሬም ሲሠራበት ይኖራል፡፡ ማዋለድ ማለት እንዲህ ነው፡፡
እስኪ ለዛሬው በአማርኛ ቋንቋ ንግግርና ጽሕፈት እየተለመዱ የመጡ ዐሥራ ሦስት የስሕተት ዓይነቶችን ላመልክት፡፡

1.      ሕገ ወጥ ጥምረት፡- ሕገ ወጥ ጥምረት የምንለው ሊጣመር በሚገባው መልኩ ባለመጣመሩ ትርጉም እየለወጠ የሚገኘውን አካኼድ ነው፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ከመለመዱ የተነሣ ስሕተትነቱ ሊጠፋ የደረሰው ‹እደ ጥበብ› ነው፡፡ ‹ሃንዲ ክራፍት› የሚለውን ለመተርጎም የምንጠቀምበት ‹እደ ጥበብ› እጁን እንጂ ሥራውን አይገልጥም፡፡ እደ ጥበብ ማለት የጥበብ እጅ ማለት ነው፡፡ ከሠሪው ጋር እንጂ ከሥራው ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ ትክክለኛው ‹ጥበበ እድ› ነው - የእጅ ጥበብ ለማለት፡፡ ልክ ተግባረ እድ - የእጅ ሥራ፣ ተግባር እንዳልነው ሁሉ፡፡ ‹ማስ ሚዲያ› የሚለውን ለመተርጎም የተጠቀምነው ‹ብዙኃን መገናኛ› የሚለውን ነው፡፡ እንግሊዝኛውን ቃል በቃል ወስደን፡፡ በአማርኛ ግን በሳድስ የሚጣመር ቃል የለም፡፡ በሳድስ ከተጣመረ ‹የ› ያስፈልገዋል፡፡ ‹የብዙኃን መገናኛ›፡፡ በራብዕ ግን ይጣመራል፡፡ ‹ዕንቆጳ ጽዮን› እንደሚለው፡፡ ይኼም ‹መገናኛ ብዙኃን› መሆን ነበረበት፡፡ ‹ዌብ ሳይት› የሚለውን ለመተርጎም ‹ገጸ ድር› መባል ሲኖርበት ‹ድረ ገጽ› በማለት እንዳለ እንግሊዝኛውን ወስደነዋል፡፡ ገጸ ድር ማለት የድሩን ገጽ የሚያሳይ ሲሆን ድረ ገጽ ማለት ግን የገጹን ድር የሚያመለክት ነው፡፡ ቅድመ ዝግጅት የሚለው ቃል ሁለት ተመሳሳይ ሐሳብ የያዙ ቃላትን ያጣመረ ነው፡፡ ቅድሚያ እና ዝግጅት፤ ሁለቱም ከሆነ ነገር በፊት የሚደረግን ነገር የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ዝግጅት ከአንድ ነገር በፊት የሚደረግ ከሆነ ለዝግጅት ምን ቅድሚያ ያስፈልገዋል?  

2.      ያለ ትርጉማቸው ቃላትን መጠቀም፡- አንዳንድ ጊዜ ከግእዝ የሚወሰዱት ቃላት በትክክለኛው ትርጉማቸው ሲገቡ አይታይም፡፡ ለዚህ የተለመደው ምሳሌ ‹ታዳጊ› የሚለው ቃል ነው፡፡ ‹ታዳጊ› ማለት ‹አዳኝ፣ ጠባቂ› ማለት ነው፡፡ ‹ታዳጊ ሀገር ሲል› የሚጠብቅ የሚያድን ሀገር ማለት ነው፡፡ ‹ታዳጊ ሕጻናት› ሲባልም ‹የሚያድኑ፣ የሚጠብቁ ሕጻናት ማለት ነው፡፡ ትክክለኛው አነጋገርና አጻጻፍ ‹አዳጊ› የሚለው ነው፡፡ መሃይምና ማዕቀፍም እንደዚሁ ናቸው፡፡ ‹መሃይም› አማኝ ማለት ሲሆን ‹ማይም› ግን ያልተማረ ማለት ነው፡፡ ‹ማዕቀፍ›ም ‹ፍሬም ወርክ› ለሚለው  መተርጎሚያ ነበር የተጠቀምንበት፡፡ ‹ማዕቀፍ› ግን ዕንቅፋት ማለት ነው፡፡ ‹ለፍሬም ወርክ› መተኪያው ቃል ማሕቀፍ - ነው፡፡ ‹ክብካቤ›ና ‹እንክብካቤ›ም ይኼው ዕጣ ነው የገጠማቸው፡፡ እንክብካቤ ማለት መደገፍ፣ ማጣደፍ፣ ማንቀርቀብ፣ ማንከባለል፣ ማድቦልቦል ማለት ነው፡፡ ‹አንከብክቤ አመጣሁት› እንዲል፡፡ መንከባከብን ለማሳየት ከሆነ ‹ክብካቤ› ነው መሆን ያለበት፡፡ የአካባቢ ክብካቤ መባል ሲኖርበት ነው ‹የአካባቢ እንክብካቤ› የሚባለው፡፡

