Thursday, March 19, 2015

ሸዋ ረገድ ገድሌየምታስፎክር ሰንጋ ገለሌ
በጦር መካከል ሳይሆኑ አያሌ
በጥይት ገዳይ ነጭ ብርገድሌ
የሴት ወንድ ናት ሸዋረገድ ገድሌ
ተብሎ የተገጠመላቸውን፣ በአምስት ዓመቱ የጠላት ወረራ ጊዜም አኩሪ ጀብዱ የፈጸሙትን የአርበኛዋን የሸዋረገድ ገድሌን ታሪክ የሚተርክ መጽሐፍ ሰሞኑን ቀርቧል፡፡ ‹ሸዋ ረገድ ገድሌ፣ የአኩሪ ገድላት ባለቤት ይሰኛል፡፡ ሺበሺ ለማ ጽፎት ዶክተር ክፍሌ ማርቆስ ገድሌ አሳትመውታል፡፡

በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ወረራ ጊዜ ለሀገራቸው አኩሪ ገድል በመፈጸምና ለነጻነታችን ዋጋ በመክፈል ስማቸው ከሚነሡ ሴቶች ሸዋረገድ ገድሌ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ በ1878 ዓም የተወለዱት ወ/ሮ ሸዋ ረገድ ገድሌ ሁለገብ እንደነበሩ ታሪካቸው ያሳያል፡፡ የቤተ ክህነቱን ትምህርት ተምረዋል፡፡ ትዳርን አልፈልግም ብለው ምናኔን መርጠው ኢየሩሳሌም ድረስ ተጉዘዋል፡፡ ከመጀመሪያዎቹ የባንክ ተጠቃሚዎች፣ የአክሲዮን ገዥዎች፣ የፋብሪካ ተካዮች መካከል አንዷ ነበሩ፡፡ የጉለሌ ቅዱስ ገብርኤልንም ያስተከሉት እርሳቸው ነበሩ፡፡ 


የሸዋረገድን ስም ይበልጥ ከፍ አድርጎ ያስጠራው አርበኛነታቸው ነው፡፡ የኢጣልያ ጦር ሊጎርሰን ማሰፍሰፉ ሲሰማ በአዲስ አበባ ከተማ በሀገር ተቆርቋሪ ዜጎች በተቋቋመው የሀገር ፍቅር ማኅበር አባልነት መጀመሪያ ከተመዘገቡት ጥቂት ሴቶች መካከል አንዷ እርሳቸው ነበሩ፡፡ ወራሪው ፋሽስት አዲስ አበባ ሲገባና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ወርዶ የኢጣልያ ባንዴራ ሲተካ ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ ስቅስቅ ብለው አለቀሱ፡፡ በዚህ ምክያትም በኋላ  ‹የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ወርዶ የገናናው የኢጣልያ ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብ በማየትሽ አልቅሰሻል›› በሚል ተከሰው ነበር፡፡ ሸዋረገድም ያለምንም ፍርሃት ‹አዎ አልቅሻለሁ፤ ያገሬን መወረርና መዋረድ ያወቅሁት የኛ ሰንደቅ ዓላማ ወርዶ የናንተ ሲውለበለብ በመታየቱ ነው፡፡ ሰው ለእናት ሀገሩ ቢያለቅስ ነውሩ የት ላይ ነው?›› ብለው ነበር የመለሱት፡፡ 
 
ወ/ሮ ሸዋረገድ ለአርበኞች ስንቅ በማቀበል፣ መሣሪያ በመግዛት፣ መረጃ በማሰባሰብ፣ መድኃኒት በመላክና ሞራል በመስጠት አምስቱን ዓመት በተጋድሎ ነው ያሳለፉት፡፡ በዚህ ምክንያት በተከሰሱ ጊዜም ‹‹ለአርበኞች ስንቅ ማቀበሌ እውነት ነው፤ይህንንም ያደረግኩት ለሀገሬ ክብር ብዬ ነው፡፡ ሰው እንኳን ለሀገሩ የእናንተ ወይዛዝርት ሀገራቸው ያልሆነቺው ኢትዮጵያን ለመውረር የጣታቸውን ቀለበት ሳይቀር መስጠታቸውን ትናገራላችሁ፡፡ እኔም ለሀገሬ የሠራሁት ሲያንሰኝ እንጂ አይበዛብኝም›› ነበር ያሉት፡፡
ወ/ሮ ሸዋረገድ ከሚጠቀሱላቸው ሥራዎቻቸው አንዱ ለቀይ መስቀል ማኅበር የነበራቸው ድጋፍ ነው፡፡ በጦርነቱ ዋዜማ ሐምሌ 1 ቀን 1927 ዓም ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ንብረታቸውን ሸጠው አስረክበዋል፡፡ እሥር ቤት በገቡ ጊዜ ከተከሰሱበት ወንጀል አንዱም ‹ቀይ መስቀልን ትረጃለሺ› የሚል ነበር፡፡ ሸዋረገድ ቀይ መስቀልን ከመርዳትም ባሻገር ኢትዮጵያውያን ወይዛዝርት እራፊ ጨርቅ እንዲያሰባስቡ በማድረግ ለአርበኞች ቁስል ማሸጊያ ይልኩላቸው ነበር፡፡ 
 
