Wednesday, March 18, 2015

የደብረ ሊባኖሱ እልቂት

 

ኢያን ካምፕቤል ፋሽስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ላይ ስለ ፈጸመቺው አሰቃቂ እልቂት የሚተርክ The Massacre of Debre Libanos, Ethiopia 1937› የተሰኘ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ ይኼ ብዙ ጊዜ የማይነገርለት ነገር ግን እርሳቸው ‹ፋሽዝም ከፈጸማቸው ጆሮ ጭው የሚያደርጉ የጭካኔ ሥራዎች አንዱ ነው› ብለው የገለጡት ዘግናኝ የሃያኛው ክፍለ ዘመን ሰብአዊ አረመኔነት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በጥናት ተመሥርቶ በዝርዝር ቀርቧል፡፡ 


ጣልያኖች የኢትዮጵያውያንን የጀግንነት መንፈስ ለመስበር ከመጀመሪያው ተዘጋጅተው ነበር የመጡት፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ አንድ ርምጃ የወሰዱት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ማንበርከክ ነው፡፡ ምንም እንኳን የተወሰኑ ጳጳሳት ከእነርሱ ጋር ለመሥራት ባያንገራግሩም እንደ አቡነ ጴጥሮስ ያለ ቆራጥ አባት መፈጠሩ፤ ብዙዎች ገዳማትና አድባራት አርበኞችን መርዳታቸው፤ ካህናቱም
ወግጅልኝ ድጓ ወግጅልኝ ቅኔ
ወንዶች ከዋሉበት እውላለሁ እኔ

እያሉ ሀገራቸውን ለመከላከል በረሐ መውረዳቸው ጣልያኖችን ዕረፍት ነሥቷቸው ነበር፡፡ በተለይም ደግሞ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓም በግራዝያኒ ላይ በተቃጣው የመግደል ሙከራ ዋነኞቹ ተሳታፊዎች አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ጋር ግንኙነት አላቸው መባሉ፡፡ አርበኛው ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ የፍቼ ተወላጅ በመሆናቸው ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ በመታሰቡ፡፡ ታዋቂው አርበኛ  ኃይለ ማርያም ማሞ  ከገዳሙ መነኮሳት ጋር ይገናኛል መባሉ ጣልያኖች በደብረ ሊባኖስ ላይ የዘንዶ ዓይናቸውን እንዲጥሉ አደረጋቸው፡፡ 

ይበልጥም ደብረ ሊባኖስ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለው ቦታ የጣልያኖችን የጥፋት ትኩረት ስቦታል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን፣ በእርሷም በኩል የጀግንነቱን መንፈስ አከርካሪውን ለመስበር ያሰቡት ፋሽስቶች የታላቁ ጻድቅ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ምዕራፍ፣ የእጨጌው መቀመጫና ለአያሌ ገዳማት መመሥረት ምክንያት የሆነውን ገዳም ለማጥፋት፣ ሲያጠፉትም ሌላውን ሊያስደነግጥ በሚችል መልኩ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲሆን ወሰኑ፡፡

በዚህም መሠረት ግራዝያኒ ያቀናበረውና ጄኔራል ማለቲ የመራው ጦር ግንቦት 10 ቀን 1929 ዓም ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ወረደ፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ፍልሰተ ዐጽም የተከናወነበትን በዓል ለማክበር የተሰበሰቡትን ምእመናንንና መነኮሳትን መጨፍጨፍም ጀመረ፡፡ በጫጋል፣ በውሻ ገደል፣ በሥጋ ወደሙ ሸለቆና በደብረ ብርሃን አጠገብ በእንግጫ በተከናወነው ጭፍጨፋ ገና ነፍስ ያላወቁ ሕጻናት የቆሎ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ1801 እስከ 2201 የሚደርሱ ምእመናንና መነኮሳት በግፍ ተረሸኑ፡፡ አውሬ እንዲበላቸውም የትም ተወረወሩ፡፡

በዚህም አላበቃም፡፡ በገዳሙ የነበሩ መጻሕፍት፣ የከበሩ ዕቃዎች፣ ንዋያተ ቅድሳት፣ ገንዘብና ሌሎች ንረቶች ተዘረፉ፡፡ ገዳሙም ነጻነት እስኪመለስ ድረስ በመከራ ውስጥ ኖረ፡፡