3.     የብዙ ብዙ፡- ቃላትን በራሳቸው ቅርጽ ማብዛት ሲገባ ብዙ ብዙ ማድረግ አንድም የቃላት ኢኮኖሚን ያባክናል፣ አንድም ደግሞ መልእክትን ያቋርጣል፡፡ መላእክቶች፣ ኢትዮጵያውያኖች፣ አዕዋፋትና አዕዋፎች፣ አራዊቶች፣አታክልቶች ግእዝና አማርኛ የተቀላቀለባቸው የብዙ ብዙ ናቸው፡፡ ወይ በግእዙ ሄዶ አዕዋፍ፣ አራዊት፣ እንስሳት፣ ዕጽዋት፣ መላእክት ማለት ወይ በአማርኛው ሄዶ ኢትዮጵያዊዎች፣ ወፎች፣ አውሬዎች፣ እንስሶች፣ እንጨቶች፣ ተክሎች ማለት ይቻል ነበር፡፡ በተለይም አማርኛ የሶፍት ዌር ቋንቋ ሲሆን አንዱ ችግር ፈጣሪዎች እነዚህ ሕገወጥ ነገሮች ናቸው፡፡  

4.     አላስፈላጊ ሰረዝ፡- ከእንግሊዝኛ ሥርዓተ ጽሕፈት ወስደነው እንደሆነም እንጃ እርስ በርሳቸው በሚናበቡ ቃላት መካከል አላስፈላጊ ሰረዝ ማስገባት በአማርኛ ጽሕፈት ውስጥ እየተለመደ በጋዜጣና በመጻሕፍት ውስጥ በብዛት እያየነው ነው፡፡ ኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ፣ ግብረ ገብ፣ መርሐ ግብር፣ ቤተ ሰብእ፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ቤተ መንግሥት የሚሉት በራሳቸው ተናበው ሊቆሙ የሚችሉ ጥምር ቃሎች ናቸው፡፡ አሁን አሁን ግን በመካከላቸው ሰረዝ ገብቶ ኪነ - ጥበብ፣ ሥነ - ጥበብ፣ ቤተ - መንግሥት እየተደረጉ በመጻፍ ላይ ናቸው፡፡ ይኼ ጉዳይ ሥራን ከማብዛት፣ ጊዜን ከመጨረስና ቦታን ከመውሰድ ውጭ የሚሰጠው ተጨማሪ ጥቅም የለም፡፡

5.     አላስፈላጊ እንግሊዝኛ፡- ይኼኛው በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ የገባ ወረርሽ ነው፡፡ ምንም ከማያስፈልጉት እንደ ‹ስቲል - እስካሁን፣ ታንክ ዩ- አመሰግናለሁ፣ ኦፍ ኮርስ- ይሔ ነገር፣ ሪሊ› ካሉት ጀምሮ በየንግግራችን መካከል እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ የሚሉት ምክንያት አልባ እንግሊዝኛዎች ብዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶች ይኼንን ከቋንቋ ንጽሕና ጋር ያያይዙታል፡፡ እንዲያ ግን አይደለም፡፡ የማያውስና የማይዋስ ቋንቋ የለም፡፡እንግሊዝኛ ከብዙ ቋንቋዎች ተውሷል፡፡ ነገር ግን ውሰት ምክንያትና ሕግ አለው፡፡ በአማርኛ ‹ቤት› የሚለውን ቃል ያህል ሁሉም ቦታ የሚገባ የለም፡፡ ቤተ ሰብ፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ቤተ መንግሥት፣ ቤተኛ፣ ቤቶች፣ ግምጃ ቤት፣ ምግብ ቤት፣ እሥር ቤት፣ ሙዚቃ ቤት፣ ጽሕፈት ቤት፣ ወዘተ፣ ወዘተ፡፡ እንዲህ በዝቶና ሞልቶ የሚገኘው ቤት ግን  በነ ‹ጃምቦ ሐውስ› በነ ‹ዲ.ኤስ. ቲቪ ሐውስ›፣ ‹ቪዲዮ ሐውስ፣ ኮፊ ሐውስ› በእንግሊዝኛ ተጽፎ ማየት ለስምንተኛው ሺ መድረስ ምልክት ለመሆን ካልሆነ በቀር ሌላ ምክንያት የለውም፡፡  