ሸዋረገድ ከርዳታው ጎን ለጎን ለአርበኞቹ የመረጃ ምንጭም ነበሩ፡፡ በከተማው የሚገኙ የጠላት መረጃዎችን በማሰባሰብና ወደ አርበኞች በምሥጢር በመላክ አርበኞች እንዲጠቀሙባቸው አድርገዋል፡፡ በዚህና በሌሎች ገድሎቻቸው ምክንያትም የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ነበር፡፡ በፈጣሪ ቸርነት ግን ሳይፈጸምባቸው ቀርቷል፡፡ የሞት ፍርዱ ባይፈጸምባቸውም የኢጣልያን እሥር ቤት ከሚያዘወትሩት አንዱ ሸዋረገድ ሆነዋል፡፡ በየጊዜው ይታሠራሉ፤ ይፈታሉ፡፡ በመጨረሻ ግን አዚናራ ወደምትባል ከሰርዲኒያ ሰሜናዊ ምዕራብ ወደምትገኝ ደሴት ታሥረው ተልከዋል፡፡ 
 
እዚያም ቢሆን ጽናታቸው አልተሰበረም፤ ወኔያቸውም አልተሰለበም፡፡ የሚያደርጉት ቢያጡ በእሥር ቤት የሚቀርብላቸውን የተበላሸ ምግብ በአሣሪዎቻቸው ፊት በመድፋትና ጦማቸውን በመዋል ፋሽስትን ይቃወሙ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታም ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ ታሥረው ተፈቱ፡፡ አዲስ አበባ ሲገቡ ግን ትግላቸውን ቀጠሉ እንጂ አላቆሙም፡፡ ሕዝቡም
 
የዘበኛ ሱሪ ካኪና ገምባሌ
እንኳን ደኅና መጣሺ ሸዋረገድ ገድሌ
 ብሎ ተቀበላቸው፡፡ 
 
በተለይም በጅቡቲ የነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ የሰጣቸውን ‹የይሁዳ አንበሳ› የሚል ጽሑፍና ዓርማ ያለበትን ወረቀት ከንጉሡ የተላከ የሚመስል መልእክት እየጻፉ ወደ በረሐ በመላክ አርበኞችን አበረታተውበታል፡፡ የአዲስ ዓለም የጣልያን ምሽግ ኅዳር 5 ቀን 1933 ዓም በአርበኞች ሲሰበር ዋናውን መረጃ የሰበሰቡትና ዐቅድ የነደፉት ሸዋረገድ ነበሩ፡፡ ከምሽጉ ሰበራ በኋላም ደጀን መሆኑን ትተው ራሳቸው ወደ ውጊያ ዐውድማ ገቡ፡፡ በተለይም መቂ አካባቢ ከሻለቃ በቀለ ወያ ጦር መካከል ተሰልፈው ተዋግተዋል፡፡ በኋላም ጅማ አካባቢ ከነበረው ከገረሱ ዱኪ ጦር ጋር ለመገናኘት ተጓዙ፡፡ በዚያ እያሉም ጠላት ድንገተኛ አደጋ ጥሎ ገጠማቸው፡፡ ለአራት ሰዓት ያህልም ተዋግተው ተማረኩ፡፡ ወደ እሥር ቤት ተወስደውም የፊጥኝ ታሠሩ፡፡ 
 
በ1933 ዓም ሀገሪቱ ከፋሽስት ኢጣልያ ወረራ ነጻ ስትወጣ ሸዋረገድ ገድሌ አርበኞችን ወደመርዳትና የበጎ አድራጎት ሥራን ወደ መሥራት ገቡ፡፡ በንግዱም መስክ ተራመዱ፡፡ ሀገራቸውን እስኪበቃቸው አገልግለው፤ ግሼን ማርያም ሄደው ሥጋወደሙን ተቀብለው፤ ከዚያም ወደ ላሊበላ ተጉዘውና ተሳልመው፤ የመጨረሻቸው መሆኑን እየተናገሩ ጥቅምት 22 ቀን 1942 ዓም ዐረፉ፡፡ ሕዝቡም 
 
እናንት ወጥ ቤቶች በርበሬ ቀንጥሱ
እናንት ሥጋ ቤቶች ሰንጋውን ምረጡ
ሸዋረገድ ገድሌ ለገና ሲመጡ፡፡
ቤተሰቧ ሰፊ ገናና ጥምቀት
ሸዋረገድ ገድሌ እንደምን ትሙት፡፡ ብሎ ገጠመላቸው፡፡ 
 