አስገራሚው ነገር ከ500 ዓመታት በፊት ግራኝ አሕመድ ገዳሙን ሲያቃጥል የሞቱት መነኮሳት ቁጥር 450 ነበር፡፡ ፋሽስት ኢጣልያ የጨፈጨፈቺው ከእርሱ አምስት ጊዜ እጥፍ የሚበልጥ መሆኑን ስናስበው የጭካኔውን መጠን ያመለክተናል፡፡

መጽሐፉን ስታነቡት ኀዘን፣ ቁጭትና ግርምት ይፈራረቁባችኋል፡፡ ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አረጋውያን በሃይማኖታቸውና በኢትዮጵያዊነታቸው ምክንያት ብቻ የደረሰባቸውን ግፍ ስናስበው ልባችን በኀዘን ፍላጻ ይወጋል፡፡ ማንበብ እስኪያቅተን ድረስ በሰቆቃወ ደብረ ሊባኖስ እንዋጣለን፡፡ ለደረሰባቸው ግፍ ተመጣጣኝ ካሣ አለማግኘታቸውን፣ ኢጣልያ የፈረመቺውን ውል እንኳን ሳታከብረው 74 ዓመታት ማለፋቸው ስትመለከቱ፡፡ ግራዝያኒ ወስዷቸው ዛሬ እንደ አቤል ደም እየተካሰሱ በሮም የሚገኙትን የገዳሙን ንብረቶች ስታስታውሱ አባቶቻችን ልጅ አለመውለዳውን ዐውቃችሁ ይቆጫችኋል፡፡

ልጅ የለንም እንጂ ልጅማ ቢኖር
ተሟግቶም ተዋግቶም ያስመልስ ነበር፤
ብለው ያንጎራጎሩ ሲመስላችሁ ትቆጫላችሁ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይኼ እኛ ዛሬ የምንቀልድበት ነጻነት ምን ያህል ዋጋ እንደተከፈለበት ስታስቡ፣ ዋጋ ከፋዮቹንም በዓይነ ኅናችሁ ስትቃኙ ትገረማላችሁ፡፡ ግርምታችሁ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ በዚያ የመከራ ዘመን የሰማዕታቱን ዐጽም ለመሰብሰብ፣ ቦታቸውም ለማወቅ በመንፈሳዊና ሀገራዊ ወኔ ታጥቀው የከወኑትም፤ ለታሪክም አስረጅ ሆነው የቆሙትን የክፉ ቀን ጀግኖች ስታስቡም ትደነቃላችሁ፡፡ እግረ መንገዳችሁን እንዲህ ያሉት የዓይን ምስክር ጀግኖች በዐረፍተ ሞት ከመገታታቸው በፊት ሌላውም ታሪካችን እንዲጻፍ ትማጸናላችሁ፡፡ አብዛኛው ሕዝብ አንብቦ እንዲጠቀምበትም በአማርኛ ታሪኩ ቢቀርብ መልካም መሆኑንም ሐሳብ ትሠነዝራላችሁ፡፡

ከዚህም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሁለት ሥራዎች እንደቀሩትም ትገነዘባላችሁ፡፡ ለእነዚህ ለእምነታቸውና ለሀገራቸው ሲሉ ለተሠዉ ሰማዕታት ተገቢውን ቦታ መስጠት፣ ታሪካቸውንም በስንክሳር ውስጥ በተገቢው ሁኔታ እንዲሠፍር ማድረግ፤ አያይዞም ደግሞ በዓላቸው በኦርቶዶክሳዊ ሥነ ሥርዓት እንዲከበርና ትውልድ ሀገራዊም መንፈሳዊም በረከት እንዲያገኝባቸው ማድረግ ይገባዋል፡፡ ለዚህም ደራሲው ኢያን ካምፕቤል አጥልቀው አጥንተው፣ ተንትነው ጽፈውታልና ምስጋና እየቸርን መጽሐፉን እናንብበው፡፡

መልካም ንባብ፡፡

20 comments:

 1. ልጅ የለንም እንጂ ልጅማ ቢኖር
  ተሟግቶም ተዋግቶም ያስመልስ ነበር፤

  ReplyDelete
  Replies
  1. ልጅ የለንም እንጂ ልጅማ ቢኖር
   ተሟግቶም ተዋግቶም ያስመልስ ነበር

   Delete
 2. you can't imagine how I regret a lot. need someone to take the lead to give recognition and help the family of those who were take part on the war! I will be part of the member!