6.     የ‹የ› ቤት ጣጣ:- በአማርኛ አጻጻፍ ውስጥ ግእዙ ‹የ›ና ኀምሱ ‹ዬ›፣ ሳልሱ ‹ዪ›ና ሳድሱ ‹ይ› ሲምታቱ ይታያሉ፡፡ ‹ባየ› ስንል ግእዙን ‹አባዬ› ስንል ግን ኀምሱን መጠቀም አለብን፡፡ ‹ዬ› ባለቤትነትን ስለምታመለክት፡፡ ‹ሰውዬ› ስንል ኀምሱን ‹ምን አየ?› ስንል ደግሞ ግእዙን፡፡ አሁን አሁን የኀምሱ ‹ዬ› ቦታ በግእዙ ‹የ› እየተወሰደ ነው፡፡ ‹ዪ› አንስታይን ለማመልከት የምትውል ነበረቺ፡፡ ‹እዪ፣ ብዪ ፣ ነዪ፣ በዪ፣ ሳዪ› ስንል አንቺ የሚለውን ባለቤትና እርሷም ሴቴ ጾታ መሆንዋን ያሳያል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በሳድሱ ‹ይ› እየተተካ ‹ብይ፣ እይ፣ ነይ፣ በይ› እየተባለ መጥቷል፡፡ ገቢ፣ ሠሪ፣ ወጪ እንደሚለው ሁሉ ‹ባዪ› መባል ሲገባው ‹እኔ ባይ› ተብሎ ይጻፋል፡፡

7.     የጨ ቤት ጣጣ፡- እንደ ‹የ› ሁሉ ‹ጨ›ም ኀምሱና ግእዙ፣ ሳልሱና ሳድሱ እየተምታታ ነው፡፡ ‹መሳጭ› ስንል ሳድሱን፣ ‹ጠጪ› ስንል ደግሞ ሳልሱን እንጠቀማለን፡፡ ‹ገልብጬ› ስንል ኀምሱን፣ ‹ሙጨ› ስንል ግእዙን እንጠቀማለን፡፡ አሁን አሁን ግን ሳልሱ ‹ጪ› በሳድሱ ‹ጭ›፣ ኀምሱ ‹ጬ› በግእዙ ‹ጨ› እየተተካ ነው፡፡

8.     የወ ቤት ጣጣ፡- በ‹ወ› ቤት ውስጥ ለአማርኛ ጸሐፊዎች አምታች የሆነው ካልኡና ሳድሱ ናቸው፡፡ ካልኡ ‹ዉ› ከሥር ነው ቅጥሉ፤ ሳድሱ ደግሞ ‹ው› ከሆነ ደግሞ ከጎን፡፡ አሁን አሁን ግን ካልኡ ‹ዉ› እየጠፋ አብዛኛው ሰው በሳድሱ ‹ው› እየተካው ነው፡፡ ካልኡ ‹ዉ› መስተአምር ነው፡፡ ‹ሰውዬዉ፣ ደንበኛዉ፣ መሄጃዉ› ሲባል በካልኡ ‹ዉ› መጻፍ አለበት በተለየ የታወቀን ነገር እያመለከተ ነውና፡፡ ‹ሰው› ሲጻፍ ግን ሳድሱ ነው፤ መስተአምር ስለሌለው፡፡

9.     ቀጥታ ትርጉም፡- ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የምንመልሳቸውን ሐሳቦች በአማርኛ ባሕል መሠረት ከመተርጎም ይልቅ እንዳለ ቃል በቃል ስንተረጉማቸው አንዳንዴ ስሜት አይሰጡም፡፡ happy new year- መልካም አዲስ ዓመት፣ take a chair፣ ወንበር ውሰድ፣ please drop me there - ጣለኝ፤ pick me - አንሣኝ፣ I will see you later - በኋላ አይሃለሁ› የሚሉት በአማርኛ ባሕል ትርጉማቸው እንደ እንግሊዝኛው አይደለም፡፡ በኛ ባሕል እንኳን አደረሰህ እንጂ መልካም አዲስ ዓመት የሚባል የመልካም ነገር መግለጫ የለም፡፡ በዚህ የተነሣም መልሱ ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ተቀመጥ እንጂ ወንበር ውሰድ፣ አድረሰኝ እንጂ ጣለኝ፣ ውሰደኝ እንጂ አንሣኝ ሌላ ነው ትርጉማቸው፡፡

