ዳንኤል ክብረት
ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓም
ባሕርዳር
ለባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ
ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋም ምሥረታ ማብሠሪያ ቀን የቀረበ የማሳሰቢያ ሐሳብ
ዩአን ሊ የተሰኘ ጃፓናዊ Breaking the message, በተሰኘው የ2006 ዓም መጽሐፉ ላይ እንዲህ ይላል፡፡ በኢንዶኔዥያ ገጠሮች ውስጥ በሠራባቸው 7 ዓመታት የታዘበው ትልቁ የሕዝብ ግንኙነት ችግር ለሕዝቡ መልእክት ለማስተላለፍ የሚመጡት ባለሞያዎች መልእክታቸው ተሟልቶ ወደ ሕዝቡ ለመድረስ አለመቻሉ ነው፡፡ ለዚህ ችግር መፈጠር ምክንያት ናቸው ያላቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው መልእክቱ ለሕዝቡ በሚመጥን መልኩ ተዘጋጅቶ አለመቅረቡ ነው፡፡ የሚተላለፈው መልእክት የአስተላላፊውን ማንነት፣ የዕውቀት ደረጃ፣ የፖለቲካ ጠገግ፣ የተማረውን የትምህርት ዓይነትና የአስተሳሰቡን መጠን የሚያሳይ እንጂ ለመልእክት ተቀባዩ ታስቦ በደረጃውና በመጠኑ የቀረበ አይደለም፡፡
‹‹ምንም እንኳን ሥጋ ሥጋ ቢሆንም ለሕጻንና ለዐዋቂ ግን በእኩል መጠንና ዓይነት አይቀርብም፡፡ ሕጻኑ ጥርሱና የምግብ ማዋሐጃ አካሉ ስላልጠነከረ በቀላሉ ሊፈጨው በሚችለው መጠን ሥጋው ደቅቆ መቅረብ አለበት፡፡ ለዐዋቂው ግን ሥጋው ጠንክሮና በቅመማ ቅመም ዳብሮ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ሥጋ ግን ሥጋ ነው›› ይላል ዩአን ሊ፡፡ መልእክት ሲቀርብም ከአቅራቢው በላይ የሚቀርብለትን ወገን ዐቅምና ችሎታ፣ ደረጃና ፍላጎት የመጠነ መሆን አለበት፡፡ ምንም የመልእክቱ ይዘት ባይቀየርም፡፡