ሰፊ ነው ታሪካቸው፡፡ ልብ የሚያሞቅ፤ ወኔ ቀስቃሽ፤ አስደማሚ፤ ከዐለት የበረታ ጽናት፤ ከእቶን የጋለ አርበኝነት፤ ከትንታግ የተንቀለቀለ የሀገር ፍቅር ታገኙበታላችሁ፡፡ ምናለ አደባባዮቻችን በንግድ ኩባንያዎች ስም ከሚጠሩ በነ ሸዋረገድ ገድሌ ስም ቢሰየሙ ብላችሁም ትቆጫላችሁ፡፡

14 comments:

 1. I appreciate you

  ReplyDelete
 2.  ምናለ አደባባዮቻችን በንግድ ኩባንያዎች ስም ከሚጠሩ በነ ሸዋረገድ ገድሌ ስም ቢሰየሙ !!!!!!
  Thank you,

  ReplyDelete
 3. ዋኖቻችንን እናስብ.... ለዚህም ማስተዋሉን ያድለን። ድ/ን ዳንኤል እግዚአብሔር ያስብህ።

  ReplyDelete
 4. Yemiyakora tarik. Silakafeliken enameseginalen. Metsihafun anebewalehu. Meni adebabayi becha foku rasu emo yeferenji honwal. Ahun "French kiss" yemilew 22 mazoriya gar...... Yasafiral. Ere yelijochachin sim erasu yeferenij eyehone new. Yekerimo sew yibelen.

  ReplyDelete
 5. ነፍሳቸውን ቅዱስ አምላክ በገነት ያኑርልን አሜን! ታሪክ ሰሚና አንባቢ ብቻ ሆነን ልንቀር ነው? የምናነበው እንጂ የምንሰራው ላይኖር ነው ማለት ነው?አቤቱ ጌታ ሆይ ኢትዬጽያችንን እንደነሱ የምናይበት, የምንወድበት ልብ ሰጠን ! ዲያቆን ዳኒ መድሃሂያለም ይጠብቅህ. አሜን!!!

  ReplyDelete
 6. selam,be ahunu seat yalechiw ethiopia endet tayataleh,zares bandira cherku enji kibru altewaredem malet yichalal ....esti zarem selebandira eyalekesu selalu sewoch tinish tsafelin!!!!

  ReplyDelete
 7. aye Emma ETHiopia ;(;( ye eni aynetun tewled feterebat !!!! EGZIABHIR YEMAREN!!! qeriwen amet beager liye qoum neger lemsrat yabqan.

  ReplyDelete
 8. እንደዚ የመሰለ ጀግና ባይኖረንም አሁንም ድረስ ግን ጥሩ ጥሩ ባንዳዎች አሉን ባንኮራባቸውም በደምብ እናፍርባቸዋለን ።
  እግዚአብሄር ልብ ይስጣቸው ሌላ ምንም አይባልም
  ሰላም ዳኒ

  ReplyDelete
 9. wa lega gegnaw Ethiopia hager maznesh talla ymatalesh karto ygadalesh bala yalaw!!

  ReplyDelete
 10. ጤና ይስጥልኝ ዲ/ን ዳንኤል

  በእውነቱ ይህን አኩሪ ገድል ተቀብሮ እንዳይቀር ላደረጉት ጸሃፊና አሳታሚ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል። ይህ መጽሃፍ እንደ እኚህ ያሉ ገድለ ብዙ ጀግኖችን በዚህ መልኩ ለህዝብ ለማድረስ የሚያበረታታ ይመስለኛል። እንደኔ እንደኔ ማስተባበር ቢቻል ፥ ባለሃብቶችንና ድርጅቶችን ከጸሃፊዎች ጋር በማቀናጀት የጀግኖቻችንን ገድል ቢያሳትሙ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ።
  መምህራችን ዳኒ በርታ ፈጣሪ እድሜውንና ጤናውን ያብዛልህ ስራህም ይባረክ።

  ቸር ያሰንብተን !!!

  ReplyDelete
 11. Enameseginalen Deacon Daniel. Libe Mulu Ena Feriha Egziabher Yalat Set Nat. Anebewalew .

  ReplyDelete
 12. ዳኒ እግዚአብሔር ይባርክህ፡፡ ምናለ አደባባዮቻችን በንግድ ኩባንያዎች ስም ከሚጠሩ በነ ሸዋረገድ ገድሌ ስም ቢሰየሙ ብላችሁም ትቆጫላችሁ፡፡ ነበር ምንታደርገዋለህ ሀገሪቷ ላይ የባንዳው ዘር ስለሚበዛ የሸዋረገድ ገድሌ ዘር ደግሞ እየቀነሰ የመጣበት ዘመን ውስጥ ስለሆንን ያለነው በቁጭት እንለፈው፡፡

  ReplyDelete