10.   የአሕጽሮት ደንብ አለመኖር፡- በአማርኛ አሕጽሮትን ስንፈጥር ልንመራበት የሚገባን ገዥ ደንብ የለንም፡፡ በዚህ ምክንያት ትርጉም የማይሰጡ፣ ለጥሪ የማይመቹ፣ ሲብስም ትርጉም የሚቀይሩ አሕጽሮቶች እናያለን፡፡ በአንድ ወቅት ‹ግምማዕድ› ተብሎ የሚጠራ የግብርና ምርምር ድጅት ነበረ፡፡ በአማርኛ ‹ግምማዕድ› መልካም ትርጉም የለውም፡፡

11.     ወጥ የፊደል አጻጻፍ ሥርዓትን አለመከተል፡- በአማርኛ ፊደሎች ስንጽፍ ሞክሼ ቃላት የሚባሉትን በተመለከተ ሁለት ዓይነት አማራጭ አለን፡፡ የመጀመሪያው ሁሉን ፊደል ለተገቢው ቃል መጠቀም ነው፡፡ሀ፣ሐ፣ኀ፣ኸ፣ ሠ፣ሰ፣አ፣ዐ፣ጸ፣ፀ የሚገቡበት አግባብ አላቸው፡፡ ይህንን ጠብቆ መጻፍ ነው፡፡ ይህንን አልቀበልም የሚል ደግሞ ወጥ የሆነ አጻጻፍን መምረጥ አለበት፡፡ ሀብትን ሲፈልግ በሀ፣ ሲፈልግ በሐ፣ ሲፈልግ በኀ መጻፍ የለበትም፡፡ መምረጥ አለበት፡፡ ሌሎችን እንዲሁ፡፡ አንድ ወጥ ሥርዓትን መከተል ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ባለመሆኑ መልክዐ ፊደሉ የተበላሸ ሥርዓተ ጽሕፈት እያየን ነው፡፡ በተለይም የአማርኛ የቋንቋ መሣሪያዎችን (language technologies) እንሥራ ስንል አንዱ አስቸጋሪው ነገር ይኼ ነው፡፡    

12.    በእንግሊዝኛ እያሰቡ በአማርኛ ማውራት፡- የቋንቋ አንዱ ጥቅም ማሰቢያነቱ ነው፡፡ ስንናገር ወይም ስንጽፍ ባሕሉ፣ አባባሉ፣ ተረቱ፣ ምሳሌው፣ ዘይቤው የሚመጣልን በራሱ በቋንቋው የምናስብ ከሆነ ነው፡፡ አሁን አሁን ግን የምናነባቸው የማኅበራዊ ሚዲያም ሆኑ የመረጃ ምንጮቻችን በእንግሊዝኛ የተጻፉ በመሆናቸው በእንግሊዝኛ እያሰብን በአማርኛ ነው የምናወራው፡፡ ‹ከዚህ በተጨማሪ›  የሚለው ጠፍቶን ‹ፕላስ› የምንለው፤ ‹ወዘተ› ጠፍቶን ‹ኤንድ ሶ ኦን› የምንለው፤ ‹እባክህ› ጠፍቶን ‹ፕሊስ; የምንለው፤ ቡድን ጠፍቶን ‹ቲም›፣ ሂደት ጠፍቶን ‹ፕሮሰስ› የምንለው የምናስበው በእንግሊዝኛ በመሆኑ ነው፡፡ እንዲህ የሚያስቡ ሰዎች አማርኛ ሐሳባችንን በሚገባ አይገልጥልንም ብለው ያስባሉ፡፡ እንደ ሳይንሱ ከሆነ ግን ቋንቋ በራሱ ምሉዕ ነው፤ ምሉዕም አይደለም፡፡ ምሉዕ ነው ሲባል የራሱን ሕዝብ ለማግባባት በቂ ነው ማለት ነው፡፡ ምሉዕ አይደለም ሲባል ደግሞ በዓለም ላይ ያሉ ነገሮችን ሁሉ ሊገልጥ የሚችል አንድ ብቸኛ ቋንቋ የለም ማለት ነው፡፡ ሐሳቡን በአማርኛ የሚያቀርብ ሰው አስቦ የሚጽፍና የሚናገር ከሆነ በተቻለው መጠን ቃሉን ለመተርጎም፣ ካልቻለም ደግሞ ሐሳቡን ለመተርጎም መሞከር አለበት፡፡ ‹ቢኮዝን›ም፣ ‹ኤንድ› ንም፣ ‹ኦፍ ኮርስ› ንም፣ ‹ቱዴይ›ንም አንዳለ ማስቀመጥ ግን ሕመም እንጂ ችግር አይሆንም፡፡