  ReplyDelete
 3. ይህንን እልቂት ጋሽ ታዬ እየደጋገመ በብከቶቹ ሲያነሳው አውቀዋለሁ። እጅግም የምደነቅበት ነገር መረጃውን በማስረጃ ማስደገፍ አለመቻሌ ነበር። እንደው ምን ላርግህ ወዳጄ። አገልግሎትህን ይቀበልልህ እጆችህንም ያበርታ!
  ዘለንደን

  ReplyDelete
 4. ዲያቆን ዳንኤል ምን እናድርግ የሞትን ትዉልድ ሆን እኮ !!!

  ReplyDelete
 5. የሚያሳዝን, የሚያሰቆጭ, እና የሚያሰለቅሰ ታሪክ!ገና መፀሀፎን ሙሉውን ሳናነበው ልባችን በሐዘን ደማ . የከፈሉት ሰማዕትነት በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም. ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል. እኛም ከቤተክህነቱ ጎን ሆነን የተቀበሉትን ሰማዕትነት እንዲከበር እንሰራ. እነሱ ደማቸውን ሰትውን አልፈዋል. ክቡራን አንባቢዎች ሆይ አንብበን ብቻ አንለፍ. የምንችለውን እናድርግ.
  ዕውቀታችንን,ገንዘባችንን,ጊዜያችንን እንሰጣቸው. ደማቸው ይወቅሰናል! ዲያቆን ዳኒ እባክህን ከአገር ውጭ ላለነው ቤተ ክህነቱ ስራውን እንዲጀምር ምን እናድርግ? በእርግጥ ሰራ ይበዛብሀል, ከቻልክ አሳብህን አካፍለን. የህሊና እረፍት እንዲኖረን አድርገን. መድሃኒያለም ይጠብቅህ አሜን!!!

  ReplyDelete
 6. አይ ዳኒ እንደው በአሁን ጊዜ ስለ ክብራችን ስለ ሀይማኖታችን ስለ ሀገራችን የሚል ህዝብ ነው ወይስ እንዴት አድርጌ ልክበር ?ቀጥፌ ሰርቄ ወንድሜን ገድዬ አብሮ አደጌን አታልዬ የሚል ወገን ተብዬ ነን ?

  ReplyDelete
  Replies
  1. አይ ዳኒ እንደው በአሁን ጊዜ ስለ ክብራችን ስለ ሀይማኖታችን ስለ ሀገራችን የሚል ህዝብ ነው ወይስ እንዴት አድርጌ ልክበር ?ቀጥፌ ሰርቄ ወንድሜን ገድዬ አብሮ አደጌን አታልዬ የሚል ወገን ተብዬ ነን ?

   Delete
 7. ልጅማ ሞልቶናል ሊያውም በብዛት
  ቁጭ ብሎ እየበላ የጉራጌ ጫት
  ታሪክ ድሮ ቀረ ይላል በኩራት
  ታሪኳን ጠብቆ ይመስል ሊያቆያት

  ReplyDelete
 8. ልጅማ ሞልቶናል ሊያውም በብዛት
  ቁጭ ብሎ እየበላ የጉራጌ ጫት
  ታሪክ ድሮ ቀረ ይላል በኩራት
  ታሪኳን ጠብቆ ይመስል ሊያቆያት

  ReplyDelete
 9. በጣም እናመሰግናለን ዳንየ! ግን ይህንን እልቂት ቤተ ክርስቲያናችን ባስቀመጠችው ሥርዓት መሠረት ጊዜውን ጠብቃ ታስባቸው ይሆን? ወይስ ባሁን አቋሟ በትናንሽ አጀንዳዎች ተሸፍና ታልፈው ይሆን ? ያሳስበኛል፡፡መልካሙን መልእክት ስለነገርኸን እግዚአብሔር ዕድሜና ጸጋ ያድልህ፡፡