13.    ሐሳባቸው የማይቀና ቃላት፡- አንዳንድ ጊዜ የእንግሊዝኛውን ሐሳብ ለመተርጎም ተብለው የሚፈጠሩ ቃላት በአማርኛ ባሕልና አገባብ አስገራሚ ትርጉም የሚሰጡበት ጊዜ አለ፡፡ ለዚህ ቀላሉ ማሳያ ‹ሥር ነቀል ለውጥ› የሚለው ሐረግ ነው፡፡ አንድ ሥር ከተነቀለ በኋላ ምን ለውጥ ይኖረዋል፤ ከኖረውም መድረቅ ነው፡፡ እንዴት ሆኖ ሥር የሚነቅል ለውጥ በአማርኛ አዎንታዊ ሐሳብ ይሆናል? ቋንቋ ማሰቢያም የአስተሳሰብ ማሳያም ነው፡፡ ‹ሥር ነቀል ለውጥ› የሚለው ጥምር ቃል የመጣው በአብዮት ልጆች ነው፡፡ ‹ሥር ነቅሎ ለመለወጥ› ስለምናስብ ይሆን ለውጣችን በአንዱ መቃብር ላይ ሌላውን የሚያመጣ እንጂ አንዱ በሌላው ላይ የሚገነባ ያልሆነው?
እነዚህ ለማሳያ የቀረቡ ናቸው፡፡ ምሁራኑ ልክ በእንግሊዝኛ ‹common Mistakes in English > እንደሚለው ያለ ለሁላችንም የሚሆን ነገር ሊያዘጋጁ የሚገባበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ሚዲያዎቻችንንና ባለ ሥልጣኖቻችንን የሚገዛ የሥነ ምግባር ደንብም ያስፈልጋል፡፡ የአማርኛ ትምህርት ጉዳይም ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ ያለ ቋንቋ ዕድገት ሌሎች ዕድገቶች ሊሳለጡ አይችሉም፡፡ የሚግባባ ኅብረተሰብ ለመፍጠር የሚያግባባ ቋንቋ ያስፈልጋልና፡፡ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ እንደጀመረውም የአማርኛ ቋንቋን በተለየ የሚያጠኑ፣ ሥርዓት የሚያወጡ፣ ደረጃ የሚሰጡ፣ የሥነ ምግባር ደንቦችን የሚያዘጋጁ፣ ሐሳቦችን የሚያፈልቁ ተቋማት ይሹናል፡፡ ካልሆነ ግን የሀገሬ ገበሬ
ሀገርሽ ምንኛ መንደርሽ ምንኛ
አላውቅበት አልኩኝ ያንቺን አማርኛ
ያለው ነገር ይደርስብናል፡፡    
 

27 comments:

 1. ይገርማል የልቤን ነው ያስቀመጥከው እግዚአብሔር ዕድሜና ጤና ይስጥህ አሁን አሁንማ ለፊደል ይጨነቃሉ የተባሉት የቤተ ክህነት ሰዎችም የሚያስነብቡን ጽሑፎች አንጀት የሚያሳርሩ እየሆኑ መጥተዋል ትርጓሜ የሐዩ ንባብ ይቀትል ነውና ይታሰብበት።

  ReplyDelete
 2. leg thfe melkam nber gen tweledew bahnew sat ylew knant ketlew ytweledew babzgaw ytmarew fedel yktarew kb slehn h hu blow gamerow ytmare bzwem sllala kwenkaw bwlegaged aydnekh cheresw endtef enge!! wa yamrez neger aywera man lyremwen lqanqaw ymysben bagerew qanq ymeqrqern ymystkakelwe begaz blh qslan slnkhwe bch tngerq ing towez leg bezw new trekwe yamerza neger!!

  ReplyDelete
 3. ዲያቆን ዳኒ መድሃሂያለም ጥበቡን ይጨምርልህ አሜን!ለብዙዎቻችን የሚያሰፈልገን መልዕክት ነው ያሥተላለፍክልን. በአማርኛ ቋንቋ መናገር የሚያሳፍረ
  መሰሎ የሚታይበት ጊዜ እየደረሰን ነው.ሁላችንም የሚጠበቅብንን እናድርግ ለውጥ እናመጣለን.በቋንቋችን እንናገር, እናንብብ ,እንፃፍ እንኩራ !ዲያቆን ዳኒ, መድሃሂያለም ይጠብቅህ አሜን!!!