  ReplyDelete
 10. ዲ. ዳንኤል እንደምን ሰነበትክ ፡፡
  እንደተባለው አባቶቻችንን ለእምነታቸው ፣ ለወገናቸው እና ለሀገራቸው ሲሉ የፈጸሙትን ጀብዱና ያበረከቱትን የቅርስ፣ የታሪክ ፣ የእምነት እና የባህላዊ ትውፊታዊ ውርስ ስንመለከት ምን ያህል ጠንካራና ላመኑበት ነገር ሲሉ አካላቸውን ፣ ነፍሳቸውንና ሀብታቸውን ሳይቀር በመሰዋት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ በመወጣት ትልቅ አደራ እንደጣሉብን መረዳት ይቻላል፡፡ ነገሩን በአጽንኦት ካየነው ደግሞ እነዚህ አባቶች በወቅቱ ይህንነ ሁሉ ሲወጡ ከሌላ ሶስተኛ ወገን የተለየ ጥቅም ፣ ምስጋና ወይንም ደግሞ ሹመትና ሽልማት ፈልገው ሳይሆን በትክክለኛ የሀገር እና ወገን ፍቅር እና የእምነት ጽናት ስላላቸውና መጭው ትውልድ ስለሀገሩ እና ስለእምነቱ ጠንካራ ፍቅር ኖሮት እሱም በተራው ሀገሩንና እምነቱን ከተለያዩ አጽራረ እምነትና ወራሪ ሀይሎች ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንዲችል የጥንካሬና የፍቅር ተምሳሌታዊ የቅብብሎሽ መንፈስ ለማስረጽ የተደረገ የጠንካራ ትግልና መስዋእትነት ውጤት ነው፡፡
  መቸም የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲን ነጥሎ ማየት አይቻልምና ሀገር ተወረረ ከተባለ የመጀመሪያ ተጠቂዋ ይህችው ቤተክርስቲያን ነች፡፡ በመሆኑም ቤተክርስቲያኒቷ በሁሉም ማለት ይቻላ ሀገራችን በተለያ ጠላቶች በተጎነተለችበት ወቅት ለችግር ስትጋለጥ እንደቆየች ግልጽ ነው፡፡ እነዚህ ጠላቶች ተደጋጋሚ ወረራ እና ጥቃት በማድረግ ዳፋዋን ለማጥፋትና የራሳቸውን የእምነት ስርዓት ለመተካት ያላሰለሰና እረፍት የለሽ ሙከራ ሲየደርጉ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ዮዲት ጉዲት (ከ842-882) ገዳማትን፣ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ታሪካዊ ሀውልቶችን እና መጸህፍትን በማቃጠል እና የእምነቱ ተከታዮችን በመግደልና በማሳደድ ለ40 ዓመታ ያህል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲን ላይ አረመኔያዊ የሆነ ትልቅ ጥፋት አድርሳለች፡፡ ቤተክርስቲያን የሚጠብቃት የመሠረታት ኢየሱስ ክርስቲስ ስለሆነ እና መሠረቷ የመይናጋና ጽኑ በመሆኑ በእነዚህ 40 የመከራና የትፋት ዓመታት ውስጥ አልፋ በማገጋም ላይ እያለችም በ15ኛው መ/ከ/ዘመን አካባቢ ግራኝ መሀመድ የተባለ ሌላ ጸረ ክርስትና ወራሪ በመነሳቱ ብዛት ያላቸው ገዳማት፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ታሪካዊ ሀውልቶች ለዳግም ጥፋት ከመዳረጋቸውም በላይ ብዛት ያላቸው መጻህፍትና ንዋየቅድሳት ተቃጥለዋል፡፡ ብዛት ያላቸው የእምነቱ ተከታዮች የሆኑ አባቶችና እናቶችም ለእልፈተ ህይወትና ለስደት የተዳረጉ ሲሆን በወቅቱ የነበሩ የተለያዩ የስልጣኔ ማዕከላትም ፈራርሰው በዮዲት ጉዲት ዘመን ከደረሰው ጉዳት ያላነሰ ጉዳት ደርሶባቸዋል ፡፡ እነዚህና ሌሎችም ችግሮች በዚያ ‹‹የጭለማ ዘመን›› ተብሎ በሚጠራው ወቅት ካለፉ በኋላ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ዘመን (ከ1928-1933 ዓ.