  ReplyDelete
 4. እግዚአብሄር እድሜህን ይባርክልህ
  አገራችን መከበሪያችን ነች ለምናምንበትና ለምንወዳት ፡ለምን ? ቋንቋችን የራሳችን ፣ታሪካችን የራሳችን (እንደ አሁኑ ሳይሆን)እንዲሁም ባህላችን የራሳችን ያልተዋስነው! በመሆኑ
  ታዲያ ምኑ የሚያሳፍረን መኩራትና መጠቀም ነው እንጂ አምላክ የሰጠንን ሀብት
  እናስብበት ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ለማድረግ 400 አመት ይወስዳል የተባለው እንዳይሆን እውነት ተፋቅረን እንኑር ከቻልን በ40 አመት
  አመሰግናለው ዳኒ መተንፈሻችን ነህ
  የሚገባው ይግባው ያልገባው ይፀልይ

  ReplyDelete
 5. Yehagerachin biherawi kuankua minchn ena meseret ye'ethiopia orthodox tewahido betekirstian mehonuan bezih lib yilual.

  ReplyDelete
 6. Batam yegrmal gen Amargn la tanagarew english eyadbalq menagrw nagr tekkel endalhon ba hola yamyamtawen gudat la tanagrew mahbarsab ba talayayu media mastamar alben .

  ReplyDelete
 7. ጥሩ ተመልክተሃል ጥንቃቄ ካልተደረገ ንባብ እስከ ዛሬ ከገደለው ይልቅ የነገው አገዳደል የከፋ ይሆናል።

  ReplyDelete
 8. ሀገርሽ ምንኛ መንደርሽ ምንኛ
  አላውቅበት አልኩኝ ያንቺን አማርኛ
  ያለው ነገር ይደርስብናል፡፡

  ReplyDelete
 9. Media=megenagna bizuhan

  ReplyDelete
 10. ‹ዌብ ሳይት› ን የገጽ ድር አይገልጸውም ማለት ነው?

  ReplyDelete
 11. Very well written article. Thank you Dn. Dani and I hope you will prepare a book on this topic soon, God willing.

  ReplyDelete
 12. አማርኛችን ይኼን ሁሉ በሽታ ሲያስተናግድ ኖርዋል ለካን። በሽታው ሁሉ አሁን ካንሰር ደረጃ ደርሷል።
  የሕክምና ርብርብ ያስፈልገዋል። የዚህ ካንሰር ልዩ ባለሙያዎች የቋንቋ ጥናት ባለሙያዎች እና የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ናቸው። በሉ እናንተ ተረባረቡ እኛ መድኃኒቱን ተከታትለን እንወስዳለን/ምክራች ሁን ተግባራዊ እናደርጋለን/።

  ግን ዲያቆን ዳንኤል በአንዳንድ ነጥቦችህና ምሳሌዎችህ አልተስማማሁም
  ለምሳሌ ቦሌ አየርመንገድ የስህተት ምሳሌ መሆን የለበትም። ቦሌ አየርመንገድ የ አውሮፕላን ማረፊያው መጠሪያ በመሆኑ የመንገድ ላይ ምልክት መሆኑ ተገቢ ነው እላለው ምክንያቱም በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የሚስተናገደው የኢዮጵያ አየር መንገድ ብቻ አይደለም።

  ሌላው፣ ሥርነቀል ለውጥ የሚለው ትችት ነው። በኔ አመለካከት ሥርነቀል ለውጥ ተገቢ ቃል ነው ምክንያቱም፤ ለውጥ የሚለው የአስተዳደር ርዕዮትን በሌላ ርዕዮተ ዓለም መተካትን ለመግለጽ የቀረበ ሃሳብ ነው እኔ እንደተረዳሁት። እንግዲህ መለወጥ እና መተካት ተወራራሽ አይደሉም ብለን የምንል ከሆነ በምሳሌህ እስማማለው። አለበለዚያ ግን ሥርነቀል ለውጥ ሲባል ፊውዳሊዝም ያልተቀላቀለበት ሙሉ በሙሉ አዲስና ልዩ የሆነ የሶሻሊዝም ሥርዓት ማምጣትን ወይም ማስተዋወቅን ያመለክታል በደርግ ምሳሌ ካየነው /የሶሻሊስም ደጋፊ አለመሆኔ ይታወቅልኝ/።

  መልካም ብለሃል በጥቅሉ። ትችትህ መሬት ጠብ አይበል፤ በሁሉ ልብ ይደር።

  ReplyDelete
 13. ዳኒ! እግዚአብሔር ያገልግሎትህን ዘመን ይባርክልህ፡፡ከዚህ የዳሰሳ ጥናትህ ብዙ ነገር ተምርያለሁ፡፡

  ReplyDelete
 14. This works for all languages too!! Do not focus only on Amharic

  ReplyDelete
 15. Woy amargna bekumsh moteshal!