ም) በሌሎች ገዳማትና አብያተክርስቲያናት የተሰውትን ሳይጨምር 1801 እሰዝከ 2201 የሚደርሱ ንጹሃን አባቶች፣ወንድሞችና እናቶች ያለምንም ጥፋታቸው በደብረሎባኖስ ገዳም መሰዋታቸው በወቅቱ ለተመለከቱት ቀርቶ ዛሬ ላይ ሆነን ለሰማነውም ቢሆን እጅግ የሚዘገንን ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ቤተክርስቲያናችንን በተመለከተ ጠላቷ ሰው ሳይሆን ዲያብሎስ ነውና ትላንትም ሆነ ዛሬ እንዲሁም ወደፊት ተመሳሳይ አደጋዎች እና ጥቃቶች መከሰታቸው አይቀሬ ነው፡፡ - እግዚአብሔር ይጠብቃት አንጅ፡፡
  ዞሮ ዞሮ ግን እነዚህ ለእምነታቸው እና ለሀገራቸው ሲሉ (ወቅቱ ሀገራችን በኢጣሊያ የተወረረችበት ሰዓት በመሆኑ) ህወታቸውን የሰጡ አባቶች ሊታሰቡና አማኒያኑም እውነታውን ተረድቶ ከእነዚህ አባቶች መማር ያለበትን ተምሮ ዛሬም ቢሆን መልክና ስልቱን ቀይሮ እተፈጸመ ያለውን ጸረ-ቤተክርስቲያናዊ ድርጊት በመቃወም እምነቱን በጽናት የመጠበቅ ሀላፊነት እንዳለበት አውቆ የሚፈለግበትን ሁሉ ማድረግ ይኖርበታል ፡፡
  ውድ ወንድማችን ዲ.ዳንኤል እንዳለው ቅድስት ቤተክርስቲያንን የሚያስተዳደሩ ብጹአን አባቶችም ያልሰሩት ብዙ የቤት ስራ እንዳለባቸው ግልጽ ነው፡፡ እግዚአብሔር በፈቀደ እያንዳንዱ ነገር የሚገለጥበትና መደረግ ያለበት ሁሉ የሚደረግበት ወቅት ሲደርስ ( ለብጹእ አቡነ ጴጥሮስ እንደተደረገው) ሊደረግ ቢችልም እነዚህንና መሰል ተጋድሏቸውና ስራቸው በተገቢው መንገድ ጎልቶ ያልተሰማላቸውን አባቶች የተጋድሎ ሂደትን የሰማዕትነታቸውን ግብ የሚያስረዳ የተጋድሎ ታሪክና የሰማዕትነት ፋይዳ የሚተርክ ጽሑፍ በማዘጋጀት እና ስንክሳር ተብሎ በሚጠራው የቤተክርስቲያኒቷ ታላቅ መጽሐፍ ላይ በማካተት ሁሉም የእምነቱ ተከታይ እንዲረዳው .ከማድረግ አንጻር የቤተክርስቲያን አባቶች ድርሻ የጎላ ቢሆንም (ብጹዓን አባቶች ጉዳዩን በመንፈሳዊ ቅኝት በማየት ትክክለኛውን ነገር ለይቶ እና አብጠርጥሮ የማወቅ ጥበብና ስልጣን ስላላችሁ) እነዚያ አባቶች (ሠማዕታት) በወቅቱ ለዚህ የከፋ ችግር የተጋለጡት ሀገርን ያላግባብ በወረረ እብሪተኛ የኢጣሊያ መንግስት በመሆኑና ጉዳዩ ከሀገር መወረርና የሉዓላዊነት መደፈር ጋር በቀጥታ የሚገናኝ በመሆኑ መንግስትም ቢሆን እነዚህ አባቶች የሚታሰቡበበት ሀውልት በስማቸው በመስራት ካልሆነም ደግሞ እንደተባለው አጽማቸው በአንድ ቦታ ተሰብስቦ (በቀይ ሽብር ለተሰውት እንደተደረገው)እንዲቀመጥና ታሪካዊ አሻራነቱ በጎላ መንገድ እንዲታሰብ ቢያደርግ ትውልዳዊ ሀላፊነትን መወጣት ነውና ቢታሰብበት ጥሩ ይሆናል፡፡
  በአጠቃላይ ግን ደራሲው ኢያን ካምብል እና ስለመጽሐፉ አጠቃላይ ይዘትና በወስጡ ስለያዘው ሀሳብ አጠር ባለ ነገርግን በጥልቅ ምልከታ የተቃኘ ማብራሪያ የሰጠንን ዲ. ዳንኤልን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ የእነዚያ ሠማዕታት አባቶች በረከት አይለየን ፤ አሜን ፡፡
  እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክልን ፣ይጠብቅልን ፡፡

  ReplyDelete
 11. ለእነዚህ ለእምነታቸውና ለሀገራቸው ሲሉ ለተሠዉ ሰማዕታት ተገቢውን ቦታ መስጠት፣ ታሪካቸውንም በስንክሳር ውስጥ በተገቢው ሁኔታ እንዲሠፍር ማድረግ፤ አያይዞም ደግሞ በዓላቸው በኦርቶዶክሳዊ ሥነ ሥርዓት እንዲከበርና ትውልድ ሀገራዊም መንፈሳዊም በረከት እንዲያገኝባቸው ማድረግ ይገባዋል፡፡

  ReplyDelete
 12. ለግብጽ ሰማዕታት የተደረገውን ስናስብ የኛ ቤተክርስቲያን ብዙ ሥራ ይጠበቅባታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ምዕመናን የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር ኃይልና ብርታቱን ያድለን

  ReplyDelete
 13. wa lega ensema ewentu bat hadwal egezabher amelak mengest smayaten endamyawersachw ytawek new yzan neger tawew egezabher amelak abat sesamelen hulme yezekaralew ahen ylaw shomet kegezabher slalhon abzetan ensile egezabher abate endsatan amen!!

  ReplyDelete
 14. ማጣቀሻ ፊልም ትሬይለር

  https://vimeo.com/87329337

  https://vimeo.com/84273170

  ReplyDelete
 15. ለኢያን ካምፕቤልና ለዲን. ዳንኤል ክብርና ምሥጋና ይገባችኋል።
  ፋሺሽት ኢጣልያኖች፤ በቫቲካን ያልተቆጠበ ድጋፍ፤ ኢትዮጵያ ላይ የፈጸሙት አሰቃቂ ወንጀል አሁንም ተገቢው ፍትሕ ያልተገኘለት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በፋሺሽቶች ከተገደሉት አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ውስጥ አዲስ አበባ በሶስት ቀኖች ብቻ የተጨፈጨፉት 30 000 ሰዎችና ደብረ ሊባኖስ የተፈጁት በሺ የሚቆጠሩ መነኮሳት ይገኙበታል። በተጨማሪም የወደሙት 2000 ቤተ ክርስቲያኖችና 525 000 ቤቶች፤ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ተዘርፎ በቫቲካንና በኢጣልያ መንግሥት እጅ የሚገኘው መጠነ ሰፊ ንብረት ሁልጊዜም ሊረሳ አይገባውም።
  ከላይ የተጠቀሰው ታሪክ እንዳለ ሆኖ፤ ባሁኑ ጊዜ ለምንገኘው ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ዋናዎቹ ጥያቄ፤ ኢትዮጵያ ፈሺሽት ኢጣልያና በቫቲካን ለደረሰባት ከባድ ወንጀል የሚገባትን ፍትሕ እንድታገኝ ምን እያደረግን ነው? እሥራኤል፤ ኬንያ፤ ናሚቢያ፤ ኢንዶኔዝያ፤ ሊቢያ፤ ወዘተ. ይቅርታ ተጠይቀው ተገቢ የሆን ካሣ ያገኙ ሲሆኑ ኢትዮጵያስ መቼ ነው መብቷና ክብሯ የሚጠበቀው?
  ለዚህ ጉዳይና ዓላማ አንድ እንቅስቃሴ አለ። (www.globalallianceforethiopia.org)
  እንደግፈው። በቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ እርዳታ ተገቢውን ፍትሕ እናገኛለን።

  ReplyDelete
 16. በጣም የሚገርም ነው፡፡ማን ይሆን የአባቶቹ ልጅ መሆኑን በተግባር የሚያሳይ.. አለበለዚያማ...ምን ይበባላል.. የእሳት ልጅ አመድ ሆነን ቀረን! አለመፈጠር ምን ኛ ደግ ነው.. ልብ ይስጠን አምላ በእውነት የእሳት ልጅ እሰሳት ትንታግ እንድንሆን..ዲ ያቀቆን አንተን አይጨምርም ፡፡አንተ የእሰሳት ልጅ እሳት እንጅ አመድ ከመባል ድነሃል፡፡የድርሻህን እየተወጣህ ስለሆነ፡፡አንተን ያበረታ አምላክ ወልድ ማሪያም እኛንም ያንቃን፡፡አሜን፡፡

  ReplyDelete