  ReplyDelete
 16. ዳኒ! እግዚአብሔር ያገልግሎትህን ዘመን ይባርክልህ፡፡ከዚህ የዳሰሳ ጥናትህ ብዙ ነገር ተምርያለሁ፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. "የሚዲያ ፖሊሲው" = አቻ ቃል ያስፈልገዋል::

   Delete
  2. "የቋንቋ ሥነ ምግባር"

   Delete
 17. "የአማርኛ የቋንቋ መሣሪያዎችን (language technologies) እንሥራ ስንል አንዱ አስቸጋሪው ነገር ይኼ ነው፡፡"
  ምነው ዳኒ እራስህ ደገምከው እኮ።

  ReplyDelete
 18. lአላዋቂ እነደቆላው በተባደላነቱ ጥራጥቅ የበዛበት ጣዕሙም እንደማይታወቅ ቡና አማርኛም እነዲኹ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለዘመናት ይዞት የመጣውን ለዛ እና ጣዕም ቋንቋዊ ባሕሉን እያጣ መምጣቱ ያሳዝነኛል፡፡ ከ ነው ይልቅ ነበር ለማለት መጣደፋችን ወደፊት የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽእኖ አሌ የማይባል ይመስለኛል፡፡ ዳኒ ነገሩን ስላነሳኸው የተሰማኝን እገልጽ ዘንድ ወደድኍ እንጂ እኔ ስለ አማርኛ ቋንቋ ጠለቅ ያለ እውቀት ኖሮኝ አይደለም፡፡ ይገርማል …….. ምሁራን እንኳን የነበረውን ጠብቀዋል ተብለው ስማቸው ከሚነሳ ይልቅ የነበረውን በማጥፋታቸው መወቀስን መርጠዋል፡፡ ፊተኞቹ ጠበብት ፊደላትን እንዴት እንደቀረጹ ለምን እንደቀረጹ መቼ እነደቀረጹ ሙያዊ ትንታኔ ከመስጠት ይልቅ ( በዘርፉ ሥራ አልተሠራም እያልኩ አይደለም) ለአንድ ድምጽ ኹለት አልያም ሦስት ፊደላትን ቀርጸዋል ብሎ መውቀሱ የኋለኞቹን ጠበብት በዘርፉ ላይ ያላቸውን የእውቀት ምጣኔ ውሱኑነት የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ የፊደላቱ አቀራረጽ ላይ ሃይማኖታዊ ይዞታ ኖረውም አልኖረውም የየትመጣነቱን እውነታ መግለጽ እና እስከዛሬ ድረስ ጠብቆ ያቆየውንም አካል (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ማለቴ ነው) ተገቢዉን ምስጋና መቸር አስፈላጊ ነው፡፡
  ከአንድ ማኅበረሰብ የፈለቀ ምሁር ከዚያ ከወጣበት ቀየ ባሻገር እሴትነቱ ለሀገራችንም እንደመኾኑ መጠን ምንም እንኳ ዘመናዊ ትምህርት ቢያጠናም የራሱን ማጥላላት አለበት ብሌ አላስብም፡፡ ላልተማረው ግን ለውጥ እንዲያመጣለት ላስተማረው ማኅበረሰቡ በማናቸውም ረገድ ያለውን መልዕክት ሲያስተላልፍ አድማጩ በማያውቀው ቋንቋ መናገሩ ኾነ ባዕድ ቋንቋ መቀየጡ ከመዘላበድ ያለፈ ቁም ነገር ያዘለ መልዕክት ለማስተላልፉ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም ፡፡ ምክንያቱም የተናገረበት ቋንቋ ለአድማጩ ባዕድ ነውና፡፡ ለማሳያ ያህል በጽሑፍ ላይ የጠቀስኸው የኢንዶኔዢያው፤ የደብረማቆሱ ……. ወዘተ በቂ ይመስለኛል፡፡
  ዳኒ የዘመናዊ ትምህርቱም ቢኾን ከዘመኑ ሥልጣኔ አብሮ እንዲዘምን በሚል ሰበብ (አብሮ መዘመኑ ጥሩ ኾኖ ሰለ) ማንነትን አስረስቶ ሌላነትን ፤ ከውስጣዊ ይልቅ አፍአዊ እንድንናፍቅ ድርጎናል፡፡ ልጆቻቸውን አለማቀፋዊ ይዘትነት አለው ተብሎ በሚታመን ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያስተምሩ ባለሥልጣናት በበዙበት ሀገር ማንነትን ያማከለ ትምህርት ተቀረጾ ይተገበራል ማለት ዘበት ነው፡፡ ከአገልግሎቱ ይልቅ አምልኮቱ የበዛበት የባዕድ ቋንቋ ይዘን እየተጓዝን ስለኾነ ትናት የነበረች ኢትዮጵያን በዛሬ እሳቤ ለነገ ማቆየቱ ትልቅ የቤት ሥራ ይመስኛል፡፡ ለዚኽ ኹሉ ተጠያቂ ማንም ይኹን ማን ወደ ራስ ማንነት የምንመለስበት ዕቅድ ያስፈልጋል፡፡ እዚኽ ላይ ግን የባዕድ ቋንቋ መማር አይጠቅምም እያልኩ አይደለም ዋናው ግን አጠቃቀማችን ነው ፡፡ ጫካ ውስጥ ያለ ሽፍታ በቢለዋ የሰው ቋንጃ ስለቆረጠ አልያም አንገት ስለቀተለበት እናቶች ቢለዋን ከማዕድ ቤታቸው አውጥተው ይጣሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡
  በተለይ ደግሞ ዳኒ በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ ቃላት ከግድፈታቸው ጸያፍ ብዜታቸው የቃላት አጠቃቀማቸው እንዴት ይቀፍፋል ለምሳሌ ውኃ ይፈሥሣል ተብሎ የሚጻፈውን ውኃ ይፈሣል በማለት ውኃን ፈሳም (ይቅርታ) ማድረጋቸው፡፡ የኼ በማጥበቅና በማላላት የሚነበብ ሳይኾን እህዲኽ አይነቱን ቃል አባት ዘር ግንዱን ለማወቅ ይመስላል፡፡ ቢኾም ግን ለብዙኃኑ ማኅበረሰብ መገናኛ እንደመኾናቸው መጠን የተቻላቸውን ጥረት ቢያደርጉ ቢያስመሰግናቸው እንጂ የሚያስኮንናቸው አይኾንም፡፡ አንተም እንደጠቀስከው ከግዴለሽነታቸው የተነሣ በቋንቋው እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ ቢዘገይም መድረስ የሚቻልበትን ያኽል ለመድረስ የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ያደረገውን ዥማሮ አደንቃለኍ፡፡ አንተንም ይኽንን ዥማሮ በዚኹ ገጸ ድርህ ስለከተብክልን ሳላመሰግንህ አላልፍም ፡፡ ዳኒ በርታ እግዚአብሔር ይርዳህ፡፡ እውነትን መሀከላቸው አቁመው "እውነት ምንድነው?" ብለው ከሚጠይቁ ሰዎች(ጠቢባን) አምላከ ቅዱሳን ይጠብቅህ ፡፡

  ReplyDelete
 19. ‘‘ብዙ ሰዎች በአዳራሽ፣ በስብሰባ ቦታዎች፣ በሚዲያ፣…’’
  ‘‘አራተኛው ምክንያት ደግሞ ፖሊሲ ወይም አሠራር አለመኖሩ ነው፡፡ በሕዝባዊ ቦታዎች፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በአደባባይ በሚነገሩና በሚጻፉ ነገሮች፣ እንዴት ባለ መልኩ መናገርና መጻፍ እንደሚገባ ሀገራዊ ፖሊሲ ወይም አሠራር ሊኖር ይገባ ነበር፡፡ ለምሳሌ በሚዲያ የሚቀርቡ መልእክቶች የሚቀርቡበትን ቋንቋ በተመለከተ የሚዲያ ፖሊሲው ቁልጭ አድርጎ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡…’’
  ዲያቆን ዳንኤል አንተ እራስህ ለአንድ ዓይነት ቃል ሁለት ዓይነት አጠቃቀም መጠቀምህን ልብ ብለኸዋል? ሚዲያ የሚለው ቃል እና መገናኛ ብዙኃን፡፡ በነገራችን ላይ መገናኛ ብዙኃን ወይስ የብዙኃን መገናኛ ነው የሚባለው?

  ReplyDelete
 20. ሀገርሽ ምንኛ መንደርሽ ምንኛ
  አላውቅበት አልኩኝ ያንቺን አማርኛ
  ያለው ነገር ይደርስብናል፡፡

  ReplyDelete
 21. ሀገርሽ ምንኛ መንደርሽ ምንኛ
  አላውቅበት አልኩኝ ያንቺን አማርኛ
  ያለው ነገር ይደርስብናል፡

  ReplyDelete
 22. ሀገርሽ ምንኛ መንደርሽ ምንኛ
  አላውቅበት አልኩኝ ያንቺን አማርኛ
  ያለው ነገር ይደርስብናል፡፡

  ReplyDelete
 23. በጣም አስፈላጊ ትምህርት ነው፡፡

  ReplyDelete
 24. አሳስባለው https://www.penpaland.com ቋንቋ ልውውጥ ላይ የተመሠረተ ድር ጣቢያ
  Android:http://app.appsgeyser.com/Penpaland

  ReplyDelete